ቅዱስ ፓትርያርኩ የልደት በዓልን አስመልከቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

ታኅሣሥ 27 ቀን 2007 ዓ.ም.

lidet 01ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2007 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክቶ ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን ታኅሣሥ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

ቅዱስነታቸው ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ቃል ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡

ቃለ በረከት ዘእምኅበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደት ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

– በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
– ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
– የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
– በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
– እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያት፤
የዘለዓለም አባት፤ የሰላም አለቃ፤ ስሙም ድንቅ መካርና ኃያል አምላክ የሆነው ጌታችን፤ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ2007 ዓ.ም. በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

“ውውእቱ ቃል ሥጋ ኮነ ወኃደረ ላዕሌነ፤ ያ ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛ ላይም አደረ” (ዮሐ.1፣14)

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

የጌታችን፤ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓል ልደት ስናከብር ከሁሉ በፊት የእርሱን ማንነት በማውሳት፤ በመረዳትና የእምነት ግብረ መልስን በመስጠት ልናከብር እንደሚገባ መገንዘቡ ተገቢ ነው፤
ከዚህ አኳያ ለመሆኑ የተወለደው ማን ነው? ለምንስ ተወለደ? በልደቱ ዕለት ለዓለም የተላለፈው አጠቃላይ መልእክትስ ምንድነው? የሚለውን ማየት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፣

ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ እንደሚያስተምሩን ከሦስት አካላተ እግዚአብሔር አንዱ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃል ስለሆነ በተለየ ኩነቱ ቃል፣ ቃለ አብ፤ ቃለ እግዚአብሔር፣ አካላዊ ቃል ተብሎ ይጠራል፤(መዝ.32፣6፤ ዮሐ.1፣1-2፤ ራእ.19፣13) ቃል ከልብ እንደሚገኝ አካላዊ ቃልም ከአብ የተገኘ ነው፤ ይሁንና ቃል ከልብ በመገኘቱ ደኃራዊ አይባልም፤ ልብም ቃልን በማስገኘቱ ይቀድማል አይባልም፡፡ በህልውናም በተመሳሳይም አካላዊ ቃል ከአብ በመገኘቱ ደኃራዊ አይባልም፣ የአካላዊ ቃል አስገኝ በመሆኑ ከወልድ ይቀድማል አይባልም፡፡ በህልውናው (በአኗኗር) ከቃል የተለየ ወይም የቀደመ ልብ እንደማይኖር ሁሉ፣ ከአካላዊ ቃል የተለየ ወይም የቀደመ የአብ ህልውና (አኗኗር) የለም፤ ቃል የሚለው ስም እኩል የሆኑ የሦስቱ አካላተ እግዚአብሔር ቅድምና እና ህልውና በምሥጢር ያገናዘበና በትክክል የሚገልጽ በመሆኑ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመለኮታዊና በቀዳማዊ ስሙ ቃል ብሎታል፤

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” በማለት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነት በያማሻያማ መልኩ ያረጋግጣል፤ (ዮሐ.1፣1-3)፡፡ እግዚአብሔር አብ አካላዊ በሆነ ቃሉ በእግዚአብሔር ወልድ ፍጥረታትን ሁሉ እንደፈጠረ፣ አካላዊ በሆነ እስትንፋሱ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ለሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ሕይወትን እንደሰጠ በቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ቦታ በግልጽ ተቀምጦአል፤ (ዘፍ.1፣1-3፤ መዝ.32፣6፤ዘፍ.2፣7፤ ሮሜ 8፣11)፡፡
በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ሥጋችንን በመዋሐድ ሰው ሆኖ ተወለደ እየተባለ ያለው ፍጥረታትን በሙሉ የፈጠረ፣ ከተፈጠረው ፍጥረት አንዳች ስንኳ ያለእርሱ የተፈጠረ ምንም እንደሌለ የተነገረለት አካላዊ ቃል ማለትም ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ነው፤

አካላዊ ቃል ከዘመን መቆጠር በፊት በመለኮታዊ ርቀትና ምልአት ከፍጡራን አእምሮ በላይ በሆነ ዕሪና፣ ዋሕድና፣ ቅድምና፣ ኩነትና ህልውና እንደ አብና እንደ መንፈስ ቅዱስ የነበረ ሲሆን፤ በሞቱ የእኛን ዕዳ ኃጢአት ተቀብሎ ከሞተ ኃጢአት ሊያድነን በአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም መጋቢት 29 ቀን መዋች የሆነው ሥጋችንን በማኅፀነ ማርያም ተዋሕዶ ሥጋ ሆነ፤ (ዮሐ.1፣14)፡፡

ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲሆነው ታሕሣሥ 29 ቀን እንደ ትንቢቱ ቃል በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ተወለደ፤ የምሥራቹም “ዛሬ መድኅን ክርስቶስ ተወልዶላችኋል” ተብሎ በመላእክት አንደበት ተበሠረ፤ (ሉቃ.2፣10-12፤ ማቴ.2፣1-11)፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ በተወለደ ጊዜ በቃል ርስትነት ሰው እግዚአብሔር ሆነ፤ በሥጋ ርስትነት አካላዊ ቃል ሰው ሆነ፤ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ይህንን ተዋሕዶ የተመለከቱ የሰማይ ሠራዊትም አካለ ሰብእን በተዋሕዶተ ቃል ለአምላካዊ ክብር ላበቃ ለእርሱ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ይሁን፤ በጎ ፈቃዱም ለሰው ይሁን” ብለው በደስታ ዘመሩ (ሉቃ.2፣13-15)

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ያደረገው በጎ ፈቃድ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ላሉ ፍጥረታት ለማንም ያልተደረገ ነው፤ (ዕብ.1፣1-14)፡፡
ምንም እንኳ ፍጥረታትን ሁሉ በቸርነቱ የሚመግብና የሚጠብቅ እርሱ ብቻ መሆኑ ቢታወቅም፣ አካሉን አካል አድርጎ በተዋሕዶ ወደ አምላክነት ደረጃ ከፍ ያደረገው፣ በመንበረ መለኮት ያስቀመጠውና የሰማይና የምድር ገዢ ያደረገው ግን ከሰው በቀር ከፍጡር ወገን ሌላ ማንም የለም፤ (መዝ.8፣4-6፤ዕብ 2፣16፤ ኢሳ.9፣6-7)፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በተለየ ሁኔታ በስሟ ላይ “ተዋሕዶ” የሚለውን ቃል መጠቀሟ የድኅነታችን መሠረት፤ የቃልና ሥጋ ተዋሕዶ መሆኑን ለማሳየት ነው፤
ምክንያቱም ቃል ሥጋን ካልተዋሐደ አይሞትምና፤ ቃል በሥጋ ካልሞተ ደግሞ እኛ ከሞትና ከኃጢአት ዕዳ ነጻ መሆን አንችልምና ነው፤

