ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? (ሮሜ 8፡35)

ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ

መጽሐፍ ቅዱስ ከጥንት ጀምሮ የሚነግረንን የሰውና የእግዚአብሔር ግንኙነት ስንመለከት ጎልተው የሚወጡ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም በአንድ በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ታላቅ በጎ ሃሳብና ልዩ አባታዊ ቸርነት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጆች ለዚህ አምላካዊ ጥሪና ቸርነት የሚሰጡት የአጸፌታ መልስ ነው፡፡ የሰዎች አጸፌታዊ መልስም ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ይህም ጥቂቶቹ ለአምላካቸው በጎ ምላሽ ሲሰጡ ቀሪዎቹ (በታሪክ ሲታይ ብዙዎቹ) ለአምላካቸው መታዘዝን እምቢ ማለታቸውንና ማመጻቸውን ነው፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የሚያሳየን ከመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ የዲያብሎስን የጎዮንሽ ክፉ ምክር ሰምተው በአምላካቸው ላይ ሲያምጹ፣ ከዚያም የተነሣ ከጸጋ ተራቁተው በራሳቸው ላይ ተደራራቢ ዕዳ በደል ማምጣታቸውን ነው፡፡ ከዚያም ዐመጽ የተጀመረው የሰው ሕይወት እየቀጠለ ክፉው ቃየን የራሱን ወንድም አቤልን በግፍ ደሙን ሲያፈስሰውና ሲገድለው እናያለን፡፡

በሰው ልጆች የመጀመሪያ ጥፋትና ዐመጽ የመጣውን ዕዳና በደል፣ አጠቃላይ በሰው ዘር ላይ የወደቀውን ብዙ ጉዳትና ጥፋት ለማስወገድና ሰውን ወደ ሕይወትና ክብር ለመመለስ ራሱ እግዚአብሔር ሰውን ፍለጋ ልዩ በሆነ አመጣጥ አካላዊ ቃል ሰው ሆኖ ወደ ፈጠራቸው የሰው ልጆች ባሕርያችንን ባሕርዩ አድርጎ ሲገለጥ ደግሞ በደስታ እንደ መቀበል ፋንታ አሁንም ብዙዎች ተቃወሙት፡፡ ነገሩ ድንገት የደረሰባቸውና ያልጠበቁት እንዳይሆንባቸው እግዚአብሔር ከገነት ሲባረሩ ጀምሮ በትንቢት፣ በራዕይ፣ በተምሳሌትና በመሳሰለው ሁሉ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ ደግሞ ደጋግሞ ሲናገር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ያ ሁሉ ትንቢትና ሱባኤ የተነገራቸው አይሁድ ለማመን የመጀመሪያዎቹ ሊሆኑ ሲገባቸው የእግዚአብሔርን እውነትና ልዩ ጸጋ ለመቀበል አልፈለጉም፡፡ ቅዱስ ወንጌል ውስተ እሊአሁ መጽአ ወእሊአሁሰ ኢተወክፍዎ – የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፣ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም በማለት ይህን አሳዛኝ እውነታ ይነግረናል፡፡ ዮሐ. 1፡12

እውነትን የሚቃወሙ አይሁድ ተቃውሟቸውና ጥላቻቸው እያደገ ሄዶ ጫፍ ሲደርስም ምንም እንኳ እርሱ በፈቃዱ ወዶ ቢያደርገውም እነርሱ ግን እናጠፋዋለን መስሏቸው በመስቀል ሰቀሉት፡፡ በመቃብር ለማስቀረትና ከዚያ ወዲያ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ነገር እንዳይነገርና ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ በማሰብ መቃብሩን ጥቂት ሰዎች ብቻቸውን ሊያንከባልሉት የማይችሉት ታላቅ ደንጊያ ገጥመው ዘጉት፡፡ ይህም አልበቃቸው ብሎ ከሮማውያን ወታደሮች እንዲመደቡ አድርገው ዙሪያውን እንዲጠብቁ አደረጓቸው፡፡ በገዢው ማኅተምም አተሙት፡፡ ሆኖም ግን ያ ሁሉ ጥረትና ጥበቃ ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩን ክፈቱልኝ ደንጊያውን አንሡልኝ ሳይል መቃብሩ እንደ ታተመ ሞትን ድል አድርጎ ከመነሣት አላገደውም፡፡ ቅዱሳን መላእክት ወደ መቃብሩ የሄዱትን ቅዱሳት አንስት ምንተ ተኃሥሣሁ ለሕያው ምስለ ምውታን ተንሥአ ኢሀሎ ዝየሰ – ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቷል እንጂ በዚህ የለም? በማለት የሞትንና የመቃብርን ይዞ የማስቀረትና የማፍረስ የማበስበስ ኃይል ድል አድርጐ መነሣቱን የምሥራች አበሠራቸው፡፡ ሉቃ. 24፡5 ሞትንና የክፋ ኃይልን ሁሉ ድል አድርጎ ለተነሣው ለመድኃኒታችንና ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን!

እርሱ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ያ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ መከራ የተቀበለውና የሞተው፣ ወደ መቃብር የወረደው እርሱ አሁን ሕያው ሆኖ መነሣቱን በመካከላቸው እየተገኘ የተወጋ ጎኑን፣ የተቸነከሩ እጆቹንና እግሮቹን በማሳየት የተነሣው ያው እርሱ መሆኑን ደጋግሞ አረጋገጠላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እነርሱ ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው ይህን የሞትን በክርስቶስ ትንሣኤ መወገድና በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወት፣ ልጅነት፣ መንግሥተ ሰማያት በእርሱ ዘንድ የተዘጋጀ መሆኑን እንዲመሰክሩ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁብሎ ላካቸው፤ ። የሐዋ. 1፡8

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን የሕይወትን ቃል እንዲሰብኩ ወደ ዓለም ሲልካቸው ምን እንደሚጠብቃቸው ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፣ . . . እያለ አስቀድሞ ደግሞ ደጋግሞ እውነታውን ነግሯቸዋል፣ አስጠንቅቋቸዋል፡፡ ማቴ. 10፡28 እንዲሁም እነርሱን የሚያሳድዷቸው እምነት አያስፈልግም ወይም በእግዚአብሔር መኖር አናምንም የሚሉ ብቻ ሳይሆኑ ይልቁንም እግዚአብሔርን ያገለገሉና ለእርሱ የቀኑ የሚመስላቸው ሃይማኖተኞች ነን ባይ የሆኑ ሰዎችም እንደሚሆኑ እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬያችኋለሁ። ከምኵራባቸው ያወጧችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው በማለት በሚገባ አስቀድሞ አስጠንቅቋቸዋል፣ አስተምሯቸዋል፡፡ ዮሐ. 16፡1-3 እምነት የለኝም ከሚለው ባላነሰ በተሳሳተ እምነት ውስጥ ያሉም እውነተኛ ክርስቲያኖችን በጽኑ ጭካኔ ሲጨፈጭፉ ኖረዋል፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን ማመን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ችግር የሚሆነው ሌላውን ሰው ግድ እኔ የማምነውን ካላመንክ በስተቀር በዚህች ምድር ላይ የመኖር መብት የለህም ሲል ነው፡፡ በምድራችን ላይ ብዙ ግፍ ሲፈጸም የኖረውና አሁንም እየተፈጸመ ያለው ከዚህ የተሳሳተ እምነትና አስተሳሰብ የተነሣ ነው፡- እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የሰጠውን ነጻነትና መብት በመጋፋት ሰዎችን በማስተማርና በሳመንና ሳይሆን በኃይልና በጉልበት በማስገደድ የራስን እምነት በሌላው ላይ መጫን፡፡ ይህም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በእግዚአብሔር እናምናለን የሚሉት ብቻ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር መኖር አናምንም፣ ሃይማኖት የለንም የሚሉትም (ይህም በራሱ እምነት ስለሆነ) ሌሎችን እንደ እኛ ካልሆናችሁ በማለት ብዙ ግፍ ሲያደርሱ ኖረዋል፣ ዛሬም ያው ሁኔታ መልኩንና ቅርጹን ቢቀይር እንጂ ጨርሶ አልቀረም፡፡

