hawi 01

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን

 ታኅሣሥ 9 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ሪፖርታዥ፡-

hawi 01ማኅበረ ቅዱሳን ለአምስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደብረ ዘይት ከተማ ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ከ6000 በላይ ምእመናን በተገኙበት በድምቀት አካሔደ፡፡

ከዋዜማው ጀምሮ መርሐ ግብሩን የተሳካ ለማድረግ የማኅበሩ ሐዊረ ሕይወት አዘጋጅ ኮሚቴ በሚመድበው መሠረት የየክፍሉ አገልጋዮች በአገልግሎት ተጠምደዋል፡፡ መርሐ ግብሩን የተሳካ ለማድረግ ሁሉም ይጣደፋል፤ የጎደለውን ይሞላል. . . ፡፡

ከሌሊቱ 12፡00 ጀምሮ አምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ከሚገኘው ከማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ጀምሮ በተለምዶ ሰባ ደረጃ እስከሚባለው ሠፈር ድረስ ሰባ 1ኛ ደረጃ የሚሆኑ የከፍተኛ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች መስመራቸውን ይዘው ተሰልፈው የምእመናንን መምጣት ይጠባበቃሉ፡፡

ከሌሊቱ12፡30 ጀምሮ ምእመናን በማኅበሩ በተወከሉ አስተባባሪዎች አማካይነት መለያ ባጅ እየተረከቡ በተዘጋጀላቸው መኪና ውስጥ በመግባት ጉዞው ተጀመረ፡፡

የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አባላት ሌሊቱን ለኢንተርኔት የቀጥታ ሥርጭት ቅድመ ዝግጅት ስናደርግ አድረን በተዘጋጀልን መኪና ወደ ደብረ ዘይት አመራን፡፡

hawi 02 2በደብረ ዘይት ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርሰቲያን ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ስንደርስ የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራን አውራ ጎዳናው ላይ ወጥተው በዝማሬ ተቀበሉን፡፡ ነጫጭ የሀገር ባሕል አልባሳት የለበሱ የማኅበረ ቅዱሳን ደብረ ዘይት ማእከል አባላት፤ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላትና ትራፊክ ፖሊሶች በሰልፍ ምእመናንን ይዘው እየመጡ ያሉትን ከፍተኛ አገር አቋራጭ አውቶቡሶችን ቦታ ለማስያዝ ይረባረባሉ፡፡ የደብረ ዘይት የጸሐይ ግለት ለደመናና ነፋሻማ አየር እጇን ሰጥታለች፡፡ የአካባቢው ምእመና ነጫጭ የሀገር ባሕል ልብስና ነጠላ ለብሰው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ይጓዛሉ፡፡ ደብረ ዘይት በጠዋቱ ደምቃለች፡፡

ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ የእለተ ሰንበት ቅዳሴው በመገባደድ ላይ ነበር፡፡ አስቀዳሽ ምእመናንን ላለመረበሽ አንድ ጥግ ይዘን ከተሳለምን በኋላ እቃዎቻችንን ይዘን ወደ ድንኳኑ በመገባት ለቀጥታ ሥርጭት አመቺ ቦታ ነው ባልነው ሥፍ ላይ ሆነን የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎቻችንን አስተካክለን የመርሐ ግብሩን መጀመር መጠባበቅ ጀመርን፡፡

ምእመናን ከመኪናቸው እየወረዱ በአስተባባሪዎች እየታገዙ በተዘጋጀው ድንኳን ውስጥ ቦታቸውን በመያዝ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የደብረ ዘይት ከተማ ምእመናን ጨምሮ ከስድስት ሺሕ ምእመናን በላይ ግቢውን ሞሉት፡፡ ሁሉም ፊት ላይ የደስታ ስሜት ይነበባል፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን ለመወያየት፤ ቃለ እግዚአብሔር ለመስማት የመጓጓት ስሜት፡፡

ከጠዋቱ 2፡50 ሲሆን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በጎንደር መንበረ መንግስት መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህርና የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ፤ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን የሊቃውንት ጉባኤ አባል፤ የኔታ ሐረገ ወይን የዝዋይ ሐመረ ኖህ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አበምኔት፤ መጋቤ ሐዲስ ደጉ ዓለም ካሳ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር፤ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ የቅዱስ ጳውሎስ መንሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህርና፤ ሌሎችም አባቶች ወደ ሥፍራው ደረሱ፡፡

ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በደብሩ ካህናት መርሐ ግብሩ በፀሎተ ወንጌል ተጀመረ፡፡

የእለቱ ምስባክ “ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር ምክር ሰናይት ለኵሉ ዘይገብራ ወስብሐቲሁኒ ይነብር ለዓለም፤ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ለሚያደርጓትም ሁሉ ምክር በጎ ናት፤ ምስጋናውም ለዘለዓለም ይኖራል” መዝ.110፡10

ጸሎተ ወንጌሉ እንደተጠናቀቀ የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙር በማቅረብ መርሐ ግብሩ ቀጥሎ በቀሲስ ፋሲል ታደሰ የመጀመሪያውን ክፍል የወንጌል ትምህርት “የእግዚአብሔር መልስ” በሚል ርዕስ ተሰጠ፡፡hawi 02

በትምህርታቸውም “እግዚአብሔር ለጠየቅነው ነገር ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ያከናውንልናል፡፡ እግዚአብሔር ዝም የሚልበት ጊዜ አለው፤ መልስ የሚሰጥበትም ጊዜ አለው፡፡ . . . ከእኛ ሁለት ነገሮች ይጠበቃሉ፡፡ በእምነት ሆነን መጸለይና በትዕግስት እግዚአብሔርን መጠበቅ፡፡” በማለት ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ከትምህርቱ በኋላ ከተመሠረተ ሃያ ዓመታትን ያስቆጠረውና ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አንቀጸ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት የጎልማሶች ክፍል፤ እንዲሁም ዘማሪ ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ መዝሙር አቅርበዋል፡፡

ክፍል ሁለት የወንጌል ትምህርትን በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በጎንደር መንበረ መንግስት መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህር “አነ ውእቱ ሕብስተ ሕይወት፤ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ዮሐ. 6፡32 በሚል ርዕስ አስተምረዋል፡፡

“ጌታችንን ይከተለው ከነበረው አምስት የገበያ ሕዝብ መሐል አንዳንዶቹ ሥጋዊ ምግብን ፍለጋ፣ አንዳንዶቹ ከደዌቸው ለመፈወስ፣ አንዳንዶቹ ትምህርቱን ለመስማት፣አንዳንዶቹ መልኩን ለማየት ሌሎቹ ደግሞ የኦሪትን ሕፀፅ፤ የወንጌልን መብለጥ ሰምተው ይነቅፉት ዘንድ ይከተሉት ነበር፡፡ ለእነዚህ ሁሉ እንደተነገረላቸው ትንቢት ለሁሉም የሚሹትን ይሰጣቸው ነበር፡፡ . . . ልጆቼ ምን ያህል እንጀራ አላችሁ? አላቸው ደቀመዛሙርቱን፡፡ እነሱም አምስት እንጀራ እና ሁለት አሳዎች ብቻ ነው ያለን፡፡ ነገር ግን ይህ ለአምስት ሺሀ ሕዝብ ምን ይበቃልን? አሉት እሱም አንስቶ አመሰገነ አበርክቶም ለሕዝቡ ሰጣቸው፡፡ በሉ ጠገቡም፡፡

… አስራ ሁለት መሶብ ትራፊም አነሱ፡፡ ይህም ሴቶች እና ሕፃናት ሳይቆጠሩ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ሲቶች በወንዶች ፊት ስለሚያፍሩ ብዙ በደንብ አንስተው አይበሉም፤ ሕፃናትም ከሚበሉት የሚፈረፍሩት ስለሚበዛ ነው፡፡ … ምስጢሩን ስንመለከት ምግቡን በምሽት ያበረከተበት ምክንያት ጠዋት ቢሆን ሁሉም ቁርሱን በልቶ ስለጠገበ ብዙ ተርፎ ተነሳ እንዳይሉ፣ ሁለተኛው በለምለም ስፍራ ላይ ያስቀመጣቸው ምክንያቱ ልብሳችን እንዳይቆሽሽ ተደላድለን ስላልተቀመጥን ብዙ ስላልበላን ተርፎ ተነሳ እንዳይሉ፣ ሦስተኛው በከተማ ሳይሆን በምድረባዳ ምንም በሌለበት ማድረጉ ምግቡ ሲያንስ ደቀመዛሙርቱ ከከተማ እየገዙ እንጂ አበርክቶት አይደለም እንዳይሉ፣ አራተኛው በጥብርያዶስ ወንዝ አጠገብ ያስቀመጠበት ምክንያት እጃችንን ሳንታጠብ ስለበላን እንጂ ብዙ ተርፎ አይነሳም እንዳይሉ፤ በመጨረሻም እስከ ዛሬ ይከተሉት የነበረው ለመብል መሆኑን ስለተረዳ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” አላቸው፡፡ ከጧት እሰከ ማታ ሳይበሉ መቆየታቸው ጾመው ጸልየው መንግሥቱን ያገኙ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋዬ አውነተኛ የሕይወት መብል፤ ደሜም እውነተኛ የሕይወት መጠጥ ነው፡፡ ሥጋዬን ያልበላ፤ ደሜንም ያልጠጣ የዘላለም ሕይወት የለውም ሲላቸው በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ አሠረው” በማለት አስተምረዋል፡፡

