ge awd 2006 2

“ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት የድርሻችንን እንወጣ” ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

ሰኔ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.

አውሮፓ ማእከል የጀርመን ቀጠና ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል የጀርመን ቀጠና ማእከል በፍራንክፈርት ከተማ ኢኮነን ሙዚየም ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ ተከፈተ፡፡ge awd 2006 2

 

ከሰኔ 27- 29 ቀን 2006 ዓ.ም./July 4-6, 2014/ እንዲታይ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ጥሪ የተደረገላቸው ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከፍቷል፡፡ ጸሎተ ወንጌል በቦታው በተገኙ ካህናት ተደርጓል፤ የዐውደ ርእዩን የዝግጅት ሒደትና ይዘት አስመልክቶም አቶ ቃለ አብ ታደሰ የዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

እንደ አቶ ቃለ አብ ገለጻ የጥንታዊቷንና የሐዋርያዊቷን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ባሕልና ትውፊት ማስተዋወቅን ዓላማው ያደረገው ዝግጅቱ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል የቤተ ክርስቲያኗን ታሪክ በአጭሩና ተመልካች በቀላሉ ሊረዳው በሚችለው መንገድ የቀረበበት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው፡፡  ሁለተኛው ደግሞ የዕውቀትና የጽድቅ እንዲሁም የልማት መሠረቶች የነበሩት ገዳማትና አድባራት እንዲሁም አብነት ት/ቤቶች ያደረጉትን አስተዋጽዖና በአሁኑ ወቅት እያጋጠማቸው ያለው ተግዳሮቶች በዝርዝር የቀረቡበት ነው፡፡ የመጨረሻው ደግሞ ከግንቦት 1984 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየውና ወደፊትም የሚሰጠው ማኅበረ ቅዱሳን ታሪክ፣ አገልግሎትና በየጊዜው ያጋጠሙት ችግሮች የቀረቡበት ክፍል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓ ያላት የአገልግሎት ታሪክ የተዳሰሰበት አንዱ የመርሐ ግብሩ አካል ነበር፡፡

 

ge awd 2006 1በክብር እንግድነት ተገኝተው ዐውደ ርዕዩን በጸሎት የከፈቱት መልዐከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሲራክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ መልአከ ፀሐይ በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የተከፈተው ዐውደ ርዕይ በፍራንክ ፈርት ከተማ ለአራተኛ ጊዜ እንደኾነ በማውሳት፤ ሁሉንም ዐውደ ርእዮች አዘጋጅቶ ለፍራንክፈርት ከተማና አካባቢው ሕዝብ ለዕይታ ያቀረበው በማኅበረ ቅዱሳን የጀርመን ቀጠና ማእከል ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን እየሰጠ ያለው አገልግሎት ሰፊና ጠቃሚ ነው ያሉት መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሲራክ፤ ለዚሁ ደግሞ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ በማለት በቅርብ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሔደው ማኅበሩ በአቡነ  ቶማስ ዘደብረ ሃይዳ ገዳም እያደረገ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

 

የዐውደ ርእዩን መከፈት አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት ምእመናንም በዝግጅቱ እንደተደሰቱ ገልጸዋል፡፡ በፍራንክፈርት ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ነቢዩ የማነ፤ ላለፉት ሦስት ጊዜያት የቀረቡትን ዝግጅቶች እንደተመለከቱ አውስተው «ይኸኛውም ዝግጅት ብዙ ያላወኳቸውን ነገሮች አሳውቆኛል፡፡ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ምን ያህል ሓላፊነታችንን እንዳልተወጣን አስገንዝቦኛል፤ ይህም በእውነት ቁጭት ፈጥሮብኛል፡፡  ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ቤትም ይሁን በውጭ የሚሰጠው አገልግሎት በእጅጉ እየጠቀመን ነውና ሁሉም ቢደግፈው» በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በተመሳሳይ ሁኔታም በከተማው ነዋሪ የኾኑት ወ/ሮ እጥፍ ወርቅ ወልዴ ባዩት ዝግጅት ብዙ ነገር እንዳወቁና «ሁሉም በውጭ የሚኖረው ምእመን በሀገራችን በችግር ላይ ያሉትን ገዳማትንና አድባራትን እንዲሁም አብነት ት/ቤቶችን ለዕረፍትም ይሁን ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ወደ ሀገር ቤት ስንሔድ በአካል በመገኘት ልናያቸው ይገባል፤ አይተንም መርዳት ይጠበቅብናል፤» ብለዋል፡፡  አቶ ኤልያስ መሸሻ ደግሞ በስዊዘርላን ነዋሪ የኾኑና ዝግጅቱ ብቁ ቁም ነገሮችን እንዳሳወቃቸው ጠቅሰው፤ «ይህን መሰሉ ድንቅና ጠቃሚ ዝግጅት በሁሉም የአውሮፓ ከተሞች ተዘዋውሮ ሊታይ ይገባዋል» ብለዋል፡፡

