በዓለ ቅዱስ ሩፋኤል

ቀሲስ ሀብታሙ ተሾሙ

ጳጉሜን ፪፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በዓለ ቅዱስ ሩፋኤል በጳጉሜን ሦስት ቀን የሚዘከር በዓል ነው፡፡ “ሩፋኤል” የሚለው ስያሜ ትርጉም “ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ” ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዕብራይስጥ ሁለት ቃላት ጥምረት የተገኘ ቃል ነው፡፡ “ሩፋ” ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት ማለት ሲሆን “ኤል” ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ የሚቀጸል ስመ አምላክ ነው:: ይህም “መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ፤….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ አታስመርሩት” እንዲል፤ (ዘፀ.፳፫÷፳-፳፪)፡፡ በመሆኑም “ሩፋኤል” የሚለው በጥምረት “ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ” የሚለውን ያስረዳል፡፡  “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል፡፡ (ጦቢት ፲፪፥፲፭) ይህ መልአክ እንደ ሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን ይጠብቃቸዋል፡፡ (ዳን.፬÷፲፫፣ዘፀ.፳፫÷፳፤ መዝ.፺÷፲፩-፲፫) ያማልዳል፤ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡ (ሉቃ.፲፫፥፮-፱፣ ዘካ.፩÷፲፪) ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያለ ማቋረጥ ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡

በተለይም በጳጉሜን ሦስተኛዋ ቀን ቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚታሰብባት ወቅት ናት፤ የተለያየ ትንታኔም ይነገርባታል፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርገው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን በሰባት መንገዶች ይገልጡታል፡፡

. ፈዋሴ ዱያን (ሕሙማንን የሚፈውስ)

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን (መድኃኒትነት) ለእርሱ የባሕሪው ነው፤ የማዳንን ጸጋ ለቅዱሳን ሰጥቷል፤ ከቅዱሳን መላእክትም ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኃጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የሚረዳ መልአክ ነው፡፡ ሄኖክ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው” በማለት ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል፡፡ (ሄኖክ ፲፥፲፫) ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ሆነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ሄኖክ “በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” እንዳለ፡፡  (ሄኖክ ፮፥፫)፡፡ ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው መልአክ ዛሬም ሁላችንን በጸሎቱ ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰን፤ አሜን፡፡

. ፈታሔ ማኅፀን፡ ማኅፀንን የሚፈታ

ብዙ እናቶች ከመካንነት የተነሳ ኀዘን ጸንቶባቸው የቆዩ መሆኑን በብሉያና በአዲስ ኪዳን ተገልጿል፤ ከእነዚህም ውስጥ ቅድሰት ሣራ፣ እናት ርብቃ፣ ራሔል፣ ቅደስት ሐና፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ የድንግል ማርያም እናት ቅድስት ሐና ይገኙበታል፡፡ እግዚአብሔር የመካኒቱን ማኅፀን ፈትቶ የተባረከ ልጅን የመስጠትን ጸጋ ለመላእኩ ቅዱስ ሩፋኤልም  ሰጥቶታል፡፡ የወላድን ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሾመ ከጌታ አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ ሴቶች ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ብለው ማየ ጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ፡፡ ቅድስት ሣራን እና እንትኩይን (የሳሙኤል እናት) ወልዶ ለመሳም ያደረጋቸው ፈታሔ ማኅፀን የሆነው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ለነፍሰ ጡር ሴቶች ረዳታቸው ሲሆን  ሕፃኑ (ኗ) በማኅፀን እያለ(ች) ተሥዕሎተ መልክዕ ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም ፈታሔ ማኅፀን ነውና ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል፤ እናቶችንም ከመፅነስ እስከ መውለድ የሚራዳቸው፣ የመካኖችንንም ማኅፀን የመፍታት ጸጋ የተሰጠው መልአክ ነው፡፡

. ሰዳዴ አጋንንት (አጋንንትን የሚያሳድድ)

አጋንንትን የማስወጣት ሥልጣን ለቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ጌታችን ሰጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በሣራ (ወለተ ራጉኤል) ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ሲያሰቃያት የነበረውን ይህን ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል (ጦቢት ፫፥፰-፲፯)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል “ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሄኖክ ፫፥፭-፯)፡፡ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ (ሄኖክ ፪፥፲፰) አዛዝኤል ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ ጋኔን ነበር፡፡

. አቃቤ ኆኅት (የምሕረትን ደጅ የሚጠብቅ)