እንግዲህ የክርስቶስ ተከታዮች (ክርስቲያኖች) ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመናቱ የየጊዜውን መስቀል ሲሸከሙና ከመስቀሉ በኋላ የሚገኘውን አክሊል ሲቀበሉ ኖረዋል፡፡ በዘመናት የሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚሸከሙት መስቀል አንድ ዓይነት አይደለም፤ ለዚህ ነው ጌታችን መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ያለው፡፡ ማቴ. 16፡24 መስቀሉን ማለቱ ለእርሱ የተዘጋጀለትን መከራ ማለቱ ነው፡፡ በክርስትና የመጀመሪያው ምስክር የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ ለአይሁድ የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ አምላክነትና መድኃኒትነት፣ እነርሱ (አይሁድ) እንቀበላቸዋለን በሚሏቸው የብሉያት መጻሕፍት ሁሉ የተነገረውና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው መድኃኒት (መሢሕ) መሆኑን፣ እነርሱም ኢየሱስን መስቀላቸው ታላቅ ጥፋት መሆኑን ሲነግራቸው ተከራክረው መርታት ስላልቻሉ በደንጊያ ወግረው ገደሉት፡፡ . . . ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም፡- ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም፡- ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር። የሐዋ. 7፡57-60 ስለ ክርስቶስ እየመሰከሩ ይህን እውነትና ሕይወት በሚቃወሙ በክፉዎች እጅ መገደልና ሰማዕትነትን መቀበል አንድ ተብሎ ተጀመረ፡፡ በክርስቶስ መከራና መስቀል የተጀመረው የክርስትና ጉዞም በሕይወት መዝገብ ላይ በደም ቀለም መጻፍ ጀመረ፡፡

በመቀጠልም ከሐዋርያት መካከል ቅዱስ ያዕቆብ በሄሮድስ እጅ በሠይፍ በመገደል ሰማዕት ሆነ፡፡ በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። የሐዋ. 12፡1-2 ከዚያ በኋላ ክርስቲያኖችን መግደልና ማሰቃየት እየሰፋና ተቋማዊ መልክ እየያዘ ሄዶ በተለይ በሮማ ግዛት ግዛት ክርስትና በዐዋጅ ሕገ ወጥ ሃይማኖት ነው ተባለ፡፡ በፋርስ ግዛትም እንዲሁ ክርስትና በመንግሥት በይፋ የሚሳደድ ሆነ፡፡ ኔሮን ቄሣር የሮም ከተማ ነዋሪ ክርስቲያኖችን በመግደሉ ሂደት እንዲተባበረውና እንዲደግፈው በማሰብ የከተማን የተወሰነ ክፍል ካቃጠለ በኋላ ይህን ያደረጉት ክርስቲያኖች ናቸው አለ፡፡ ከዚያም ክርስቲኖያችን ያገኛቸው ሁሉ እንደ ሀገር ጠላት በመቁጠር ገደላቸው፡፡ በዚህም ቁጥራቸውን እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው የብዙ ብዙ የሆኑ የክርስቲያኖች ደም ፈሰሰ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስም አንዱ በስቅላት ሌላው በምትረተ ሠይፍ ሞቱ፡፡ አንዳንዶቹ የሮም ቄሣሮች ደግሞ ክርስቲያኖችን ማታ ማታ ሰቅለው በእሳት እያነደዱ እንደ ሻማ እንደ መብራት እስኪጠቀሙባቸው ደረሱ፡፡

በዚያን ዘመን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለው ሕይወታቸውን ለሰማዕትነት የሰጡትን ቅዱሳን አባቶችና እናቶች እንዲሁም ሕጻናት ቁጥራቸውን ቀርቶ ግምታቸውን እንኳ ማንም ሊያውቀው አይችልም፡፡ ይህን ለመረዳት አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ ያለውን ብቻ ጠቅሰን እንለፍ፡፡ በዚያን ዘመን ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ በቀላሉ ለመግደል የሚያስችሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ባለመኖራቸው ምክንያት በግብጽ እና በሦርያ የነበሩ ክርስቲያኖች የሚገድሏቸው ወታደሮች እጃቸው ከመግደል እየደከመና ሠይፋቸው በደም እየታለለ እነርሱም እስኪያርፉና መሣሪያቸውን እስኪወለውሉ ድረስ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ለመገደል ለብዙ ቀናት ወረፋዎችን ይጠብቁ ነበር ይሏል፡፡

መንገድ ላይ እንደ ወደቀውና በድንጋይ ላይ እንደ በቀለው ዘር የጊዜውን መከራ ፈርተውና የዚህን ዓለም ሕይወት ወድደው ክርስቶስን የካዱ ቢኖሩም ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ግን በየጊዜው የሚሆነውን መከራ በጽናት ተቀብለው ለሃይማኖታቸው ለክርስቶስ መስክረዋል፡፡ ሲኖሩም ኑሯቸው ሁሉ የሰማዕትነት ሞትን በመጠበቅ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችን ከማሳደድ የተመለሰውና ታላቅ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፡-

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼያለሁ። ሮሜ 8፡36-39

እግዚአብሔርም ምእመናን መከራውን በጽናት እንዲቀበሉ በቅዱስ ቃሉ፣ አጽናኝና አበረታች መላእክትን በመላክና በተለያዩ መንገዶች ሥቃዩን ያሥታግሣቸውና ያበረታቸው ነበር፡፡ ለአብነትም በሮማውያን ቄሣሮች በእነ ኔሮንና ድምጥያኖስ ዘመን ይደርስ የነበረውን መከራ በራእየ ዮሐንስ ላይ በታናሽ እስያ የነበሩትን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲህ በማለት ያበረታታቸው ነበር፡-

በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል። . . . ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን፣ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም። ራ. 2፡8-11

ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም መከራውን በጽናት ይቀበሉ ነበር፡፡ አንዲት ነፍሰ ጡር የነበረች እናት ሃይማኖቷ ክርስቲያን በመሆኑ ምክንያት ብቻ ታስራ ሳለ በሮማውያን ሕግ ነፍሰ ጡሮች አይገደሉ ስለ ነበር ምነው በውስጤ ያለው ጽንስ ቶሎ ተወልዶልኝ ለሃይማኖቴ መስክሬ በሞትኩ ብላ ጸለየች፡፡ ልትወልድ ስትል ምጡ ሲያስጨንቃት ከጠባቂዎቹ ወታደሮች መካከል አንዱ ባያት ጊዜ ምነው ቶሎ ብዬ ለክርስቶስ መስክሬ በሞትኩ ስትይ አልነበር? ተፈጥሯዊ የሆነው ምጥ ይህን ያህል ካስጨነቀሽ ከእኛ እጅ የምትቀበዪውን መከራማ እንዴት አድርገሽ ትችይዋለሽ? አላት፡፡ እርሷም ይህን (ምጡን) የምቀበለው ብቻዬን ነው፤ ስለ ክርስቶስ የምቀበለውን መከራ ግን የምቀበለው ብቻዬን ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ነው፣ እንዲያውም መከራውን የሚቀበለው ራሱ ነው አለችው፡፡ አዎ፣ ስለ ክርስቶስ ያልተከፈለ ዋጋ የለም፤ ለእርሱ የማይከፈል ውድ ዋጋም የለም!

አሁንም ክፉዎች የመዳንን መንገድና እውነትን አንቀበልም ማለታቸው ሳያንስ ሌሎችንም እንደ እኛ ካልሆናችሁ በማለት ለማስገደድና የራሳቸውን አስተሳሰብና እምነት በሌሎች ላይ በኃይል ለመጫን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ክርስቶስን አንክድም የሚሉ ክርስቲያኖችን አንገታቸውን እንደ ከብት አጋድመው በሠይፍ እያረዱ ይገኛሉ፡፡ ራሱን እስላማዊ መንግሥት – Islamic State (IS) ብሎ የሚጠራው ቡድን ከወር በፊት 21 ግብጻውያን ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ክርስቶስን አንክድም በማለታቸው ብቻ አንገታቸውን አርደው ገድለዋቸዋል፡፡ በሶሪያና በኢራቅ በየጊዜው ብዙ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ ይገደላሉ፣ ይሠቃያሉ፤ የቀሩትም ሀገር ለቀው ይሄዳሉ፡፡

ሰሞኑንም ይኸው ራሱን እስላማዊ መንግሥት – Islamic State (IS) ብሎ በሚጠራው ቡድን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ታምነው የክርስትና ሃይማኖታቸውን አንክድም በማለታቸው ምክንያት የተወሰኑት በጥይት ተደብድበው፣ ሌሎቹ ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ በሠይፍ ታርደው የተገደሉትን ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንን ስናስብ መከራቸውና ስቃያቸው ይሰማናል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ለእመ አሐዱ አካል ሐመ የሐምም ምስሌሁ ኩሉ ነፍስትነ – አንድም አካል ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ እንደሚለው የእነርሱ ጭንቀትና ስቃይ የእኛም ጭንቀትና ስቃይ ነውና። 1 ቆሮ. 12፡26-27 እነርሱስ አንድ ጊዜ ተቀብለውት ሄደዋል፣ ለእኛ ግን በየጊዜው የማይረሳና ባስታወሱት ቁጥር ውስጥን የሚያደማ የማይሽር የሕሊና ቁስል ነው፡፡ እነዚህ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የተቀበሉት መከራና ግፍ የሁላችንም መከራና ግፍ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ የሚቀበሉት መከራና የሚጋደሉት ተጋድሎ የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው የክርስቶስ የመከራው አካል ነው፡፡ ጌታችን የኋላውን ቅዱስ ጳውሎስ የቀደመውን ሳውል በሚያስደንቅ ሁኔታ ሲጠራው ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ? አለው፡፡ እርሱም ጌታ ሆይ ማን ነህ? ባለው ጊዜ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ ያለው ይህን የሚገልጽ ነው፡፡ የሐዋ. 9፡3-5 ጌታችን የክርስቲያኖችን ስደትና መከራ የራሱ አድርጎ ለምን ታሳድደኛለህ? አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ አለው እንጂ ለምን ታሳድዳቸዋለህ? አላለውም፡፡ ስለሆነም እነዚህ ወንድሞቻችን ስለ ሃይማኖታቸው የተጋደሉት ተጋድሎና የተቀበሉት መከራ የክርስቶስ የመከራው አካል ነው፤ የሰውነት የአካል ክፍሎች የሚሠሩት ሥራ የራስ ሥራ አካል ነውና፡፡

ይህ የወንድሞቻችን መከራና የግፍ ሞት ሁለት ገጽታ ያለው ነው፡፡ በአንድ በኩል የገዳዮቻቸውን ጭካኔና አረመኔነት ስንመለከተውና የወንድሞቻችንን ስቃይ ስናስበው በእጅጉ ይዘገንናል፤ ማንኛውንም ሰው የሆነን ሁሉ ይነካል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመዳን መንገድ ስለ ሆነችው ስለ ክርስትና እምነታቸው ሲሉ በእግዚአብሔር ኃይል ጨክነው ለክርስቶስ መስክረው መሞታቸውንና እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናታቸውን ስናስበው ደግሞ ልዩ የሆነ ደስታ ይፈጥራል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥቂት ቀናት በፊት በግብጽ 21 ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንደ መሰከሩ ሁሉ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ 30 እውነተኛ መስካሪዎችን አገኘች፡፡ እነዚህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍሬዎች ናቸውና! እንኳን ወላጆቻቸውንና ከዚህ ሞታቸው አስቀድሞ ያውቋቸው የነበሩት ሰዎች ይቅርና አገዳደላቸውን የሚያሳየውንና አይ ኤስ የለቀቀውን ምስል ወድምፅ የተመለከተን ማንኛውንም ሰው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ወንድሞቻችን በቅድስት ሥላሴ ስላላቸው እምነት፣ ስለ ክርስቶስ አምላክነትና መድኃኒትነት፣ በአጠቃላይ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ስለ ሆነችውና ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለ ተሰጠችው አንዲት ሃይማኖት መስክረው መሞታቸው እያሳዘነ የሚያስደስት፣ እያስለቀሰ እልል የሚያሰኝ ነው፡፡ በቀድሞ ዘመን ክርስቲያኖች ለሃይማኖታቸው መስክረው ወደሚገደሉባቸው ቦታዎች ሲወሰዱ እናቶችና አባቶች ልጆቻቸውን፣ ሚስቶች ባሎቻቸውን፣ ወዳጅም ወዳጁን አይዞህ፣ በርታ፣ ጽና፣ ምስክርነትህን ፈጽም፣ የምትሄደው ወደ ክርስቶስ ነው እያሉ አንዱ ሌላውን ያበረታታ ነበር፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ወንድሞቻችን ቤተሰቦች ሰው እንደ መሆናቸው ማዘን ባይቀርም የእነዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ወላጆች ቤተሰቦች በመሆናቸው ሊደሰቱና እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ይገባቸዋል፡፡ ይህ ለሁሉ የሚገኝ
ጸጋና ክብር አይደለምና!

