ካለፈው የቀጠለ….

ማንኛውም ችግር በቅርብ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሊሆን ይችላል እንጂ መፍትሔ የሌለው አይደለም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ችግሩ እንዳለ ይረዱና የችግሩ መንሥኤን፣ አደጋውንና መፍትሔውንም ጭምር በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል፡፡ በዚህም የተነሣ መፍትሔ ብለው የሚሞክሩት ነገር የባሰ ችግር ይሆንባቸዋል፡፡ እኛ መፍትሔ የሚመስለን ነገር የባሰ ሌላ ችግር እንዳይሆን ይረዳን ዘንድ መፍትሔ ያልናቸውን በሁለት ከፍለን እንመለከታቸዋልን፡፡

ሀ.የታመሙትን ብቻቸውን ማድረግ፡- ጥንትም የእስራኤልን ታሪክ መለስ ብለን ስንመለከት በሽተኞችን ብቻቸውን ያደርጓቸው ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው የእስራኤልን ልጆች ለምጻሙን ሁሉ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ በሰውነቱ የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳረከሱ ከወንድ እስከ ሴት ከሰፈሩ አውጧቸው፡፡ የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ ከሰፈሩ አወጧቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደተናገረው የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ” (ዘኍ.፭፥፩-፬) እንዲል፡፡ ይህ የሚደረግበት ምክንያት በሽታው ከበሽተኛው ወደጤነኛው እንዳይዛመትና ለእግዚአብሔር ቤት ክብር ሲባልም ነበር፡፡ በሀገራችንም በሽታ በተከሰተባቸው ዘመናት በሽተኞችን የሚጠይቁበት ሰዓት ሳይቀር የተወሰነ ነበር፣ ካልሆነም አይጠይቁም፣ ነገር ግን ሕመምተኞች በረኃብ እንዳይጎዱ የሚያደርጉበት ዘዴም ነበራቸው፡፡

ለ.የህክምና አገልግሎት ማግኘት፡- የጥበብ ባለቤት እግዚአብሔር ጥበብን በተለያየ መንገድ ይገልጣል፡፡ ከሚገልጣቸው ጥበቦች መካከል የህክምና ሙያ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ህክምናውን መከታተሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ስመ አጋንንትን እየጠሩ እናድናለን የሚሉትን ጠንቋዮችን ነው እንጂ በህክምና ባለሙያዎች እንድንገለገል ቤተ ክርስቲያንም ትፈቅዳለች፡፡

የባለሙያ ምክር ማግኘት በቅዱስ ወንጌል እንደምናገኘው ሰዎች ሲታመሙ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እየሄዱ አድነን ይሉት ነበር፡፡ “ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ ጌታ ሆይ ብላቴናዬ ሽባ ሁኖ እጅግ እየተሰቃየ በቤት ተኝቷል ብሎ ለመነው” (ማቴ. ፰፥፭-፮) እንዲል፡፡ በዚህ ምንባብ የምናገኘው የመቶ አለቃው ታሪክ የሚያስረዳን በሽተኞች ወደ ባለሙያ በመሄድ በባለሙያ እንዲረዱና ከበሽታቸው እንዲፈወሱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማቴ. ፲፭፥፳፩-፳፰ የምናገኛት የከነአናዊቷ እና በዮሐ. ፱፥፩-፲፪ የዐይነ ሥውሩን ታሪክ ስንመለከት የምናገኘው ማንኛውም ሰው ሲታመም ወደ ባለመድኃኒት መሄድ እንደሚገባ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም በዘመናችን የተከሠተውን በሽታ ለመከላከል የባለሙያ ምክር ማግኘት ያስፈልጋል፡፡

ሐ. አላስፈላጊ ጭንቀትን ማስወገድ፡-  ባለሙያዎች የበሽታውን ክፋት በተለይም በፍጥነት ከሰው ወደሰው መተላለፍ እንደሚችል ሲያስረዱን ለጥንቃቄ ነው እንጂ አላስፈላጊ ጭንቀት እንድንጨነቅ አይደለም፡፡ በመሠረቱ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃልም አለማሰብ አንችልም እንጂ እንዳንጨነቅ ግን ተነግሮናል፡፡ “ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?” (ማቴ.፮፥፳፯) ተብለናል፡፡ ስለዚህ ብንጨነቅ ተጨማሪ በሽታ እንፈጥራለን እንጂ መፍትሔ ማምጣት ስለማንችል አስበን አስፈላጊውን መፍትሔ ከመፈለግ ያለፈ አላስፈላጊ ጭንቀትን ግን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል፡፡ “ልባችሁ አይታወክ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ፡፡” (ዮሐ.፲፬፥፩) ስለዚህ ተጨንቀን የምናመጣው ስለሌለ በመጨነቃችን ራሳችንን ልንጎዳ ስለምንችል መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ክርስትናውን በተግባር የምንኖረው መቼ ይሆን? ልብ ብለን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ደግሞስ እግዚአብሔርን መጠጊያ ያደረግን እግዚአብሔርን መጠጊያ ካላደረጉት ካልተሻልን ምንድን ነው ልዩነታችን? ይህንም ማሰብ ግድ ይለናል፡፡

ሀ. ጽኑዕ እምነት፡- ጽኑዕ እምነት ያለው ሰው ከሥጋም ሆነ ከነፍስ መከራ ይድናል፡፡ “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይተወት አለው” (ዮሐ.፮፥፵፯) በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረ የሚያምን ከመቅሰፍተ ሥጋ ከመቅሰፍተ ነፍስ ይድናል፡፡ ቢሞትም አስነሣዋለሁ ይለናል፡፡ በሥጋ ቢሞት በነፍሱ አይሞትም ማለት ነው፡፡ ደግሞም ያመኑበትን ከሕመማቸው ፈውሷቸዋል፡፡ እውራንን አብርቷል፤ ለምጻሞችን አንጽቷል፤ ጎባጦችች አቅንቷል፤ የአራት ቀን እሬሳ አልዓዛርንም አንሥቷል ስለዚህ ማመን የመጀመሪያውና ቀዳሚው መፍትሔ ነው፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “አምላክነሰ ኃይልነ ወጸወንነ ወራዳኢነ ውእቱ ለምንዳቤነ ዘረከበነ ፈድፋደ፤ አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን ነው፤ ባገኘን በታላቅ መከራም ጊዜ ረዳታችን ነው፡፡ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢፈልሱ አንፈራም” (መዝ.፵፭፥፩-፪) በማለት እንደተናገረው ጽኑ እምነት ያለው ሰው መጠጊያውንም፣ መመኪያውንም እግዚአብሔርን ያደረገ ሰው አይፈራም፡፡ በዘመናችን የመጣው በሽታ እንዲህ ብታደርጉ መከላከል ትችላላችሁ እየተባልን ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ግን ምድርም ብትነዋወጥ፣ ተራራችም ወደ ባሕር ልብ ቢፈልሱ አንፈራም እንዳለ አባቶቻችን ነቢያትን አባቶቻችን ሐዋርያትን አባቶቻችን ቅዱሳንን አብነት አድርገን እምነታችንን አጽንተን ልንኖር ይገባል፡፡

