ገብርሔር

በዲ/ን አባተ አስፋ
ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርሔር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርሔር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መሀከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቅሉ ቤተክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ አሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡

በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሔዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡

ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው «እንዲያተርፉበት» ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ሓላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡

ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት ሁለት አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡

ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ቀጥለን እንደምናነበው ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሠርተው የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን አደረክባት ተብሎ ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረ በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው አናነባለን፡፡

በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡

1. የአገልጋዮቹ ጌታ፡-

ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እናያለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ /ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ አውጡት/ ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ታላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

2. በጎ አገልጋዮች:-

በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡

3. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ:-

ይህ ሰው የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡

ሀ. የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሔድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተነገጋገርነው እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትዕዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡

ለ. ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፡- ከሔደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ ስለፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፡፡» ሲል መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ውሸት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡

ሐ. እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፡- ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትዕዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡

የመጽሐፈ ቅዱስ መተርጉማን አባቶች የዚህን ምሳሌያዊ ታሪክ ምስጢር ሲያስተምሩ የአገልጋዮቹ ጌታ የፍጡራን ጌታ የሆነ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደሆነ እንዲሁም ሦስቱ አገልጋዮች በተለያየ ደረጃ ያሉ ምዕመናንን እንደሚወክሉ ያስተምራሉ፡፡

ከዚህ የወንጌል ክፍል ምን እንማራለን?

ከተጠቀሰው ታሪክ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም አበይት የሆኑትን ሁለቱን እንመልከታቸው፡፡

1. ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ እንዳለ እንረዳበታለን

እግዚአብሔር እያንዳንዳችን በሃይማኖት ሆነን የምናፈራውን ፍሬ ይፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ከእኛ ፍሬን ቢፈልግም ያን ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይል ግን የእግዚአብሔርን ልጅነት ካገኘንበት ከዕለተ ጥምቀት ጀምሮ እንደሚያስፈልገን መጠን እየሰጠን ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቁጥር እጅግ ብዙ ቢሆኑም በአይነታቸው ግን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምስጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው ፡፡ዮሐ.3-3 ሁለተኛው አይነት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ ሰውየው አቅም ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር ፣ በተለያዩ ልሳናት መናገር ፣ አጋንንትን ማስወጣት … የመሳሰሉት ከዚህኛው አይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ 1ኛ ቆሮ.12-4፡፡

በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው አይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ40 ና 80 ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውሃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው ፡፡ ዮሐ.19-24፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡›› 1ኛ ዮሐ.3-1 ያለው፡፡

እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡›› ገላ.4-7 ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡

ትልቁ ችግር ግን ተጠማቂው ሰው ይህን የልጅነት ክብር አለመረዳቱ ነው፡፡ የልጅነቴን ክብር ተረድቻለሁ እያለ የሚያወራውም ቢሆን የልጅነቱን መክሊት በልቡናው ውስጥ ቀብሮ አንድም ፍሬ ሳያፈራ ስለማንነቱ ለማውራት ቃላት ሲመርጥ ጊዜውን ያባክናል፡፡ አብዛኛው ግን የክርስትና እምነት ደጋፊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊገለጥ የሚገባው እንደ ሀገር ልጅነታችን በምናሳየው የደጋፊነት /የቲፎዞነት/ ስሜት አይደለም፡፡ ደጋፊነት በጊዜ ና በቦታ ለተወሰነ ያውም ኃላፊ ለሆነ ድርጊት ነው፡፡ ክርስትና ግን በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ የሚኖርበት የህይወት መስመር እንጂ የሚደገፍ ጊዜያዊ ድርጊት አይደለም፡፡

ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡በዚህም መክሊት እንድንሰራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡

2. እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንረዳለን

እግዚአብሔር ያለ አንድ አላማ ለሰዎች ኃላፊነትን የሚያሰከትል ስጦታ አልሰጠም አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለሆነ አላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

መንጋውን እንዲጠብቁለት ሥልጣንና የተለያዩ የአገልግሎት ሰጦታዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸው አሉ፡፡ዮሐ. 21-15 ፤ ገላ.1-15-16፡፡ ሆኖም ግን የተሰጣቸው ኃላፊነት የሚያስጨንቃቸው፣ ከልባቸው በእውነተኛ ትህትና የሚተጉ ያሉትን ያህል የሚያገለግሉበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር መቀበላቸውን እንዲሁም የሚያስጠይቃቸው መሆኑን እስኪዘነጉ ድረስ መንገዳቸውን የሳቱ አሉ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰዎች መሀከል እንደ ድልድይ ሆነው ያገለግሉበት ዘንድ በተሰጣቸው ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

እንዲሁም ደግሞ ተሰባኪውን ወደ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ የነሱ ደጋፊ፣ ስለክብራቸው ተሟጋች እንዲሆን በህዝቡ መሀከል ጎራ እንዲፈጥርና የጳውሎስ ነኝ የአጵሎስ ነኝ እንዲል የሚያደርጉት ሰባኪዎችም ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ማንም ይሁን ማን ግን ስለተሰጠው መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ እንደሚጠይቀው መዘንጋት የለበትም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

«ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ ( የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ናት)»፡፡

የንግግርና ሥነ ጽሕፈት ሙያን የተካኑ ምሁራን በትምህርት ጌጣቸው እንደሚሉት «ውሃን ከጥሩው ሲቀዱት፣ ነገርን ከሥሩ ሲያመጡት» ውሃው ጠጭውን፣ ነገሩም ሰሚውን ያረካዋል፡፡ በዚህ እውነተኛ ሃይማኖትን ከጊዜው ስመ መሳይ ኑፋቄና የለየለት ክሕደት ለይቶ በሚያሳይ ትምህርታችን «አበዊነ = አባቶቻችን» ያልናቸው እነማን እንደሆኑ በጥቅል ማመልከት እንወዳለን፡፡ የቃሉን ዐይነ ምስጢር ቁልጭ አድርጎ ለመግለጽ ያህል አባትነት መልክና ይዘቱ፣ ግብርና ዐይነቱ በጣሙን ብዙ ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ «የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖት» ባለቤቶች ብለን በትምህርታችን ርእስ በመሪነት ያነሣናቸው፡፡

– ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ በደብር ቅዱስ የነበሩ አርእስተ አበውን፣
– ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የነበሩትን የእግዚአብሔር ሰዎች፣
– አዕይንተ አርጋብ ዐበይት ደቂቅ ነቢያትን፣

ይልቁንም «አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው = አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ» ከማለታቸው አስከትለው «እግዚኦ ኀበ መኑ ነሐውር እንዘ ቃለ ሕይወት ዘለዓለም ብከ፣ ወንሕነሰ አመነ፣ ወአእመርነ፣ ከመ አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልዱ ለእግዚአብሔር ሕያው = አቤቱ! የዘለዓለም ደኅንነት የሚገኝበት ትምህርት ከአንተ ዘንድ እያለ ወደማን እንሔዳለን? እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጁ ክርስቶስ እንደሆንህ ዐውቀን አምነናል» ማቴ.16-16፣ ዮሐ. 6-68-70 ብለው መስክረው ሲያበቁ ሃይማኖትን አብርተው ያረጋገጡ፣ ሁለንተናቸው በደመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርሰቶስ ተኮልቶ የበራ፣ የጠራ ጽሩያነ አዕንይት የትምህርት፣ የሃይማኖት፣ የክህነት አባቶቻችን የሆኑ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የተሟሟቁ ቅዱሳን ሐዋርያትን ነው፡፡

ደግሞም የእነርሱን ዓላማና ግብር የተከተሉ ሰብአ አርድዕትና ምሉአነ አእምሮ ሠለስቱ ምእት ሊቃውንትን፣ ተጋዳልያን ሰማዕታትና ጻድቃን፣ ቅዱሳን ማለታችን ነው፣ እንጂ የመጀመሪያው የወንድሙ ነፍሰ ገዳይ የቃኤል ልጆችን ሁሉ አደባልቀን፣ ነገርን ከነገር አጣልፈን፤ ምስጢሩንም ደብቀን፣ ከሐድያን፣ ጣዖት አምላኪዎች መስሕታንን ቀደምት አበው ከሆኑ ብለን ሳናስተውል በጅምላው አይደልም፡፡ ስለይህ የእነዚህን ቅዱሳን = የተለዩ አበው የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖት የሆነችው «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች የጸናች ናት፡፡» በዚች መሠረትነት ለሁለት ሺኽ ዘመናት እምነቷ፣ ሥርዐቷ፣ ባህሏ ተጠብቆ ለሕዝበ ክርስቲያን የሚገባውን መንፈሳዊና ሐዋርያዊ፣ ማኅበራዊም አገልግሎት ስታቀርብ የኖረች ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ብሔራዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የገጠሙአትን ችግሮች፣ ፈተናዎች በታላቅ ትዕግሥት፣ በጾምና በጸሎት፤ በመንፈሳዊ ጥበብ የማለፍ ልምድና ዕውቀቷ በዓለም የተመሰከረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአለንበት ጊዜ እምነቷን፣ ሕጓንና ሥርዐቷን ለማፋለስ በግልና በቡድን የተነሣሡ የእምነት ተቀናቃኞች በየአቅጣጫው በመዝመት ላይ መሆናቸው ለሕዝበ ክርስቲያን ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤ አሁንም የበለጠ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የመናፍቃንና የሃይማኖት ለዋጮች እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያልተለመደና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ቀድሞ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ምክንያቱም አዝማቹ ጠላት በሞተ ሥጋ የማያርፍ ዲያብሎስ እንደሆነ በብሩህ ልቡና ይታወቃል፡፡ በመልካም እርሻ /ማሳ/ የተዘራው ንጹሕ ስንዴና ጠላት ጨለማ ለብሶ በስንዴው ማሳ ላይ የበተነው እንክርዳድ እስከ መኸር ጊዜ ዐብረው እንደሚኖሩ ጌታችን ራሱ ባለቤቱ በቅዱስ ወንጌል አስተምሮናል ማቴ. 13-24 – 31 ይህ የማይሻር ቃል ስለሆነ ሌላ ምን ይባላል? ዐይነ ኅሊናችንን ወደ ቀደመው ታሪክ ስናቀና በአበው ሐዋርያት ዘመንም በመልካም እርሻ ላይ በብርሃን የተዘራውን ጥሩ ዘር፣ ለማበላሸት የጥፋት ዘር በጨለማ የሚበትኑ ቢጽ ሐሳውያንና መናፍቃን ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩና ሲያምሱ ኖረዋል፡፡

በቀና ሃይማኖት ስምና ጥላ ተሸፍነው ትክክለኛውን እምነትና መሠረት ለማፋለስ ከማሴርም ዐልፈው ራሳቸውን በአማልክት ደረጃ በማስቀመጥ ሰዎችን ወደ ጥፋት በሚያደርስ መንገድ ለመምራት የቃጣቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ሁሉም እንደገለባ እሳት ብልጭ እያሉ ጠፍተዋል፡፡ በዓለም ላይ የበተኑት የጥፋት ዘር ግን ክሕደት የሚያብብበት ካፊያ ባካፋ ቁጥር በምንጭ ላይ እንደወደቀ ዘር በፍጥነት ይበቅላል፡፡ የእውነት ፀሐይ ስትወጣ ደግሞ መልሶ ይጠወልጋል፡፡ እንደነ ይሁዳ ዘገሊላ፣ እንደነ ቴዎዳስ ዘግብጽ የመሳሰሉት ከብዙዎች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ «ቴዎዳስ ዘግብጽ» አምላክ ነኝ ብሎ ተነሥቶ እሰከ አራት መቶ የሚደርሱ ተከታዮች አፍርቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ አልተጓዙም እርሱም፣ ተከታዮችም ፀሐየ ጽድቅ ሲወጣ እንደሚጠወልገው ሣር ፈጥነው ጠፍተዋል፡፡ ይሁዳ ዘገሊላም እንደዚሁ ነው፡፡ አልቆየም፤ ጠፍቷል፡፡ /ግ.ሐ. 5-37/

ጥንታዊት ሐዋርያዊት ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ለመበታተን የሚጥሩት ሁሉ መሠረቷ በክርስቶስ ደም የጸናውንና በቅዱሳን አባቶቻችን ዐፅም የታጠረችውን ቤተ ክርስቲያን ሲገፏትና ሲነቀንቋት ፈተናውን በትዕግሥት በማስተዋልና በትምህርት በመከላከል ትቋቋመዋለች፡፡ ይህ የብዙ ዘመን ልማዷ ነው፡፡ መቼውንም ቢሆን ግራ አያጋባትም፡፡

አባቶቻችን ያቆዩን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጥንታዊት የቀናች፣ የጠራች፣ ስለሆነች ተካታዮቿን የምታኮራ እንጂ የምታሳፍር አይደለችም፡፡… በሰዎች የግል ድካም እንጻርም አትመዘንም፡፡ ለመከራም አትበገርም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዛሬ ድረስ በእምነቷ፣ በጾሟና በጸሎቷ የማያቋርጥ የገቢረ ተአምራት ወመንክራት፣ ኀይላትም ሥራ ስትሠራ የምትገኝ ለተከታዮቿ ተስፋ ሆና የምትኖር እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ርግጥ ነው፤ በቅን ልቡናና በትሑት ሰብእና ለተቀበለው ሸክሟ ቀላል ቀንበሯ ልዝብ ነው፡፡ ዳሩ ግን በገድል የተቀመመ ሕጓ፣ ባህሏና ሥርዐቷ ጥብቅ ስለሆነ የሕግና የሥርዐት ቀንበር ላለመደ ስስ ጫንቃ አይመችም፡፡ መንገዱ ቀጭን፣ በሯ ጠባብ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም መንግሥት የምትወርሰው በመከራ መስቀልና ብዙ ትዕግሥት፣ በዚሁ ቀጭን መንገድ ተጉዞና በጠባቡ በር ዐልፎ ስለሆነ በቀና ሃይማኖት ጸንቶ፣ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሕይወቱን = አኗኗሩን በሥነ ምግባር፣ ገዝቶ በአበው፣ መንፈሳዊ መንገድ መጓዝ ለክርስቲያን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ. 7-13-05 የሐዋ.14-22 ይህ ጠባብ በርና ቀጭን መንገድ የሃሪካችን መዛባት የለበትም፡፡ ተቆርቋሪዎች እንሁን፡፡ የወይራ ዛፍ ተቀጥላው ብሳና ቢሆን እጅግ ያሳፍራልና፡፡ በነገረ ጠቢባን «ሳይረቱ አይበረቱ» ተብሏልና፡፡

ለመሆኑስ አባቶቻችን ታቦት ተሸክመው እየዘመቱ ከጾም ጸሎታቸው ጋር በተጋድሎ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው በአቆዩአት ኢትዮጵያ ሀገራችን ነጻነታችንን ማን ይነካብናል ብለን እንሰጋለን? ሕግ አክባሪነትና ወሰን የሌለው ትዕግሥታችን ካልሆነ በስተቀር ለመሥዋትነቱ ከቶ የእነማን ልጆች እንደሆን ሊዘነጋ አይገባምና በአካልም በመንፈስም ስለ ሃይማኖታችን እንበርታ፡፡ የእውነተኛ ሃይማኖት ዐላማው፣ ውጤቱ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ትንሽም አለመፍራት መሆኑን ማስታወስ አለብን፡፡ ት.ዳ.3-13-ፍጻ፡፡ አሁንም እንደ ቀድሞው መንፈሰ ኀይልን ታጥቀን እንነሣ፤ አምላካችን እንደ አባቶቻችን የኀይልና የጥበብ መንፈስን እንጂ የፍርሀትና የመደንገጥ ሀብትን አልሰጠንምና በሃይማኖታችን ማንንም አንፍራ፤ አንሸበር፡፡ የዜግነት ግዴታችንን እየተወጣን መብታችንን ጠብቀን ለማስጠበቅ እንታገል፡፡ 2ጢሞ.1-7፡፡

