“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር” (መዝ.፻፲፭፥፭)

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ነሐሴ ፳፫፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ተክለ ሃይማኖት ማለት የስሙ ትርጓሜ “የሃይማኖት ተክል ማለት” ነው። ተክል ሥርም፣ ግንድም፣ ቅጠልም፣ ቅርንጫፍም ነውና ተክለ ሃይማኖት እንጂ ሌላ አላላቸውም። በእርሳቸው ተክልነት ቅርንጫፍ የሆኑ ፲፪ ከዋክብት አሉና “ተክል” አላቸው። ተክል ባለበት ልምላሜ አለ፤ እርሳቸው ባሉበትም የኃጢአት ፀሐይ፣ የርኩሰት ግለት የለም፤ የጽድቅ ዕረፍት እንጅ። ተክል ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ተደግፎት ይኖራል! ቢቆርጡት ለመብል ለቤት መሥርያ ይሆናል፤ ቢያቆዩት ማረፊያ መጠለያ ይሆናል፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በዐጸደ ነፍስ ሆነው በምልጃ በጸሎት ያግዛሉ፤ ያማልዳሉ፤ በሕይወት ሳሉም በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ኃይል ለብዙዎች ዕረፍት ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል ተክል ያላቸው ፍሬያቸውን ዋጋቸውን እርሱ ጌታ ስለሚሰጣቸው ነው! ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በጥምቀት የሥላሴን ዘር በልባችን እንቀበላለን፤ ይህቺም ዘር በውኃ ምግባር በቅላ በቅድስና ፀሐይ አድጋ አብባ ፴፣፷፣፻ ፍሬ ታፈራለች። ቅድስና ማለት በልብ ያለች የሥላሴን ዘር ለፍሬ ማብቃት ነው ብሎ እንደተረጎመው (የዮሐንስን ወንጌል ትርጓሜ ይመልከቱ) ተክለ ሃይማኖት ያላቸው ለዚህ ነው! ሃይማኖት በቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ማመን ነውና ተክለ ሥላሴ ሲላቸውም ነው! የሰጣቸውን ዘር ለፍሬ አብቅተዋልና “ተክል” አላቸው። በሌላ በኩልም ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ለቅዱሳን የተሰጠ ቅዱሳን ለቅዱሳን የሚያስረክቡት የዘለዓለም ሕይወት በመሆኑ ተክለ ሃይማኖት ያላቸው ይህንን ያልተቋረጠ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ይዘው ስላስቀጠሉ ነው።

ድካም በማብዛት እንደ ነቢያት፣ ወንጌልን በማስተማር እንደ ሐዋርያት፣ በመገረፍ እንደ ሰማዕታት፣ አጥንቱ ከሥጋው ጋር እስኪጣበቅ ከሰውንቱ ማለቅ ብዛት የሚያቃጥለውን ላብ እንደ ደም በማፍሰስ ከስግደቱ የተነሣ የሰውነቱ መለያ እስኪቆጠር ድረስ ተባሕትዎን በመያዝ እንደ መነኮሳት በመንፈሳዊ መገዛት የሚገዛ፣ ጸሎቱ እንደ ማይደርቅ የውኃ ምንጭ ወይም እንደ ትንፋሽ ሌሊትና ቀን የማያቋርጥ ለጌታው የታመነ፣ ስም አጠራሩ በበጎ የቆመ፣ የመዐዛው ሽታ እንደ ተወደደ ሽቱ የሆነ፣ የነገሩ ጣዕም ስሙም በሁሉ አፍ እንደ ማር የጣፈጠ፣ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ የተመረጠ፣ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “ተክለ ሃይማኖት ማኅቶት እምኢትዮጵያ ሰዳዴ ጽልመት እግዚአ መናፍስት” (መጽሐፈ ሰዓታት) በማለት ከኢትዮጵያ ላይ የድንቁርና፣ የጣዖት አምላኪነት፣ የክሕደትን ጨለማ ያስወገደ ብርሃን በርኩሳት መናፍስት ላይ የተሾመ የእግዚእ ኀረያና የጸጋ ዘአብ ልጅ ተክለ ሃይማኖት በነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። (ገድለ ተክለ ሃይማኖት)

