medaliya 1

ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገቤ ምስጢሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖሬ ነው

ሐምሌ 5 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ሰሞኑን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በመመረቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች የተሸለመችውንmedaliya 1 አንዲት እኅት ለዛሬ እንግዳችን አድርገናታል፡፡ አንዱን የወርቅ ሜዳልያዋንም “በግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፍ በመንፈሳዊ ሕይወቴ እንድበረታና ዓላማዬን እንዳሳካ እገዛ አድርጎልኛል” ለምትለው ማኅበረ ቅዱሳን በሥጦታ አበርክታለች፡፡ የዩኒቨርስቲ ቆይታዋን፤ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ስለነበራት ተሳትፎ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ አነጋግረናታል፡፡ መልካም ቆይታ፡፡

ጥያቄ፡- ራስሽን ብታስተዋውቂን?

ፋንታነሽ ፡- ፋንታነሽ ንብረት እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ሚዛን ግቢ ጉባኤ ነው፡፡ የተመረቅሁት አዲስ የትምህርት ዘርፍ በሆነው በኮፕሬቲቭ አካውንቲንግ /Cooprative Accounting/ በመጀመሪያ ዲግሪ ነው፡፡

ጥያቄ፡-  ከቤተሰብ ርቀሽ ወደ ዩኒቨርስቲ መግባቱ አልከበደሽም?

 
ፋንታነሽ፡-  ወደ ዩኒቨርስቲው ስገባ ከለመድኩትና ካደግሁበት አካባቢ የተለየ ስለነበር ከብዶኛል፡፡ የገጠሙኝ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ሴት መሆኔ፤ ለዩኒቨርስቲው አዲስ ከመሆን ጋር ተዳምሮ ብቸኝነት፤ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ያለመሟላት ችግሮች ነበሩ፡፡ ቀስ በቀስ ለመድኩት፡፡ በእግዚአብሔር ኃይል ችግሮቹን ሁሉ መቋቋም ቻልኩ፡፡

 
ጥያቄ፡- በግቢ ጉባኤ ላይ የነበረሽ ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር?

ፋንታነሽ፡- ወደ ዩኒቨርስቲው ስገባ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ የማውቃቸውን ልጆችን አገኘሁ፡፡ በግቢ ጉባኤያት  አማካይነት ከእሑድ እስከ ሰኞ የሚካሔዱትን መርሐ ግብሮች መረጃ ወሰድኩኝ፡፡ ሰዓቴን አብቃቅቼ በዚሁ መሠረት መከታተል ጀመርኩኝ፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር እያለሁ በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እሳተፍ ስለነበር ብዙም አልተቸገርኩም፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ በአስተባባሪነትና በመዝሙር ክፍል ውስጥ በአባልነት ማገልገል ጀመርኩ፡፡ ዩኒቨርስቲ ከገባሁ በኋላ የቤተሰብ ተጽእኖ ውጪ ስለሆንኩ ራሴን በአግባቡ የመምራት ሓላፊነት ስላለብኝ ከፍተኛ ጥንቃቄ አደርግ ነበር፡፡በግቢ ጉባኤ አገልግሎትም ጥሩ ተሳታፊ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡

ጥያቄ፡- የትምህርት አቀባበልሽ እንዴት ነበር?

 
ፋንታነሽ፡-  ብዙ ማንበብ አልወድም፡፡ ትልቁ አቅሜ የነበረው በክፍል ውስጥ የነበረኝ ትምህርት የመቀበል ችሎታ ነው፡፡ በምንም ምክንያት የትምህርት ክፍለ ጊዜዬን አልቀጣም፡፡ በአግባቡም እከታተላለሁ፡፡ ከትምህርት ውጪ የማሳልፈው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ማታ ማታ በጣም ለአጭር ሰዓት የቤት ሥራዎቼን መሥራት፤ በክፍል ውስጥ ስማር ግር ያለኝ ነገር ካለ በድጋሚ መከለስ ላይ አተኩራለሁ፡፡ እንደ ሌላው ተማሪ ለረጅም ሰዓት መሸምደድ አልወድም፡፡

