“ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ በሰላም ትኖራላችሁ” (ሐዋ.፲፭፥፳፰)
ሐዋርያት በወቅቱ ደቀ መዛሙርቱን የላኳቸው መልእክት እንዲህ የሚል ነበር። “ሥርዓት እንዳናከብድ፤ ሌላም ሸክም እንዳንጨምር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋራ ነውና ነገር ግን ይህን በግድ ትተው ዘንድ እናዝዛችኋለን። ለአማልክት የተሠዋውን፣ ሞቶ የተገኘውን፣ ደምንም አትብሉ፤ ከዝሙትም ራቁ፤ በራሳችሁ የምትጠሉትንም በወንድሞቻችሁ ላይ አታድርጉ፤ ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ በሰላም ትኖራላችሁ”፡፡(ሐዋ.፲፭፥፳፰-፳፱)፤ሐዋርያት ለሕዝቡ ከመጨነቃቸው የተነሣ “ሥርዓት እንዳናከብድ ሌላም ሸክም እንዳንጨምር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ነውና” በሚል መልእክቱን ልከዋል፡፡ ዛሬም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፈውን መመሪያ መስማት ከምእመናን ይጠበቃል። በምእመናን ላይ ሥርዓት እንዳይከብድ፣ ምእመናኑ በመጣው መዓት እንዳይደናገጡ፣ ባልጸና እምነታቸው የመጣውን መዓት መቋቋም ተስኗቸው ከቤቱ እንዳይወጡ በማዘን ነውና ቃላቸውን ሊሰማ ይገባል።