ዘጠነኛው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ሊካሄድ ነው

ዘጠነኛው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ በመጭው እሑድ ግንቦት ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ/ም ሊካሄድ እንደሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ መምህር ዕንቈ ባሕርይ ተከሥተ አስታወቁ፡፡

የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም የሐዲስ ኪዳን ደቀ መዛሙርት ተመረቁ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማእከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም የመጻሕፍተ ሐዲሳት እና ሊቃውንት ጉባኤ ቤት 18 የሐዲስ ኪዳን ደቀ መዛሙርት ኅዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተመረቁ፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግፍ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገለጸ

በአለፉት ሳምንታት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎችን ከሚማሩበት ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች በማሳደድ እና የተወሰኑትን እንዳይወጡ በማገድ ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ማፈናቀል የጀመሩት የጥፋት ኃይሎች በመቱና ቦንጋም ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸሙ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት የተደረገው ሙከራ ከሸፈ!

ኅዳር ፲፪ የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል ከተከበረ በኋላ ኅዳር ፲፭ በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ተሰቅለው የነበሩትን ሰንደቅ-ዓላማዎችን እያወረዱ ወደነበሩት የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች…..

አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውና መዘረፋቸው ተገለጸ

 

                                                                                                                                                                                                                                                                       በሕይወት ሳልለው     

በሲዳማ ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት በሁላ ወረዳ ቤተክህነት ሥር ወይም በሁላና ቦና ዙሪያ ወረዳ ፫ አብያተ ክርስቲያናት በጥፋት ኃይሎች መቃጠላቸውና ፪ ደግሞ መዘረፋቸው  ተገለጸ፡፡ከሐምሌ ፲፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በቆየው የሲዳማ ዞን ክልል ይሁንልን ጥያቄ ረብሻ ለአብያተ ቤተ ክርስቲያናት መቃጠልና መዘረፍ መንስኤ መሆኑም ተገልጿል፡፡

መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ፤ የሲዳማ፤ጌዴኦ፤አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ «ሀገረ ስብከቱ ከወረዳ ቤተክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ጥበቃቸውን እንዲያጠናክሩና ምእመናንም ተደራጅተው ራሳቸውንና አብያተ ክርስቲያናትን እየጠበቁና እንዲከላከሉ መልእክት የተላለፈ ቢሆንም የጥፋት ኃይሎቹ ከአካባቢው የፀጥታ ኃይልና ከምእመናን አቅም በላይ በመሆናቸው የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ ችለዋል» በማለት አስረድተዋል፡፡የደረሰው ቃጠሎ በመጀመሪያ በዶያ ቅዱስ ሚካኤል የ፲፰ አባወራዎችን ንብረት በማጥፋት፤ ፸፪ ንዋያተ ቅዱሳትን ሙሉ በሙሉ በእሳት አውድሟል፡፡ ቤተክርስቲያኗን ለማትረፍ ሲረባረቡ የነበሩትን ፲ ሰዎችም አደጋ እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡

ዶያ ቅዱስ ሚካኤል

በሌላ በኩል በ፳፻፰ ዓ.ም. ተመሥርቶ ከኅዳር ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጋታማ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ጥፋት ኃይሎች በእሳት ሙሉ ለሙሉ ተቃጥሏል፡፡ ፵፫ አባወራዎች ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲቃጠል፤  በአይነት ፵፯ የሚሆኑ ንዋያተ ቅድሳት ሙሉ በሙሉ በእሳት ተቃጥለዋል፡፡

፵፫ የሚሆኑ አባወራዎች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በየሰው ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የገታማ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን

የሉዳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የውስጥ ንዋያተ ቅድሳት በእሳት ተቃጥለዋል፡፡ የቤተ  ክርስቲያኑ በር፤መስኮት እና መንበር ሲሰባበር፤ደጀ ሰላሙ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጽሙ በነበሩ ምእመናን ላይም የሀብት ዝርፊያ በቤታቸው ተካሔዷል፡፡ አቶ ሽፈራው ማሞ በተባሉት አባት ከፍተኛ የአካል ጉዳትም እንደደረሰ ምንጮች አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡

ሉዳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

የጭሮኔ ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ሕጉ እስከ አሁን ያለበት ቦታ አልታወቀም፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንና ንዋያተ ቅዱሳቱን ያቃጠሉት ግለሰቦች የካህናትን ልብሰ ተክህኖና የሰንበት ተማሪዎች አልባሳትን ለብሰው፤ ቆብ አጥልቀውና መስቀል ይዘው በመዞር ከጨፈሩ በኋላ ተመልሰው ቤተ  ክርስቲያኗን ማቃጠላቸውን የዐይን እማኞች አብራርተዋል፡፡

ንዋያተ ቅዱሳቱን

በተጨማሪም በ፲፱፻፱ የተመሠረተው የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ደግሞ በደረሰው ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ተዘርፏል፡፡ አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ መቃብር ቤቶች በርና መስኮቶች ተሰባብሯል፡፡

የቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ  ክርስቲያን

ሦስት ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔት ተገድለዋል፡፡ ፪፻፶ ምእመናን ተሰደው ቦሬ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው ይገኛሉ፡፡በተፈጠረው ችግር የ፹፭ ዓመቱ አቶ ግርማ መልካ መንገድ ላይ ተገድለው ሲገኙ፤አቶ የኔነህ ተስፋዬ መገደላቸውን፤ እና ወጣት አድሱ የኔነህ ደግሞ አባቱን እያሳከመ እንዳለ መገደሉን ተገልጿል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ ሀገረ ስብከቱ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር በአካባቢው ላይ የነበሩትን ምእመናን ለመታደግ ችሏል፡፡ የተጎዱ ምእመናንን ለመደገፍና የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ ለማቋቋም ኮሚቴ መቋቋሙን የሐዋሳ ማእከል ገልጿል፡፡

