የቤተ ክርስቲያንን ቅርስ ዘርፈው እጅ ከፍንጅ የተያዙ ተጠርጣሪዎች ከእስር ተፈቱ

በካሣሁን ለምለሙ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሜታ ሮቢ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘውን የሙጤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ቅርስ ዘርፈው እጅ ከፍንጅ የተያዙ አራት ግለሰቦች በፍርድ ቤት ትእዛዝ ከእስር መፈታታቸውን የወዳ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ መሪጌታ ክፍሌ ቱቦ አስታወቁ፡፡

እንደ መሪጌታ ክፍሌ ገለጻ ዘራፊዎቹ ወንጀሉን ከመፈጸማቸው በፊት በአድአበርጋ ወረዳ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የቅርስ ዝርፊያ ወንጀል ሊፈጽሙ ሲሉ በአካባቢው ምእመናንና የፀጥታ ኃይሉ ርብርብ ሊከሽፍ እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡

ዘራፊዎቹ የዝርፊያ ሙከራ ካደረጉበት አካባቢ ተነሥተው በሜታ ሮቢ ወርዳ ቤተክህነት ሥር የሚገኘውን የሙጤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ቅርስ ለመዝረፍ እንዳሰቡ ሀገረስብከቱ ከምእመናን በደረሰው ጥቆማ መሠረት የቤተ ክርስቲያኑን ጥበቃ በማጠናከር እንዲሁም ለአካባቢው የፀጥታ ኃይል በማሳወቅ ዘራፊዎቹ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ቅርሱን ዘርፈው በመውጣት ላይ እንዳሉ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም “ወንጀሉን የፈጸሙት አራቱ ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ከተያዙበት ዕለት አንሥቶ በሦስት ምስክሮች ፖሊስ ጣቢያም ሆነ ፍርድ ቤት ተመስክሮባቸው በእስር ይገኙ  የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የፖሊስንና የዐቃቤ ሕጉን አቤቱታ በመተው ግለሰቦቹን በሠላሳ ሺህ ብር ዋስትና ለጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ዓ.ም ቀጠሮ በመስጠት ከእስር ፍትቷቸዋል›› ብለዋል፡፡

በፖሊስ ጣቢያም ሆነ በፍርድ ቤት የተመሰከረባቸውን ተጠርጣሪዎች ያለምንም ምክንያት ፍርድ ቤቱ ከእስር መፍታቱ ቅር እንዳሰኛቸው የገለጡት ሥራ አስኪያጁ ጉዳዩን ወደ በላይ አካል ለመውሰድ እንዳሰቡም ተናግረዋል፡፡

የሜታ ሮቢ ወረዳ ፖሊስ ሳጅን ዶሻ በለው በበኩላቸው በቤተ ክርስቲያን ቅርስ ዘረፋ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦችን እጅ ከፍንጅ እንደያዙ ገልጠው፤ ተጠርጣሪዎቹ በሦስት ምስክሮች ተመስክሮባቸው በሕግ ጥላ ሥር እንደዋሉ ተናግረዋል፡፡

ሳጅን ዶሻ አያይዘውም “በሦስት ምስክሮች የተመሠከረባቸው ተጠርጣሪዎች በእስር ቆይተው ቶሎ ብይን ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በዋስ የሚለቀቁ ከሆነ ግን ሊጠፉ ይችላሉ በማለተ የሚስማን ሥጋት እንዳለብን ለፍርድ ቤቱ ያመለከትን ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን በሠላሳ ሺህ ብር ዋስ ተፈትተው ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንሰበስባለን›› እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግም ሆነ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በእስር እንዲቆዩ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን  በሠላሳ ሺህ ብር ዋስትና ተለቀው ለጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ጊዜ መከላከያ ይዘው እንዲቀርቡ ሲወሰን ለእኔም “ተጨማሪ የማጣራት ሥራ መሥራት ያስፈልግኛል” ሲል ተጨማሪ ጊዜ እንደጠየቀ ሳጅን ዶሻ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ምእመናንም ሆኑ አገልጋዮች ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያናቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ በማስገነዘብ ፖሊስም ከቤተ ክርስቲያኗ ጎን በመቆም ሕግ የማስከበርን ሥራ እንደሚሠራ ያረጋገጡት ሳጅን ዶሻ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮችም ሆኑ ምእመናን መሠል የወንጀል ጥርጣሬ ሲኖራቸው ቀድመው ለፖሊስ ማሳወቅ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