‹‹ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል›› (መዝ.፲፪፥፭)

በሰው ዘንድ የነበረውን መርገም በማጥፋት የሁሉም ፈጣሪ አምላካችን እግዚአብሔር ሞትን ድል አድርጎ ዓለምን አዳነ። ትንሣኤ ሙታን በተባለው የሙታን መነሣትም ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው በመነሣት የዘለዓለማዊ ሕይወት መገኛ ጥበብ ወይም የድኅነት መንገድ ሆነልን፡፡

ትንሣኤ

ለሰው ልጆች ዘለዓለማዊ ትንሣኤ በኩር የሆነው የክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ መድኃኒዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባታችን ለአዳም በገባው ቃልኪዳን መሠረት በአይሁድ እጅ መከራ መስቀልን ከተቀበለና ነፍሱን በራሱ ሥልጣን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ዐርብ በ፲፩ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ መስፍኑ ጲላጦስን አስፈቅደውና ከመስቀል አውርደው ዮሴፍ ራሱ ባሠራው መቃብር በንጹሕ በፍታ ገንዘው ቀበሩት፤ መቃብሩንም ገጥመው ሲሄዱ ጸሐፍት ፈሪሳውያንና መስፍኑ በመቃብሩ ላይ ማኅተማቸውንና ጠባቂዎችን አኖሩ፡፡ በሦስተኛው ቀን እሑድ በእኩለ ሌሊት መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በታላቅ ኃይል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ!!!

ሆሣዕና

‹ሆሼዕናህ› ከሚለው በዕብራይስጥ ቃል የተገኘው ‹ሆሣዕና› ትርጉሙ ‹እባክህ አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ ‹‹አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፡፡›› (መዝ.፻፲፯፥፳፭-፳፮) የሆሣዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም›› በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሣዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡ (ዮሐ.፲፪፥፲፫)

ኒቆዲሞስ

በግሪክ ቋንቋ ኒቆዲሞስ የሚለው ቃል ትርጓሜ ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን የሚያመለክት ነው፡፡ በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን በሚሰብክበት ጊዜ አንድ ፈሪሳዊ ከአይሁድ አለቆችና መምህራን ወገን የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው እንደነበረና የጌታችንን ቃል በሌሊት ወደ እርሱ በመሄድ እንደተማረ በወንጌለ ዮሐንስ ተጠቅሷል። (ዮሐ.፩፥፪)

ጥንተ ስቅለት

ለዓለም ሁሉ ድኅነት መድኃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ መጋቢት በባተ በ፳፯ኛው ቀን በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ልጆቹም ይህን እናዘክር ዘንድ ዓይን ልቡናችንን ወደ ቀራንዮ እናንሣ!

ገብር ኄር

በጎ አገልጋይ ለጌታው ታምኝ እንደመሆኑ ‹‹ገብር ኄር›› ይባላል፡፡ ይህም ስያሜ ለዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት እንደተሰጠ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይገልጻል፡፡ የስያሜው መነሻ የሚገኘው ደግሞ በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው በማቴዎስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)

ጥንተ ሆሣዕና

የዓለም መድኃኒት አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንባባና ልብስ ተነጥፎለት በአህያ ውርንጭላዋ ተጭኖ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት ‹‹ጥንተ ሆሣዕና›› በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይዘከራል፡፡ ሆሣዕና ማለት ‹‹አሁን አድን›› ማለት ነው፤ (ማሕቶተ ዘመን ገጽ ፻፷)

ደብረ ዘይት

ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ቦታ የሚገኘው ተራራ ደብረ ዘይት የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተያዘበት ነው፡፡ ቤተ ፋጌ እና ቢታንያ በኮረብታው ጫፍ እና በምሥራቅ ዳገት ላይ ይገኛሉ። ጌታችን ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአት በዚህ ተራራ ላይ ተናገሯል።

‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› (ዮሐ.፭፥፩-፱)

ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የነበረው አንድ በሽተኛ ሰው በጌታችን ቃል ተፈውሶና አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ መሄዱ በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቧል፡፡

ቤተ መቅደስ

ቤተ መቅደስ ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ትርጓሜው ‹የተቀደሰ ቤት› የሚል ሲሆን ይህም የእግዚአብሔር አምላካችን ማደሪያ ወይም ቤት ነው፤ ቤተ መቅደስን የሚወክሉ አካላትም ሦስት ናቸው፡፡