“ተዘጋጅታችሁ ኑሩ’’ (ማቴ.፳፬፥፵፬)

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
ጳጉሜን ፩፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ጌታች አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ የነገራችው ኃይለ ነው፤ ‘’ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደሚመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ፤ እወቁ ባለቤት ሌሊት ሌባ በየትኛው ጊዜ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃ፤ ቤቱንም እንዲቆፈር ባልተወ ነበር’’ አላቸው፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡት ሰዓት ይመጣልና፤ እንግዲያስ ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታ በቤት ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝ ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባርያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል፤ አገልጋዩን ታማኙን ሰው አምላካችን እግዚአብሔር በመንግሥቱ ይሾመዋል፡፡

ዝግጅት ማለት ምንድን ነው?

ዝግጅት ማለት ቅድመ መሰናዶ ማለት ሲሆን በመጸሐፈ ምሳሌ ፮፥፮ ላይ ጠቢቡ ሰሎሞን “አንተ ታካች ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ፣ መንገዱንም ተመልክተህ ቅና፤ ከእርሱም ይልቅ ብልህ ሁን፤ ጌታ ሳይኖረው፣ መሰማሪያ ሳይኖረው፣ የሚያሠራውም ሳይኖረው መብሉን በበጋ ይሰበስባል፤ በመከርም ጊዜ በሰፊ ቦታ ያስቀምጣል’’ እንዳለን እንዲሁም ከክስተት በፊት መጠንቀቅ ማለት ነው፡፡ በዚህም በኦሪት ዘፍጥረት ፵፩፥፶፫-፶፯ ላይ ‘’ቅዱስ ዮሴፍ ግብጻውያን እንዳይርባቸው እህል አስቀመጠ፤ እንዲሁም ሀገሮች ሁሉ ከዮሴፍ እህል ይገዙ ዘንድ ወደ ግብጽ ወጡ’’ እንዲል፡፡ ዝግጅት ማለት ሥራ አለመቀመጥ ማለት ሲሆን በኢዮብ ፫፥፳፮ ላይ “ተዘልዬ አልተቀመጥኩም፤ አላረፍኩም” እንደተባለው ነው፡፡

ለምን እንዘጋጃለን ?

፩ኛ. ‘’ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣበት ጊዜና ሰዓት ስለማይታወቅ’’፤ ሁልጊዜ ተዘጋጅተን መጠበቅ አለብን፡፡ (ማቴ.፳፬፥፵፫፣የሐዋ.፩፥፱) እንዲሁም የምንሞትበት ጊዜ እና ሰዓት አይታወቅምና፡፡
፪ኛ. መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ነው፡፡ በ ማቴዎስ ወንጌል ፳፭፥፴፬ “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ” በማለት ጌታችን ተናግሯል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈው የራእይ መጽሐፍ ላይ ደግሞ “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆቿ ወደ ከተማይቱ እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያነጹ ብፁዓን ናቸው” በማለት ተነግሮናል፡፡ (ራእ.፳፪፥፲፬)

ዝግጅት በምን ይገለጣል?

በንስሓ

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የስብከቱ መጀመሪያ ያደረገው ቃል “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” የሚለውን ነው፡፡ (ማቴ.፬፥፲፯) ንስሓ ለመንግሥተ ሰማያት የምታበቃ መታወቂያችን ናት፣ ንስሓ ነፍስን የምታድን፣ ውሳጣዊ ማንነታችንን የምታጠራ ናትና፡፡

ጌታችን ባልታሰበው ቀን ይመጣል፤ ነቅቶ ልብሱን የሚያነጻ ብፁዕ ነው፡፡(ራእ.፲፮፥፲፭፣ ፩ኛ ዮሐንስ ፩፥፰) ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናታልላለን፡፡ ኃጢአት ማለት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሰናክል እንቅፋት ነው፡፡