በሰፊዋ ሀገራችን እንኳን ተወልደው ያሉ ዜጎቿ ቀርቶ ከተለያዩ ሀገሮች የሚመጡ ባዕዳን ሁሉ በተለያየ እምነታቸው ተከራይተውና ተጎራብተው እንዲኖሩ ቤተ ክርስቲያናችን አልተቃወመችም፡፡ ከማንኛውም የእምነት መሳይ ተቋም ደልላ የእንጀራ ልጆች ለማፍራትም አትፈልግም፡፡ ከጅሏትም አያውቅ፡፡ ይህን የሚያደርጉ ግን ሌሎች ናቸው፤ እዚህ ላይ ስማቸው ባይጠራም በዚሁ የሃይማኖት መሳይ ኑፋቄ የደላላነት ግብራቸው ይታወቃሉ፡፡ ማቴ. 7-15

«የሁሉ ሰው መብትና ነጻነት ሰብአዊ ፍላጎትም ተጠብቆ በእኩልነት እንኑር» የሚለውን የአስተዳደር መርሕ እንቀበላለን፡፡ አምላካዊ ሕግም ነው፡፡ በሃይማኖት ከማይመስሉን ጋር ግን በእምነት ጉዳይ መቼም ቢሆን አንድነት የለንም አይስማማንም፡፡ ከይዞታችንና መብታችን ሌሎች እንዲገቡብንም አንፈልግም፡፡ እኛም ከነሱ የምንሻው ምንም ነገር የለም፡፡ አይጠቅመንምና፡፡ ይህ ምርጫችን ነው፡፡ ግድ የሚለን የለም፡፡ «ሲኖሩ ልጥቅ፣ ሲሔዱ ምንጥቅ» የሚለው የአበው ምሳሌያዊ ቃለ ኀይል ሥጋችንን ዐልፎ ዐጥንታችንን በማስተዋል አለምልሞታልና፡፡ ይልቁንም «ብርሃንን ከጨለማ ጋር የሚቀላቅለው ማነው?» የሚለው ቃለ ቅዱስ መጽሐፍ ጠፈር፣ ደፈር ሆኖ ይከለክለናል፡፡ክርስትናችንን ይበርዝብናል ክልክል ነው፡፡ 2ኛቆሮ.6-14-ፍጻ፡፡ ይህን በጥሞና እንገንዘበው፡፡ እኛ ሃይማኖት መጽደቂያ፣ ምግባረ ሃይማኖት ማጽደቂያ እንጂ የሥጋ መተዳደሪያ እንዳልሆነ በውል ስለምናውቅ የሃይማኖትን ጉዳይ ከማናቸውም ሥጋዊና ጊዜያዊ ደስታ ጥቅም ጋር አናያይዘውም፡፡. . . ለዚህም ብለን ሃይማኖትና ሥርዐታችንን አንሸጥም፤ አንለዋውጥም፡፡ ይህ የቅዱሳን አበው ትውፊታችን ነው፡፡ ከደማችን የተዋሐደ ክርስቲያናዊ ጠባያችንም ይኸው ነው፡፡ ሮሜ12-18 ነገር ግን ይህ አቋምና ጠባያችን ከሞኝነት ተቆጥሮ ያላችሁን ሁሉ እንቀማችሁ እንቀስጣችሁ የሚሉንን አምረን እንቃወማለን፡፡ ይገባናልም፡፡ ብዙዎች የእምነት ተቋሞች ሳይሆኑ ነን ባዮች የታሪክና የሃይማኖት መሠረታቸውን እየለቀቁ፣ የነበራቸውን ትውፊት በቁሳቁስና በኃላፊ ጥቅም እየለወጡ ባዶ እጃቸውን ስለቀሩ እኛ ከቅዱሳን አበው ወርሰን ጠብቀንና አጥብቀን የያዝነውን ነፍስ እንዳላወቀ ሕፃን «ካክሽ» እያሉ በማስጣል እኛነታችንን ሊአስረሱን ይፈልጋሉ፤ አልፈው ተርፈውም ወቅትንና አጋጣሚን ዐይነተኛ ተገን /መሣሪያ/ በማድረግ፣ ነገሮችንም ከፖለቲካና ከግዚያዊ ችግር ጋር በማስተሳሰር የሕዝብን አስተያየት ለማዘናጋትና የመብታችን ተካፋዮች ለመሆን መስለው ይቀርባሉ፡፡ ከሃይማኖት መሳይ ቤተሰባቸው ለጊዜያዊ ችግር የሚገኘውን ጥቂት ርዳታ የሃይማኖት፣ የታሪክና የቅርስ መለወጫ ሊአደርጉትም በእጅጉ ይሻሉ፡፡

እውነተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን «ኩራት እራቱ» ስለሆነ እንደኤሳው ብኩርናውን በጊዜያዊ ጥቅም /ነገር/ አይለውጥም፡፡ «ነብር ዥንጉርጉርነቱን» እንደማይለውጥ የኢትዮጵያ ሕዝብም፣ ለሃይማኖቱ፣ ለክብሩ፣ ለታሪኩና፣ ለነጻነቱ መሞት እንኳ የተለየ መታወቂያው፣ የማይለወጥ ጠባዩ ነው፡፡ ኤር. 13-23፡፡

በዐያሌው ከልብ የተወደዳችሁ፣ እውነቱ ያልተሰወራችሁ የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆይ!

የእምነታችሁና ሥርዐታችሁ ጠባቂዎች፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሕይወቷ ደስታዋና ክብሯ ተከታዮቿ እናንት ምእመናን ስለሆናችሁ ልጆቻችሁና ወዳጆቻችሁ በዐዲስ የሃይማኖት ትምህርት መሰል ክሕደት እንዳይወስዱ ጊዜና ቦታ በማይገድባቸው ወደ ጥፋት በሚወስዱ ሰፋፊ መንገዶች ከሚመሩ አዘናጊዎች መናፍቃንና ቢጽ ሐሳውያን መምህራን እንድትጠበቁ፣ «ዐደራ»! ትላችኋለች እናታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡፡ ደግሞም በቅዱሳን አበው ሃይማኖታችሁ እንድትጸኑ ታሪካችሁን፣ ሀገራችሁን ባህላቸሁን፣ ፍቅራችሁን፣ አንድነታችሁን ጠብቃችሁ በጥንቃቄና በሥርዐት እንድትኖሩ፣ እኛም እጅግ ጥብቅ የሆነ መንፈሳዊ ፍቅር የተመላ መልእክታችንን በእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕያው ስም ከቅን ልቡና በመነጨ ሐሳብ አናስተላልፋልን፡፡ 1ቆሮ.14-15

መድኀኒታችን እንዳስጠነቀቀው ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፤ የዘመኑን ምትሐታዊ ሒደትና ይዘት ዕወቁ፤ በመንፈሳዊ ሕይወት ጽኑ፡፡ በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ከዓለም ኅብረተሰብ የምናገኘው ጊዜያዊ ርዳታ በሰብአዊና ማኅበራዊ ግዴታ ላይ የተመሠረተ እንጂ የሃይማኖትና የታሪክ ለውጥ መዋዋያ አይደለም፡፡ የመልካም ጠባይና ማንነት መለወጫም አይደለም፡፡ ድኽነትን ከየቤታችን ለማጥፋት ሥራን እንውደድ፡፡ እርስ በርስ እንረዳዳ፡፡ ችግረኛውን ተባብረን ነፃ እናውጣው፡፡ እንደቀሞው ባህላችን ያለንን ተካፍለን ዐብረን እንብላ እንጂ መነፋፈግን አንልመድ፡፡ በዚህ ጊዜ የበረከት አምላክ ረድኤት በረከቱን ይሰጠናል፡፡ ወገንና መጠናችንንም ለይተን ዕንወቅ እንጂ የቅዱሳን አበው ልጆች እዚህ ላይ አትኩረን ልብ እንበል፡፡ በምንም ሰበብ እንደ ገደል ውሃ ክንብል አንበል፡፡ ይህን ከመሰለው ደካማ ሐሳብም ልጆቻችሁን በብዙ ዘዴ ጠብቁ፡፡ የሃይማኖት ፍቅር ቁም ነገሩም ከቤተሰብ በላይ ስለሆነም ይህን አትርሱ፡፡ ምንም ቢሆን ክፉን ማስወጣት ያቃተው ስንኳ ቢኖር መውጣት አያቅተውም፡፡ ማቴ. 10-36-40

በቤተሰብ አባላት በወዳጅ ዘመድና በጎረቤት መስለው የሚመጡ የበግ ለምድ ለባሾችን ዕወቁባቸው፡፡ ፊልጵ. 3-2 ዋናው ዘዴ ከእነርሱ ጋር ዐብሮ አለመራመድ፣ ዐብሮ አለመገኘት ነው፡፡ ከደጃቸውም አለመቆም ነው፡፡ የእነርሱ የሆነንም ሁሉ አለመከጀል፣ ፈጽሞ አለመንካት ነው፡፡ የጠላት ገንዘብ ምግብ፣ ልብስና ቁሳቁስ በሙሉ የተወገዘ፣ እርኩስ ነው፡፡ ሕርም ነው፣ መርዝ ነው፡፡ ደዌ ክሕደትን ያመጣል እንጂ ጤና ሕይወት አይሆንም፡፡ እንወቅ፡፡ በሌላ በኩል በእውነቱ ከሆነ አንድ ልጅ እናቱ መልካም ፍትፍት ምግብ አዘገጅታ ባትሰጠው እንኳ ከጎረቤት ሔዶ በመርዝ የተቀመመ ምግብ መብላትና መታመም፣ ዐልፎም መሞት የለበትም፡፡ እንደዚሁም ታዲያ በሥራዋና በመልካም አቋሟ ሁሉ እንደ መማር፣ ባይሆንም እንደ መጠየቅ «እናቴ ቤተ ክርስቲያን ጮኻ ባታስተምረኝ ነው» እያሉ ከክሕደትና ኑፋቄ ማኅበር እንደ እሳት ራት ዘሎ መግባት አግባብ አይደለም፤ የሰውነት መመዘኛም አይሆንም፡፡ እንግዲያውስ ተጠበቁ፡፡ ተጠንቀቁ፤ ሌላ የሚያዋጣ ነገር ፊጽሞ አይገኝም፤ ዐጉል መዋተት ብቻ ይሆናል፡፡ በዚህ ዐዲስ ዘመን ዐዳዲስ የሃይማኖት መሳይ ድርጅት የቀናች አንዲት እውነተኛ የአበው ሃይማኖትን ሊተካት ቀርቶ ሊመስላት አይችልም፡፡ ይህን የመሰለው ሐሳብ የዘባቾች ከንቱ ዘበት ነው፡፡

ሰው ሆኖ በተዋሕዶ ተገልጾ በባሕርይ ክብሩ ያለ መድኀኒታችን የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከባለቤቱ እንደባዘነ የቤት እንስሳ በዚህ ዘመን በየሜዳውና በየግል አጋጣሚ «አገኘሁት» አይባልም፡፡ ድፍን ያለ ሐሰት ነው፡፡ እናስተውል፡፡ ወይም እራሳቸውን እንኳ በማያውቁ ልሙጥ ማይማን ዘባቾች «ተቀበሉት» የሚባልለት ቁስ አካል፣ አልያም ማደሪያ የሌለው ባይተዋር አይደለም፡፡ ዓለምን በእጁ የያዘ እርሱ በእኛ የሚወሰን ይመስል የተለያየ ችግር ባለባቸው፣ ተግባር ሥጋዊን በጠሉ፣ የዕለት ምግብ ፈላጊዎች ልንጎተትና በእነርሱ ዐቅም ተታለን በየዛኒጋባው ልንመሰግ የሚገባን ሰብአዊ ግብር አይደለንም፡፡ አሁንም በሃይማኖት ቁሙ፣ ጠንክሩ፣ ንቁም በተማራችሁትና በያዛችሁት እውነተኛ ሃይማኖታችሁ ጽኑ፡፡ ባይረዳችሁ እንኳ ከእናታችሁ ቅድስት ቤተክርስቲያን ተግታችሁ ተማሩ፤ ጠይቁ፡፡ «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች፣ የጸናች እውነተኛም ናት» አማራጭ ተለዋጭ ፈጽሞ የላትም፤ ዘለዓለማዊት ናት፡፡ በባዕድ ዘመን አመጣሽ ትምህርት እንዳትወሰዱ አሁንም፣ ምን ጊዜም ተጠበቁ፤ ዕወቁ፤ ተጠንቀቁ፡፡ በቃለ አበው ሐዋርያት ተገዝታችኋል፡፡ ስለእውነተኛዋ ሃይማኖታችሁ በየትና በማን እንደምትማሩ ለይታችሁ አስተውሉ፡፡ ተረዱም፡፡ በቀናች ሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ በሰላም በብርታት እንድትኖሩም፣ ለጸሎትና ምህላ ትጉ በሥራችሁ ሁሉ እንዳትሰናከሉም፣ እንቅፋታችሁን «ወአምላከ ሰላም ለይቀጥቅጦ ለሰይጣን በታሕተ እገሪክሙ ፍጡነ = የሰላም አምላክ ፈጥሮ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይቀጥቅጠው!!!» ኀያሉ አምላክ ኀይል፣ ከለላ፣ ይሁነን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት፣ ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት ግርማ ሞገስ ይሁነን፡፡ ሮሜ 16-20፣ 1ኛቆሮ.16-13፣ ገላ.1-8፣ ቆላ.2-6-11

ምንጊዜም «ክፉ አይልከፋችሁ፣ ደግ አይለፋችሁ»

 

ከሊቀ ትጉሃን ኀ/ጊዮርጊስ ዳኘ
በጠ/ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ም/ሓላፊ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አምላከ ሰማያት ወምድር

«በህልምም ተረድቶ ወደገሊላ ሀገር ሄደ፤……. ናዝሬት ወደምትባልም ከተማ መጥቶ ኖረ»

ሕዳር 6 ቀን እመቤታችን ጌታን ይዛ ከግብጽ /ከስደት/ ወደ ኢየሩሳሌም መመለሷ ይታሰባል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቀጥሎ ካለው የማቴዎስ ወንጌል ምንባብ በመነሳት ይህንን አስመልክቶ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው ላይ ያስተማረውን ትምህርት እናቀርባለን፡፡
«ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በህልም ታይቶ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሳ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ ዮሴፍም ተነስቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ ፈንታ በይሁዳ መንገሱን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ፤ በህልምም ተረድቶ ወደገሊላ ሀገር ሄደ፤ በነቢያት ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ» /ማቴ. 2-19-23/፡፡

ዮሴፍ የሕፃናቱ ገዳይ መሞቱን ሰምቶ ከስደት ተመልሶ ወደ ሀገሩ ተመልሶ መጣ፡፡ ነገር ግን ገና እግሩ ሀገሩን እንደረገጠ በድጋሚ የቀደመውን አደጋ ቅሪት /ተረፍ/ አገኘ፤ የክፉው ገዢ ልጅ ንጉስ ሆኗል፡፡

ሄሮድስ በንጉስነት የሚመራትን ሀገር /እስራኤልን/ ለሦስት ከፋፍሎ ሦስቱ ልጆቹ በእርሱ ስር ሆነው በሀገረ ገዢነት እንዲመሯት አድርጎ ነበር፡፡ እርሱ ከሞተ በኋላ ቆይተው እነዚህ ልጆቹ መንግስቱን ለሦስት ተካፍለውታል፡፡ የበላይ ንጉስም አልነበረም፡፡ አሁን ግን ሄሮድስ ገና መሞቱ ስለሆነ መንግስቱ ገና አልተከፋፈለምና ልጁ አርኬላዎስ ለጥቂቱ ለጊዜው መንግስቱን ተቀብሎ ንጉስ ሆነ፡፡

ዮሴፍ በአርኬላዎስ ምክንያት ይሁዳ መቀመጥ ከፈራ /ቤተልሔም የምትገኘው በይሁዳ ነው/ በወንድሙ በሄሮድስ አንቲጳስ ምክንያት ናዝሬት መቀመጥን ለምን አልፈራም? /ናዝሬት የምትገኘው የሄሮድስ አርኬላዎስ ወንድም ሄሮድስ በአንቲጳስ በሚገዛት በገሊላ ነው/ ይህ በቂ ምክንያት አይሆንም?

