ሰዋስወ ግእዝ

ሰኔ 13 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ት ኑኀሚን ዋቅጅራ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በቅድሚያ በሕያውና ዘለዓለማዊ በሆነ በእግዚአብሔር ስም የከበረ ሰላምታዬን እያቀረብኩ ስለ ግእዝ ቋንቋ አጠር ባለ መልኩ እገልጻለሁ፡፡

የግእዝ ቋንቋ ቀዳማዊነት

ቋንቋ ማለት መግባቢያ መተዋወቂያ መነጋገሪያ አሳብ ለአሳብ መገላለጫ ወዘተ…… ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ባለበት ቦታ ሁሉ ቋንቋ አለ፤ ቋንቋም ባለበት ቦታ ሕዝብ አለ፤ ያለ ሕዝብ ቋንቋ ያለ ቋንቋ ሕዝብ ሊኖር አይችልም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ስለ ግእዝ ቋንቋ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ስንነጋገር፡-

ከአንዳንድ ቀደምት የታሪክ ጸሐፊዎችና የግእዝ ቋንቋ መጻሕፍትን ጽፈው ካስረከቡን ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የቋንቋው ባለቤቶች እንደምንረዳው፡- የግእዝ ቋንቋ አመጣጥ በኢትዮጵያ መነሻ ሊሆነን የሚችለው ከስምንተኛው ምዕተ ዓመት ቅድመ ልደት ክርስቶስ ጀምሮ ነገደ ሴም /የሴም ዘሮች/ወገኖች/ ቋንቋቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሴማዊ ቋንቋ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ቋንቋ ሆነ፡፡ ነገደ ሴም ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ቋንቋቸውን በመግባቢያነት አሳድገው፣ ሥነ ጽሑፋቸውን አስፋፍተው፣ በባቢሎን በአካድና፣ በአሶር ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ለሁለት ተከፍለው ግማሾቹ ሴማውያን ሰሜንና ምስራቅ እስያን፣ ግማሾቹ ሴማውያን ደግሞ ደቡቡ እስያን ይዘው ይኖሩ ነበር፡፡

የሰሜን እስያ ሴማውያን ቋንቋ /የአካድ ቋንቋ/ አማራይክ፣ ዕብራይስጥንና ፊንቄን ሲያስገኝ የደቡብ እስያ ሴማውያን ቋንቋም /አካድ ቋንቋ/ ሳባን ግእዝንና የተለያዩ በኢትዮጵያ ውስጥ በመግባቢያነት የምንጠቀምባቸውን ሴማውያን ቋንቋዎች አስግኝቷል፡፡ በደቡብ እስያ ይኖሩ የነበሩ ነገደ ሴም በተለያየ ምክንያት እየፈለሱ ወደ ደቡብ ዐረብ፣ ወደ የመንና ወደ አካባቢዋ መጥተዋል ከዝያም ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአክሱምና በአካባቢዋ ሰፍረው ይዘዋቸው ከመጡት ቋንቋዎቻቸው መካከል በታሪክ ጎልተው የሚታወቁና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩትና በአሁኑ ሰዓትም በአገልግሎት ላይ የሚገኙት ቋንቋዎች የሳባ እና የግእዝ ቋንቋዎች ናቸው፡፡

ነገደ ሴም /ሴማውያን/ ቋንቋዎቻቸውን /ሳባና ግእዝን/ ከነገደ ካም ቋንቋ ጋር አስማምተው በመያዝ ሁሉንም ቋንቋዎች ሲናገሩዋቸው ኖረው ነበር፡፡ በኋላ ግን ሳባና ግእዝ እየተለመዱና እየተስፋፉ እየዳበሩም ከመሄዳቸው የተነሣ የነገደ ካምን ቋንቋ እየዋጡት መጥተው ሁለቱ ሳባ እና ግእዝ ቋንቋዎች ብቻ ሀገራዊ ቋንቋዎች ይሆኑ ጀመር እየቆዩ ግን ሁለቱ /ሳባና ግእዝ/ በጣም ተመሳሳይና ተቀራራቢ በመሆናቸው እንደ አንድ ቋንቋ ሆነው ይነገሩ ጀመር፡፡ ይኸም ጽሑፉ /ፊደሉ/ በሳባ እንዲጻፍ እና መነጋገሪያ ቋንቋውን ደግሞ በግእዝ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ ነገደ ሴም በሳባ ቋንቋቸው ሳባውያን፣ በግእዝ ቋንቋቸው ደግሞ አግአዝያን ተብለው የሚጠሩት ከዚህ መነሻነት ነበር፡፡

ለዚህም መረጃ የሚሆኑን ሳባና ግእዝ ቋንቋዎች ተጽፈውባቸው የሚገኙት ጥንታውያን የኢትዮጵያ ቅርሶች እንደ የአክሱምና የላሊበላ ሐውልቶች በየሐ እና በአዱልስ ወዘተ….. የተለያዩ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎችና ቅርጻ ቅርጾች እስከ አሁን ቆመው የሚገኙ የዚህ ቋሚና ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ የሳባና የግእዝ ቋንቋዎች በዚህ ሁኔታ እስከ 324 /፫፻፳ወ፬/ዓ.ም. አካባቢ ድረስ አብረው ሲነገሩ ቆይተዋል በኋላ ግን የሳባ ንቋ እየተዳከመና በግእዝ ቋንቋ እየተዋጠ ይሄድ ጀመር እንደ ምንም እየተንገዳገደ እስከ 350 /፫፻፶/ ዓ.ም. ቆይቶ ከዚህ በኋላ ከሥነ – ጽሑፍ ከመነጋገሪያነትም ፈጽሞ ቀረ የግእዝ ቋንቋ ግን ከ324 /፫፻፳ወ፬/ዓ.ም. ጀምሮ ብቸኛ ሀገራዊ ቋንቋ በመሆን እስከ ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም የአማርኛ ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል እንደ ነበር የታሪክ ጸሐፊዎች በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡
፩.፪. የግእዝ ፊደላት አመጣጥ

