የካቲት ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ የታነፀች፣ ከሁሉ በላይ የሆነች አንዲትና ቅድስት አካለ ክርስቶስ ናት (ኤፌ. ፩፥፳፪፤ ኤፌ. ፪፥፳)፡፡ ‹‹ከሁሉ በላይ የሆነች›› የሚለው ሐረግ ሰማያዊ ሥልጣኗን እና ልዕልናዋን የሚገልጽ ነው፡፡ ይህም ማለት የትኛውም ቅዱስ መጽሐፍ ወይም ንዋይ በእርሷ ውስጥ ይሆናል እንጂ ከበላይዋ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የገለጸውን እውነት የያዘ እንጂ ከቤተ ክርስቲያን በላይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ስለሆነች ከክርስቶስ አካልነት በላይ የሆነ ስለሌለ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን በላይ ያለ የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ቆላ. ፩፥፲፰)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የመጻሕፍት ሁሉ ራስ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ናት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቋንቋ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የተጻፈውም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ነው፡፡ ጸሓፊዎቹ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው፡፡ በቅድስናቸው ለእግዚአብሔር ቅሩባን ስለሆኑ የእግዚአብሔር ቃል ለሚላክላቸው አብያተ ክርስቲያናት በሚገባቸው ቋንቋ ጽፈዋል፡፡ መጻፋቸውም የእነርሱን ክብር ለመግለጽና ቤተ ክርስቲያን የምትመራበትን ሕግ ለመደንገግ ሳይሆን ቤተ ክረስቲያን የምታምነውን እምነት ለመመስከርና በመንፈሳዊ ሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ያሉ ምእመናን እንዲመከሩበት፣ እንዲገሠጹበት፣ ልባቸውን እንዲያቀኑበት ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የገለጠውን እውነትና ቤተ ክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር የምታምነውን እምነት የያዘ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተሰፍሮና ተቈጠይሮ ሁሉ ነገር የተካተተበት ማለት አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በማየት፣ በማድረግ፣ በቃል የሚተላለፍ ብዙ ሀብት አላት፡፡ እንዲያውም የተጻፈው በጣም ጥቂቱ ነው፡፡ ሆኖም በአንዳንድ የእምነት ድርጅቶች ዘንድ ነገረ ቤተ ክርስቲያንን በሙሉ ጠቅልሎ በመጽሐፍ ሥር የማድረግ የተሳሳተ አካሔድ አለ፡፡ ይህም በሉተራውያን ዘንድ “Sola Scriptura” ወይም “Only Bible” (መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ) ተብሎ የሚታወቀው ሲሆን ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊትም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የማይደግፈው ግለሰባዊ አሳብ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አይደለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን የምትቀበልበትን ሃይማኖታዊ እይታ በግልጽ ማሳየት ነው፡፡
የቅዱሳት መጻሕፍት ጥንተ ታሪክ