የመጀመሪያ ዓመት ላይ ግን ትንሽ ያነበብኩ ይመስለኛል፡፡ ግቢውን ለመላመድ፤ የአስተማሪዎቹን የትምህርት አሰጣጥና የፈተና አወጣጥ ግንዛቤ ስላልነበረኝ ይህንን ለመቋቋም በመጠኑም ቢሆን አነበብኩ፡፡ ቀሪዎቹን ዓመታት ግን ለንባብ ብዙም አልተጨነቅሁም፡፡ ተማሪ ከተማሪ በትምህርት አቀባበል ረገድ እንለያያለን፡፡ አንዳንዱ ለረጅም ሰዓት የማንበብ ልምድ ይኖረዋል፡፡ እኔ ግን ከእግዚአብሔር የተሰጠኝ ስጦታ ነው፡፡ ክፍል ውስጥ በአስተማሪዎቼ የሚሰጠውን ገለጻ በደንብ የመያዝ ብቃቱ አለኝ፡፡ ሙሉ ለሙሉ እንዳልረሳው መጠነኛ ክለሳ ብቻ ነው የማደርገው፡፡

ጥያቄ፡- ከተማሪዎች ጋር ለመላመድ አልተቸገርሽም?

ፋንታነሽ፡- የክፍለ ሀገር ልጅ ነኝ፡፡ የመጣሁት ከዳንግላ ነው፡፡ ዶርም/ማደሪያ/ የተመደብኩት ከአዲስ አበባ ልጆች ጋር ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ለመቅረብ ጥረት አድረጌ ነበር፡፡ ዓለማዊ ፕሮግራሞች በግቢው ውስጥም ሆነ ውጪ ሲዘጋጁ አብሬያቸው እንድሔድ ይገፋፉኛል፡፡ “ሕይወት ማለት እኮ ይህ ነው” ይሉኛል፡፡ እኔ ግን በትምህርቴም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ስኬታማ መሆን ዋነኛው ዓላማዬ ስለነበር አሳባቸውን አልተቀበልኳቸውም፡፡ የራሴን አካሔድ በመምረጥ በእነሱ ተጽእኖ ሥር ላለመውደቅ ጥረት አደረግሁ፡፡ ቅርበቴ ሁሉ ከመንፈሳዊ እኅቶችና ወንድሞች ጋር እንዲሆን ወሰንኩ፡፡ የወሰድኩት አቋም ትክክል እንደነበር ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ያስደስተኛል፡፡ ትክክል ነበርኩ፡፡

ጥያቄ፡- እስቲ ስለ ውጤትሽ አጫውቺን?

ፋንታነሽ፡- በመጀመሪያ ዓመት ያመጣሁት ውጤት 3.98 ነበር፡፡ አንድ “B” ብቻ ነው ጣልቃ የገባው እንጂ ሁሉንም “A” ነው ያመጣሁት፡፡ በተከታታይ ዓመታት አራት ነጥብ ነው ያስመዘገብኩት፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ዓመት ላይ ፈተና እየወሰድን እናቴ በመታመሟ ምክንያት ከቤተሰብ እንድመጣ መልእክት ስለደረሰኝ ለዩኒቨርስቲው አስፈቅጄ ሄድኩኝ፡፡ ስመለስ ምንም ሳላጠና ተፈትኜ “B” አመጣሁ፡፡ በዚህም መሠረት ስመረቅ አጠቃላይ ውጤቴ /GPA/ 3.96 ሆነ፡፡

ጥያቄ፡- በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የደረጃ ተማሪ ነበርሽ?

ፋንታነሽ፡- በጭራሽ!! በአንደኛም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴ የደረጃ ተማሪ አልነበርኩም፡፡ በመካከለኛ ደረጃ ላይ እገኝ ነበር፡፡ ዩኒቨርስቲ ስገባ ውስጤን በደንብ ያሳመንኩት ይመስለኛል፡፡ ዓላማዬ ስኬታማ እሆን ዘንድ ነበር ተሳካልኝ፡፡

ጥያቄ፡- በዩኒቨርስቲው ቆይታሽ ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጪ መሆንሽ ያሳደረብሽ ተጽእኖ አልነበረም?

