ዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ

‹‹ታጠቡ ንጹሐንም ሁኑ›› /ት.ኢሳ. ፩፡፲፮/

……ካለፈው የቀጠለ

ምን እናድርግ?

በእምነት ውስጥ የሚኖር ሕዝብ እና ሃይማኖት ያለው ሕዝብ ምንጊዜም ክፉ ነገር ሲከሰት ወደ ፈጣሪው ይጮሀል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት አምልኮተ እግዚአብሔር ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ስለዚህ የመጣውን መቅሰፍት ለማስቀረት የሚከተሉትን ሥራዎች መሥራት እንደሚጠቅም እናምናለን፡፡

ጸሎት ማድረግ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በምንም አትጨነቁ፤ ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ፤ ማልዱም፤ እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ›› /ፊልጵ. ፬፥፮ / እንዲል ሳይጨነቁ እግዚአብሔርን አዎ በድያለሁ፤ ይቅር በለኝ ብሎ ወደ ፈጣሪ መጮህ መፍትሔን ያመጣል፡፡ በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላልና፡፡

ቅዱስ ያዕቆብም ጸሎት በሽታን እንደሚፈውስ ይገልጻል፤ ‹‹ወእመቦ ዘይደዊ እምኔክሙ ለይጸውዕ ቀሳውስተ እለ ውስተ ቤተ ክርስቲያን ከመ ይጸልዩ ላዕሌሁ ወይቅብዕዎ ቅብዐ ጸሎት በስሙ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወጸሎተ ሃይማኖት ያሐይዎ ለድውይ ወያነሥኦ እግዚአብሔር ወእመኒ ቦቱ ኃጢአት ይትኃደግ ሎቱ፤ የታመመ ሰው ቢኖር ይጸልዩለት ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትን ይጥራ፤ ጸሎት በሃይማኖት ድውዩን ያድነዋልና፤ እግዚአብሔርም ያነሰዋል፤ ኃጢአትም ቢኖርበት ትሰረይለታለች›› / ያዕ.፭ ፥፲፬/ በማለት ሰው ተጸጽቶ ፈጣሪውን ከለመነ ከጠየቀ ምላሽ እንደሚያገኝ ቅዱስ ቃሉ ያስተምረናል፡፡

ጌታችን በጥንተ ስብከት ሐዋርያትን ሁለት ሁለት አድርጎ ወደ አገር በላካቸው ጊዜ ድውያኑን ይቀቧቸው እና ይድኑ እንደነበር እነሆ ቅዱስ ወንጌል ይመሰክራል /ማር. ፮ ፥ ፯-፲፫/ ፤ በቀደመ ሥራቸው ሐዋርያት አእምሮውን ካሳጣው ሰው ጋኔን ማውጣት ቢያሸንፋቸው ያድነው ዘንድ ወደ ጌታችን አደረሱት፤ ስለ እርሱ ጌታ ተናገረ፤ ያለ ጾም እና ያለ ጸሎት ይህንን ዘመድ ወይም ሰይጣን ማስወጣት አይቻላቸውምና፡፡ / ማቴ. ፲፯፥፲፯ ፳፩/

ነቢዩ ዳዊትም በመዝሙሩ መጽሐፍ በድኃውና በችግረኛው ላይ የሚያስታውል ሰው ብፁዕ ነው አለ፤ እግዚአብሔርም በተኛበት አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ እርሱ በታመመበት አልጋ ሳለ ደዌውን ይለውጥለታል፡፡ / መዝ. ፵፥፩/ መጽሐፈ ነገሥትም ስለ ደዌው የአፍሮንን አምላክ ይጠይቅለት ዘንድ የላከውን አካዝያስን እግዚአብሔር እንደዘለፈው በዚያን ጊዜም ፈጥኖ እንደገደለው ይናገራል፡፡ / ፪ኛ ነገ. ፩፥፪/

እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚችል የሁሉ መድኃኒት ነውና ቅዱስ ያሬድ ‹‹እስመ እግዚአብሔር ዐቃቤ ስራይ ውእቱ በመለኮቱ ወፈውሰ ድውያን ውእቱ በትስብእቱ፤ እግዚአብሔር በመለኮቱ መድኃኒት ቀማሚ በሰውነቱ ደግሞ የተቀመመ መድኃኒት ነው›› እንዲል፡፡

ሕላ መያዝ

‹‹ክፉ ነገር ፣ የፍርድ ሰይፍ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤት እና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮሀለን፤ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ አሉ›› /መ.ዜና መዋዕል ካልዕ ፳፥፱ / እንዲል ለሁሉም ነገር በኅብረት ወደ ፈጣሪ በመጮህ ክፉውን ነገር  ማስወገድ ይቻላል፡፡

ማዕጠንት ማጠን

ዕጣን በቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ የአምልኮ መግለጫ ነው፤ በተለይም ጸሎትን ለማሳረግ ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ‹‹የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ››/ ራዕ. ፰፥ ፬ / እንዲል፣ የጠፋው የክርስቶስ መስቀል የተገኘው በዕጣን ነው፤ አሁንም የጠፋው መድኃኒት የሚገኘው በእግዚአብሔር ነው፤ ምክንያቱም ማዳን የእግዚአብሔር ነውና፡፡

የቅዱሳንን እምነት እና ጸበል መጠቀም

በልዩነት በበሽታ በተለይም በወረረሽኝ እና በተላላፊ በሽታዎች ቃል ኪዳን ለተገባላቸው ቅዱሳን የእነሱን እምነት መቀባት፣ጸበላቸውን መጠጣት፣ በጸበላቸው መጠመቅ መድኃኒት ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ሁሉም ቅዱሳን ከአምላካችን ከልዑል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለዋል፤ ሁሉም ቅዱሳን ያድናሉ፤ ይማልዳሉ፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያናችን ገድላቸው እንደሚገልጸው ቅዱስ ቂርቆስ፣ አቡነ ሀብተ ማርያም እና አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ተላላፊ በሽታ እንደሚያድኑ ቃል ኪዳን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስለሆነም የቅዱስ ቂርቆስን፣ የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን እና የአቡነ ሀብተ ማርያምን ገድል ማንበብ፣ በቤታችን ማስነበብ፣ የእነዚህን ቅዱሳን እምነት እና ጸበል መጠቀም፣ በቃል ኪዳናቸው መማጸን በሽታን ለመከላከል ይጠቅማል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ‹‹ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፤ መቅሰፍትም ወደ ቤትህ አይገባም፤ በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና›› /መዝ. ፺፩፥፲ እንዲል በመንገድህ ማለቱ በሕይወትህ ሲል ነው፤ መላእክቱን፣ ቅዱሳንን ማለቱ ነው፡፡የቅዱሳኑን እምነት መቀባት፣ ጸበል መጠጣት፣ መልክእ መድገም እና ገድል ማንበብ በሽታውን ለመከላከል ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክም አባቶቻችን ችግሮች ሲከሰቱ መፍትሔ ለመፈለግ ቅዱሳን አባቶችንን መመኪያ በማድረግ ነው፡፡ ለአብነትም ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ይዘው ጣሊያንን ድል ነስተዋል፡፡

