“ጽና፥ እጅግም በርታ” (መጽሐፈ ኢያሱ ፩፥፯)

በረቂቅ መቻል

እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጅ አብዝቶ ሲበድል ሌላ ጊዜ ደግሞ የሰውን ልጅ ለበለጠ ዋጋ ማዘጋጀት ሲፈልግ መቅሰፍትን ወደ ምድር ይልካል፡፡ በበደል ምክንያት የሚመጣው መቅሠፍት አሁን ዓለምን እያስጨነቀ ያለው ኮሮና በሽታ አይነት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሰዓት እኛም በክርስቶስ ክርስቲያን የሆንን የክርስቶስ ልጆች እንደመሆናችን መጠን በጾም በጸሎት ይህን የመከራ ጊዜ ልናንልፍ ይገባል፡፡

የእግዚአብሔር ምሕረት አይለየን እንጂ በርካቶቻችን ላለፉት ዓመታት ፈጣሪያችንን፣ ሰዎችን ብሎም ደግሞ እናት የሆነችውን ቅድስት ሀገር አብዝተን ስንበድል ከርመናል፡፡  የምናደርገውን ባለማወቅ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ይልቅ የራሳችንን ፍላጎት እያስቀደምን ሀልዎተ እግዚአብሔርን ዘንግተን አልያም መኖሩን እያወቅን በድፍረት ኃጢአት ሠርተናል፡፡ አሁን ግን ጊዜው የእግዚአብሔር ቁጣ የተገለጠበት ሆኗል፡፡ ይህን ያዩ ዐይኖቻችን ማመንና መገዛት ስላቃታቸው እግዚአብሔር በብዙ ነገር አለመብቃታችንን ሊያስረዳን ይፈልጋል፡፡

ኃያላንና ብርቱዎች በገንዘባቸውና ባላቸው ቁሳዊ ነገር ሁሉ ይህን መቅሠፍት ይመክቱታል ብለው አንዳንድ ሰዎች ያስባሉ፡፡ እግዚአብሔር ለደከሙና ለጦም አዳሪዎች ቸርነቱን እንደሚያበዛ ግን አልተረዱም፡፡ አሁን የመጣብንም ደዌ ዘመቅሠፍት ኃያላኑንና ድሀ አደጉን እኩል የሚያደርግ ሆነ፡፡  ለመጣብን መከራ መዳኛ የሚሆነን በአባቶች መሪነት ወደ መንፈሳዊ ስፍራ የሚያደርሰንን ምግባር ማከናወን ብቻ ነው፡፡

ምድራዊ ሀገራችን ቤተክርስቲያን እንደመሆንዋ ሲከፋንም ሆነ ሲጨንቀን ወደ ዐጸዷ በመሄድ የምንማጸንባት፣ በመከራ ጊዜ የምንሸሸግባት እና እውነተኛ ሐሤትንና ዕረፍትን የምናገኝባት የዘለዓለም ቤታችን እንደመሆንዋ ዛሬ ከእርሷ መራቃችን ሊያስከፋን ይገባል፡ይህም የክርስቲያን ጦራችንን በአግባቡ ታጥቀንና ይዘን ለዚህ ክፉ ቀን መጠቀም ባለመቻላችን ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ምዕራፍ ፮፥፲፩-፲፪ ላይ “የሰይጣንን ተንኮል መቋቋም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ፡፡ ሰልፋችሁ ከጨለማ ገዦች ጋርና ከሰማይ በታች ካሉ ከክፉዎች አጋንንት ጋር ነው እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና” እንዲል፡፡

በክርስቶስ ክርስቲያን የሆንን ሁሉ ባለፉት ዓመታት ያሳለፍነውን መከራ ማሰብ ይገባል፡፡ ነገን ለመኖር ትናንትን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ከትናንት ስሕተታችን ተምረን እግዚአብሔርን የምናገለግል ሰዎች መሆን እንዳለብን በማሰብ ልንዘጋጅ ይገባል፡እግዚአብሔር በምክንያት ስለፈጠረን አገልጋዮቹ በመሆን በተሰጠን ሰውነትና ሀብተ ክርስትና በአግባቡ የምንጠቀም ሰዎች መሆን አለብን፡፡

በመጽሐፈ ኢያሱ እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፤ “ኢያሱም የሕዝቦቹ አለቆች በሰፈሩ መካከል አለፉ፤ ሕዝቡም አምላካችሁ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር እስከ ሦስት ቀን ይህንን ዮርዳኖስ ተሻግራችሁ ልትወርሱት ትገቡበታላችሁ፣ ስንቃችሁን አዘጋጁ ብላችሁ እዘዙአቸው ብሎ አዘዘ”፡፡ (መጽ.ኢያ. ፩፥፲-፲፪) ያን ጊዜ ትእዛዙን ሁሉም ተቀብለውት ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ እኛስ አባቶችና ቅድስት ቤተክርስቲያን በየቀኑ የምትሰጠንን ትምህርትና መመሪያ ተግባራዊ አድርገን ይሆን?