አንዳንዴ በተለያየ ደዌ ተይዘን ቢሆን እንኳን ያቺ ንስሓ ደዌያችንን ትፈውሳለች፤ እኛ የማናውቀው የሥጋዊ በሽታችንን ታነጻለች፤ ነፍስንም ታበራለች፡፡ በሰውነታችን ከአራቱ ባሕርያት በዝቶ የሚገኘው አንዱ ውኃ ነው፤ ውኃ ለምን በዛ? ነፋስ ለምን አነሰ? እሳት ለምን አነሰ? መሬታዊ ባሕርይ ለምን አነሰ? የውኃ ባሕርያችን ለምን በዛ? ምክንያቱም ውኃ ያደፈ፣ የቆሸሸ፣ የተበላሸ እና ንጹሕ ያልሆነን ነገር ያጠራልና፤ ውኃ የማይሰለች፣ የሰው ልጅ እና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በደስታ በርካታ የሚጠጡት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህም ሁል ጊዜ እኛ ባወቅነው እና ባላወቅነው ስሕተት እንወድቃለንና፡፡ ውኃ ያደፈን እንደሚያጠራ ሁሉ እኛም በንስሓ የሚታጠብ ሕይወት ስላለን ሁል ጊዜ ለመታጠብ ዝግጁ የሆነ ሥጋ ስለሚኖረን እንዲሁም ሰዎች ነንና በሰውነታችን በዝቶ የሚገኘው ውኃ ስለሆነ እንዲሁም እኛ ሰዎች ስለሆንን በሦስት ነገር ስለምንስት፣ ስለምንበድል በማሰብ፣ በመናገር እና በተግባር እንበድላለን፤ እግዚአብሔርንም እናሳዝናለን፤ እነዚህ ሦስት ነገሮች በውስጣችን ስላሉ መንጻትም፣ መታደስም ስላለባቸው ውኃችን በዝቷል፡፡ ነፋሳዊ ማንነታችን ግን ኅሊናችን ነው፤ ሰይጣን ሊሸሸን የሚችለው ኅሊናችን ንጹሕ ሲሆን ነው፤ ኅሊናችን በጎ ካሰበ ሰይጣንን የሚያባርር ከሆነ ሰይጣን በምንም ተአምር ወደ እኛ አይቀርብም፡፡ በንስሓ ውኃ ስንታጠብ በመላእክት ዘንድ ፍጹም ደስታ ይሆናል፤ ንስሓ በምድር በሰማይም ክብርን የምታሰጥ ናትና። (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘዓርብ)

ሥጋ ወደሙን በመቀበል

አገልግሎታችን ሊጠነክር የሚችለው በሥጋ ወደሙ ሲታሰር ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚች ምድር የመጣው ለእኛ ለኃጢአተኞች ነው፡፡ (ማቴ.፱፥፲፯) ለጻድቃን አይደለም፤ ጠፍተን ለነበርን፣ ለእኛ ለበደልነው፣ ላሳዘነው፣ ላስከፋነው ነው፡፡ (ሉቃ.፳፫፥፵፩)ያ በኃጢአት አረንቋ ውስጥ ዕድሜ ልኩን የኖረው ፈያታዊ ዘየማን “እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” ያለው “እኔ በደለኛ ነኝ፤ እኔ ኃጢአተኛ ነኝ” በማለት ንስሓ ስለገባ ነው፡፡ (ማቴ.፱፥፲፯) ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ማን ጠቆመው?” ይላል፤ ማን ነገረህ? ነፋሱ ነው? ጥላው ነው? ወይስ የትኛው ነው የነገረህ? ንስሓ እንድትገባና እግዚአብሔር መሓሪ እንደሆነ ማን ነገረህ? አሁንስ ለእኛ ማን ነው የሚነግረን? ነቢዩ ዳዊት ኃጢአት ሲሠራ ነቢየ እግዚአብሔር ናታን ተላከለት፤ እኛስ ስንበድልና ስናሳዝን ማን ነው መጥቶ የሚነግረን? ዕለት ዕለት ቤተ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ ትነግረናለች፤ እኛ ግን በሚገባ አልሰማንም፡፡