ጥንቃቄ ማድረግ

የጤና ባለሙያ ምክሮች ትምህርተ ሃይማኖት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፤ ለሰው ልብ ማስተዋልን የሚሰጥ፣ ጥበብንም የሚገልጽ እግዚአብሔር ነውና፡፡ እምነት አለኝ ብሎ እሳት የሚጨብጥ የለም፤ ስለሆነም ከፍጡር የሚጠበቀውን ማድረግ አዋቂነት ነው፡፡ በሀገራችን ሞኝን ሁለት ጊዜ እባብ ይነድፈዋል ይባላል፤ ይኸውም አንድ ጊዜ ሲያይ፣ሌላ ጊዜ ሲያሳይ ነው፡፡ ከፍጡር የሚጠበቀውን ሳናደርግ ፈጣሪ ይጠብቀናል ካልን ፣ ያለን ፍጹም እምነት ምን ያህል እንደሆነ መፈተሽ ይገባል፡፡ መጠንቀቅ ግን አለማመን አይደለም፤ ለዚህ ደግሞ የዘወትር የአቡነ ዘበሰማያት ጸሎታችን ‹‹ወደ ፈተና አታግባን›› ምስክራችን ነው፤ ጥንቃቄ ይጠብቃል፤ ማስተዋልም ይጋርዳልና፡፡

ትእዛዝን ተቀብሎ መተግበር

ሁሌም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያዘውን ትእዛዝ ተግባራዊ ማድረግ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፤ ሰው ሁሉ በበላይ ላሉ ባለሥልጣኖች ይገዛ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና ያሉትም ባለስልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፤ ለባለሥልጣን አልገዛም ያለ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንቢ ማለቱ ነው መገዛትን እንቢ የሚሉም በራሳቸው ላይ ቅጣትን ያመጣሉ /ሮሜ. ፲፫ ፥፩ / እንዲል ቃሉ አባቶች የሚሉትን መመሪያ መተግበር ይገባል፡፡

ራስን አለመጠበቅ እና አለመጠንቀቅ ዋጋ ያስከፍላል፤ ‹‹ዐዋቂ ሰው ክፉ ሰው በኃይል ሲቀጣ አይቶ ይገሰጻል፤ አላዋቂዎች ግን ሲያልፉ ይጎዳሉ››/መ.ምሳሌ ፳፪፥፫ / እንዲል ይህ መቅሰፍት የመጣው ለተግሳጽ ለትምህርት ነው፤ ተግሳጹን አይቶ ትምህርት መውሰድ ደግሞ አዋቂነት ነው፡፡

አባት እርፍ ሲያነሳ ልጅ ድግር ሊሸከም ይገባዋል፤ ስለዚህም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የልጅነት ግዴታችን ነው፤ መከራ የሚደርስብን እንድንማርበት እንጅ እንድንማረርበት አይደለም፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እናንተ ግን ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የመንግሥት እና የክህነት ወገን፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱም የተለየ ወገን ናችሁ›› /፩ኛ.ጴጥ. ፪ ፥ ፱ / ይላል፤ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን አዳኝነት የሚመሰክሩ ቅዱሳን ናቸው፡፡ በዚህ ምድር ሲኖር ደግሞ ክርስቲያን ከኃጢአት በስተቀር የመንግሥቱም ሆነ የክህነቱም ወገን በመሆኑ ሁለቱም የሚመለከተው በመሆኑ ከቤተ ክህነት የሚሰጡ መመሪያዎችን ተቀብሎ ጥንቃቄ የሚያደርግ የተመረጠ ትውልድ ነው፤ እንዲሁም ከመንግሥትም የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ይገባዋል፡፡

የእግዚአብሔርን ቃል ብንፈጽም፤ ለእግዚአብሔር የሚበጀውን ብናደርግ፤ ትእዛዙን ሰምተን ብንፈጽም፤ ሥርዓቱን ሁሉ ብንጠብቅ ኖሮ ይህ ሁሉ መረበሽ ባልነበር፡፡ አሁንም በንስሓ ሳሙና ታጥበን እግዚአብሔርን እንለምነው፤ የመጣው ቁጣ፣ በሽታ፣ ወረርሽኝ ይመለሳል፤ እርሱ እግዚአብሔር ቸርና ነውና ከቁጣ ወደ ምሕረት ይመለሳል፡፡

 ‹‹እርሱም አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፣ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፣ ትእዛዙንም ብታዳምጥ፣ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፡፡ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና›› /ኦ.ዘፀ. ፲፭፥፳፮/ ይላልና ወደ እግዚአብሔር እንጩህ፡፡