ፈጣሬ ኵሉ ዓለም እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ እጅግ አክብሮ የፈጠረው የሰው ልጅን ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን ክብሩን ሲገልጹ ሰውን “የፍጥረታት አክሊል – The Crown of Creation” ብለው ይጠሩታል፡፡ የፍጥረታት አክሊልነቱም በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ መፈጠሩ፣ ፍጥረታትን ሁሉ ከእግዚአብሔር በታች እንዲገዛ በፍጥረታት ላይ መሠልጠኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር “ሥሉጥ በላዕለ ኵሉ ፍጥረት፤ በፍጥረት ሁሉ ላይ የሠለጠነ (ሥልጣን ያለው)” እንደሆነ ሁሉ ሰውንም በጸጋ “ሥሉጥ በላዕለ ኵሉ ምድር፤ በምድር ሁሉ ላይ የሠለጠነ (ሥልጣን ያለው)” አድርጎታል፡፡ በጥንተ ተፈጥሮው የሰው ልጅ መጻሕፍትም ሆኑ መምህራን የማያስፈልጉት ዐዋቂ ፍጥረት ነበር፡፡ እንደ አባ ማቴዎስ በአእምሮ ጠባይዕ፣ እንደ አብርሃምና እንደ ሙሴ ጸሊም በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ የሚያውቅ ማለት ነው (ትርጓሜ ወንጌለ ዮሐንስ)፡፡ በለባዊ አእምሮው ሥነ ፍጥረትን አንብቦና መርምሮ ረቂቁን እውነት የሚረዳ ከሃሊ ዘበጸጋ ነበር፡፡ የሰው የመጀመሪያ መጽሐፍም ሥነ ፍጥረት ነው፡፡ ለሰው የመጀመሪያ እውነተኛ መምህሩ መምህረ ኵሉ ዓለም እግዚአብሔር ነው፡፡
እግዚአብሔር ለአዳም ትእዛዛቱን አስተማረው፡፡ ከመጀመሪያ ትምህርቶቹም ዋናው “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” (ዘፍ. ፪፥፲፮-፲፯) የሚለው ነበር፡፡ አዳም ግን እውነተኛ መምህሩን ትቶ የክፉ ፍጡር ትምህርትን ተማረ፤ “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” (ዘፍ. ፫፥፬-፭) ብሎ ሰይጣን የነገረውን ሰማ፡፡ ተማሪው ከሁለቱ ትምህርቶች ሁለተኛውን መረጠና በፈተና ወደቀ፡፡ የመጀመሪያ መምህሩን ትምህርት ይረዳም ዘንድ ከዚያ በኋላ ብቁ ልቡና አልነበረውም፡፡ ወደ ታላቁ መምህር ለመመለስ ሌሎች መምህራን እንዲደግፉት ግድ ሆነ፡፡
ክፉው መምህር ካሳታቸው በኋላ አዳምና ሔዋን ያልተጻፈውን ፊደል አዩ፣ ያልተከተበውን አነበቡ፡፡ “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች” (ዘፍ. ፫፥፮) እንዲል፡፡ ከዚህም በኋላ ፍጥረታትን የሚያነቡ ሳይሆኑ ፍጥረታት የሚያስደነግጡአቸው ድንጉጦች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ካደላቸው ከንጽሐ ጠባይ ደረጃ ስለወደቁና ወደ ቀደመ ክሂሎታቸው መመለስ ስላልቻሉ በሰውኛ ፊደል የተጻፉ መጻሕፍትን በማንበብ መመርኮዝ ግድ ሆነባቸው፡፡ የሰው ልጅ ፍጡር ባልሆነ ብርሃን ረቂቁንና የማይታየውን ዓለም ከማየት እና በማየት ከሚገኘው ዕውቀት ከመስማት ወደሚገኘውና ውስን ወደሆነው ዕውቀት በመውረዱ ምክንያት መጽሐፍ አስፈለገው፡፡ ስለዚህ መጻሕፍት የሰው የባሕርዩ መምህራን አይደሉም፡፡ ከውድቀቱ በኋላ የተሰጡት ደጋፊዎች እንጂ፡፡ ይህንም የቤተ ክርስቲያን መምህራን በሚከተለው ምሳሌ ይገልጹታል፤
ሰው የሚራመደው በሁለት እግሩ ነው፡፡ እግሩን ሲታመም ወይም ሲያረጅ በሁለት እግሩ መራመድ ስለሚያቅተው ምርኩዝ ይይዛል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሰው በቅድመ ተፈጥሮው በራሱ መቆምና መራመድ የሚችል ነበር፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ካረጀና ከታመመ በኋላ መቆምም መራመድም ይችል ዘንድ መጻሕፍትና መምህራን ምርኩዝ እንዲሆኑት ተሰጡት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው ይህን ይበልጥ ሲያብራራልን “በቀለም ከተቀረፁ የመጻሕፍት ቃላት ይልቅ በልቡናችን ያደረ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይመራን ዘንድ እጅግ ንጹሕ ሕይወት ሊኖረን እንጂ የተጻፈ ነገር ሊያስፈልገን አይገባም ነበር” ብሏል፡፡ ይህን ካለ በኋላ ግን መጻሕፍትን በጥንቃቄ መያዝ እንደሚገባን ሲያስተምረን “ይህን ጸጋ ከእኛ እንዲርቅ አድርገናል፡፡ እንግዲህ ሁለተኛውን ታላቅ ስጦታ (መጻሕፍትን) አጥብቀን እንያዝ” ብሏል፡፡ ይህ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ከጊዜ በኋላ አስፈላጊ በመሆናቸው የተሰጡ እንጂ ሁሉ ነገር ከእነርሱ የጀመረ አለመሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