ከትምህርት ወንጌሉ በመቀጠል ዘማሪ ዲ/ን እንግዳ ወርቅ በቀለ፤ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን መዝሙር በማቅረብ ቀጥሎ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰባሳቢ አቶ አምሳሉ ደጀኔ የደብረ መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክና እየተከናወኑ ስለሚገኙ የልማት ሥራዎች ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

hawi 05አቶ አምሳሉ ባቀረቡት ሪፖርትም አካባቢው የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ “በአጥቢያው ከአሥር ሺሕ በላይ ምእመናን የሚገኙበት ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ አምልኮተ እግዚአብሔር ለመፈጸም ባለመቻላችን ምእመናኑን ፊርማ በማሰባሰብ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመሆን ለማስፈጸም ችለናል፡፡ በዚህም መሠረት የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የመሠርት ድንጋይ ተቀምጦ በሦስት ወራት ውስጥ ተሠርቶ ተጠናቋል፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያኑ ጠባብ በመሆኑ ወደፊት በተሻለ ሁኔታ ለመሥራት የታሰበ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመክፈት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን” በማለት ሪፖርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

የከስዓት በፊቱ መርሐ ግብር በማጠናቀቅ የምሳ መርሐ ግብሩ ቀጥሏል፡፡

ከምሳ መልስ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ወረብ ” ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናቲነ አስተጋብአነ ሀበ ትረፍቅ መካነ፤ እስመ ዝርዋን አግብርቲከ ንህነ፤ በኃጢዓት የተበተን እኛን ሊቀ ካህናችን ክርስቶስ በፍቅር ሰብስበን” በማለት አቅርበዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ ማኅበሩ በዩኒቨርስቲዎችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ እንዲሁም በአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት እያከናወናቸው ስለሚገኙት ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ቀጥሎ የተካሔደው የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር ሲሆን ጥያቄዎቹ ከማኅበሩ አባላትና ምእመናን በተለያዩ ጊዜያት ሲጠየቁ የነበሩ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹንም ለመመለስ ከሊቃውንቱ መካከል መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን የሊቃውንት ጉባኤ አባል፤ መጋቤ ሐዲስ ደጉ ዓለም ካሣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር፤ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ መምህር ሲሆኑ ጥያቄዎቹ በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ አቅራቢነት ተስተናግደዋል፡፡

hawi 03ከጥያቄዎቹ መካከል፡- የኑሮ ውድነት እና ሀብት የማካበት ትኩረታችን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜ ከመስጠት እያገደን ስለሆነ ምን እናድርግ? ቅዱስ ጳውሎስ ሀገራችን በሰማይ ነው ስላለ እኛ ክርስቲያኖች በምድራዊት ሀገራችን ላይ እንዴት እንሥራ? ባለትዳሮች ከትዳር አጋራቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እና ከሌሎች ቤተሰብ አባላት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? ፖለቲካ ኃጢአት ነው? ለሱሰኛ እና ለጠጪ ባንመጸውት ኃጢአት ይሆንብናል ወይ? ንስሐ አባት ለምን ያስፈልጋል? ነፍስን ለፈጠረ እግዚአብሔር በቀጥታ ኃጢአትን መናዘዝ አይቻልም ወይ? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከጥያቄና መልሱ በኋላ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳሰ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ባስተላለፉት መልእክት “ሁሉም ነገር የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ለእምነቱ፤ ለሀገሩና ለአንድነቱ የቆመ በመሆኑ ረጅሙን ጉዞ በመጓዝ ወደ ሀገረ ስብከታችን መጥቶ ይህንን መንፈሳዊ ጉባኤ መካፈል በመቻሉ ተደስተናል፡፡ በሊቃውንቱ ቀኑን ሙሉ ሲነገር የዋለው ቃለ እግዚአብሔር በሚገባ ከያዝነውና ወደ ሕይወታችን መለወጥ ከቻልን ቤተ ክርስቲያንና ሀገራችንን የሚጠቅም ሥራ ልንሠራ እንችላለን፡፡ ሁላችንም ሓላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡ ማኅበሩ በሚቀጥለው ጊዜ ሊያዘጋጅ ያሰበው ጉባኤም ከሀገረ ስብከታችን አይወጣም” ብለዋል፡፡

hawi 04ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምእዳንም “እናንተ እድለኞች ናችሁ፡፡ እኔ በእድሜዬ እንዲህ ያለ ጉባኤ አይቼ አላውቅም፡፡ በውጭ ያሉ ወገኖቻችሁ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ተከራይተው ነው አገልግሎት የሚያገኙት፡፡ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብላችሁ በተረጋጋ መንፍስ ሆናችሁ ትማራላችሁ፡፡ ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ፡፡ ቀኑን ሙሉ ቃለ እግዚአብሔር ሲነገር ነው የዋለው፡፡ የተነገረውን ሁሉ የሰማ በሥራ መተርጎም ይጠበቅበታል፡፡ ሁላችንም የሰማነውን ለሌሎች ብናስተላልፈው ብዙ ሥራ ሊሠራ ይችላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን! ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡ በውጭ ያሉትም በአገልግሎታችሁ ይደሰታሉ፡፡ አንዳንዶች ያልገባቸው ሌላ አድርገው ይተረጉሙት ይሆናል፡፡ ዛሬ የተማርነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶን አስተምህሮ የተከተለ ትምህርት ነው፡፡ ይህንን የሚቃወሙ ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው የወጡ ብቻ ናቸው” በማለት የተናገሩ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳንን፤ የደብሩ ሰበካ ጉባኤንና ምእመናንን አመስግነዋል፡፡

በዚሁ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

 

1464794 583027858417920 875634623 n

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በድምቀት ተካሔደ

ማኅበረ ቅዱሳን ለ5ኛ ጊዜ ያዘጋጀውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ደብረ ዘይት በሚገኘው ደብረ መድኃኒት ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ታኅሳስ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ከ 5000 ምዕመናን በላይ በተገኙበት አካሔደ፡፡ ዝርዝሩን እንደደረሰን እናቀርባለን፡፡1464794 583027858417920 875634623 n

Baptism

“ግብረ ፊልጶስ” የተሠኘ ሲምፖዚየም እንደሚዘጋጅ ተገለጸ

ታኅሣሥ 05 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

“ግብረ ፊልጶስ – ሐዋርያዊ ጉዞ በኢትዮጵያ በቀድሞው፤ በመካከለኛውና በአሁኑ ዘመን” በሚል መንፈሳዊ ጉባኤ በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ አማካይነት ሲምፖዚየም እንደሚዘጋጅ ተገለጸ፡፡ Baptism

 

ተኅሣሥ 12 እና 13 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በሚካሔደው ሲምፖዚየም ላይ ከዚህ በፊት በተልተሌ፤ ጂንካ፤ ከረዩ፤ መተከልና ግልገል በለስ አካባቢዎች ተጠምቀው የእግዚአብሔር ልጅነትን ያገኙ ምእመናን በአካል በመገኘት በጉባኤው ላይ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ያቀርባሉ፡፡

Baptism1የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ክፍሉ ያከናወነውን የአራት ዓመታት የሥራ ሪፖርት፤ እንዲሁም ጥናታዊ ጽሑፍ የሚቀርቡ ሲሆን በጥናታዊ ጽሑፉ ላይና ወደፊት ሊሠሩ በታቀዱ ሥራዎች ላይ ውይይት ይካሔድባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ተጠምቀው ነገር ግን በአጥቢያቸው ቤተ ክርስቲያንና ሰንበት ትምህርት ቤት ለሌላቸው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ይከናወናል፡፡

ይህንን መርሐ ግብር በማኅበሩ ድረ ገጽ (www.eotcmk.org) ላይ የቀጥታ ዓለም አቀፍ ሥርጭት የሚተላለፍ በመሆኑ ምእመናን መከታተል እንደሚችሉ ክፍሉ አስታውቋል፡፡

 

0202023 1

የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ ቅርስነት ተመዘገበ

 ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

  • የመስቀል በዓል አከባበር ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው 10 ቅርሶች መካከል የመጀመሪያው የማይዳሰስ ቅርስ በመባል መመዝገቡን አስመልክቶ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡

 0202023 1
የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኢትዮጵያ የመሰቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች (Intangible) በቅርስነት መመዝገቡን አስመልከቶ ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡

አቶ ዮናስ ደስታ የፌደራል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክተር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ (Intangible) ሆኖ የተመዘገበው ዩኔስኮ የሚጠይቀውን ሒደት ጠብቆና የተለያዩ የግምገማ መሥፈርቶችን አልፎ አዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ከኅዳር 23 – 28 ቀን 2006 ዓ.ም. እያደረገ ባለው ስምንተኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ላይ በትናንትናው ዕለት ተቀብሎ አጽድቆታል”  በማለት ገልጸዋል፡፡

አቶ ዮናስ የመስቀል በዓል አከባበርን በቅርስነት ለማስመዝገብ የተደረገውን ጥረት ሲገልጹ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያዎች አማካይነት ጥናቱ ተከናውኖ ሰነዱ ለዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ኖሚኔሽን  በ2004 ዓ.ም. መቅረቡን አውስተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘገቡ ለጉባኤው ከቀረቡት 31 የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል 23ቱ ሲመረጡ የመስቀል በዓል አከባበር ከተመረጡት ውስጥ አንዱ በመሆኑና እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