 

እስከ እሑድ ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. /July 6, 2014/ ድረስ የሚቆየውና በበርካታ ምእመናንና ጀርመናውያን እንደሚጎበኝ የሚበሚጠበቀው በዚህ ዝግጅት ጥናታዊ ጽሑፎችና የቤተ ክርስቲያኗን ልዩ ልዩ ባሕሎች የሚያስተዋውቁ ትዕይንቶችና ስብከተ ወንጌል ይቀርባሉ፡፡

 

በሀገረ ጀርመን አስራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲኾን ሁሉም በደቡብ ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ስር የታቀፉና አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ መንበረ ጵጵስናውን በፍራንክፈርት ከተማ ያደረገው ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስም ብፁዕ አቡነ ሙሴ ናቸው፡፡        


a 27 2006 1 1

ከአጤ ዋሻ ተዘርፎ የነበረው ታቦተ መድኃኔዓለም ወደ መንበረ ክብሩ ተመለሰ

 ሰኔ 27 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

a 27 2006 1 1ከሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ደብረ ብርሃን ከተማ በአሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የአጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተዘርፎ ጅቡቲ ውስጥ ለ17 ዓመታት ተደብቆ የነበረው ታቦተ መድኃኔዓለም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ መንበረ ክብሩ ገብቷል፡፡ /ሚያዚያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ታቦቱ ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ መግባቱን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል/፡፡ 

ታቦቱ ሐምሌ 27 ቀን 1989 ዓ.ም. ሌሊት ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ተሰርቆ ለ17 ዓመታት ጅቡቲ ውስጥ በአንድ የሌላ እምነት ተከታይ ቤት ውስጥ ተደብቆ ከቆየ በኋላ ጅቡቲ ለሚገኘው ለምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳደሪ ለአባ ዮናስ መልከ ጼዲቅ ከቤተሰቡ መካከል በአንዱ መረጃው ይደርሳቸዋል፡፡ አባ ዮናስ በደረሳቸው መረጃ መሠረት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በማሳወቅ ታቦቱን ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡

a 27 2006 1 2ሚያዚያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የቅርስ ጥበቃና ቤተ መዘክር ለጊዜው እንዲቀመጥ በማድረግ፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ወደ አጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አሸኛኘት ተደርጎለታል፡፡

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መዘምራንና ምእመናን በደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለታቦቱ ደማቅ አቀባበል በማድረግ በአጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወደ መንበረ በክብሩ አስገብተውታል፡፡

ብፁዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምእዳን ለታቦቱ መመለስ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ አካላት ምሥጋናቸውን አቅርበው ምእመናን በተለይም በየአጥቢያው የሚገኙ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ወደ አጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለመድረስ በጣም አስቸጋሪና ውጣ ውረድ የተሞላበት ገደልን መውረድ ስለሚጠይቅ በርካታ የቤተ ክርስቲያን የከበሩ ንዋያተ ቅድሳት በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ተሸሽገውበት እንደነበር የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ አባቶች ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢጣሊያ ጦር በአድዋ ጦርነት ድል እንዲነሱ ካደረጋቸው አንዱ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት በመሆኑ ይህንን ታቦት ለመዝረፍ ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮ የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው ፍጹም ፍቅር የነበራቸው አባቶች ታቦቱን ከቤተ መቅደስ በማውጣት ጦርነቱ እስኪያበቃ አጤ ዋሻ ወስደው ሸሽገውታል፡፡

ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በ1937 ዓ.ም. ካህናቱ ታቦቱን አጅበው ከአጤ ዋሻ ወደ አዲስ አበባ መልሰውታል፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ካህናቱ በታማኝነት ታቦቱን ጠብቀው በማኖርና በክብር በመመለሳቸው በወርቅ የተለበጠ የመድኃኔዓለም ታቦት ይዘው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡

ከ1937 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ይህ ታቦት በ1989 ዓ.ም. ተሰርቆ ጅቡቲ ውስጥ በሌላ እምነት ተከታይ ቤት ውስጥ ተደብቆ ቆይቷል፡፡ በቤቱ ውስጥ ደብቆ ያስቀመጠው ግለሰብ የተሰደደ ሲሆን፤ ሚስቱ ስታብድ ልጁ ሞቶበታል፡፡ በዚህ የተደናገጠው ሌላው የሰውየው ልጅ በቤታቸው ውስጥ ታቦት እንዳለና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲወሰድ ራሱ መጥቶ መረጃ በመሥጠቱ ታቦቱ ወደነበረበት በክብር ተመልሷል፡፡

 

mkgermany exhibition 2

ልዩ ዐውደ ርዕይ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ይካሔዳል

ሰኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም.

