ዘጠነኛው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ሊካሄድ ነው

በካሣሁን ለምለሙ

ዘጠነኛው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ በመጭው እሑድ ግንቦት ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ/ም ሊካሄድ እንደሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ መምህር ዕንቈ ባሕርይ ተከሥተ አስታወቁ፡፡

በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ስለሃይማኖታቸውና ስለሀገራቸው ጉዳይ የያገባኛል ስሜት እንዲኖራቸው ማድረግ የጉባኤው አላማ እንደሆነ የገለጡት ኃላፊው የሰንት ትምህርት ቤት ወጣቶች ሐሳባቸውን በግልፅ የሚለዋወጡበትና ልማድ የሚቀስሙበት መድረክም ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ያገጠሟቸውንና ሊገጥሟቸው የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዛቸውን አቅጣጫ ለመጠቆም ጉባኤው አስፈላጊ ነው፡፡ ጉባኤው በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውን የሰንበት ትምህርት ወጣቶችና አባቶች የሚሳተፉበት ሲሆን የተጀመረውም ከዛሬ ስምንት ዓመታት በፊት በቀድሞው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አማካይነት እንደሆነ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ጉባኤው ከተጀመረ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ያጋጠሟት ችግሮችንና መልካም አጋጣሚዎችን በጥልቀት የሚዳሰሱበትና የሚተነተኑበት እንደሆነ ኃላፊው አስገንዝበው የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹም ሪፖርት የሚያቀርቡበት፤ የጋራ ዕቅድ የሚያዘጋጁበት በቀጣይ ጊዜያት ተግባራዊ ስለሚሆኑ ሥራዎች የሚመክሩበት፤ የቤተ ክርስቲያኗን ህልውና በማስጠበቅ ዙርያ በትኩረት የሚመከሩበትና አቋም የሚያዙበት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ውስጣዊ አሠራርና ውጫዊ ፈተናዎች ጉባኤው በሚገባ የሚገመግም እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው የሚካሄደው በቪዲዮ ኮንፍረስ አማካይነት ሲሆን የሚመለከተው አካል ሁሉ ተሳታፊ እንደሚሆን ኃላው ገልጸዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ በየቤታቸው ወይም በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሁነው ጉባኤውን በቀጥታ ስርጭት ይከታተላሉ፡፡ በጉባኤው ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ በርካታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚገኘም ኃላፊው አረጋግጠዋል፡፡

ጉባኤው ከዚህ ቀደም በአካል ይካሄድ እንደነበር የጠቀሱት ኃላፊው ነገር ግን በዚህኛው ዓመት ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በቪዲዮ ኮንፍረስ ብቻ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡ ጉባኤው በአካል ይካሄድ በነበረበት ወቅት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይቆይ እንደነበር ታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተካሄዱት የሰንበት ት/ቤት አንድነት ጉባኤያት ብዙ በረከቶችን ይዞ የመጣ ሲሆን ወጣቶችና ሕፃናት ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እንዲሁም በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚነሱ ጭቅጭቆችና አለመግባባቶች እንዲቀንሱና ችግሮቹ ሁሉ በሰለጠነ ውይይት ብቻ እንዲፈቱ ጉባኤው ላለፉት ስምንት ዓመታት እገዛ እንዳደረገ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ላለንበት ዘመን የሚመጥን ሥራና ዕቅድ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስፈልጋት ኃላፊው ገልጸው ዕቅዶችንም በተግባር መተርጎም የሚችሉ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዳሉ ጠቁመው የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ችግሮች በትኩረት በመፍታት የውጩን ፈተና ደግሞ ከቤተ መንግሥት ጋር በመሆን መፍታት እንደሚያስፈልግም ኃላፊው አሳስበዋል፡፡