በመሆኑም የኮሚቴው አባላት በጥፋቱ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት መረጃ በመሰብሰብ፣ ምእመናንን በማጽናናትና ከሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ድጋፍ በማሰባሰብ ተጎጂዎችን እየረዱ እንደሆነ ሀገረ ስብከቱ ገልጿል፤ ይበልጥ ለመደገፍ በባንክ አካውንት ቁጥር 1000290647936፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ከፍቶ ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ ይገኛል፡፡

በአፋን ኦሮሞ የተዘጋጁ ሦስት የኮርስ መጻሕፍት ታትመው በሥርጭት ላይ የሚገኙት

 

– Barattootni Yaa’iiwwan Mooraa Afaan Oromoon barattan Baga Gammaddan! Kitaaboleen koorsii sadii Afaan Oromootiin, adeemsa barnoota isa haaraatiin qophaa’anii isiniif dhiyaataniiru! Kanneen kaanis dhiyootti isin harka gahu!

 

በአፋን ኦሮሞ የምትማሩ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች፡- እንኳን ደስ አላችሁ!

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት በአፋን ኦሮሞ የተዘጋጁ ሦስት የኮርስ መጻሕፍት ታትመው ቀርበውላችኋል! ሌሎቹም መጻሕፍት በቅርቡ ታተመው በእጃችሁ ይገባሉ!!!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ኅዳር ፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት አቋቁማ መደበኛ የሃያ አራት ሰዓት የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ከጀመረች ከሁለት ዓመታት በላይ ተቈጥረዋል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን፣ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን አጀማመርና ጠቅላላ አገልግሎት በአጭሩ የሚያስቃኝ ጽሑፍ ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ ይኹንላችሁ!

በቤተ ክርስቲያናችንና በአገራችን ታሪክ እንደሚታወቀው ያልተበረዘና ያልተከለሰ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማና ሥርዓተ አምልኮ፣ የትርጓሜና የባሕረ ሐሳብ ትምህርት፣ በብራና የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ መሥዋዕተ ኦሪት ይቀርብባቸው የነበሩና እስከ አሁን ድረስ ተጠብቀው የቆዩ ጥንታውያን አድባራትና ገዳማት፣ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቶች፣ ሥርዓተ ማኅሌትና የመንፈሳውያን በዓላት አከባበር ሥርዓት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በሙሉ ዓለምን የሚያስደምሙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሀብቶችና ልዩ ስጦታዎች ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በመጽሐፋቸው እንደ ጠቀሱት ሙሉ ትምህርት፣ ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሉ፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ኪነ ጥበብ፣ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ፣ እምነት፣ ነጻነት፣ አንድነት፣ የአገር ፍቅር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ካበረከተቻቸው ብዙ ስጦታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው ማብራሪያ አሁንም ቢኾን ትውልዱ ጀግንነትን፤ አገር ወዳድነትን፤ ለሃይማኖት፣ ለታሪክና ለባህል ተቆርቋሪነትን ይዞ እንዲያድግ በማስተማርና በማበረታታት ረገድ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ አላት (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ)፡፡

በረከታቸው ይደርብንና ካሁን በፊት በየጊዜው የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቃል በማስተማርና መጻሕፍትን በማሳተም እነዚህን ሀብቶቿን ለመጠበቅና ለዓለም ለማስተዋወቅ ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡ ከኅትመት ውጤቶች ባሻገርም መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ቃለ እግዚአብሔር ለማስተማር ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ብዙ ደክመዋል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት ባይሰጥም ቀደም ሲል የተጀመረው የሬድዮ መርሐ ግብር እንደዚሁም አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት መንፈሳዊ መጽሔቶች፣ ጋዜጦችና ድረ ገጾች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙኃንን በተለይም የቴሌቭዥን ሥርጭትን በመጠቀም ረገድ እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያሉ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚነገረው በሁለት ቋንቋዎች ብቻ የሚግባቡና በቍጥር ከዐሥር ሚሊዮን የማይበልጡ ምእመናን የሚገኙባት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከዐሥር በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን በመክፈት ትምህርተ ወንጌልን በመላው ዓለም በማዳረስ ላይ ትገኛለች፡፡ በምእመናን ብዛት ከኢትዮጵያ ብዙ እጥፍ የምታንሰዋ ግብጽ በዚህ መልኩ የመገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ ከኾነች ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎችን የሚናገሩና ወደ አምሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን ባለቤት ለኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ብቻ ሳይኾን በርካታ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጓት አያጠያይቅም፡፡ ይህን እውነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቅዱስ ሲኖዶስ ባሳለፈው ውሳኔ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዓመታት በፊት የሃያ አራት ሰዓት የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ማሠራጨት ጀምራለች፡፡

በ፳፻፱ ዓ.ም በታተመው ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት እንደ ተገለጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት እንዲቋቋም ለማድረግ ጥናት እንዲካሔድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሰነው በጥቅምት ወር ፳፻፮ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ነው፡፡ በዚያው ዓመት በግንቦት ወር በተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፤ ሦስት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በርካታ ባለሙያዎችና ሊቃውንት የተሳተፉበት ጥናት ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ፣ የአርትዖትና የቴክኒክ መመሪያ ጸድቆ ሥራው እንዲጀመር ተወስኗል፡፡