ስለ ግእዝ ቋንቋ ስንነጋገር በመጀመሪያ ለማንኛውም ቋንቋ መሠረት ስለሚሆነው ስለ ፊደል አመጣጥ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ስለ ፊደል አመጣጥ ሊቃውንት ብዙ ትንታኔ ይሰጡበታል ይኸውም ፊደል ማለት ጽሑፍ ነው ምክንያቱም “ፈደለ” ጻፈ ከሚለው ከግእዝ ቃል የወጣ ነው ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ “ፈደለ” የሚለውም ቃል የሦስት ፊደላት ጥምረት በመሆኑ እነዚህ ፊደላት ከየት እንደመጡ መነሻቸውን /ምንጫቸውን/ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ለዚህ በቂ የሆነ መረጃ እናገኛለን፡፡ የፊደል ስልት አንድም ቅርጽ የተጀመረው የአዳም ሦስተኛ ትውልድ በሆነው በነቢዩ በሄኖስ ዘመን ነው፡፡ ነቢዩ እግዚአብሔርን በማገልገል የታወቀ ደግ ስለ ነበር ለደግነቱ መታወቂያ /መታሰቢያ/ ይሆነው ዘንድ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሕግ ማሰሪያ የሚሆነውን ፊደል በጸፍጸፈ ሰማይ /በሰማይ ገበታነት/ ተገልጦ ታይቶታል፡፡

ስለዚህ የፊደል ቅርጽ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለሥነ-ጽሑፍ በር መክፈቻ በማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡ መጠሪያ ስሙንም ጽሑፍ ለማለት ፊደል ብለውታል፡፡ ይኸስ እውነትነቱ ምን ያህል ያገለግላል ቢሉ በዚያን ጊዜም በጸፍጸፍ ሰማይ ታየ የሚባለው ፊደል የእብራይስጥ ፊደል እኛ አሁን አሌፉት እያልን የምንጠራው ነው፡፡

ስለዚህ ይህ ፊደል ከፊደልነት ጥቅሙ ጋር እንደ ኅቡዕ ስም ይገመታል /ይታመናል/ ምክንያቱም የእያንዳንዱ ፊደል ትርጒም ከእግዚአብሔር ህልውና እና እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ካደረጋቸው የቸርነት ሥራዎች ጋር የተዛመደ ትርጒም ስለሚሰጥ (ስለአለው) ነው፡፡ ይህ እውነታ እና የስም አጠራር ትርጒም ግን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት አባቶች የፊደላት ትርጒም አሰጣጥ ላይ በግልጽ ተጽፎ የሚገኝ ነው /ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት በሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ/ በተጻፈው መጽሐፍ በግልጽ እንረዳዋለን ይህን መነሻ በማድረግ የሥነ-ጽሑፋችን በር መክፈቻ የአሌፋቶችን ስም ፊደል የሚል ስያሜ በመስጠት እንጠቀምበታለን፡- ስለዚህ ማንኛውንም ነገር ለመጻፍ ለመጪውም ትውልድ ለማስተላለፍ በጽሑፍ መቀረጽ ስላለበትና ራሱ ፊደሉ የሥነ-ጽሑፍ መጀመሪያ ስለሆነ ጽሑፍ ለማለት ፊደል ተብሎ ተጠርቷል፡፡

ለዚህም የቤተ ክርስቲያን  አባቶች ሊቃውንት አጽንዖት ሰጥተው ሲያስቀምጡት “ዘእንበለ ፊደል ኢይትነገር ወንጌል” ይላሉ ይህ ማለት ወንጌል ሳይቀር የሚጻፈው /የሚተረጎመው/ በፊደል አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ስለ ፈደል ጠቃሚነት የሚሰጡትን ሐተታዎች ከብዙ በጥቂቱ እንመልከት፡-

፩. ፊደል- ብሒል ነቅዓ ጥበብ ውእቱ፡፡

ፊደል የአእምሮ መገመቻ የምሥጢር መመልከቻ ነው ምክንያቱም ያለ ፊደል ምንም አይታወቅምና ፡፡

፪. ፊደል – ብሂል ነቅዓ ጥበብ ውእቱ፡፡

ፊደል የጥበብ ሁሉ መገኛ ምንጭ ነው፡፡

፫. ፊደል – ብሂል መራሔ ዕውር ውእቱ፡፡

ፊደል የእውር መሪ ነው፤ ምክንያቱም ሰውን ሁሉ ከድንቂርና አውጥቶ ወደ ብርሃን ይመራልና፡፡

፬. ፊደል – ብሂል ጸያሔ ፍኖት ውእቱ፡፡

ፊደል ማለት መንገድ ጠራጊ ነው፤ ምክንያቱም አላዋቂነትን /ድንቁርናን/ ከሰው ልጅ ጠርጎ /አጽድቶ/ ከፍጹም ዕውቀት ያደርሳልና፡፡

፭. ፊደል ብሂል -ርእሰ መጻሕፍት ውእቱ፡፡

ፊደል ማለት የመጻሕፍት ሁሉ ራስ /አናት/ ነው ምክንያቱም ያለ ፊደል ምንም ነገር መጻፍ አይቻልምና፤ /ኢተወልደ መጽሐፍ ዘእንበሌሁ ለፊደል/ ያለ ፊደል ምንም ነገር ሊጻፍ አይቻልምና

የግእዝ ቋንቋ ከሴማውያን ፊደሎች መካከል አንዱና ዋናው ጥንታዊ ቋንቋ ስለሆነ፣ የራሱ የሆነ ብዙ ቃላትን ከነፍቺዎቻቸው ይዞ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንጻር ፊደል የማንኛውም ጽሑፍ መነሻ ስለሆነ፣ ጽሑፍ ብሎ ለመጥራት መጠሪያውን ፊደል ብለውታል፡፡ በአጠቃላይ ቋንቋ እንደ ማንኛውም ቋንቋ የራሱ የሆነ የአጻጻፍን ሥልትና ቅርጽ የተከተለ ጥንታዊና መሠረታዊ ቋንቋ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ይቆየን