ቦታውን በመቀየር ጉዳዩ እንዲሸፈን፣ እንዲረሳ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥቃቱ / ግድያው/ ሙሉ በሙሉ የተካሄደው «በቤተልሔምና በአውራጃዋ» ነው /ማቴ. 2-6/፡፡ ስለዚህ ግድያው ከተፈፀመ በኋላ ወጣቱ አርኬላዎስ የሚያስበው ሁሉም እንደተፈፀመ እና እርሱም /ጌታም/ ከብዙዎቹ ሕፃናት ጋር አብሮ እንደተገደለ ነው፡፡

ስለዚህ ዮሴፍ ወደ ናዝሬት መጣ፡፡ በአንድ በኩል አደጋውን ለማስቀረት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞ /native/ ቦታው ለመኖር፡፡ ተጨማሪ ድፍረት እንዲሆነውም በጉዳዩ ላይ ከመልአኩ ምክር ተሰጠው፡፡ «በህልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ ሀገር ሄደ»

ታዲያ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ናዝሬት የሄዱት እንዲህ ባለ መልኩ ነው ለምን አላለም? ምክንያቱም ከጌታችን ልደት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄዱ ከነገረን በኋላ እንዲህ ይላል፡፡ «በዚያም በእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ወደ ገሊላ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ » /ሉቃ. 2-39/ ወደ ናዝሬት የሄዱት ከግብጽ ሲመለሱ መሆኑን አይነግረንምን?

ቅዱስ ሉቃስ እየተናገረ ያለው ወደ ግብጽ ከመውረዳቸው በፊት ካለው ጊዜ ነው፡፡ ምንም ነገር ከህጉ ውጭ እንዳይፈጸም ከጌታችን ልደት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ሕጉ የሚያዘውን ሁሉ ፈጽመዋል፡፡

«እንደ ሙሴ ህግ የመንጻታቸው /ማለትም 40 ቀን/ በተፈጸመ ጊዜ በጌታ ሕግ የበኩር ልጅ ወንድ ልጅ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደተጻፈ፣ በጌታ ፊት ሊያቆሙት በጌታም ሕግ ሁለት ዋልያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደተባለ መስዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት» /ሉቃ.2-21-24/ «ሁሉንም እንደህጋቸው ከፈፀሙ በኋላ ወደ ገሊላ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ፡፡ /ሉቃ.1-39/ ጌታ «ኦሪትና ነቢያትን ልፈጽማቸው እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም» /ማቴ.5-17/ እዳለው፡፡ ይህ ከመደረጉ /ሕጉ ከመፈጸሙ/ በፊት ወደ ግብጽ እንዲወርዱ አልሆነም፡፡ ይህ እስኪሆን ተጠበቀ ከዚያ ወደ ናዝሬት ሄዱ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ግብጽ እንዲወርዱ፡፡

ግብጽ ደርሰው ከመጡ በኋላ ግን ቅዱስ ማቴዎስ እንደተናገረ መልአኩ ወደ ናዝሬት እንዲወርዱ ያዘቸዋል፡፡ መጀመሪያ ወደ ናዝሬት የሄዱት ግን ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ሳይሆን ቅዱስ ሉቃስ እንዳለው የመኖሪያ ቦታቸው /ከተማቸው/ ስለነበረ ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ቤተልሔም የሄዱት ለሕዝብ ቆጠራው እንጂ እዚያ ለመቆየት አይደለም፡፡ ስለዚህ ቤተልሔም የሄዱበትን ምክንያት ሲፈጽሙ ወደ ናዝሬት ተመለሱ፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ናዝሬት የሄዱበትን ሌላም ምክንያት ይነግረናል፤ ትንቢት፡፡ «በነቢያት ልጄ ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ» /ማቴ.2-23/

ይህንን የተናገረው የትኛው ነቢይ ነው» አትጓጉ አትጨነቁም፡፡ ምክንያቱም ከትንቢት ጽሑፎች ብዙዎች ጠፍተው ነበርና፡፡ ይህንንም በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ከተመዘገበው ታሪክ ማወቅ እንችላለን፡፡
«የቀረው ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ በአኪያ ትንቢት ስለ ናባጥም ልጆች ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በኢዩኤል ራእይ የተጻፈ አይደለምን?» እነዚህ ሁሉ ተጽፈዋል የተባሉት ትንቢቶች ግን ዛሬ በእኛ ዘንድ አልደረሱም፡፡

ምክንያቱም አይሁድ ስለ መጻሕፍቱ ቸልተኛ ስለነበሩና በተደጋጋሚ ከአምልኮተ እግዚአብሔር ይወጡ ስለነበር አንዳንዶቹ ጠፍተው ነበር፡፡ ሌሎቹንም ራሳቸው አቃጥለዋቸው ቀዳደዋቸው ነበር፡፡ ሁለተኛው መቃጠላቸው እንደተፈፀመ ነቢዩ ኤርምያስ በትንቢት መጽሐፍ ይነግናል፤

«ንጉሱም /ሴዴቅያስም/ ክርታሱን /የነቢዩ የኤርምያስን ትንቢት የያዘ/ያወጣ ዘንድ ይሁዳን ላከ፤ እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ክፍል ወሰደው፡፡ ይሁዳም በንጉሱ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ፊት አነበበው፡፡ ንጉስም በክረምት በሚቀመጥበት ቤት ተቀምጦ ነበር፤ ከፊቱም እሳት ይነድድ ነበር፡፡ ይሁዳም ሦስትና አራት ዐምድ በአነበበ ቁጥር ንጉሱ በብርዕ መቁረጫ ቀደደው፡፡ ክርታሱንም በምድር ውስጥ ባለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወደ አለው እሳት ጣለው፡፡» /ኤር.30-23/

የመጀመሪያውን /መጥፋታቸውን/ በተመለከተ ደግሞ የመጽሐፈ ነገሥት ፀሐፊ የኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ አንድ ቦታ ተቀብሮ ተደብቆ ቆይቶ በችግር መገኘቱን ይነግረናል፡፡ «ታላቁ ካህን ኬልቅያስ ፀሐፊውን ሳፋንን የጠፋውን «የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ» አለው»፡፡ /2ኛ ነገ.12-8/

ምንም ቀኝ ገዥ ባልነበረበት ጊዜ መጽሐፎቻቸው መጠበቅ እንዲህ ከከበዳቸው በግዞት ስር በነበሩባቸው ዘመናትማ የበለጠ ጥፋት ይኖራል፡፡

አንድ ነቢይ ይህንን ትንቢት በእርግጠኝነት እንደተናገረው ለማወቅ ግን ሐዋርያቱ በተለያየ ቦታ እርሱን ናዝራዊ ብለው መጥራታቸው ማስረጃ ነው፡፡

«ጴጥሮስም «ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስተህ ሂድ» አለው» /ሐዋ.3-6/

«እንግዲህ እናንተ ሁላችሁ የእስራኤልም ወገን ሁሉ በናዝሬቱ በኢየሱስ ስም ይህ ሰው እንደዳነና በፊታችሁ በእውነት እንደቆመ እወቁ» /ሐዋ.4-10/

ታዲያ ይህ ስለ ቤተልሔም የተነገረው ትንቢት ላይ ጥላ ማጥላት አይሆንምን? ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም ነቢዩ ሚኪያስ ክርስቶስ /መሲሕ/ ከቤተልሔም እንዲወጣ ተናግሯል፡፡ በፍጹም ምክንያቱም መጀመሪያ ነቢዩ ያለው «በቤተልሔም ይኖራል» ሳይሆን ከቤተልሔም ይወጣል» ነው፡፡
ጌታችን በናዝሬት መኖሩ ናዝራዊም መባሉ የሚያስተምረን ታላቅ ነገር አለ፡፡ ይህች ቦታ /ናዝሬት/ በጣም ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣት ቦታ ነበረች፡፡ ለምሳሌ ናትናኤል «በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ይወጣልን?» ብሎ ጠይቋል /ዮሐ. 1/ እንዲሁም የናዝሬት ከተማ ብቻ ሳትሆን አጠቃላይ የገሊላ አውራጃ የተናቀ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው ፈሪሳውያኑ «ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሳ መርምርና እይ» /ዮሐ. 6-52/ ያሉት፡፡ እርሱ ግን ከእነዚህ ቦታዎች ወጣ መባልን አያፍርበትም ደቀ መዛሙርቱንም የመረጠው ከገሊላ ነው፡፡ ይህም ጽድቅን ገንዘብ ካደረግን /ከሰራን/ አፍአዊ /ውጫዊ/ የሆነ የክብርና የሞገስ ምንጭ እንደማያስፈልገን ለማሳየት ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት ለራሱ ቤት እንኳን እንዲኖረው አልፈለገም፤ «የሰው ልጅ ግን አንገቱን የሚያስገባበት የለውም» ብሏል፤ ሄሮድስም በእርሱ ላይ ሴራ ሲጎነጉንበት ተሰዷል፤ ልደቱ በከብቶች በረት ሲሆን የተኛውም በግርግም ነው፤ እናቱ እንድትሆን የመረጠውም በዚህ ምድር መስፈርት ዝቅ ያለችውን ትንሽ ብላቴና ነው፤ ይህ ሁሉ እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንደ መዋረድ እንዳንቆጥርና እያስተማረንና ራሳችንን ለመልካም ምግባር ብቻ እንድንሰጥ ግድ እያለን ነው፡፡

ስለዚህ በእነዚሁ ሁሉ ነገሮች «እኔ ለዓለሙ ሁሉ ባይተዋር እንድትሆኑ ሳዛችሁ እናንተ በተቃራኒው በሀገራችሁ፤ በወንዛችሁ በዘራችሁ፣ በአባቶቻችሁ የምትኮሩት ለምንድን ነው?» እያለን ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ምንም ምግባር ሳይኖራቸው በአባቶቻቸው ይመኩ የነበሩትን እንዲህ ብሏቸዋል «አብርሃም አባት አለን በማለት የምትድኑ አይምስላችሁ» /ማቴ.3-9/ ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ይላል «ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤላዊ አይደለም፤ ከአብርሃም ዘርም ስለሆኑ ሁሉም ልጆች አይደሉም» /ሮሜ. 8-6-8/

እስኪ ንገሩኝ የሳሙኤል ልጆች እነርሱ የአባታቸውን የመልካም ምግባር ሕይወት ወራሾች ሳይሆኑ፤ በአባታቸው መልካምነት /ታላቅነት/ ምን ተጠቀሙ? የሙሴስ ልጆች የእርሱን ፍጹምነት ሳይደግሙ በእርሱ መልካምነት ብቻ ምን ተጠቀሙ? እነርሱ /የሙሴ ልጆች/ መንግስቱን አልወረሱም፤ ነገር ግን መሪ የነበረው ሙሴ አባታቸው ሁኖ ሳለ መንግስቱ የተላለፈው በምግባሩ የሙሴ ልጅ ለሆነው ለሌላው /ለኢያሱ/ ነው፡፡

ጢሞቲዎስስ የተወለደው ከግሪካዊ አባት መሆኑ /ዕብራዊ አለመሆኑ/ ምን ጎዳው) ወይም የኖህ ልጅ /ከነአን/ ባርያ ሆነ እንጂ በአባቱ መልካም ምግባር ምን ተጠቀመ? ኤሳውስ ቢሆን የያቆብ ልጅ አልነበረምን? አባቱስ በእርሱ ጎን አልነበረምን? አዎ አባቱ እርሱ በረከቱን እንዲቀበል ፈልጎ ነበር፤ እርሱ ለዚህ ብሎ አባቱ ያዘዘውን ሁሉ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ክፉ ስለነበረ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አልጠቀሙትም፤ ቀድሞ የተወለደ  ቢሆንም፤ አባቱም በዚህ ረገድ ያሉትን ነገሮች ለማድረግ ከእርሱ ጋር ቢሆንም ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስላልነበር፣ ሁሉን ነገር አጣ፡፡

ስለ ሰዎች ብቻ ለምን እናገራለሁ አይሁድ የእግዚአብሔር ሕዝቦች /ልጆች/ ነበሩ፤ በዚህ ታላቅ ልደት ግን ምንም አልተጠቀሙም፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ሁኖ ለዚህ የተከበረ ልደት የሚገባ መልካምነት ከሌላው የበለጠ የሚቀጣ ከሆነ ለምን የቅርብ እና የሩቅ አባቶቻችሁን እና አያቶቻችሁን ትቆጥራላችሁ»

ይህ የሚሆነው በብሉይ ኪዳን ብቻ ሳይሆን በሐዲስ ኪዳንም ነው፡፡ ያመኑና የተጠመቁ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፤ ነገር ግን ከእነዚህ መካከል ወደ እግዚአብሔር መንግስት የማይገቡ አሉ፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን እንኳን ያለ ምግባር ብቻውን የማይጠቅም ከሆነ፤ እንዴት ከሰዎች መወለድ ሊጠቅም ሊያኩራራ ይችላል? ስለዚህ ከታላላቅ ሰዎች በመወለድ በሃብት፣ በዘር፣ በሀገር ራሳችንን አናኩራራ፤ ይልቁንም እንዲህ የሚያደርጉትን እንገስጻቸው፡፡ በድሕነትና /ድሀ በመሆንና/ እነዚህን ነገሮች በማጣትም አንዘን፤ እነዚህ ነገሮች በእግዚአብሔር መንግስት አይጠቅሙንምና፤ ይልቁንም የመልካም ምግባር ባለሀብቶች ለመሆን እንጣር፤ . . . .