ድርጅቱ፣ በቋሚ ሲኖዶስ በተሰየመው የቦርድ ሥራ አመራር ከአንድ ዓመት በላይ ተጨማሪ ጥናቶችን ሲያደርግ ቆይቶ በጥቅምት ወር ፳፻፰ ዓ.ም ለሥራው የሚያስፈልገው በጀት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወስኖለታል፡፡ ቦርዱ የተፈቀደውን በጀትና የተጠናውን ጥናት ወደ ተግባር ለመለወጥ ውድድር በማድረግ ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እንዲቀጠር አድርጓል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ግቢ ውስጥ ይገኛል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አባታዊ መመሪያ ሰጭነት አስፈላጊ ቅድመ ኹኔታዎችን በሟሟላት፣ ተደጋጋሚ ውይይቶችንና ዓለም አቀፍ ዳሰሳዎችን በማድረግ ለሥርጭቱ ያመነበትን የሳተላይት ጣቢያ አወዳድሮ በመምረጥና የውል ስምምነት በማዘጋጀት በአፋጣኝ የሥርጭት አገልግሎቱን ጀምሯል፡፡ በኢየሩሳሌም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረትም የቴሌቭዥን መርሐ ግብራቱ በአገር ውስጥ ተዘጋጅተው ኢየሩሳሌም በሚገኘው የሳተላይት ድርጅት አማካይነት ይሠራጫሉ፡፡ የቴሌቭዥን ጣቢያው የሥርጭት አድራሻም የሚከተለው ነው፤

Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Television (EOTC TV)

Satellite: Eutelsat/Nilesat (ኢትዮጵያ)

Frequency …. 11353 (5) Vertical

Symbol rate …. 27500/FEC…5/6

Satellite: Galaxy 19 (G-19) (ሰሜን አሜሪካ)

Frequency …. 11960/Vertical

Symbol rate …. 22000/FEC…3/4

የድርጅቱ መዋቅርና አገልግሎት የተሟላ እንዲኾን በአስተዳደርና ፋይናንስ፣ በመርሐ ግብር ዝግጅት እና በቴክኒክ ዘርፍ ቦርዱ በሰየማቸው የቅጥርና የምዘና ኮሚቴ አባላት አስፈጻሚነት የሠራተኞች የቅጥር ሒደት ተከናውኗል፡፡ በቅጥር ሒደቱም ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በወጣው ማስታወቂያ መሠረት ላመለከቱ ሠራተኞችና ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቅድሚያ ተሰጥቷል፡፡ የሥርጭቱን አጠቃላይ ይዘትና ዓይነት በተመለከተም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቦርድ አባላትና የሚዲያ ባለሙያዎች የሚገኙበት የይዘትና የዓይነት ዝግጅት ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ ይዘቱንና ዓይነቱን የሚያርምና የሚገመግም የኤዲቶሪያል ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡ የኤዲቶሪያል ኮሚቴው አባላትም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪጁ የተሰየሙና በቦርዱ የተመረጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ድርጅቱ ካለበት ሠፊ ሥራና ከባድ ሓላፊነት አኳያ በቋሚነት የሚያስፈልጉት በርከት ያሉ ስቱዲዮዎች፣ የቅድመ ሥርጭትና ድኅረ ሥርጭት ተግባራት ማከናወኛነት የሚያገለግሉ በርካታ ክፍሎች፣ አብያተ መዛግብት፣ አስተዳደርና የባለሙዎች ቢሮዎች እንዲሟሉ ለማድረግ ድርጅቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች መመሪያን በመቀበል በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

(ምንጭ፡- ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ ፱ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፲፪፤ ጥቅምት ፳፻፱ ዓ.ም፣ ገጽ 77-78)፡፡

ጽሑፋችንን ለማጠቃለል ያኽል፣ የሥልጣኔ ውጤቶች በተበራከቱበትና አብዛኞቹ ወጣቶች ዓለማዊ መልእክት በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ውስጥ በወደቁበት በአሁኑ ዘመን ወጣቱን ትውልድ ወደ ጥፋት ከሚወስዱ መልእክቶች ለመታደግ ያመች ዘንድ ትምህርተ ወንጌልን ለማዳረስና ኦርቶዶክሳዊ ሕይወትን ለማስተማር፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓተ እምነት፣ ትውፊትና ልዩ ልዩ ሀብቷን ወይም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን ለትውልድ ለማቆየት ብሎም ለዓለም ለማስተዋወቅ፤ እንደዚሁም በየጊዜው በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ መመሪያዎችንና መልእክቶችን በአፋጣኝ ወደ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለማስተላለፍ መገናኛ ብዙኃንን፣ ከመገናኛ ብዙኃንም የቴሌቭዥን ሥርጭትን መጠቀም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

በዚህ ዓላማ መሠረት የተጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቭዥን ሥርጭትም በልዩ ልዩ ዓምዶቹ ትምህርተ ወንጌል በመስጠት፤ ቅዱሳት መካናትን፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶችን በማስተዋወቅ፤ ጠቃሚ የኾኑ ማኅበራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን በማቅረብና መንፈሳዊ ዜናዎችን በመዘገብ አገልግሎቱን እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስቀጠልና ለምእመናን ለማዳረስ ይቻል ዘንድም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ሐሳብ አስተያየት በመስጠትና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ በተቻለን አቅም ዂሉ የቤተ ክርስቲያናችንን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት በመደገፍ የሚጠበቅብንን ክርስቲያናዊ ሓላፊነት እንወጣ ሲል የማኅበረ ቅዱሳን አማርኛ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል መንፈሳዊ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የፀረ ተሐድሶ አገልግሎት በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹እንግዲህ ሒዱና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ዅሉ አስተምሩ፤›› (ማቴ. ፳፰፥፲፱) በማለት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባዘዘው ቃል መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ተልእኮዋ ስብከተ ወንጌልን ለዓለም ማዳረስና ያላመኑትን በማሳመን፤ ያመኑትን እንዲጸኑ በማድረግ ዅሉንም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ማቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን አካላቸው ከውስጥ፣ ልቡናቸው ከውጭ የኾነ፤ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሚጠሩ፤ በኅቡዕም፣ በገሃድም አስተምህሮዋን የሚፃረሩና ምእመናኗን የሚያደናግሩ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ለሐዋርያዊ ተልእኮዋ እንቅፋት ኾነውባታል፡፡ ይህን የመናፍቃንን ሤራ ለመከላከልም ልዩና ወጥ አሠራር መዘርጋት ተገቢ መኾኑ ስለ ታመነበት ቅዱስ ሲኖዶስ በወርኃ ግንቦት ፳፻፰ ዓ.ም ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በዛሬው ዝግጅታችን የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ከተግባር ላይ አውለው ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን በትጋት እያከናወኑ ከሚገኙ አህጉረ ስብከት መካከል የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ አገልግሎትን በአጭሩ ልናስታውሳችሁ ወደድን፡፡ መልካም ንባብ!

መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት፣ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ

በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሚመራው የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዐሥራ አምስት ወረዳ አብያተ ክህነት እና ከአራት መቶ በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉት ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት እንደ ገለጹልን፣ ሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያትን በየቦታው በማዋቀር፣ ሰባክያነ ወንጌልንና ካህናትን በመመደብ የስብከተ ወንጌል ተልእኮውን በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንቅፋት የኾነውን የተሐድሶ ነን ባዮች መናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመቈጣጠርም የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተቀብሎ የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ኮሚቴን አቋቁሞ አገልግሎቱን ቀጥሏል፡፡ ከሥራ አስኪያጁ ማብራርያ እንደ ተረዳነው ኮሚቴው የተቋቋመው ከሀገረ ስብከት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ነው፡፡ ዓላማው ምእመናን ከኑፋቄ ትምህርት ተጠብቀው በኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ጸንተው እንዲኖሩ ማድረግ ሲኾን፣ አባላቱም ከሀገረ ስብከቱ ሠራኞች ጀምሮ ከካህናት፣ ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ ከማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ከምእመናን የተመረጡ ናቸው፡፡

‹‹የመናፍቃንን ሤራ ለማፍረስና ምእመናንን ከቅሰጣ ለመከላከል የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው ድርሻ የጎላ ነው›› ይላሉ ሥራ አስኪያጁ የኮሚቴውን አስፈላጊነት ሲገልጹ፡፡ ሀገረ ስብከቱ በአፋጣኝ ኮሚቴ አቋቁሞ አገልግሎት መጀመሩ እንደሚያስመሰግነው የሚያብራሩት መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ፣ በዚህ ተግባሩም ለሌሎች አህጉረ ስብከት እንደ አብነት ከመጠቀሱ አልፎ የልምድ ተሞክሮ በማካፈል ላይ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ቤተ ክርስቲያን በሰጠችው አደራ መሠረት አባላቱን በማስተባበር፣ መመሪያ በማዘጋጀት፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ መረጃዎችን በማቅረብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ከሀገረ ስብከቱ ጎን ኾኖ የኮሚቴውን አገልግሎት እየደገፈ እንደሚገኝና የማእከሉ ድጋፍም ለሀገረ ስብከቱም ኾነ ለኮሚቴው ብዙ ሥራ እንዳቀለለት አስረድተዋል፡፡

ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ፣ በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የናዝሬት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል አስተዳዳሪ እና የሀገረ ስብከቱ ፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ኮሚቴ ሰብሳቢ

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የናዝሬት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ ደግሞ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው ሰብሳቢ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳብራሩት ኮሚቴው አገልግሎቱን የጀመረው በወርኃ ታኅሣሥ ፳፻፱ ዓ.ም ሲኾን፣ ወደ አገልግሎት ከመግባቱ አስቀድሞ መተዳደርያ ሕጉንና የሥነ ምግባር ደንቡን፣ እንደዚሁም የሥልጠና ሰነዱን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከማጸደቁ ባሻገር ለአባላቱ የሥራ ድርሻቸውን አሳውቋል፡፡ የኮሚቴውን ዓላማ ለምእመናን ማስተዋወቅ፤ በየዐውደ ምሕረቱ የሚሰጠው ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግና ሥልጠና መስጠት ከኮሚቴው ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ሲኾን፣ የመናፍቃንን እንቅስቃሴ፣ ጫናዎቹንና መከላከያ መንገዶቹን በማመላከት ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ ማሳወቅም በሥልጠናው የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ኮሚቴው፣ ካሁን ቀደም ለሀገረ ስብከቱና ለየወረዳ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣ ለካህናት፣ ለሰንበት ት/ቤት አባላትና ለማኅበረ ምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናውም በናዝሬት ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ለሙሉ የተሰጠ ሲኾን፣ በየገጠሩ ለሚኖሩ ምእመናንም በቅርብ ጊዜ እንዲዳረስ ይደረጋል፡፡