በታሪኩ ውስጥ ስለ ኢያሱ መሪነትና ስለሕዝቡ ተመሪነት፤ መግባባትና በመታዘዝም የሚገኘውን ዋጋ እንመለከታለን፡፡ “ኢያሱም የሮቤልን ልጆች የጋዳንም ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌቶቹን  እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፤ የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስቡ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ያሳርፋችኋል፤ ይህችን ምድር ይሰጣችኋል፤ ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ ምድር ይቀመጡ፡፡ ነገር ግን እናንተ ጽኑዓን ኃያላን ሁሉ ተሰልፋችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ተሻገሩ፤ እርዱአቸውም፤ እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፋችሁ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፡፡ እነርሱም ደግሞ አምላካችሁ እግዚአብሔር ባርያው ሙሴን በፀሐይ መውጫ ወደተሰጠችው ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ፤ ትወርሱማላችሁ፡፡ እነርሱም ለኢያሱ መልሰው እንዲህ ብለውታል፡፡ “ያዘዝከንን ነገር ሁሉ እናደርጋለን፤ ወደምትልከንም ስፍራ እንሔዳለን፤ በሁሉም ለሙሴ እንደታዘዝን እንዲሁ ለአንተ ደግሞ እንታዘዘላን፤ ብቻ አምላክህ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር እንደነበር ከአንተ ጋር ይሁን፡፡ በትእዛዝህ የሚያምጹ  የምታዘውንም ቃል ሁሉ የማይሰሙ እነርሱ ይገደሉ፤ ብቻ አንተ ጽና አይዞህ፡፡” (መጽ.ኢያ.፩፥፲፪-፲)

ይህ የመጽሐፍ ክፍል ለኛ የሚሆነንን እና ከወቅቱ ጋር የሚጠቅመንን ትልቅ መልእክት ይዟል፡፡ በሁላችን ልብ የሚኖረው እግዚአብሔርን መወደድን ከፈለግን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን መሪነት የመረጥናቸውን የቤተክርስቲያን መሪዎችን ሐሳብ ማድመጥና መተግበር ያስፈልጋል፡፡

የኢያሱ ተከታዮች የቀደመውን ሙሴንና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በማስተዋል እየጠበቁ ስለነበር የሚሰጣቸውን መመሪያ ከመተግበር አልፈው መሪያቸው እንዳይዝልባቸው ሲያበረቱት  በሐሳብ ሲደግፉት እንዲሁም ጊዜውን ለመሻገር በወጣው መመሪያ መሠረት የማይራዱትንም ሲያወግዙና ሲገዝቱ አስተውለናል፡፡ እኛስ ከኮሮና ጋር ተያይዞ ይህንን ክፉ ሰዓት ልታሻግረን በቆመችልን የቅድስት ቤተክርስቲያንና የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ምን ያህል ተግብረናል? ምን ያህል ጸንተን በመቆም እኛን ለማዳን ቀን ከሌሊት በጸሎት የሚደክሙልንን አባቶች በሐሳብና በመታዘዝ አብሮነታችንን አሳይተን ይሆን?

ይህ ደዌ መቅሠፍት ከሀገራችንም ሆነ ከምድራችን የሚርቅበት ጊዜው ስለማይታወቅ እኛ በምግባራችንና በክርስትናችን ጸንተን ሌሎችን የምናጸና ሰዎች ልንሆን ይገባል፡፡ በአሁኑ ሰዓት እያስጨነቀን ያለውን ፈተና ያለቸልተኝነት በመተጋገዝ እና በመረዳዳት በየደረጃው የሚሰጡንን ምክሮችና አቅታጫዎች በመተግበር ባለንበት ጸንተን እንድንኖርና እግዚአብሔርም በግብጽ  የነበረውን መከራ በእውነት እንዳየው የኛንም መከራ አይቶ በዓይነ ምሕረቱ እንዲመለከተን እንማፀን፡፡