በፍቅር በመኖር

ቅዱስ ጳውሎስ “ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍጻሜ ነው” ይለናል፡፡ (ሮሜ ፲፫፥፲) እኛ ክርስቲያኖች የምንናገረውን ነው የምንተገብረው ወይስ የምንኖረውን ነው የምንናገረው? “ከዐመፃ ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” እንደተባለውም አሁን የምናየው ነገር ይህ ነው፤ (ማቴ.፳፬፥፲፪) በፍቅር መኖር ስንጀምር እግዚአብሔርን እናየዋለን፤ እርሱ በእኛ ይከብራል፤ አምላክነቱን እኛ እናውቀዋለን፤ እርሱም እኛን ይጠብቀናል፡፡

በሃይማኖት ፍቅር አለ፤ ሃይማኖት ያለው ሰው እግዚአብሔር አለው ማለት ነው፤ ሃይማኖት ያለው ሰው ፍቅር አለው ማለት ነው፤ ሃይማኖት ያለው ሰው መንግሥተ ሰማያት የእርሱ ናት ማለት ነው፤ ሃይማኖት ያለው ሰው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታማልደዋለች፤ ሃይማኖት ያለው ሰው በማንኛውም ነገር አይፈራም፤ ሃይማኖት ያለው ሰው ይጸናል፤ ለአገልግሎት አያጉረመርምም፤ መቼ ላገልግል? እንዴት ላገልግል? በማለት ለአገልግሎት ይፋጠናል፡፡ እንደ ማርታ አያጉረመርምም፤ ስለሌላውም ይጨነቃል፤

ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “ምሕረት፣ ርኅራኄ፣ ቸርነት፣ ትሕትና፣ የዋህነት እና ትዕግሥትን ልበሱ” ብሎ በነገረን መሠረት ክርስቲያናዊ ባሕርያችን በትሕትና የተሞላ ሊሆን ይገባል፡፡ (ቆላ.፫፥፲፪) አገልግሎታችን የሚከናወነው በትሕትና ነው፤ መታዘዝንም ያመጣል፤ ትሕትና ውስጣችን ካለ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይኖራል፤ ምንም ያህል የከፋ ጊዜ ላይ ብንሆንና ችግርና መከራችን ቢበዛ በሥቃይ ውስጥ ሆነንም አገልግሎታችንን በትሕትና ልንፈጽም ይገባል እንጂ በምሬት የተሞላ አንደበትና በቂምና በጥላቻ የታወረ ልብ ካለን እንጠፋለን፡፡ ስለዚህም ትሕትናንና ትዕግሥትን ገንዘብ በማድረግ ወደ እግዚአብሔር በንስሓ በመመለስ በሃይማኖት ጸንቶ መኖር አስፈላጊ ነው፡፡

በጾም እና በጸሎት

በጾምና በጸሎት ያልታገዘ ክርስትና ሕይወት እንደባዶ ዕቃ ነው፡፡ ምክንያቱም አምላካችንን እግዚአብሔርን የምንገናኝበትም ሆነ በጸሎት ምሕረትን የምንለው በጸሎት በታገዘ ጾም ነው፡፡ ጌታችን “አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” በማለት አስተምሮናል፡፡ (ማቴ.፳፩፥፳፫) በጸሎት አምነን ስንኖር የጎደለውን ይሞላልናል፤ ከጠፋንበት ይመልሰናል፤ አገልግሎታችን የፍቅር አገልግሎት ይሆናል፡፡

በጸሎት የታገዘ ጾም ደግሞ ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ ማንኛውንም ችግርና መከራ አልፈን በሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር ይረዳናልና፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ለዚህ ተግባር ይረዳን ዘንድ አጽዋማትን በወቆቶች ከፍላ ታስተምረናለች፡፡ እነዚህም ሰባት የዐዋጅ አጽዋማት ሲሆኑ ሁለት ደግሞ የፈቃድ ጾሞች አሉን፡፡ እነዚህን ወቅቶች ጠብቀን፣ አምላካችን እግዚአብሔርን እያመሰገንን፣ በሕጉና በሥርዓቱ መኖር ያስፈልገናል፡፡ ለዚህም ሁል ጊዜ ተዘጋጅቶ መኖር ያሻል!

አምላካችን እግዚአብሔር ተዘጋጅተን እንድንኖር፣ መንግሥቱንም እንድንወርስ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን!