የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጸሎት ተከፈተ!

በሕይወት ሳልለው

በዓመት ፪ ጊዜ የሚካሔደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. በጸሎት ተከፈተ! በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰባት ያለውን ችግር ለመፍታት ከአሁን ቀደም ጸሎተ ምሕላው በአግባቡ ያልተካሔደ መሆኑን በመግለጫቸው ያሳወቁት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት «በአክሱምና በሌሎች ጥቂት ገዳማትና አድባራት በዕንባና በልቅሶ የታጀበ ጸሎተ ምሕላ ቢደረግም፤ በርእሰ ከተማ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በብዙ ቦታ ጸሎተ ምሕላው ተጠናክሮ እንዳልተካሄደ ለማወቅ ተችሏል» በማለት አስታውቀዋል፡፡

ሁላችንም ከእህልና ውኃ በመለየት መጸለይና ፈጣሪያችንን  መማጸን እንዳለብንም ቅዱስ ፓትርያርኩ አስገንዝበዋል፡፡ «ሁሉን ማድረግ የሚቻለው፤ ምንም ምን የሚሳነው የሌለ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ብቻ ነውና፤ እሱ በመሠረተልን ስልት እጃችንን ወደ እግዚአብሔር እንድንዘረጋ፤ ሕዝቡም ሁሉ፤ ሀገሪቱም በአጠቃላይ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር እንድትዘረጋ፤ እኛም በየሀገረ ስብከታችን ተገኝተን፤ራሳችን መሪዎች ሆነን ጸሎተ ምሕላውን እንድንመራ፤ ትምህርተ ወንጌሉን እንድንሰጥ፤ቂም በቀል እንዲከስም፤ ይቅርታ እንዲያብብ፤ ያለማቋረጥ የሽምግልና ሥራን መሥራት ከሁላችን ይጠበቃል» ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

እንዲሁም አያይዘው በሀገራችን ውስጥ ያለውን ጦርነት በመንቀፍ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ከሕዝቡ ጋር በመወያየት በሰላማዊ መንገድ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት፤ ማንኛውንም አይነት ግጭት በመቃወምና አንድነትን በመፍጠር፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት እንደሚጥር ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በአሻገር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኃይለ ቃል ከመጠቀምና ስም ከማጥፋት እንዲታቀቡ በእግዚአብሔር ስም አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የዚህ ዓመት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  በአቤቱታ ከተመለሱት የቤተ ክርስቲያኗ ታላላቅና ሁለት መለስተኛ ሕንጻዎች ማግስት በመከናወኑ ከሌላው ዓመት እንደሚለይ አስታውቀዋል፡፡

 

የብፁዕ አቡነ ገሪማ ዜና ዕረፍት

 

በሕይወት ሳልለው

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ ሚያዝያ ፳፯፤ ፳፻፲፩ ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ከሰላሣ ላይ ባልቻ ሆስፒታል ውስጥ ያረፉት ብፁዕ አቡነ ገሪማ፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በተደረገ ትብብር ህክምና ቢደረግላቸውም በሕይወት መቆየት አለመቻላቸው ተገልጿል፡፡ ከፍተኛ የዓይን ሕመም ስለነበረባቸው አሜሪካን ድረስ በመሔድ መታከማቸውን የገለጹት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፤ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ አገልግሎታቸውን ማቋረጥ የማይፈልጉ አባት ነበሩ ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

«ታላቅ አባት ነበሩ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቅ ጥላ አጥልቶብናል! እንደነዚህ አይነት አባት መተካት የማይቻልበት ዘመን ላይ ነው የደረስነው፤ አስተዋይ፤ ትዕግሥተኛና ሁሉንም ችለው ሥራቸውን ያከናውኑ ነበር፤» ሲሉም ኀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

የብፁዕነታቸው  የቀብር ሥነ ሥራዓት ቅዱስ ሲኖዶሱ ሚያዝያ ፴፤፳፻፲፩ ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ ፭ ሰዓት ላይ እንደሚፈጸም ወስኗል፡፡