ከሰብሳቢው ገለጻ እንደ ተረዳነው ስለ መናፍቃን እንቅስቃሴ መረጃ በማሰባሰብና ለምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በመስጠት አገልግሎቱን የጀመረው ኮሚቴው፣ ወደፊትም ይህን መንፈሳዊ ተልእኮዉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ተግባሩን በሥርዓት ለማከናወን እንዲያመቸውም በሳምንት አንድ ቀን ጉባኤ ያካሒዳል፡፡ የኮሚቴው አባላት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው መሥራታቸው፤ ምሥጢር ጠባቂነታቸው፤ ከራስ ሐሳብና ጥቅም ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የሚያስቀድሙና ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ልምድ ያዳበሩ መኾናቸው ለአገልግሎቱ መፋጠን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው ይላሉ ሊቀ ጉባኤ የአባላቱን ጥንካሬ በማድነቅ፡፡

ማኅበረ ምእመናን ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ በሚገባ እንዲያውቁ የሚያበቃ ትምህርትና ሥልጠና መስጠት፤ በየዐውደ ምሕረቱ የሚቀርበው ትምህርተ ወንጌል በስፋት እንዲቀጥል መደገፍ፤ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ እንዲዳከምና ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ እንዲስፋፋ ማድረግ፤ ሐሰተኞች መምህራንን በመከታተል ከስሕተታቸው እንዲታረሙ መምከር፤ ካልተመለሱም ተወግዘው እንዲለዩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ ኮሚቴው ወደፊት ለማከናወን ያቀዳቸው ተግባራት መኾናቸውንም ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ራሳቸውን ‹ተሐድሶ› ብለው የሚጠሩ መናፍቃን ማን ይነካናል ብለው በድፍረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እየተሳደቡ፣ አባቶችንም እያጥላሉ እንደ ኾነ፤ የተሳሳተ ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ፤ ቍጥራቸውም በዘመናት ሳይኾን በቀናት እየጨመረ እንደ መጣ ጠቅሰው፣ በሀገረ ስብከቱ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ የተቋቋመው እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ይህን የመናፍቃኑን እንቅስቃሴ ለመከላከል መኾኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ ኃይለ ኢየሱስ ከበረ፣ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው ጸሐፊ

የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ኃይለ ኢየሱስ ከበረ በበኩላቸው ኮሚቴው ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ባለው መዋቅር ልዩ ልዩ ክፍሎችን የሚመሩ ሰባት አባላት እንዳሉት፤ ከክፍሎቹ መካከልም የትምህርትና ግብረ መልስ፣ መረጃና ትንተና፣ ቁጥጥርና ክትትል፣ እንደዚሁም የመርሐ ግብር ክፍል ተጠቃሾች መኾናቸውን አስታውሰው፣ የመናፍቃንን እንቅስቀሴ በሚመለከት ለወጣቶች ልዩ ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡ ጸሐፊው እንዳስረዱት፣ ኮሚቴው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ መቋቋሙ የልምድ ማነስ፣ የመረጃ ችግር፣ የድጋፍ ሰጪ አካላት እጥረት እና የመናፍቃን እንቅስቃሴ በፍጥነት መስፋፋት ከመሰናክሎች መካከል የሚጠቀሱ ሲኾን፣ በአዎንታዊ መልኩ ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ የሚደርስ ሰፊ መዋቅር ያለው መኾኑ፤ አገልግሎቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስፋት መዳረሱ፤ ወጥነት ባለው አሠራር መዋቀሩ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴውን አገልግሎት በአርአያነት እንዲጠቀስ ያደርገዋል፡፡

በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ እና ጸሐፊው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፤

