“ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ  በሰላም ትኖራላችሁ” (ሐዋ.፲፭፥፳፰)

ያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

በአንጾኪያ፣ በሶርያና በኪልቅያ ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለተጠመቁ ክርስቲያኖች ይህን ኃይለ ቃል ሐዋርያት ተናግረውታል። በእነርሱ ትእዛዝ ቃሉን ለምእመናን የገለጹት በርናባስ የተባለ ይሁዳና ሲላስ ናቸው። እነዚህም በሐዋርያት ምስክርነት እንደተገለጸው ስለጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሉ ሰውነታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።

ያም ወቅት ከእግዚአብሔር ያልታዘዙ ሰዎች ሕገ ኦሪትን ካልተቀበላችሁና ካልተገዘራችሁ አትድኑም እያሉ የሚያስገድዱበት ስለነበር እነርሱ የሚሏቸው የእግዚአብሔር ትእዛዝ እንዳልሆነ ለማስረዳት የተነገረ ነው። ለሕገ ኦሪት ተቆረቆርን የሚሉ የሙሴን መምህርነትና እርሱ የሠራላቸውን ሕግ እናከብራለን የሚሉ አይሁድ ሕገ ወንጌል እንዳይሰበክ እንቅፋት የሆኑበት ዘመንም ነበር። በዚህ ጊዜ ይህ እነርሱ እየሰበኩት ያለው የክርስቶስ ትእዛዝ እንዳልሆነ እና ትእዛዙን የያዙ መሆናቸውን ለማስረዳት የሐዋርያትን መልእክት ይዘው ሔዱ። እነዚህ የተላኩት የሐዋርያትን መልእክት መያዝ ብቻ ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ስም ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እንደነበርም ሐዋርያት መስክረውላቸዋል።

ዛሬም ገዳማውያን አዝዘዋል፣ ፈውስ መድኃኒቱ ተገኝቷል በሚል በገዳማውያን ስም የሚነግዱ አሉ። በስመ ባሕታውያን ቃላችንን ባለማክበራችን ይህ መዓት እንደመጣብን ለማሳመን በመጣር ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጭ የሚናገሩ፣ በጉባኤያት የሚነገረውን በሚያፈርስ መንገድ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ሕዝቡን ሰብስበው ሐሰት እየተናገሩ፣ ሰው በእግዚአብሔርና በቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዳይታመን የሚያደርጉ አሉ። በርካታ ሰዎች በመነኰሳትና በባሕታውያን ስም እየነግዱ በመሆኑ ምእመኑ ሊያስተውልና ሊጠነቀቁ ይገባል። ይልቁንም ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠቻቸውንና ስለ ክርስቶስ ስም ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡትን እውነተኛ አባቶች መቀበል ይጠበቅባቸዋል።

ሐዋርያት በወቅቱ ደቀ መዛሙርቱን የላኳቸው መልእክት እንዲህ የሚል ነበር። “ሥርዓት እንዳናከብድ፤ ሌላም ሸክም እንዳንጨምር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋራ ነውና ነገር ግን ይህን በግድ ትተው ዘንድ እናዝዛችኋለን። ለአማልክት የተሠዋውን፣ ሞቶ የተገኘውን፣ ደምንም አትብሉ፤ ከዝሙትም ራቁ፤ በራሳችሁ የምትጠሉትንም በወንድሞቻችሁ ላይ አታድርጉ፤ ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ በሰላም ትኖራላችሁ” (ሐዋ.፲፭፥፳፰-፳፱)

ሐዋርያት ለሕዝቡ ከመጨነቃቸው የተነሣ “ሥርዓት እንዳናከብድ ሌላም ሸክም እንዳንጨምር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ነውና” በሚል መልእክቱን ልከዋል፡፡ ዛሬም ቅዱስ ሲኖዶስ   የሚያስተላልፈውን መመሪያ መስማት ከምእመናን ይጠበቃል። በምእመናን ላይ ሥርዓት እንዳይከብድ፣ ምእመናኑ በመጣው መዓት እንዳይደናገጡ፣ ባልጸና እምነታቸው የመጣውን መዓት መቋቋም ተስኗቸው ከቤቱ እንዳይወጡ በማዘን ነውና ቃላቸውን ሊሰማ ይገባል።