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ዜማ፤ ቅኔና አቋቋምን ጨምሮ የመንፈሳዊ ትምህርት ከመማራቸው ባሻገር ዘመናዊ ትምህርታቸውን በሐረር የራስ መኰንን አዳሪ ትምህርት ቤት እና በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡በታሪክ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪና በነገረ መለኮት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡

በአገልግሎት ዘመናቸውም የተለያዩ ኀላፊነት ያለባቸውን ሥራዎች ለማከናወን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ የቅድስት ሥላሴ እና የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጆች ዲን በመሆን አገልግለዋል፡፡

በተጨማሪም በመንበረ ፓትርያርኩ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ቢሮ ዋና ጸሓፊ፤ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊም ነበሩ፡፡

በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት የተሰረቁት የቅዱስ ገብርኤል፤የቅዱስ ዮሐንስና የገብረ ክርስቶስ ጽላቶች መገኘታቸውን ፖሊስ ገለጸ

በሕይወት ሳልለው

ሰኞ መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.፤ የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከመቃጠሉ በፊት የቅዱስ ገብርኤልና የበዓለወልድ ጽላቶች በመሰረቃቸው በወቅቱ በአካባቢው ሰዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ለወረዳው ፖሊስ አስተዳደር በማመልከታቸውም በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ፤ የቅዱስ ገብርኤል ጽላት ከሂደቡ አቦቴ ወረዳ እንድሪስ ወንዝ ውስጥ ሊገኝ እንደቻለ ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡ ሆኖም ግን የበዓለወልድ ጽላት እስከአሁን እንዳልተገኘ አያይዞ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩም መጋቢት ፲፬ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ከቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የተሰረቁት የቅዱስ ዮሐንስና የገብረ ክርስቶስ ጽላቶች መገኘታቸውንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡በዕለቱ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ኪዳን ለማድረስ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በደረሱበት ወቅት የቤተ መቅደሱ በር ተከፍቶ እንዳገኙትና በመደናገጥ ፍለጋ ቢጀምሩም ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስና የገብረ ክርስቶስ ጽላት፤ እንዲሁም ንዋያተ ቅድሳት በቦታቸው እንዳልነበሩ ሊገነዘቡም ችሏል፡፡ የማኅበሩ አባላትና የሰንበት ተማሪዎቹም በመደናገጥ ሁሉም በየፊናቸው ከሌሊቱ ፲፩ ሰዓት ጀምሮ ለፍለጋ እንደተሰማሩና እስከ ማግሥቱ ቀን ፲ ሰዓት ድረስ ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቅሷል፡፡

ነገር ግን የሰንበት ተማሪ በሆነው ወጣት አብርሃም ታደሰ አማካኝነት በተገኘው ፍንጭ ከተጠረጠሩት ግለሰቦች አንደኛውን በመለየት ወንጀሉን ለፖሊስ አሳውቀዋል፡፡ የቀረበውን ሪፖርት በመመርኮዝ ፖሊስም የተጠረጠሩትን ሦስት ግለሰቦች በመከታተል መኖሪያ ቤታቸውን ከማወቁም በላይ ፍተሻ በማድረግ ከተጠርጣሪዎቹ አንደኛው ቤት ውስጥ የቅዱስ ዮሐንስና የገብረ ክርስቶስ ጽላትን ለማግኘት ችሏል፡፡ የጠፉትንም ንዋያተ ቅድሳት ተራራ ላይ ወስደው ማቃጠላቸውን ወንጀለኞቹ ከሰጡት ሪፖርት አረጋግጧል፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች በዚህ ወቅት ስብሰባ በማካሄድ አፋጠኝ የመፍትሔ እርምጃ እንደሚወስዱ ለማኅበራችን አሳውቀዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረስብከት በኤጀሬ ወረዳ የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ

 