አውሮፓ ማእከል

mkgermany exhibition 2በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል የጀርመን ቀጠና ማእከል “ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት የድርሻችንን እንወጣ” በሚል መሪ ቃል ልዩ ዐውደ ርዕይ፤ ዐውደ ጥናትና የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር በፍራንክፈርት ከተማ ኢኮነን ሙዚየም ከሰኔ 27- 29 ቀን 2006 ዓ.ም./July 4-6, 2014/ እንደሚካሔድ ቀጠና ማእከሉ አስታወቀ፡፡

በዝግጅቱም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ታሪክ አስተዋጽኦና ወቅታዊ ሁኔታ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ እንቅስቃሴ በጀርመንና በአውሮፓ፤ የቅዱስ ያሬድ አጠቃላይ የዜማ ባሕል እና ሌሎችም ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ የማኅበሩ አባላትና ምእመናን ታዳሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

 

entoto raguale

ሰበካ ጉባኤው ለካህናት ደመወዝ ለመክፈል እንደተቸገረ አስታወቀ

ሠኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

entoto ragualeሠኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተደረገው ጉባኤ ላይ የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ለካህናት ደመወዝ ለመክፈል በመቸገሩ በቤተ ክርስቲያኑ ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ችግር እያጋጠመው መሆኑን ገለጠ፡፡

entoto ragual 4የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ወልደ መድኅን ተክለ ብርሃን የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያንና የርዕሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከግቢያቸው አጥር ውጭ ምንም ይዞታ የሌላቸው በመሆኑ እና ቀደም ሲል የነበረው 270.9 ሄክታር ይዞታ በመነጠቁ ምክንያት አልምተን የገቢ ምንጭ የምንፈልግበት ሁኔታ የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አስተዳዳሪው ደብሩ ይዞታው ከተመለሰ የልማት ሥራ በመሥራት ከችግር መላቀቅ የሚቻል መሆኑን ጠቁመው፣ ጉዳዩንም ለሚመለከተው አካል ማሳሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡

የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ወንዳፍራሽ ኃይሉ የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ቁጥር ከ150 የማይበልጡ በመሆናቸው ከምእመናኑ በሚገኘው አስተዋጽኦ የካህናቱን ደምወዝ መክፈል አልተቻለም፡፡ የቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ወዳጆች በሚያደርጉት አስተዋጽኦ እንጂ ደብሩ ከከተማ ራቅ ያለ በመሆኑ ምንም የገቢ ምንጭ የለውም ብለዋል፡፡

ደብሩ በአሁኑ ሰዓት 51 አገልጋዮች አሉት፡፡ አገልጋዮቹ ቀን ከሌሊት በትጋት ቢያገለግሉም ሰበካ ጉባኤው ካለው ዐቅም አንጻር ደምወዝ ከከፈላቸው ሦስት ወር እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡ አገልጋዮቹም በችግር ምክንያት የቀን ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኑ ፀሐፊ የሆኑት መጋቤ ምሥጢር አባ ፍሬ ስብሐት አድማሱ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያኑ ከተተከለ መቶ ሠላሳ ዐራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በዐፄ ምኒልክ ዘመን የመጻሐፍት፣ የቅኔና የድጓ መምህራን እንዲሁም ሦስት መቶ ሊቃውንት የነበሩት መሆኑን ጠቁመው፣ ዛሬ ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶቹ ፈራርሰዋል፡፡ ተማሪዎችና መምህራን ፈልሰዋል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሊቃውንት አብዛኛዎቹ ከእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት የተገኙ ናቸው ያሉት ጸሐፊው በአሁን ሰዓት ጉባኤዎቹ ታጥፈዋል፡፡ ይህ የሆነው ከገንዘብ ማጣት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገራችን ነግሠው የነበሩት ዐፄ ዳዊት በእንጦጦ ተራራ ላይ መናገሻ ከተማቸውንና ቤተ መንግሥታቸውን አድርገው ይኖሩ ነበር፡፡ ንጉሡ ከቋጥኝ ድንጊያ ዋሻ ፈልፍለው ቤተ መቅደስ አሠርተው ሲያስቀድሱ ነበር፡፡ በ1860 entoto ragual 3ዓ.ም መጨረሻ ዐፄ ምኒልክ እንጦጦ ከተማ ከቆረቆሩ በኋላ፣ የልዑል እግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማሳነጽ በነበራቸው ምኞት ከደብረ ሊባኖስ ገዳም አባቶችን አስመጥተውና ቦታውን አስባርከው የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ወኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ሊታነጽ መቻሉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ በውስጡ የቋጥኝ ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ፣ የነገሥታት ዘውድና አልባሳት፣ የወርቅ፣ የብር፣ የነሀስና የዕፅ ንዋያተ ቅድሳትንና ቅርሶችን የያዘ ነው፡፡ ደብሩ እነዚህን ቅርሶች ሙዝየም በማስገንባት ለጎብኚዎች ክፍት ያደረገ ሲሆን ሕዝበ entoto raguale 2.jpgክርስቲያኑ ወደዚህ የተቀደሰ ቦታ በመምጣት፣ በመሳለምና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት የበረከቱ ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ደብሩን መርዳት ለምትፈልጉ የልማት ባንክ ቁጥርን ይጠቀሙ፡፡ 0173060913900