መከራው የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ጎዳት? ወይስ ጠቀማት?

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሰማዕታት በገጠማት በዚያ ሁሉ መከራ እየደከመች ሄደች ወይስ እየጠነከረች? የምእመናን ቁጥርስ እያነሰ ሄደ ወይስ እየበዛ? ታሪክ እንደሚያስረዳን በክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤው የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመከራው እየበዛችና እየጠነከረች ሄደች እንጂ ጠላቶቿ እንዳሰቡት እየደከመችና እየጠፋች አልሄደችም፡፡ ይልቁንም አሳዶጆቿና ገዳዮቿ የነበሩት ቄሣሮች እነ ኔሮን፣ እነ ድምጥያኖስ፣ እነ ትራጃን፣ እነ ዳክዮስ፣ እነ ቫሌንቲኖስ፣ እነ ጋሌሪዮስ፣ እነ መክስምያኖስ፣ እነ ድዮቅልጥያኖስ፣ እነ ሉቅያኖስና መሰሎቻቸው ሞተው የት እንደ ወደቁ መቃብራቸው እንኳ የማይታወቅ ሲሆን እነርሱ የገደሏቸውና ያሰቃዩዋቸው ክርስቲያኖች ግን ስማቸው በዓለም ይታወቃል፣ መቃብራቸውንና ዐጽማቸው ያረፉባቸውን ቤተ ክርስቲያኖች ምእመናን በታላቅ ክብርና ፍቅር ይሰለሟቸዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ያልተጠቀሱትን ገዳዮቻቸውን ግን በመልካም እንኳ የሚያነሳቸው የለም፣ በግፍ የሞቱትን ቅዱሳን ክርስቲያኖች ግን የክርስቲያኑ ዓለም ብቻ ሳይሆን ቅን ሕሊና ያለው ሰው ሁሉ የሚያከብራቸው ናቸው፡፡

ክርስትና በዓለም የተስፋፋው በአፍና በመጽሐፍ በሚደረገው ስብከት ብቻ አልነበረም፤ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ዓይናቸው እያየ ሞትን ሲንቁትና ፊት ለፊት ሲጋፈጡት በማየትም ነበር እንጂ፡፡ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ሰውነታቸው ሕማምና መከራ የሚሰማውና ስቃይን የማይወድ፣ ለአካላቸው መለዋወጫ፣ ለሕይወታቸውም ምትክ የሌላቸው ሲሆን እንዲህ ሞትን የሚንቁትና ደስ እያላቸው የሚሞቱት በትምህርታቸው እንደሚሉት አምላካቸው በእውነት ሞትን በትንሣኤው ድል ያደረገው በመሆኑና ከዚህ ዓለም ሕይወት በኋላ እርግጠኛ የሆነ ሌላ ሕይወት ቢኖር ነው እያሉ አሕዛብ ከክርስቲያኖች የምስክርነት ዐውድ ሕያው ወንጌልን ይማሩ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሣ ክርስቲያኖቹን እንዲገድሉ ከተመደቡት ወታደሮች መካከል እንኳ ሳይቀር በክርስቲያኖች ጽናትና በስቃያቸው ጊዜ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ከሚሠራቸው የተለያዩ ገቢረ ተአምራት የተነሣ እኔም በእነዚህ ሰዎች አምላክ አምኛለሁ እያሉ በደማቸው እየተጠመቁ ሰማዕታት የሆኑ ብዙዎች አሉ፡፡

ለአብነትም በአርብኣ ሐራ ሰማዕታት የተፈጸመውን ብቻ እናስታውስ፡፡ የሮማ የምሥራቁ ክፍለ ግዛት ገዢ በነበረው በሉቅያኖስ ባለ ሥልጣናት ለጣዖታት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሲታዘዙ እምቢ በማለታቸው በከተማው ውስጥ በነበረ አንድ በረዷማ የውኃ ኩሬ ላይ የጣሏቸው አርባ ክርስቲያን ወታደሮች ነበሩ፡፡ ከዚያ ከተጣሉበት በረዷማ ኩሬ ፊት ለፊት ደግሞ ለመታጠቢያነት ተስማሚና ምቹ የሆነ የፍል ውኃ መታጠቢያ ነበር፡፡ ከአርባው መካከል አንደኛው ከቅዝቃዜው ጽናት የተነሣ አውጡኝ አለና ወዲያውኑ እየሮጠ በሙቅ ውኃው መታጠቢያ ለመታጠብ ሄደ፡፡ ወዲያውኑ እንደ ገባም ሰውነቱ ብስክስክ ብሎ ሞተ፡፡ የእነዚያን ተጋዳይ ወታደሮች ሥቃያቸውን ሲከታተሉ ከነበሩት አስፈጻሚ ወታደሮች መካከል አንደኛው ራሱን በፍል ውኃው እያሞቀ ይህን እንግዳ ነገር እየተመለከተ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም መላእክት ከሰማያት ወርደው ለአርባው ተጋዳዮች አክሊል ሲያቀዳጇቸው የአንደኛው አክሊል ግን ተንጠልጥሎ በአየር ላይ ሲቀር ተመለከተ፡፡ ያን ጊዜ ያ ወታደር በወጣው ሰው ቦታ ገብቶ በክርስቶስ ታምኖ ወዲያውኑ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ፡፡ (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ስለ አርብኣ ሐራ ሰማዕታት፣ ትምህርት፣ ትምህርት 19)

በተለይም ደግሞ በጣም ብዙ ክርስቲያኖችን በመግደልና በማሰቃየት ወደር ያልነበረውን አርያኖስ የተባለውን የግብጽ ገዢ ፍጻሜ ማስታወሱ ለዚህ ሕያው ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አርያኖስ በሮማ ግዛት ውስጥ ክርስቲያኖችን በማሰቃየትና በእነርሱ ላይ ይፈጽም በነበረው በጭካኔው ወደር የለሽ ነበር፡፡ አንድ ቀንም የእርሱ አጫዋች (አዝማሪ) የነበረው ፈልሞን በፊቱ ቆሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ክርስቲያን መሆኑ መሰከረ፡፡ ያን ጊዜ አርያኖስ ፊልሞንን እና አብላዮስ የተባለውን ጓደኛውን በፍላጻ እንዲነድፏቸው አዘዘ፡፡ አንዲት ፍላጻም ወደ አርያኖስ ተመልሳ ዓይኑን አወጣችው፣ የፍላጻው ሕማምም እጅግ አሠቃየው፡፡ በጣም እየተሠቃየ ሳለ ከክርስቲያኖቹ አንዱ ከሰማዕታቱ ደም ወስደህ ብትቀባው ትድን ነበር አለው፡፡ እርሱም ይህን ያህል እየጠላኋቸውና እያሰቃየኋቸው ይምሩኛልን? ቢላቸው አዎ፣ በክርስትና ጠላትን መውደድና ለጠላት መጸለይ እንጂ መበቀል የለም አሉት፡፡ እንደ ነገሩት ከሰማዕታቱ ደም ወስዶ ቁስሉን ሲቀባው ወዲያውኑ ተፈወሰ፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱም በክርስቲያኖች አምላክ አምኖ ጣዖታቱን ሰባብሮ ክርስቲያኖችን ምሕረት የሌለው ሥቃይ ስላሠቃያቸው ታላቅ ጸጸት ተጸጸተ፡፡ ከዚያም ስለ ክርስቶስ መስክሮ በሌላ ገዢ ተገድሎ ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ (ስንክሳር መጋት 7 እና 8)