ግእዝ ከእስያ ልሳናት ጋር ሲነጻጸር

በዓለም የሥነ ልሳን ጥናት መሠረት የአካድ /የአሦር – አካዳውያን/ ቋንቋ ጥንታዊ ማንነቱ የተረጋገጠው በአንዳንድ የሥነ ጽሑፎች ቅሪት ሲሆን ይህ ቋንቋ በሥነ ልሳን ተማራማሪዎች ዘንድ የምሥራቅ ሴማዊ ልሳን ተብሎ በቅርብ ጊዜ ከተገኘው ከኤብላዊ ቋንቋ ጋር የሚመደብ ነው፡፡ አካድ እና አሦር በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በኦሪት ዘፍጥረት የተገለጹ እና ከኖኅ ዘመን በኋላ የታወቁ መካናተ ሥልጣኔ ናቸው፡፡ በሥነ ጽሑፍ መረጃ የአከድ ልሳን 2500 ቅ.ል.ክ. እንደነበረ ይናገራል፡፡ በኋላ በአራም የአራማውያን የተባለው ቋንቋው ራሱን የገለጸበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሥነ ቅሬተ ምድርም ሆነ በሥነ ልሳን ተመራማሪዎች ዘንድ አካድ የኢኮኖሚ፣ የሕግ የአስተዳደር፣ የታሪክና የሥነ ጽሑፍ መረጃዎች እንደነበረው የተረዳ ነው፡፡


    
የካምም ልጆች ኩሽ፣ ምጽ/ስ/ ራይም፣ ፋጥ፣ ከነዓን ናቸው፡፡ የኩሽም ልጆች ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ሬጌም፣ ሰበቅታ ናቸው፡፡ የሬጌም ልጆችም ሳባ፣ ድዳን ናቸው፡፡ ኩሽም ናምሩድን ወለደ፣ እርሱም በምድር ላይ ኃያል መሆን ጀመረ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ እንደናምሩድ ተባለ፡፡ የግዛቱም መጀመሪያ በሰናኦር አገር በባቢሎን አሬክን አርካድ ሌድን ናቸው፡፡ አሦርም ከዚያች አገር ወጣ፡፡ ነነዌን የረሆቦት የተባለችውን ከተማ ካለህን በነነዌና በካለህ መካከልም ሬሴንን ሠራ፡፡ እርስዋም ታላቂቱ ከተማ ናት ምጽራይምም ሉዲምን ኢኒሜቲምን ላህቢምን ነፍታሌምን ጳጥሮሰኒምን ከእነርሱ የፍልስጥኤም ሰዎች የወጡባቸውን ከሳሎሂምን ቀፍቶሪምንም ወለደ፡፡ ዘፍ. 10፡6-14

 

አፍሪካዊያንም በየዘመናቱ የሥልጣኔ ማእከሉን በወንዞች ጤግሮሰ እና ኤፍራጥስ ዳር እንደ መሠረቱ ፤ አካዳውያን ፈለገ ግዮንን የራሱን ለአፍሪካውያን ሕዝቦች የሥልጣኔ መሠረት አድርጎ መቆየቱ የሚታወስ ታሪክ ነው፡፡ አፍሪካውያን በራሳቸው ፊደል ቢጠቀሙም በተለያዩ የዓለም ዐቀፍ ተጽዕኖዎች ሥር በመውደቃቸው መሠረታዊውን ፊደል ጽሕፈታቸውንና ቋንቋቸውን ሊያጡ ችለዋል፡፡ ይህንን ፊደል ጠብቃ የተገኘችው ኢትዮጵያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ፊደልና ቋንቋም በሥነ ጽሑፍ መረጃነት ለዓለም ከቀረቡት ልሳናት የሚታወቅባቸው ባሕርያት ሲኖሩት ከጠፋው ከአካድ ቋንቋ ይብልጥ በሥነ ጽሑፍ መረጃነቱ ራሱን ያሳደገ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህንም በቋንቋው ጠባያት ከአካድ ጋር ቢመሳሰል በራሱ ደግሞ ከአፍሮ እስያ ከቋንቋ መለየት ይህ ሴማዊና ካማዊ ብሎ ለመጠቅለል የሚያስቸግር ቢሆንም በቋንቋ ጥናት ዋና የመለያ ፍጥረት በማጥናት መመደብ የሚቻል ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር ግእዝን ሴማዊ፣ ደቡብ ሴማዊ፣ ሰሜን ሴማዊ /በኢትዮጵያ/ አድርገው የሚከፋፍሉበት፡-

 

– ልዩ ልዩ አስማተ መካናት መመሳሰል ምሳሌ- ሳባ
– የቋንቋዎቹ የራሳቸው መመሳሰል
– የሥነ ቅርጽ መመሳሰል ወዘተ ሲሆን ግእዝ ከነዚህ ቋንቋዎች መደብ የሚለዩት ጠባያት አልነበሩትም፡፡ ወይም ደግሞ በእነዚህ ቋንቋዎች የተዘነጉ ጽሑፎች በግዕዝ ግን አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡ ለአብነትም ያህል «ተስዐቱ» የሚለው የጥንት ሥርው ምን ይመስላል የሚለው ሲጠና ከአረማይክ ይልቅ የግእዝ «ታስዕ» የሚለው ቃል ቀዳሚነት ጥንታዊነት ይኖረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አረማይክ ያጣውን ግእዙ በመጠበቅ እንዴት አረማይኩ ለግእዝ በዘመኑ ያጣን ቃል ሊያቀብለው ቻለ የሚል ጥያቄ አስነሥቷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ግእዝ በድምጸ ንባቡ የለሌሎች የአፍሪካ ልሳናት እና የሩቅ ምሥራቅ ልሳናት የሚታወቁበትን የድምፀት ንበት በመያዝ ከአፍሪካ ልሳናት ጋር ሊያመሳስለው ይችላል፡፡


 
ምሳሌ፡

                ቀዳማይ     –     ካልአይ

አካድያን  –     ያቅቱል       –     ያቀትል
ዐረበኛ    –     ቀተለ         –     ያቀቱል
ግእዝ     –     ቀተለ         –     ይቀትል
   