ፋንታነሽ፡- ከቤተሰብ ጋር ስንኖር እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችን፤ የት ገባሽ፤ የት ወጣሽ ስለምንባል ቁጥጥሩ ይበዛል፡፡ ቁጥጥራቸው ለመልካም እንደሆነና ጥሩ ደረጃ ላይ እንድንደርስ ከማሰብ የሚመነጭ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲ እንደምገባ ካወቅሁበት ቀን ጀምሮ ራሴን ሳዘጋጅ ነበር፡፡ ከገባሁም በኋላ በዙሪያዬ ያሉትን ፈተናዎች ለመቋቋም ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ የቤተሰቦቼ ቁጥጥር ጠቅሞኛል እንጂ አልጎዳኝም፡፡ ተጽእኖም አልፈጠረብኝም፡፡

ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ በመኖርሽ ተጠቅሜያለሁ ትያለሽ?

ፋንታነሽ፡- ቤተ ክርስቲያን ለኔ መሠረቴ ናት፡፡ እምባዬን ጠርጋልኛለች፡፡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ የማማክረው፤ የሚደግፈኝ በሌለበት ሲጨንቀኝ፤ ዙሪያው ገደል ሲሆንብኝ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ አለቅሳለሁ፡፡ ለእመቤቴ ጭንቀቴን ሁሉ እነግራታለሁ፡፡ መንገዴንም ቀና ታደርግልኛለች፡፡ እረጋጋለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ባይደግፈኝ ኖሮ እዚህ ደረጃ መድረስ አልችልም ነበር፡፡ በመንፈሳዊም ሆነ በስጋዊ ሕይወቴ ተጠቅሜያለሁ ማለት ይቻላል፡፡

ጥያቄ፡- በግቢ ውስጥ ትልቁ የተማሪዎች ችግር ምንድነው?

ፋንታነሽ፡- ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በተለይም ራስን ካለማዘጋጀት የሚመነጩ ችግሮች በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም፡፡ ተማሪዎች በእምነት ከማይመስላቸው ሰው ጋር ይገጥማሉ፡፡ በተለይም እህቶች ከወንዶች ጋር በሚኖራቸው ቅርበት የማንኛውም እምነት ተከታይ ይሁን እንዳልባረር ያስጠናኛል፤ ይደግፈኛል፤ ያለብኝን የፋይናንስ ችግር ያቃልልልኛል በማለት ይቀራረባሉ፡፡ ወዳልተፈለገ አቅጣጫም ያመራሉ፡፡ ሂደቱ ያስፈራል፡፡ አደርግልሻለሁ – አድርጊልኝ ወደመባባል ይደርሳሉ፡፡

ሌላው በዩኒቨርስቲ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ሃሜት ነው፡፡ በግቢ ጉባኤያት ውስጥ ጭምር የሚከሰት ነው፡፡ አንመካከርም፡፡ በነበርኩበት ግቢ ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ክፍተት ነው ከምላቸው ነገሮች አንዱ ይህ ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ አንዱን መገሰጽ ያለመቻል ችግር፡፡

ጥያቄ፡- በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ምን ያህል ረድቶሻል?

ፋንታነሽ፡- በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ጥሩ ነው፡፡ ሁሉንም ኮርሶች መጨረስ ባንቸልም ስለ እምነታችን ጥሩ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው፡፡ የማላውቀውን እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ በተለይም መንፈሳዊ ሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ ረድቶኛል፡፡ በራስ ጥረት ደግሞ ማበልጸግ፤ ማጠንከር ያስፈልጋል፡፡

ጥያቄ፡- ከወንድሞችና እህቶች ጋር የነበራችሁ ቅርበትና መደጋገፍ እንዴት ይገለጻል?

ፋንታነሽ፡- የመደጋገፍ፤ የመተባበር እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ አንዳችን ከተኛን ሌሎቻችን የመቀስቀስ፤ የመደጋገፍ፤ አብሮ ቤተ ክርስቲያን የመሄድ ልምዱ የዳበረ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከንስሀ አባቶቻችሁ ጋር ያላችሁ ቅርበት ብትገልጪልን?