‹‹በቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና ቢበዛባትም የተመሠረተችው በክርስቶስ ደም ነውና አትሸነፍም›› የሚሉት መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት፣ የኮሚቴው ዓላማ ከግብ ደርሶ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማፋጠን ይቻል ዘንድ አባቶች ምእመናንን ተግተው ቃለ እግዚአብሔርን እንዲያስተምሩ፤ ምእመናኑም ትክክለኛ እረኞቻቸውን በመለየት ቃሉን እንዲማሩ፤ በአጠቃላይ መላው ሕዝበ ክርስቲያን በፈተናዎች ሳይደናገጡ በጸሎት እንዲበረቱና ራሳቸውንም ሌሎችንም ከኑፋቄ ትምህርት በመጠበቅ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ በበኩላቸው፤‹‹ከአሁን በፊት የተሐድሶ መናፍቃን ጉዳይ የማኅበረ ቅዱሳን የፈጠራ ወሬ ነው ይባል ነበር፡፡ አሁን ግን ጉዳዩ ቤተ ክርስቲያንን የሚፈታተን መኾኑ ተደርሶበታል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም የመናፍቃኑን እንቅስቃሴ በመከላከል ረገድ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ኾኖ የሚጠበቅበትን የልጅነት ድርሻ በመወጣት ላይ ነው፡፡ ወደፊትም በዚህ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ሊቀጥል ይገባል›› ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ በተጨማሪም የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴው ዓላማ ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ በማስጠበቅ እነርሱን ለመንግሥተ ሰማያት ማዘጋጀት እንደ ኾነ ተገንዝበው፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናን በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በዕውቀት፣ ወዘተ. በመሳሰሉ መንገዶች አገልግሎቱን በመደገፍ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ሊቀርፉና የስብከተ ወንጌል ተልእኮውን ሊያስፋፉ እንደሚገባ በኮሚቴው ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ የሀገረ ስብከቱ፣ የየወረዳ አብያተ ክህነቱና የየሰበካ ጉባኤያቱ ሠራተኞች፤ የየሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች፣ የማኅበረ ቅዱሳንና የሌሎችም መንሳውያን ማኅበራት ድጋፍ ኮሚቴው አገልግሎቱን በአግባቡ እንዲወጣ አድርጎታል የሚሉት አቶ ኃይለ ኢየሱስ ከበረ ደግሞ፣ ለወደፊትም ከዚህ በበለጠ ውጤታማ ይኾን ዘንድ የአባቶች፣ የወንድሞችና እኅቶች ተሳትፎ እንዳይለየን ሲሉ ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴውን ዓላማ በፍጥነት ከግብ ለማድረስ ይቻል ዘንድም ዅሉም ምእመናን በተለይ የሰንበት ት/ቤትና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የመናፍቃንን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ለኮሚቴው እንዲያቀርቡ፤ ማኅበረ ቅዱሳንን የመሰሉ ድጋፍ ሰጪ አካላትም በቁሳቁስ፣ በገንዘብ፣ በሐሳብ፣ በመረጃ አቅርቦትና ሥልጠና በመስጠት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ ጸሐፊው መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ዝግጅት ክፍላችንም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አስተምህሮ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለትውልዱ ይዳረስ ዘንድ የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ በማሳለፉ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን አክብሮት እየገለጸ፣ እንደ ምሥራቅ ሸዋ ዅሉ ሌሎች አህጉረ ስብከትም ሐዋርያዊ ተልእኮውን እንዲያስፋፉና የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ አቋቋመው የመናፍቃንን ሤራ እንዲከላከሉ በመደገፍ ዅላችንም የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነታችንን እንወጣ ሲል ያሳስባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የወደቁትን እናንሣ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹እናንተ የአባቴ ቡሩካን፣ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ፡፡ ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳም ኾኜ ተቀብላችሁልና፡፡ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜም ጐብኝታችሁኛልና፤ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና፤›› (ማቴ. ፳፭፥፴፬-፴፯) ተብሎ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው፣ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ከምንበቃባቸው ትእዛዛት መካከል አንደኛው ሰዎችን መርዳት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን መርዳት የሚያስገኘውን ሰማያዊ ዋጋ ሲገልጽም ‹‹በእኔ ካመኑ ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁትን ዅሉ ለእኔ አደረጋችሁት፤›› በማለት ቃል ኪዳን ሰጥቷል (ማቴ. ፳፭፥፵)፡፡

ይህን ቃል ባለማስተዋልና በሥጋዊ ስንፍና በመያዝ ለራሳችን ድሎት ብቻ የምንሽቀዳደም ራስ ወዳዶች ብዙዎች ብንኾንም፣ በአንጻሩ ቃሉን ተስፋ በማድረግ በገዛ ፈቃዳቸው ተነሣሥተው፣ በማኅበር ተሰባስበው ሰዎችን በመርዳት ክርስቲያናዊ ተግባር የሚፈጽሙ በጎ አድራጊ ምእመናን በየአገሩ አሉ፡፡ ጧሪ ቀባሪ ያጡ ሕሙማንንና አረጋውያንን የማሳከም፣ የመከባከብና ራሳቸውን እንዲችሉ የማገዝ ዓላማና ርእይ ሰንቀው በአዲስ አበባ ከተማ ከተቋቋሙ የበጎ አድራጎት ማኅበራት መካከል የወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር አንዱ ነው፡፡ የማኅበሩ ተቋማዊ ጠባይዕና አሠራር ምን ዓይነት ነው? የገቢ ምንጩ ምንድን ነው? ሒሳብ አያያዙስ እንዴት ነው? ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች የሚያሰባስበው በምን ዓይነት መሥፈርት ነው? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን አንሥተንላቸው፣ የማኅበሩ መሥራች አቶ ስንታየሁ አበጀ ማብራርያ ሰጥተውናል፡፡ የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በዛሬው ዝግጅታችን፣ መሥራቹ የሰጡንን ቃለ ምልልስ እና ማኅበሩ ባሳተመው ብሮሸር ላይ የተጠቀሱ ተግባራቱን መነሻ በማድረግ የማኅበሩን አገልግሎት እናስቃኛችኋለን፡፡ መልካም ንባብ!

አቶ ስንታየሁ አበጀ፣ የማኅበሩ መሥራች

የወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር ከዐሥራ ዘጠኝ ዓመታት በፊት በአቶ ስንታየሁ አበጀ አስተባባሪነት ተመሠረተ፡፡ እኒህ ምእመን በደረሰባቸው ሥጋዊ ችግር ምክንያት ጠያቂ አጥተው በየጎዳናውና በየመቃብር ቤቱ ሲንገላቱ ኖረው ከዓመታት በኋላ ቆመው መሔድ ስለ ተቻላቸው ‹‹እግዚአብሔር በልዩ ጥበቡ እኔን ከወደቅሁበት ያነሣኝ ለትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ እንደኔ የሚጠይቃቸው ያጡ ሰዎችን ከየወደቁበት ማንሣት አለብኝ›› የሚል መልካም ርእይ ሰንቀው፣ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር ኾነው መስከረም ፩ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም ‹‹የወደቁትን አንሡ›› በሚል ስያሜ የነዳያን መርጃ ማኅበር አቋቋሙ፡፡ ማኅበሩ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነዳያንን የመደገፍ፣ አረጋውያንን የመንከባከብና ጧሪ ቀባሪ ያጡ ወገኖችን የመርዳት ተልእኮውን ቀጥሏል፡፡