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ሞትን ድል ማድረጉና የሞትን ኃይልና አስፈሪነት ማጥፋቱ ለሰዎች ከተገለጠበትና ለዓለምም ከሚገለጥበት አንደኛው መንገድ ይህ የክርስቶስ አካላትና ተከታዮች (ክርስቲያኖች) መከራንና ሞትን በጽናት መቀበላቸው፣ ሞትን መናቃቸውና ፊት ለፊት መጋፈጣቸው ነው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑ ወይም ስለሚመጣው ሕይወት በሃይማኖታቸው ቁርጠኛ ያልሆኑ ሰዎች እንደ ጦር የሚፈሩትን ሞት፣ እንዲሁም ሌት ተቀን የሚጨነቁለትን የዚህን ዓለም ሕይወት በክርስቶስ ትንሣኤ ያመኑ ክርስቲያን ሰማዕታት ሲንቁትና ፊት ለፊት ሳይፈሩ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ሲጋፈጡት ሲያዩ ብዙዎች ከሞት በላይና ባሻገር ስላለው ሕይወትና እውነት በሰማዕታት ጽናትና ብርታት አማካይነት ተምረዋል፡፡ ከአሕዛብ ወገን፣ ሰማዕታቱን ይገድሉና ያሠቃዩ ከነበሩት ከወታደሮችም ሳይቀር በዚሁ ተስበው ለሰማዕትነት የበቁት በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ክርስቶስ ሞትን ድል ባያደርገው ኖሮ ሰማዕታትም ሞትን መጋፈጥና መናቅ ባልቻሉ ነበር፡፡ የእነርሱ ተጋድሏቸው፣ መከራቸውና ድል አድራጊነታቸው የመስቀሉ ድል፣ የትንሣኤው ኃይል ቀጣይ አካልና ሕያው ምስክር ነው፡፡ የእነርሱ ጽናትና ተጋድሎ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደረገው መሆኑን በተግባር የሚመሰክሩ ምስክሮች ናቸው፤ ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፣ ስለዚህም ነፍሴ ፈለገቻቸው እንደ ተባለ፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት ሰማዕታት – ምስክሮች፣ መስካሪዎች የተባሉትም ለዚህ ነው፡፡ መዝ. 118፡129

ስለሆነም መከራ መስቀል ክርስትና የተመሠረተበት፣ ያደገበትና የኖረበት ሕይወት እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ክርስትናን የሚያዳክመው መከራ ሳይሆን ምንነቱን አለመረዳትና ቁሳውይነት፣ ቅምጥልነትና ሥጋውይነት ናቸው፡፡ ሰማዕትነትማ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሞትን ያህል ከባድ ነገር ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ሞትን ባሸነፈው በትንሣኤው ኃይል የናቁትንና ለብዙዎች ኢአማንያን በክርስቶስ ማመንና ሰማዕት እስከ መሆን መድረስ ምክንያት የሆኑ ብዙ መንፈሳዊ ጀግኖችን ያፈራችበት ነው፡፡ ለዚህ ነው በሁለተኛው መቶ ዓመት ማብቂያና በሦስተኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ የነበረው የክርስትና መብት ተሟጋቾችና ጠበቆች መካከል አንዱ የሆነው የሰሜን አፍሪካው የቅርጣግናው ሊቅ ጠርጠሉስ ስለ ክርስትና እምነት ንጹሕነትና እውነተኛነት ለአሳዳጆችና ለመከራ ዳራጊዎች በጻፈው የጥብቅና መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲል የገለጸው፡-

“አሠቃዩን፣ ግደሉን፣ ንቀፉን፣ ኰንኑን፣ አቃጥሉን፣፤ የእናንተ ክፋት፣ ግፍና ጭካኔ የእኛ ንጽሕና ማረጋገጫ ነው፡፡ እናንተ በወገራችሁንና በቆረጣችሁን መጠን ቁጥራችን እልፍ እየሆነ ይሄዳል፤ ደመ ሰማዕታት የክርስቲያኖች ዘር ነው፡፡ – Torture us, condemn us, crucify us, destroy us! Your wickedness is the proof of our innocence. . . . The more we are hewn down by you, the more numerous do we become. The blood of the martyrs is the seed of the Church. Apologeticus, Chapter 50)

አዎ፣ ምንም ያልበደሏቸውንና አንዳችም መከላከያ የሌላቸውን ወንድሞቻችንን በክርስትና ሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ በግፍ መግደላቸው ሁለት እውነታዎችን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ከእነዚህም አንደኛው እውነተኛ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅርና ጽናት፣ እንዲሁም እውነተኛነት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የገዳዮቹ እምነታቸው ከመሠረቱ ስህተትና ውሸት መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም እውነትን የያዘ ሰው ያ አምነዋለሁ የሚለውን እውነት በማስረዳት ማሳመን ይገባዋል እንጂ እውነትን በግድ መጫን አይቻልም፡፡ ስለሆነም ገዳዮቹ እምነታቸውና አስተሳሰባቸው ሌላውን ሰው ሊያሳምን የማይችል ደካማና ሐሰት ስለሆነ በኃይልና በመሣሪያ ኃይል ካልሀነ በስተቀር የሰውን አእምሮ ማሳመን የማይችል መሆኑን ራሳቸው ቀርጸው ያሠራጩት ምስልና ድምፅ ይመሰክርባቸዋል፡፡ በዚህም በአንድ በኩል እግዚአብሔርን አምነውና መስክረው የሞቱትን የወንድሞቻችንን አሟሟትና ማንነት እንድናውቅ ስላደረጉን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን የገዳዮቹን የእምነት አስተሳሰብ ባዶነትና ሐሰትነቱ ከጥንትም የታወቀ ቢሆንም አሁን ደግሞ ከራሳቸው ንግግርና ድርጊት እንዲጋለጥ ያደረገውን ምስል ወድምፅ በማሠራጨታቸው እናመሰግናቸዋለን፡፡ እንደ ገደሏቸው ሳይነግሩን የሆነ ቦታ ጥለዋቸው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዓለም ይህን ሁሉ ትምህርት ከየት ያገኝ ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዓመት ማብቂያ ገደማ በተፈጸመው የክርስቲያኖች ጭፍጨፋ ስለ ክርስቶስ መስክረው የሞቱ ቅዱሳን ሰማዕታት ነፍሳቸው እንዲህ ብላ ወደ እግዚአብሔር ፍትሕን ጠይቃ ነበር፡- “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፡- ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ።” በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸው መልስ “እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው” የሚል ነበር። ራእ. 6፡9-11 እስከዚያው ድረስ ግን “ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፡፡”