የአምላክ ሰው ሆኖ መወለድ ለሰው ልጅ ያስገኘለት ክብር እስከዚህ ድረስ መሆኑን መገንዘብና ማወቅ ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ ነው፤
ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋችን ዛሬ በመለኮት ዙፋን ተቀምጦ ዓለምን ማለትም ሰማያውያኑንና ምድራውያኑን በአጠቃላይ እየገዛ ይገኛል፤ (ዕብ. 2፣5-8)፡፡
ይህ ታላቅና ግሩም ምሥጢር የተከናወነው በሰው ብልሃትና ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ የተፈጸመ አስደናቂ ጸጋ ነው፤
በዚህ ፍጹም የተዋሕዶ ፍቅር ሰማያውያኑና ምድራውያኑ እውነተኛውን ሰላም ማለትም በጌታችን ልደት የአምላክና የሰው ውሕደት እውን ሆኖ ስላዩ “ሰላም በምድር ሆነ” አሉ፡፡ ሰማያውያኑ ፍጡራን ዛሬም ያለ ማቋረጥ ሰው ለሆነ አምላክ ይህንን የሰላም መዝሙር ይዘምራሉ፤ እኛ ምድራውያኑም የዘወትር መዝሙራችን “ሰላም በምድር ይሁን” የሚለው ሊሆን ይገባል፡፡

ምክንያቱም በሰላም ውስጥ ሃይማኖትን መስበክና ማስፋፋት አለ፤ በሰላም ውስጥ ልማት፣ ዕድገትና ብልፅግና አለ፤ በሰላም ውስጥ መቻቻል፣ መከባበርና መተማመን አለ፤ ሰላም ውስጥ መደማመጥና መግባባት አለ፡፡
ስለሆነም በልደተ ክርስቶስ ከተዘመረው መዝሙር የሰማነው ዓቢይ መልእክት “ሰላም በምድር ይሁን” የሚለው ነውና ከሁሉ በላይ ለእርስ በርስ መፋቀርና ለሰላም መጠበቅ ቅድሚያ መስጠት የዘወትር ግዳጃችን ሊሆን ይገባል፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱን ያደረገው በትሑታኑ መኖሪያ ማለትም በእንስሳቱ በረትና በእረኞቹ ሠፈር እንደነበር ልናስታውስ ይገባል (ማቴ. 10፣29-31)
ስለሆነም የእርሱ ደቀመ መዛሙርት የሆን እኛም ከልደቱ መልእክት ትምህርትን ወስደን በዚህ ቀን በጤና፣ በዕውቀት፣ በሀብትና በልዩ ልዩ ምክንያት አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ መንፈሳዊ ድኽነት ከተጫናቸው ወገኖች ጋር አብረን በመዋል፣ አብረን በመመገብና እነርሱን ዘመድ በማድረግ በዓሉን ልናከብር ይገባል፤ (ማቴ.25፣40)፡፡

በመጨረሻም፤

ልደተ ክርስቶስ መለያየትንና ጥላቻን ያስወገደ፤ በምትኩ እግዚአብሔርንና ሰውን በማዋሐድ ለሰው ልጅ አዲስ የድኅነት ምዕራፍን የከፈተ እንደሆነ ሁሉ፣ እኛ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያትም ድህነትን በአጠቃላይ ለመቀነስ የጀመርነው አዲስ የልማትና የዕድገት መርሐ ግብር ከግብ ለማድረስ አሁንም ሌት ተቀን ጠንክረን በመሥራት ሀገራችንን በልማት እንድናሳድግ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ይቀድስ፡፡ አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክኩስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ታኅሣሥ 29 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

 

 

የማቴዎስ ወንጌል

ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት

ታኅሣሥ 23 ቀን 2007 ዓ.ም.

ጌታችን እና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀዳሚት ሰንበት በእርሻ መካከል ባለፈ ጊዜ በጣም ተርበው የነበሩ ደቀመዛሙርት እሸቱን ቀጥፈው እያሹ በሉ፡፡ ፈሪሳውያንም “ሰንበትን ስለ ምን ይሽራሉ?” ብለው ደቀ መዛሙርቱን ከሰሷቸው፡፡ ጌታችን ግን ከሚያውቁት ታሪክ የዳዊትንና የተከታዮችን እንዲሁም የቤተ መቅደሱን አገልጋዮች ታሪክ ጠቅሶ ከነገራቸው በኋላ ‹”ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ ምሕረትን እወዳለሁ፤ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኮነናችሁም ነበር፡፡ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና፡፡” ሲል መለሰላቸው፡፡

 

ይህም በበትረ ርኃብ ይመቱ፣ በረኃብ እንደ ቅጠል ይገረፉ ብላችሁ ባልፈረዳችሁባቸው ነበር፡፡ የሰንበት ጌታዋ ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ ነውና ሲላቸው ነው፡፡

 

ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ፡፡ እጁ የሰለለችውንም ሰው ፈወሰው፡፡ በሰንበት ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? ባሉት ጊዜም በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዷል አላቸው፡፡ ብዙ በሽተኞችንም ፈወሳቸው፤ ሕዝቡ በሥራው ሲደነቅ ፈሪሳውያን ግን “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” ብለው በሰደቡት ጊዜ “ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም፡፡ በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም” ሲል መለሰላቸው፡፡

 

የሰው ልጅ ያለው ራሱን ነው፡፡ ስድብ ያለውም ክህደትን ነው፡፡ ይህም እርሱ ስድብ እንደሚገባው መናገሩ ሳይሆን ለመሰደቡ /ለመካዱ/ ምክንያት ሥጋ መልበሱ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን የሚክዱ ግን ምክንያት የላቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በካዱት ጊዜ ስለሚለያቸው ስለ ኃጢአቱ እንዲጸጸትና ራሱን እንዲወቅስ የሚያደርግ መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ ዮሐ. 16፤8፡፡ “በዚህ ዓለም ቢሆን” ሲል ስለ ኃጢአቱ ተጸጽቶ ወደ ካህኑ በመቅረብ እግዚአብሔር ይፍታህ” ስለማይባል ነው፡፡ “በሚመጣው ዓለም” ሲል ደግሞ በምድር ያልተፈታ በሰማይም ስለማይፈታ ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ደቀመዛሙርቱን በምድርም የምታሥሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፡፡” ብሎ ሥልጣን ሰጥቷቸዋልና፡፡

 

በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን “ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን” ባሉት ጊዜም “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም” ብሏቸዋል፡፡ ቀጥሎም በዮናስ ስብከት ንስሐ የገቡትን የነነዌ ሰዎችን እና በጆሮዋ የሰማችውን የሰሎሞንን ጥበብ በዓይኗ ለማየት በእምነት ወደ ኢየሩሳሌም የገሰገሰችው የኢትዮጵያ ንግሥት /ንግሥት ሳባን/ በዚህ ትውልድ ላይ ይፈርዱበታል ብሏቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚያ በዮናስ ስብከት እና በሰሎሞን ጥበብ አምነዋል፡፡ እነዚህ ግን የዮናስ እና የሰሎሞን ፈጣሪ ቢያስተምራቸው አላመኑምና ነው፡፡

 

የባሰ ነገር እንደሚያጋጥማቸው ሲናገር መንፈስ ርኩስ ሰይጣን በጠበል በጸሎት ከሰው ከተለየ በኋላ ተመልሶ ይመጣል፣ ጸሎቱን ጠበሉን ትቶ ባገኘውም ሰው ላይ ከእሱ የከፉ ሰባት አጋንንትን ይዞ ያድርባቸዋል፡፡ “ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል” ብሏቸዋል፡፡

 

በመጨረሻም ጉባኤ እንዲፈታ የሚወድ ይሁዳ እናትህ እና ወንድሞችህ በውጭ ቆመዋል አለው፡፡ ጌታችንም ለነገረው “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማናቸው?” ሲል መለሰለት፡፡ ወንድሞች የተባሉት አብረውት ያደጉት የዮሴፍ ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህም የእመቤታችን አገልጋይና ጠባቂ አረጋዊው ዮሴፍ ከሞተችው ሚስቱ የወለዳቸው ናቸው፡፡ ይህም፡-

1ኛ/ ከእናት ከአባት ክብር የእግዚአብሔር ክብር እንደሚበልጥ፣

2ኛ/ ከጉባኤ መካከል ጉባኤ አቋርጦ መነሣት እንደማይገባቸው ሲያስተምራቸው ነው፡፡

 

አማኑኤል፥ ጌታ መድኃኒት

ታኅሣሥ 21 ቀን 2007 ዓ.ም.

 

ዲ/ን ታደለ ፈንታው

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ እነሆ ድንግል በድንግልና ትጸንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፡፡/ኢሳ፯፥፲፬/ የሚለው የነቢያት ቃል ፍጻሜውን አገኘ፡፡ይህ ትንቢት የይሁዳ መንግሥት በጦርነት ከበባ ላይ በነበረበት ጊዜ ሁለቱ የሦርያና የእስራኤል ነገሥታት የኢየሩሳሌም ቅጥር ሊያፈርሱ በተነሡበት ጊዜ የተነገረ ትንቢት ነው፡፡

 

ንጉሡ አካዝ በታላቅ ጭንቀት ላይ ነበር፡፡ ከተማዋን ለማዳን ያለ የሌለ ጥበቡን ሊጠቀም አሰበ፡፡ የከበቡትን ወገኖች በውኃ ጥም ያሸንፍ ዘንድ ዋናውን ምንጭ መቆጣጠር ዓይነተኛ መፍትሔ እንደሆነ እቅድ አወጣ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ሁለቱንም ነገሥታት ያጠፋቸዋልና አትፍራ አለው፡፡ አግዚአብሔር ከሰማይ ሠረገላና ሠራዊት ቢልክ እንኳን ይህ ይፈጸማልን) አለው፡፡

 

እግዚአብሔር የንጉሡን እምነት ማነሥ ተመልክቶ ምልክትን እንዲለምን ነገረው፡፡ ከጥልቁ ወይም ከከፍታውም ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትን ለምን አለው፡፡ ፀሐይን ዐሥር ዲግሪ ወደኋላ መመለስ፣ ጨረቃም በመንፈቀ ሌሊት እንዳያበራ ከዋክብትም መንገዳቸውን ይቀይሩ ዘንድ መለመን ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሰማይ ከወረደበትና በሰው ልጆች መካከል ከተመላለሰበት ምስጢር ጋር ቢነጻጸር እዚህ ግባ የሚሉት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አካዝን ያስደሰተህን ሁሉ ጠይቅ አለው፡፡ ጠይቅ የተባለው ምልክት ብቻ ቢሆን ቀላል ነበር፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ የሆነ ስለሆነ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል ተባለ፡፡ ይህ ምልክት ድንግል በድንግልና የወለደችው በቤተ ልሔም ይሁዳ የተወለደ መድኅን ክርስቶስ ጌታ መድኃኒት ነው፡፡

ጌታ መድኃኒት/ሉቃ 2፥፲፩/

ስለመድኅን ክርስቶስ በመላእክት የተነገረው ነገር እጅግ ያስደንቃል፡፡  ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንደሚከተለው ተርኮታል፡፡ « በዚያም ሌሊት መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ወደእነርሱ ቀረበ፤ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትንም ፈሩ፡፡ መልአኩም አላቸው እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡ ይህም ምልክት ይሆንላችኋል ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ፡፡ ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡´/ሉቃ 2፥፰-፲4/

 

ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባውና ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ጌታ መድኃኒት ያለውን ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ኢየሱስ በማለት ጠርቶታል፡፡ ሁለቱም ከመላእክት ሰምተው ነው በዚህ ስም የጠሩት፡፡ ኢየሱስ ማለት ጌታ መድኃኒት እንደሆነ የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ብቻ ሳትሆን በብሉይ ኪዳን ቤተክርስቲያንም ዘንድ ይህ ስም የታወቀ ነበር፡፡  ኢየሱስ የሚለው ስም በብሉይ ኪዳን ቤተክርስቲያን ዘንድ የታወቀ በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን የተለየ ስም ነው፡፡

 

ኢየሱስ የሚለው ስም በአይሁድ ዘንድ የታወቀ እንደነበረ ታሪክ ጸሐፊው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ይናገራል፡፡ በዚህ ስም የሚታወቁ ዐሥራ ሁለት ስሞችን ዘርዝሯል፡፡ አይሁድ ድኅነት ይፈልጉ ጠብቀውም ይሹት እንደነበረ ከስም አወጣጣቸው ይታወቃል፡፡ ልጆቻቸውን መድኃኒት በማለት ጠርተዋቸዋል፡፡ ምንም እንኳን የመሲሑን መምጣት ትንቢት የተናገሩ ከወገኖቻቸው ከአይሁድ ብዙዎችን ያለፉ ቢሆኑም እውነተኛ መድኃኒት ግን አልነበሩም፡፡ እውነተኛው መድኃኒት « በሥጋ ከዳዊት ዘር ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው እንደ ቅድስና መንፈስ በኃይል የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ሆኖ የተገለጠው/ሮሜ 1፥4/´ መድኅን ክርስቶስ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡

 