 

የማቴዎስ ወንጌል

ሰኔ 24 ቀን 2006 ዓ.ም.

ምዕራፍ 3

ይህ ምዕራፍ ስለጌታ መጠመቅ ይናገራል፡፡ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ስብከት እየሰበከ ከምድረ በዳ የመጣ ነው፡፡ አስቀድሞ በነብየ ልዑል ኢሳይያስ ስለ ዮሐንስ ተነግሮ ነበር፡፡ ኢሳ.41፡3፡፡ ልብሱ የግመል ጠጉር በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ስለነበር ይህ ሁኔታው ከነብዩ ኢሳይያስ ጋር ያመሳስለው ስለነበር በኤልያስ ስም ተጠርቷል፡፡ ሚል.4፡5፣6፡፡

ኤልያስና መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን የሚያመሳስላቸው ሌላም ነገር አለ፡፡

  • ኤልያስ አክዓብና ኤልዛቤልን ሳይፈራ ሳያፍር በመጥፎ ሥራቸው እንደገሰጻቸው መጥምቁ ዮሐንስም ሄሮድስን የወንድምህን የፊልጶስም ሄሮድስን የወንድምህን የፊልጶስን ሚስት ልታገባ አልተፈቀደልህም በማለት ገስጾታል፡፡

  • ኤልያስ ንጹሕ ድንግላዊ እንደ ነበር ሁሉ መጥምቁ ዮሐንስም ንጹሕ ድንግል ነው፡፡

ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት በመሆኑ በኢየሩሳሌምና በይሁደ የነበሩ ሁሉ ኃጢአታቸው እየተናዘዙ ከእርሱ ዘንድ ይጠመቁ ነበር፡፡

ፈሪሳውያን ሊጠመቁ ወደ እርሱ ዘንድ ሲመጡ አይቶ “እናንተ የእፉኝት ልጆች” በማለት ገሰጻቸው፡፡ ከእፉኝት ልጆች ጋር አይሁድን ያመሳስላቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ እፉኝት አፈማኅፀንዋ ጠባብ ስለሆነ ከወንዱ እፉኝት አባላዘር ከስሜትዋ የተነሣ ስለምትቆርጠው ወንዱ እፉኝት በፅንስ ጊዜ ይሞታል፡፡ የእፉኝት ልጆች አባታቸውን ገድለው ይፀነሳሉ፡፡ ኋላም የመወለጃቸው ጊዜ ሲደርስ ቀደም ተብሎ እንደተገለጸው አፈማኅፀንዋ ጠባብ ስለሆነ የእናታቸውን ሆድ ቀደው ይወጣሉ፡፡ ያን ጊዜ እናታቸው ትሞታለች፡፡ አይሁድም እንደ አባት የሆኑአቸውን ነብያትን /እነኤርሚያስን/ የጌታን ልደት በመናገራቸው ገድለዋቸዋል፡፡ ኋላም እንደ እናት የሚራራላቸውንና የሚወዳቸውን ጌታ ቀንተው ተመቅኝተው ይገድላሉና በእፉኝት ተመሰሉ፡፡

መንፈስ ቅዱስንም በእሳት መስሎ ተናግሯል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእሳት የተመሰለበትም ምክንያት፡-

እሳት ምሉዕ ነው፡፡ በየትም ቦታ ይገኛል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነው፡፡ የማይገኝበት ሥፍራ የለም፡፡

እሳት በምልዓት ሳለ ቡላድ ክብሪት ካልመቱ አይገለጽም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር፣ ምስጢር ሲያስተረጉም፣ ተአምር ሲያሠራ እንጂ በእኛ ላይ አድሮ ሳለ አይታወቅምና፡፡

