‹‹ሐሰትን አትነጋገሩ›› (ሌዋ.፲፱፥፲፩)

ግንቦት ፴፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ከሁሉም አስቀድሞ ሰዎች ፈጣሪ እግዚአብሔር የእውነት አምላክ እንደሆነ ልንረዳ ይገባናል፡፡ እርሱ እውነተኛና የእውነት መንገድ እንደሆነ ስንናውቅ መንገዳችን በእውነትና ስለ እውነት ይሆናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› በማለት እንደተናገረው በሕይወታችን ውስጥ እውነትን ማሰብ፣ እውነትን መናገር እንዲሁም በእውነተኛው መንገድ መጓዝ የሚቻለን አምላካችን እውነተኛ መሆኑንና ሐሰትን እንደሚጠላ ስናውቅ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፮)

በምድር ስንኖር አብረናቸው ከምንኖራቸው ቤተ ሰቦቻችን፣ ዘመዶቻችን እና ጎረቤቶታችን፣ በትምህርት ቤትና በቤተ ክርስቲያን ከምናገኛቸው መምህራኖቻችን እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር በሚኖረን ማንኛውም ንግግርና ውይይት ላይ ሐሰትን መናገር ኃጢአትን በመሆኑ ‹‹ሐሰትን አትነጋገሩ›› በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ (ሌዋ.፲፱፥፲፩)

የኃጢአት ሁሉ መነሻ ሐሰት ነው፤ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ በሐሰትና በትዕቢት ተነሣስቶ አምላኩን በመካድ ‹‹ፈጣሪያችሁ እኔ ነኝ›› በማለት ራሱ ክዶ መላእክትን ከፍሎ እንዳስካደ ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡ በእምነት የጸኑት እነ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሚካኤልና ሌሎችም መላእክት እውነተኛውን አምላክ ማወቅና ማገልገል ቻሉ፡፡ ሌሎች የካዱት መላእክት ግን ከመረገምም ባሻገር ወደ ዘለዓለማዊ እሳት እንዲጣሉ ተፈረደባቸው፡፡ የኃጢአት መጨረሻው ወደ ገሃነመ እሳት መጣል ነው፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ ትንሽ ወይም ትልቅ ኃጢአት የለም፡፡

በሐሰት አለመነጋገር ከእውነት የራቀን ማንኛውንም ሐሳብ ለሌሎች አለማውራት ነው፤ ሐሰት ትንሽ ጥፋት ቢመስለንም በተለይም ሥር ከሰደደና ሲበዛ እጅግ ከባድ ችግር በሕይወታችን ሊያመጣብን ይችላል፡፡ በዓለማችን ማኅበረሰብ ውስጥ በሐሰት ወሬ የተነሣ የተጣሉ የቤተ ሰብ አባላት፣ ባልና ሚስቶች እንዲሁም ጓደኛማቾች ቁጥርና ጉዳት ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡ በሰዎች መካከል ፍቅር፣ መተሳሰብና መተዛዘን እንዲኖር የማይፈልገው ጠላት ዲያብሎስ የሚዋደዱ ሰዎችን ለማጣላት በሌሎች ላይ በማደር ሐሰትን በማናገርና በሐሰት በመመስከር ያጣላል፡፡ ይህን ነገር እኛ በራሳችን እንዲሁም በሌሎች ሕይወት የተመለከትነው ይሆናል፡፡ በወንድማማችና በእኅታማማቾች መካከል ስምምነትና ፍቅር እንዳይኖር፣ ባልና ሚስት አንድ ሆነው ትዳራቸውን እንዳይመሩ፣ በጎረቤታማቾች መሐል ጥል እንዲፈጠር ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች አይጠፉምና አንዱን ከሌላው ለማጣላት የሚጠቀሙበት መንገድ ሐሰትን መናገር ነው፡፡

