‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ታማኝ አገልጋይ ማነው?›› (ማቴ.፳፬፥፵፭)

        መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፤ ስያሜውን የሰጠውም ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡  ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በሆነው ጾመ ድጓ የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብር ኄርን  ወይም ታማኝ አገልጋይን የሚያወሳ ነው፡፡

ለዚህም ምሳሌ እንዲሆነን በማቴዎስ ወንጌል ላይ የተጻፈው ታሪክ እናነሳለን፤ አንድ ባለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠውም አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሄደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ ዐስር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡

ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‹‹ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ አምስት አተረፍኩ አለው፡፡ ‹‹ገብር ኄር ወምእመን ዘበሁድ ምእምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍስሐሁ ለእግዚእከ፤ አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ‹‹ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፡፡ አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› አለው፡፡

አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ቀርቦ ‹‹ጌታዬ አንተ ክፉና ጨካኝ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሰበስብ እንደሆንክ ስለአወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ አለው፡፡ አንተ ሰነፍ ባሪያ መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር፤ እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር፡፡

የዚህን መክሊት ውሰዱና አስር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል፤ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል፡፡ይህን ሰነፍ ባሪያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑዕ ጨለማ ወደአለበት ውሰዱት፤ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበትም ጨምሩት››አለ፡፡(ማቴ.፳፭፥፲፬-፳፭)

ባለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፤ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው፤ መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት በዕለተ ምጽአት ለሁሉም በአገለገለው አገልግሎት ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡

ያገለገሉትን ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፎች ደግሞ ጥርስ ማፋጨት ስቃይ ጽኑዕ ጨለማ ባለበት ሲዖል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ከላይ ያነሳነው የቅዱስ ወንጌል ቃል ‹‹ታማኝ አገልጋይ ማነው?›› ይህ እያንዳንዱ በአርዓያ እግዚአብሔር የተፈጠረ የሰው ልጅ ጥያቄ ነው፤ የዚህን አምላካዊ ጥያቄ መልስ መስጠት ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡

ታማኝ አገልጋይ ማነው?

. ታማኝ አገልጋይ ነቢዩ ሙሴ

ሙሴ ታማኝ አገልጋይ እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ ‹‹በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በህልም አናግረዋለሁ፤ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው››፡፡ (ዘኁ.፲፪፥፮) ይህ የፍጡር ምስክርነት ሳይሆን በፈጣሪው የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ በእውኑ በዘመናችን እንኳን ፈጣሪ ፍጡራን ታማኝነቱን የሚመሰክሩለት አጋልጋይ ይኖር ይሆን? የሙሴን ታማኝ አገልጋይነት በረሃ፣ ስደት፣ መከራ እና ቁጣ ያልበገረው አርባ ዓመት ስለ ወንድሞቹ በመሰደድ፣ አርባ ዓመት ደግሞ የተሰደደላቸው ወንድሞቹን በመምራት ባሕር በመክፈል፣ ጠላት በመግደል፣ መና በማውረድ፣ ደመና በመጋረድ ውኃ ከዓለት አፍልቆ በማጠጣት፣ መከራውን ከወገኖቹ ጋር በመቀበል፣ የቀኑ ሀሩር የሌሊቱን ቁር /ብርድ/ ታግሶ በታማኝነት አገልግሏል፤ ታማኝነቱ እስከሞት ነበር፡፡

‹‹ሙሴም ወደ እግዚብሔር ተመልሶ ወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኀጢአት ሠርተዋል፡፡ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ፤ ከባለሟልነትህ አውጣኝ››፡፡(ዘጸ.፴፪፥፴፩) ታማኝ አገልጋይ ‹‹እኔ ልሙት፤ ሌሎች ይዳኑ የሚል ነው፤ አሁን የምናየው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሰዎች ይሙቱ፤ እኔ ልኑር፤ ሰዎች ጾም ይደሩ፤ እኔ ልብላ፤ ሰዎች ይራቆቱ እኔ ልልበስ፤ ሰዎች ይዘኑ፤ እኔ ልደሰት›› ነው፡፡

ታማኝ አገልጋይ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም፡፡ ዛሬ በዓለማችን የምንመለከተው ግን ‹‹ጩኸት ለአሞራ መብል ለጅግራ›› የሚባለውን መሰል ነው፡፡ በታማኝ አገልጋዮች ድካም የሚሸለሙ ታማኝ አገልጋዮች በሠሩት ሥራ የሚያቀርቡ፣ የሚወደሱ፣ ከጥቅሙ እንጂ ከድካሙ መክፈል የማይሹ እንቅፋት የሚመታው እግርን ነው፡፡ አክሊል የሚቀዳጀው ግን ራስ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደራስ አክሊል ዘውድ የሚጸፋ ብቻ ሳይሆን እንደ እግር እንቅፋቱን፣ እሾሁን፣ መከራውን፣ ውጣ ውረዱንና ድካሙን የሚቀበል ነው፡፡ በጥቅም ጊዜ ለራሱ በአካፋ የሚዝቅ ወይም በጭልፋ የሚጨለፍ አይደለም፡፡ ሙሴ ባሕር የከፈለው፣ መና ያወረደው፣ ደመና የጋረደው፣ ወይም ውኃ ያፈለቀው ለራሱ አልነበረም፤ ለሚመራቸው ሕዝብ ነበር እንጂ፡፡ ታማኝ አገልጋይ ያሰኘውም ይኸው ነው፤ በዚህ ከብሮበታል፤ ተመስግኖበታልም፡፡