እግዚአብሔር ክርስቲያኖችን በግፍ በገደሏቸው ላይ ፍርድን በቶሎ ያልሰጠበት ዋና ምክንያት እንደ እነዚያ ያሉና ስለ ክርስቶስ መስክረው የሚሞቱ በየዘመኑ የሚነሡ ሰማዕታት መኖራቸውን እርሱ በአምላክነቱ ስለሚያውቅ ይህ የሰማዕትነት ዕድል እንዳይቀርባቸው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ለክርስቶስ እየመሠከሩ የሚሞቱ አሉና እርሱ የሚያውቃቸው እነዚያ ሰዎች ለዚህ ክብር ሳይበቁ እንዳይቀሩ የፍርድ ጊዜውን እርሱ ባወቀ አቆይቶታል፡፡ ግፍ ፈጻሚዎችን ቀድሞ በአንደኛው መቶ ዓመት ላይ አጥፍቷቸው ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ወደፊትም እንዲሁ እርሱ የሚያውቃቸው ሰማዕታት ይህን የሰማዕትነት አክሊል አያገኙም ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን የመሰሉ ጌጦቿን አታገኝም ነበር፡፡ ሰማዕታት የቤተ ክርስቲያን ጌጦች ናቸውና፤ በከመ ከዋክብት ያሠረግውዎ ለሰማይ በሥኖሙ ከማሁ ሰማዕትኒ ያሠረግውዋ ለቤተ ክርስቲያን በገድሎሙ – ከዋክብት ሰማይን በውበታቸው እንደሚያስውቡት ሰማዕታትም በገድላቸው ቤተ ክርስቲያንን ያስጌጧታል እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡ (ጾመ ድጓ ዘቴዎቅሪጦስ)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነትን መቀበል ሕይወቷ ነው፡፡ በዮዲት ጉዲት ዘመን፣ በግራኝ አህመድ ዘመን፣ በሱስንዮስ ዘመን ቁጥራቸውን እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው ብዙ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት መስክረው ዐርፈዋል፡፡ በሙሶለኒ ፋሽስት ወረራ ዘመንም እንዲሁ የደብረ ሊባኖስ፣ የዝቋላ፣ የማኅበረ ሥላሴ፣ እንዲሁም የሌሎች የብዙ ገዳማት መነኰሳትና ባሕታውያን ስለ ሃይማኖታቸው በግፍ ተጨፍጨው በሰማዕትነት ሞተዋል፡፡ ገዳማቱ ግን አሁንም አሉ፣ መነኰሳትና ባሕታውያንም፣ ምአመናንም እንዲሁ አሉ፡፡ ክፉ ያደረጉት ተጎዱ እንጂ ክፉው የደረሰባቸውን አልጎዷቸውም፡፡ እውነተኛ ጉዳት ማለት በጊዜው ጊዜ አይቀር የነበረውን የሥጋ ሞት በሰው እጅ መቀበል ሳይሆን መልካም ሊሠሩበት በተሰጣቸው ጊዜና አእምሮ በሰዎች ላይ ግፍና ጭካኔ ፈጽሞ ከእግዚአብሔር መለየትና ሊቀር ይችል የነበረውን ሞተ ነፍስ በፈቃድ በራስ ላይ ማምጣት ነውና፡፡

ስለሆነም እንዲህ ለሚያደርጉ ክፉዎች ሰዎች ልናዝንላቸውና ልንጸልይላቸው ይገባል፡፡ ጌታችን እንዲህ ብሎ አስተምሮናልና፡

ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዷችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።ማቴ. 5፡43-48