መሥራቹ እንደ ገለጹልን ማኅበሩ ለዓላማው ማስፈጸሚያ የሚውለውን የገቢ ምንጭ የሚያገኘው ከአባላቱ ወርኃዊ መዋጮ፣ እንደዚሁም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከሚኖሩ በጎ አድራጊዎች ነው፡፡ በሒሳብ አያያዝም ዘመናዊና ሕጋዊ አሠራርን በመከተል ገቢውንና ወጪውን በደረሰኝ ይቈጣጠራል፤ ኦዲትም ያስደርጋል፡፡ የሚተዳደረውም በቦርድ አወቃቀር ሲኾን፣ ሕጋዊ ፈቃድና እውቅና አግኝቶ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ተመዝግቧል፡፡ የራሱ መተዳደርያ ደንብና ስልታዊ ዕቅድም አዘጋጅቷል፡፡ ወደፊት ለሚያከናውናቸው ተግባራትም ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ማኅበሩ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ሳይለይ ልዩ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከሠላሳ በላይ በሚኾኑ ሠራተኞቹ አማካይነት ድጋና ክብካቤ ያደርጋል፡፡ በዚህ ተግባሩ ባበረከተው አገራዊ አስተዋጽዖም በየጊዜው ከመንግሥትና ከሌሎች ልዩ ልዩ ተቋማት የምስጋና ገጸ በረከትና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

የማኅበሩ ማእከል ውጫዊና ውስጣዊ ገጽታ በከፊል

ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ፳፻፰ ዓ.ም ድረስ ለስድስት መቶ ሃያ ሦስት ሰዎች የምግብ፣ የመጠለያና የሕክምና ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሁለት መቶ አንዱ በማኅበሩ በተደረገላቸው ርዳታ ከሕመማቸው ተፈውሰዋል፡፡ አራቱ በማኅበሩ ውስጥ ተቀጥረው በማገልገል ላይ ሲኾኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በልዩ ልዩ የሥራ መስክ ተሰማርተው ራሳቸውን እያስተዳደሩ ነው፡፡ ሦስት መቶ ዐሥራ ሁለቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ማኅበሩ ካሁን በፊት ቤት ተከራይቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲኾን፣ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ ለጋስዮን አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከመንግሥት በተሰጠው ቦታ ባስገነባው የአረጋውያን መጦርያና መንከባከቢያ በርካታ ሕሙማንንና አረጋውያንን አሰባስቦ የምግብ፣ የልብስ፣ የመጠለያና የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የሚለዩትንም በክብር እንዲሸኙ ያደርጋል፡፡ በዚህ ዓመትም አገልግሎቱን በይበልጥ አጠናክሮ በከፍተኛ ባለሙያዎች በመታገዝ ከሦስት መቶ በላይ አረጋውያንን በማእከሉ በማሰባሰብ፤ ለሦስት መቶ አረጋውያን የተመላላሽና የቤት ለቤት ድጋፍ በማድረግ፤ እንደዚሁም ለአረጋውያኑና ለተንከባካቢዎቻቸው ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የበጎ አድራጎት ተልእኮውን ሲወጣ ቆይቷል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡

ጕብኝት ባደረግንበት ወቅት እንዳስተዋልነው በማኅበሩ እየተጦሩ ከሚገኙ ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ የአብነት መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ሓላፊነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያንና የአገር ባለውለታዎች በሕመም፣ በጤና እና በእርጅና ምክንያት የአልጋ ቁራኛ፣ የደዌ ዳኛ ኾነው ጎዳና ላይ በወደቁበት ወቅት ይህ ማኅበር ደርሶላቸው አስፈላጊውን ዅሉ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ በተለይ የአእምሮ ሕሙማንና ከአንድ በላይ በኾነ የጤና እክል የተጠቁ ማለትም የማየትም የመስማትም የመንቀሳቀስም ችግር ያለባቸውና ሰውነታቸውን መቈጣጠር የማይችሉ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች ኹኔታ ልብን ይነካል፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚንቀሳቀሱትም፣ የሚመገቡትም፣ የሚለብሱትም፣ የሚጸዳዱትም በሰው ርዳታ ነው፡፡ እነርሱን ያየ ሰው የማኅበሩን ዓላማ በግልጽ ይረዳዋል የሚል እምነት አለን፡፡ የማኅበሩ መሥራች እንደ ነገሩን የሠራተኞችን ደመወዝ ሳይጨምር ለሕሙማኑ የዳይፐር መግዣ ብቻ በየቀኑ ከአንድ ሺሕ አራት መቶ ስልሳ አምስት ብር በላይ ወጪ ይደረጋል፡፡ ይህም ማኅበሩ ሰውን ለመርዳት ሲል የሚከፍለውን መሥዋዕትነትና የሚያሳልፈውን ውጣ ውረድ የሚያመለክት ነው፡፡