እሳት ከመነሻው ማለትም ክብሪት ጭረን ስንለኩሰው በመጠን ነው፡፡ ገለባውን ወረቀቱን እንጨቱን እየጨማመርን ስናቀጣጥለው ግን ኃይሉ እየጨመረ፣ እየሰፋ እየተስፋፋ ይሄዳል፡፡

መንፈስ ቅዱስም መጀመሪያ በ40 ቀን ለወንዶች በ80 ቀን ለሴቶች በጥምቀት ጊዜ ጸጋውን ሲሰጥ በመጠኑ ነው፡፡ ኋላ ግን በገድል በትሩፋት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን እያደገ ይመጣል፡፡

እሳት የነካው ምግብ ይጣፍጣል፡፡ ማለትም አሳት ጣዕምን መዓዛን ያመጣል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በሕይወታችን ጣዕመ ጸጋንና መዓዛ ጸጋን የምናገኘው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

  • እሳት በአግባቡ ቢጠቀሙበት ለሰው ልጅ ጥቅም ይውላል፡፡ ዳሩ ግን አያያዙን ካላወቁበት ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአግባቡ በወንጌል የተጻፈውን መሠረት አድርገው ለሚመረምሩት ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል፡፡ ጸጋን ያጐናጽፋል፡፡ ነገር ግን ከተጻፈው ውጭ በአጉል ፍልስፍና በትዕቢት ሊመረመሩ የሚነሡ ሁሉ ትልቅ ጥፋት በሕይወታቸው ያመጣሉ፡፡

  • እሳት ገለባም ይሁን እንጨት፣ እርጥብ ይሁን ደረቅ ያቀረቡለትን ሁሉ ሳይመርጥ ያቃጥላል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በንጹሕ ልቡና ሆኖ ለሚለምነው ሁሉ ሕፃን ዐዋቂ ድኻ ሀብታም ሳይል የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡትን መሥዋዕት ይቀበላል፡፡

  • አሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ተስማሚ ነው፡፡ ጥሩ ምርት ይገኝበታል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ያመቻል፡፡

  • እሳት ተከፍሎ አይኖርበትም፡፡ ማለትም ከአንዱ የሻማ መብራት ሌላ ሻማ ብናበራ የሻማው መብራት አይጉድልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ወይም የጸጋ መጉደል መቀነስ ሳይኖርበት እስከ ምጽአት ድረስ ለምእመናን ጸጋውን ሲሰጥ ይኖራል፡፡

  • ሸክላ ሠሪ ሥራዋን ሠርታ ስትጨርስ ስህተት ያገኘችበት እንደሆነ እንደገና መልሳ ከስክሳ በውኃ ለውሳ በእሳት ታድሰዋለች፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ንጹሕ ሆኖ የተፈጠረ ሰው ከእግዚአብሔር ሕግ ቢወጣና በኃጢአት ቢያድፍ በንስሐ ሳሙና ታጥቦ በመንፈስ ቅዱስ ታድሶ አዲስ ሰው ይሆናል፡፡

መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ስለአጠመቀው ሲመሰክር ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ነኝ ብሏል፡፡ በዚህም የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ተናግሯል፡፡ “መንሹም በእጁ ነው” ሲል ገበሬ በመንሽ ፍሬውን ከገለባው እንደሚለይ ጌታችንም ጻድቃንን ከኃጥአን የመለየት ሥልጣኑ የራሱ ነውና፡፡ በጐተራ መንግሥተ ሰማያትን፣ በስንዴ፣ ጻድቃንን፣ በገለባ፣ ኃጥአንን፣ በማይጠፋ እሳት፣ ገሃነመ እሳትን መስሎ ተናግሯል፡፡

ይጠመቅበት ዘንድ ጌታ በኢየሩሳሌም ካሉት ወንዞች ሁሉ ዮርዳኖስን የመረጠበት ምክንያት፡-

  1. በተነገረው ትንቢት መሠረት ነው፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ በሚጠመቅበት ጊዜ የሚሆነውን አስቀድሞ ተንብዮ ነበር፡፡ ያን ለመፈጸም ነው መዝ.113/114፡3-5፡፡

  2. ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ኤልያስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደ ዐረገ ምእመናንም አምነው ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማይ ለመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡

  3. የእምነት አባት አብርሃም ነገሥተ ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሲመለስ የጌታን ቀን ሊያይ ወደደ፡፡ ጌታም ምሳሌውን ሊያሳየው ዮርዳኖስን ተሻግሮ እንዲሄድ አዘዘው፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ሲሄድ መልከ ጸዴቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዓ አኰቴት ይዞ ተቀብሎታል፡፡ አብርሃም የምእመናን ምሳሌ ሲሆን ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ፣ መልከ ጸዴቅ ደግሞ የካህናት፣ የቀሳውስት ኅብስተ በረከት፣ ጽዋዓ አኰቴት የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነው ዘፍ.14፡10-20፡፡