ማስታወሻ- አካድያን ያቅትል ሲል በ «ይ»እና በ «ቅ» መካከል አናባቢ«አ»ኔ ሲጨምር ግእዙ ግን አይጨምርም፡፡ በተጨማሪም በግእዝ ቋንቋ በቀዳማይ አንቀጽ ዝርዝር ጊዜ የአገናዛቢ ቅጥያዎችን የምንጨምር ሲሆን አካድያን ግን የሰማዊነት ባሕርይን የሚያሳይ ነው፡፡

 
ቀዳማይ፡-
ግእዝ – አካድያን
አነ – ቀተልኩ – አቅቱል
አንተ – ቀተልከ – ተቅቱል
አንቲ – ቀተልኪ – ተቀቱሊ
አንትሙ – ቀተልክሙ – ተቅቱላ
አንትን – ቀተልክን – ተቅቱላ
ንሕነ – ቀተልነ – ኒቀቱላ
ውእቱ – ቀተለ – ተቅቱል
ይእቲ – ቀተለት – ኢቅቱል
ውእቶሙ – ቀተሉ – ኢቅቱሉ
ውእቶን – ቀተላ – ኢቅቱላ
ለካልአይ – ግእዝ – አካድያን
አነ – እቀትል – አቀትል
አንተ – ትቀትል – ተቀተል
አንትሙ – ትቀትሉ – ተቀተላ
አንትን ትቀትላ – ተቀተላ
ንሕነ – ንቀትል – ኒቀተላ
ውእቱ – ይቀትል – ኢቀተላ
ይእቲ – ትቀትል – ተቀተላ
ውእቶሙ – ይቀትሉ – ኢቀተሉ
ውእቶን – ይቀትላ – አቀተላ
አንቲ – ትቀትሊ – ተቀተሊ
 

ጥንታዊ ቃላትን እየወሰዱ ቋንቋን በአንድ መመደብ የሚቻል ነው፡፡ ጥንታዊ አናባቢ /ኧ/ ከአካድያን ይልቅ በግእዝ መጠበቁ ግእዝን ልዩ ያደርገዋል፡፡ አካድያን እና ግእዝ በካልአይ የመጥበቅ ድምጽ ሲኖራቸው ጥንታዊ የደቡብ ዐረብ ልሳን ግን የሌለው በመሆኑ ግእዝን እንዴት ከሌላው ቋንቋ ከሳባ መጣ እንላለን? በተጨማሪ የግእዝን ከሌሎች ከሚመስላቸው ከማዕከላዊው ምሥራቅ ሀገራት ቋንቋዎች ስናገናኘው የጥንታዊ የቋንቋ ባሕርይ ቅርጽና ድምጽ መያዙን የምናገኝባቸው ቃላት እንጠቀማለን፡፡

 
ጥንታዊ ቃል – የአካድ – ዐረበኛ – ዕብራይስጥ – የሦርያ – ግእዝ
አብ «-»    አብ –         አብ –     አብ –         አባ –   አብ
ልበ – ልብ – ሉብ /ጥ/ – ሌይብ /ጥ/ – ሌባ – ልብ
ቤት /በይት – ቢቱ – በይት – ባይ /ቤት – በይት /ታ – ቤት
ደም- – – ደም – ዳም – ድማ – ደም
ዐይን – ዓን – ዐይን – ዐዪን – ዐይ-ና – ዐይን
ወይን – – – ወይን – ያዪን – – – ወይን
ወዘተ. . .
ይ – – – /ይ/ አልቦ ዪ – ይ

አይቴ ብሔሩ ለግእዝ?

 

ግእዝ የማን ቋንቋ ነው? የካም ወይስ የሴም ቋንቋ የሚለው የብዙዎች ምሁራን ጥናት እና ጥያቄ እየሆነ መጥቷል፡፡ ግእዝን የሴም የሚያደርጉት የሶቢየት ምሁራን ኤቢ ዶጎልስኪ /A.B. Dogopolsky/ እና ኢጎር ዲያኮኖፍት /Igor Diaknoft/ ግእዝ የደቡብ ሴማዊ ልሳን ሳይሆን በዐረብ ምድር የመጀመሪያዎቹ የአፍሪካውያን ወይም የኩሻውያን ቋንቋ ነው ይላሉ፡፡

 

የዚህን ወገን ሐሳብ የሚጋሩት ደግሞ ቸክ አንተ ዲዮፕ /Cheik Anta Diop1919/ «ተርሰሃሌ» ጥበቡ፣ «አቤንጃ»፣ ኃይሉ ሀብቱ /1987/፣ አስረስ የኔሰው፣ ሺናይደር /1976/ እና አየለ በክሪ/1997/ ወዘተ ናቸው፡፡ ለዚህ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ ከአፍሮ እስያ ቋንቋዎች ብዙዎቹ የሚገኙት በኢትዮጵያ ነው የሚል ሲሆን በተጨማሪም በጣም ብዙ ቋንቋዎች በተለያዩ ቡድኖች በተቀራረበ እና በተወሰነ መልከዓ ምድር ስለሚነገሩ ነው፡፡

 

መርቶኔን /A.Murtonen/ ግእዝን ሴማዊ /ከኢትዮጵያ የወጣ/ ቋንቋ ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡ ሊኦኔል ቤኤንደርም በተመሳሳይ ሁኔታ፡፡ ከዚህም አልፈው ግእዝን የአዳም ቋንቋ፤ የመላዕክት ቋንቋ የሚሉት አልጠፋም፡፡ ምንም እንኳን የካም ወይም የሴም ብለው ቢከፍሉትም፡፡ ተጠቃሾቹም ሲዲ ጳውሎስና አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ናቸው፡፡

 

«ሴማዊ ነው»፡፡ የሚለውን ሐሳብ ቢቀበሉትም የግእዝ ተናጋሪዎቹ እነማን እንደነበሩ አላውቅም የሚሉት ጌታቸው ኃይሌ ናቸው፡፡

 