በማእከሉ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሕሙማንና አረጋውያን ጥቂቶቹ

በአጠቃላይ ‹‹መልካም ሥራ የክፉ ቀን ስንቅ ነው›› በሚለው መሪ ቃሉ የሚታወቀው የወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር በጤና፣ በእርጅና ወይም በሌላ ልዩ ልዩ ምክንያት በየመንገዱ ወድቀው የሚለምኑ ወገኖችን በማሰባሰብ፤ እንደዚሁም በያሉበት ቦታ ባለሙያዎችን በመላክ የሕክምና፣ የምግብ እና የልብስ ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ለወደፊትም ይህን ተግባሩን በስፋት አጠናክሮ ለመቀጠል ዕቅድ አውጥቶ በመተግበር ላይ ነው፡፡ የማእከሉ ክሊኒክ በአካባቢው ለሚገኙ ድጋፍ ፈላጊ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ፤ ተጨማሪ የመጠለያና የሆስፒታል ተቋማትን መገንባት፤ የጎዳና ላይ ምጽዋትን ተቋማዊ በማድረግ ነዳያን ወጥ በኾነ መንገድ ርዳታ እንዲያገኙ ማመቻቸት፤ ከርዳታ ድርጅቶችና በጎ አድራጎት ማኅበራት ጋር በጥምረት በመሥራት የአረጋውያንን ችግር በጋራ መፍታት ከማኅበሩ ዕቅዶች መካከል የሚጠቀሱ ተግባራት ናቸው፡፡

‹‹ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር ውስጥ ይፈጸማሉ፤›› የሚሉት የማኅበሩ መሥራች አቶ ስንታየሁ አበጀ የየተቋማት ሠራተኞች፣ የድርጅት ባለቤቶች በጥቅሉ በጎ አድራጊ ወገኖች መጥተው ሕሙማኑን በመጠየቅና ቦታውን በመጐብኘት፣ የሚቻላቸው ደግሞ በምግብ፣ በቁሳቁስ (ልብስ፣ ፍራሽ፣ አልጋ፣ ወዘተ.) አቅርቦት እንደዚሁም የገንዘብ፣ የጉልበትና የሐሳብ ድጋፍ በማድረግ ቢተባበሩ የወደቁ ወገኖችን በማንሣት፣ ነዳያንን በመደገፍ፣ የታመሙትን በማሳከምና አረጋውያንን በመከንከባከብ ማኅበሩ ከዚህ ቀደሙ በበለጠ ሓላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚቻለው አስረድተዋል፡፡ መሥራቹ እንደ ነገሩን ክርስትና፣ ሰርግ፣ ምረቃ፣ ተዝካርና የመሳሰሉ መርሐ ግብሮችን ማኅበሩ በሚያከራያቸው አዳራሾች ማዘጋጀት ደግሞ ሌላው የርዳታ ማድረጊያ መንገድ ነው፡፡ በመጨረሻም ላለፉት ዓመታት በልዩ ልዩ መንገድ ማኅበሩን በመደገፍ፤ እንደዚሁም ለትውልድ እንዲተላለፍ ኾኖ በታነጸው የአረጋውያን መጦርያ ማእከልና ክሊኒክ ግንባታ በመሳተፍ ላበረከተው አስተዋጽዖ አቶ ስንታየሁ ኅብረተሰቡን በእግዚአብሔር ስም አመስግነው፣ ‹‹ወደፊትም ማኅበሩ በሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ዓቅሙ በሚፈቅደው ዅሉ በመሳተፍ ኅብረተሰቡ ታሪካዊ አሻራውን እንዲያኖርና ወገናዊ ግዴታውን እንዲወጣ ይኹን›› ሲሉ በአረጋውያንና በዓቅመ ደካሞች ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አምላካችን በመንግሥቱ ያስበን ዘንድ ዅላችንም ከማኅበሩ ጋር በመኾን የወደቁትን እናንሣ የዝግጅት ክፍላችን መልእክት ነው፡፡ ማኅበሩን መደገፍ፣ በአባልነት መሳተፍ ወይም በመጦርያ ማእከሉ የሚገኙ ሕሙማንንና አረጋውያንን መጠየቅ ለምትፈልጉ የማእከሉ አድራሻ፡- አዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ፈረንሳይ ለጋስዮን ከገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን 600 ሜትር ገባ ብሎ ራስ ካሣ በሚባለው ሰፈር ከአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ ስለ ማኅበሩ አገልግሎት የበለጠ መረጃ ለማግኘትም በሚከተሉት አድራሻዎች መጠየቅ ይቻላል፡፡

የቢሮ ስልክ ቍጥር፡- +251-111-243-401

አቶ ስንታየሁ አበጀ፡- 09 12 01 70 32 /09 35 99 92 92

ወ/ሮ ዓይናለም ኃይሌ፡- 09 11 23 91 59 /09 35 40 17 17

የፓስታ ሳጥን ቍጥር፡- 25404

E-mail፡- yewodekutnansu@gmail.com

aynalemamit@yahoo.com

Web site፡- www.yewedekutnansu.org

ገንዘብ በባንክ ገቢ ማድረግ የምትፈልጉ፣ የወደቁትን አንሡ የነዳያን መርጃ ማኅበር፡-

  1. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሐል ከተማ ቅርንጫፍ፣ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ቍጥር፡- 10000 0454 4513 ወይም 10000 2418 3959
  2. ኅብረት ባንክ ሒሳብ ቍጥር፡- 1141 1161 0272 1018 አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ብላችሁ እንድትልኩ ማኅበሩ ይጠይቃል፡፡ ገንዘቡ ወደ ባንክ ከገባ በኋላም ለሒሳብ ቍጥጥር ያመች ዘንድ በሦስት ኮፒ አሠርታችሁ አንዱን ኮፒ ለማኅበሩ እንድታደርሱ በአክብሮት ያሳስባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