ወንጌል ከተጻፈውም በላይና የቀደመች እንደሆነች
ብዙ ጊዜ ወንጌል ስንል አራቱ የወንጌላውያን መጻሕፍት ብቻ ቀድመው ይታሰቡን ይሆናል፡፡ አንዳንድ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚሉ የእምነት ድርጅቶች እንደሚሉትም የተጻፈው ብቻ ወንጌል የሚመስለንም እንኖር ይሆናል፡፡ የተጻፈውም ሆነ ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ግን ወንጌል በጽሑፍ ብቻ የተገደበ እንዳልሆነ ያስተምረናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤” ሲል አራቱ ወንጌላት ተጠቃለው አልተጻፉም ነበር (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፩)፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል” ብሎ ስለ ማርያም እንተ ዕፍረት በመሰከረ ጊዜ ማቴዎስም፣ ማርቆስም፣ ሉቃስም፣ ዮሐንስም ገና ወንጌልን አልጻፉም ነበር (ማቴ. ፳፮፥፲፫)፡፡ ይህ ቃል በተነገረ ጊዜ እንኳን ወንጌልን ሊጽፉ እምነታቸውም የተሟላ አልነበረም፡፡ ይህም በመከራው ጊዜ ከዮሐንስ በስተቀር ሁሉም በመሸሻቸው ተገልጧል፡፡ ስለዚህ ጌታ “ይህ ወንጌል” ሲል የተጻፈውን ብቻ የምናስብ ከሆነ ስሕተት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ወንጌል በቃልም፣ በመጽሐፍም፣ በሕይወትም የምትሰበክና የተሰበከች እንጂ በመጻሕፍት ተጠቃላና ተካትታ የተቀመጠች ብቻ አድርጎ ማሰብ ስሕተት ነው፡፡ ሐዋርያት በቃልም በመጽሐፍም ሰብከዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በሕይወቱ ባገኘው መገለጥ ተሰብኳል (ሐዋ. ፱)፡፡ እንዲያውም የቅዱሳት መጻሕፍት ጸሐፍያን በጽሑፍ የተሰበከው ጥቂት መሆኑንና በቃል ብዙዎች እንደተሰበኩ ገልጸዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ጽፎ ሲያጠቃልል “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” (ዮሐ. ፳፩፥፳፭) የሚለው ሁሉ ነገር አለመጻፉን ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ከተጻፉት በላይ ቤተ ክርስቲያን በትውፊት ያቆየችልን ብዙ ነገር መኖሩን መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ቅዱስ ሉቃስም ገና ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር ለሚጽፍለት ቴዎፍሎስ ለተባለው ሰው “የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርከው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ” (ሉቃ. ፩፥፩-፬) ብሏል፡፡ ይህ በዓይን ያዩ፣ ወንጌልን ሳይጽፉ በቃል ወይም በሌሎች መጻሕፍት ያስተማሩና ለነቅዱስ ሉቃስም ያስተላለፉ መኖራቸውን በቅድሚያ ሲያስረዳ ወንጌሉ የተጻፈለት ቴዎፍሎስ እንኳን አስቀድሞ በቃል መማሩንም የሚያሳይ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስም እርግጡን ያውቅ ዘንድ ወይም ያረጋግጥ ዘንድ ጻፈለት እንጂ ከዚያ በፊት ያልተማረ ስላልነበር ለማስተማርና ለማሳወቅ የጻፈለት አይደለም፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቱ ይቀድማል?
ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ በፊት የነበረችና መጽሐፍ ቅዱስን የጻፈች፣ ከእግዚአብሔር የተቀበለችውን በመጽሐፍ የተቀመጠውን እውነት ጠብቃ ያስተላለፈች የእግዚአብሔር መንግሥት ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በቤተ ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከተጻፉት መጻሕፍትም ውስጥ አምላካውያት የሆኑትን በቀኖና ለይታና ቀድሳ ለምእመናን የሕይወት ምግብነት የሰጠች መሆኗን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትቀድማለች፤ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑም ምስክሯ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የጻፈችውና የምትተረጉመው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ያስገኘ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለአዋልድ መጻሕፍት ወላጃቸው ነው፡፡ ይህንም በብዙ ማስረጃና አመክንዮ እንደሚከተለው እናያለን፤
፩. መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የቤተ ክርስቲያንን ቀዳሚነት ይመሰክራል
የሚከተሉት ጥቅሶች ቅዱሳት መጻሕፍቱ ከመጻፋቸው በፊት ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች በደንብ ያስረዳሉ፤
- “በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት” (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፪)፡፡
አንድ መልእክት (ደብዳቤ) ሲጻፍ ሦስት አካላት መኖራቸውን መረዳት ተገቢ ነው – ላኪው፣ መልእክቱና ተቀባዩ፡፡ ላኪውና ተቀባዩ በሌሉበት መልእክቱ ሊጻፍ አይችልም፡፡ የመልእክቱ ላኪ ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ተቀባይዋ ደግሞ በቆሮንቶስ አገር ያለች የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ከመልእክቱ ላኪውና ተቀባዩ የሚቀድሙ ከሆነ መልእክቱን ለመቀበል ቅዱስ ጳውሎስንና ቤተ ክርስቲያንን በቅድምና መቀበል ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህን ሲያስረዳ ቅዱስ ጳውሎስ ገና መልእክቱን ለመጻፍ ሲጀምርና ለማን እንደሚጽፍ ሲገልጽ “በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን” ማለቱ እርሱ መልእክቱን ከመጻፉ በፊት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች የሚያሳይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ቀድማ መኖሯ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ስትቀድስም ነበር፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰዎችን ለመቀደስ የግድ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው መልእክት አላስፈለጋትም ነበር፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ የመልእክቱ ባለቤት “በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት” በማለት ገለጸ፡፡ ይህን የመሰሉና ተመሳሳይ እውነትን የሚመሰክሩ ብዙ ጥቅሶችን ማንሣት ይቻላል፡፡
- “በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤” (፪ኛ ቆሮ. ፩፥፩)፡፡
- “በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤” (ገላ. ፩፥፩)፡፡
- “ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤” (፩ኛ ተሰ. ፩፥፩)፡፡
- “እንዲሁም የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈሕ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ” (ራእ. ፩፥፲፩)፡፡ ባለራእዩ ቅዱስ ዮሐንስም በተመሳሳይ ራእዩን ካየ በኋላ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲጽፍ ተገለጸለት፡፡ ይህም ከመጽሐፉ በፊት አብያተ ክርስቲያናቱ እንደነበሩ የሚያስረዳ ነው፡፡ ዮሐንስም ራእዩን በማየት ይከብር ዘንድ መጽሐፍ አላስፈለገውም ነበር፡፡
፪. አመክንዮአዊ ማረጋገጫ
ከመጻሕፍት ሁሉ ቀድሞ የተጻፈው መጽሐፈ ሄኖክ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ ከመጻፉ በፊት ሰው ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ያለ መጽሐፍ ኖሯል፡፡ መጽሐፈ ኢዮብና አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት ከዚያ በመቀጠል ተጻፉ፡፡ የነቢያት መጻሕፍት ሺሕ ዓመታት ዘግይተው ክርስቶስ ሊወለድ በመቶዎች የሚቈጠሩ ዓመታት ሲቀሩት ተጻፉ፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ለመጀመሪያዎቹ ዐርባ ዓመታት መጻሕፍት አልተጻፉም፡፡ ከዚያ በኋላም የማቴዎስ ወንጌልንና የያዕቆብ መልእክትን የመሰሉት ቀድመው ተጻፉ እንጂ አብዛኞቹ የተጻፉት እስከ ፸ ዓ.ም. ድረስ ቆይተው ነው፡፡ የሐዲሳት መጻሕፍት የተጻፉት ደግሞ በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ነበር፡፡ ይህም የሚያስገነዝበው፡-
ሀ. ለጽድቅና ለድኅነት የሚያስፈልገው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ቢሆን ኖሮ መጽሐፉ በአንዴ አልቆና ተጠቃሎ ከአዳም ጀምሮ ላሉት ሁሉ ካለመድሎ መሰጠት አልነበረበትምን? መጽሐፍ ያልተሰጣቸውስ “እኛ በኃጢአት የወደቅነው መጽሐፍ ቅዱስ ስላልነበረን ነው” ብለው ምክንያት እንዲያቀርቡ ዕድል አይፈጥርላቸውም ነበርን? አምልኮን በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የምንገድበው ከሆነ ለሁሉም ሁሉንም መጻሕፍትን ባለ መስጠቱ የእግዚአብሔር ፈታሒነት ላይ ጥያቄ አያስነሣም ነበርን?