በአንጻሩ ካም ወይም ሴም የሚለውን ቃል ከቋንቋ ጋር በማገናኘት የተጠቀመበት የጀርመን መልእክተኛ ጆህን ሊዊድግከፈ /Johunn Luowigkapf1810-1881/ ነው፡፡ ከርል ፍሬድሪክ ሌፐሲየስ /Karl Freidrich Lepsius/ ካምን ሴማዊ አይደለም ይላል፡፡ ከቋንቋ ጥናት በመነሳት ነው ይህን ሊል የቻለው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት ያለው የሥነ ልሳን ጥናት ከሐረገ ዘር ይልቅ መልክዐ ምድራዊ በመሆኑ የካምጠሴም ቋንቋ መባሉ ቀርቶ በአፍሮ እስያነት ውስጥ በአጠቃላይ የሚታይ ነው ይላል ዮሴፍ ግሪን በርገ /Joseph Green berg/፡፡ የዮሴፍ ግሪን በርገ /Joseph Green berg/ ሐሳብ የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ሐሳብ የተስማማ ነው፡፡

 

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ካለው ግንዛቤ የተነሣ የኢትዮጵያን ቋንቋ ግእዝን አፍሪካዊ የኢትዮጵያ ልሳን ውልደቱን እና እድገቱን ኢትዮጵያ አድርጎ በዘመነ ባቢሎን ሊነገር የሚችል ዓለም ዓቀፋዊና ጥንታዊ ልሳን ነው ብሎ ያምናል፡፡ የግእዝ የመጀመሪያ ጽሑፍ በ500 ቅ.ል.ክ የተጻፈ ሲሆን በአናባቢ መጻፍ የተጀመረው ግን በ4ኛው መቶ ዓ.ም ነው፡፡ ይህንንም በተከታይዮች አርእስተ ነገር ላይ ለማሳየት እንሞክራለን፡፡

የግእዝ ቋንቋ ፡ –

ሀ. የጽሕፈት ዘዴ አቡጊዳ
ለ. የጽሕፈት አቅጣጫ ከግራ ወደ ቀኝ አግድም /ከሳባ የሚለይበት ነው/
ሐ. እያንዳንዱ ፊደል በአናባቢ የተገለጸ እና አናባቢ የሌለው ሆኖ ሊጻፍ የሚችል ዓለማቀፋዊና ጥንታዊ ልሳን ነው ብሎ ያምናል፡፡
   

3 የግእዝ ቋንቋ ፊደላትና ትርጉም፡-
    

የግእዝ ቋንቋ ፊደላት የራሳቸው መለያ ትርጉም ሥዕላዊ መገለጫ ያላቸውና ከጥንት ጀምሮ ከጥቅም ላይ የዋሉ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ የግእዝ ቋንቋ መሠረታዊ ድምጾችን ሳይለቅ ከዘመን ዘመን በሚደረገው የሥነ ጽሕፈት ልውጠትም አዳዲስ ፊደላትን ለመፍጠር ያስቻሉ ፊደላትን ይዟል፡፡ እነዚህ ፊደላትም ለአፍሪካ እንደመሠረትነት ያገለገሉ ከመሆናቸውም በላይ ለአሁኑ የሥነ ጽሑፍ ሀብታችን መሠረቶች ናቸው፡፡ ፊደላቱ በአናባቢ ተዋሕደው ቃላትን ሊወልዱ ቋንቋን ሊያበለጽጉ ችለዋል፡፡ የራሳቸው የሆነ ቅርጽ እና ፍቺም ያልተለያቸው ናቸው፡፡

ነዛሪ የጉሮሮ እግድ – አ – አሌፍ አልፍ አብ
ነዛሪ የከናፍር ፈንጂ – በ – ቤት ባዕል
ነዛሪ የትናጋ ፈንጂ – ገ – ጋሜል ገምል
ነዛሪ የጥርስ ፈንጂ – ደ – ዳሌጥ ዳ/ን/ልት
ነዛሪ የጉሮሮ ፍትግ – ሀ – ሆይ ሆይ ሀወይ
 
የከናፍር ትናጋ ደኃራይ – ወ – ዋው ዋዌ ዋሕድ
ነዛሪ የጥርስ ፍትግ – ዘ – ዘይ ዛይ
ኢነዛሪ የማንቁርት ፍትግ – ሐ – ሔት ሐወት ሕያው ሕይወት
ነዛሪ የትናጋ ፍትግ – ኀ – ኀርም ኄር
ኅዩል ኢነዛሪ የጥርስ ፈንጂ – ጠ – ጤት ጠይት ጠቢብ
ቅሩብ የከናፍር ትናጋ ደኃራይ – የ – ዮድ የማን
ኢነዛሪ የትናጋ ፈንጂ – ከ – ከፍ ከሃሊ
ጎናዊ – ለ – ላሜድ ለዊ ልዑል
ከናፍራዊ ወአንፋዊ – መ – ሜም ማይ ምዑዝ
የጥርስ ወአንፋዊ – ነ – ኖን ነሐስ ንጉሥ
ኢነዛሪ የጥርስ ፍትግ – ሠ – ሣምኬት ሣውት
ነዛሪ የማንቁርት ፍትግ – ዐ – ዐይን ዐቢይ
ኢነዛሪ የከንፈር ፈንጂ – ፈ – ፈፍ ፈቁር
ኀዩል ኢነዛሪ የጥርስ ፍትግ  – ጸ – ጻዴ ጸደቅ ጻድቅ
ፀ – ፀጰ

ኀዩል ኢነዛሪ የትናጋ ፈንጂ – ቀ – ቆፍ ቅዱስ
የድድ ተርገብጋቢ – ረ – ሬስ ራእስ
ኀዩል ኢነዛሪ የጥርስ ፈንጂ – ሰ – ሳን ስቡሕ
ኢነዛሪ የጥርስ ፈንጂ – ተ – ታው ተዊ ትጉህ
ነዛሪ የከንፈር ፈንጂ – ጰ – ጰይት ጴት
ኢነዛሪ የከንፈር ፈንጂ – ፐ – ፐ ፌ
    