በሕይወት  ሳልለው

በትናትናው ዕለት በሰሜን ሸዋ በሰላሌ ሀገረስብከት በኤጀሬ ወረዳ የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች የቤተ ክርስቲያኑን ጣሪያና መጋረጃ በማቃጠል ግድግዳውን ሙሉ ለሙሉ አፍርሰዋል፡፡ቁጥራቸው ባልተረጋገጠ ግለሰቦች ላይ ከባድ ጉዳት ሲያደርሱ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያንንም እንደዘረፉ ፖሊስ አያይዞ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም እንደተገለጸው፤ በቃጠሎው ሳቢያ በወቅቱ ረብሻ ተነስቶ ነበር፡፡ ሌሎች ሶስት ቤተ ክርስቲያናት ላይም ተመሳሳይ ጥፋት ሊፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦችን የአካባቢው ሰዎች ባደረገለት ትብብር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ችሏል፡፡

እኛም በቀጣይ ዝርዝር መረጃ ሲደርሰን እንገልጻለን፡፡

አእመረ አሸብር “የቅዳሴ ሥርዓት” ሲያካሔድ በቁጥጥር ሥር ዋለ

 

“የቅዳሴ ሥርዓት” እየፈጸምን ነው በማለት ሲያጭበረብሩ

                                                                                                                            በእንዳለ ደምስስ

 በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በኑፋቄው ምክንያት የተወገዘው አእመረ አሸብር ከግብረ አበሮቹ ጋር በግለሰብ ቤት ውስጥ “የቅዳሴ ሥርዓት” ሲያካሔድ የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡

 “መዳን በማንም የለም” በሚል ርእስ በ፳፻፲፩ ዓ.ም ባሳተመው የኑፋቄ መጽሐፉ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዞ የተለየው አእመረ አሸብር በአርባ ምንጭ ከተማ በጫሞ ቀበሌ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከግብረ አበሮቹ ጋር ቅዳሴ እንቀድሳለን በማለት የቤተ ክርስቲያንን ንዋያተ ቅድሳት በመጠቀም ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ክክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር የማይገናኝ ተራ ነገር በማቅረብ “ሥጋ ወደሙ” ነው በማለት፣ የመጾር መስቀል በመጠቀም “የቅዳሴ ሥርዓት” ሲያካሄዱ እንደነበር ከሥፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

     ከዓርብ የካቲት ፰ ቀን ጀምሮ እስከ እሑድ የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ጉባኤ ማዘጋጀታቸውንና ዓርብና ቅዳሜ የትምህርትና የምክክር ጉባኤ፣ እሑድ “ቅዳሴ” እናካሒዳለን በማለት ቀደም ብለው በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ በለቀቁት ማስታወቂያ እንዲሁም ከተማው ላይ ማስታወቂያ በባነር አሠርተው በይፋ መስቀላቸውን የዓይን እማኞች ገልጠዋል፡፡

         የሀገረ ስብከቱ የፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ኮሚቴ፣ የአርባ ምንጭ ደ/መ/መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ፣ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች እንዲሁም ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በመሆን ወደ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሄድ ጉዳዩን አሳውቀዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም ቅዳሜ የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም “የቤተ ክርስቲያንን ንዋያተ ቅድሳትን ስለማስከበር” በሚል ለሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው መፍትሔ እንዲፈልጉ ለአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት፣ ለአርባ ምንጭ ከተማ ፍትሕና ፀጥታ ጽ/ቤት፣ ለጋሞ ጎፋ ዞን ፍትሕና ፀጥታ ጽ/ቤት፣ ለጋሞ ጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ጽ/ቤት በደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡

   ብፁዕነታቸው ለሚመለከታቸው አካላት በላኩት ደብዳቤም ከዚህ ቀደም በኑፋቄያቸው በሀገረ ስብከቱ ተወግዘው የተለዩ ግለሰቦች ቅዳሴ እንቀድሳለን በማለት ቤተ ክርስቲያን ላይ በማላገጥና የራሷን የሆኑትን ቅዳሴዋንና ንዋያተ ቅድሳቷንና ከራሷ ያገኙትን መዓርግ በመያዝና በመጠቀም በ፲/፮/፳፻፲፩ ዓ.ም ፕሮግራም ሊያካሔዱ ማሰባቸውን ያስረዳል፡፡ ፕሮግራም እንደሚያካሄዱም በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ በመልቀቅ ምእመናንና ቤተ ክርስቲያንን ያስቆጣ ድርጊት በአርባ ምንጭ ደ/መ/መድኃኔዓለም ሰበካ ጉባኤ የቀረቡ የሕዝብ አቤቱታዎች እንደደረሳቸው የገለጹት ብፁዕነታቸው የሚመለከተው አካል ለሰላም ሲባል ትልቅ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ ሊሰጥ ይገባዋል በማለት አሳውቀዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በተጨማሪም በዚሁ አቤቱታቸው “የዚህች ቤተ ክርስቲያንም ሆነ የሀገረ ስብከቱ አቋም ሰላምን መስበክ ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው ከዚህች ቤተ ክርስቲያን እስከወጡ ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን መገልገያ ንብረቶች (ንዋያተ ቅድሳት) ሥርዓቷንም ሆነ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ያገኙትን መዓርጋት ሊተዉና የራሳቸውን እምነት ሊያካሔዱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የራሳቸውን ፕሮግራም ማካሔዱን እንደማይቃወሙና የቤተ ክርስቲያን የሆኑትንም ንብረቶች እና ሥርዓቶች ሊመልሱ ይገባል ብለዋል፡፡

እሑድ ጠዋት በቦታው መረጃው የደረሳቸው የሕግ አካላት ባለመገኘታቸው ከፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ኮሚቴ፣ ከሰበካ ጉባኤ እንዲሁም ከስብከተ ወንጌል የተውጣጡ አባላትና ወጣቶች እንዲሁም ምእመናን ተሰባስበው ቅዳሴ ወደሚያካሔዱበት ቤት በመሔድ ግለሰቦቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት እንዲመልሱ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የለበሱትን ልብሰ ተክህኖ በማስወለቅ፣ ከበሮ፣ መስቀል፣ መጻሕፍትና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት ይዘው ወደ አርባ ምንጭ ደ/መ/መድኃኔዓለም ሲመለሱ፣ የሕግ አካላትም በመድረስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ሥር በማዋል ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል፡፡

ሰኞ ጠዋት የችግሩን አሳሳቢነት በመግለጽ አስፈላጊና ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗ ጥያቄ እንዲመለስ በማለት በብፁዕነታቸው የተጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ በመያዝ ለሚመለከተው አካል ቢያመለክቱም የሚመለከተው አካል ደብዳቤውን ተቀብሎ ጉዳዩ ከባድ በመሆኑ ከዞኑና ከከተማው ኃላፊዎች ጋር መመካከር አለብን በማለቱ ክስ እስካሁን አለመመሥረቱ ተገልጿል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ሲኖዶስ እያከናወነ ስላለው  ጥረት ሲገልጹ “ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችን መገለጫ የሆኑትን ያሬዳዊ ዜማና ንዋያተ ቅድሳት ለማስጠበቅ ውይይቶችን ሲያደርግ እንደቆየና በአሁኑ ወቅትም የአእምሮ ንብረት በሚል ኮሚቴ ተቋቁሞ በጥናት ላይ ይገኛል” ብለዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከትም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አማካይነት የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ አዋቅሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጠዋል፡፡

     በሕግ አካላት ቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት ግለሰቦች ውስጥ አንዱ አእመረ አሸብር ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የሊቃውንት ጉባኤ አባል የነበረና በኑፋቄው ምክንያት የተወገዘ ግለሰብ  ነው፡፡ የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ጠዋት ከፖሊስ ጣቢያ እንደተለቀቁም የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት እንዲከበሩ ሀገረ ስብከቱ          ለሚመለከታቸው አካላት የጻፈው ደብዳቤ