ለ. በሽተኞች ለጊዜው አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ፡- መቆጠብ ያለባቸው አካላት ካሉ እንዲቆጠቡ ማድረግ:: በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፲፭፥፩ እስከ ፍጻሜ ከሰውነቱ ፈሳሽ የሚወጣ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ እስከ ሚነጻ ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ አይገባም ነበር፡፡ ይህ በብሉይ ኪዳን የነበረው የአምልኮ ሥርዓት ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳንም ከብሉይ ኪዳኑ የሚለይ ሥርዓት እንዳለ ብናምንም ሙሉ በሙሉ ግን አልተሻረም፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሰውነቱ የቆሰለና ፈሳሽ ያለበት፣ ለሰው ሥነ ልቡና የማይመች ሕመም ያለበት፣…ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገባም፡፡ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፪ “ምእመናን አንድነቱን ሦስተነቱን ሕማሙን ሞቱን ለመስማት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በንጽሕና በጸጥታ ሁነው ሊቆሙ ይገባል” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ስለዚህ ሕመም ያለበት ሰው በመጀመሪያ በንጽሕና ሊቆሙ ይገባል ይላልና ንጽሕናውን አለመጠበቁ አንድ ጉዳይ ሲሆን ሌላው ደግሞ በጸጥታም ይላልና የሚስል ከሆነ፣ በሕመሙ የሚረበሽ ከሆነ እርሱም፣ ተረብሾ ሌላውንም ይረብሻልና በዚህ ወቅት በቤት ውስጥ መሆንና መጸለይ ግድ ይላል፡፡

አገልጋይ ካህን ቢሆንም እንኳን ደም የሚፈሰው ከሆነ፣ የማያቋርጥ ፈሳሽ ካለበት፣ ሌላም ለዐይነ ሥጋ የይመቹ ሁኔታዎች ካሉበት እንዲያገለግል አይፈቀድለትም፡፡ ስለዚህ ወደሌሎች የሚዛመት በሽታ ያለበት ከሆነ ሌላውን እንዳይጎዳ ሲባል ለጊዜው አገልግሎት እንዳይሰጥ ቢደረግ ጥፋት የለውም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “መሥዋዕተ ወቍርባነ ኢፈቀድኩ ሥጋከ አንጽሕ ሊተ፤ መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድሁም ሥጋህን አንጻልኝ።” (መዝ.፴፱፥፮) በማለት እንደነገረን እግዚአብሔር የውስጣችን ንጽሕና እንደሚያስደስተው ሁሉ የውጫችን ንጽሕናም ያስደስዋልና መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህ አስተምህሮ ስላላት ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የታመሙ አገልጋዮችን እንዲያገለግሉ አትፈቅድም፡፡

ንጽሕናን መጠበቅ ሲባል ንስሓ ገብቶ ውስጣዊ ንጽሕናው መጠበቅ እንዳለበት ሁሉ ውጫዊ ንጽሕናውንም መጠበቅ ያስፈልገዋል፡፡ በቅዱስ ወንጌል “አገልጋዮችም ወደ መንገድ ወጥተው ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉም ቤት በተጋባዦች ሞላ፡፡ ንጉሡም ተጋባዦቹን ሊያይ በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አገኘ፡፡ ወዳጄ ሆይ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ አለው ያም ሰው ምላሽ አጣ ከዚህም በኋላ ንጉሡ አገልጋዮቹን እጁንና እግሩን አስረው በውጭ ወዳለ ጨለማ ይጥሉት ዘንድ አዘዘ፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡ የተጠሩት ብዙዎች የተመረጡት ግን ጥቂጦች ናቸው፡፡” (ማቴ.፳፪፥፲-፲፬) ተብሎ እንደተጻፈ ንጹሕ ለብሶ ራስን ንጹሕ አድርጎ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ለጊዜው ንጹሕ መሆን የማንችልበት አጋጣሚ ካለ ግን የሰርግ ቤት የተባለችው ቤተ ክርስቲያን ናትና ወደ ሰው የሚተላለፍ ሕመም ይዘን፣ ንጹሕ ሳንሆን ብንገባ በንጉሡ አንደበት አስወጡትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ውሰዱት መባል ይኖራልና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ 