ሐሰት የማኅበረሰባዊ ቀውስን ከማምጣት አንጻር ያመጣው ጉዳት እጅግ ከባድ ነው፤ ለሰዎች የሚያስፈልገንን ፍቅር፣ መተሳሰብና መተዛዘን እንድናጣ የሚያደርገን ነገር በሐሰተኝነት የተነሣ የሚፈጠረው ተአማኒነትን ማጣት እና የጥላቻ ስሜት ነው፡፡ ምክንያቱም ደጋግመን ሰዎችን የምንዋሽ እንዲሁም ንግግራችን በአብዛኛው በሐሰት ላይ የተመረኮዘ ከሆነ ተአማኒነትን እናጣለን፡፡ ይህም እያደር ጥላቻን ይፈጥራል፡፡

በምድር ላይ መኖር የምንችለው ደግሞ በመዋደድ መተዛዘንና መተሳሰብ ስንችል ነው፤ በጥላቻ ስሜት የምንመራው የይምሰል ኑሮአችን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን የእያንዳንዳችን ሕይወት ምስክር ነው፡፡ የኑሮ ዋጋ ግሽበት በናረበት በዚህ ጊዜ የዕለት ዕለት ኑሮአችንና ወጪያችንን ለመሸፈን አቅቶን የምንጨነቅበት ይህን ወቅት አልፈን ከመጣብን መከራና ችግር መላቀቅ ያልቻልነው ምድራዊ ጥቅም እና ሥጋዊ ፍላጎታችንን ለሟሟላት ስንል በሐሰት መኖራችን ነው፡፡ ካለንበት ችግር ለመውጣት፣ ገንዘብ ለማግኘት፣ በምድር ለመክበርና በሥልጣን ለመኖር ስንል እንዋሻለን፤ ይብዛም ይነስም ግን ሐሰት መናገራችን ለጥፋት እንደሚዳረገን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ምንም ያህል መከራ በፊታችን ቢጋረጥብን እውነትን ከያዝን አምላካችን እግዚአብሔር ያለብን ችግር ይፈታልናል፤ ከሥቃይም ያወጣናልና፡፡

ከዚህ ላይ አንድ ምሳሌ የሚሆነን ታሪክ እናንሣ፤ ሶስና የተባለች ቅድስት ነበረች፤ እናትና አባቷም ደጋግ ነበሩ፤ ሶስናንም የኦሪትን ሕግ አስተማሯት። እርሷም እጅግ መልከ መልካም ነበረች፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ትኖር ነበር፤ ኢዮአቄም የተባለ ሰው ባልም ነበራት፡፡ እርሱም እጅግ ባለጸጋ ነበር፤ በዚያም ወራት ሁለት ግብዞች የሆኑ መምህራን ነበሩ፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ቀትር በሆነ ጊዜም ሶስና ወደ ባሏ ተክል ቦታ ገብታ በዚያ ስትመላለስ እነዚያ መምህራን ሁልጊዜ ያዩዋት ስለነበር አብረዋት ለመተኛት ተመኙ። በዚህም ጊዜ ሁለቱም ፈቃዳቸውን ለመፈጸም ቢፈልጉም መናገር ስላፈሩ እርስ በርሳቸው በልቡናቸው ያለውን ነገር አልተነጋገሩም፡፡ ይደርሱባት ዘንድ ይወዱም ስለነበር ያገኟትም ዘንድ ሁል ጊዜ ይጠብቋት ነበርና የምሳ ሰዓታቸውን ተጠቅመው ሊገናኟት ፈልገው ተሰነባበቱ፡፡ ነገር ግን አንዱ ሌላውን ያታለለ መስሎት ሁለቱም ተመልሰው በዚያ መንገድ ተገናኙ፡፡ ከዚያም ተያዩና ፍላጎታቸውን ተነጋገሩ፤ ሶስናንም ብቻ ለብቻ የሚያገኙበትን ጊዜ ተቃጠሩ።