በብሉይ ኪዳን ዘመን ለምሳሌ ኢያሱ ማለት መድኃኒት ማለት ነበር፡፡ በዚህ ስም የተጠሩ ሁሉ ስሙ እንጂ አማናዊ የሆነው ኃይሉ በእነርሱ ዘንድ አልነበረም፡፡ አማናዊ ኃይል ያለው እውነተኛው መድኃኒት በተገለጠ ጊዜ ይህን ስም ብቻውን ይጠራበታል፡፡ የነገር ጥላው አማናዊ በሆነው ነገር ተተክቷልና «እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል´/ዮሐ፫፥፴/ የሚለውን የመጥምቁን ቃል ልብ ይሏል፡፡ እርሱ ብቻ ልዑል፥ መድኃኒት ነው፤ ሕዝቡንም ከኃጢአታቸው ፈጽሞ የሚያድናቸው ነው፡፡/ማቴ ፩፥፳፩/
ሌሎች መድኃኒት ተብለው ቢጠሩ የሰው ልጆችን ከዘላለማዊ ሞት መታደግ አልተቻላቸውም፡፡ ስለኃጢአታቸውም ተገብተው ደማቸውን አላፈሱላቸውም፡፡ እርግጥ ነው በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ብዙ ቅዱሳን አጥንታቸውን ከስክሰዋል ደማቸውን አፍስሰዋል ለሕዝቡ ግን እውነተኛ ድኅነትን ማምጣት አልተቻላቸውም፡፡ እርሱ ግን እውነተኛ መድኃነት ጌታም ነው፡፡

 

ኢየሱስ የሚለው ስም ሊሠራ ያለውን የጽድቅ ሥራ ፈጽሞ ያሣየ ነው፡፡

 ስም ግብርን ይገልጣልና መልአኩ « እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ´/ማቴ ፩፥፳፩/ በማለት እንደተናገረው ስሙ እንዲሁ ሆነ፡፡ እንደገናም ስሙ ክርስቶስ ነው፡፡ መሲሕ ማለት ነው፡፡ አዳኝ መድኃኒት የሚለው ስሙ ግብሩን ሰው የሆነበትን ፣በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የታየበትንም ምስጢር ይገልጣል፡፡ ለሰው ልጆች ድኅነት ያስፈለጋቸው ከኃጢአታቸው የተነሣ ነው፡፡ ኃጢአትን ባይሠሩ መድኃኒት ባላስፈለጋቸው ነበር፡፡ ኢየሱስ የሚለው የአምላካችንም ስም በምድር ላይ የታወቀ ባልሆነ ነበር፡፡ እንዲህ የሚለው የወንጌል ቃል የታመነ ነው፡-« ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደአባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ´/ገላ ፩/ ከዚህ ክፉ ዓለም ከኃጢአት ነፃ ያወጣን ዘንድ መሞት ነበረበት ለመሞት ደግሞ መወለዱ የግድ ነው፡፡ እኛን ሊያክል እኛን ሊመስል በእኛ ጎስቋላ ሥጋ ይገለጥ ዘንድ ይገባው ነበርና፡፡ኃጢአት ገዳይ መርዝ ነው፤ ነገር ግን መድኅን ክርስቶስ አሸንፎታል፡፡

 

ስለዚህ ከመድኅን ክርስቶስ ጋር ላለን ግንኙነት መሠረቱ ጽድቃችን ሳይሆን መርገማችን፥ መልካምነታችን ሳይሆን ክፋታችን ፥ መቆማችን ሳይሆን ውድቀታችን ነው፡፡ በተጎበኘንም ጊዜ በእኛ ዘንድ የተገኘው በጎነት ሳይሆን ክፋት ጽድቅ ሳይሆን ኃጢአት፥ ጸጋ ሳይሆን ከንቱነት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደዚህ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነ ነው ይላል፡፡ ሐዋርያው ይሄን ሲል ከኃጢአት ቅጣት ሊታደገን እንደመጣ ያመለክታል፡፡ምንም እንኳን አእምሮአችን በኃጢአት ምክንያት ቢበላሽም ልቡናችን ቢጨልምም በኃጢአት ምክንያት ምውት ብንሆንም ክፋትን አስወግዶ በጎነትን ይሰጠን ዘንድ፥ ኃጢአትን አስወግዶ ጽድቅን ያለብሰን ዘንድ፥ የጨለመውን ልባችን በፍቅሩ ብርሃን ያበራልን ዘንድ፥ የሕያው የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ፡፡ በበረት ተወለደ፥ አድግና ላህም ትንፋሻቸውን ገበሩለት፥ የዐሥራ ዐምስት ዓመት ብላቴና ወሰነችው፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት በእርግጥም ያስደንቃል፡፡

የጌታ ሰው መሆን በጊዜው ጊዜ የተፈጸመ ነው

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይሄንን የክርስቶስን የቸርነት ሥራ እንዲህ በማለት በማያሻማ ቃል የገለጠው ነው፡- «ወአመ በጽሐ ጊዜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ዘተወልደ እምብእሲት የዘመኑ መጨረሻ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ወደ ዓለም ላከ´/ገላ ፬፥4/ በእርግጥም አበው ሰማያትን ቀድደህ ምነው ብትወርድ ፥ ተራሮች ምነው ቢናወጡ፤እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፥ አሕዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ፡፡ ያልተጠባበቅነውን የጽድቅ ሥራህን በገለጥህ ጊዜ ወረድህ፥ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ፡፡ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም፤ ዓይንም አላየችም፡፡/ኢሳ ፶፫፥፩-፬/ በማለት የመሰከሩለት በተስፋ የጠበቁት ትንቢት የተናገሩለት ሱባኤ የቆጠሩለት አምላክ የዘመኑ መጨረሻ በደረሰ ጊዜ ተገለጠ፡፡

 

ዓለሙ ያለ እርሱ ጨለማ ነበረ፡፡ በኃጢአትም የተያዘ፤ በኃጢአት ፈጽመን የተያዝን ከሆንን እምነት አይገኝብንም፡፡ የብሉይ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ስለዚህ ቀን ብዙ ጮኸች፡፡ ስለዚህ ቀን ደስታ ብዙ መከራን ተቀበለች፤ ትንቢት አናገረች፤ ሱባኤ አስቆጠረች፡፡ መድኀኒታችን ግን በጊዜው እንጂ ያለጊዜው አልመጣም፡፡ «ሳሕሉ ለእግዚአብሔር በጊዜሁ´ በማለት ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረ፡፡ በእኛም ሕይወት እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር የቸርነት፣ የምሕረት ሥራውን የሚሠራው በጊዜው እንጂ ያለጊዜው አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህንን ጊዜ በቅዳሴው በሰዓታቱ በኪዳን ጸሎቱ፣ በጸበሉ፣በጾሙ እያራራች ወደ አምላካችን እንድንቀርብ እያበረታታች ጊዜውን እንድንጠብቅ የምታደርገን፡፡ ጌታችን ከጊዜው ቀድሞ ከጊዜውም ዘግይቶ አይመጣም፤ በጊዜው ጊዜ እንጂ፡፡ እርሱ ፈጽሞ ቀጠሮ አክባሪ ነው፡፡ ሰው የሆነው በፍጹም ቀጠሮው ጊዜ ነው፡፡ ጊዜው ረዘመ ብሎ አይዘነጋም፡፡