የሩቅ ምሥራቅ ግንኙነት ጣቢያ በህንድ ሀገር ፭ተኛ ዙር ሐዊረ ሕይወት አደረገ

         ሕይወት ሳልለው

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ  የማኅበረ ቅዱሳን የሩቅ ምሥራቅ ግንኙነት ጣብያ በህንድ ሀገር የሚኖሩ አባላቱንና ምእመናንን በማስተባበር ከጥር ፲፭ እስከ ጥር ፳፩ ቀን  ፳፻፲፩ ዓ/ም ወደ ኬሬላ ፭ተኛውን ዙር የሐዊረ ሕይወት ጉዞ አካሄደ፡፡

በአባ ጂኦ ዮሴፍ መሪነት ፺፱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች መንፈሳዊ ጉዞ አድርገዋል፡፡ በህንድ ኬሬላ ግዛት ኮታይም ከተማ ወስጥ በሚገኙ ቅዱስ ጊዮርጊስና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን  ማርታ ማርያም ኦርቶዶክስ ሴርያን ቤተ ክርስቲያን፣ የመነኮሳት ገዳም፣ ማር ባስልዮስ ገዳም እንዲሁም የኦርቶዶክስ ቲኦሎጂካል (ነገር መለኮት) ሴሚናሪ እና የማር ባስልዮስ ክርስቲያን የኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጅ ኮሌጅንም በዋነኛነት ጎብኝተዋል፡፡

ኮትያም ወደሚገኘው ኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተደረገው ጉዞ ላይ ለምእመናኑ፤ “የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት” በሚል ርእስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ከህንድ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያነጻጸረ ትምህርት በዶ/ር ረጂ ማቲው ተሰጥቷል :: በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተማሪዎች የበገና መዝሙርና በህንዳውያን ዘማሪዎች በህንድ ቋንቋ የተዘጋጀ መዝሙር በጋራ ቀርቧል፡፡ በጉዞው ላይ የነበሩት አባ ኦ ቶማስም “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በባህልና በበርካታ ንዋያተ ቅድሳት የታጀበች ናት” ሲሉ አድነቀዋል፡፡  በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተመሠረተችው ዘቫላካራ ማርታ ማርያም ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቀድሞው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንደተጎበኘ አባ ጂኦ ለምእመናኑ አስታውቀዋል፡፡፡፡

ከማእከሉ በአውቶብስ ሦስት ሰዓት፤ በጀልባ አንድ ሰዓት ተኩል የሚፈጀው እና በደሴት ወደተከበበው የቅዱስ ቶማስ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዞም ያደረጉ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗ በቁጥር ትንሽ አባላት እና ጥቂት አገልጋይ እንዳሏትም አስገንዝቧቸዋል፤ ከዚህ ባሻገር በቅዱስ ቶማስ የተመሠረተችው የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በወቅቱ ሲጠቀሙበት የነበሩት ባህላዊ ቅርሶችና ንዋየ ቅድሳትን ጎብኝተዋል፡፡ የጉዞው ተሳታፊዎችም “ከቦታው በረከትን አግተኝናል” ሲሉም የምስክርነታቸውን ቀል ሰጥተዋል፡፡

በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በመቋሚያና በበገና ህብር የቀረበው ያሬዳዊ ዝማሬ መርሐ ግብር ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጠው መ/ር ሳምሶን ስለመሳሪያዎቹ ለህንድ አባቶችና ለምእመናን ገለጻ አድርጓል፡፡ ስለአጠቃላይ መርሐግብሩ ከተሳታፊዎች ሐሳብ ተሰብስቦ፣ የአጋጠማቸው ችግሮች ላይ ውይይት በማድርግና የመፍተሔ አቅጣጫ በመስጠት፣ ፭ተኛው ዙር ሐዊረ ሕይወት  በሰላም ተጠናቋል፡፡

 

 

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለስብከተ ወንጌል የሚሰማሩ ሰባክያነ ወንጌል ተመረቁ

 