  4. የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ ነው፡፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን የባርነት ስማቸውን እንዲጽፉለት አድርጐ የዕዳ ደብዳቤውን አንዱን በሲኦል ሌላውን በዮርዳኖስ ወንዝ አኑሮት ስለነበር ጌታም በዮርዳኖስ ያለውን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ በዚያ ተጠመቀ ቆላ.2፡14፡፡

ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ

ሀ. ሰማይ ተከፈተ፣
ለ. አብ በደመና ሆኖ ስለ ወልድ መሰከረ፣
ሐ. መንፈስ ቅዱስም በጥንተ ተፈጥሮ በውኃ ላይ እንደታየ አሁን በሐዲስ ተፈጥሮ ታየ፡፡

ይህም አስተርእዮ /ኤጲፋንያ/ ይባላል፡፡ የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት የተገለጠበት ወቅት ነውና የመገለጥ ዘመን ተብሏል፡፡

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ቁጥር 1 መስከረም 1989 ዓ.ም.

 

sewa sewe brhan 3

የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርትን አስመረቀ

 ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

sewa sewe brhan 3በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመደበኛና በማታ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ 212 ደቀመዛሙርትን በዲፕሎማ አስመረቀ፡፡

ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሔደው የምረቃ መርሐ ግብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዲፕሎማና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ደቀመዛሙርት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት ቃለ ምእዳን “ቤተ ክርስቲያን ከአጽናፈ ዓለም አሰባስባ፤ አስተምራ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ልታሰማራችሁ በዝግጅት ላይ ቆይታችኋል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ሐብት በመሆኑ ያገኛችሁትን እውቀት ለወገኖቻችሁ እንድታካፍሉና ቤተ ክርስቲያን የጣለችባችሁን ሓላፊነት እንድትወጡ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ፤ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፤ የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ደቀመዛሙርቱ መንፈሳዊ ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል የሚዘጋጁበት ወቅት እንደሆነ አስታውሰው፤ በአባቶች ቡራኬ ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኮሌጁ ዲን መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሃና ባቀረቡት ሪፖርት በመማር ማስተማሩ ሂደት ያጋጠሟቸውን ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት መምህራን ሲለቁ በቦታቸው ቶሎ ተተኪ ያለመመደብ፤ የሚመሩ ደብዳቤዎች ባልታወቀ ሁኔታ መጥፋት፤ ኮሌጁ ለሚጽፋቸው ደብዳቤዎች ምላሽ ያለማግኘት፤ የሥራ ጣልቃ ገብነት ጎልተው ከሚታዩት ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጁ ምሁራንን እያፈራ የሚገኝ ቢሆንም ዘመኑን ባልተከተለ አሠራር እየተጓዘ ከአባቶች እንደተረከብነው ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ እንችላለን ወይ? በሚል ጥያቄ ውስጥ እንደሚገኙም መጋቤ ጥበብ ምናሴ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮሌጁ በየዓመቱ የሚቀበላቸው ደቀመዛሙርት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱም እንደማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

sewa sewe brhan 2ከተመራቂ ደቀ መዛሙርቱ መካከል አባ ኪሮስ ወልደ አብ የትምህርት ቆይታቸውን አስመልክቶ የተሰማቸው ስሜት ሲገለጡ “ትምህርት ጀመርኩ እንጂ አልጨረስኩትም፤ የበለጠ እንድማር አነሳሥቶኛልና እቀጥልበታለሁ፡፡ በኮሌጁ ቆይታዬም በእቅድ መመራት በመቻሌ በጥሩ ሁኔታ ተምሬ በማዕረግ ለመመረቅ ችያለሁ” ብለዋል፡፡

 

ተመራቂ ደቀመዛሙርት ያወጡትን የጋራ መግለጫ በተወካያቸው አማካይነት ያቀረቡ ሲሆን፤ በኮሌጁ ውስጥ አንዳንድ መልካም ሥራዎች ቢኖሩም በኮሌጁ ቆይታቸው በስፋት ይታያሉ ያሏቸውን ችግሮች ዳስሰዋል፡፡ የትምህርት አሠጣጡ ዘመኑን የዋጀsewa sewe brhan 1 ያለመሆን፤ ለመምህራን በቂ ደሞዝ ያለመከፈል፤ ከሌሎች መሰል የቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ጋር የልምድ ልውውጥ ያለማድረግ፤ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙ መጻሕፍት በቂ ያለመሆናቸው፤ የመደበኛ ተማሪዎች ቁጥር መቀነስ እንደ ችግር ከጠቀሷቸው ውስጥ ይገኙበታል፡፡