እግዚአብሔርን ይዞ ያፈረ የለም የታመነ አምላክ ነውና፤ በእግዚአብሔር የሚታመን፣ የእግዚአብሔርን ቃል የሚፈጽም፣ ትእዛዙን የሚተገብር ከምድር ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ረጅም ዕድሜን ያገኛል፤ ሰላምን ይጎናጸፋል፤ ጉስቁልናን ያስወግዳል፤ ፍጹም ጤናን ይሰጣል፤ የተሰበረ ልብንም ይጠግናል፤ ‹‹ዛሬ ያዘዝሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት፤ ብታደርጋትም እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጅ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጅ በታች አትሆንም፡፡›› /ኦ.ዘዳግም. ፳፰ ፥፲፫/

ሰባት አጋንንት የወጡላት ማርያም መግደላዊት ከዲያቢሎስ ቁራኝነት ተላቃ ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ጋር ትቆጠራለች ብሎ ማን አሰበ?

ሰባት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት የደሟ ምንጭ እንደሚደርቅ ማን አሰበ?

ዮናስ ከዓሳ ነባሪ ሆድ ወጥቶ በሕይወት እንደሚኖር እና ሕዝቡን እንደሚያስተምር ማን ገመተ?

ነህምያ ከምርኮ በኋላ የኢየሩሳሌምን ቅጽር እንደሚሰራ ማን ጠበቀ?

ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ የዓይን ምልክት ያልነበረው ሰው ዓይን እንደሚሰራለት ማን አስተዋለ?

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሚያድነው የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ሁሉ ዘንድ ታውቋልና እርስዋም ከኃጢአት እና ከዓለም ፍትወት እንለይ ዘንድ በዚህ ዓለምም በጽድቅ፣ በንጽሕናና በፍቅር እንኖር ዘንድ ታስተምረናለች››/ቲቶ. ፪፥፲፩/ እንዳለን የሚያድነን ጽድቅ መሥራት ነው፤ የሚያድነን በፍቅር መኖር ነው፤ የሚያድነን ከኃጢአት መለየት ነው፤ የሚያድነን ከፍትዎት መለየት ነው፤ የሚያድነን በንጽሕና መኖር ነው፡፡

‹‹ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብል እና በመጠጥ፤ በመቀማጠል እና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያች ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች›› /ሉቃ .፳፩፥፴፬/ እንዲል ቅዱስ ቃሉ አሁን ላይ በዚህ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሽዎች የሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች ሞትን እየተጎነጩ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በሽታው ለአስታማሚ፣ ለጠያቂም ሆነ ለቀባሪም የማይመች  በድንገት እንደሚወስድ ጎርፍ ነው፡፡ ስለዚህ በቶሎው ንስሓ ገብቶ ተጸጽቶ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ይገባል፡፡

 ኮሮና ቫይረስ ዓለም አቅሙን ያወቀበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት  ከበሽታና ከሞትም ለመዳን ራስን በንጽሕና መጠበቅ፣ በነፍስ በኩል ደግሞ ከኃጢአት ራስን ማንጻት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ  በመንፈሳዊ ሕይወት በሰላም ለመኖር ራስን ማንጻት እንደሚገባ ቅዱስ ቃሉ ያስተምረናል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ክፋትን ማስወገድ እንዳለብን፣ ክፉ ማድረግን መተው እና መልካም መሥራትንም መማር እንደሚገባ፣ መታጠብና መንጻት አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምራል፤ ‹‹ታጠቡ ንጹሐንም ሁኑ፤ የሰውነታችሁን ክፋት ከዐይኖቼ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግንም ተው፤ መልካም መሥራትንም ተማሩ፡፡›› /ት.ኢሳ. ፩፥፲፮/

አካላዊ ጤንነታችንን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ጤንነታችንንም እንጠብቅ ፡፡

አካላዊም መንፈሳዊም ንጽሕናችንን ጠብቀን እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን፡፡