ፋንታነሽ፡- ዩኒቨርስቲው በቅርቡ ከመከፈቱ አንጻር ከንስሀ አባቶቻችን ጋር የመገናኘትና የመመካከር ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን አብረውን የነበሩ ብዙ ወንድሞችንና እህቶችን አጥተናል፡፡

ጥያቄ፡- ከፍተኛ ውጤት በማምጣትሽ ምንድነው የተሸለምሽው?

medaliyaፋንታነሽ፡- ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ነው የተሸለምኩት፡፡ አንዱ ከዩኒቨርስቲው አጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ነጥብ በማምጣቴ የተሸለምኩት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከተመራቂ ሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ነጥብ በማምጣቴ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የበቃሽበት ዋነኛ ምሥጢር ምንድነው?

ፋንታነሽ፡- የኔ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ትልቁ ምስጢር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖሬ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን ትምህርት ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር አጣጥሞ መጓዝ እንደሚቻል የኔ ውጤት ምስክር ነው፡፡ ሌሎችንም የሚያስተምር ነው፡፡

ጥያቄ፡- ሜዳልያሽን ለማኅበረ ቅዱሳን ለመስጠት እንዴት ወሰንሽ?

ፋንታነሽ፡- ማኅበሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ በመሆኑ፤ በተለይም በግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እምነታቸውን እንዲያውቁ የሚያደርጋቸው ጥረቶች በጣም ያስደስተኛል፡፡ እኔም የዚህ ጥረት ውጤት በመሆኔ፤ ሌሎችም የኔን አርአያ እንዲከተሉ ለማድረግ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ወደፊት ካንቺ ምን እንጠብቅ?

ፋንታነሽ፡- እድሉ ቢያጋጥመኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በየአመቱ የሚሰጠውን የነጻ ትምህርት እድል / /Scholarship/  ተጠቃሚ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ በጣም እያሰብኩበት ነው፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንንና አገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ አቅሜ የሚፈቅደውን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ፡፡ በተለይም ማኅበረ ቅዱሳን የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ማገዝ እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡

ጥያቄ፡- ለተማሪዎች የምታስተላልፊው መልእክት ካለሽ?

ዩኒቨርስቲ ስንገባ ማንም አያየኝም የሚል ድምዳሜ ላይ ስለምንደርስ ራሳችንን ወደፈለግነው አቅጣጫ የመምራት ነገር ይታያል፡፡ ከጓደኛ ምርጫ ጀምሮ ችግሮች ይታዩብናል፡፡ የመጣንበትን ዓላማ በመዘንጋት ደካማ ውጤት በማስመዝገብ እስከ መባረር እንደርሳለን፡፡ ከማይመስሉን ጋር በመግጠም ዳግም ልንንሳ በማንችልበት ሁኔታ አልባሌ ቦታዎች ላይ እንወድቃለን፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ የወደፊት ህይወታችንን ለማሳካት ብለን ከቤተሰቦቻችን መለየታችንን ማሰብ ይገባናል፡፡ ዓላማችን መማር ነው፡፡ ጠንክረን በመማር የወደፊት ህይወታችንን አቅጣጫ ማስያዝ ይጠበቅብናል፡፡ የወደፊት ህይወታችን የተመሰረተው ዛሬ በምናስመዘግበው ውጤት ነው፡፡ የመጨረሻ ግባችን ምን መሆን እንዳለበት ከመጀመሪያው ውስጣችንን አሳምነን መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ነፃነት የሚባለውን ነገር ከፈለግን ከተመረቅን በኋላ የራሳችንን ሕይወት የምንመራበት አንዱ መንገድ ስለሆነ ያኔ እንደርስበታለን፡፡ ነፃነትን እንደፈለጉ ከመሆን ጋር ማዛመድም የለብንም፡፡ ዓላማ ሊኖረን ግድ ነው፡፡

እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

እኔም እግዚአብሔር ይስጥልኝ!!