ቅዱስ ሩፋኤልም ስለ ራሱ ማንነት በሰጠው ምስክርነት “የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” አላቸው፤ (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያን በወደቡ አጠገብ ነበረች፤ ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለምስጋና የታደሙትን ምእመናን ሊያጠፋ ዓሣ አንበሪውን ጠላት ዲያቢሎስ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ምእመናኑም ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔር በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮሁ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ “እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጥ ጸጥ ብለህ ቁም!” አለው፤ አንበሪው ጸጥ አድርጎ በማቆም ምዕመናኑንም ከሞት ታድጓቸዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሩፋኤል መዝገበ ጸሎት እና አቃቤ ኆኅት ይባላል፡፡

. መራኄ ፍኖት (መንገድ መሪ)

ቅዱስ ዳዊት “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ” እንዲል (ዘፀ.፳፫፥፳)። ይህ ኃይለ ቃል ሰውን መንገድ የመምራትና የመጠበቅ ሥልጣን ቅዱስ እግዚአብሔር ለመላእክት እንደተሰጣቸው የሚያስረዳ ሲሆን የጦቢትን ልጅ ጦቢያን ከነነዌ የሜዶን ክፍል ወደ ሆነችውና ራጌስ ወደምትባለው ሀገር ሲሄድ አዛርያስ  (ቅዱስ ሩፋኤል) በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ ጦቢያና አዛርያስ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ሲደርሱ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረዶ  መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል “ጦብያን ያዘው፤ ዓሣውን እንዳትለቀው” አለው፤ ጦቢያም ከዓሣው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል “ጦብያን ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን” አለው፡፡ ከዚያም መነገዱደን እየመራቸው ለመሄድ ከፈለጉበት ቦታ አደረሳቸው፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል “መራኄ ፍኖት” (መንገድ መሪ) ይባላል፡፡ (መጽሐፈ ጦቢት)

. መልአከ ከብካብ (ጋብቻን የሚባርክ መልአክ)

የራጉኤል ልጅ ሣራ ሰባት ጊዜ ብታገባም ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ አድረዋል፡፡ ይህንን ክስትትም የጦቢት ልጅ ጦቢያ ያውቅ ነበር፡፡ ለአዛርያስም “ስለዚህ እኔ ለአባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ፤ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም፤ ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ” አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ፤ አይዞህ አትፍራ፤ አትሞትም፤ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ያዘው ያልኩህ ለምን ይመስልሃል? ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል፤ ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ፤ እርሷም የተዘጋጀች ናት፤ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን›› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለው፤ እርሷን ብቻ እንዲያገባ በሙሉ ሐሳቡ ወሰነ፡፡

ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው፤ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት፤ ሰጥቸሃለሁ፤ አይዞህ፤ አትጠራጠር፤ አሁንም ብላ፤ ጠጣ፤ ለዛሬም ደስ ይበልህ›› አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን ‹‹በይ እኅቴ! ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ›› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ለመጨረሻ ላይመለስ ሄደ፤ ከዚያ በኋላ አልተመለሰም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ በመሆኑም  የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ “መልአከ ከብካብ” ይባላል፡፡ ዛሬም በምልጃው ላመኑት ጋብቻን ይባርካል፣ ትዳርንም ያጸናል፡፡

. ከሳቴ እውራን (ዓይነ ስውራንን የሚያበራ)

የሣራንና የጦቢያን የጤንነታቸውን ነገር ሲረጋገጥ የሰርጉ ቀን የሚሆን የዐሥራ አራት ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ አለሔደም ነበር፤ የዐሥራ አራት ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡  ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ በመጣ ጊዜ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ወደቀ፤ እንደ ወደቀም ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን የአባቱን ዓይን ሲቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡ በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል አማካኝነት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን በራለት እንዳበራለት ቅዱስ ሩፋኤል ዛሬም በሒዲስ ኪዳንም በምልጃው ለሚያምኑት ሥጋዊ ዓይንና መንፈሳዊ ዓይንን የሚያበራ መልአክ ነው፡፡

የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ጸሎትና አማላጅነት ልጅ ለሌላቸው መልካም የልጅ ፍሬን፣ ለታመሙት ድኅነትን፣ ለባለ ትዳሮች እግዚአብሔር የፈቀደውን መልካም ትዳርን እንዲሰጥልን  የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱስ ሩፋኤል ተረዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር፣ ተአምረ ሩፋኤል