አዎ፣ ክርስትና የሚጠሉንን የምንጠላበትና ክፉ ያደረጉብንን በዚያው በክፋት መንገድ አጸፋ የምንመልስበት ሳይሆን ስለ ክፉ አድራጊዎቹ ጥፋት ከልብ የምናዝንበትና የጥፋታቸውን ምንነት ተረድተው ወደ አእምሯቸው ይመለሱ ዘንድ እግዚአብሔርን የምንለምንበት ሕይወት ነው፡፡ ክርስትና ድንጋይ ለወረወረብን መልሰን የምንወረውርበት፣ ጉድጓድ በማሰብን ላይ ሌላ ጉድጓድ የምንቆፍርበት አይደለም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰቀሉትና ያ አልበቃቸው ብሎ ተጠማሁ ባለ ጊዜ እንኳ መራራ ሐሞትን በአፉ ላደረጉለት ለክፉዎች አይሁድ እንኳ አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁም ይቅር በላቸው ብሎ እንደ ጸለየላቸው እኛም ለክፉ አድራጊዎችና ለጠላቶቻችን የምንጸልይበት ሕይወት ነው፡፡ አለዘበለዚያ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ልንሆን አንችልም፡፡ ክፉዎች ክፉ በመሆናቸው በእነርሱ ክፋት ተገፋፍቶ ወይም እልክ ውስጥ ገብቶ እነርሱ በሄዱበት የክፋት መንገድ መሄድ ገና ከጅምሩ መሸነፍና ድል መነሣት ነውና፡፡ ምክንያቱም የክፉ ሰው ድርጊቱና ዓላማው ሌላውንም እንደ እርሱ ክፉ ማድረግና ወደ እርሱ የክፋት አስተሳሰብና ድርጊት እንዲሳብ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ አስተሳሰብና ድርጊት እንደ ክፉዎቹ ሰዎች አስተሳሰብና ድርጊት ከሆነ ብርሃን ወደ ጨለማ፣ ጨው ወደ አልጫ ተለወጠ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገና ሲጀመር መሸነፍ ነው፤ ክፉው መልካሙን አጠፋው ማለት ነውና፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ መጽሐፍ ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፉሲል በአጽንዖት የሚያስጠነቅቀን፡፡ ሮሜ 12፡21 በክፉ መሸነፍ ማለት ወደ ክፋ መሳብና ክፉዎቹ እንደሚያደርጉት ለማድረግ መነሣት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ ካለ በኋላ ቀጥሎ በክፉ አትሸነፉ አለ እንጂ “በክፉ አታሸንፉ” አላለም፡፡ ምክንያቱም ክፉን በመልካም ብቻ እንጂ በክፉ
ማሸነፍ አይቻልምና፡፡ ክፉ መሆን ከጀመረ ግን በክፉ ተሸንፏል ማለት ነው፡፡ ሰው በክፉዎች ምክንያት እርሱም የሚከፋ ከሆነ ከጅምሩ ተሸንፏል ማለት ነውና፡፡ ፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ የድንጋይ ናዳ ሲያወርዱበት ለነበሩት አይሁድ ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ ጸለየላቸው እንጂ አጥፋቸው አላለም፡፡ ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስም ጸሎት እንዲሁ በከንቱ አልቀረም፡፡ እርሱን ሲወግሩ የነበሩትን ሰዎች ሲያስተባብርና ልብሳቸውን ሲጠብቅ የነበረው ሳውል የተባለው ኃይለኛ ጸረ ክርስቲያን ወጣት (የኋላው ቅዱስ ጳውሎስ) የእግዚአብሔር ቸርነት ልቡን እንዲነካውና ወደ ክርስትና እንዲመለስ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህንንም አንድ ሊቅ የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ለቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስን አስገኘላት ብሏል፡፡ በየዘመናቱ የነበሩ ክርስቲያኖች ሁሉ መከራ በሚያደርሱባቸው ላይ እንዲሁ ስህተታቸውን የሚገነዘብ ልቡና እንዲሰጣቸውና ወደ እውነት እንዲመለሱ ጸለዩላቸው እንጂ በክፉው መንገድ እንበቀላቸው ብለው አልተነሡም፡፡ በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ታላላቅ የቤተ መንግሥት ተወላጆችና መኳንንት ከነበሩት ወገን ሰማዕትነትን የተቀበሉት እነ ቅዱስ ቴዎድሮስ፣ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ ቅዱስ ዮስጦስ፣ ቅዱስ አቦሊ፣ ቅዱስ ፊቅጦር . . . በጦር ሜዳ ጀግንነታቸውና አርበኝነታቸው የታወቁ ኃያላን ነበሩ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቲያኖችን ማሰቃየት ሲጀምር በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር ትጥቃቸውን መፍታትና ስለ ክርስቶስ መክራ ለመቀበል በመዘጋጀት ወደ ፊቱ ቀርበው ሃይማኖታቸውን መመስከር ነበር፡፡ የእነርሱ ታማኝ ሠራዊትና ወዳጆች ከነበሩት ብዙዎች ስለ እነርሱ በመቆጨትና በመቆርቆር ዲዮቅልጥያኖስን ወግተን እናጥፋውና እናንተ ግዙን ሲሏቸው አልተቀበሏቸውም፡፡ እነዚህ ሰማዕታት መጀመሪያ ያደረጉት ነገር በዘመኑ የነበራቸውን አርበኝነት፣ ኃያልነት፣ የወገንና የሠራዊት ድጋፍ ሁሉ ትተው ስለ ክርስቶስ መስክሮ ለመሞት ብቻቸውን መቅረብ ነበር፡፡ ክርስትና በሠይፍ የተመሠረተና ለመስፋፋትም ሠይፍ የሚያስፈል
ገው አይደለምና፡፡ ሠይፍን የሚያነሱማ እነርሱው ራሳቸው በሠይፍ እንደሚጠፉ ባለቤቱ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ ማቴ. 26፡52 ታሪክም ይህንኑ እውነታ ያስተምረናል፡፡

ክርስትና በዚህ ዓለም የድሎትና የቅንጦት ኑሮ የሚመኙበትና የሚኖሩበት ሳይሆን ክርስቶስ በዚህ ዓለም የመስቀል ሞት ስለ እኛ በፈቃዱ እንደ ተቀበለና እንደ ተነሣ ክርስቲያኖችም በዚህ ዓለም የሚደርስባቸውን መከራ በትዕግሥት በጥብዐት በመቀበል በትንሣኤው ኃይል ድል የሚያደርጉበት ነው፡፡ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት ተብሏልና፡፡ 1 ጢሞ. 5፡6

እነዚህን ወንድሞቻችንን ወደ እግዚአብሔር ፈጥነው እንዲሄዱ አደረጓቸው እንጂ አልጎዷቸውም፡፡ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለዩዋት እንጂ አልገደሏትም፤ ነፍስን ለመግደል ማንም አይችልምና፡፡ ይህ የሥጋና የነፍስ መለያየት (ሞተ ሥጋ) ደግሞ በሕማምም ሆነ በዕድሜ ብዛት መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ከዚያ ቀድመው ለክርስቶስ መስክረው ወደ አምላካቸውና መድኃኒታቸው እንዲሄዱ አደረጓቸው እንጂ አንዳችም አልጎዷቸውም፡፡ ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታበል ቃሉ እንዲህ ብሏልና፡- ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም። ዮሐ. 11፡25-26 ለክርስቶስ መስክሮ መሞት ደግሞ ለአንድ ክርስቲያን እጅግ ታላቅ ጸጋና መታደል ነው፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ተብሏልና፡፡ ማቴ. 10፡32

ቅድስናን (ሰማዕትነትን) እውቅና መስጠትን በተመለከተ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን የሆኑትን ቅዱሳን ናቸው ስትል ቅድስናቸውን እውቅና የመስጠት ጉዳይ እንጂ ቅዱሳን የማድረግ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህም ማለት እነዚያን ሰዎች ቅዱሳን የሚያደርጋቸው እግዚአብሔር ባሳየው የሕይወት መንገድ መጓዛቸውና እርሱን ደስ ያሰኙ መሆናቸው እንጂ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ናቸው ብላ በምትሰጠው ውሳኔ አይደለም ማለት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅድስናቸውን የማወቅ ውሳኔ የሚመጣው ከሰዎቹ ቅድስና እንጂ የሰዎቹ ቅድስና ከቤተ ክርስቲያን ውሳኔ የሚመጣ አይደለም ለማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያውቃቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት የሆኑ ቅዱሳን ሁሉ በዚህ ዓለም ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሁሉንም ሊያውቃቸው መቸም መች አይችልም፡፡ ምክንያቱም በየበረሓው ወድቀው ከእኩያት ፍትወታትና ከክፉ መናፍስት ጋር ተጋድለው እግዚአብሔርን አገልግለው ያለፉና እንኳን ቅድስናቸው መኖራቸው እንኳ ከእግዚአብሔር በቀር በሰዎች ያልታወቀ ብዙ ቅዱሳን ነበሩና፣ ዛሬም ይኖራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወበኀቤዬሰ ፈድፋደ ክቡራን አዕርክቲከ እግዚኦ ወፈድፋደ ጸንዑ እምቀደምቶሙ እኄልቆሙ እምኆጻ ይበዝኁ – አቤቱ ወዳጆችህ በእኔ ዘንድ እጅግ ብዙዎች ናቸው፣ ብቆጥራቸውም ከአሸዋ ይልቅ በዙ የሚለው ለዚህ ነው፡፡ መዝ. 138፡17-18