ሐ. በሽተኞችን መንከባከብ፡- በዚህ ዘመን የተከሰተው በሽታ የጤና ባለሙያዎች የሚሉንን ብቻ የምንከተል ከሆነ አብሮነታችንን የሚጻረር፣ እርስ በእርሳችን እንዳንተሳሰብ የሚያደርገን ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሃይማኖታችን ጽናት የምግባራችን በጎነት የሚለካው ደግሞ በዚህ ዘመን ነውና ተገቢውን ጥንቃቄ ባደረገ መልኩ ሕመምተኞችን ልንንከባከባቸው ይገባል፡፡ በቅዱስ ወንጌል “ብልና ነቀዝ በሚያበላሹት ሌቦችም ቈፍረው በሚሰርቁበት በምድር ለእናንተ መዝገብ አትሰብስቡ፡፡ ነገር ግን ብልና ነቀዝ በማያበላሹት ሌቦችም ቈፍረው በማይሰርቁት በሰማይ ለእናንተ መዝገብን ሰብስቡ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ በዚያ ይኖራልና፡፡” (ማቴ.፮፥፲፱-፳፩) ተብሎ እንደተጻፈ ብል የማይበላው ሌባ የማይሰርቀው፣ ወንበዴ የማይዘርፈው ሰማያዊ ሀብት ማከማቸት የሚቻልበት ዘመን እንደሆነ ልንረዳው ይገባል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ምጽአት ለቅዱሳኑ የሚመሰክርላቸው “ተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳም ሁኜ ተቀብላችሁኛልና፤ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፣ ታምሜ ጎብኝታችሁኛልና፤” (ማቴ. ፳፭፥፴፭) በማለት ሲሆን ኃጥኣንን ደግሞ እነዚህን ባለማድረጋቸው ይወቅሳቸዋል፡፡ ሕመምተኞች በዚህ ወቅት የማንደርስላቸው ከሆነ ይራባሉ፤ ይጠማሉ፤ ይታረዛሉ፣ ሕመሙም እየጸናባቸው ይሄዳል፡፡ ሕመሙ ከሚጎዳቸው በላይ ረኃቡ፣ ጥሙ፣ እርዛቱ፣ የሥነ ልቡና ጫናው ወዘተ የሚጎዳቸው ሊብስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ክርስትናችንን መሠረት ያደረገ በጎ ምግባር መሥራት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡

ሐ. መጸለይ፡– የጸናውን እምነት በውስጣችን ሰንቀን ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይኖርብናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” ብሎናል፡፡ ይህ ወቅት ታላቅ ፈተና የተከሠተበት ነውና ከዚህ ከተቃጣብን ፈተና ለመዳን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ አብዝተን መጸለይ ይኖርብናል፡፡

መ.ንስሓ መግባት፡- መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ ንስሐ ነው፡፡ ንስሐ ከሞት የድናል፤ ከእግዚአብሔር ያስታርቃል፤ በሕይወት እንድንኖር ያስችለናል፡፡“በዚያ ወራትም ሰዎች ወደ እርሱ መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለቀላቀለው ስለገሊላ ሰዎች ነገሩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “ይህቺ መከራ ስለ አገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ይልቅ ተለይተው ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሏችኋልን አይደለም፤ እላችኋለሁ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ፡፡ ወይስ በሰሊሆም ግንብ ተጭኖ የገደላቸው ዐሥራ ስምንቱ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ሰዎች ይልቅ ተለይተው ኃጢአተኞች ይምስሏችኋልን አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደነርሱ ትጠፋላችሁ፡፡” (ሉቃ.፲፫፥፩-፭) እንዲል፡፡

ከላይ እንደተመከትነው እስራኤላውያን ኃጢአታቸው ሲበዛ፣ በቸነፈር፣ በሞት ቀጣቸው፡፡ ንስሓ ሲገቡ ግን የተቃጣውን መዓት በምሕረቱ መለሰላቸው፡፡ ዳዊት በበደለ ጊዜ የታዘዘበት መዓት ቸነፈር ነበር በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ሞቱ፡፡ ነገር ግን ዳዊት በመሪር እንባ ወደ ፈጣሪው ሲያለቅስና በበደለው ጥፋት ሲጸጸት እግዚአብሔር የቃጣውን መዓት መለሰለት፡፡ ሰብአ ነነዌ ኃጢአታቸው እግዚአብሔርን በአሳዘነ ጊዜ እንዲሁ ሊቀጣቸው እንደሆነ በነቢዩ በዮናስ አማካኝነት ነገራቸው፡፡ የነቢዩን ቃል ሰምተው በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ እግዚአብሔር የተቃጣውን መዓት መለሰላቸው፡፡