0202023 2አቶ ዮናስ የመሰቀል በዓል አከባበር በዓለም አቀፍ ደረጃ የመመዝገቡ ፋይዳን ሲገልጹም ቅርሱን የተመለከቱ መረጃዎች በዩኔስኮ ድረ ገጽ ላይ የሚለቀቅ በመሆኑ ሀገረ አቀፍና ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ እንደሚረዳው፤ የቱሪስት መስህብ መሆኑ፤ ከቀድሞ በተሻለ እንክብካቤ የሚደረግለትና ለትውልድ እንዲተላለፍ እገዛ ማድረጉን፤ ዓለም አቀፍ አጥኒዎችና ተመራማሪዎችን መሳቡ ዋና ዋናዎቹ  ጥቅሞች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የሰሜን ተራሮች፤ አክሱም ጸዮን ሐውልቶች፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፤ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፤ ጢያ ትክል ደንጋዮች፤ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፤ ሐረር ጀጎል፤ የኮንሶ ባሕላዊ መልክአ ምድር እና  የፋሲል ግቢ ኢትዮያ ከዚህ ቀደም ያስመዘገበቻቸው የሚዳሰሱ (tangible) ቅርሶች መካከል ዘጠኙ ሲሆኑ ብቸኛው የመስቀል በዓል አከባበር ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ይመደባል፡፡

meskel 8

የመስቀል በዓል በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ

 የኢትያጵያ የመስቀል ክብረ በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን UNESCO /ዩኔስኮ/ አስታወቀ፡፡

meskel 8
ዝርዝሩን እንደደረስን እናቀርባለን፡፡

 

02 hawir hiwot

ሐዊረ ሕይወት (የሕይወት ጉዞ)

02 hawir hiwot

mesa

ማኅበረ ቅዱሳን ከስደት ተመላሾችን ለመደገፍ እንደሚሠራ አስታወቀ

 ኅዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ማኅበረ ቅዱሳን ከሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ወኖቻችንን ለመደገፍ ቀጣይ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

mesa ማኅበረ ቅዱሳን ከሳውዲ አረቢያ በመመለስ ላይ ለሚገኙ ከ2ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ኅዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ቦሌ በሚገኘው የስደተኞች ጊዜያዊ መቀበያ ጣቢያ በመገኘት የምሳ ግብዣ ባደረገበት ወቅት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ማኅበሩ በዚህ በጎ አድራጎት ተግባር ላይ ለመሳተፍ የተነሣበትን ምክንያት ሲገልጹ “ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ክርስትናም፤ እንደ ዜግነት የወገኖቻችን በዚህ ሁኔታ ላይ መገኘት ያስጨንቀዋል፡፡ ችግሩንም ለመፍታትና ወገኖቻችንን ለመደገፍ ማኅበራችን የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት በማመን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የምሳ ግብዣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን ለመደገፍ ምእመናንንና አባላትን በማስተባበር ቀጣይ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡” ብለዋል፡፡

mesa 1አቶ ተስፋዬ አያይዘውም እነዚህ ወገኖቻችን ሠርተው በሚልኩት ገንዘብ በርካታ ቤተሰብ የሚተዳደር በመሆኑ ቤተሰብ እንዳይበተን፤ ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንዳይደናቀፉ ከፍተኛ ሥራ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ በዚህ ሀገራዊ በሆነ ችግር ላይ መፍትሔ ለመሻት እየተንቀሳቀሰች መሆኗንና፤ ማኅበረ ቅዱሳንም በጋራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሠራ በመግለጽ ምእመናንና አባላትም ማኅበሩ የሚያከናውነውን ተግባር እንዲደግፉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ምሕረተአብ ሙሉጌታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራልና የጊዜያዊ ጣቢያው ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተባባሪ ከስደት ተመላሾችን አቀባበል በተመለከተ ሲገልጹ “ከመንግሥት ጥረት ጎን ለጎን የተለያዩ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት፤ ማኅበራትና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ከስደት ተመላሽ ወገኖቻችንን ለመርዳት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ 79ሺህ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 49 ሺሕ ወንዶች፤ 26ሺሕ ሴቶች እንዲሁም ከ3ሺሕ በላይ ሕፃናት ናቸው፡፡”በማለት ገልጸዋል፡፡ አስፈላጊውንም ምዝገባና መስተንግዶ እየተደረገላቸው ወደየትውልድ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ምሕረተአብ ማኅበረ ቅዱሳንና ሌሎችም ማኅበራት እያደረጉ ላሉት ወገኖቻችንን የመርዳትና የመደገፍ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አቶ መስፍን መንግሥቱ “ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያዊያን” በሚል ከነጋዴው ኅብረተሰብ የተቋቋመ ማኅበር አስተባበሪ ሲሆኑ ቦሌ በሚገኘው ጊዜያዊ የስደተኞች መቀበያ ጣቢያ ሲያስተባብሩ አግኝተናቸው ላቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “የተፈጠረው ድንገተኛ ችግር እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወቅት ተባብረን ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ በዚህም መሠረት ወገኖቻችንን ለመርዳት ተሰባስበን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዶክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም ደብዳቤ በማስገባት ድጋፍ መስጠት እንደሚገባን ተወያተናል፡፡ የተቀደሰ ዓላማ በመሆኑም ወደ ተግባር መግባት ትችላላችሁ በማለት ፈቃድ ሰጥተውናል፡፡ ስደተኞቹ መግባት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በአጭር ሰዓት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ከመስተንግዶ ጀምሮ እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል፡፡

mesa 2
ከስደት ከተመለሱት መካከል ስሟን መግለጽ ያልፈለገች አንዲት እኅት በሳውዲ አረቢያ ስለነበረው የሥራዋ ሁኔታ ስትገልጽ “ከሀገሬ ከወጣሁ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፡፡ ሁለት ሕፃናት ልጆቼን ትቼ ያልፍልኛል ብዬ ነበር አወጣጤ፡፡ ነገር ግን እዚያ የገጠመኝ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ነበር፡፡ ከአሰሪዬ ቤት ውጪ ለሦስት ቤቶች በነጻ እንድሠራ አድርጋኛለች፡፡ ለምን ብዬ በጠየቅሁበት ወቅት ደብድባኝ ጎኔን ኦፕራሲዮን እሰከመሆን ደርሻለሁ፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ እንድሠራ ስታደርገኝ ቆይታለች፡፡ ከዚህ ሥቃይ በሀገሬ ልሙት ብዬ ነው የመጣሁት” በማለት ተናግራለች፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት ክፍል ሦስት

 

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

ባለፈው ዕትማችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዝርወት /ከኢትዮጵያ ውጪ/ ያደረገችውን ረዥም ሐዋርያዊ ጉዞ የሚዳስስ ጽሑፍ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

1.1. ውስጣዊ ችግሮች

ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የታሪክ ጉዞዋ ያጋጠሟት ችግሮች ወደ ኋላ ሲቃኙ በብዛት ከልዩ ልዩ አረማውያንና አላውያን ነገሥታት የመጡባት ውጫዊ ፈተናዎች በርከት ብለው ይታያሉ፡፡ እሷን ለመፈተን የማይታክተው ዲያብሎስ በዚህ ዘመን ደግሞ ከውጫዊው ፈተና ባልተናነሰ መልኩ አንዳንድ ክፍተቶችን በመግቢያነት እየተጠቀመ ቤተ ክርስቲያኗ በተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች እንድትፈተን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህን ችግሮች አንድ በአንድ እንደሚከተለው እንዳስሳለን፡፡

ሀ. አስተዳደራዊ ችግር

በዝርወት ያለችዋ ቤተ ክርስቲያናችን በስደት ካሉ ልጆቿና አካባቢው ከሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ሊገኝ የሚችል ኃይሏን በአግባቡ ተጠቅማ አገልግሎቷን እንዳታጠናክር በተለይ ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ የገጠማት የአስተዳደር መለያየት ዕንቅፋት ሆኖባታል፡፡ ዛሬ በምንገኝበት ሰፋ ሰፋ ባለ ሁኔታ ብንከፍለው በውጭው ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስት ዓይነት አስተዳደር አላት፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያኗ በየአካባቢው ባቋቋመቻቸው አህጉረ ስብከት በኩል በማእከላዊው የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ታቅፎ /በእርግጥ ይህም ቢሆን ያለው አስተዳደራዊ ቁርኝት የሚያረካ አይደለም/ አገልግሎት የሚሰጠው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሀገራችን ከተከሠተው የመንግሥት ለውጥ ጋር ተያይዞ ወደ ሰሜን አሜሪካ የተሰደዱትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛ ፖትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በመያዝ ዘግይተው እሳቸውን የተቀላቀሉት ሌሎች ብፁዓን አበው መሠረትነው ባሉት ስደተኛ ሲኖዶስ ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከሁለቱም አይደለንም ገለልተኛ ነን በማለት የተቀመጠው ክፍል ነው፡፡ ይህ የአስተዳደር ልዩነት ሌሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከቱ የመጡ ችግሮችን እየወለደ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተጠናክራ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን እንዳትሰጥ ዕንቅፋት ሆኖባታል፡፡