እንደዚሁም በዚህ ዓለም ሲኖሩ ኃጢአተኞች መስለው፣ እብድ መስለው፣ የውሻ አስከሬን እስከ መጎተትና አመንዝራ እስከ መምሰል ደርሰው፣ ሰው እንኳን ቅድስናቸውን ሊያውቀው ይቅርና ጥሩ ሰዎች እንኳ አድርጐ የማይመለከታቸው ብዙ ቅዱሳን እንደ ነበሩ ዜና አበውና መጽሐፈ ገነት፣ እንዲሁም ስንክሳርና የተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ድርሳናት ይነግሩናል፡፡ ከሰማዕታት መካከልም ታላላቅ ተጋድሎ የተጋደሉና ብዙ ዓይነት ጸዋትወ መከራ የተቀበሉ፣ ብዙ ጊዜ ሞተው የተነሡና እግዚአብሔር ብዙ ተአምራት ያደረገላቸው ብዙ ሰማዕታት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚታወቁት ግን በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ሆኖም በሰዎች ዘንድ አለመታወቃቸው በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን ክብራቸውን በእኛ ዘንድ ከታወቁት ሰማዕታት ያነሰ አያደርገውም፤ የክብራቸው መሠረት በእኛ ዘንድ መታወቅ አለመታወቃቸው፣ በዓል ያላቸውና የሚታሰቡ መሆን አለመሆናቸው አይደለምና፡፡ ይህን በተመለከተ አንድ ሊቅ ሲያስረዳ በሰማይ ባሉ ከዋክብት መስሎ አስረድቷል፡፡ በሰማይ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑና ቁጥራቸው ይህን ያህል ተብሎ የማይታወቁ ከዋክብት አሉ፡፡ ለእኛ የሚያበሩልንና መኖራቸውን የምናውቃቸው ካሉት ከዋክብት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ እንደ ሆኑ ከቅዱሳንም እኛ የምናውቃቸው ለአርአያና ለትምህርት ይሆኑን ዘንድ በጣም ጥቂቶቹን ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ከመራቃቸው የተነሣ ለእኛ በጣም ጥቃቅን መስለው የሚታዩንና ከነመኖራቸው የማናውቃቸው ትሪሊዮን ጊዜ ትሪሊዮንና ከዚም በላይ በቁጥር ሊገለጽ የማይቻል የሆኑ ከዋክብት እንዳሉ ሁሉ በቅዱሳንም እንዲሁ ነው፡፡ ለእኛ የሚታዩትና የምናውቃቸውም ሆኑ የማይታዩት የማናውቃቸው ከዋክብት የጋራ መገለጫቸው በሰማይ ያሉ ሰማያውያን መሆናቸው እንደ ሆነ ሁሉ የቅዱሳን የጋራ መገለጫቸው ሁሉም ሰማያውያንና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ መሆናቸው ነው፡፡

በእግዚአብሔር ቸርነት የሚገኝ ቅድስና ከሚገኝበት መንገድ አንዱ ሰማዕትነት ነው፡፡ ሰማዕታትም የሰማዕትነት አክሊል የሚቀዳጁት ሰማዕታት ናቸው ተብሎ ሲወሰንላቸው ወይም ዐዋጅ ሲታወጅላቸው ሳይሆን ለአምላካቸው ያላቸውን ጽኑ ፍቅርና ታማኝነት መከራውንና ሞቱን ሳይፈሩ ምስክርነታቸውን በሰጡና ከዚያም የሞትን ጽዋ በጽናት በተቀበሉ ጊዜ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመዋቅሯ ሰማዕት ብላ እውቅና የምትሰጠው ከእነርሱ ከበረከታቸው ለመሳተፍና ለምስክርነታቸው ዕውቅና ለመስጠትና ለማክበር ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ለሰማዕትነታቸው ዕውቅና የመስጠት አለመስጠቱ ጉዳይ እነርሱ በሚያገኙት ጸጋና በሚሆኑት ላይ አንዳችም ለውጥ የማያመጣ ስለሆነ ብዙም የሚያጣድፍ ጉዳይ አለመሆኑንና ረጋ ብሎ አስተውሎ ቢደረግ የሚያመልጥ ነገር አለመኖሩን ተገንዝቦ በተረጋጋ መንፈስ ማድረጉ መልካም ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ከእነዚህ ሰማዕታት የሚከተሉት ነገሮች እንማራለን፡-

1.ክርስትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን አንሥቶ በየዘመናቱ ዓይነቱና ስፋቱ ይለያይ እንጂ ጉዞው በመስቀል ላይ ማለትም በመከራ ላይ መሆኑን፣

2.ክርስትናን ከምድረ ገጽ ለማጥፋትና በዓለም ላይ የአረመኔ ሥርዓት ለመመሥረት አይ ኤስ እና መሰሎቹ የተለያዩ ቡድኖች ክርስቲያኖቹን በመግደልና አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን በማቃጠልና በማፍረስ ላይ መሆናቸውን፣

3.ይህ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየሆነ ያለው አደጋ ችላ ሊባል የሚገባው ሳይሆን እያንዳንዱ ክርስቲያን በንቃት ሊከታተለው የሚገባ መሆኑንና ሕሊናዊና መንፈሳዊ ዝግጅት፣ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ የልብ ጸሎት የሚያስፈልግ መሆኑን፣ እና

4.በመጨረሻም እነዚህ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ለክርስቶስ ታምነው ሞትን በጽናት መቀበላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁላችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ጽኑ ፍቅር አጽንተን በመከራም እንኳ ቢሆን ጸንተን እንድንቆም የሚያስተምር ሕያው ወንጌል መሆኑን ነው፡፡ እነርሱ በሠይፍ ለመታረድና በጥይት ተደብድበው እስከሚገደሉ ድረስ ለሃይማኖታቸው ከጸኑ እኛ ከዚያ ደረጃ ባልደረሱ ተራና ጥቃቅን ሰበቦችና ምክንያቶች ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳንክድና በእርሱ ካለን ሕይወት እንዳንለይ፣ በክርስቶስ ያለንን እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊና ሐዋርያዊ እምነት እስ መጨረሻው አጽንተን እንድንጠብቅ የወንድሞቻችን ደም ሕያው ሆኖ ከፊታችን እየጮኸ ያስተምረናል፡፡

እኛም እንደ ወንድሞቻችን መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ ሕማምኑ ምንዳቤኑ ተሰዶኑ ረሐብኑ ዕርቃንኑ መጥባሕትኑ ጻዕርኑ -ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ልንልና በዚህ ሕይወት ልንኖር ይገባናል፡፡ ሮሜ 8፡35

እግዚአብሔር አምላክ ከእርሱ አንድነትና የአባትነት ፍቅር ከሚለይ ነገር ሁሉ ይጠብቀን፣

እኛንም ፈቃዱ ቢሆን እንደ ወንድሞቻችን በጽናት እንድንቆምና ለአክሊለ ሰማዕት እንድንበቃ ያድርሰን፣ አሜን፡፡