 

የጌታ ሰው መሆን ትንቢት የተነገረለት ሱባኤ የተቆጠረለት እንጂ እንዲሁ በድንገት የተከናወነ እንዳልሆነ እንመለከታለን፡፡ ብሉይ ኪዳን ይሄንን የሚመለከቱ ትንቢታትን የተመላ ነው፡፡ የሚወለድበት ሥፍራ፣ የሚወለድበት ጊዜ ፣የአወላለዱ ጠባይ አስቀድሞ የተነገረ ነው፡፡ ክርስቶስ በወሰነው ጊዜ በዚህ ዓለም ተገለጠ፤ የሆነው በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሆነ ነው፡፡ ሁሉን የሚያውቅ ጌታ የማንኛውንም ድርጊት ጌዜ እርሱ ወስኖታል፡፤ በሕይወታችን የሚከሰተው ማንኛውም ነገር በእርሱ ፈቃድ የሚከናወን በእርሱ ዘንድ ጊዜውም አስቀድሞ የታወቀ ነው፡፡ አንድም ነገር ያለጊዜው አይሆንም ከጊዜውም አንዲት ሴኮንድ እንኳን አይዘገይም፡፡ ፈቃዱ በተወሰነለት ጊዜ ይከናወናል ሊያፈጥነውም ሊያዘገየውም የሚቻለው ወገን የለም፡፡

የክርስቶስ ሰው መሆን ፍርሐትን ያራቀ ነው፡፡

 የጌታ መልአክ ለእረኞች እንዲህ አላቸው፡-« እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ሆነ ተወልዶላችኋልና´/ሉቃ 2፥፲/ መልአኩ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ምስራች አለ እንጂ ወንድ ሴት፣ ጥቁር ነጭ፣ ባሪያ ጨዋ አይሁዳዊ የግሪክ ሰው አላለም ፡፡ ዘር ነገድ ጎሳ አልተመረጠበትም፤ ጥሪው የተላለፈው ለሁሉም ነው፡፡ ምስራች ዜናው ለሕዝብም ለአሕዛብም ነው ለተቀበሉት ሁሉ የተደረገ ነው፡፡ መልአኩ እረኞችን አትፍሩ አላቸው፡፡እረኞች ወገን ከሆንን ያስፈራን ምንድነው) በኃጢአት መያዛችን አይደለምን፡፡ ስለዚህ ኃጢአታችን ያስወግድልን ዘንድ በርግጥ ሰው ሆነ፡፡ ስለዚህ ምን ያስፈራናል አምላካችን በመካከላችን ሳለ፡፡ አሁን ጌታ ተወልዶአልና ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው፡፡

 

አማኑኤል በመካከላችን የሆነ ብቻ አይደለም ሰውን ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ የሰውን ባሕርይ ባሕርዩ ያደረገ ጭምር ነው እንጂ፡፡ አሁን አንድ ነገር እናውቃለን እግዚአብሔርን የሚያስቸግረው የኃጢአታችን ብዛት አይደለም ወደእርሱ ለመቅረብ የተከፈለልን ዋጋ ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናችን እንጂ፡፡ የተወለደው ሁሉን የሚችለው አምላክ ነው፡፡ ለዘላለም በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድም እኛ ወደሰማይ መውጣት አለዚያም እግዚአብሔር እኛ ወደአለንበት ስፍራ መውረድ ነበረበት፡፡ ከዚህ ውጪ ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበት ዕድል የለም፡፡ እኛ ወደ እርሱ ዘንድ መውጣት እንዳልተቻልን በተመለከተ ጊዜ እግዚአብሔር ይፈልገን ዘንድ እኛ ወደ አለንበት ስፍራ መጣ፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ያስደንቃል፡፡

 

መላእክት ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን የምስራች ያሉት ቅዱስ ወንጌልን ነው፡፡ ክርስቶስ እግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ወንጌል የሚባል ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ከጌታ ልደት አስቀድሞ ነቢያት ነበሩ፤ ነገር ግን እነዚህ ነቢያት እውነትን መመስከራቸው ብቻ ዓለም ከኃጢአት እስራት እንዲፈታ አላስቻለውም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለዓለሙ የሆነውን የምስራች እንዲያበስሩ የላካቸው ቅዱሳን መላእክት ጦር የታጠቁ ደገር የነቀነቁ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን የሰላም ምልክት በሕፃኑ እጅ በበረት/በከብቶች ግርግም/ የተያዘ ነበር፡፡ ሰዎች እንደጠበቁት በነገሥታት እልፍኝ የተከናወነ አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ ራሱን ዝቅ አድርጎ ትሑት ሆኖ መጣ፡፡

 

አስቀድመን እንደተናገርነው ወደ ምስራቹ ቃል የቀረቡ ትጉ፣ ያላንቀላፉ፣ መንጋቸውን በጥንቃቄ ሲጠብቁ የነበሩ እረኞች መድኅን ክርስቶስን ያገኙት በበረት ነው፡፡ የተጠቀለለው በሐር ጨርቅ አልነበረም፡፡ ምድራውያን ነገሥታት ከሚደፉት ዘውድ አንዱን እንኳን አልደፋም የሰማይና የምድር ንጉሥ ሆኖ ሳለ፡፡ እንደ ድኃ የተጠቀለለው በጨርቅ ነው፡፡ የእናቱ ትሕትና ያስደንቃል፡፡ እናንተ ድኆች ሆይ ደስ ይበላችሁ ሀብታም ሳለ ክርስቶስ ስለእናንተ ደኃ ሆኗልና፡፡ እናንተ መሳፍንቶች የምድር ነገሥታት ሆይ ትውልዱ ሰማያዊ የሆነውን ተመልከቱት! በእንግዶች ማረፊያ እንዳልተገኘለት ተመልከቱ! የሰው ልጆች ሆይ እነሆ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ /ወልደ አብ ወልደ ማርያም/ አጥንቱ ከአጥንታችሁ ስጋው ከስጋችሁ የሆነ ዝቅ ዝቅ ያለበትን መጠን ተመልከቱ! ክርስቶስ የድኆች፣ የማይጠቅሙ የተናቁ ወገኖች ባልንጀራ ሆነ፤ ከቀራጮች ጋር ተመገበ፡፡
 