ከላይ እንዳየነው የግእዝ ፊደላት ቢሆኑም ቋንቋ ምንጊዜም በለውጥ ስለሚሄድ ስለሚወልድ እና ስለሚረባ ሌሎች ልዩ ልዩ ድምጾችን እንደፈጠረ እንረዳለን፡፡ ለዚህም የ «ሰ»ን ድምጽ የመሰለ «ሠ» የ«በ»ን ድምጽ የመሰለ ፐ እና ጰ ሌሎችም በየዘመናቱ ሲፈጠሩ ከመግባቢያነት አልፈው በሥነ ጽሑፍ ደረጃ ታሪክን አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም ዛሬ የማይነገሩ «ደ»ን የመሰለ ደ፣ ዘ የጠበቁ.. ወዘተ በየዘመናቱ እንደነበሩ የሥነ ልሳን ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ የግእዝ ፊደላት ትርጉም እና ሃይማኖታዊ ምስጢ ብቻ ሳይሆን ሥዕላዊ መገለጫዎች እንደነበሩት መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ፊደላቱም በሥዕልነት ብቻ ሳይሆን መሠረተ አኀዝ መሆናቸውንም እንመለከታለን፡፡ ምሳሌ አ አልፋ ሲባል የበሬ ቀንድ እንደሚመስል አልፋም በላሕም ተተክቶ በመ.ቅ ይገኛል፡፡ ምሳሌ፡- አባግዐኒ ወኩሎ አልሕምተ ሲል መዝ. 8.7 በዕብራይስጥ ጾጊ ወአላፊም ይላል /ኪ.ክ/፡፡ ጥናት እንደሚያመለክተውም ላሕም ልሔም /እንጀራ/ ከእብራይስጥ ቃል የተወሰደ እና ከአላፊም ቦታ የገባ መሆኑን የሚጠቁም የሥነ ጹሑፍ መረጃ ይገኛል፡፡ ጋሜል ገመል /አባ ገሪማ የሚገኝ ወንጌል እንደ ሚያስረዳው/፡፡ ከፍ የሚለው ቃልም በትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 1.7 እግሮቻቸው ከፍ ያሉ እግሮች ነበሩ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ ኮቴ ነበር ሲል ጥጃ ከፍ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ዮድ በቀኝ እጅ፣ ነ በእባብ፣ መ በውኀ ሞገድ፣ ዐ በዐይን፣ ፈ በአፍ፣ ረ በራስ፣ ተ በመስቀል፣ በ በቤት… መመሰላቸው ፈጣሪ ለሰው ልጅ ራሱን በሚታይ ነገር ከመግለጽም በላይ የፊደላትን ትርጉም ብቻ ሳይሆን ነገረ ድኅነትንም በመስቀል ምልክት በታው/ተ መደምደሙን ያሳየናል፡፡ በግእዝ ፊደላት የድምጽ ለውጥን በማድረጋቸዉ ከጊዜ ብዛት ትርጉማቸዉ ሲዛባ እና ሥዕላዊ መገለጫቸው በተወሰነ ደረጃ ጎድሎ የዘፈቀደ ትርጉም ሊሰጣቸዉ ይችላል፡፡ ምሳሌ «ጥ»ሽ «ት» ወይም «ት»ሽ «ጥ» በመለወጥ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፡፡ በአንጻሩም በቋንቋው የድምጽ ትርጉም ሊሠራላቸው እና ከአንድ በላይ የተለያዩ ትርጉም ሊኖራቸዉ መቻሉ የማይቀር ነው፡፡ የፊደላቱ መለዋወጥ ግን ትርጉም የሚያበላሽ ምስጢር የሚያፋልስ መሆኑ የተረዳ ነው፡፡ ይኽንኑ ለመግለጽ ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ «መዝገብ ፊደል» በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል፡፡

እንዳገኙ መጣፍ በድፍረት በመላ
የቋንቋ ደረመን የመጽሐፍ ቢስ ገላ
ንባብ የሚያሳክክ ምስጢር የሚቆምጥ
መልክአ ትርጓሜ የሚለዋውጥ፡፡
   

ይህን ማለታቸውም የፊደል ቁጥር ማጉደሉ፣ ምስጢር ማበላሸቱ ሥርዓተ ልሳን ማፋለሱ አንድና ብዙ ሩቅና ቅርብ ሴትና ወንድ አለመጠንቀቁ ጸያፍነቱና ግዴለሽነትን በማምጣቱ ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔ ይሆን ዘንድ ታላቁ ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማስ ጀምበሬ በመልእክታቸው ሊቃውንቱ ተስማምተው ጉባኤ ሠርተው ሊወያዩበት ይገባል ብለዋል፡፡ የፊደላቱ ምንነትና ምስጢር ሊጠፋ የቻለው እንደነ መልአከ ብርሃን አባባል የጽሕፈት ትምህርት ቤት ባህልና ትውፊት መረሳቱና ጸሓፍያን ለፊደላት ትርጉም ሳይጨነቁ ለቅርጽ ማማር ብቻ ትኩረት መስጠታቸው ነውና ይኽንኑ ሥርዓት ባለቅኔዎችም ባለማስተዋል ለቤት መምቻ ውበት መጠቀማቸው ነው፡፡

 

የግእዝ ፊደላት ለአኀዝ መሠረት ናቸው ስንል የምናነሳው ዝምድናቸውን ሲሆን ለምሳሌ የግእዝ 6 7 ቁጥሮች «-» ምልክት ሳይኖራቸዉ ይገኛሉ፡፡

የግእዝ ቁጥሮች መሠረታቸው ፊደል ነው፡፡ ስንል እንደ ፊደሎችም ቁጥሮች ከዘመን ዘመን ቅርጻቸዉን መልካቸውን ሲለዋውጡ እና የአሁኑን መልክ ሲይዙ ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይም ቋንቋው የራሱ የሆነ ሥርዓተ ነጥብ የሥነ ጸሑፍ አካሄድ የምንባብ አጀማመር እንዳለው ይታወቃል፡፡