ስለዚህ ዛሬም  ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ኵሉ ዐረየ ወኅቡረ ዐለወ አልቦ ዘይገብራ ለሠናይት አልቦ ወኢ አሐዱ፤ ሁሉም ተካክሎ በአንድነት በደለ አንድ ስንኳን በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም” (መዝ.፶፪፥፫) እንዳለ በደላችን እጅግ በዝቶ እግዚአብሔርን አሳዝኗል፡፡ ትልቁና ዋነኛው መፍትሔ ወደ እግዚአብሔር መመለስና እግዚአብሔርን መለመን ነው፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል “አሁንስ ይላል አምላካችሁ እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾም በለቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ቊጣው የዘገየ ምሕረቱም የበዛ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ” (ኢዩ.፪፥፲፪-፲፫) በማለት የእግዚአብሔርን ጥሪ እንዳስተላለፈልን ከልብ ሆነን በንስሓ ልንመለስ ያስፈልጋል፡፡ ሃይማኖት እንደሌላቸው ሰዎች እኛም ከምንጨነቅ ይልቅ እግዚአብሔር ወደ ንስሓ ሊጠራን ፈቅዶ ነው በማለት እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀምም ያስፈልጋል፡፡

ሠ. ሥጋ ወደሙን መቀበል፡- መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በአጽንኦት ያስተማረው ትምህርት ቢኖር የሥጋ ወደሙ ነገር ነው፡፡ ያለዚህ ሕይወት ሊኖረን እንደማይችል ዋናው ጉዳይ የክርስቶስን ሥጋ ወደሙ ተቀብለን በሕይወት መኖር እንዳለብን አስተምሮናል፡፡ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛይቱ ቀን አነሣዋለሁ፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ነውና፤ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ፡፡” (ማቴ.፮፥፶፬-፶፮)
እንዲል፡፡ የሰው ልጅ የመፈጠር ዓላማው የፈጣሪውን የአምላኩን ስም እየቀደሰ ክብሩን ወርሶ መኖር ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ከእኛ ጋር የሚኖርበትን እኛም ከክርስቶስ ጋር የምንኖርበትን መንገድ ከተነገረን ከክርስቶስ ጋር ከመኖር በላይ ምንም ነገር መፈለግ የለብንምና እየጸለይን በንስሓ እየተመላለስን፣ ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን መኖር ይጠበቅብናል፡፡

በአጠቃላይ ይህ ለዓለም ሕዝብ ሥጋት የሆነውን በሽታ ከመጠን በላይ በሆነ ፍርሃትና በአላስፈላጊ ጭንቀት ሳንደናገጥ አስፈላጊ የሆነውን ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል ይኖርብናል፡፡ ሙያውን የገለጸው ራሱ እግዚአብሔር ነውና የባለሙያዎችን ምክር ሳናቃልል በተግባር በማዋል በዋናነት ግን ከመቸውም በበለጠ ሃይማኖታችንን በማጽናት እግዚአብሔርን ልንለምነው ይገባል፡፡ በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር እየሠራን የምንጋፈጣቸው ችግሮች በስተጀርባቸው በረከት ይዘው ይመጣሉና አደገኛነቱን ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ጸንተን ብንቀበለው በረከት እንዳለውም ማሰብ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁ በቸልተኝነት ሳንመለከት ወደ እግዚአብሔር እየጸለይን የሚመጣውን በጸጋ መቀበል በኃጢታችን የመጣም ከሆነ አቤቱ ይቅር በለን በማለት መዓቱን በምሕረት እንዲመልስን መለመን ግድ ይለናል፡፡ በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር ሠርተን አምላካችንን ለምነነው ከመጣው መዓት እንዲሠውረን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ጥበቃ፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን፤አሜን፡፡