ለ. የተቀመጠ ግብና ዓላማ አለመኖር

ዓለም ዛሬ በደረሰበት የአሠራር ደረጃ አንድ ተቋም በሰፊው መክሮና ተችቶ ያስቀመጣቸው ዓላማዎችና ግብ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ የዕለትም ይሁን የዓመት እንቅስቃሴውን እየገመገመ የደከመውን የማጠናከር በጠነከረው የመቀጠል እርምጃ የሚወስደው አስቀድሞ ካስቀመጣቸው ዓላማዎችና ግብ አንጻር ነውና፡፡ ይህንን አጠቃላይ መርሕ በጥንቃቄ ተግባራዊ የሚያደርግ ሕዝብና መንግሥታት ባሉበት በውጭው ዓለም የምትንቀሳቀስ ቤተ ክርስቲያናችን ለምትሰጠው አገልግሎትና በሰው ዘንድም ይሁን በደሙ በመሠረታት ክርስቶስ ዘንድ ለሚጠበቅባት ሰማያዊ አገልግሎት መሪ የሚሆኑ በግልጽ የተቀመጡ ዓላማዎችና ግብ ሊኖራት ሲገባ እንቅስቃሴዎቿ ሁሉ በየጊዜው በሚፈጠሩ ሁኔታዎች መሠረትነት የሚመራ ሆኗል፡፡

ሐ. የአሠራር መመሪያ አለመኖር

አንድ ተቋም የቆመለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንዲችል ከሚያደርጉት መሠረታውያን ነገሮች አንዱ ግልጽና ለአሠራር የሚያመች አንድ መሠረታዊ መመሪያ መኖሩ ነው፡፡ ከዚህ መሠረታዊ መመሪያ በመነሣትም በየደረጃው እንዲያገለግሉ ሆነው የሚቀረጹ መመሪያዎች ሊኖሩት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ መመሪያዎች አማካይነት ተቋሙ እየተንቀሳቀሰ ድካሙንና ጥንካሬዉን በየዕለቱ እየገመገመ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡

በውጭው ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ አገልግሎቷን በተቀላጠፈ መልኩ እንድትፈጽም የሚያስችላት የአገልግሎት ፖሊሲም ይሁን መመሪያ የላትም፡፡ ድንገት ከውስጥም ይሁን ከውጭ የሚመጡ የአገልግሎት አሳቦች ወዲያው በሚመነጩ ደግም ይሁኑ መጥፎ ዘዴዎች ይፈጸማሉ እንጂ ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት ቃለ ዐዋዲውን መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጀችው የውጭ ሀገር አገልግሎት መመሪያ የለም፡፡ ለማዘጋጀትም ፍላጎቱ ያለ መስሎ አይታይም፡፡

መ. በዕቅድና ሪፖርት አለመመራት

በውጭው ዓለም ያለችዋ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን በሚመሩ ዕቅዶችና አፈጻጸሟን በሚገመግሙ ሪፖርቶች አትመራም፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር የማእከላዊው የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ነፀብራቅ መስሎ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም በሥርዓት በሚመራበት ሀገር ካለች ቤተ ክርስቲያን ተመሳሳይ ኋላ ቀርነት አይጠበቅም፡፡

ሠ. ወደ ባዕዳኑ ለመድረስ ያለው ጥረት አናሳ መሆን

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባላት የተስተካከለ ትምህርተ ሃይማኖትና ሰማያዊ ሥርዓት ብዙዎች ባዕዳን ከማድነቅ አልፈው በጥምቀት የሥላሴን የጸጋ ልጅነት አግኝተው ወደሷ ለመጠቃለል ይማልላሉ፡፡ ነገር ግን በአንጻሩ በየደረጃው ያለው የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ይህንን ተረድቶ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሲንቀሳቀስ አይታይም፡፡

ረ. ራሷን ለሌሎች ያለማስተዋወቅ ችግር

ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የታሪክ ዘመኗ በመንፈሳውያን ልጆቿ የዳበሩ በቃልም በመጣፍም እየተወረሱ የቆዩ ልዩ ልዩ የሥነ ዜማ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ሕንፃ፣ የሥነ ፍልስፍና ወ.ዘ.ተ. ዕውቀቶች አሏት፡፡ እነዚህ ዕውቀቶች በመልክ በመልኩ እየሆኑ ለማያውቀው ዓለም ቢቀርቡ ቤተ ክርስቲያኗን በማስተዋወቅና ገንዘብም በማስገኘት በኩል ቀላል የማይባል ሚና ይጫወታሉ፡፡ ነገር ግን በውጭው ዓለም ምናልባት አልፎ አልፎ እዚህና እዚያ ሊጠቀሱ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ካልሆነ በስተቀር በተጠናከረ መልኩ ሲፈጸም አይታይም፡፡ ይህንን ተግባር በማከናወን በኩል ሰፊ ሚና ሊጫወቱ በሚችሉ ኢንተርኔት ሬድዮ ቴሌቪዥን ፓልቶክ በመሳሰሉት መገናኛ ብዙኃን ቤተ ክርስቲያናችን ከሌሎች ኋላ ብትሰለፍ እንጂ ለውድድር የምትደርስ አትመስልም፡፡

ሰ. በአካባቢው ተወልደው የሚያድጉ ሕጻናትን ለማስተማር የሚያገለግል ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት አለመኖር ምእመናን በስደት ሕይወት የሚወልዷቸውን ልጆች የሀገራቸውን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዐተ እምነት እንዲሁም ቋንቋ ባሕልና ታሪክ ተምረው ያድጉ ዘንድ ከቤተሰባቸው ቀጥሎ ሐላፊነት ያለባት ተቋም ቤተ ክርስቲያናችን ናት፡፡ ነገር ግን ይህንን ሐላፊነቷን እንድትወጣ የሚያስችላት ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት የላትም፡፡

 

1.2. ውጫዊ ችግሮች

ሀ. የቦታ እጥረት

በአካባቢው ከሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በንብረትነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሆነ ሕንፃ ያለው አንድም የለም፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ስጦታ ሊባል በሚችል ሁናቴ በሀገሩ ከሚኖሩ የእምነት ድርጅቶች ሕንፃ ያገኙ ቢሆንም እንደራሳቸው ቆጥረው ሊገለገሉበት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም በአካባቢው የምትገኘዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቦታ ችግር አለባት ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡

ለ. የመናፍቃን ጥቃት

ወቅታዊው የቤተ ክርስቲያናችን በመናፍቃን የመጠቃት ችግር በሀገር ቤት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በልዩ ልዩ ችግር የተነሣ ሀገሩን ለቆ በስደት በአውሮፓ የሚገኘው ምእመንም በመናፍቃኑ ልዩ ልዩ ሴራ እየተነጠቀና እየተደናገረ ይገኛል፡፡ በጥናቱ ሒደት ለመረዳት እንደተቻለው መናፍቃኑ በእናት ቤተ ክርስቲያኑ ጉያ ያለውን ምእመን ለመንጠቅ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ውስጥ የምእመናኑን የማኅበራዊ ሕይወት ጉድለት፥ ሕመም፥ የገንዘብ እጦት፥ ትዳር ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉትን መጠቀም ዋናው ነው፡፡ እርስ በርስ በመረዳዳት በኩል ደግሞ በእኛ ምእመናን ዘንድ ድካም ይታያል፡፡

ሐ. ወቅታዊው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ

ምእመኑ በወቅቱ ፖለቲካ ክፉኛ በመናወጡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን በአንድም በሌላ መንገድ በወቅቱ ፖለቲካ እጇ እንዳለባት በመቁጠር ምእመኑ አባቶቹን እንዲርቅና እንዲያወግዝ፥ አባቶችም የምእመኑን ጥያቄ በወግ እንዳይሰሙ አድርጓቸዋል፡፡

መ. የባሕል ተፅዕኖ

በአካባቢው ላለችዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ዕንቅፋት የሆነው ምእመናኑ በሚኖሩበት ሀገር ባሕልና ልማድ ተፅዕኖ ሥር መውደቃቸው ነው፡፡ ይህ ተፅዕኖ ደግሞ በምእመናኑ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በካህናቱም አካባቢ ይታያል፡፡

IV. መፍትሔዎች

የዚህ ጥናት ዓላማ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሉባትን ችግሮች ዘርዝሮ የሚፈቱባቸውን የመፍትሔ አሳቦች ማቅረብ ነው፡፡ ለችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ የሚባሉ ነጥቦች በዝርዝር ይቀርባሉ፡፡ አንዳንዶቹ የመፍትሔ ሐሳቦች የራሳቸው የሆኑ ዝርዝር የስልት ጥናቶች የሚያስፈልጋቸው ይመስላሉ፡፡

ሀ. በአኅጉሩ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኗ ምልዓተ ጉባኤ /ካህናትና ምእመናን/ ተወያይተው የሚያስቀምጧቸው ዓላማዎችና ግቦች ማዘጋጀት

በዚህ ጥናት ሒደት እንደታየው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ አካባቢ ልታከናውናቸው የሚችሉ በርካታ ተግባራት አሉ፡፡ ተግባራቱን ለማከናወንም የተለያዩ አካላት ትምህርተ ሃይማ ኖቷን፣ ሥርዓተ እምነቷንና ትውፊቷን አክብረው አብረዋት ሊሠሩ እንደሚፈልጉ ታይቷል፡፡ በመሆኑም በአኅጉሩ ያለችዋ ቤተ ክርስቲያን አካባቢው የሚጠይቀውን አገልግሎት በስደት ላለው ምእመንም ሆነ በትክክለኛው ትምህርቷና ሰማያዊ ሥርዓቷ ተማርኮ ወደ ዕቅፏ ለመግባት በደጅ ቆሞ ለሚጠባበቀው መንፈሳዊ ድጋፍ መስጠት እንድትችል በመሪ አሳብነት የሚያገለግሉ ዓላማዎችና ግቦች በአስቸኳይ ልታስቀምጥ ይገባል፡፡ ለዚህም አኅጉሩ ውስጥ ያሉትን ካህናትና ምእመናን ያሳተፈ አንድ አጠቃላይ ጉባኤ ማድረግ ይገባል፡፡