ዝክረ ልሳነ ሰብእ ቀዳማዊ

1. ግእዝ ምስለ ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመናት የፈተና ገፈታ ቀማሽ በመሆን፣ ልጆቿን እያበረታታች ለሀገራዊ ሀብት መጠበቅም እስከ ሰማዕትነት እያበረከተች በየአድባራቱና ገዳማቱ ጠብቃ አሳድጋ ለዚህ ትውልድና ዘመን ካቆየቻቸው ዕሤቶች አንዱ ግእዝ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ቤተ መዘክር፣ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት፣ ቤተ ክርስቲያን ግምጃ ቤት፣ ቤተክርስቲያን የሥልጣኔ ማዕከል፣ ቤተ ክርስቲያን ከተማ ሀገር በመሆን ስታገለግል ቆይታለች፡፡

ስለዚህም ነው በሀገሪቱ የታሪክና የመዛግብት ጥናት ላይ የረጅም እድሜ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር ሪቻድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ባህል ጠባቂ ናት ሲሉ በውዳሴ ዘጽድቅ የሚመሰክሩላት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የግእዝን ሥነ ጽሑፍ ሆነ ቋንቋ እንደሚከተለው ጠብቃ አስረክባናለች፡፡

በየጉባኤያቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ማዕከለ ትምህርት በመሆን ለዘመናት ሕዝቡን አገልግላለች፡፡ በራሷ ባሕላዊ ሥርዓተ ትምህርት ዜማውን ቅኔውን ትርጓሜ መጻሕፍቱን በዚሁ ቋንቋ ስታስተላልፍ ቆይታለች፡፡ እነዚህም ትምህርቶች የሚከናወኑበትን ትምህርት ቤት ከቤተክርስቲያኗ ዐውደ ምሕረት ዙሪያ በተዘጋጁ የመቃብር ቤቶች፣ ዙሪያውን  በተሠሩ ጎጆች አልያም በዙሪያዋ በተተከሉ ዐጸዶች አትሮንሷን ዘርግታ፣ አዘጋጅታ፣ ዜማውን አሰምታ፣ ግሱን አስገስሳ ምስጢሩን አብራርታ አስተላልፋለች፡፡ ይህንንም ስታደርግ ለደቀመዛሙርቱ ከሰንበቴው ከደጀ ሰላሙ ረድኤት እያሳተፈች ነው፡፡

በሊቃውንት የሊቃውንት፣ የፍቅር ሀገር፣ ሕይወተ ክርስትና፣ ፍሬ በረከት ስላላቸውና ዘወትር ቃለ እግዚአብሔርን በመናገር፣ ደቀ መዝሙር ሲያጠፋ ሲያርሙ ሲሳሳት ሲያስተካክሉ፣ የተበላሸውን ሲያቀኑ ባሳለፉት ድካም ሀብተ ታሪክን አውርሰዋል፡፡ የደረሷቸውን ቅኔያት፣ የጻፏቸውን መጻሕፍት ዜና መዋዕላቱን ጭምር ሲደጉሱ፣ ሲኮትቱ የተሻለ ቅርጸ ፊደልን ሲያወርሱን ወዘተ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው አብልጠው በመኖራቸው ነው፡፡ በመሆኑም ዳዊቱን እየደገሙ፣ መጻሕፍትን እየተረጎሙ ያብራሩበትም በዚሁ ልሳን ነው፡፡ በዚህ ሳይወሰኑ ሌትም ቀንም እንቅልፍ አጥተው ከማኅሌቱ፣ ከሰዓታቱ፣ ከጉባኤ ቤቱ ሳይለዩ ስለ ነገዋ ቤተ ክርስቲያን በመጨነቅ ያስተማሩትን ደቀ መዛሙር «ኦ ወልድየ ጽንዐ በጸጋሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅዱር ላዕሌከ በመንፈስ ቅዱስ» ልጄ ሆይ አድሮብህ ባለው በመንፈስ ቅዱስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋው ጽና ምከር አስተምር ብለው የቃል አደራ በመስጠት በየአህጉሩ ሲያሰማሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ጸሎታቸውን ለሀገር በሱባኤ ሲያደርሱ ኖረዋል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ሀገረ ሙላዳቸውን በመተው ደበሎ ለብሰው፣ ቁራሽን ተማምነው፣ አኮፋዳቸውን ከሰሌን አዘጋጅተው፣ ዳዊታቸውን በትከሻቸው አንግበው በትምህርተ ቤተክርስቲያን ዘመናቸውን ያቆዩ ተማሪዎችም ባለውለታ መሆናቸው የማይዘነጋ ነው፡፡ እድሜ ሳይገድባቸው ገና በልጅነት እድሜያቸው ጥሬ እየቆረጠሙ በውርጭ እየተነሡ ሀገር ለሀገር በመዞር ምስጢር ሲሸምቱ የአባቶቻቸውን ትውፊት በቃል በመጽሐፍ ያስተላለፉ ደቀ መዛሙርቱም እነዚሁ ናቸው፡፡ እነዚህም በሌሊት እየተነሡ ከመምህራቸው እግር ሥር ሆነው በብርዱ፣ በቁሩ ሲቀደሱ ሲያስቀድሱ፣ የሌሊቱን ዝናብ ታግሰው ሳይታክቱ በመምህራቸው ጓሮ በትጋት የተማሩባቸውን ጉባኤያት እያስታወሱ ሲያስተላልፉ ኖረዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ያለኀፍረት ራሱን ዝቅ አድርጎ በምእመናን ደጃፍ ዐረፍ ብሎ የተገኘውን እየተዘከሩ ወደ ጉባኤው ሲመለሱ እያዜሙ፣ ቅኔውን እየቆጠሩ፣ ወንዙን እየተሻገሩ፣ ተራራውን እየወጡ፣ እየወረዱ የአራዊቱን ድምጽ እየሰሙ፣ ተፈጥሮን እየቃኙ፣ ምስጢርን እያዩ ያዩትንም በቅኔው እየቀመሙ ለነባር ሲያስተላልፉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለክብረ በዓሉ ያለውን ቀለም በአፋፍ ላይ ሆነው እየቀጸሉ በጎጆአቸው ሌሊቱን ሲያዜሙ በራሳቸው ቋንቋ «አዛኘን» እስኪ በልልኝ  በመባባል እየተሳሳሉ ለዘመናት ትምህርቱን አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መምህራቸውን በእርሻ፣ በማሳ፣ በሥራ እየረዱ ነው፡፡