ምንጭ /Saint Jhon Chrysostome, homily 9 on the Gospel of St. Mathew/

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዘመነ ጽጌ

 
 
ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩና መንበሩ ከዚያም ወደ ሚበልጥ ክብር ለመመለስ የተወለደው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከህፃንንቱ ጀምሮ ስደትን እና መከራን ተቀብሏል፡፡
ጌታ ሲወለድ ሰብአ ሰገል «የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንስግድለት መጥተናል» እያሉ በኮከብ እየተመሩ በመጡ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ የሮማውያን ተወካይ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችን ንግሥና ምድራዊ ንግሥና መስሎት መንግስቴን ሊቀማኝ ነው ብሎ ደነገጠ፡፡ ፊሪሳውያን «መሲህ ተወልዶ ከሮማውያን አገዛዝ ነጻ ያወጣናል፡፡» ብለው ያምኑ እንደነበር ስለሚያውቅም ይህ የተፈጸመ መስሎት ጭንቀቱ በረታ፡፡ የተወለደውን ሕፃንም ለመግደል ተነሳ፡፡
 
ስለዚህም ሰብአ ሰገልን አስጠርቶ «ሂዱ ሕፃኑን ፈልጉ ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔም እንድሰግድለት ወደ እኔ ተመልሳችሁ ያለበትን ንገሩኝ» በማለት በሽንገላ ተናገራቸው፡፡

ጠቢባኑም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውን ቀጥለው ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት ፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡

የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተደብቀው ተመለሱ፡፡

«እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነስ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ » /ማቴ. 2 13  14/

ዮሴፍም ተነሣ፤ በዕድሜዋ በጣም ልጅ የነበረችው እመቤታችን ገና የተወለደውን ሕፃን አቅፋ የምትቀመጥበት አህያም ተዘጋጀ፡፡ ጉዞአቸውን ጀመሩ፡፡ ከእስራኤል ወደ ግብጽ በእግር ለመሔድ የሲናን በረሃ ማለፍ የግድ ነው፡፡ በዚያን ዘመን ከእስራኤል ወደ ግብጽ የሚወስዱ ሦስት የተለያዩ መንገዶች ነበሩ፡፡ በሽፍቶች ላለመጠቃት መንገደኞች በቡድን በቡድን ሆነው በእነዚህ መንገዶች ይሔዱ ነበር፡፡

እነርሱ ግን ንጉሥ ሔሮድስ ተከታትሎ ሊይዛቸው ስለሚችል በእነዚህ መንገዶች መሔድ እንደሌለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ ባልታወቁ መንገዶች መሔድ ነበረባቸው፡፡ ለበርካታ ቀናትና ሳምንታት ሸለቆዎችን በመውረድና ኮረብታዎችን እየወጡ ጉዛአቸውን ቀጠሉ፡፡ ሽማግሌው አናጢ ዮሴፍ ከፊት ሁኖ አህያዋን ባልተስተካከለውና ማለቂያ የሌለው በሚመስለው የበረሃ መንገድ ላይ ይመራ ነበር። ሰሎሜም ስንቃቸውን ይዛ ከኋላ ትከተል ነበር፡፡ በጣም አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ጉዞ ነበር፡፡ ቀን ቀን የሚያቃጥለውን የፀሐይ ሐሩር ሌሊት ሌሊት ደግሞ የበረሀውን ውርጭ /ብርድ/ መታገል ነበረባቸው ምግባቸውንም በተአምራት ያገኙ ነበር፡፡

በመጨረሻም በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተመዘገበው ግንቦት 24 ቀን ግብጽ ደረሱ፡፡ በግብጽም ባሉ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋወሩ፣ ጌታም በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ተአምራትን አደረገ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተቀብለው ሲያስተናግዷቸው ሌሎች ደግሞ አሳደዋቸዋል፤ መከራንም አጽንተውባቸዋል፡፡ በዚሁ ስድታቸው ወቅት ጌታ እና እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያም መጥው ሀገራችንን ባርከዋል።

ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በስደት ከቆዩ በኋላ ሄሮድስ ሞተ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ «የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነስቶ ሕጻኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ሀገር ገባ» ማቴ 2-19-21/

ቅዱስ ዮሴፍ ይህንን «.. ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ..» የሚለውን የመልአኩን ቃል የሰማው ቁስቋም በምትባል በግብጽ ባለች ቦታ ነው፡፡

በኋላ በዚህች ቦታ ላይ የእመቤታችን ቤተክርስቲያን ተሰርቶ ቅዳሴ ቤቱ ኅዳር 6 ቀን  ከብሯል። ሃያ ሦስተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቴዎፈሎስ /384-412 ዓ.ም/ ደግሞ በጌታ እና በእመቤታችን ስደት ወቅት የሆነውን ነገር እንዲገለጥለት ለብዙ ጊዜ ጸሎት ካደረገ በኋላ ህዳር 6 ቀን እመቤታችን ተገልጣለት በጉዞው ወቅት የሆነውን ነገር ሁሉ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ ኅዳር 6 ቀን በሁሉም ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የእመቤታችን ከስደት የመመለሷ ነገር የሚታሰብበት ሁኗል፡፡

በሀገራችን መስከረም 25 ቀን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀምራል፡፡ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን ዘመነ ጽጌ ማለት የአበባ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበትና ሜዳዎችንና ተራሮችን የሚያስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ የተባለ ጌታን ያስገኘች እመቤታችን በአበባ ትመሰላለችና ዘመኑ የጌታንና የእመቤታችንን ነገር በአበባና በፍሬ ለመመሰል የተመቸ ነው፡፡

ስለዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከመስከረም 26 ቀን ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ቀን ድረስ የጌታን እና የእመቤታችን ስደት ታስባለች፡፡

በዚህ ዘመን ቅዱስ ያሬድ እና አባ ጽጌ ድንግል ባዘጋጇቸው ድርሰቶች የጌታችን እና የእመቤታችን ስደት በማኅሌት ይታሰባል፤ ምስጋና እና ልመና ይቀርባል። እነዚህን ለየሳምንቱ በሚዘጋጁት ትምህርቶች እናቀርባቸዋለን፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ስደቱን ለማሰብና በረከት ለማገኘት በርካታ ክርስቲያኖች ዘመኑን በጾም ያሳልፉታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው /Homilies on the Gospel of Saint Mathew/ ይህንን ስደት አስመልክቶ ያስተማረውን ትምህርት ከዚህ ቀጥለን አቅርበናል፡፡

ሰብአ ሰገልም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በህልም ለዮሴፍ ተገልጾ፡- ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሳና ሕፃኑን ከእናቱ ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚህ ተቀመጥ አለው እርሱም  ተነስቶ  ሕፃኑና እናቱን ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን  ከግብፅ ጠራሁት የተባለው ይፈጸም ዘንድ ወደ ግብፅ ሄደ። ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።

ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደተሳለቁበት ባወቀ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ /ጌታን ለማስገደል በማሰብ / ጌታ በተወለደባት ከተማ በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ሕጻናትን አስገደለ፡፡ /ማቴ. 1.13-18/

እዚህ ላይ ሕፃኑን በተመለከተና ሰብአ ሰገልን በተመለከተ ልንጠይቃቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምን ሰብአ ሰገልም፣ ሕፃኑም /ጌታም/ በዚያው አልቆዩም? ለምን እነርሱ እንደ ተሳዳጅ /fugitive/ በድብቅ ወደ ፋርስ፣ እርሱም ከእናቱ ጋር ወደ ግብፅ ሄዱ?

ከዚህ ሌላ ምን መደረግ ነበረበት? ጌታ በሄሮድስ እጅ መውደቅና ከዚያ አለመገደል ነበረበት? እንዲህ ቢያደርግም ኖሮ ሥጋን መዋሃዱ ግልጽ አይሆንም ነበር፡፡ የክርስቶስ የማዳን ሥራም አይታመንም ነበር፡፡

ሥጋን መዋሃዱን የሚያሳዩ ይህን የመሳሰሉ በርካታ ነገሮች ተደርገው፣ ሥጋን ለበሰ /ተዋሃደ/ መባሉ ተረት /ውሸት/ ነው የሚሉ ካሉ ሁሉን ነገር እንደ አምላክነቱ ብቻ ቢያደርገውማ ከእነዚህ የሚበልጡ ብዙዎች በተሳሳቱ ነበር፡፡

ሰብአ ሰገልንም በፍጥነት የላካቸው አንደኛ ለፋርስ ሰዎች መምሀራን እንዲሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታን ለማስገደል ላሰበው ሄሮድስ እየሞከረ ያለው የማይቻል ነገርን መሆኑን አስረድቶ የሄሮድስን እብደት ለማቆምና ንዴቱን አስታግሶ ከከንቱ ድካሙ እንዲያርፍ ለማድረግ ነበር፡፡

ምክንያቱም አምላካችን ጠላቶቹን በግልጽ እና በኃይል ማስገዛት ብቻ ሳይሆን በቀላል እና ትንሽ በሚመስሉ ነገሮች ማሳመንም፣ ያውቅበታል፡፡

ለምሳሌ ግብጻውያንን በግልጽ /በኃይል/ ንብረታቸውን ለእስራኤል እንዲያስረክቡ ማድረግ ሲችል እርሱ ግን በጥበብ ያለ ጦርነት ይህንን እንዲያደርጉ አድርጎአቸል፡፡ ይህም አድራጎቱ ከሌሎቹ ተአምራት ባልተናነሰ ሁኔታ በጠላቶቹ ዘንድ የሚፈራ አድርጎታል፡፡

ለምሳሌ ፍልስጤማውያን ታቦተ ጽዮንን ማርከው በመውሰዳቸው በተቀጠቀጡ ጊዜ የሀገራቸውን ጠቢባን ከእግዚአብሔር ጋር ለመዋጋት እንዳይሞክሩ በነገሯቸው ጊዜ ከሌሎች ተአምራት ጋር ይህንን እግዚአብሔር በሥውር የሠራውንም ሥራ አንስተውታል፡፡ በግልጽ ከተደረጉት የተለየ አድርገው አላዩትም፡፡ 1ኛ ሳሙ. 6-6

በዚህ ጊዜም የተደረገው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ደም የጠማውን ነፍሰ ገዳይ ሊያስደንቅ የሚችል ነገር ነበር፡፡ ሄሮድስ ሊያስብ የሚገባው እንዲህ ነበር፡፡ ሰብአ ሰገል እንደካዱት፣ እንደተናቀና መሳቂያ መሳለቂያ እንደሆነ ባወቀ ጊዜ መደንገጥ ትንፋሹ መቆም ነበረበት፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ካላሻሉት /ካላስተካከሉት/ ግን እርሱን ከጥፋቱ ለመመለስ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረገ እግዚአብሔር በእርሱ ጥፋት ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ሄሮድስ ከዚህ በኋላ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ያደረገው የእብደቱ ብዛት እነዚህ ሁሉ እውነተኛ ግልጽ ነገሮች እንዲያሳምኑት ስላላደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ከጥፋቱ መመለስ አልቻለም፡፡ በክፋቱ ስለ ቀጠለበትም ስለ ሞኝነቱ የከፋ ቅጣት ተቀብሏል፡፡

ሕፃኑ ለምን ወደ ግብጽ ሄደ? የመጀመሪያውን ምክንያት ወንጌላዊው ራሱ በግልጽ ይነግረናል፤ «ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ» /ማቴ. 1-15/

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ድርጊት ለዓለም መልካም ተስፋ ተሰብኳል፡፡ በዚያን ጊዜ በዓለም ካለው ቦታ ሁሉ በከፋ ሁኔታ ባቢሎን /ፋርስ/ እና ግብጽ በእምነተ ቢስነት /በአምላክ አልባነት/ ነበልባል ተቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም ከመጀመሪያው ሁለቱንም እንደሚያስተካክል ምልክት ሰጥቶ ሰዎችን ማዳኑ /ስጦታዎቹ/ ለዓለሙ በሙሉ እንደሆኑ አውቀው በተስፋ እንዲጠብቁ አደረጋቸው፡፡ ለዚህም ወደ አንዱ /ባቢሎን፣ ፋርስ/ ሰብአ ሰገልን ላከ፣ ሌላውን /ግብጽን/ ራሱ ከእናቱ ጋር ጎበኘ፡፡

ከዚህም ሌላ በዚህ የምንማረው ሌላ ትምህርት አለ፤ ከፍ ያለ ጽናት ሊኖረን እንደሚገባ፡፡ ይህ ምን ዓይነት ነው? ክፉ ሃሳብ /ተንኮል/ እና ክፉ ድርጊት ገና በመጠቅለያ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በእርሱ ላይ እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ በልደቱ ጊዜ መጀመሪያ ክፉ ነፍሰ ገዳይ፣ ተነሳበት ከዚያም ስደት እና ሀገርን ትቶ መሄድ ተከተለ፡፡ ያለ ምንም ጥፋትና በደል ከቤቷ እንኳን ርቃ ተጉዛ የማታውቀው እናቱ ወደ አረመኔዎች /barbarians/ ሃገር ተሰደደች፡፡ አስጨናቂና አስቸጋሪ የሆነ ረጅም ጉዞ እንድታደርግ ታዘዘች፡፡ ይህንን የሰማ ሰው መንፈሳዊ አገልግሎት ሲፈጽም አስጨናቂ ችግሮችና ህመሞች ቢደርሱበትና ህመሞች ቢያጋጥሙት መሸበር የለበትም፡፡

«የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ስለፈጸምኩ መሸለም መከበርና ታዋቂ መሆን ሲገባኝ ለምን ይህ ሆነ?» ማለትም የለበትም፤ ነገር ግን ሁላችንም ይህንን እንደ ምሳሌ ወስደን ሁሉን ነገር በደስታ መቀበል አለብን፡፡ መንፈሳዊ ነገሮች ባሉበት ሁሉ ተቃዋሚ እንደማይጠፋ እና የመንፈሳዊ ነገሮች ሂደትም ይህ መሆኑንም መረዳት አለብን፡፡

ቢያንስ ይህ ነገር የሆነው በሕፃኑና በእናቱ ብቻ ላይ ሳይሆን በሰብአ ሰገልም ላይ መሆኑን እናስተውል፡፡ እነርሱም እንደ ተሳዳጅ /fugitive/ ሆነው በምስጢር እንዲሸሹ ሆነዋል፡፡

ሌላም አስደናቂ ነገር ተመልከቱ፡፡ የእግዚአብሔር ሐገር፣ የተስፋ ምድር የተባለችው ፍልስጤም በጌታ ላይ የተንኮል መረብ /ሤራ/ ስትዘረጋ የኀጢአትና የጣኦት አምልኮ ሀገር የሆነችው ግብጽ ደግሞ ተቀብላ አዳነችው፡፡

ጌታችን በእግረ ሥጋ በተመላለሰባቸው ዘመናት ያደረጋቸው አብዛኞቹ  ነገሮች ወደፊት ሊመጡ ላላቸው ነገሮች ትንቢት ናቸው፡፡

ዮሴፍ ጌታንና እናቱን ይዞ ወደ ግብጽ እንዲሄድ በመልአክ ታዘዘ፡፡ ግብጽ በሥፋት ጣኦት የሚመለክባት ሀገር ነበረች፡፡ ይህም በኋላ ክርስትና በአምልኮት ባዕድ ወደ ነበሩ ህዝቦች /አሕዛብ/ ዘንድ ለመውሰዷ ትንቢት /ምልክት/ነው፡፡ እመቤታችን ጌታን ይዛ ወደማታውቀው ሀገር ስትሰደድ ቤተልሄም /ይሁዳ/ ሄሮድስ ባስገደላቸው ሕፃናት በሰማዕታት ደም ተጥለቅልቃለች፤ የሄሮድስ ጭፍጨፋና ሕፃናቱን መግደሉ ወደፊት ክርስቲያኖች በአይሁድ እጅ ለሚቀበሉት ሰማዕትነት ምሳሌ ነው፡፡