የክርስቶስ ልደት የደስታ ምንጭ ነው፡፡

የጌታ መልአክ ለእረኞቹ አላቸው« እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና፡፡/ሉቃ 2፥፲/ በርግጥም የጌታ መልአክ ቃል ለሕዝቡ ሁሉ የደስታ ምንጭ እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ መድኃኒት ተወልዶላችኋልና፡፡ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ የሆነ መድኃኒትን፡፡ በርግጥ የነፍሱን ሐኪም ሲያገኝ ደስታው ፍጹም የማይሆንለት ማነው) በኃጢአት እስር ቤት ያላችሁ ነፃ ሊያወጣችሁ መጥቷል፡፡ ቤተ ልሔም እውነተኛ የእንጀራ ቤት ሆነች፡፡ ቅዱሳኑ ሁሉ ደስ ይበላችሁ ስትጠብቁት የነበረ ተስፋ በእርግጥ እውን ሆኗልና፡፡ ደስታው በእረኞች ዘንድ ተጀመረ፤ ሕዝብና አሕዛብን አዳረሰ፡፡

 

የክርስቶስ መወለድ መላእክትን ያስደነቀ ነው፡፡

መላእክት በታች/በምድር/ በበረት በላይ/በሰማያት/ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ቢመለከቱት አደነቁ፡፡ « እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡´/ሉቃ 2፥፲፬/ መላእክት የጌታን ልደት እንዴት አስቀድመው እንደሰሙ አናውቅም፤ ነገር ግን የጌታ መወለድ ዜና በሰማያውያን ዘንድ በደረሰ ጊዜ ምን ዓይነት መደነቅ እንደሚፈጠር መገመት እንችላለን፡፡

 

በርግጥም የማይወሰነው ተወስኖ መላእክት ሊያዩት የሚመኙት አምላክ የትሕትናን ሸማ ተጎናጽፎ በበረት መገኘት እጅግ ያስደንቃል፡፡ የጌታ ሕይወቱን ግርፋቱን ሞቱን ሲመለከቱ ምን ያህል ይደነቁ! በርግጥም ለዘመናት ተሰውሮ የነበረውን ይሔንን ታላቅ ምስጢር ተመልክቶ ሊደነቅ የማይችል ማን ይኖራል) ወደ ምድር በመጡና ወደ ቤተልሔም በቀረቡ ጊዜ ከሰው ልጆች ጋር በአንድነት ዘመሩ፡፡ ዘላለማዊው ሕፃን ሆኖ ዘመን ሲቆጠርለት አደነቁ፤ ፍጥረታትን የተሸከመ እርሱ በእናቱ ጀርባ ታዝለ ፡፡

 

ፍጥረታትን የሚመግብ እርሱ የእናቱን ጡት ተመገበ፡፡ ሁሉን በቃሉ የፈጠረ እርሱ ፍጥረታትንም የተሸከመ ደካማ ስጋን ባሕርዩ አድርጎ እናቱ ተሸከመችው፡፡ በሕፃን መጠንም ተወለደ፡፡ የነገሥታት ንጉሥ መሆኑን የምትገነዘቡ ወገኖች አድንቁ! ደኃ ሆኖ ትመለከቱታላችሁ፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ በማለት ያደንቃል፡- « የዕብራውያን ጌታ ከዕብራዊት ድንግል ተወለደ፥ ሐዋርያቱን በሰባ ሁለት ቋንቋ ያናገረ፥በሰናዖር የአሕዛብን ቋንቋ የተበተነ ቋንቋ እንደማያውቅ ሰው እናቱ በምትናገርበት ልሳን የዕብራውያንን ቋንቋ አፉን ፈታ፤ ይህንንም ቋንቋ እየተናገረ አደገ´፡፡

 

አዲስ የተወለደው ንጉሥ ወዴት ተኛ) የወርቅ ፍራሽ ከዝሆን ጥርስ የተሠራ አልጋ ተዘጋጀለትን) በቄሣሮች ቤተ መንግሥት የተሻለ ክፍል ሰጡትን) አይደለም፡፡ መድኅን ክርስቶስ የተኛው በከብቶች ግርግም ነው፡፡ ከብቶች በሚመገቡት በረት ንጉሡ ክርስቶስ ተኛ፡፡ ክፉ ሰዎች በረትም ማደሪያ ሆኖ ረጅም ጊዜ በዚያ ይቀመጥ ዘንድ አልፈቀዱለትም፡፡ ክፉ ሰዎች እነርሱ ባማረ ቤት ባማረ ኑሮ እየኖሩ ዕረፍት የሚነሣቸው የድሆች ተረጋግቶ መቀመጥ ነው፤ እነርሱን ሳያሳድዱ ወይም ጨርሰው ሳያጠፉ እንቅልፍ የላቸውም፡፡ አይሁድ በጌታ ላይ የፈጸሙት ተመሣሣይ ነገርን ነው፡፡ እናቱ ሕፃኑን ይዛ ወደ ግብፅ ተሰደደች፡፡ በእንግድነት አገር እንግዳ ሆነ፡፡ ከስደት ከተመለሰ በኋላ በናዝሬት አደገ፡፡ መላእክት በዚህ ሁሉ ነገር የሚደነቁ አይመስላችሁም አሳዳጁ ሲሳደድ የትሕትናውን ወሰን ተመልከቱ!
 

የክርስቶስ መወለድ የሰው ልጆች ሁሉ አድናቆት ነው፡፡

መላእክት በጌታ ልደት ከተደነቁ የሰው ልጆችማ በዚህ ታላቅ ምስጢር ምን ያህል እጹብ እጹብ ማለት ይገባቸው ይሆን) እግዚአብሔር የበደሉ የሰው ልጆች ቃሌን ተላልፈዋልና እንደወጡ ይቅሩ ይጥፉ አላለም፡፡ ለድኅነታቸው የሚሆን አስደናቂ የድኅነት መንገድን አዘጋጀ፡፡ የማዳን ሥራውን እርሱ የሚፈጽመው እንጂ ለፍጡር የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ፍጡር ይህን ማድረግ የሚቻለው አይደለምና፡፡ ስለዚህም ነው የሰው ልጅ አምላክ በሆነ በክርስቶስ ደም እንጂ በፍጡር ደም ሊድን ያልተቻለው፡፡ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስ፡፡ «እኛ በጸጋ አማልክት ነን ክርስቶስን ከባሕርይ አምላክነት የሚያሳንስ አንዳችም ነገር አውርዶ ከእኛ ጋር ስለሚያስተካክለው አዳኛችን መሆን አይቻለውም´ ይላል፡፡

 

ስለዚህ ጌታና መድኃኒት ንጉሥም የሆነ እርሱ ተበድሎ እርሱ የሚክስ ሆነ፡፡ ይኼንን ማድረግ የሚቻለው ከእርሱ በቀር ሌላ ስለሌለ አምላክ ስጋን ተዋሓደ፡፡ በርግጥ ራሳችንን ብንመረምር እግዚአብሔር ይሄንን ያህል ይወድደን ዘንድ ራሱንም ለመስቀል ላይ ሞት አሳልፎ ይሰጥልን ዘንድ የሚያደርግ አንዳች ነገር በእኛ ላይ እንደሌለ ትገነዘባላችሁ፡፡ እግዚአብሔር አብዝቶ ቢጠራን አጥብቀን ከፊቱ የሸሸን ወገኖች ነን፡፡/ሆሴ፲፩፥፩/

 

የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን!