 

ለ. የአካባቢውን ሁሉን ዐቀፍ ሁኔታ ያገናዘበ ዝርዝር መመሪያ ማዘጋጀት

ዓለም አቀፋዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራቡ ዓለም በስደት ያሉ ልጆቿንና የሚፈልጓትን ለማገልገል በሐዋርያዊ እግሮቿ ገስግሳ ከተሻገረች በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማዕከላዊው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የቤተ ክርስቲያኗን በምዕራቡ ዓለም መስፋፋት አስፈላጊነት አምኖ ለተግባራዊነቱ ቢንቀሳቀስም እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ይተዳደሩባቸው ዘንድ የውጭውን ዓለም ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ልዩ ልዩ መመሪያዎችን አውጥቶ አልሰጠም፡፡ በሀገር ቤቱ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ መሠረት የተዘጋጁ መመሪያዎች ባሕር ተሻግረው እንዲያገለግሉ ይጠብቃል፡፡ ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ የሕግና ሥርዓት ምንጭ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን ከሚመራ አካል የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በመሆኑም ይህ አስፈላጊ ግን የተረሳ ሳይሆን ጨርሶ ያልታሰበ ጉዳይ በአስቸኳይ ትኩረት ተሰጥቶት በውጭው ዓለም ያለች ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን የምትፈጽምባቸው ዐቢይም ይሁን ዝርዝር መመሪያዎች ሊዘጋጁና በተግባር ሊውሉ ይገባል፡፡ ለዚህም የአኅጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች በአስቸኳይ በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አጠቃላይ የአሠራር መመሪያ አርቅቆ ለውሳኔ የሚያቀርብ አንድ ኃይለ ግብር /Task Force/ ሊሰይሙ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ መፍትሔ አሳብ ተግባራዊ መሆን ከታች ለሚዘረዘሩ አስተዳደራዊ የመፍትሔ አሳቦች እንደ መሠረት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡

ሐ. አስተዳደራዊ አንድነትን መፍጠር

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አሐቲ ከሚያሰኟት ነገሮች አንዱ ማዕከላዊ በሆነ አንድ መንፈሳዊ አስተዳደር መመራቷ ነው፡፡ በመሆኑም በማዕከላዊው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና በአውሮፓ ባለችው ቤተ ክርስቲያን መካከል የጸና ግንኙነት እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም ከሁለቱም አካላት ከፍተኛ ተግባር ይጠበቃል፡፡ ማዕከላዊው አስተዳደር በውጪው ዓለም ያለችዋን ቤተ ክርስቲያን መምራት እንዳለበት ተገንዝቦ ሊንከባከባት የአገልግሎት መመሪያም ሊሰጣት ይገባል፡፡ በየወቅቱ በሚያደርጋቸው ልዩ ልዩ ጉባኤያት ጠንካራ ውክልና ኖሯት እንቅስቃሴዎቿ ሁሉ እየተገመገሙ የደከመውን በማጠናከር የጎደለውን በመሙላት አገልግሎቷን በተጠናከረ መልኩ እንድትቀጥል ማድረግ ይገባዋል፡፡ አልፎ አልፎ በሚያደርጋቸው አስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎችም በዝርወት ያለችዋን ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉና የሚመሩ አባቶችን እና ምእመናንን ቅር የሚያሰኙ ተግባራት መፈጸም የለበትም፡፡ የሚወስዳቸውን አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሁሉ በውጪው ካሉ አባቶች ጋር እየተመካከረ ሊሆን ይገባል፡፡

በውጪ ያሉ አባቶችና ምእመናንም አሐቲ በምትሆን ቤተ ክርስቲያን ከማዕከላዊው አስተዳደር ጋር አንድ መሆናቸውን ከልባቸው ሊያውቁት ይገባል፡፡ በመሆኑም ከላይ ለሚመጡ ትእዛዞችና የማስተካከያ አሳቦች ተገዥዎች መሆን አለባቸው፡፡ እነሱም አንዳንድ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ወደ ላይ እየላኩ የማስወሰን ልምድ ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደየ ደረጃው ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን አበው ወደ አኅጉሩ እየሔዱ ምእመናንን እንዲባርኩና በመንፈሳዊ አባትነታቸው የምእመኑን ችግር በቅርብ እንዲያዩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከላይ ለተባሉትም ሆነ ላልተባሉት ጉዳዮች ተግባራዊነት እያንዳንዱን የግንኙነት እንቅስቃሴ በግልጽ የሚያመላክት አጠቃላይና ዝርዝር መመሪያ ሊዘጋጅ ያስፈልጋል፡፡ ይኽ ዐቢይ ጉዳይ በሁለቱም አካላት ትኩረት ተሰጥቶት በአስቸኳይ ካልተተገበረ በትንሹም ቢሆን ብቅ እያለ የሚመስለውና በአሜሪካ የሚሰማው የቤተ ክርስቲያን ፈተና በዚህም መምጣቱ የሚቀር አይኾንም፡፡

መ. የዕቅድንና ሪፖርትን ጥቅም አስመልክቶ የተለየ ግንዛቤ መፍጠር

እንኳን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ያህል የተቀደሰ ተግባር የትኛውም ቀላል እንቅስቃሴ በዕቅድና በሪፖርት በሚመራበት በዚህ ዘመን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ተልእኮዋን ለማስፈጸም የሚረዷት ሁነኛ የሥራ ዕቅዶች አውጥታ የዕቅዶቹንም ተፈጻሚነት በየጊዜው ሪፖርት እያቀረበች አለመወያየቷ አሳፋሪ ነው፡፡ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን በዓመት አንድ ጊዜ በምታደርገው ጉባኤ ዕቅዶችና ሪፖርቶች ሲቀርቡ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን የሚቀርቡት ዕቅዶችም ይሁኑ ሪፖርቶች ቤተ ክርስቲያኗ በዝርወት ላለው ሕዝብ ማድረግ የሚገባትን ያገናዘቡ ሳይሆኑ በቢሮ ሥራ የሚያልቁ በአመዛኙ ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኗ ልትንቀሳቀስባቸው የሚገቧትን ጉዳዮች በየጊዜው እያገናዘቡ የሚቀርቡ የአገልግሎት ዕቅዶች እየነደፈች ያንንም ለምእመናኗ በግልጽ እያሳወቀች ልትንቀሳቀስ ይገባል፡፡ የሚፈለጉት አገልግሎቶች በዕቅድነት እየተያዙ እንዲፈጸሙ አባቶችንም ሆነ ምእመናኑን የማንቃትና የማደራጀት ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡

ሠ. ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ነጻ የሆኑ ጉባኤያትን በማዘጋጀት አባቶች ስለሚሰጡት አገልግሎት እንዲወያዩና ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ

በጀርመን የሚያገለግሉ ካህናት ልዩ ልዩ ዓመታዊ በዓላትን መሠረት እያደረጉ በዓሉን በሚያደርገው አጥቢያ እየተገናኙ ይወያያሉ፡፡ ነገር ግን በጥናቱ ሒደት እንደታየው ብዙ ጊዜ የሚወያዩት በጥቃቅን አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንጂ ስለ አገልግሎታቸውና የመሳሰሉት ላይ አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም ካህናት የሚንቀሳቀሱት የሳምንቱን መጨረሻ የትራንስፖርት ቲኬት በመግዛት ስለሆነ በዓሉ ካለቀ በኋላ በሩጫ ወደየመጡበት ይመለሳሉ፡፡ በመሆኑም ካህናቱ ስለ አገልግሎታቸው የሚወያዩባቸውና አዳዲስ ሥልቶች የሚቀ ይሱባቸው ራሳቸውን የቻሉ ጉባኤያት ማዕከላዊ በሆኑ ቦታዎች ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ጉባኤያት አማካይነት በአገልግሎት ጉዟቸው ስላጋጠሟቸው ችግሮች ይወያያሉ፤ ምእመናኑን የበለጠ የሚያገለግሉባቸውን መንገዶች ይተልማሉ ወ.ዘ.ተ.