መልአኩ ተገልጦ የተነጋገረው ከእመቤታችን ጋር ሳይሆን ከዮሴፍ ጋር ነበር፡፡ ምን አለው? «ተነሳ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ..» የእመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ መጽነስ ሲነግረው ያለው «እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ» ነበር፡፡ አሁን ግን እጮኛህን አላለውም «የሕፃኑን እናት» አለው እንጂ፡፡ ምክንያቱም እመቤታችን ጌታችንን ከወለደች እና በጌታ ልደት ጊዜ የሆኑትን ነገሮች /ኮከቡን፣ ሰብአ ሰገልን/ ካየ በኋላ ሁሉን ነገር ተረድቶ ተረጋግጦ ነበር፡፡ በቂ ነገር ዓይቶ፣ ባየው ነገር ተረጋግቶ ነበር፡፡ ስለዚህ መልአኩ አሁን በግልጽ ይናገራል «ልጅህን» ወይም «እጮኛህን» አላለም፡፡ «ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሂድ አለው» እንጂ፡፡ የስደቱንም ምክንያት አብሮ ይነግረዋል፤ «ሄርድስ የሕፃኑን ነፍስ ይፈልጋልና፡፡»

ዮሴፍ ይህንን ሲሰማ ቅር አልተሰኘም፤ «ይህን ነገር ለመረዳት ይከብዳል፤ ሕዝቦቹን ያድናቸዋል አላለከኝም ነበር? አሁን ደግሞ ራሱን እንኳን ማዳን አይችልምን? እኛም ከቤታችን ወጥተን ርቀን ለብዙ ጊዜ መሰደድ አለብን አሁን ያለት ነገሮች ከተሰጠው ተስፋ /ቃል/ ጋር ተቃራኒ ናቸው፡፡» አላለም ጻድቅ እና እውነተኛ አማኝ ነበርና፡፡

ምንም እንኳን መልአኩ መመለሻውን ግልጽ ሳያደርግ እስከምነግርህ ድረስ በዚያው ተቀመጥ ቢለውም ስለሚመለሱበት ጊዜ አልተጨነቀም፤ አልጠየቀምም፡፡ ዮሴፍ ፍርሃትም እንኳን አላሳየም፡፡ ሁሉንም ነገር በደሰታ ተቀበለ እንጂ፡፡

ሰውን ወዳጅ የሆነው እግዚአብሔር መከራንና ደስታን በሰዎች ሕይወት ላይ ያመጣል፡፡ በችግር ወይም በደስታ ብቻ አያኖርም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ችግርን /ሀዘንን/ እና ደስታን /ሃሴትን/ እያፈራረቀ ያመጣል፡፡ አሁንም ያደረገው ይህንኑ ነገር ነው፡፡ ዮሴፍ ድንግልን ጸንሳ ባያት ጊዜ ተጨነቀ፤ ተረበሸ፤ ታወከ፡፡ በዚህ መሃል ግን መልአኩ ተገልጦ ፍርሃቱን አስወገደለት፡፡ ሕፃኑን ተወልዶ ባየ ጊዜም ከፍ ያለ ደስታ ተደሰተ፡፡ ደስታው ብዙም ሳይቆይ አደጋ መጣ፤ በሰብአ ሰገል መምጣት ከተማው ተረበሸ ንጉሡም ከእብደቱና ከክፋቱ የተነሳ የተወለደውን ሕፃን ሊገድል ተነሳ፡፡ ይህ ጭንቀት ደግሞ በደስታ ተተካ ኮከቡና የሰብአ ሰገል ለጌታ መስገድ እጅግ አስደሳች ነበሩ፡፡ ከዚህ ደስታ በኋላም ጭንቀትና ፍርሃት መጣ፡፡ መልአኩ «ንጉሥ ሄሮድስ የሕፃኑን ነፍስ ይፈልጋል፡፡» ብሎ ነገረው፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችን በሕዝብ ፊት ተዓምራት ለማድረግ ጊዜው ገና ነውና መሰደድ አስፈለገው፡፡ ምክንያቱም ገና በልጅነቱ ተአምራትን በአደባባይ /በሕዝብ ፊት/ ቢያደረግ፣ ሥጋን እንደተወሃደ አይታመንም ነበር፡፡

በአንድ ጊዜ ሁሉን ማድረግ ሲችል ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅጸን ያደረው፣ እንደ ሕፃናት ጡትን እየጠባ፣ በጥቂት በጥቂቱ ያደገው፣ ሥራውን እስኪጀምርም ሠላውን ዘመን በዝምታ /በስውር ተዓምራት/ ያሳለፈው፡- የተዋህዶን ነገር እንረዳ ዘንድ ነው፡፡

አይሁድ ትንቢቱን በተመለከተ ጥያቄ ቢያነሱ እና ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባለው ስለ እኛ ነው ቢሉን ይህ የትንቢት አካሄድ /መንገድ/ ነው እንላቸዋለን፡፡ ብዙ ጊዜ ስለተወሰኑ ሰዎች የተናገረው የሚፈጸመው በሌሎች ነው፡፡ ያዕቆብ ሊሞት ሲል ልጆችን ሰብስቦ በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባቸው ሲነገራቸው እንዲህ ብሎ ነበር፡-

ስምኦንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤

ሰይፎቻቸው የአመጽ መሣሪያ ናቸው፡፡

ከምክራቸው ነፍሴ አትግባ፡፡

ከጉባኤያቸውም ጋር ክብሬ አትተባበር

በቁጣቸው ሰውን ገድለዋልና

በገዛ ፈቃዳቸው በሬን አስነክሰዋልና፡፡

በያዕቆብ እከፍላቸዋለሁ፡፡ በእስራኤልም እበትናቸዋለሁ፡፡ ዘፍ. 49-7

ይህ ግን በእነርሱ አልተደረገም በልጆቻቸው እንጂ፡፡ በዘፍ. 9-25 ላይ ተጽፎ እንደሚገኘውም ኖህ እንዲህ ብሎ ነበር፡- «ከነአን ርጉም ይሁን ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን» ይህ የተፈጸመው በከንአን ሳይሆን በእርሱ ዘሮች ነው፡፡

ይህ መቼ እና እንዴት እንደሆነ በመጽሐፈ ኢያሱ እና በመጽሐፈ ዜና መዋዕል፤ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እንዲህም ሆነ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቆላውም በታላቁ ባሕር ዳርና ሊባኖስ ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ ኬጢያዊ፣ አሞራዊም፣ ከነአናዊም፣ ኢያቡሳዊም፣ ይህን በሰሙ ጊዜ ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ ወጡ፡፡

በዚያም ቀን ኢያሱ ለማኅበሩ በመረጠው ሥፍራ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቆራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው፡፡ /ኢያ. 9-1-27/

1ኛ ዜና.8-7 ሰሎሞንም ኬጤያውያንንም፣ አምራውያንንም፣ ፌርዜያውያንንም ኢያቡሳውያንንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ… ገባሮች አድርጎ መለመላቸው፡፡

ይስሐቅ «ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፡፡ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ»፡፡ ብሎ ያዕቆብን የመረቀው ምርቃት የተፈፀመው በእርሱ ሳይሆን በልጆቹ ነው፡፡ ዘፍ. 27-19

ስለዚህ እርሱ ባይወለድ ኖሮ፣ ትንቢቱ ፍጻሜውን አያገኝም ነበር፡፡ ወንጌላዊውም ያለውን አስተውሉ፡- «ይፈፀም ዘንድ፡፡» ይህም እርሱ ባይመጣ አይፈፀምም ነበር ማለት ነው፡፡

በዚህኛውም ጊዜ የተደረገው /የሆነው/ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ነው፡፡ መጀመሪያ ለእስራኤል የተነገረው ነገር በኋላ በጌታ ተፈጽሟል፡፡ ደግሞስ የእግዚአብሔር እውነተኛ ልጅ ሊባል የሚችለው የትኛው ነው? ጥጃን ያመለከና ለቤልሆር ልጆቹን የሰዋ? ወይስ በባሕሪው ልጅ የሆነና የወለደው አባቱ «የምወደው ልጄ» ብሎ የሚያመሰግነው?

ከዚህም ሌላ /ግብጽ መሄዳቸው/ እመቤታችን ከፍ ያለ ክብር ያላት እንደሆነች እንዲታወቅ ተደርጓል፡፡ ህዝቡ የሚመኩበትን ከእግዚአብሔር ያገኙትን ስጦታ እርሷም ለራሷ አግኝታለችና፡፡ ማለትም፣ እነርሱ ከግብጽ በመውጣታቸው /ከስደት በመመለሳቸው/ ይመኩና ይኮሩ ነበር፡፡ ይህንኑ የሚመኩበትን ነገር ለእመቤታችንም ስጣት፡፡

ያዕቆብና ህዝበ እስራኤል ወደ ግብጽ በመሄዳቸውና ከዚያም በመመለሳቸው የእርሱን ግብጽ ሄዶ መመለስ ምሳሌ እየፈጸሙ ነበር፡፡ እነርሱ ግብጽ የሄዱት በረሃብ /በድርቅ/ የመጣ መሞትን ለማምለጥ ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ በተንኮል መሞትን ለማምለጥ ነው፡፡

እነሱ /ህዝበ እስራኤል/ ግብጽ መሄዳቸው ከረሃቡ /ከድርቁ/ ተርፈዋል፡፡ እርሱ ግን እዚያ በመሄዱ በኪዳተ እግሩ /በእግሩ በመርገጥ/ ምድሪቱን ቀድሷታል፡፡

በዚህ ራሱን ዝቅ በማድረጉ መሀልም ግን የአምላክነቱ ማሳያዎች /ምልክቶች/ ተገልጸዋል፡፡ ሰብአ ሰገልና እርሱን ለማምለክ በኮከብ እየተመሩ መጡ፤ አውግስጦስ ቄሳርም የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ በማወጅ ልደቱ ቤተልሔም እንዲሆን አገለገለ፤ በግብጽም በርካታ ተዓምራት ተደርገዋል፡፡

አሁን ወደ ግብጽ ብንሄድ በረሃው ከማንኛውም የአትክልት ስፍራ የተሻለ ሥፍራ ያማረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመላእክት አምሳል ያመሰግኑበታል የሰማእታት ብሔር፣ የደናግል በአት፣ የሰይጣን አገዛዝ ድል የተመታበትና የክርስቶስ መንግስት ደምቆ የሚያበራበት ቦታ ነው፡፡

በትምህርተ ሃይማኖታቸው /doctrine/ ካላቸው ትክክለኛነት በተጨማሪ፣ በህይወታቸውም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያሉ፡፡ ያላቸውን ሁሉ ትተው ራሳቸውን ከዓለም ካገለሉና ለዓለሙ በሙሉ ከተሰቀሉ በኋላ በድጋሚ የተቸገሩትን ይረዱ ዘንድ የጉልበት ሥራ ይሠራሉ፡፡

ስለሚጾሙና ብዙ ጊዜ በተመስጦ ስለሚያሳልፉ፤ ቀናቱን /ጊዜን/ ሥራ በመፍታት /ቦዝነው/ ማሳለፍ ተገቢ ነው ብለው አያስቡም፡፡ ስለዚህም ቀኑን በጸሎት ሌሊቱንም በዝማሬና በትጋት ያሳልፉታል፡፡ ከዚህም የሐዋርያውን አሰር ይከተላሉ፡፡

«ከማንም ብር ወይም ወርቅ አላስፈለገኝም እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲህ እየደከማችሁ ድውያንን ልትረዱና፣ «እርሱ ራሱ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጽዕ ነው» የሚለው የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ አሳየኋችሁ፤» ሐዋ. 10-34 ይህንን የሐዋርያውን ቃል ሲሰሙ በበረሃ ያሉት የግብጽ መነኮሳት እንዲህ ይላሉ፡- «እርሱ /ሐዋርያው/ በእግዚአብሔር ቃል እንዲመግባቸው ብዙዎች እየጠበቁት የእጅ ሥራ ይሠራ ከነበረ፣ መኖሪያችንን በገዳም፣ በዱር፣ በበረሃ ያደረግን፣ የከተማ ጾር /ፈተና/ የቀረልን እኛማ ከጸሎታችንና ከተመስጦአችን የተረፈንን ጊዜ ለተመሳሳይ ሥራ ልናውለው ምን ያህል ይገባናል)!»

እኛም ራሳችንን እንመርምር ሀብታምም ድሃም የሆንን እነዚህ መነኮሳት ከሰውነት /እጅና፣ እግር/ በስተቀር ምንም የሌላቸው ሲሆኑ የተቸገሩትን ለመርዳት እንዲህ ከወጡና ከወረዱ የተረፈንን እንኳን ለእነዚህ ሰዎች /ችግረኞች፣ ድውያን/ የማንሰጥ እኛ ለዚህ አድራጎታችን ምን ምክንያት፣ ምን ማስተባበያ ማቅረብ እንችላለን፡፡

ታላቁን አባት ቅዱስ እንጦንስን እናስታውስ፡፡ ይህ ሰው የተወለደው ፈርኦን በተወለደበት ሀገር ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ምክንያት እነርሱን አልመሰለም፡፡ የነበረው ሰማያዊ ራእይ ስለጠበቀው እግዚአብሔር በሚወደው መልኩ ህይወቱን አሳልፏል፡፡ ከጽድቁ የተነሳ ከእርሱ በኋላ የሚመጡ መነኮሳት ምን ዓይነት እንደሚሆኑ እግዚአብሔር አሳይቶታል፡፡

ጻድቁ እንጦንስን ታሪክ ማንበብና ማድነቅ ብቻ ሳይሆን በሕይወት መተርጎምም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አለመበርታት ቦታን፣ አለመማርን፣ የአባቶችን መርገም… ምክንያት አናድርግ፡፡

ነገሮችን በማስተዋል ስንመለከት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለእኛ መሰናክል መሆን አይችሉም፡፡ አብርሃም ጣኦት አምላኪ አባት ነበረው /ኢያ. 24-2/ ነገር ግን የአባቱን ክፋት አልወረሰም፣ የሕዝቅኤልም አባት አካዝ ኀጢአተኛ ሰው ነበር፡፡ ሕዝቅያስ ግን የእግዚአብሔር ወዳጅ ነበር፡፡

ዮሴፍም በግብጽ ሆኖ ራሱን በትምህርት አስጊጧል፡፡ ሦስቱ ሕፃናትም በባቢሎን ቤተመንግስት ሆነው ታላቅ ራስን መግዛት አሳይተውናል፡፡ ሙሴም በግብጽ ነበር፣ ቅዱስ ጳውሎስም በዓለም ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ያሉበት ቦታና ሁኔታ ከጽድቅ ጉዞአቸው አላደናቀፋቸውም፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

ርእሰ ዓውደ ዓመት ዮሐንስ

ክፍል ሁለት

በዓሉ እንዴት ይከበራል?