ከዚህም በኋላ በተክል ቦታው ውስጥ ሆነው ሲጠብቋት ሶስናም እንደሁል ጊዜ ከሁለቱ ደንገጡሮቿ ጋር ገባች፤ አልቧት ስለነበርም በተክል ቦታው ውስጥ ልትታጠብ ፈለገች። ተደብቀው ከሚጠብቋት ከሁለቱ ረበናት በቀር በዚያ ማንም ማን አልነበረም። ሶስናም ደንገጡሮቿን ዘይትና ሽቱ አምጥተው እንዲያጥቧትና የተክሉንም ደጅ እንዲዘጉ አዘዘቻቸው። እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ፤ የተክሉን ደጃፍ ዘግተው ያዘዘቻቸውን ለማምጣት ወጡ፤ የተደብቁትን ረበናት ግን ማንም ያያቸው አልነበረም።

ደንገጡሮቿ ከወጡ በኋላ ግን ሁለቱ ረበናት ተነሥተው ወደ እርሷ ሮጡ፤ ‹‹እነሆ የተክሉ ደጃፍ ተዘግቷል፤ የሚያየን የለምና እንደርስብሽ ዘንድ እንወዳለንና እሺ በይን፤ ይህ ካልሆነ ከአንቺ ጋር ሰውን እንዳገኘን ተናግረን እናጣላሻለን፤ ስለዚህም ደንገጡሮችሽን ከአንቺ አሰወጥተሽ ሰደድሽ።›› አሏት፡፡ በዚህም ጊዜ ሶስና አለቀሰች፤ ‹‹በሁሉም ፈጽሞ ተጨነቅሁ፤ ባደርገው እሞታለሁ፤ ባላደርገውም አልድንም፤ ከእጃቸው ማምለጥንም አልችልም፤ በእግዚአብሔር ፊት ከምበድል ኃጢአት ሳልሠራ በእጃችሁ መውደቅ ይሻለኛል›› አለች። ሶስናም ጮኸች፤ እነዚያም ረበናት ከእርሷ ጋር ጮኹ፤ ከዚያም አንዱ ሩጦ ሄዶ የተክሉን ደጃፍ ከፈተ፤ በቤቷም የነበሩትም ጩኸታቸውን ሰምተው ወጥተው ወደ እነርሱ ሮጡ፤ ሁለቱ ረበናትም በሐሰት ወነጀሏት፡፡

በማግሥቱ ሕዝቡ በተሰበሰበበት መካከልም ሁለቱ ረበናት እንዲህ በማለት ተናገሩ፤ ‹‹ብቻችንን በተክል ውስጥ ስንመላለስ እርሷ ከሁለቱ ደንገጡሮቿ ጋር ገባች ደንገጡሮቿንም ልካቸዋለችና የተክሉን ደጃፍ ዘግተው ሄዱ፤ ከዚያም በኋላ አንድ ጐልማሳ ከተሠወረበት መጥቶ አብሮዋት ተኛ። እኛ ግን በዚያ ተክል ዳርቻ ሁነን ኃጢአታቸውን አየን፤ ወደ እነርሱም ሮጥን አንድነት ተኝተውም አገኘናቸው። እኛም እርሱን መያዝ ተሣነን፤ እርሱ በርትቶብናልና አመለጠን፤ የተክሉንም ደጃፍ ከፍቶ ወጣ። እርሷን ግን ይዘን ሰውዬው ማን እንደ ሆነ ጠየቅናት ግን አልነገረችንም፤ ለዚህም ነገር ምስክሩ እኛ ነን›› አሉ። ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ በሶስና ላይ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ ተሰምቶ አያውቅም ነበርና ዘመዶቿና አሽከሮቿ እጅግ አፈሩ፤ አባቷ፣ እናቷ፣ ቤተሰቦቿ፣ የሚያውቋትም ሁሉ አለቀሱላት። እነዚያም ሁለቱ መምህራን በሕዝቡ መካከል ተነሥተው እጆቻቸውን በራሷ ላይ አኖሩ። ቅድስት ሶስና ግን እግዚአብሔርን በማመን እያለቀሰች ወደ ሰማይ ተመለከተች።