ረ. አካባቢ ተኮር የሆኑ ትምህርቶችን መስጠት

ሰዎች በምግባራቸው ጎልብተው በእምነታቸው እንዳይጸኑ ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ አካባቢያዊ ተጽእኖ ነው፡፡ ይህ እውነታ በአውሮፓ በሚኖሩ ምእመናን ሕይወት ላይ በግልጽ ይታያል፡፡ በመሆኑም ወጣቶችም ይሁኑ ታላላቆቹ ምእመናን በእምነታቸው እንዲጸኑ ችግራቸውን ያገናዘቡ ትምህርቶች በልዩ ልዩ መንገድ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ በዚሁ ተወልደው ለሚያድጉ ሕፃናት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡

ሰ. ከተለያዩ የእምነት ድርጅቶችና የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ቦታዎች የሚገኙበትን መንገድ መፈለግ

በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደተሰማው አውሮፓና አውሮፓውያን ብዙ ገንዘብ አፍስሰው የገነቧቸው የጸሎት ቤቶች የቀደመ አገልግሎት ተቀይሮ የልዩ ልዩ ሥጋዊ ተግባራት ማከናወኛዎች ሆነዋል፡፡ ያ ዕጣና ፈንታ ያልደረሳቸውም ተዘግተው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሀገሩን ሕጋዊ ሒደት ጠብቃ እነዚህን ቦታዎች ማግኘት እንድትችል መንቀሳቀስ ይገባታል፡፡

ቀ. ስለ መናፍቃን እንቅስቃሴ መግለጽ

ምእመናኑ ከመናፍቃኑ ቅሰጣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲጠብቁ በልዩ ልዩ መንገዶች መናፍቃን የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በመግለጽ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይም መናፍቃኑ ምእመናንን ለመንጠቅ የሚጠቀሙባቸውን እርዳታ መሰል ዘዴዎች በማጥናት በቤተ ክርስቲያን በኩል አገልግሎቱ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል፡፡

በ. የፖለቲካ አመለካከቶች ከቤተ ክርስቲያንና አካባቢዋ እንዲጠፉ ማድረግ

በምዕራቡ ዓለም ቤተ ክርስቲያናችን ካሉባት ችግሮች አንዱ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች ምእመንነታቸውን ተገን በማድረግ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ መዋቅሮች በመግባት ቤተ ክርስቲያኗን የግል ዓላማቸው ማራመጃ ማድረጋቸው ነው፡፡ ይህ ድርጊት ምእመኑን ከእናት ቤተ ክርስቲያኑ ይለያል፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያኗ በልዩ ልዩ መዋቅር ያሉትን ፖለቲካዊ አመለካከቶች ከቤተ ክርስቲያኗ እየነቀሉ የማውጣት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ይህንንም ለማድረግ ምእመናንን በግልጽ ስለጉዳዩ እያነሡ ማስተማር፣ አመለካከቱ ያላቸውን አባቶችም ይሁን ግለሰቦች መምከርና ማስመከር እንቢ ያሉትንም በምእመናን ትብብር ከቤተ ክርስቲያኗ ማኅበር እንዲለዩ ማድረግ መቻል ይኖርበታል፡፡

ተ. የገጽታ ግንባታ ሥራ መሥራት

ከላይ እንደቀረበው በአውሮፓ ያለው ምእመን በብዛት ለአባቶች ክብር አይሰጥም፡፡ ይህም ከቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ሱታፌ እንዲርቅ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ምእመኑ ለአባቶቹ ፍቅር ባጣበት በዚህ ዘመን የአባቶችን ገጽታ የማድመቁና ጥብቅና የመቆሙ ሥራ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ሰባክያንም ሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት በአገልግሎታቸው ሒደት ከምእመናን ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሁሉ ስለ ካህናት ማንነትና ስለ አገልግሎታቸው አስፈላጊነት መልካሙን በመግለጽ የሕዝብ ግንኙነት ሥራቸውን ሊሠሩ ግድ ይላል፡፡

ቸ. አካባቢውን ያገናዘቡ የቃለ እግዚአብሔር ማስተላለፊያ መንገዶችን መጠቀም

ዛሬ ዓለም በደረሰበት የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ዕውቀትን በቀላል ወጪና የሰው ኃይል ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ የሚያስችሉ መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ መረጃ መረብ፣ የርቀት ትምህርት፣ ፓልቶክ፣ የቴሌፎን ጉባኤ፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉት ናቸው፡፡ እነዚህ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት አገልግሎት ላይ በሚውሉባቸው ሀገራት አገልግሎት የምትሰጥ ቤተ ክርስቲያናን ለዓላማዋ ማስፈጸሚያ መጠቀም የውዴታ ግዴታዋ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየዘርፉ የሠለጠኑ ምእመናንን መመልመልና ወደ አገልግሎቱ ማሰማራት ይጠበቅባታል፡፡

ነ. ራሷን የምታስተዋውቅባቸው ልዩ ልዩ መንገዶችን መቀየስ

በአካባቢው ቤተ ክርስቲያኗ ራሷን ለማስተዋወቅ ከላይ የተዘረዘሩትን መንገዶች ከመጠቀም በተጨማሪ ልዩ ልዩ ዐውደ ርእያትን፣ ሲምፖዝየሞችን፣ የባሕል ማስተዋወቂያ ዝግጅቶችን ወዘተ. ማዘጋጀት ትችላለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ

 

የማይስማሙትን እንዲስማሙ አድርጎ ፈጠራቸው

ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ከሰባት እርስ በርሳቸው ከማይስማሙ ነገሮች ፈጥሮታል:: አራቱ ባሕርያት እግዚአብሔር በጥበቡ ካላስማማቸው በቀር መቼም የማይስማሙ ባላንጣዎች ናቸው፡፡ ምን አልባት ተስማምተው ከተገኙም በጽርሐ አርያም ባለው የእግዚአብሔር ማደሪያ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ ግን ባለጠጋው እግዚአብሔር የውኃ ጣራ፤ የእሳት ግድግዳ ያለው አዳራሽ ሠርቷል፤ ዓለም ከተፈጠረ እስከ ዛሬ ተስማምተው ይኖራሉ እንጂ አንዱ ባንዱ ላይ በክፋት ተነሳስቶ ውኃው እሳቱን አሙቆት፤ እሳቱም ውኃውን አጥፍቶት አያውቅም፡፡ ይህ ትዕግስታቸው በፍጥረት ሁሉ አንደበት ሠሪያቸውን እንዲመሰገን አድርጎታል::

በታች ባለው ምድራዊ ዓለምም ያለው ብቸኛው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሰው ልጅ ነውና እነዚህ እርስ በእርስ የማይስማሙ መስተጻርራን ነገሮች ተስማምተው የሚኖሩበት ዓለም ሆኗል፡፡ እሳት ከውኃ፤ ነፋስ ከመሬት ጋር የሚያጣብቃቸውን የፍቅር ሰንሰለት የሰው አዕምሮ ተመራምሮ ሊደርስበት የማይችል ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ግን እንዴት ይሆናል? ነፋስ መሬትን ሳይጠርገው፤ መሬትም ነፋስን ገድቦ ይዞ መላወሻ መንቀሳቀሻ ሳያሳጣው፤ ተስማምተው እንዲኖሩ ያደረገ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡ ውኃና እሳት ተቻችለው አንድ ቤት ውስጥ መኖር ችለዋል፤ የጥንት ጠላትነታቸውን በጥበበ እግዚአብሔር አስታራቂነት እርግፍ አድርገው ትተው ከሞት በቀር ማንም ላይለያቸው በቃል ኪዳን ተሳስረዋል፡፡

አሁን እሳት ውኃን በቁጣ ቃል አይናገረውም ውኃም በእሳት ፊት ሲደነግጥ አይታይም እንዲያው ሰው በሚባለው ዓለም ውስጥ በሰላም ይኖራሉ እንጂ፡፡ የነቢዩ ዳዊት ቃል ለነርሱ ያለፈ ታሪክ ማስታወሻ ቃል ነው፡፡ “ከመጸበል ዘይግህፎ ነፋስ እምገጸ ምድር፤ ከምድር ገጽ ላይ ነፋስ እንደሚበትነው አፈር…..” ይባል ነበር አባቶቻችንም ስለ ወንጌላዊው ማቴዎስ ሲተርኩልን “ሶቤሃኬ ተንሥአ ማቴዎስ ወንጌላዊ ከመ ተንሥኦተ ማይ ላዕለ እሳት፤ ውኃ በእሳት ላይ በጠላትነት እንዲነሣ ወንጌላዊው ማቴዎስም ተናዶ ተነሣ” በማለት ወንጌልን ለመጻፍ የተነሣበትን ምሥጢር አጫውተውናል፡፡ ማንኛውም ነገር አጥፊና ጠፊ ሆኖ ከተነሣ በእሳትና በውኃ መመሰል የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልዩ ሥነ ተፈጥሮ ባረፈበት የሰው ሕይወት ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እሳትና ውኃ እስከ መቃብር የሚዘልቅ የፍቅር መንገድ ጀምረዋል ነፋስና መሬትም እስከ ፀኣተ ነፍስ ላይለያዩ ወስነዋል፡፡ ይህ የፍቅር ኑሯቸው ደግሞ ሌላ አዲስ ነገር ፈጠረላቸው ለመላእክት እንኳን ያልተደረገ አዲስ ነገር እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ላይ እንዲያደርግ አስገድዶታል፤ የማትሞትና የማትበሰብስ ነፍስን በሥጋ ውስጥ አኖራት፡፡ ሌላ አስደናቂ ነገር ነው፡፡ የአራቱ መስተጻርራን መዋሐድ የፈጠረው ሌላ አስደናቂ መዋሐድ፡፡