የጎንደር ማዕከል 2ኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አካሄደ

 

 

 

ታኅሣሥ 4 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ /ከጎንደር ማእከል/

 

 

በማኅበረ ቅዱሳን የጎንደር ማእከል ሁለተኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በጥንታዊው ደብረ ገነት ባሕሪ ግንብ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 28 ቀን 2007 ዓ.ም አካሄደ፡፡

በመርሐ ግብሩ የማኅበሩ መልእክት በአቶ አማረ አበበ የሰሜን ምዕራብ ማዕከል ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊ፣ ትምህርተ ወንጌል በዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ መዝሙር በማእከሉ መዘምራን ቀርቧል፡፡

ከስዓት በኋላ በቀጠለው መርሐ ግብር ገዳማውያን አባቶች አባ ኃይለ ሚካኤል የማን እንደ አባ አቡነ ያሳይ ገዳም መነኩሴ እና አባ ገብረ ዋሕድ የዋልድባ ገዳም ቤተ ሚናስ አበምኔት መንፈሳዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በአብርሐም ቤት እንግዳም ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ የሕይወት ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

ምን እንጠይቅልዎ በተሰኘው መርሐ ግብርም በነገረ ክርስቶስ እና በነገረ ማርያም ዙሪያ ጥያቄዎች ተነስተው በመልአከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መልስ ተሰጥቷል፡፡ በመጨረሻም በአበራ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ጉባኤ ቤት መምህር ቅኔ ቀርቧል፡፡

በመርሐ ግብሩ ከ1800 በላይ ምእመናን የተሳተፉ ሲሆን፤ በጎንደር ፋና ኤፍ ኤም 98.1 ሬድዮ ጣቢያ ከጉባኤው በፊትና በኋላ የዘገባ ሽፋን አግኝቷል

 

የደሴ ማዕከል ግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ክፍል “መራኄ ፍኖት” የአንድነት የጉዞ መርሐ ግብር አካሔደ

ታኅሣሥ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ከደሴ ማእከል

 የደሴ ማዕከል ግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ክፍል እስከ ዛሬ ከተለመደዉና ግቢ ጉባኤያት ከሚያደርጉት ጉዞ ለየት ባለ መልኩ ደሴና ኮምቦልቻ የሚገኙ 9 ግቢ ጉባኤያትን፣ የደሴ ወረዳ ማዕከል አባላትን፣ አባቶችን እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትን በአንድነት ያሳተፈ መራኄ ፍኖት የግቢ ጉባኤያት የአንድነት የጉዞ መርሐግብር ኅዳር 14 ቀን 2007 ዓ.ም በደብረ ነጎድጓድ ሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ገዳም አካሄደ፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ 1359 የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና ከ70 በላይ የማዕከሉ አባላት፣ አባቶች እና በደሴ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ሥር ካሉ ሰንበት ትቤቶች የተዉጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

መርሐ ግብሩ በአባቶች ጸሎት ተጀምሮ በግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ያሬዳዊ ዝማሬ፤ በቦሩ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መምህር አካለወልድ እና በመምህር ኃ/ማርያም ዘዉዱ ወደ ቅዱሳት መካናት ስንጓዝ ምን ማድረግ እንደሚገባ እና እንዲሁም የመንፈሳዊ ጉዞን ዓላማ መሠረት ያደረገ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ከደሴ ከተማ ከሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተጋብዘው በመጡ  መዘምራንም መዝሙር ቀርቧል፡፡

 

የተሳታፊዎችን ቀልብ የሳበዉ ሌላዉ መርሐ ግብር ምክረ አበዉ ሲሆን፤ “ወጣትነትና መንፈሳዊ ሕይወት” በሚል ርዕስ ቆሞስ አባ ኤልያስ ታደሰ፤ መ/ር ኃይለማርያም ዘዉዱ፣ ቀሲስ ጸጋዉ እና መሪጌታ ገብረ ማርያም በጋራ በመሆን በተለይ የወጣቱን ዝንባሌ በማገናዘብ ግቢ ጉባኤያትና ወጣትነት፣ ኦርቶዶክሳዊ  ወጣት ምን መምሰል አለበት፣ ስልጣኔ እና ሃይማኖት፤ እንዲሁም ሃይማኖትና ፍልስፍና በሚሉ ርእሶች ሰፋ ያለ ትምህርተ ሃይማኖትና አባታዊ ምክር ሰጥተዋል፡፡

 

የማዕከሉ የበገና ድርደራ ሠልጣኞች የበገና መዝሙር በማቅረብ ከተማሪዎች የተሰበሰቡ የተለያዩ ጥያቄዎች በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ እንዲሁም በ2006 ዓ.ም በወሎ ዩኒቨርስቲ ደሴ ካምፓስ ግቢ ጉባኤ ሰብሳቢ የነበረዉና የዋንጫና የሜዳሊያ ተሸላሚው ዲ/ን ቶሎሳ ታዬ፤ እንዲሁም በ2006 ዓ.ም የዚሁ ግቢ ጉባኤ ጸሐፊ የነበረችዉ ተማሪ የሺ ሀብተ ሥላሴ ልምዳቸዉንና ተሞክሯቸዉን  ለተሳታፊዎች አካፍለዋል፡፡ በደሴ ደብረ መዊዕ ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና ቅዱስ መርቆሪዎስ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር በመሪጌታ ዳዊት አስማረ ቅኔ ቀርቧል፡፡
 

 

ለአብነት ደቀመዛሙርት የሕክምና አገልግሎትና የጤና አጠባበቅ ሥልጠና ተሰጠ

ታኅሣሥ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዲ/ን ደስታ ይዲ/ትባረክ /ከወልድያ ማዕከል/

በማኅበረ ቅዱሳን የወልድያ ወረዳ ማዕከል ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ኅዳር 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በምሥራቀ ፀሐይ ወይብላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም ጉባኤ ቤት የአቋቋም ትምህርት በመማር ላይ ለሚገኙ ሃምሳ የአብነት ትምህርት ደቀመዛሙርት የሕክምና አገልግሎት፣ የጤና አጠባበቅ ሥልጠና እና የመጸዳጃ ቁሳቁሶች  ድጋፍ አደረገ፡፡