ሞት ቀጥተኛ ትርጉሙ መለየት ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “መሞት፣ መለየት፣ በነፍስ ከሥጋ፣ በሥጋ ከነፍስ መራቅ፣ እየብቻ መሆን፣ መድረቅ፣ መፍረስ፣ መበስበስ፣ መነቀል፣ መፍለስ፣ መጥፋት፣ መታጣት” እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ (ገጽ፣፭፻፹፩) አያይዘውም “ሞት በቁሙ የሥጋዊና የደማዊ ሕይወት ፍጻሜ በአዳም ኃጢአት የመጣ ጠባይዓዊ ዕዳ ባሕርያዊ ፍዳ” በማለት ይፈቱታል፡፡ የተለያየ ሞት ቢኖርም በዚህ ርእሳችን ስለ ሥጋ ሞት እንመልከት። የሥጋ ሞት የሚባለው የነፍስ ከሥጋ መለየት ማለት ነው፡፡

ይህ ሞት ለፍጥረት ሁሉ የማይቀር ሁሉም የሚቀምሰው ነው። “መኑ ሰብእ ዘየሐዩ ወኢይሬእያ ለሞት” “ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? (መዝ.፹፱፥፵፰) በማለት ቅዱስ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህ ሞት የሚያስፈራ ሳይሆን የሚናፈቅ ከእግዚአብሔር ጋር የምንኖርበት ወደ ዘለዓለም ዕረፍት የምንሸጋገርበት ድልድይ ነው። ሞት የማይቀር ነውና ኃጢአትን እንጅ ሞትን መፍራት አይገባንም። ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፍንና ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን በመናፈቅ እንዲህ ይላል፤ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። ነገር ግን በሥጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ አላስታውቅም። በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው።” (ፊል. ፩፥፳፩-፳፬)

በርእሳችን “የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” በማለት ቅዱስ ዳዊት የተናገረውን በማንሳት እናጠቃል፤ የአባታችን ተክለ ሃይማኖት ሞት ወይም ዕረፍታቸው፣ ወደ ዘለዓለም ዕረፍት የተሸጋገሩበት፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት፣ የድካም ዋጋቸውን አክሊል የተቀዳጁበት ድንቅ ዕለት ነው። ገድላቸው እንደሚነግረንም በዚህች ቀን እግዚአብሔር ከእናቱ ከድንግል ማርያም ከባለሟሎች መላአክት ከቅዱሳን ጋር በኅብረት ወደ አባታችን መጥቶ እንዲህ አላቸው ይላል፤ “ወዳጄ ተክለ ሃይማኖት ሆይ እንዴት አለህ ከድካምና ከኀዘን ወደ ዘለዓለም ዕረፍት፣ ከባርነት ወደ ነፃነት ላወጣ ወደ አንተ መጥቻለሁ። መታሰቢያህን ለሚያደርግ ስምህን ለሚጠራ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ….፡፡” ይህ ነገር ያልከበረ ምን ክቡር ነገር ይኖር? እንደ ንጉሥ በመላእክት ታጅቦ በንግሥተ ሰማይ እና ምድር በድንግል ማርያም እየተባረከ በነገሥታት ንጉሥ በክርስቶስ መጎብኘት በደስታ ወደ ዘለዓለም ዕረፍት መግባት የከበረ ገናና ነውና የቅዱሳን ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው አለ።

አምላካችን በቸርነቱ ለአባታችን ተክለ ሃይማኖት በተሰጣቸው ቃል ኪዳን ይማረን፤ በረከታቸው ረድኤታቸው አይለየን፤ አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለውላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!