በማኅበረ ቅዱሳን ዐቢይ ማዕከል መምህር የሆኑት ሊቀጠበብት ሐረገወይን አገዘ «ቤተ ክርስቲያን በዓሉን በመንፈሳዊና ማኅበራዊ ክንውኖች ታከብረዋለች» በማለት እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡
 

መንፈሳዊ ክንውኖች

የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ጽላት ባለባችው አብያተ ክርስቲያናት ከዋዜማው /ጳጉሜን 5/6/ ከሰዓት/ ጀምሮ በሌሎቹ ደግሞ ከምሽት ጀምሮ ማኅሌት ይቆማል፡፡ በዕለቱ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን እና የአዲስ ዓመትን መግባት በሚያነሱ ያሬዳዊ ዜማዎች ምስጋና ሲቀርብ ያድራል፡፡

በበዓሉ ዕለት ጠዋት /ረቡዕ እና ዓርብ ከሆነ ከሰዓት/ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ካህናትና ምዕመናንም ሥጋ ወደሙ ይቀበላሉ፤ ቤተ ክርስቲያን በዓላትን የምታከብርበት ዋና ምክንያትም ይኸው ነውና፤ ምዕምናን ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት የዕረፍት ቀን ያገኙ ዘንድ፡፡

አይሁድ የዘመን መለወጫ በዓላቸው የሆነውን ሮስ ሆሻና /በዓለ መጥቅዕ/ በሚያከብሩበት ዕለት ሊቀ ካህናቱ የአገልግሎት አልባሳቱን ለብሶ ቆሞ የዓመቱ በዓላት የሚውሉበትን ቀን ያውጅ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ትውፊት በመከተል ከቅዳሴ በኋላ /ቅዳሴው ከሰዓት ከሆነ ከቅዳሴው ቀደም ብሎ ሊሆን ይችላል/፡፡ የባሕረ ሀሳብ አዋቂ የሆኑ አባቶች የዓመቱ ተለዋዋጭ በዓላትና አጽዋማት የሚወሉባቸውን ቀናት በባሕረ ሃሳብ ቀመር እያሰሉ ያውጃሉ፡፡ 

በዚህም መሠረት መስከረም አንድ ቀን 2002 . የሚከተለው ይታወጃል፡፡ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ነው፡፡

 

በዓላት /አጽዋማት

የሚውሉበት ቀን

ጾመ ነነዌ

ጥር 17

ዐቢይ ጾም

የካቲት 1

ደብረ ዘይት

የካቲት 28

ሆሣዕና

መጋቢት 19

ስቅለት

መጋቢት 24

ትንሣኤ

መጋቢት 26

ርክበ ካህናት

ሚያዝያ 20

ዕርገት

ግንቦት 5

ጰራቅሊጦስ

ግንቦት 15

ጾመ ሐዋርያት

ግንቦት 16

ጾመ ድኅነት

ግንቦት 18

 

ከዚህ በኋላ በዓመቱ የሚቀርቡ መስዋዕቶችን ሁሉ ወክለው ስንዴ /መገበሪያ/ ወይን /ዘቢብ/ ዕጣን፤ ጧፍ፣ወዘተ ይቀርቡና ይባረካሉ፡፡ በመጨረሻም ሠርዎተ ሕዝብ ይደረጋል፤ ሕዝቡ ይሰናበታል፡፡

ማኅበራዊ ክንውኖች

«ከዚህ በኋላ ማኅበራዊ ክንውኑ ይቀጥላል» ይላሉ ሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን፡፡ በዓሉን ምክንያት አድርገው ሰዎች ወዳጆቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን እንዲሁም የተቸገሩትና የሚበሉት የሚጠጡት ያጡ ወገኖችን በመጥራት ይጋብዛሉ፡፡ እነርሱም ይጋበዛሉ፡፡

«ይህ በበዓላት ላይ በእምነት ከማይመስሉን ጋር ሳይቀር የሚደረገው መተሳሰብና የፍቅር ግንኙነት ማኅበረሰቡን አንድ አድርጎ ይዞ የኖረ ገመድ ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባል፡፡» ይላሉ ሊቀጠበብት፡፡

ከዚህም በተጨማሪ «በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ፣ የሚበሉትና የሚጠጡት ያጡ ነዲያን ወገኖቻችንን ልናስብና «ብራብ አብልታችሁኛል» የሚለውን አምላካዊ ምሥጋና ለመስማት የሚያበቃ ሥራ ለመሥራት ልንተጋ ይገባናል» በማለት ያሳስባሉ፡፡

የበዓሉ መንፈሳዊ ትርጉም /ፋይዳ

የአዲስ ዓመት በዓል ለእኛ ለመንፈሳዊያን ሁለት ዋና ዋና መንፈሳዊ ትርጉሞች /ፋይዳዎች/ አሉት፡፡

  1. የምስጋና ዕለት ነው

በእርግጥ እግዚአብሔርን ማመስገን የዘወትር ተግባራችን መሆን አለበት፡፡ እርሱ ኅልፈት የሌለበት ዘመናትን ግን የሚያሳልፍና የሚለዋውጥ እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት አሳልፎ ለአዲስ ዓመት ሲያደርሰን ደግሞ ቢያንስ ለሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ልናመሰግነው ይገባል፡፡

. ቅዱስ ዳዊት «ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤ የምህረትህነ ዓመት ትባርካለህ» /መዝ.64.11/ እንዳለው ያለፈውን ዓመት ሙሉ በመግቦቱ ከምንተነፍሰው አየር ጀምሮ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ስላዘጋጀልንና በጠብቆቱም እኛ ከምናውቃቸውና ከማናውቃቸው ነገሮች ጠብቆ ወደ አዲሱ ዓመት ስላደረሰን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡

. ቅዱስ ዳዊት «አንተ ኃጢአትን ብታስብ፤ አቤቱ በፊትህ ማን ይቆማል» እንዳለው እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ቢያስብብን እና እንደ ኃጢአታችን ቢፈርድብን አንዲት ደቂቃ እንኳን መኖር አንችልም ነበር፡፡ እርሱ ግን ኃጢአታችንን እየታገሰ፤ አይቶ እንዳላየ እየሆነ በንስሃ እንድንመለስ ዕድሜ ይጨምርልናል፡፡ ሰዎች ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔደው ጲላጦስ ስለገደላቸውና ደማቸውን በመስዋዕታቸው ጋር ስለቀላቀለው ሰዎች የነገሩት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው «ይህች መከራ ስላገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ይልቅ ተለያይተው ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? አይደለም፡፡ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ፡፡» አላቸውና የሚከተለውን ምሳሌ ነገራቸው፡፡

«አንድ ሰው በታወቀች በወይኑ ቦታ ውስጥ በለስ ነበረችው፤ ፍሬዋን ሊወስድ ወደ እርስዋ ሔዶ አላገኘም፡፡ የወይኑን ጠባቂም፡– «የዚችን በለስ ፍሬ ልወስድ ስመላለስ እነሆ ሦስት ዓመት ሆነኝ አላገኘሁም፤ እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቁረጣት» አለው፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አለው «አቤቱ አፈር ቆፍሬ በሥሯ እስካስታቅፋት ፍግም እስከ አፈስባት ድረስ የዘንድሮን ተዋት፡፡ ምናልባት ለክረምት ታፈራ እንደሆነ ያለዚያ ግን እንቆርጣታለን» /ሉቃ.131-9/

ስለዚህ የዘመን መለወጫን በዓል የምናከብረው እግዚአብሔር በዕድሜያችን ላይ ሌላ ዓመት የጨመረልን በቸርነቱ ኃጢአታችንን ታግሶ የንስሐ ጊዜ ሊሰጠን መሆኑን በማስተዋልና ለዚህም ምስጋና በማቅረብ፤ እንዲሁም ቀጥለን እንደምንመለከተው የተጨመረልንን ዓመት ተጠቅመን ለከርሞ አፍርተን እንድንገኝ ለንስሐ እና ለለውጥ በመነሣት መሆን አለበት፡፡

2. ንስሐ እና ለውጥ

ንስሐ ማለት በኃጢአት መጸጸት፤ ኃጢአትን ለመተውና አዲስ ሕይወት ለመጀመር መወሰን ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፤ «የአህዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁት ያለፈው ዘመን ይበቃል» /1ጴጥ. 4.3/

መንፈሳዊ ሕይወትና የክርስትና ጉዞ ሁል ጊዜ ራስን መመርመርና የቆሙበትን ማወቅ፤ ከዚያም የተሻለ ነገር ለማድረግ መወሰንን ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁል ጊዜ መደረግ ያለት ቢሆንም የዘመን መለወጫ ወቅት ደግሞ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የተሻለ የሥነ ልቡና ዝግጅት ያለበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

ስለዚህ የዘመን መለወጫ በዓልን ስናከብር ከበዓሉ አስቀድሞ ወይም በኋላ ባሉት ቀናት ውስጥ ይህንን ለማድረግ ጊዜ መመደብና ቁጭ ብለን በዕርጋታና በጥሙና ያለፈውን ዓመት መገመግም፣ የነበሩትን ደካማ ጎኖች /ችግሮች/ እና ጠንካራ /መልካም/ ነገሮች ነቅሰን ማውጣት ከነበሩት ችግሮች ውስጥ በአዲሱ ዓመት ልንፈታቸው የሚገቡ ችግሮችን ለይተን ማስቀመጥ ይገባናል፡፡ ከዚያም ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ «እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል» /ያዕ.4.15/ እንዳለው፡፡ እያንዳንዳቸውንም እንዴት አድርገን እንደምንቀርፋቸው አስበን ስልት መቀየስና ዕቅድ ማውጣት ዕቅዳችንን ለመፈጸምም መወሰን ይገባናል፡፡

ሊቀጠበብት ሐረገወይን «የምንቀበለው ዓመትአዲስሊባል የሚችለው እኛ መታደስ ከቻልን ብቻ ነው» ይላሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዲስ ኪዳንን ሲመሠርት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነገሮችን አድሷቸዋል፡፡ ደካማ የነበሩትንም ነገሮች አጠንክሯቸዋል አበርትቷቸዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩትን ክህነት፣ መስዋዕት፣ ሕግ፣ በኃጢአት የተበላሸውን የሰው ልጅ ባሕርይ እና ሌሎቹንም ሁሉ መቅረት ያለባቸውን አስቀርቶ፣ መስተካከል ያለባቸውን አስተካክሎ፣ ሐዲስ ኪዳንን ሠርቷል፡፡ ጌታችን ይህንን ካደረገ በኋላ ያለውን ዘመን «ዘመነ ሐዲስ» ያስባለው የእነዚህ ነገሮች መስተካከል ነው፡፡

«ይህ በእያንዳንዳችን ሕይወት መደረግ አለበት፡፡ መጪው ዓመት አዲስ ዓመት፣ አዲስ ዘመን የሚሆንልን ዓመቱ ችግሮቻችንን ቀርፈን፣ ጥንካሬዎቻችንን አጎልብተን የተሻለ ሕይወት የተሻለ አመለካከት የተሻለ ሥራ የምንጀምርበት ከሆነ ነው፡፡ ይህ ካልሆነና አምና የነበረውን ችግር ሁሉ መልሶ መድገም ካለ ግን ዓመቱ ለእኛ አዲስ ዓመት አይደለም» ይላሉ ሊቀጠበብት፡፡

ይህ ነገር በግለሰብ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብም በአገልግሎታችንም ሁሉ መደረግ አለበት፤ ያን ጊዜ እውነትም ወደ አዲሱ ዓመት እንሸጋገራለን፡፡

«የዘመን መለወጫ በዓል የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ እንዲሆንልን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት፣ የቅዱሳን ሁሉ አማላጅነትና ተራዳኢነት ከእኛ ጋር ይሁን፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

adye abeba 2006

ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ

ጳጉሜን 5 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዲ/ን ዘላለም ቻላቸው

“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” /1ኛ.ጴጥ.4.3/

adye abeba 2006መስከረም 1 ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ ይህንን ምክንያት አድርገን በዚህ ጽሑፍ የዘመን አቆጣጠርን ምንነትና ታሪክ፣ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር እንዲሁም የዘመን መለወጫ በዓልና አዲስ ዓመት ሊኖራቸው የሚገባውን መንፈሳዊ ትርጉምና ፋይዳ አስመልክተን አንዳንድ ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን፤

የዘመን አቆጣጠርን መጀመር አስፈላጊ ያደረጉ ሁለት ዋና ዋናምክንያቶች ነበሩ፡-

1. አዳም በበደሉ ምክንያት ከገነት ተባሮ ወደዚች ምድር ሲመጣ በመጸሐፈ ቀሌምጦስ እንደተጠቀሰው እግዚአብሔር «ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎት ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ቀን አንድ ሺሕ ዓመት መሆኑንና ይህ አምስት ቀንተኩል የተባለው ጊዜ 5500 ዓመት መሆኑን አዳምም ፣ ቀደምት አበውም ያውቁ ነበር እግዚአብሔር ዕፀ በለስን እንዳይበላ አዳምን ሲያዘው «ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞትለህ» ብሎት ነበር /ዘፍ.2.17፡፡ ይሁን እንጂ አዳም የሞተው በሰው አቆጣጠር 970 ዓመት ኖሮ ነው፡፡ይህ እግዚአብሔር ቀን ብሎ የገለጸው ምን ያህል እንደሆነ ለአዳም የሚያሳውቅ ነበር፡፡

 

ክቡር ዳዊትም “ሺሕ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን እንደ ሌሊትም ሰዓት ነውና” /መዝ.89.4/ በማለት መናገሩ ደግሞ ቀደምት አበው ስሌቱን እንደሚያውቁት የሚጠቁም ነው፡፡እንግዲህ አበውና ነቢያት ይህንን በተስፋ ሲጠብቁት የነበረውን የእግዚአብሔርን የማዳን ቀን የሚቆጥሩት የዘመን አቆጣጠር አስፈለጋቸው፡፡

2. የሰው ልጆች ወደ ምድረ ፋይድ ከወረዱ በኃላ “በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ.. ወደ መጣህባት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ » /ዘፍ.2 .16-17/ በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት የሚበሉትን ለማግኘት የግብርና እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምረው ነበር፡፡በዚህ ጊዜ አየሩ የሚሞቅበትንና የሚቀዘቅዝበትን፣ ዝናም የሚኖርበትንና የማይኖርበትን፣ ቀኑ የሚረዝምበትንና የሚያጥርበትን ጊዜ ለማወቅና ሥራን ከዚህ አንጻር ለማቀድና ለመተግበር የዘመን መቁጠሪያና የጊዜ መስፈሪያ አስፈልጓቸዋል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች የሰው ልጆች የተለያዩ መስፊሪያዎችን /መለኪያዎችን/ በመጠቀም ጊዜን / ዘመንን ሰፍረዋል፡፡ በሁሉም ቦታ የነበሩትና ዐበይት የሚባሉት የዘመን መስፈሪያዎች እግዚአብሔር «ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ፣ ለዕለታት፣ ለዘመናትና ለዓመታት ምልክት ይሆኑ ዘንድ» / ዘፍ.1. 14- 15/ የፈጠራቸውን የፀሐይንና የጨረቃን እንቅስቃሴ መሠረትያደረጉት መስፈሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም፡-

ሀ. ዕለት- አንድ ዕለት አንድ ቀንን /የብርሃን ክፍለ ጊዜን / እና አንድ ሌሊትን /የጨለማ ክፍለ ጊዜን/ ያካተተ ፀሐይ አንድ ጊዜ ከወጣች በኋላ ተመልሳ እስክትወጣ ድረስ ያለውን ጊዜ የያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ዕውቀታችን አንድ ዕለት ምድር በራሷ ዛቢያ አንድ ጊዜ የምትሸከረከርበት ጊዜ ነው፡፡