ለ. በጥንቱ ዘመን መጻሕፍት ለየተጻፉላቸው ሰዎች በጥቅል (Scroll) መልክ ይገኙ ነበር እንጂ አሁን እንዳለው ሁሉም በአንድነት ተጠርዘው በአንድ ሰው እጅ ማግኘት አይቻልም ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ባለው መልኩ ተሰብስቦ በአንድነት መገኘት የቻለው የማተሚያ ማሽን ከተሠራና በወረቀት ማተም ከተጀመረ በኋላ ነው፡፡ ምዕራፍና ቊጥር ወጥቶለት ለንባብ አመቺ የሆነው ደግሞ ከዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ነው፡፡ በጥንቱ ዘመን እያንዳንዱ መጽሐፍ በየቦታው በጥቂት መጠን ብቻ ይገኝ ነበር፡፡ የሮሜ መልእክት የሚገኘው ሮማውያን ዘንድ፣ የቆሮንቶስ መልእክት ከቆሮንቶስ ሰዎች ዘንድ … ወዘተ እንጂ እንደዚህኛው ዘመን በአንድ ጊዜ ተባዝተው ሁሉም ዘንድ የሚገኙ አልነበረም፡፡ ለዐራት ሺሕ ዓመታት ያክል የተጻፉትን እነዚህን ቅዱሳት መጻሕፍት ከሐሰተኞቹ ለይታና በቀኖና ወስና “እነዚህን ተጠቀሙ” ያለችው ቤተ ክርስቲያን አይደለችምን?
ቤተ ክርስቲያን ይህን ባታደርግ እኛም ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ የማንገናኝ በሆንን ነበር፡፡ ወንጌላትን በጊዜው ብዙዎችን ያስቱ ከነበሩት “የይሁዳ ወንጌል”፣ “የበርናባስ ወንጌል” ከተባሉትና እነዚህን ከመሰሉት እንዲሁም “የማቴዎስ፣ የማርቆስ ወንጌል” ተብለው ብዙ ሐሰት ከተጨመሩባቸው ለይታ “መጻሕፍተ ወንጌላት ዐራቱ ብቻ ናቸው” ባትለን ኖሮ በብዙ ጥፋት ውስጥ የምንሆን አልነበርንምን? እርሷ በቀኖና ሰፍራ ቈጥራ የሰጠችውን መጽሐፍ ተቀብሎ ሰጪዋን ቤተ ክርስቲያንን አልቀበልም ማለትስ ስሕተት አይደለምን? በተመሳሳይ መልኩ ቀኖናን ሠርታ አዋልድ መጻሕፍትን ስትሰጥ አለመቀበልስ አለማወቅ አይደለምን?