በፍርዱ አደባባይ ላይ የተሰበሰቡት መምህራንና መኳንንትም ስለነበሩ በአደባባይ የተሰበሰቡ ሰዎች የተናገሩት ነገር እውነት መስሏቸው አምነው እንድትሞት ፈረዱባት፤ ቅድስት ሶስናም በዚህ ጊዜ ቃሏን አሰምታ ጮኸች፤ ‹‹ዘለዓለም ጸንተህ የምትኖር የተሠወረውን የምታውቅ የሚደረገውን ሁሉ ሳይደረግ የምታውቅ ፈጣሪ ሆይ በሐሰት እንደመሰከሩብኝ አንተ ታውቃለህ፤ እነዚህ መምህራን ክፉ ነገርን ባደረጉብኝ ገንዘብ የሠራሁት ኃጢአት ሳይኖር እነሆ እሞታለሁ›› አለች። እግዚአብሔርም ቃሏን ሰማ።

የሞት ፍርድም ተፈርዶባት ልትገደል በምትወሰድበት ሰዓት እግዚአብሔር በመካከላቸው የነበረውን የነቢዩ ዳንኤልን ልቡናን አነሣሣ፤ ‹‹እኔ ከዚች ሴት ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ ቃሉን አሰምቶ ተናገረ። ሕዝቡም ‹‹አንተ የምትናገረው ይህ ነገር ምንድን ነው?›› በማለት ጠየቁት። እርሱም በመካከላቸው ቁሞ ‹‹አላዋቂዎች የምትሆኑ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሳትመረምሩና ነገሩን ሳትረዱ በእስራኤል ልጅ ላይ እንዲህ አድርጋችሁ እንደዚህ ያለ ፍርድን ትፈርዳላችሁን?›› አለ፤ ‹‹እነዚህ መምህራን በሐሰት መስክረውባታልና ወደ አደባባይ ተመለሱ›› አላቸው።

የተሰበሰበው ሕዝብ በሙሉ እየሮጡ ወደ አደባባይ ተመለሱ፤ አለቆችም ዳንኤልን ‹‹እግዚአብሔር አንተን አልቆሃልና በመካከላችን ተቀምጠህ ተናገር›› አሉት። ዳንኤልም እየራሳቸው አራርቃችሁ አቁሙአቸው፤ እኔም ልመርምራቸው›› አላቸውና አንዱንም አንዱን አራርቀው አቆሟቸው። ዳንኤልም አንዱን ጠርቶ ‹‹….ይህችን ሴት ካየሃት ሁለቱን ሁሉ በምን ዓይነት ዛፍ ሲጫወቱ አየህ?›› በማለት ጠየቀው፤ እርሱም ‹‹በኮክ ዛፍ ሥር ሲጫወቱ አየኋቸው›› በማለት መለሰ፤ ……እርሱን ደግሞም አርቆ ሁለተኛውን ‹‹…..ሁለቱ ሲጫወቱ ያየህበት ዛፍ ምንድን ነው?›› አለው፤ ‹‹ሮማን በሚባል ዛፍ ሥር አየኋት›› ብሎ መለሰ። በዚህም መልስ ሐሰታቸው ታውቆባቸው ሶስና ከተፈረደባት የሞት ፍርድ ነጻ ወጥታለች፡፡ ሕዝቡም ሁሉ በአድናቆት በመጮህ ቅድስት ሶስናን ያዳነ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ እነዚያ ሁለቱ መምህራንም በሞት ፍርድ ተቀጡ። (ዳን.፲፫፥፶፬‐፶፰)

ይህን ታሪክ ያነበበ ወይም የሰማ ሰው የእውነትን ኃይል ብቻም ሳይሆን የሐሰተኝነትን ጥፋትና አስከፊ ቅጣት መረዳት እንደሚችል ይታመናል፡፡ ምክንያቱም ጊዜው ይቅረብም ይራቅ ሐሰተኞች መጋለጣቸው አይቀርምና በሞት ቅጣት ይቀጣሉ፡፡ የሐሰት መዘዙ በዚህ ምድር የሞት ቅጣት ሲሆን በዚያኛው ዓለም ደግሞ ወደ ዘለዓለማዊ እሳት መጣል ነው፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር በእውነት መንገድ የምንጓዝ እውነተኞች እንድንሆን ይርዳን፤ አሜን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር መስከረም ፳፰