                               ተመራቂዎች በከፊል

በእንዳለ ደምስስ

  በማኅበረ ቅዱሳን አዳማ ማእከል ሥር የሚገኘው የደብረ ዘይት ወረዳ ማእከል ከአዳአ ወረዳ ቤተ ክህነት፤ ከበጎ አድራጊ ምእመናንና ማኀበራት ጋር በመተባበር በሁለተኛ ዙር ገጠር ተኮር የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማጠናከር በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ለ፰ ወራት በሂዲ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወካህን መልከ ጼዲቅ አብያተ ክርስቲያናት ያሰለጠናቸውን ፴፬ ተተኪ ሰባክያነ ወንጌል ጥር ፭ ቀን ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም የአድአ ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህን፤የየአጥቢያዎቹ አስተዳዳሪዎች፣ በጎ አድራጊ ምእመናንና የደብረ ዘይት ወረዳ ማእከል አባላት በተገኙበት አስመረቀ፡፡

ሰልጣኞቹ ከ፲ አጥቢያዎች የተመለመሉ ሲሆን፣፱ የትምህርት አይነቶችን ሲከታተሉ መቆየታቸውን፣አብዛኛዎቹ ሰልጣኞችም ካህናትና ዲያቆናት መሆናቸው አቶ ሀብታሙ ዘውዱ የወረዳ ማእከሉ ሰብሳቢ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡ካህናቱና ዲያቆናቱ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ስልጠናውን መውሰዳቸውም ለወደፊቱ ከስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተጨማሪ የቤተ የመቅደስ አገልግሎትን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ እንደሆነና አብያተ ክርስቲያናቱም ለሥልጠና የሚሆኑ ቦታዎችን በማመቻቸት የነበራቸው ተሳትፎ ታላቅ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

“የሥልጠናው ዋና ዓላማ ምእመናን በሚያውቁት ቋንቋ በማስተማር ከነጣቂ ተኲላዎች ለመጠበቅ ነው፡፡ የሥልጠናው ሙሉ ወጪም ብር 123,348.90 (አንድ መቶ ሀያ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንትብር ከዘጠና ሳንቲም) በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የቀድሞ ግቢ ጉባኤ ተመራቂዎች የተሸፈነ ነው” ብለዋል፡፡ የቀድሞ ተመራቂዎቹ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የጠቆሙት ሰብሳቢው ይህንን መልካም ተሞክሮ ሌሎችም ማኀበራት በመውሰድ ሊማሩበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልእክትም “ሰልጣኞች ከምረቃ በኋላ ትምህርት በቃን ሳትሉ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እግር ሥር  ቁጭ ብላችሁ መማር፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይገባችኋል፡፡ ዋናው ዓላማችሁንም ባለመዘንጋት ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው ቦታዎች እየተዘዋወራችሁ ቤተ ክርስቲያን የጣለችባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ ይጠበቅባችኋል” በማለት በሪፖርታቸው አስገንዝበዋል፡፡

የደብረ ዘይት ወረዳ ማእከል አባላት ከግልና ከማኀበራዊ ጉዳያቸው ቅድሚያ ለሥልጠናው ልዩ ትኩረት መስጠታቸው፣ የአዳአ ወረዳ ቤተ ክህነት ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላትና ለአጥቢያዎች መመሪያ በመስጠት ስልጠናው የተሳካ እንዲሆን ታላቅ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሊቀ ካህን መልአከ ፀሐይ ቀሲስ እንዳለ ሐረገወይን ባስተላለፉት መልእክትም የወረዳ ማእከሉ ለስበከተ ወንጌል አገልግሎት መስፋፋት የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡ ሲሆን ለተመራቂዎችም “በቋንቋ ምክንያት የሚጠፋውን ትውልድ ከሞት ወደ ሕይወት የመመለስ አደራ አለባችሁ” ብለዋል፡፡

