“በሕይወት መኖር የሚፈልግ ከክፉ ይሽሽ መልካሙንም ያድርግ”

በዚህ ወቅቱ ዓለም በከባድ እና አስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ነው፡፡ ይህን ቸነፈር በሰው ጥንቃቄ ብቻ መቋቋም የሚቻል አይደለም፡፡ ሆኖም በግዴለሽነት እንዳንጓዝ ይልቁንም አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመክሩናል፡፡ በሃይማኖት ጸንተው በምግባር ቀንተው፣ ጥንቃቄም አድርገው የኖሩ አባቶቻችን በነፍሳቸውም፣ በሥጋቸውም ድነዋል፡፡ እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን በነፍስም በሥጋም እንድንድን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡

በሕይወት ለመኖር ከክፉ መራቅ መልካም የተባለውን ማድረግ  ያስፈልጋል፡፡ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “በምትገቡባትም በማንኛይቱም ከተማ ወይም መንደር በዚያ የሚገባው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ መርምሩ” (ማቴ.፲፥፲፩) በማለት ያስተማረው አንዱ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የነፍስም የሥጋም አምላክ ነው፡፡ የነፍሳችንንም ሆነ የሥጋችንን መጎዳት አይፈልግም፤ አይፈቅድምም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን አምነን ከእኛ የሚጠበቀውንም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም በሚገቡበት ሀገርና ከተማ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ እንዲመረምሩ ታዘዋል፡፡ ለእነርሱ የተነገረው ትእዛዝ የእኛም ነውና የምንችለውን ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ይላል፡፡

የዓለም ስጋት የሆነው የኮቪድ-፲፱ ኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን ገብቷል፡፡ ከሰዎች ጋር የምናደርገው ግንኙነት የተመጠነ፣ በቦታም የተራራቀ እንዲሆን ለተጎዱት መልካም ማድረግ  ይኖርብናል፡፡ በግዴለሽነት ከሚመጣብን መከራ እንድን፣ በሽታ ሊያስተላልፉ ከሚችሉ ነገሮች እንርቅ እንዲሁም ወረርሽኙ በእኛ ክፋት  ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ በሽታውን ሊያባብሱ ከሚችሉድርጊቶች መራቅ ይገባል፡፡

የፈርዖንና ፈርዖናውያን ጭካኔያቸው ሲበረታና አልመለስ ሲሉ ከታዘዘባቸው መቅሰፍት አንዱ ቸነፈር ነው፡፡ እስራኤላውያንም እንዲሁ ከፈርዖናውያን ጭካኔ የሞላበትና የዐመፅ ግዛት ነጻ ያወጣቸውን አምላክ ረስተው በበደል ሕይወት ሲመላለሱ ያመጣባቸው መቅሰፍት ቸነፈር ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን የመጣውንም መቅሰፍት በምን ምክንያት ይሆን ብሎ መገንዘብና ክፉ ከሆነው ነገር ሁሉ መራቅ ያስፈልጋል፡፡

መልካም ማድረግ፡- ምንም እንኳን በሽታው የሚተላለፍባቸው መንገዶች እርስ በእስር መተሳሰብን የሚያርቁ፣ መረዳዳትን የሚቃወሙ፣ አብሮነትን የሚጻረሩ ቢሆኑም ነገር ግን በባለሙያ ምክር እየታገዙ፣ ደግሞ ጽኑዕ የሆነውን የሃይማኖት ትምህርት ልብ እያሉ ቤተ ክርስቲያኗ የምታስተምረውን ቁርጠኝነት መወጣት የክርስትናችን መገለጫ መሆን አለበት፡፡

