‹‹አቤቱ÷ በመዓትህ አትቅሠፈኝ÷ በመቅሰፍትህም አትገሥጸኝ›› (መዝ. ፴፯፥፩)
ከጥንት ጀምሮ ዓለም በእንደዚህ ዓይነት በሽታ ስትጠቃ እንደቆየች ታሪክ ምስክር ነው፤ እንደ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስና የቅርብ ጊዜ ክስተት የሆኑት ኢቦላና ሳርስ በሽታዎች ሰዎችን በተለያዩ መንገድ በመያዝና በማሠቃየት ለሞት ዳርገዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከተጠቁት የዓለም ክፍላት ውስጥ አንዷ ናት፤ በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ሺዎችን አጥታለች፤ አሁንም እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ያለው ኮሮና ቫይረስ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እንደገባ ምንጮች የሕክምና ማስረጃ ምንጮ ይፋ አድርገዋል፡፡
በዓለም ዙሩያ በሕክምናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ለበሽታው መድኃኒት በማጣታቸው መንግሥታት ለዜጎቻቸው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቀዋል፤ መከላከያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሏቸውን መንገዶች አስታውቀዋል፡፡
ነገር ግን ቤተክርስቲያናችን ሰዎች በክፉ ደዌ ሲያዙ ፈውሰ ሥጋን የሚያገኙት በጸበል፤ በጾምና በጾሎት እንደሆነ ታስተምራለች፤ እንደነዚህ ዓይነቱ ተዛማች በሽታም የእግዚአብሔር ቁጣ መሆኑን ታስረዳለች፡፡ ልበ አምላክ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹አቤቱ÷ በመዓትህ አትቅሠፈኝ÷ በመቅሰፍትህም አትገሥጸኝ›› ሲል አምላኩን ተማጽኗል፡፡ (መዝ. ፴፯፥፩)