ለ. ውርኅ- ወርኅ ማለት በግእዝ ጨረቃ ማለት ነው፡፡ አንድ ወርኅ የሚባለው ጊዜ ሙሉ ጨረቃ ከወጣች በኋላ ድጋሚ እስከምትወጣ ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ በአሁኑ ዕውቀታችን / በጥንቱም ጨምሮ/ ይህ ጨረቃ መሬትን አንድ ጊዜ ዙራ ለመጨረስ የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ አንድ ወር ሃያ ዘጠኝ ተኩል ዕለታትን ይፈጃል፡፡

ሐ. ዓመት- አንድ ዓመት ማለት መሬት አንድ ጊዜ በፀሐይ ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ ይህም 365 ከ1/4 / ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከሩብ/ ዕለታት ይፈጃል፡፡ይህ ከመታወቁ በፊትም ግን የዓመት ጽንሰ ሓሳብ ነበር፡፡

 

ፕሮፊሰር ጌታቸው ኃይሌ የፅንሰ ሐሳቡን አመጣጥ እንዲህ ያስረዳሉ፡-

ሰዎች ርዝመታቸው እኩል የሆኑ ሁለት ሻማዎችን ሠሩና ልክ ፀሐይ ስትወጣ /ቀኑ ሲያልቅና ሌሊቱ ሲጀምር/ አንዱን ሻማ አበሩት፡፡ ልክ ፀሐይ ስትወጣ እሱን አጠፋናሌላውን / ሁለተኛውን/ ሻማ አበሩት፤ ጧት ፀሐይ እንደገና ስትወጣ / ሌሊቱ አልቆ ሌላ ቀን ሲጀምር/ ሻማውን አጠፉት፡፡ አሁን እንግዲህ ከየሻማዎቹ /ከሁለቱ ሻማዎች/ ምን ያህል እንደተቃጠለላቸው ሲያስተያዩት ከሁለቱ ሻማዎች የተቃጠለው እኩል አለመሆኑን ተመለከቱ በዚህም የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ እኩል አለመሆኑን ተረዱ፡፡ ቀደም ብለውም የቀኑና የሌሊቱ ርዝማኔ በተለያዩ ወቅቶች የተለያየ መሆኑን ልብ ብለው ነበርና ይህንን ሙከራቸውን ሲቀጥሉ በቀኑና በሌሊቱ ርዘማኔ /በሚቃጠለው የሻማዎቹ መጠን/ መካከል ያለው ልዩነት ከወቅት ወቅት የተለያየ እንደሆነ ተመለከቱ፡፡ ይህን ሙከራቸውን ሲቀጥሉ ግን በየ182 /ተኩል/ ዕለቱ ቀኑና ሌሊቱ እኩል የሚሆኑባቸው ሁለት ዕለታት በዓመት ውስጥ እንዳሉ ተገነዘቡ፡፡ እነዚህ ዕለታት አንዱ የሙቀት ወራት ከመጀመሩ በፊት የሌላው ደግሞ የቅዝቃዜው ወራት ከመጀመሩ በፊት የሚመጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት አንድ ጊዜ እኩል ሁኖ ደግሞበዚያው ወቅት እኩል እስከሚሆን ድረስ ያለውን ጊዜ ማለትም /182 ተኩል +182=365/ ዕለት አንድ ዓመት አሉት፡፡ አሁን ባለን ግንዛቤ ምድር በራሷ ዛቢያ እንደተሽከረከረች በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች፡፡ ምድር በፀሐይ ዙሪያ የምትዞረው ወደ ጎን 23 ተኩል ዲግሪ ያህልአጋድላ ነው፡፡ ይህ የቀንና የሌሊት ርዝመት መለያየትም የሚከሰተው በዚህ ማጋደል ምክንያት ነው፡፡

 

እንግዲህ በአጠቃላይ ዋናዎቹ የጊዜ / የዘመን/ መስፊሪያዎች ዕለት፣ ወር እና ዓመት ናቸው፡፡ ሦስትቱም ተመላላሽ ክስተቶችን / ለምሳሌ የፀሐይን መውጣት/ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚሀ ተመላላሽ ክስተቶች አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው እስኪከሰቱ የሚፈጁት ዘመንnወይም ጊዜ ዓውድ ይባላል፡፡ ዓውድ ማለት ዙሪያ፣ ክብ፣ እንደ ቀለበት ዙሮ የሚገጥም ማለት ነው፡፡ ስለዚህዓውድ ማለት ክስተቶቹ አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው እስኪመጡ ድረስ ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከላይ ያየናቸው ሦስት መስፈሪያዎች/ ዕለት፣ ወርኀ፣ ዓመት/ ዓዕዋዳት / ዓውዶች/ የሚወጡበት ጊዜ ዓውደ ዕለት፣ ዓውደ ወርኀ፣ ዓውደ ዓመት ይባላሉ፡፡

መጀመሪያ ላይ ሰዎች እነዚህን ሦስቱን መስፈሪያዎች /ዓዕዋዳት/ /በተለይም ቀንና እና ወርን/ለየብቻቸው ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ ከዚህን ያህል ቀን፣ከዚህን ያህል ወር በኋላ /በፊት/ እያሉ ጊዜን ይለኩ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስቱን በቅንብር/በቅንጅት/ ለመጠቀም ሲፈለግ ግን የዘመን አቆጣጠር ስሌት ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም አንድ ወር 29 ከግማሽ ቀን ነው፡፡ እንዲሁ እንዳለ ለመቁጠር ቢፈለግ የመጀመሪያው ወር ጠዋት ላይ ቢጀመር ሁለተኛው ወር ምሽት ላይ ይጀምራል፣ ሦስተኛው ደግሞ ድጋሚ ጠዋት ላይ ይጀምራል፤ ይህን ለመቅረፍ ወሩን ሙሉ ሰላሳ ቀን ቢያደርጉት ከትክክለኛው ወር /የጨረቃ ዐውድ/ ግማሽ ቀን ይተርፋል፤ 29 ቀን ብቻ ቢያደርጉት ደግሞ ግማሸ ቀን ይጎድላል፡፡

አንድ ዓመት 365 ከሩብ ዕለታት አሉት፡፡ ዓመትን በወራት ለመቁጠር ቢፈለግ፤ዓመቱን 12 ወር ቢያደርጉት የዓመቱ /የዕለታት ቁጥር /29.5X12=354/ ብቻ ይሆናል፡፡ይህም ከትክክለኛው ዓመት /365-354=11/ ዕለታት ያህል ያንሳል፡፡13 ወር ቢያደርጉት ዓመቱ /365X13=385.5/ ቀናት ይሆናል ይህም ከትክክለኛው ዓመት /383.5-365=19/ ቀናት ያህል ይበልጣል፡፡ ስለዚህ እነዚህን መስፈሪያዎች በቅንጅት ለመጠቀምይህንን አለመጣጣም የሚፈታ ቀመር /የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት/ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የዘመን አቆጣጠሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአይሁድን፣የሮማውያንን እና የሀገራችንን አቆጣጠሮች በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ የአይሁድ ዘመን አቆጣጠር የአይሁድ ዘመን አቆጣጠር እያንዳንዳቸው 29 እና 30 ዕለታት ያሏቸው 12 ወራት አሏቸው፤

 

 

.

የአይሁድ ወራት

የዕለታት ብዛት

ወራቱ በእኛ

1

ኒሳን

30

መጋቢት/ ሚያዝያ

2

ኢያር

29

ሚያዝያ/ ግንቦት

3

ሲዋን

30

ግንቦት/ ሰኔ

4

ታሙዝ

29

ሰኔ/ ሐምሌ

5

አቭ

30

ሐምሌ/ ነሐሴ

6

አሉል

29

ነሐሴ/ መስከረም

7

ኤታኒም

30

መስከረም/ ጥቅምት

8

ቡል

29/30

ጥቀምት/ ኅዳር

9

ከሴሉ

30/29

ኅዳር/ ታህሳስ

10

ጤቤት

29

ታህሳስ/ ጥር

11

ሳባጥ

30

ጥር/ የካቲት

12

አዳር 1

29

የካቲት/ መጋቢት

 

 

እነዚህ የዓመቱ 12 ወራት በአጠቃላይ 354 ያህል ብቻ ዕለታት ይኖሯቸዋል፡፡ ይህም በትክክለኛው ዓመት በ11 ዕለታትያህል ቢያንስም አዲስ ዓመት ይጀምራሉ፡፡ ልዩነቱ በሁለት ዓመታት 22 ዕለታት፣ በሦስት ዓመት ደግሞ 33 ዕለታት ያህል ይሆናል፡፡ስለዚህ በየሦስት ዓመቱ ከአስራ ሁለተኛው ወር ጳጉሜን በፊት አንድ ሌላ ወር ይጨምሩና የዓመቱን የወራት ቁጥር ዐሥራ ሦስትያደርጉና ልዩነቱንያስተካክሉታል፡፡

የኢትዮጵያውያንና የግብጻውያን ዘመን አቆጣጠር

የሀገራችን ኢትዮጵያ እና የጥንት ግብጻውያን /ዛሬም ድረስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን Yየምትጠቀምበት/ የዘመን አቆጣጠር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለታችንም እኩል ሰላሳ ቀናት ያሏቸው12 ወራት አሉን፡፡ እነዚህ 12 ወራት / 12X30=360/ ቀናት አሏቸው፡፡ እነዚህ ቀናት በትክክለኛው ዓመት በ/365.25-360=5.25/ ቀናት ያንሳሉ፡፡ይህንንም 5 ቀናት/ በ4 ዓመት አንድ ጊዜ 6 ቀናት/ ያሏትን 13ኛ ወር በመጨመር ያስተካክሉታል፡፡የኢትዮጵያውያን እና የግብጻውያን ወሮች ስም እንደሚከተለው ነው፡፡

 

 

ተ.ቁ

የግብጽ ወሮች

የኢትዮጵያ ወሮች

1

ቱት/ዩት

መስከረም

2

ባባ/ፓከር

ጥቅምት

3

ሀቱር

ኅዳር

4

ኪሃክ/ከያክ

ታኅሣሥ

5

ጡባ/ቶቢር

ጥር

6

አምሺር/ሜሺር

የካቲት

7

በረምሃት

መጋቢት

8

በርሙዳ

ሚያዝያ

9

በሸንስ

ግንቦት

10

ቦኩሩ

ሰኔ

11

አቢብ

ሐምሌ

12

መስሪ

ነሐሴ

13

ኒሳ/አፓጎሜኔ

ጳጉሜን

/ባሕረ ሐሳብ፣ፕ/ ጌታቸው ኃይሌ ፣ገጽ.65/

የሮማውያን ዘመን አቆጣጠር

የጥንት ሮማውያን የመጀመሪያው የዘመን መቁጠሪያ 30 እና 31 ቀናት ያሏቸው 10 ወራት ብቻ ነበሩት፡፡ በአንድ ዓመት ያሉት ቀናት ቁጥር 304 ብቻ ነበር፡፡ሮማውያን ይህን ያዘጋጀው የሮማ ከተማን የመሠረተው ሮሙለስ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በ713 ዓመት ቅ.ል.ክ ኑማ ፓምፒለስ /Noma Pompilos/ የተባለ የሮማ ንጉሥ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ወራት ጨመረበት፡፡

ጁሊያን የዘመን አቆጣጠር /Julian Calander/ የሮማው ንጉሥ ጁልየስ ቄሳር ለሲጃነስ የተባለ እስክንድርያዊ ሥነ ከዋክብት ተመራማሪን አማክሮ ጥንታዊውን የሮማውያን ዘመን አቆጣጠር አሻሽለው 30 እና 31 ቀናት ያላቸው11 ወራትና 28 ቀናት የአራት ዓመቱ 29 ቀናት ያሉት አንድ ወር ያለው የዘመን አቆጣጠር አዘጋጀ፡፡

አሁን ምዕራባውያን የሚጠቀሙበት የጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠርም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከተደረጉበት የቀናት ማስተካከያ በስተቀር ይኸው የጁልያን አቆጣጠር ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ልዩ ልዩ አቆጣጠሮች መኖራቸው እንደ እውነቱ ከሆነ የሚያስከፋ አይደለም፤ ሁሉምዓላማቸው አንድ ነውና፤ ሦስቱን የጊዜ መስፈሪያዎች ማጣጣም፡፡ ጥያቄ ሊሆኑ የሚገባቸው የሚከተሉት ሁለት ነጥቦች ናቸው፡፡

1. የዘመን ቁጥር ልዩነት

ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ የዘመን አቆጣጠር መለያየትን መነሻ እንዲህ በማለት ያብራራሉ፤ «ክብ የሆነ ነገር ሲከብ ከየትኛውም ቦታ መጀመር ይቻላል፤ የዘመን አቆጣጠር /ዓውደ ዓመትም/ ይኸው ነው፡፡ ዋናው ነገር አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ አንድ ታላቅታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ ነው፤ የዘመን አቆጣጠሮቹም ልዩነት መንስኤው ይኸው ነው» ይላሉ፡፡

ባሕረ ሐሳብ፣ ጌታቸው ኃይሌ፣ ገጽ.65/ ለምሳሌነትም ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ጊዜ መነሻ ማድረጋቸውን/ በኋላም ታላቁ እስክንድር የነገሠበት ዘመን የዘመን ቆጠራ መነሻ ሆነው እንደ ነበር ይጠቅሳሉ፡፡ መሐመድና ተከታዮች ከመካ ወደ መዲና ያደረጉትን ስደት መነሻ የሚያደርገው ኢስላማዊ የዘመን አቆጣጠርም ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡ የአይሁድን አቆጣጠር ትተን ከላይ ያየናቸው ሁለቱ የዘመን አቆጣጠሮች /የምዕራባውያኑ የጁልስ ጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠርና የኢትዮጵያና የግብጽ አቆጣጠር/ ሁለቱም ዘመንን የሚቆጥሩት ከክርስቶስ ልደት መነሻ አድርገው ነው፡፡ይሁን እንጂ እኛ ዛሬ 2002 ዓ.ም ነው ስንል እነርሱ ደግሞ 2009 ዓ.ም ነው ይላሉ፡፡

በመካከሉ የ7/8 ዓመታት ልዩነት አለ፡፡እንግዲህ ጥያቄው ትክክለኛው የትኛው ነው? የሚለው ነው። ጉዳዩ መጻሕፍትን ሊያጽፍ የሚችልና በእርግጥም የተጻፉበት ቢሆንም ለማሳያ ያክል ሁለት ነገሮች እንመልከት፡-

 

  1. አሁን ባለው የምዕራባውያን አቆጣጠር ሄሮድስ የሞተው 4 ዓመት ቅ.ል.ክ ነው። ሄሮድስ የሞተው ጌታ ተወልዶ በስደት ሦስት ዓመት ያህል በግብጽ ከቆየ በኋላ ነው፡፡ይህ ማለት በእርሱ አቆጣጠር ጌታ የተወለደው በ7 ዓመት ቅ.ል.ክ ነው ማለት ነው።እንግዲህ ጌታ በትክክል በተወለደበት በአንድ ዓ.ም እነርሱ ጌታ ሰባት ዓመት ሆኖታል ይላሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት አሁን ካላቸው ቁጥር ላይ ሰባት ዓመት መቀነስ አለባቸው፡፡