ሐ. የቤተ ክርስቲያንን ከሁሉ በላይ መሆንና ፍጹም የሆነ ሥልጣኗን የምናውቅ አሥራው መጻፍት ተብለው የሚታወቁት መጻሕፍትን ሰብስቦ ሰማንያ አንድ ብቻ ናቸው ብሎ ማን ነገራችሁ? ብንባል “ቤተ ክርስቲያን” እንላለን፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚሉት ወገኖች ግን “መጽሐፍ ቅዱስን ‘ስልሳ ስድስት’ ያላችሁ ማነው” ቢባሉ ማን ይሉ ይሆን? እንቀበላቸዋለን የሚሏቸው “ስልሳ ስድስትቱ መጻሕፍት” ራሳቸው “ስልሳ ስድስት ብቻ” ወይም “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” አይሉምና፡፡
፫. መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ አለመያዙን ያስረዳል
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤” (ዮሐ. ፳፥፴) በማለት ክርስቶስ ያደረጋቸው ሁሉ የተጻፉ እንዳልሆነ አስረድቷል፡፡ እንዲያውም እርሱ ያደረገውን ሁሉንም እንጻፍ ማለት እንደማይቻል ሲገልጽ “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ብሏል፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ታሪክ፣ ሁሉንም ሥርዐት … ወዘተ ጠቅልሎ እንዳላካተተ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህን ስንል ግን በጽሑፍ ደረጃ አልዘረዘረም ማለታችን እንጂ ከምሥጢር ምልዐት አንጻር የጎደለው ነገር አለው ማታችን አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሁሌም ምሉዕ ነውና የእግዚአብሔር ቃል የሚገኝበት መጽሐፍም ሕፀፅና ጉድለት የማይገኝበት ምሉዕ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ባነሣው ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መንፈሳዊ ዕውቀት የምንፈልግ ከሆነ የቀረው ነገር የት እንደሚገኝ አዋልድ መጻሕፍትን ጠቁሞናል እንጂ “ሁሉንም ጠቅልዬ ይዣለሁና እኔን ብቻ አንብቡ” አላለም፡፡ የሚከተሉት አሳቦችም ይህንኑ የሚያስረዱ ናቸው፡፡
- “የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በአሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በአዶ ራእይ የተጻፈ አይደለምን?” (፪ኛ ዜና. ፱፥፳፱)፡፡
- “የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?” (፩ኛ ነገ. ፲፬፥፳፱)፡፡
- “የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል” (፩ኛ ነገ. ፲፩፥፵፩)፡፡
ማጠቃለያ
መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ምንጭና ራስ ነው፡፡ ማንኛውም ትምህርት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወይም ሥርዐት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሰው ጋር የሚጋጭ ከሆነ በቤተ የቤተ ክርስቲያናችን ተቀባይነት የለውም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የትምህርተ ሃይማኖት ዋና ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የሥርዐትና የታሪክ ዋና ምንጭም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዘውን የምትፈጽም፣ የምታስተምርና የምትኖር መጽሐፍ ቅዱሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስንም እንድናነበውና እንድንማርበት አዘጋጅታ የሰጠችን እርሷው ናት፡፡ ይሁንና አንዳንድ መናፍቃን መጽሐፍ ቅዱስን የሚከተሉ መስለው ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ያልሰበከች አስመስለው ስለሚያቀርቡ ተንኮላቸውን ተረድተን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የማይለውን እንደሚል አድርገው በማቅረብና አጣመው በመተርጎም የሚስቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ከሁሉ የምትቀድመውን ቤተ ክርስቲያን እየተቃወሙ እርሷ ለዓለም ሁሉ የሰጠችውን ቅዱስ መጽሐፍ የተቀበሉ የሚያስመስሉት፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሚዋጉአት ክፍሎች ተሐድሶ ፕሮቴስታንቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ከሚያታልሉበት ፕሮቴስታንታዊ መንገድ አንዱ ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው አስተምህሮ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም አመክንዮም የማይደግፉትን ይህን የስሕተት መንገድ በመያዝ ቤተ ክርስቲያንን ይከሳሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ቢሉም መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክርላትን ልዕልናዋን አይቀበሉም፡፡ የመረጡትን ይወስዳሉ፤ ያልተስማማቸውን ይተዋሉ፡፡ አስቀድመን እንዳየነው አንድ አማኝ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን የምትይዝና ከሁሉ ይልቅ የበለጠች መሆኗን መረዳት ይገባዋል፡፡ አንድ ጥያቄ ቢፈጠርበት እንኳን በቤተ ክርስቲያ ውስጥ ካለ አይቸገርም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ያላወቀውን ነገ ያውቃል፤ ዛሬ ያልተረዳውን በሕይወትም፣ ከአባቶች ጠይቆም ይረዳል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ካላሳያችሁኝ የሚል አይሆንም፡፡ ይልቁንስ በመጽሐፍ ተጽፎ ያላገኘውን ከሁሉ ይልቅ ከፍ ካለችው ከቤተ ክርስቲያን ለማግኘት ይጥራል እንጂ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! ይህ ትምህርት፣ ከታኅሣሥ ፲፮ – ፴ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በታተመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በንቁ ዓምድ ሥር ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