በጥቂቱም ቢሆን ከመላእክት ጋር ዝምድና ያላት ነፍስ በእጅጉ ከማይስማማት የሥጋ ባህርይ ጋር ተስማምታ መኖሯ አስደናቂ ነገር ነው፡፡ አራቱ ባህርያት ልዩነታቸውን አጥፍተው በፍቅር ተስማምተው ብታይ እሷም ሁሉን ረስታ ከሥጋ ጋር ተስማምታ ለመኖር ወሰነች እናም ሥጋ ብዙ ድካሞች እንዳሉበት ብታውቅም ከነድካሙ ታግሳው አብራው ትኖራለች፡፡ ሥጋ ይተኛል ያንቀለፋል፤ እሷ ግን በድካሙ ሳትነቅፈው እንዲያውም ተኝቶም በሕልም ሌሎችን የሕልም ዓለማት እንዲጎበኝ በተሰጣት ጸጋ ይዛው ትዞራለች፡፡ በሕልም ሠረገላ ተጭኖ በነፍስ መነጽርነት አነጣጥሮ የተመለከተውን አንዳንዱን ሲደርስበት ሌላውንም በሩቅ አይቶ ተሳልሞ ሲተወው ይኖራል፡፡

ያዕቆብ እንዳየው የተጻፈው ሕልም አስገራሚ ከሚባሉት ሕልሞች ዋናው ነው፡፡ ምክንያቱም በምድር ያለ ሰው የእግዚአብሔርን ዙፋን በሕልም ያየበትና የሰማይ መላእክትን የአገልግሎት ሕይወት የተካፈለበት ሕልም ስለሆነ ነው ዘፍ28÷10፡፡ ያዕቆብ በነፍሱ ያየው ይህ አስደናቂ ሕልም ከሦስት ሺህ የሚበዙ ዓመታትን አሳልፎ ፍጻሜውን በክርስቶስ ልደት አይተናል ዮሐ1÷50፡፡ ታዲያ ነፍሳችን በዘመን መጋረጃ የተጋረዱ ምሥጢራትን ሳይቀር አሾልካ መመልከት የምትችል ኃይል ናት ማለት ነው፤ እሷም የፍቅር ውጤት ናት፡፡ ተፈጥሮአችን ከምታስተምረን ነገሮች አንዱ ትዕግስት ነው፡፡ ሁልጊዜ ትዕግስት ፍቅርን፤ ፍቅር ደግሞ ሁሉን ሲገዛ ይኖራል ሰማያዊም ሆነ መሬታዊ ኃይል ለነዚህ ነገሮች ይሸነፋል ምን አልባት ሰው ሁሉን አሸንፎ የመኖሩ ምሥጢር ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ ተፈጥሮው ትዕግስትን፤ ትግስት ደግሞ ፍቅርን ወልዳለታለች ከዚህ የተነሣ ተፈጥሮን መቆጣጠር የቻለ እንደሰው ያለ ማንም የለም፡፡ እስኪ ልብ በሉት ሞትን በቃሉ የሚገስጽ፣ ደመናትን በእጆቹ የሚጠቅስ፣ የሰማይን መስኮቶች የሚመልስ፤ እስከ ሰባተኛው ሰማይ ወጥቶ የሚቀድስ የሰው ልጅ አይደል? ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሁሉም ነገር ለሰው አገልግሎት ሲባል የተፈጠረ ነው፡፡ የማይስማሙትን አስማምቶ ባንድ ላይ ማኖር መቻል ትልቅ ጥበብ ከመሆኑም በላይ ትዕግስት ካለ ሁሉም ፍጥረት ተቻችሎ ባንድነት መኖር እንደሚችልም አመላካች ነው፡፡

ተቻችለው የመኖራቸው ምሥጢር፡-
እያንዳንዳቸውን ብንመለከት አራቱም ባህርያት ለያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ባሕርያት አሏቸው፡- የእሳት ባህርይ ውእየትና /ማቃጠል/ ይብሰት /ደረቅነት/ ሲሆን፤ የውኃ ደግሞ ቆሪርነትና /ቀዝቃዛ/ ርጡብነት /ርጥብነት/ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱም ባህርያት በምንም ይሁን በምን መስማማት አይቻላቸውም እግዚአብሔር ግን በሌላ በኩል የእርቅ መንገድ ፈልጎ ሲያስታርቃቸው እንመለከታለን፡፡ ይሄውም በነፋስና በመሬት በኩል ነው፤ የነፋስ ባህርያት ውእየትና ቆሪርነት ሲሆን የመሬት ባህርያት ደግሞ ይቡስነትና ርጡብነት ናቸው፡፡ አሁን ዝምድናውንና ማንን በማን እንዳስታረቀ ስንመለከት እሳትና ውኃን በነፋስ አስታርቋቸዋል፡፡ ነፋስ በውዕየቱ ከእሳት፤ በቆሪርነቱ ከውኃ ጋር ተዘምዶ አለው፤ በመካከል ለሁለቱም ዘመድ ሆኖ በመገኘቱ እሳትን ከውኃ ጋር አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ የመሐል ዳኛ ባይኖራቸው ኖሮ እሳቱ ውኃውን እንደ ክረምት ነጎድጓድ አስጩሆት ውኃውም እሳቱን እንደ መብረቅ ሳይታሰብ በላዩ ላይ ወርዶበት ተያይዘው በተላለቁ ነበር፡፡

ነፋስና መሬትን ደግሞ ውኃን ሽማግሌ አድርጎ ሲገላግላቸው እናያለን ውኃ በቀዝቃዛነቱ፤ ነፋስን በርጥበቱ መሬትን ይዘመዳቸዋል ይህን ዝምድናውን ተጠቅሞ ሁለቱን መስተጻርራን በትዕግስት አቻችሏቸው ይኖራል፡፡ አብረው በመኖራቸው ደግሞ ነፋስ ከመሬት ትእግስትን ተምሯል አብሮ መኖር ከሰይጣን ጋር ካልሆነ ከማንኛውም ፍጥረት ጋር ካወቁበት ጠቃሚ ነው፤ አብሮነት የለወጣቸው ህይወቶች ብዙ ናቸው፡፡ ዐስራ ሦስቱን ሽፍቶች ያስመነነው አንድ ቀን ከናፍርና ከሚስቱ ጋር የተደረገ ውሎ ነው፤ ያውም ገንዘብ ሊዘርፉና አስካፍን ሊማርኩ ሄደው ህይወታቸውን አስማረኩ፤ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ሄደው ላልታጠቀው ተንበረከኩ፡፡ ክርስትና እንዲህ ሲሆን የእውነተኛነቱ ማረጋገጫ ነው ምክንያቱም ክርስትና ማለት አንዱ ብዙዎችን የሚያሸንፍበት፤ ወታደሩ ንጉሡን የሚማርክበት፤ ገረድ እመቤቷን የምታንበረክክበት ያሸናፊዎች ሕይወት ነውና፡፡ ሳይታኮሱ ደም ሳያፈሱ አብሮ በመዋል ብቻ ከህይወታቸው በሚወጣው የሕይወት መዓዛ ብቻ የሰውን አካሉን ብቻ ሳይሆን ልቡን ጭምር መማረክ ያስችላል፡፡ ዐስራ ሦስት ሰው ባንድ ጊዜ እጅ የሰጠውም ከዚህ የተነሣ ነው እናም አብሮነት የሚጎዳው ከሰይጣን ጋር ብቻ ከሆነ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን የአትናስያን ሕይወት የለወጠ፤ ኃጢአቷን ከልቧ እንደ ሰም ያቀለጠ፤ ላንዲት ሰዓት ከዮሐንስ ሐጺር ጋር የነበራት ቆይታ ነው፡፡ እነ ማርያም ግብፃዊትን ከዘማዊነት ወደ ድንግልና ሕይወት የለወጠስ ላንድ ቀን ብቻ ወደ ኢየሩሳሌም ከሚሄዱ ሰዎች ጋር የተደረገ ውሎም አይደል? ያን የመሰለ የቅድስና ሕይወት ባንድ ጀንበር የገነባ አብሮነት በመሆኑ የሕይወት ትምህርት ቤት ነው፡፡

በእርግጥ እግዚአብሔር ያልባረካት ሕይወት ከማንም ጋር ብትውል ለውጥ እንደሌላት በይሁዳ፣ በዴማስ፣ በግያዝ ሕይወት ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን የተሰበረ መንፈስ ለሌላቸው ቅንነት ለጎደለባቸው ማለት እንጅ አብሮ በመኖር የሚገኘውን ጥቅም የሚተካ ሌላ ነገር አለ ማለት አይደለም፡፡ ነፋስን በቅጽበት ዓለማትን መዞሩን ትቶ ባህሩን የብሱን መቆጣቱን ረስቶ ተረጋግቶ እንዲኖር ያደረገው ከመሬት ጋር አብሮ መኖሩ እኮ ነው ፡፡

መሬትም በአንጻሩ ከነፋስ ጋር በመኖሩ ፈጣን ደቀ መዝሙር ሆኗል፡፡ መሬትን የምናውቀው የማይንቀሳቀስ ፅኑ ፍጥረት መሆኑን እንጂ መሬት ሲንቀሳቀስ የምናውቀው አይደለምን? በሰው ባህርይ ውስጥ የመሬትን ባህርይ ተንቀሳቃሽ ያደረገው ከነፋስ ጋር አብሮ መሠራቱ ነው እንጂ ሌላ ምን አለው መጽሐፍ ስለ መሬት ሲናገር የተናገረው እንዲህ ነበር፡፡ ”ዘአጽንኣ ለምድር ዲበ ማይ፤ ምድርን በውኃ ላይ ያጸናት” መዝ 135÷6 በማለት የምድርን ፅናት ይመሰክራል፡፡ ሰውን ስንመለከተው ሌላ አዲስ ፍጥረት ይመስለን ይሆናል እንጂ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ሁለት ፍጡራን አንዷ ከሆነቸው ምድር የተገኘ ምድራዊ ፍጥረት ነው፡፡ ነገር ግን የሚንቀሳቀስ ምድር መሆኑ አስገራሚ ፍጥረት ያደርገዋል የዚህ ምሥጢር ደግሞ የተሠራበትን ምድር በነፋስ ሠረገላ ላይ ጭኖ የፈጠረው መሆኑ ነው የተጫነበት ሠረገላ ፈጣን ከመሆኑ የተነሣ የማይንቀሳቀሰውን እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል፡፡