  2. ፍላቪየስ ጆሴፈስ የተባለው የአይሁድን ታሪክ የጻፈው ሊቅ እንደ መሰከረው ጌታ የተወለደበት ዓመት ነው ተብሎ በወንጌል ላይ የተጻፈው የቆጠራ ዓመት /ሕዝቡ ሁሉ የተቆጠረበትን ዘመን /ሉቃ.2.1/ በጎርጎሪያን ዘመን አቆጣጠር «7 ዓመተ እግዚአ /A.D/ ላይ ነው፡፡» በማለት መረጃ ትቶልናል ይህ ማለት ደግሞ ከምዕራባውያኑ ዘመን አቆጣጠር ላይ 7 ዓመቶች የግድ መቀነስአለበት ማለት ነው፡፡ ያ ሲደረግ ደግሞ የኛን ዘመን አቆጣጠር ያመጣል፡፡

 

2. የዘመን መለወጫ ቀን ልዩነት

ሁለተኛው ጉዳይ የዘመን መለወጫ ወርና ዕለት ልዩነት ነው፡፡ እኛ መስከረም 1 አዲስ ዓመት ስንጀምር እነርሱ በ January 1 / በእኛ ታኅሣሥ 23/ አዲስ ዓመት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ከየት የመጣ ልዩነት ነው? የእኛ እና የግብጻውያን አቆጣጠር እዚህ ጉዳይ ላይ ከአይሁድ አቆጣጠር ጋር ይስማማል፡፡በአይሁድ አቆጣጠር የመጀመሪያው ወር ኒሳን የሚባለው /በእኛ መጋቢት/ ሚያዝያ/ ነው፡፡«ይህ ወር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ይሁናችሁ፣ በዚህም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የአንድ ዓመት ተባዕት ላይ ወስደው ይረዱ፡፡ /ዘፀ.12.1-14/ ተብሎ የተሰጣቸውን የፋሲካ በዓል የሚያከብሩት በዚህ ወር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ የዓመት በዓል አድርገው የሚያከብሩት «የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁናችሁ፡፡ በዚሁ በመለከት ድምጽ የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ መስዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት» /ዘሌ.13.23-25/ ተብሎ የተሰጣቸው የሮሽ ሆሻና፣/የመለከት በዓል ወይም በዓለ መጥቅዕ/ ተብሎ የሚጠራው በዓል ነው፡፡ ይህም ማለት አዲስ ዓመት የሚያከብሩት በሰባተኛው ወር በኢታኒም ወር /በእኛ መስከረም ጥቅምት/ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችንም ትምህርት ዓለም የተፈጠረው መጋቢት 29 ቀን ነው፡፡ መስከረም ደግሞ ከመጋቢትጀምሮ ሲቆጠር ሰባተኛው ወር ነው ይህም ከአይሁድ ዘመን አቆጣጠር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አይሁድስ ቢሆኑ የመጀመሪያው ወር እያለ አዲስ ዓመትን ለምን በሰባተኛው ወርያከብራሉ ለሚለው ጥያቄ ሁለት ዓይነት ምላሾች /ምክንያቶች/ ይሰጣሉ፡፡

የመጀመሪያው ምክንያት «ሰባተኛው ወር ኖኅ ከመርከብ የወጣበት ወር በመሆኑ ይህ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ተደርጎ መከበር በመጀመሩ ነው» የሚል ነው፡፡ በዘመን መለወጫ ዕለት ልጃገረዶች አበባ እና ለምለም ሣር መያዛቸው ርግቢቱ ለኖኅ ካመጣችው ለምለም ወይራ /ቄጠማ/ ጋር ተያይዞ የተጀመረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሁለተኛው ደግሞ መስከረም የቀንና የዕለቱ ርዝመት እኩል የሚሆኑበት ወር በመሆኑ ነው የሚል ነው፡፡ የመስከረም1 ቀን ስንክሳር «የተባረከ የመስከረም ወር የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ርእስ ነው፤ የቀኑ ሰዓትም ከሌሊቱ ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ሁለት ነው» ይላል፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባው ሌላው ጉዳይ በቤተክርስቲያናችን ትምህርት እመቤታችን ጌታን የጸነሰችው መጋቢት 29 ቀን ነው፡፡ይህም ቅዱስ ጳዉሎስ ፣የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ተወለደ» /ገላ.4.4/ እንዳለው የ5500 ዘመኑ ፍጻሜ /ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ/ ነው፡፡ ጽንሰትን መጋቢት 29 ካልን በኋላ ልደትን ታህሣሥ 29 ቀን እናከብራለን፡፡ ከመጋቢት 29 እስከ ታህሣሥ 29 ድረስ 9 ወር ከ5 ቀን ነው፡፡ /ጳጉሜን ጨምሮ/፡፡ ጳጉሜ 6 በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ ታህሣሥ 28 ቀን ልደት ስለሚከበር አሁንም በመሐሉ ያለው ጊዜ 9 ወር ከአምስት ቀን ይሆናል፡፡

የዘመን ቆጠራ ለቤተ ክርስቲያን

የዘመን ቆጠራ ከጌታችን ልደት በፊት የነበረው ሃይማኖታዊ ፋይዳ የሰው ልጆች ሁሉ /በተለይ አበውና ነቢያት/ በተስፋ ይጠብቁት የነበረውን የጌታችንን መምጣት የቀረውን ጊዜ ለማወቅ ነበር፡፡ተስፋው ከተፈፀመ በኋላ ደግሞ የዘመን ቆጠራ ዋና አገልግሎቱ በዓላትና አጽዋማት በዓመቱ የሚወሉበትን ዕለት ለማወቅ ነው፡፡ እነዚህ በዓላት እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ለሰው ልጆች ያደረጋቸው ድንቅ ነገሮችና ውለታዎች የሚታሰቡባቸው ናቸው፡፡ በመጀመሪያ እነዚህ በዓላት ሁሉ መጀመሪያ በተደረጉባቸው ቀናት ይከበሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ ስቅለት መጋቢት 27፣ ትንሳኤ መጋቢት 29፣ ልደት ታኅሣስ 29፣ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ኅዳር 12፣ ወዘተ. . . ማለት ነው፡፡ አጽዋማቱም እንዲሁ፡፡

የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የነበረው ዲሜጥሮስ ግን አንዳንድ በዓላትና አጽዋማት መጀመሪያ በተፈጸሙባቸው ዕለታት እንዲውሉ ይመኝ ነበር፡፡ በተለይም ነነዌ የዐቢይ ጾም መጀመሪያ፣ እና የጾመ ሐዋርያት መጀመሪያ ሁል ጊዜ ሰኞ እንዲውሉ፤ ደብረ ዘይት፤ ሆሳዕና፤ ትንሳኤ ጰራቅሊጦስ ከእሁድ እንዳይወጡ፣ ርክበ ካህናት፣ ጾመ ድኅነት፣ ከረቡዕ፤ ዕርገት ከኀሙስ ስቅለት ከዓርብ እንዳይወጡ ይመኝ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ «ዲሜጥሮስ ሆይ ይህ ሁሉ በሐሳብ አይፈጸምም፤በተግባር ቢያደርጉት ካልሆነ» ብሎ ሱባኤ እንዲገባ ነገረው፡፡

 

ዲሜጥሮስም ሱባዔ ገባና የተመኘውን ሊያደርግበት የሚችል ቀመር ተገለጠለት፡፡ ቀመሩን በመጠቀምም ግብጻውያን እነዚህ በዓላት የሚውሉቸውን ቀናት በየዓመቱ እየወሰኑ ማክበር ጀመሩ፡፡በ325 የተደረገው የኒቅያ ጉባኤም ትንሳኤ ሁል ጊዜ እሁድ እንዲከበርና በዓሉ የሚከበርበትን ዕለት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን እንድታስታውቅ በመወሰኑ ይህ ቀመር ተስፋፍቷል፡፡ቀመሩ ወደ ሃገራቸንም መጥቷል፡፡ ስሙም ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡

ቀመሩን እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘነው ትምህርቱን በድጋሚ ካስፋፋው 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ከነበረው ከግብጻዊው ዲያቆን ከዮሐንስ አቡሻክር በመሆኑ የአቡሻክር ትምህርትም ተብሎ ይጠራል፡፡ /ባሕረ ሐሳብ፣ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ፣ገጽ 19/ የእኛ ሀገር ሊቃውንትም አስፋፍተውታል፤አራቀውታልም፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ቀመር በመጠቀም በየዓመቱ የሚውሉትን ተለዋዋጭ በዓላት እና አጽዋማት መቼ እንደሚውሉ ትወስናለች፡፡

ስለ ዘመን አቆጣጠር ይህንን ያህል ካልን ቀጥለን ደግሞ ዐቢይ ትኩረታችን ስለሆነው ስለ ዘመን መለወጫ በዓል እንነጋገር፡፡

 

የዘመን መለወጫ በዓል የበዓሉ ስያሜዎች

 

ይህ በዓል “የዘመን መለወጫ”፤ “አዲስ ዓመት” ከሚሉት በተጨማሪ ሌሎች ስሞችም አሉት፡፡

 

ሀ. ቅዱስ ዮሐንስ-

a st.john 2006ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተብሎ ከጌታችን ስብከት አስቀድሞ እንደሚመጣና ጥርጊያውን እንደሚያዘጋጅ በነቢዩ ኢሳይያስ ተነግሮለት ነበር /ኢሳ.40.3/፡፡ በዚህም መሠረት በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ተነስቶ «መንግሥት ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» «እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» በማለት ስለ ጌታችን አዳኝነት መስክሯል፤ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው እየገሰፁ ንስሐ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ጌታችንንም በዮርዳኖስ ወንዝ አጥምቋል፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ዕረፍት/ምትረት ርእስ/ የሚታሰበው መስከረም ሁለት ቀን ቢሆንም እንኳን ተግባሩ በዘመነ ወንጌልና በዘመነ ሐዲስ መካከል የነበረ መሸጋገሪያ በመሆኑ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መታሰቢያ በዓል የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ከሚሆነው ካለፈው ዓመት የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ወደሚሆነው አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ በሆነው በመስከረም አንድ ቀን እንዲከበር፤ በዓሉም በእርሱ ስም እንዲሰየም አባቶ ወስነዋል፡፡

ለ. ርእሰ ዓውደ ዐመት

ዓውድ ማለት ዙሪያ፣ ክብ፣ ክስተቶች አንድ ጊዜ ከተከሰቱ በኋላ ደግመው የሚመጡበት ጊዜ ማለት መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ዓውደ ዓመት ማለት ዓመቱ አንድ ጊዜ ከተጀመረ በኋላ ሁለተኛ ዓመት እስኪጀመር ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ ዓመትን መቁጠር ከየትኛውም ወር እና ቀን መጀመር ይቻላል፡፡ኅዳር 13 ብንጀምር አንድ ዓውደ ዓመት ማለት እስከሚቀጥለው ኅዳር 12 ቀን ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን መደበኛው ዓውደ ዓመት የሚጀምረው መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ርእሰ ዓውደ ዓመት የተባለውም «የሁሉም ዓውደ ዓመት መጀመሪያዎች ቁንጮ ነው» ለማለት ነው፡፡

ሐ. ዕንቁጣጣሽ

ሐጎስ ዘማርያም ለምለም በቀለን ለመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ ያቀረበችውን ጽሑፍና ሌሎች የቃል ማስረጃዎችን ጠቅሶ በሐመር መጽሔት የ1997 ዓ.ም መስከረም/ ጥቅምት ዕትም ላይ በቀረበው ጽሑፍ «ዕንቁጣጣሽ» ለሚለው የዚህ ስያሜ ሁለት ዋና ዋና መነሻዎችን እንዳሉት ገልጿል፡፡

 

  1. ዕንቁጣጣሽ የሚለው ቃል ሁለት ቃላት ካሉት ጥምር ቃል የተገኘ ነው፡፡ ዕንቁ እና ጣጣሽ ከሚሉ ዕንቁ የከበረ ዋናው ውድ የሆነ አብረቅራቂ ድንጋይ ነው፡፡ ጣጣሽ የሚለው ቃል ፃዕ ፃዕ ከሚለው የግእዙ ቃል የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙ ግብር፣ ጣጣ፣ ገጸ በረከት፣ ማለት ነው፡፡ለምሳሌ በሸዋ አካባቢ ግብር አለብኝ ሲል «ጣጣ አለብኝ» ይላል፡፡ይህ ስያሜ ለበዓሉ የተሰጠው ከንግሥተ ሳበ /ንግሥት ማክዳ/ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ንግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰሎሞንን ለመጎብኘት ሔዳ ሳለ የጸነሰችውንቀዳማዊ ምኒልክን በወለደች ጊዜ ሕዝቡ ንጉሥ ተወለደ ብሎ እልል እያሉ «አበባ እንቁ ጣጣሽ» እያለ ገጸ በረከት ለንግሥቲቱ አበረከቱ፡፡ያ የዘመን መለወጫ በዓልም ልጃገረዶች የአበባ ገጸ በረከት የሚያቀርቡበት ስለሆነ ዕንቁጣጣሽ ተባለ፡፡

  2. ዕንቁጣጣሽ ግጫ ማለት ነው፤ ግጫ ደግሞ የሣር ዓይነት ነው፡፡የአበባ፣ የእርጥብ ስጦታ መስጠት የተጀመረው በኖኅ ዘመን ነው፡፡ ኖኅ የጥፋት ውኃ በጎደለ ጊዜ መጉደሉን ለማረጋገጥ ርግብን ልኳት የወይራ ቅጠል አምጥታለች ይህ የሆነበት ወቅት የመስከረም ወር በመሆኑ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የዘመን መለወጫ ሆነ፡፡በርግቧ አምሳልም ልጃገረዶች የተለያየ ዓይነት ሣርና አበባ በመያዝና በማደል በዓሉን ያከብራሉ፡፡ በሣሩ ስምም በዓሉ ዕንቁጣጣሽ ተባለ፡፡

ምኩራብ

ሦስተኛው ሰንበት ምኩራብ ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት «ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ»

«ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ» እያለ ኢየሱስ በአይሁድ ምኩራብ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡፡ የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 21፡12-13 ተጠቅሷል፡፡

ቆላስ 2፡16-23 «እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለፈቃድ እየገባ፣ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፣ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፣ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል፡፡ ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ት ምህር ት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እንደሰው ሥርዓትና ት ምህር ት፡- አትያዝ አትቅመስ፣ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም ሁሉ እንደምትኖሩ ስለምን ትገዛላችሁ) እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና፡፡ ይህ እንደገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቈን ጥበብ ያለው ይመስላል፣ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም፡፡»

ያዕ 2፡14-26 « ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል) እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን) ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል) እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡
 
ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል፡፡ በእግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፡፡ አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን) አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን) እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን) መጽሐፍም አብርሃምም እግዚአብሔር አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን) ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡»
 
የሐዋ.ሥራ 1ዐ፡1-9 « በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፡፡ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፡- ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ ጌታ ሆይ ምንድር ነው) አለ፡፡ መልአኩም አለው፡- ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን ዐረገ፡፡ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ፡፡ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፣ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፣ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው፡፡ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፣ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ፡፡
 
መዝ 68፡9
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡
 
የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡
 
ዮሐ 2፡12-25 «ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ፡፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፡፡ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ፡፡ ስለዚህ አይሁድ መልሰው ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክ ት ታሳየናለህ) አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን) አሉት፡፡ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ፡፡
 
በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፣ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡»
 

                        ወስብሐት ለእግዚአብሔር