፪. ታማኝ አገልጋይ ነቢዩ ዳዊት

ዳዊት ዘመነ መሳፍንት አልፎ ዘመነ ነገሥት ሲተካ እስራኤልን በንጉሥነት እንዲያገለግል እግዚአብሔር ከበግ ጥበቃው ወስዶ ሥልጣን ሰጠው፤ ያልተመነ የሳዖልን በትረ መንግሥት በሳሙኤል እጅ ተቀብቶ ተቀብሏል፡፡

በተሰጠው ሥልጣን በታማኝነት ሕዝበ እስራኤልን መርቷል፡፡ ታማኝነቱንም እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ መሰከረለት ለእርሱም መስክሮለታል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እንደልቡ የሆነ ሰው መርጧልና››‹‹የዘይቱን ቀንድ ሞልተህ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተልሔም እልክሃለሁ›› እንደተባለው፡፡ (፩ ሳሙ.፲፫፥፲፫፣ ፲፮፥፪)

‹‹ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱስ›› እንዲል፡፡(መዝ.፹፰፥፳) ‹‹ባሪያዬ ዳዊትን አገኘሁት፤ የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት›› ይህን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሰዓታት በተባለው ድርሰቱ፡- ‹‹ረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ብዕሴ ምእመነ ዘከመልብየ›› አገልጋዬ ዳዊትን እንደ ልቤ የታመነ ሰውን ሆኖ አገኘሁት›› ሲል ተርጉሞታል፡፡ የተገኘው በታማኝነት ነበር፤ ከነገሠ በኋላም ታማኝ ነበር፤ አሁን በዚህ ዓለም የምንኖር እኛ ግን በድኅነት ታማኝ እንሆንና ሀብት ሹመት ሥልጣን ሲመጣ ታማኝነትን እናጣለን፤ እንዲያውም ታማኝነትን እንንቀዋለን፡፡ መስረቅ ጀግንነት፣ መዋሸት ሥልጣኔ ይመስለናል፡፡ ዳዊት ሳይሾም በጎቹን በመጠበቅ ታማኝ ነበር፡፡ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ አንበሳ ቢመጣ በኋላው ተከትሎ ነብሩን በጡጫ አንበሳውን በእርግጫ ብሎ በጎቹን ያስጥለው ነበር፡፡

‹‹እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፤ ከመንጋውም ጠቦት ይወሰድ ነበር፤በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፤ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሳብኝም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር፡፡ይህም ፍልስጥኤማዊ ከነዚያ እንደ አንዱ ይሆናል፤ እንግዲህ እገድለው ዘንድ ከእስራኤል ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሄድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቆላፍ ምንድን ነው? ከአንበሳና ከድብ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል››አለ፡፡ (፩ ሳሙ. ፲፯፥፴፬)

ዛሬስ ቢሆን በእስራኤል ዘነፍስ በምእመናን ላይ የሚገዳደሩ ብዙ ፍልስኤማውያን ተሰልፈዋል፤ እነዚህን ድል የሚነሣ በጎቹን ምእመናን ከተኩላ ከአንበሳና፣ ከድብ አፍ የሚታደግ ታማኝ አገልጋይ ማነው? ‹‹ከምእመናን ተግዳሮት የሚያርቅ ፈጣሪዬ ከመከራ ያድነኛል›› ብሎ የሚታመን የኢ-አማንያን ብዛት የማያስፈራው ማን ነው? ከትንሽነቱ እስከ ታላቅነቱ የታመነ አገልጋይ ማነው? ለተሾመበት ሓላፊነት ታማኝ ማነው? አሁንም ዓለማችን ከሥጋውያን ባለ ሥልጣናትም ሆነ ከመንፈሳዊያን መሪዎች የምትሻው ታማኝ ሰው ነው፡፡ በሙስና ያልተዘፈቀ ጉቦ አይኑን ያላጨለመበት ለመንጋው አርአያና ምሳሌ የሚሆን ሰው ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡ በመኀላ የተቀበለውን የአገልግሎት ሓላፊነት የማይዘነጋ ታማኝ መሆን አለበት፡፡

መንጋው በክህደት ሲጠፋ ዝም ብሎ የሚያይ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ አገልጋይ አይደለም፤ ታማሚው እየተሰቃየ የሚዝናና፣ ቆይ ሻይ ልጠጣ የሚል፣ ሐኪም ታማኝ አይደለም፡፡ ፍርድ የሚያጎድል ድሆችን የሚበድል ለደሃ አደጎች የማይፈርድ ዳኛ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡

ቅቤ በሙዝ እና በድንች ቀላቅሎ፣ በርበሬ በገል ጨምሮ ሌሎችን አጭበርብሮ የሚሸጥ ነጋዴ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ እየነገደ ያለው በሰው ሕይወት መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ እንደየ አቅሙ በተሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ታማኝ መሆን አለበት፡፡

፫.    ታማኝ አገልጋይ ቅዱስ ዮሴፍ

ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምግባቸውን ተሸክሞ፣ የእርሱ ስንቅ ቢያልቅ የወንድሞቹን ስንቅ ሳይበላ በትንሽ የታመነ ሰው ነበር፤ ወንድሞቹ ሸጠውት በቤተ ጴጥፋራ በሚያገለግልበት ጊዜም ታማኝ ነበር፤ ታማኝነቱ በጲጥፋራ ቤት ጌታ አድርጎታል፡፡

‹‹ዮሴፍ ተሸጠ፤ አገልጋይም ሆነ፤ እግሮቹ በእግር ብረት ስለሰሉ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች፤ ቃሉ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው፤ ንጉሥ ላከ፤ ፈታውም፤ የሕዝብ አለቃ አድርጎ ሾመው፤ የቤቱም ጌታ አደረገው፤ በገንዘቡ ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው፡፡ አለቆቹን እንደ እርሱ ይገስጽ ዘንድ፣ ሽማግሌዎችን እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ››፡፡ (መዝ.፻፬፥፲፯) በዚህ ሁኔታ የነበረው ዮሴፍ የጌታው ሚስት ሲወጣና ሲገባ ዐይኗን ጣለችበት በዝሙት አዐይን ተመለከተችው፡፡

‹‹የጌታውም ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለችበት፤ ከእኔም ጋር ተኛ አለችው፤ እርሱም እምቢ አለ፡፡ ለጌታው ሚስቱ እንዲህ አላት፤ እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ሁሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፡፡ በቤቱ ያለውን ምንም የሚያውቀው የለም፤ በዚህ ቤት ከአኔ የሚበልጥ ሰው የለም፡፡ ሚስት ስለሆንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? እንዴትስ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን እሠራለሁ?››፡፡ (ዘፍ.፴፱፥፯)

በዮሴፍ ታማኝነት የጌታው ቤት ተባርኳል፤ ሀብቱ በዝቷል፡፡ በታማኝነቱ በቤቱ ያለውን ሁሉ ተረክቦ ነበር፤ የቀረበለት ፈተና ግን ከባድ ነበር፤ ይህን በታማኝነቱ ማለፍ ችሏል፡፡ ዛሬ በእያንዳንዱ ጓዳ ልጅ ብዙ ክፋት እንዲሁም በደል ይፈጸማል፡፡ ልጅ በፈላ ውኃ የሚቀቅሉም ሰዎች አሉ፤ ሥርቆትም የሚፈጽሙ በርካታ ናቸው፡፡ በጥቃቅን ዕቃዎች እንኳን የሚታመን ጠፍቷል፡፡ ዮሴፍ ግን በታማኝ አገልጋይነቱ በመጣበት መከራ ቢታሰር እንኳ ያለ ሹመት አላደረም፤ የእስረኞች አለቃ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ሲወጣም ግብፅን በሙሉ መርቷታል፡፡ በግብፃውያን በሙሉ ተሾሟል፤ በጥቂቱ ታምኗልና፡፡ ‹‹በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል›› እንዲል፡፡ (ማቴ.፳፭፥፳፬)

ከሦስቱ ታማኝ አገልጋዮች ሕይወት ሁሉም የሰው ልጅ ታማኝ አገልጋይነት የሚያሰጠውን ክብርና ጸጋ ተመልክቶ በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ታማኝ መሆን መጀመሪያ የሚጠቅመው ለራስ ነው፤ ከዚያም ለሀገር፣ ለወገን፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ላመኑት፣ ላላመኑት ሁሉ ይጠቅማል፡፡ በመጨረሻም የጽድቅ አክሊልን ያቀዳጃል፤ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፤ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ያስከብራል፡፡

ጻድቃን፣ ሰማዕታትና ቅዱሳን በታማኝ አገልግሎታቸው ፈጣሪያቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡ በሓላፊው ገንዘብ ያልታመኑት ይሁዳ፣ ሐናንያ፣ ሰጲራ፣ የደረሰባቸውን ጉዳት አይተናል፤ በአካን ወልደ ከርሚንም ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶበታል፡፡ (ሐዋ.፭፥፩፣ ፩፥፳፭)

ለዚህ ነበር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ፥ አድነኝ፥ ደግ ሰው አልቆአልና፥ ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሎአልና››ያለው፡፡ (መዝ.፲፩፥፩) ስለዚህ ሁሉም በአለበት የአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሀለሁ›› የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል መስማት ይገባዋል፡፡ መልካም አገልግሎት አገልግለን መንግሥቱን እንድንወርስና ‹‹ገብር ኄር›› እንድንባል አምላካችን ይርዳን፤ አሜን፡፡