የደብረ ዘይት ወረዳ ማእከል ከአድአ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ ከበጎ አድራጊ ምእመናንና ማኅበራት ጋር በመተባበር በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተተኪ ሰባኪያነ ወንጌል ለማፍራት ፕሮጀክት ቀርጾ በመጀመሪያው ዙር በድሬ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከ፰ አጥቢያዎች የተመለመሉትን ፳፫ ሰልጣኞችን ለስምንት ወራት አሰልጥኖ የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በአባቶች ቡራኬ አስመርቋል፡፡

ምንጭ፤ምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 26ኛ ዓመት ቊ8ቅጽ 26ኛ ቊጥር 398 ከጥር 1-15 ቀን2011ዓ.ም

 

 

 

በቃጠሎ የወደመውን ቤተ ክርሰቲያን ለመገንባት እንቅስቃሴ ተጀመረ

 

በእንዳላ ደምስስ

ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም በቃጠሎ የወደመውን የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሊቀ ኅሩያን መ/ር ወጋየሁ ደምሴ የባሌ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ ገለጹ፡፡

“በቃጠሎው ቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ ለሙሉ ወድሞ ነው የደረስነው፡፡ ሕዝቡም ከፍተኛ ሐዘን ነው የተሰማው፡፡ ሁላችንም ልባችን ተሰብሮ በዕንባ ስንራጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ አልቅሶ ብቻ አልተበተነም፡፡ዕንባውን አብሶ ገንዘብ የማሰባሰቡን ሥራ በመጀመር የመፍትሔ እርምጃ ነው የወሰደው፡፡” ሲሉ የገለጹት የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ናቸው፡፡ሀገረ ስብከቱ ካህናቱን፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትን፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ተወካዮችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በማሰባሰብ ዘጠኝ አባላት ያሉት የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ በማዋቀር ቤተ ክርስቲያኑን በድጋሚ ለመገንባት ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራው መጀመሩንና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ማሰባበሰብ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

ከገንዘብ በተጨማሪም ምእመናን የአንገት ሐብላቻውንና የጣት ቀለበታቸውን በመስጠት፣ እናቶች ከመቀነታቸው እየፈቱ በመንፈሳዊ ስሜትና ቁጭት አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ማበርከታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

ሙስሊሙ ኅብረተሰብም በቤተ ክርሰቲያኑ መቃጠል ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማውና በቦታው በመገኘት ገንዘብ በመለገስ፣ እንዲሁም የግንባታ እቃዎችን ለመስጠት ቃል በመግባት መሳተፋቸውን፣ ቤተ ክርስቲያኑን ለማሠራትም በመስጊድ ውስጥ ሙስሊሙን በማስተባበር ገንዘብ ለማሰባበስብ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ ተናግረዋል፡፡

“በዛሬው ውሏችንም ለተቋቋመው የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ እወቅና ለመስጠት ሰበካ ጉባኤው ለወረዳው ቤተ ክህነት፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱም ለሀገረ ስብከቱ ደረጃውን ጠብቆ በደብዳቤ በመጠየቅ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡” ያሉት ሊቀ ኅሩያን መ/ር ወጋየሁ የባንክ ሒሳብ (አካውንት) በመክፈትም ሕጋዊነት ባለው አሠራር ገቢ የማሰባሰብ ሂደቱ እንደቀጠለ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎትን በተመለከተም ቤተ ክርስቲያኑ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ስላለው ከሰበካ ጉባኤውና ከሕንፃ አሰሪ ኮሚቴው ጋር በመመካከር አዳራሹን በማመቻቸት ሙሉ የቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት ማለትም ኪዳንና ቅዳሴ ሳይቋረጥ መቀጠሉንና የቃጠሎውን መንስኤ በተመለከተም የሕግ አካላት እያጣሩ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡

በባሌ ሀገረ ስብከት የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ

በእንዳለ  ደምስስ

በባሌ ሀገረ ስብከት ሮቤ ከተማና አካባቢው ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ላይ ለጊዜው ባልታወቀ መንስኤ መቃጠሉን መ/ር ያሬድ ገ/ማርያም የወረዳው ቤተ ክህነት ጸሐፊ ገለጹ፡፡

የቃጠሎው መንስኤና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት መ/ር ያሬድ፤ ቤተ ክርስቲያኑ በቃጠሎው ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መውደሙንና በአገልጋዮችና በአካባቢው ምእመናን ጥረት ታቦቱን ብቻ ማዳን መቻሉን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ዝርዝሩን እንደደረሰን እናቀርባለን፡፡

 

በጥምቀት በዓል የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥሪያቸውን አስተላለፉ!