በእስራኤልም ታሪክ በሽተኞችን በአንድ በኩል ጤነኞችን በሌላ በኩል አድርጎ በሽታው እንዳይዛመት የማድረጉ ጥበብ እንደነበር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ክሥተት በቅዱስ መጽሐፍ የተመዘገበው መማር ያለብንን ጥበብ እንድንማር ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ለሰዎች መፈተንና መውደቅ ምክንያት ከመሆን መቆጠብ እንዳለብን “መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም  ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት” (ሉቃ.፲፯፥፩) በማለት እንዳስተማረ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከምንም በላይ የሚባሉ ጉዳዮችን ባለማስተዋል ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ከወዲሁ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትታወቀው በእርስ በእስር መተሳሰብ፣ አብሮ በመብላት፣ አብሮ በመጠጣት፣ አንዱ ለአንዱ በችግሩ ወቅት በመድረስ ነው፡፡ በዘመናችን የመጣው መቅሰፍት ግን አብሮነትን፣ መተሳሰብን፣ አንዱ ለአንዱ መድረስን ወዘተ የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ስለዚህ በበሽታው የተጠረጠሩትንም ሆነ መያዛቸው በእርግጠኝነት የተረጋጠባቸውን ሕመምተኞች የማግለል ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያት ሊከሠት የሚችለው አደጋ ደግሞ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊም ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ በበሽታው ምክንያት መገለል የደረሰባቸው ሰዎች በቀለኛ እንዲሆኑም ሊያስገድዳቸው ይችላል፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውንም ዘመን አልፋበታለች፡፡ ምንም ዘመናዊ ግንዛቤ ባልነበረበት ወቅት እንዲህ ያለ ወረርሽኝ ሲመጣ ማታ ማታ በመሄድና በመጠየቅ፣ ከበሽተኛው ጋር ሊኖር የሚችለውን ንክኪ በመገደብ፣ በሽተኛው በምግብ እጦት፣ አይዞህ ባይ ባለመኖርና በብቸኝነት የባሰ ችግር ላይ እንዳይወድቅ ይጠይቁት ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት እንደዚያ ያለውን ዘመን ካለፈች ዛሬ ደግሞ የተሻለ የባለሙያ ምክር ማግኘት የሚቻልበት፣ የትምህርቱም ሁኔታ አንጻራዊ በሆነ መንገድ የተስፋፋበት ዘመን ነውና ወቅቱ የሰጠንን የመከላከያ መንገድ ተጠቅመን ታሪክ ሊረሳው የማይችል ክፋት ሳይሆን ታሪክ ሊረሳው የማይቸል የመልካምነት ሥራ ልንሠራ ግድ ይለናል፡፡ ለዚህም ነው በሕይወት መኖር የሚፈልግ ከክፉ ይራቅ መልካሙንም ያድርግ የሚለውን መልእክት ማስተላለፍ የተፈለገው፡፡

አንዳንዴ ክርስትና የሚገለጸው በክፉና በአስጨናቂ ጊዜ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “በእተዝ ይጼሊ ኀቤከ ኵሉ ጻድቅ በጊዜ ርቱዕ፤ ስለዚህ ጻድቅ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይጸልያል።” (መዝ.፴፩፥፮) እንዳለን ምን አልባትም የእምነት ጽናታችን የሚፈተንበት ወቅት እንደሆነም መዘንጋት የለብንም፡፡ ምክንያቱም አንድ ጉዳይ በማድረግና ባለማድረግ የሚመጣውን ውጤት እንዲሁም የችግሩን ክብደትና ቅለት መለየት ካልተቻለ ብናደርገውም ባናደርገውም ጉዳት ይኖረዋል፡፡ ሶስና በረበናት እጅ ተይዛ ሳለ ያስጨነቃት በሁለቱም አቅጣጫ ጽኑዕ ሐሳብ ላይ የሚከት ጉዳይ ነበር፡፡ “ባደርገውም እሞታለሁ ባላደርገውም እሞታለሁ” (ዳን.፲፫፥፳፪) ያለችበት ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ የሃይማኖት ጽናት በዚህ ጊዜ ይገለጻል፡፡ ነገር ግን የሚበልጠውን ጉዳት አስቀርቶ መጠነኛውን ጉዳት መሸከም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጊዜ በሽተኛውን መንከባከብ ነው የሚጎዳው ወይስ አለመንከባከብና በሽታው ወደ እኔ እንዳይዛመት ማደረግ ነው የተሻለው የሚለውን ማገናዘብና በጥንቃቄ መመልከት ግድ ይላል፡፡ ግን ይህን ያህልም ሊሆን ስለማይችል በባለሙያ ምክር በመታገዝ አስፈላጊውንና መልካም የሆነውን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

የባለሙያ ምክርን ቸል አለማለት

 ጠቢቡ ሰሎሞን ይህን ሲያስረዳ “መልካም ምክር ትጠብቅሃለች፤ የተቀደሰች ማስተዋልም ትጋርድሃለች” (ምሳ.፪፥፲፩) በማለት ተናግሯል፡፡ የምክርን አስፈላጊነት በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም “ለሚያደርጋት ምክር መልካም ናት” (መዝ.፻፲፥፲) በማለት አስረድቷል፡፡ ታዲያ ለሚያደርጋት ተባለ እንጂ ሰምቶ ብቻ ለሚሄድ ምንም ፋይዳ እንደሌለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በሽታው እንዳይዛመት ከባለሙያ አንጻር የሚነገረውን መልእክት ሃይማኖትን በማይሸረሽር መልኩ መተግበር ይኖርብናል፡፡ ይህ ሲባል ግን እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ማድረግ ያለብንን የጸሎት፣ የጾም፣ የንስሓ ሕይወት ማጠናከርንም መዘንጋት የለብንም፡፡