 
ምዕመናን ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው ባላቸው ፍቅር ሃይማኖታቸውን ከቤተ ክርስቲያን አጣምረው ኖረዋል፡፡ በባህል ግንባታውም ተሳትፈዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ተማሪንም ከመሶባቸው ማዕድ ሳይሰስቱ እየመገቡ ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ቤተክርስቲያን እንድትገለገል ጧፉን መጋረጃውን አሥራቱን ሲያስገቡ ባደረጉት አስተዋፅኦ የቤተ ክርስቲያኗ ሀብቷ እንዲህ ሊተላለፍ ችሏል፡፡ ዋዜማ እየደገሱ ቁመት ሲያስቆሙ ዕድሞ ሲያስከብሩ ኖረዋል፡፡

2. የግእዝ ቋንቋ እንዲያድግ ለምን አስፈለገ?

ባህል በቋንቋ ይለካል፡፡ እምነቶች ሥነ ሕዝብ ማኅበራዊ መሠረቶች /ዐምዶች ልምዶች ዕውቀቶች ሁሉ በቋንቋ አሉ፡፡ በአደጋ ላይ ያለ ቋንቋ ማለትም በአደጋ ላይ ያለ ዕውቀት አሳሳቢ፤ ባህል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ አገባብ የሚታወቀው ዕውቀት ካፀፀ መሠረት የለሽ ድካምን ያስከትላል፡፡

በመሆኑም ቋንቋ የኅብረተሰብእ /የአንድ ሕዝብ አካል ነው፡፡ ስለ ሕይወት ባህል ልምድ የሚፈስ ዕውቀት ሁሉ ትርጉም የሚኖረው በራስ ቋንቋ በሚገኝ ዕውቀት እንጂ የተጻፈን በመቀበል አለመሆኑ ደግሞ የራስ ቋንቋን ማወቅ ወሳኝ መሆኑን ያሳያል፡፡ ልሳናት በአባቶች ቅድመ አያቶች ቀሩ ማለት የልጆች ሀገራዊ አንደበታቸው ማንነት የሚጠብቁበት ኃይል ጠፋ ማለት ነው፡፡ የእኛ ማንነትና ታሪካችን ያለው የተቆራኘው በብዙ መንገድ ከቋንቋችን /ከግእዝ ጋር ነውና ያለበትን ደረጃ ልንመረምርና ልናስተውለው ይገባል፡፡ ሌላው ይቅርና መለያችን ልዩነታችን እንኳን በቋንቋችን ሰዋስው አገባብ ሊታወቅ ይችላል፡፡ ቋንቋችን ካልተጠበቀ የሚተላለፈው ዕውቀት ትውፊት ባለበት ይቆማል፡፡ አብሮ አስሮ የያዘቸውን እውቀቶች ፍልስፍናዎች ሁሉ ይዞ ይጠፋል፡፡ ነገር ሁሉ በአዲስ ይጀምራል፡፡ ሥር የሌለው በአሸዋ የተገነባ ሕንፃን ይመስላል፡፡ የሌሎች የባህል ጎርፍ በመጣ ጊዜ በቀላሉ ይወድቃል፡፡ ቋንቋን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን እንደገና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ በስደት፣ በዝርፊያ በዓለም ዙሪያ በየቦታው ያሉትን የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ሊመረምሩ የሚችሉ ልጆች ሊተኩ ያስፈልጋል፡፡ የተበረዘውን ማቅናትና የጠፋውን ታሪክ መፈለግ፣ የተለየንን የጥበብ ምንጭ ፍለጋ መውጣት መውረድ ያስፈልጋል፡፡ ሊጠፉ የተቃረቡትንም መጠበቅና ብሎም ዘመኑ ባፈራቸው መሳሪያዎች ተጠቅሞ በመቅረጽ ለትውልዱ ማስተላለፍ ትልቁ ኃላፊነት ይኸው ነው፡፡

አፍሪካውያን ዛሬ ቋንቋቸውን ለመጠበቅ የሚያደክማቸው ለብዙ ዘመናት በተሰላ እቅድ ሥር ተጽዕኖ በመውደቃቸውና በሌላኛው የቅኝ ግዛት መንገድ ማለፋቸው ነው። እንዳልነው ይህ ችግር ደግሞ ዛሬም ከአፍሪካ ምድር ስላልተወገደ በአደጋ ላይ የነበሩ ዕውቀቶች ሁሉ ጠፍተዋል፡፡ መፍቀርያነ ባህል አፍረንጅም በመብዛታቸው ነባሩ/ የአከባቢው መንፈሳዊውም ሆነ ቁስ አካላዊው ዕውቀት እየተረሳ መጥቷል፡፡ ይህንን እየተረሳ ያለ ሀብት ደግሞ ለመጠበቅ ልምዱ ያላቸው ወላጆችና ሽማግሌዎች አስረካቢ ሕፃናት ተረካቢ ሊሆኑለት ይገባል፡፡ እንግሊዘኛቸውን ሲናገሩ በማበላሸታቸው የሚስቁ ይቅርታ የሚጠይቁትን ወጣቶችን ልብ አማርኛን ግእዝን ግን በማበላሸታቸው ግን ይቅርታ የማይጠይቁትን አእምሮ ሊያጠቁት ይችላሉ፡፡ በዚያውም ላይ የውጪውን ቋንቋ በመጠቀም የአንደበታቸው አርአያነት ብቻ ሳይሆን መልዕክቱ የተዛባ እየሆነ መጥቷል፡፡