                                                                                                        ሕይወት ሳልለው
የጥምቀት በዓል አከባበር በጃንሜዳ እና በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በድምቀት በተከበረበት ቀን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ለቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላላፉት መልእክት ላይ ምእመናን በተለይም ወጣቶች በፍቅርና በመቻቻል መኖር እንዳለባቸው አሳሰቡ፡፡“የዛሬ ፵ ዓመት የሆነውን ዓይነት አካሄድና ታሪካዊ ስሕተት እንዳትፈጽሙ ተጠንቀቁ! የምትሹትንና የምትመኙትን ማግኘት የምትችሉት አንድነትና ሰላም እስካለ ብቻ ነው፡፡ አርቆ በማየትና አስተውሎ በመራመድ፤በትዕግሥትና በመቻቻል ሳይሆን በኃይልና በጉልበት የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን ብላችሁ ከሆነ ሁሉንም ልታጡ ትችላላችሁና አስተውሉ!” በማለት ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፤ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ፤ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ፤እንዲሁም የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኂሩት ካሣው፤ ረ/ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ የአዲስ አበባ ከተማ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና ከተለያዩ ሥፍራዋች ለመጡ ምእመናን መልካም የጥምቀት በዓልን የተመኙት ፓትርያኩ፤ይህ በዓል የንስሓ ጥሪ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡“መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ”፤ብሎ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን፤በዚህ አስከፊ ዘመን የንስሓን አስፈላጊነት መረዳትና መተግበር እንዳለብን አሳስበዋል፡፡
በዓለ ጥምቀት በዋነኛ የመዳን ሥርዓት መጀመሪያ መሆኑና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥር ፲፩ ቀን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ እኛ እንድንጠመቅ እንዳስተማረን “ወውእቱ ያጠምቀክሙ በመንፈስ ቅዱስ ወበእሳት፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤”ተብሎ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፮ ላይ እንደ ተገለፀውም ለእኛ ድኅነት ሆኖልናል፡፡

“ጥምቀት ማለት ሰፋ ያለ ትርጒም ቢኖረውም ምሥጢራዊ ትርጒሙን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው መንፃት፤መለወጥ፤ መሻገር፤ አዲስ ሕይወት፤ አዲስ ልደት፤ አዲስ ምሕረት የሚሉትን ሐሳቦች ያመሰጥራል” በማለትም ቅዱስ ፓትርያርኩ አብራርተዋል፡፡ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማርቶማ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ሶርያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፤የቅዱስነታቸውን ሐሳብ በመደገፍ እንዲህ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማርቶማ

“ይህ በዓል የብርሃን በዓል ቢሆንም እኛ እንደምናውቀው ዓለማችን በድቅድቅ ጨለማ የምትገኝ ሲሆን ለዚህ ጨለማ ብርሃን ያስፈልገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ተስፋ ናት፡፡ ምክንያቱም ይህን የመሰለ በዓል በየትኛውም ዓለም አይከበርምና፡፡እኛም በዚህ ታላቅ በዓል ወቅት በጸሎት ከእናንት ጋር ነን፤”በማለት ከማጽናናታቸውም በተጨማሪ በክርስቲያኖች መካከል መልካም የሆነና የጠነከረ ግንኙነት ሰላም እንዲኖር ያደረገ እግዚአብሔርን ዘወትር እንደሚያመሰግኑና እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠብቅልንና ኢትዮጵያን እንዲባርክ በመመኘት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