ደቀመዛሙርቱ እንደመፍትሔ ካቀረቧቸው ውስጥ፤ የትምህርት አሰጣጡ በሚመጥን መልኩ ቢቀረጽ፤ ተቋማዊ አቅሙን ወደ ዩኒቨርስቲነት ቢያሳድግ፤ በከፍተኛ ውጤት ለሚመረቁ ደቀመዛሙርት የነጻ ትምህርት እድል ቢመቻች የሚሉት ሐሳቦች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ከ212 ተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል 12ቱ በመደበኛነት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንድ በብሉያት፤ አንድ በሐዲሳት ትርጓሜ የተመረቁ ናቸው፡፡ 200 ደቀመዛሙርት ደግሞ በማታው የትምህርት መርሐ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የኮሌጁ መምህራንና የተመራቂ ደቀመዛሙርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

 

የሚዛን ተፈሪ ማዕከል 14ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ

 

ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በሚዛን ተፈሪ ማዕከል ሚዲያ ክፍል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የሚዛን ተፊሪ ማዕከል ከሰኔ 13 እስከ 15 2006 ዓ.ም 14ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ በአቡነ ተክለ ሃይማኖትና ቅዱስ ኡራኤል የእናቶች አንድነት ገዳም የስብከተ ወንጌል አዳራሽ አካሄደ፡፡

ሦስት ቀናት በፈጀው ጉባኤ የማእከሉ 2006 ዓ.ም ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማዕከሉ ሰብሳቢ በአቶ መስፍን ደጉ የቀረበ ሲሆን፤ በእቅድ አፈጻጸሙ በተገቢው ሁኔታ የተከናወኑትን፤ ያጋጠሙ ችግሮች ፤ የተወሰዱ የመፍትሄ ሃሳቦች እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ችግሮች ከአባላት የአገልግሎት ዝለት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ክፍሎች ያቀዷቸውን እቅዶች አባላት የማስፈጸም አቅማቸዉ ያልተመጣጠነ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በቀረበው ሪፖርት መሠረት የተሻለ የእቅድ አፈጻጸም እንዲሁም ዝቅተኛ የዕቅድ አፈጻጸም ያሳዩ ክፍሎችም ተለይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ለ2007 ዓ.ም. ክፍሎች ራሳቸውን በማጠናከር ያቀዷቸውን እቅዶች ተግባራዊ በማድረግ ጠንክረው እንዲሰሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የ2007 ዓ.ም ዕቅድ በማዕከሉ የዕቅድ ዝግጅትና ከትትል ክፍል ቀርቦም በውይይት በማዳበር ማስተካከያ ተደርጎበት ጸድቋል፡፡

ከማእከሉ አባላት በተጨማሪም ከሀገረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነት፣ ከዋናው ማዕከል፣ ከምዕራብ ማዕከላት ማስተባበርያ፣ ከወረዳ ማዕከላት፣ ከግቢ ጉባኤያትና ከግንኙነት ጣብያዎች ተወክለው የመጡ እንግዶች በጉባኤው ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

 

በንባብ ባሕል ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ

ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የንባብ ባሕልን ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል አዘጋጅነት ሰኔ 28 ቀን 2006 ዓ.ም ከ8፡00-11፡00 ሰዓት በማኅበሩ ሕንፃ ላይ እንደሚቀርቡ ማእከሉ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን የሚቀርቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ሁለት ሲሆኑ፤ “ትርጉም ያለው የንባብ ባሕል”፤ እንዲሁም “የንባብ ባሕልን ለማሳደግ የተለያዩ አካላት ሚና” በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያረጉ የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ አበበ ገልጸዋል፡፡

ትርጉም ያለው ንባብ ምንድን ነው? የንባብ ባሕልን ያሳደጉ አገራት ልምድ ምን ይመስላል? የንባብ ልምድ በሀገራችን እና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሚመስሉ በጥናቶቹ ይዳሰሳሉ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል በየዓመቱ በሀገራችን የንባብ ባሕልን ለማበረታታት ከሚያዘጋጀው የመርሐ ግብር አካል አንዱ ሲሆን፤ ጥናቶቹም የንባብ ባሕላችን ምን ላይ እንደሚገኝ የሚዳስሱና የሚያነብ ትውልድን ለመፍጠር ምን መደረግ እንዳለበት የሚያመላክቱ መሆናቸውን አቶ ሰይፈ ጠቁመዋል፡፡

ይህ የንባብ ጉባኤ ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ በንባብ ባሕል ላይ የሚሠሩ አካላት፣ ምሁራን፤ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት፤ እንዲሁም ምእመናን ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

 

የማቴዎስ ወንጌል

ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም.