ብዙዎቹ በባለሙያ የሚሰጡት መልእክቶች ከቤተ ክርስቲያን ሕግና ቀኖና አንጻር ተቀራራቢነት አላቸው፡፡ ለምሳሌ በሽታው እንዳይተላለፍ ከሚወሰዱ ጥንቃቄዎች መካከል ንጽሕናን መጠበቅ አንዱ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ቤተ ክርስቲያንም አስፍታና አምልታ የምታስተምረው ነው፡፡ ማንም ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ ሰውነቱን ታጥቦ፣ ልብሱን አጥቦ፣ ንጹሕ ልብስ ለብሶ መግባት አለበት፡፡ የሌሎችን ሥነ ልቡና ከሚረብሹ የውስጣዊም ሆነ የውጫዊ ንጽሕናዎችን  መጠበቅ አለበት፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከምን ጊዜውም በበለጠ በዚህ ጊዜ ለምእመናን መድረስ አለባት፡፡ በትምህርቱ፣ የባለሙያን ምክር ተግባራዊ በማድረግ፣ በጸሎተ ምሕላው፣ ምእመናን ባለመገንዘብ ለምን የሚል ጥያቄ የሚያነሷቸውን ጉዳዮች ሕግና ሥራቱን በማሳወቅ፣ ማድረግ የሚገባቸውን አድርጉ ማድረግ የማይገባቸውን ደግሞ አታድርጉ በማለት ከመንግሥት በተሻለ መልኩ ቀዳሚ ሚና ልትወስድ ይገባታል፡፡ በዚህም በምእመናን ላይ የሚደርሰውን የሥነ ልቡና፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የሃይማኖታዊ ጫናዎችን መቀነስ ይቻላል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ቀኖና በሚፈቅደው መንገድ ሕመምተኞች አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚደረግበትን መንገድ መፈለግ፡፡ ለምሳሌ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ፈሳሽ ነገር ያለባቸው፣ ደም የፈሰሳቸውና የሚፈሳቸው፣ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ወዘተ ምእመናን ቢሆኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገቡም፤ ካህናትም ቢሆኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገቡም አገልግሎትም አይሰጡም፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ የወሰዳቸው ጊዜያዊ መፍትሔዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ሐዊረ ሕይወትን ላልተወሰነ ጊዜ ያህል ማራዘም፣ ወርኃዊ ጉባኤያትን መሠረዝ፣ በግቢ ጉባኤያት የሚከናወኑ ታላላቅ ጉባኤያትን፣ ሌሎችንም በርካታ ምእመናን የሚሰባሰቡባቸውን ጉባኤያት ሁሉ ለጊዜው አቁሟል፡፡ ለጊዜው እንዲቀጥሉ የተደረጉት የጸሎትና የምሕላ መርሐ ግብሮች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ቀኖና የተከተሉ እንጂ የጣሱ አይደሉም፡፡

እንዲሁ ቅዱስ ሲኖዶስም መሠረታዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና ባልጣሰ መልኩ አስፈላጊ የሆነውን መልእክት ለምእመናን አስተላልፏል፡፡ ለምሳሌ በርካታ ምእመናን የሚሰበሰቡባቸው ጉባኤያት እንዳይከናወኑ፣ የንግሥ በዓል በቅዳሴና በማኅሌት ብቻ ታስበው እንዲያልፉ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ዘርዘር ብለው በመቆም መንፈሳዊውን አገልግሎት እንዲያከናውኑ ወዘተ የሚሉት ለምእመናኑ ደኅንነትና ጥንቃቄ ሲባል መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ ከመጣብን ወቅታዊ ቸነፈር እንድንድን አላስፈላጊ ጭንቀትን አርቀን፣ ሃይማኖትን ማጽናት፣ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ፣ ንስሓ መግባት፣ ሥጋውን ደሙን መቀበል፣ በሽተኞችንም ብታመም አልጠየቃችሁኝም የሚለው የወንጌል ቃል እንዳይጣስብንና በዕለተ ምጽአት ከእኔ ሂዱ እንዳንባል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሔር ጭንቀታችንን ከልባችን ከነገርነው ወደ እርሱም ከተመለስን መሐሪ፣ ይቅር ባይ፣ ምሕረቱ የበዛ፣ የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሣ አምላክ ነውና ከልባችን ጸልየን የመጣብንን መቅሰፍት እንዲመልስልን፣ በቸርነቱ ይቅር እንዲለን በምሕረት ዐይኑ እንዲመለከተን ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