በወቅቱ የነበሩት ምእመናን የነበረውን ችግርና እነርሱም ለመተው የሚችሉትን ነገር ተከልክለዋል። ምክንያቱም ከአሕዛብ የተመለሱ ስለሆነ ሥርዓት አልለመዱም፤ “አድርግ አታድርግ” የሚለው ትዝዛዝ ለእነርሱ አዲስ ነበርና ሲከብድባቸው ተማርረው ክርስትናውን እንዳይተውት ነበር። እነርሱ ለመተው የሚችሉትን ብቻ ሳይሆን ችግሩ በጣም የገዘፈውን ነው። በወቅቱ ግዙፍ የነበሩትና እንዲተውት የተከለከሉት የሚከተሉት ናቸው።

፩. ለአማልክት የተሠዋውን፣  ሞቶ የተገኘውን፣  ደምንም እንዳይበሉ የሚሉት በመጀመሪያ ደረጃ የተጠቀሱ ሲሆኑ እነዚህ ከመብል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው። በዋናነት የሐዲስ ኪዳን ትምህርት የሚያጠነጥነው “ይህን ብላ፤ ይህን አትብላ” የሚለው ላይ አይደለም። ከመብላትና ካለመብላት ጋር ተያይዞ መብላት የግድ ነው ተብሎ የተሰበከው ሥጋ ወደሙን ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የምእመናን ሰውነት ክርስቶስ በደሙ ያከበረው አካሉም ያደረገው ነውና የክርስቶስ አካል ለሆነው ክቡር ሰውነት ሲባል የረከሱ ነገሮችን እንዳያደርግ ተከልክሏል። እነዚህ ለጣዖት የተሰዋ፣ ሙቶ የተገኘ፣ ደም ወዘተ አትብሉ የተባሉትም በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንቶ የሚኖር ሰው ለሌላ አምላክ ተገዢ ያለመሆኑ ምልክት እንዲሆንለት ነው።

፪. ከዝሙትም እንዲርቁ፡- ዝሙት በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የረከሰ ሥራ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ዋጋ ከፍሎ የራሱ አካል ያደረገውን ሰውነቱን መርከስ ስለሌበት ሐዋርያትም ከኃጢአት ከለከሏቸው።

ዝሙት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ሥራ እንደሆነ ሲራክ “ባልዋን ትታ የምትሄድ ሴት እንዲሁ ናት፤ ከሌላ ወንድ ልጅን ትወልዳለች። በእግዚአብሔር አንዲት ክህደት አደረገች፤ ሁለተኛም ባሏን ከዳችው፤ ሦስተኛም በሴሰኝነቷ ሰረቀች፤ ከሌላ ወንድም ልጅን ወለደች። (ሲራ.፳፫፥፲፰-፳፫)  በማለት ያስረዳል።

ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፤ “ሥጋችሁም ለእግዚአብሔር ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ እግዚአብሔርም ለሥጋችሁ ነው፡፡… ሥጋችሁ የክርስቶስ አካል እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን አካል ወስዳችሁ የአመንዝራ አካል ታደርጉታላችሁን አይገባም፡፡ ከአመንዝራ ጋር የተገናኘ ከእርሷ ጋር አንድ አካል እንዲሆን አታውቁምን?…ከዝሙት ራቁ፤ ኃጢአት የሚሠራ ሰው ሁሉ ከሥጋው ውጭ ይሠራልና ዝሙትን የሚሠራ ሰው ግን ራሱ በሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል፤ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር ለተቀበላችሁት በእናንተ አድሮ ላለ ለመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ለራሳችሁም አይደላችሁም በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን በሥጋችሁ አክብሩት፡፡” (፩ቆሮ. ፮፥፲፫-፳)

ከላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ዝሙት ኃጢአት ስለሆነ ከዚህ መከልከልን የግዴታ አድርገው አዘዟቸው።

፫. በራሳቸው የሚጠሉትን በወንድሞቻቸው ላይ እንዳያደርጉ፤ ይህ ጉዳይ በክርስትና አስተምህሮ ብቻ ሳይሆን እንደሰብአዊ ፍጡር ሰው ለራሱ የማይወደውን ለሌላ ማድረግ የለበትም። በሃይማኖት ለሚኖር ደግሞ እጅግ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ ስለሆነ ሐዋርያት ከለከሏቸው።

ከላይ የተጠቀሱት ድርጊቶች በዚያ ዘመንም ሆነ በእኛ ዘመን መደረግ የሌለባቸው ናቸው። በዝሙት ኃጢአት በረከሱ ጊዜ ሰብአ ትካትን በንፍር ውኃ፣ የሰዶምና የገሞራን ሕዝብ ደግሞ በዲን እሳት አጥፍቷቸዋል። ዛሬም እንዲሁ ኃጢአታችን በዝቶ ሊሆን ይችላልና የተፈቀደልንን ብቻ እንጂ ያልተፈቀደልንን ልናደርግ እንደማይገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስረዱናል።

በዘመናችን የተከሠተውን በሽታ ማንም ቢሆን በራሱ ላይ እንዲከሠት የሚፈልግ የለም። የተያዙት በሽተኞችም ቢሆኑ መቼም ሳይወዱ በግድ ተያዙ እንጂ የተያዙት አካላት ወደውትና ፈልገውት አይደለም። ግን በራሳቸው የማይፈልጉትን ለሰዎች ለማስተላለፍ ግን የፈጠኑ ሁነዋል። በዚያን ወቅት የሐዋርያት ትምህርት በእናንተ ላይ ሊያደርጉባችሁ የማትወዱትን በሌሎች ላይ አታድርጉ ነበር። ይህ ትምህርት ዛሬም በትኩረት ሊታሰብበት የሚገባ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ ምእመናን መታዘዝን ገንዘብ ማድረግ ይጠቅባቸዋል። አባቶቻችን የሚያዝዙን በሽታው ከአንዱ ወደ አንዱ እንዳይዛመት፣ የግል ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ፣ በማንኛውም እንቅስቃሴ አካላዊ ርቀትንም እንድንጠብቅ እና የመሳሰሉትን ነው። እነዚህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ለሚያነብ ሰው የሚከብዱ ትእዛዛት አይደሉም። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ሑር ሕዝብየ ወባእ ቤተከ ወእጹ ኆኅተከ ወተሀብእ ሕዳጠ ምእረ እስከ የኃልፍ መዓቱ ለእግዚአብሔር፤ ሕዝቤ ሁይ ሂድ ወደ ቤትህ ግባ፤ ለጥቂት ጊዜም ተሰወር፣ መዓቱ እስኪያልፍ ድረስ” በማለት እንዳያስተማረን ይህ የመጣው መዓት እስኪያልፍ ድረስ የታዘዝነው ነገር የሚከብድ አይደለም፤ ብንፈጽመው በታዛዥነታችን በረከትን እናገኛለን እንጂ የሚጎዳን አይደለም፤ እኛ የምናደርገው ጥንቃቄና መታዘዝ ከእግዚአብሔር ቸርነት ጋር ከመጣብን መከራ  ይጠብቀናል። በመሆኑም “ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ  በሰላም ትኖራላችሁ (ሐዋ.፲፭፥፳፰)” ተብለናልና በሽታው ከሚተላለፍባቸው መንገዶች ተጠብቀን መከላከያዎችን ተግብረን ከመጣብን በሽታ እንድንድን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ አሜን።