ምዕራፍ ሁለት 

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የምንረዳውና የምንገነዘበው ጌታ በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን እንደተወለደ እንረዳለን፡፡ ቤተልሔም ማለት ቤተ ኅብስት ማለት ነው፡፡ ስምዋም የተሰየመው ካሌብ ኤፍራታ የተባለች ሚስት አግብቶ ወንድ ልጅ ከኳ በወለደ ጊዜ እንጀራ እገባ እገባ ብሎት ስለነበር የልጁን ስም ልሔም /ኅብስት/ አለው፡፡ በልሔም ቤተልሔም ተብላለች፡፡

የጥበብ ሰዎች ከሩቅ ምሥራቅ መጥተው የበረከት ሳጥናቸውን ከፍተው ለጌታ ገጸ በረከት አበርክተውለታል፡፡

  • ወርቅ-ለመንግሥቱ

  • ዕጣን ለክህነቱ

  • ከርቤ- ለመራራ ሞቱ፡፡ ምሳሌ ናቸው፡፡

ሰብዓ ሰገል ከሄዱ በኋላ ጌታ ሄሮድስ ሊገድለው ስለሚፈልገው አስቀድሞ በነብያት በተነገረው መሠረት ወደ ግብፅ ተሰደደ ሆሴ.11፡1፡፡

ንጉሡ ሄሮድስም ጌታን ያገኘ መስሎት 144ሺ የቤተልሔም ሕፃናትን አስፈጅቷል፡፡ ከሔሮድስ ሞት በኋላ ጌታ ከስደት ተመለሰ የስደት ዘመኑ 3 ዓመት ከመንፈቅ ነበር፡፡ ራዕይ 12፡7፡፡

እድገቱንም በነቢያት አስቀድሞ እንደተነገረው በናዝሬት ከተማ አደረገ፡፡ ናዝሬት የወንበዴዎች የቀማኞች የተናቁ ሰዎች ከተማ ነበረች፡፡ ጌታም ወደ ተዋረድነው ወደ እኛ መጥቶ ከውርደት ሊያድነን መሆኑን ሊያስገነዝበን በናዝሬት ኖረ፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 3ኛ ዓመት ቁጥር 1 ታኅሥሥ 1988 ዓ.ም.

ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ የድረ – ገጽ አገልግሎት ሊጀምር ነው

ሰኔ 13 ቀን 2006 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል የኦሮምኛ ድረ ገጽ አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀምር የዋና ክፍሉ ሓላፊ ዲያቆን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ገለጹ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊት የጠበቁ ትምህርቶችን በኦሮምኛ ቋንቋ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ዘዴዎች ለምእመናን ለማሰራጨት እቅድ ከያዘ መቆየቱን የገለጹት ዲያቆን ዶ/ር መርሻ፤ የድረ ገጽ አገልግሎቱ ቅድሚያ ተሰጥቶት ለምእመናን ተደራሽ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት “በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኦሮምኛ ድረ ገጽ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፤ ወደፊት የኅትመትና የብሮድካስት ዝግጅቶችን ለምእመናን ለማዳረስ ማኅበሩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ ያደርጋል” ብለዋል፡፡

የኦሮምኛ ዝግጅት ንዑስ ክፍል አስተባባሪ ዲ/ን መዝገቡ ከፍያለው ለኦሮምኛ ድረ ገጽ መከፈት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ሲገልጹ “በኦሮሚያ ክልል ምእመናን ስለ እምነታቸው በቋንቋቸው መማር አለመቻላቸው፤ በቋንቋው የተዘጋጁ ሃይማኖታዊ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ውጤቶች አለመኖር እና ምእመናን በሌሎች የእምነት ተቋማት መወሰዳቸው ነው” በማለት ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት እና ያሉትን ምእመናን ለማጽናት፤ የጠፉትንም ለመመለስ እንዲቻል ከዐውደ ምሕረት ስብከት በተጨማሪ በመገናኛ ብዙኀን ዘዴዎች ወደ ምእመናን ለመድረስ አዲስ የተዘጋጀው ማኅበራዊ ድረ ገጹ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

በድረ ገጹም ትምህርተ ሃይማኖት፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ነገረ ቅዱሳን፤ ስብከት፤ ለጥያቄዎች ምላሽ /ከምእመናን ለሚጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት/፤ መዝሙር እና ኪነጥበብ ወዘተ. . . የተካተቱበት ሥራዎች እንደሚቀርቡ ዲ/ መዝገቡ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የድረ ገጹ አድራሻ፡- www.eotcmk.org/afaanoromo

በተያያዘ ዜና ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝኛ ድረ ገጽ በቅርቡ የሚጀምር ሲሆን፤ የድረ ገጹ አድራሻ፡- www.eotcmk.org/site-en መጎብኘት ይቻላል፡