መሬትም ለፈጣኑ የነፋስ እግሮች ጭምትነትን ያስተምርለታል፡፡ ባጭር ጊዜ አድማሳትን ማካለል የሚቻለው ነፋስ ጭምትነትን ገንዘብ ሲያደርግ ትዕግስትን ለብሶ ሲመላለስ ማየት ምንኛ ድንቅ ነው፡፡ ከዚያም በላይ አራቱንም በሌላ ሁለት ነገር እንከፍለዋለን፡- ቀሊልና ክቡድ ብለን፡፡ ቀሊላኑ እሳትና ነፋስ ሲሆኑ ክቡዳኑ መሬትና ውኃ ናቸው፡፡ እንደ ውኃና ነፋስ ምን ቀላል ነገር ይኖራል? እንደ መሬትና ውኃስ ማን ይከብዳል? ቢሆንም ግን አብረው ይኖራሉ እንዲያውም ክቡዳኑ መሬትና ውኃ ከላይ የተቀመጡ ሲሆን ቀሊላኑ እሳትና ነፋስ ግን ከስር ሆነው ክቡዳኑን ሊሸከሙ ከእግዚአብሔር ተወስኖባቸዋል፤ ሁለቱም እርስ በእርስ ተጠባብቀው ይኖራሉ፡፡ ነፋስና እሳት ቀላል ከመሆናቸው የተነሣ ወደ ላይ እንዳይወጡ መሬትና ውኃ ከላይ ሆነው ይጠብቃሉ፤ መሬትና ውኃ ደግሞ ከባዶቹ ናቸውና ወደታች እንውረድ ሲሉ ነፋስና እሳት ሓላፊነቱን ወስደው ከመውደቅ ይታደጓቸዋል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ስጦታ ሰውን ወደታች ወርዶ እንጦርጦስ እንዳይገባ፤ ወደ ላይም ወጥቶ እንዳይታበይ ማእከላዊ ፍጡር አድርጎ ሲጠብቀው ይኖራል፡፡ ፈጡራንን ሲፈጥር በመካከላቸው መረዳዳትን የግድ ባያደርገው ኖሮ ማንኛውም ፍጡር አብሮ ለመኖር ባልተስማማ ነበር፡፡ ምንም ላንጠቅመው የሚወደንና የሚጠብቀን የሰማዩ አምላክ ብቻ ይሆናል፡፡ ፍጥረታት ግን እርስ በእርስ ተጠባብቀው የሚኖሩት አንዱ ያለ አንዱ መኖር ስለማይችል ብቻ ነው፡፡

እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ ነፋስ እሳቱን አግለብልቦ አንድዶት እሳቱም በፋንታው ውኃውን አንተክትኮት ውኃም መሬትን ሰነጣጥቆ ጥሎት አልነበረምን? ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር የተሰወረ አልነበረምና አራቱንም ኑሯቸውን እርስ በእርስ የተሳሰረ አድርጎታል፡፡ መሬትና በውስጧ የሚኖሩ አራቱ ባህርያት ተስማምተው መኖራቸው ከመሬት በላይ የሚኖሩ ፍጥረታት ተስማምተው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ አንዱ ሌላውን በመታገሱ የተከሰተ ነውና ለሁሉም ነገር መሠረቱ ትዕግስት መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡

ከዕለታት አንዳንድ ቀናት አሉ አራቱ ባህርያት የማይስማሙባቸው፡፡ ታዲያ በነዚህ ቀናት ሰው ተኝቶም እንኳን አይተኛም፤ የነፋስ ባህርይ የበረታ እንደሆነ ሲያስሮጠው ከቦታ ቦታ ሲያንከራትተው ያድራል፤ የመሬት ባህርይ ቢጸና ደግሞ ከገደል ሲጥለው፤ ተራራ ተንዶ ሲጫነው ያያል፤ እሳታዊ ባህርይም በእሳት ተከበን፤ እሳት ቤታችንን በልቶ ሲያስለቅሰን ያሳያል፤ ውኃም እንደሌሎቹ ሁሉ ሰውን በባህሩ ሲያጠልቀው ውኃ ለውኃ ሲያመላልሰው ያድራል፡፡ እያንዳንዳቸው ተስማምተው እንዲኖሩ ባያደርጋቸው ሰው በመኝታው እንኳን እረፍት ማግኘት እማይችል ፍጡር ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትዕግስት ለማንኛውም ነገር መሠረት ነው፡፡

ሁሉም በጎ ነገሮች በሰማይም በምድርም የሚገኙት የትዕግስት ውጤቶች መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ሰው በራሱ የትዕግስት ውጤት መሆኑን ካየን የምንጠብቀው አዲሱ ዓለም መንግሥተ ሰማይ የትዕግስት ስጦታ ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ የሚለው “እስከ መጨረሻው የታገሰ ይድናል” ነውና፡፡ ሞታችንን የገደለው፤ ጨለማን የሳቀየው ማነው? ክርስቶስ በዕለተ አርብ በህማሙ ወቅት ያሳየው ትእግስትም አይደል! ይሄ ትዕግስት ፍጥረቱን ሁሉ ያስደነቀ ትዕግስት ነበር፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አንዱ “ኦ! ትዕግስት ዘኢከሠተ አፉሁ በሕማሙ በቅድመ እለ ይረግዝዎ፤ በመከራው ወቅት በሚወጉት ሰዎች ፊት የማይናገር ትዕግስት” ሲል በቅዳሴው ያደንቃል፡፡ በዚህ አስደናቂ ትዕግስቱ እኮ ነው ኃይለኛውን እስከ ወዲያው ጠርቆ ያሰረው ማቴ12÷29፡፡ ኃይለኛውን አስሮ ቤቱ ሲዖልን በርብሮ አወጣን፡፡ እንግዲያውስ ትዕግስት ጉልበት ነው፤ ትዕግስት ውበት ነው፡፡ በዓለም ላይ በጦርነት ከተሸነፉት በትዕግስት የተሸነፉት ይበዛሉ፤ ባለ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ጦር የነበረው ሰናክሬም በሕዝቅያስ ትዕግስት መሸነፉን አንዘነጋውም፡፡

 

books 26

“አትሮንስ” የመጻሕፍት ውይይት መርሐ ግብር ሊጀመር ነው

 ጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. 

በእንዳለ ደምስስ

books 26ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መጻሕፍት የንባብ ባሕልን ለማዳበር በየደረጃው ከሚሠራቸው ተግባራት በተጨማሪ “አትሮንስ” የተሰኘ በመጻሕፍት ላይ የሚደረግ የውይይት መርሐ ግብር ኅዳር 1 ቀን 2006 ዓ. ም. በማኅበሩ ኤዲቶሪያል ቦርድ አስተባባሪነት ይጀመራል፡፡

ንባብ ዕውቀትን ለማዳበር፤ አስተሳሰብን ለማስፋት፤ ሚዛናዊ ብያኔን ለመሥጠት፤ የአባቶችን ሕይወትና ትምህርት ለማወቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጸው የኤዲቶሪያል ቦርድ ክፍል፤ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ማንበብ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኛ መንገድን የሚጠርግና ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን በመገንዘብ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

የመርሐ ግብሩ ዋነኛ ዓላማም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱ የነገረ ሃይማኖት፤ የታሪክና የአስተዳደር መጻሕፍትን ማስተዋወቅ፤ የመንፈሳዊ መጻሕፍት የንባብ ባሕልን ማዳበር፤ በንባብ ባሕል ላይ የላቀ ልምድ ያላቸውን ሊቃውንት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ማድረግ፤ በመንፈሳዊ መጻሕፍት ላይ የውይይት ባሕልን ማሳደግና የልምድ ልውውጥን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀ መርሐ ግብር መሆኑን ከማኅበሩ ኤዲቶሪል ቦርድ ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

መርሐ ግብሩ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል በኤዲቶሪያል ቦርድ የመጻሕፍት አርትዖት ክፍል ሥር ራሱን የቻለ ማስተባበሪያ ሆኖ እንደሚደራጅ የተገለጸ ሲሆን ዕቅድና ሪፖርት፤ አስፈላጊው በጀትም እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡

“አትሮንስ” የመጻሕፍት ውይይት መርሐ ግብር ወር በገባ በመጀመሪያው እሑድ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡00 ሰዓት በማኅበሩ ሕንፃ ላይ በየወሩ እንደሚዘጋጅ ክፍሉ አስታውቋል፡፡ ኅዳር 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በሚካሄደው መርሐ ግብርም “የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” የተሰኘውና በረዳት ፕሮፌሰር ሉሌ መላኩ የተጻፈው መጽሐፍ ውይይት ይካሄድበታል፡፡

ምእመናን በተጠቀሰው ቀን፤ ሰዓትና ቦታ በመገኘት መርሐ ግብሩን መከታተል እንደሚችሉም የማኅበረ ቅዱሳን የኤዲቶሪያል ቦርድ ክፍል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