ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሊጀምር ነው
ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
በማኅበረ ቅዱሳን የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ከኅዳር 12 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እንደሚጀምር የኅትመትና ኤልክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ም/ክትል ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ ገለጹ፡፡
በNilesat, OBS /Oromiya broadcast Service/ ለሠላሳ ደቂቃ ዘወትር እሑድ ከረፋዱ 4፡30-5፡00 ሰዓት እንዲሁም በድጋሚ ረቡዕ ከጠዋቱ 12፡30-1፡00 ሰዓት የሚሠራጨው መርሐ ግብር የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊትን ጠብቆ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለ እምነታቸው እንዲያውቁ እና ጸንተው እንዲኖሩ፣ እንዲሁም ከእምነታቸው ለወጡ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ታስቦ መጀመሩን ምክትል ሓላፊው አስታውቀዋል፡፡
የኦሮሞ ማኅበረሰብን ከቤተ ክርስቲያን ለመነጠል በርካታ መጻሕፍት ታትመው እየወጡ በመሆናቸው የማኅበረ ቅዱሳን የአፋን አሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ይህንን ለመከላከል ምእመናን ለማስተማር፣ እምነታቸውን ጠብቀው ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ ፕሮጀክቱ መቀረጹንም ገልጸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ ምእመናንን የሚያንጹ በርካታ በትምህርተ ሃይማኖት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን፣ የጸሎት መጻሕፍትንና መጽሔት በማሳተም፣ በኦሮምኛ ድረ ገጽ ጭምር ሲያሠራጭ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በቅርቡም Dangaa Lubbuu/ የነፍስ ምግብ/ የተሰኘ መጽሔት በማሳተም ለምእመናን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡


በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎት ተጀመረ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን እንዲሁም በሬድዮ አያሰራጨ የሚገኘውን መንፈሳዊ መርሐ ግብር በአውሮፓም ምእመናን ባሉበት ሆነው በቀላሉ በስልክ ሥርጭቱን መከታተል እንዲችሉ ማድረጉን የአውሮፓ ማእከል አስታወቀ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር የንዋያተ ቅድሳት ማምረቻ ክፍል ነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ቃጠሎ እንደደረሰበት የልማት ተቋማት አስተዳደር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ፍስሐ ገለጹ፡፡
በዕለቱ ቀኑን ሙሉ መብራት ጠፍቶ ስለነበር ምንም ዓይነት ሥራ አገልጋዮቹ እንዳለከናወኑ የገለጹት ዳይሬክተሩ ቃጠሎው የተከሰተው አገልጋዮቹ ከወጡ በኋላ በመሆኑ የአደጋው መንስኤ እሰካሁን አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡ አደጋው የተከሰተበት ምክንያት ፖሊስ የቴክኒክ ምርመራ በማካሔድ ላይ ስለሚገኝ ምርመራው እንደተተናቀቀ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል፡፡


በጎንደር ከተማ በደብረ ስብሐት ቀሐ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም 61 የላይ ቤት የአቋቋም ደቀ መዛሙርት ተመረቁ፡፡
በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መምህር ዳንኤል ኃይሉ የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ቅኔ፣ መሪጌታ ድረስ ቦለድ በቀሐ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የድጓ መምህር ሰሎሞን ምቅናይ እና የድጓ ዜማ፤ የማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል የመዝሙር ክፍል አባላት እና የደብረ ስብሐት ቀሐ ኢየሱስ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡
የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያሠለጠናቸውን ደቀመዛሙርት ሐምሌ 25 ቀን 2007 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ አስመረቀ፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተከናወነው የምረቃ መርሐ ግብር ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የገዳሙ የበላይ ሓላፊዎች፤ የገዳሙ ሊቃውንት እና ደቀመዛሙርቱ በተገኙበት ቅዱስነታቸው በዲፕሎማ እና በሠርተፊኬት ለተመረቁ ደቀመዛሙርት የምሥክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ገዳሙን በታማኝነት እና በቅንነት ለ50 ዓመታት ያገለገሉት የእድሜ ባለጸጋው አባት መጋቤ ሀብታት አባ እስጢፋኖስ ወልደ ኢየሱስ ከገዳሙ የተበረከተላቸውን ካባና የምሥክር ወረቀት ከቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ ተቀብለዋል፡፡