 

በዕለቱ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በስፍራው በመገኘት ለደቀመዛሙርቱ ትምህርተ ወንጌል በወልድያ ማእከል ጸሐፊ ዲያቆን ቃለ ጽድቅ ካሳ ማኅበረ ቅዱሳን የሚያደርገውን ድጋፍ እና አገልግሎት በማስመልከት “የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለትውልዱ ይዳረስ ዘንድ የእናንተ ደኅንነት መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎቱ ዋና ትኩረት አድርጎ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ የወረዳ ማእከሉ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል የተለያዩ የሕክምና ባለሞያ አባላቱን በማስተባበር ይህን ስልጠና ለእናንተ አዘጋጅቷል፡፡ ምንም እናንተ ቃለ እግዚአብሔርን ያወቃችሁ ብትሆኑም ዘመኑን እየዋጀን ራሳችንን ልንጠብቅ እና ክርስትናችንን ልናጸና ስለሚገባ ሥልጠናው ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡

 

ደቀመዛሙርቱ በጉባኤ ቤቱ በሚማሩበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በዋነኛነትም በተለያየ ምክንያት ከሥነ ምግባር ውጭ በመሆን ከምእመናን ጋር ያላቸውን ግንኙነትም ሆነ የትምህርት ቆይታቸውን ከሚያሰናክሉ ነገሮች ተቆጥበው የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናክሩ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት ተደርጓል፡፡

 

በወረዳ ማእከሉ የሚገኙ የማኅበረሰብ ጤና አጠባበቅ፣ የዓይን፣ የሥነ ልቦና፣ የውስጥ ደዌ ሕክምና ባለሞያዎችን በማስተባበር ለደቀመዛሙርቱ ስለ ግል እና አካባቢ ንጽሕና፣ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተላላፊ በሽታዎች ትምህርት ተስጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም የዓይን፤ የሥነ ልቦና፣ የውስጥ ደዌ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው የሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ የልብስና የገላ ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለሁሉም ደቀመዛሙርት በማከፋፈል፤ ለሆድ ውስጥ ሕመም የሚሆን መድኃኒት እንዲወስዱም ተደርጓል፡፡

 

ደቀመዛሙርቱም ትምህርተ ወንጌል እርስ በእርስ ለመማማር እና የስብከት ዘዴን ለማጠናከር የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ክፍሉም ከሚመለከታቸው አካላትና ከማኅበሩ አባላት ጋር በመሆን ለጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚሰጥ ተገልጾላቸዋል፡፡

 

በተጨማሪም ለመጠለያ ቤት ግንባታ ፕሮጀት የወረዳ ማእከሉ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል እንቅስቃሴ እንደሚያካሂድና ለመጸዳጃ ቤት መስሪያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን እንደሚያቀርብም ተገልጿል፡፡

 

የጉባኤ ቤቱ የአቋቋም መምህር መሪጌታ ሀብተ ማርያም በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት “ማኅበሩን ከዚህ በፊት በሚሠራው ተግባር አውቀዋለሁ፡፡ በርካታ ፈተናዎችን እያለፈ ተስፋ ባለመቁረጥ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲህ መፋጠኑ ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡ ዛሬም በዚህ ጉባኤ ቤት ላለን ይህን የመሰለ ሥልጠና እና የሕክምና አገልግሎት መስጠቱ የቤተ ክርስቲያንን ትንሣኤ የሚናፍቅ እና ለቤተ ክርስቲያን ጥብቅና የቆመ መሆኑን ያስገነዝበናል እና ተማሪዎቼም ብትሆኑ ይህን ልትገነዘቡ ይገባል፡፡ ከዚህ በተለየ በርካታ ችግሮች ስላሉብን ወደፊት ማኅበሩ አይዟችሁ እያለ ከጎናችን እንዳይለየን” ብለዋል፡

“ስለ ሃይማኖታችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ዘብ የምንቆምበት ወቅት አሁን ነው”

/ብፁዕ አቡነ ሉቃስ/

ኅዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም.

abune lukas 01የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ከገጠሟት ልዩ ልዩ ፈተናዎች ይልቅ በዚህኛው ትውልድ የደረሰባት ፈተና (ሙስናና ብልሹ አሠራር፤ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በውጭ ካሉ አባቶች ጋር ያልተቋጨው ዕርቀ ሰላም) ወደ ፊት እንዳትራመድ አድርጓታል፡፡ በእርግጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ችግሮች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ችግሮችን ከማውራት ይልቅ መፍትሔው ላይ ማተኮር ለቤተ ክርስቲያኒቱም ለመንጋውም ጠቃሚ ስለሚሆን ነው እንጂ፡፡

 

በዚህ ሒደት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች በጥልቀት እየተወያየ መፍታሔ የሚሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው ጥቅምት 2007 ዓ.ም ባካሔደው ጉባኤ ብዙ ደስ የሚያሰኙ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ይህንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክተን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የሠላሳ ሦስተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቅዱስ ሲኖዶስ እይታ ምን ይመስል ነበር?

የሠላሳ ሦስተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በአህጉረ ስብከት፣ በድርጅቶች፣ በልማት ተቋማት ከፍተኛ ለውጥ የታየበት፣ በማኅበራዊና በሰብአዊ እንቅስቃሴም መልካም ነገሮች የታየበት ነው፡፡ ዕድገት ነበረው፤ ለውጥ ነበረው፡፡ ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ አላስፈላጊ የሆኑ ጎኖች ነበሩት፡፡ ይህም ጥቂት የሚባሉ ታዛቢ ግለሰቦች የፈጠሩት ሁካታ፤ አግባብነት የሌለው ጥያቄ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ክፍተት እንደ እጥረት በማየት እርምት እንዲሰጥ በምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

 

ወደፊትም እንዲህ አይነት ችግር እንዳይፈጠር ቃለ ዐዋዲው፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በሚያዘው መሠረት ጉባኤው የሚመለከታቸው ተሳታፊዎችና ታዛቢዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው እንዲቀመጡ ይሆናል፡፡ በጋራ መግለጫው የተወሰኑትንና ቅዱስ ሲኖዶስ እርምት እንዲሰጥባቸው የወሰነባቸውን ተግባራት መፈጸምና አለመፈጸማቸውን ክትትል የሚያደርጉ ቋሚ ሲኖዶስ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የአህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ጊዜ ወስዶ በጥልቀት የተወያየባቸው ነጥቦች ምን ምን ናቸው?


የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የውይይት አጀንዳዎች አጠቃላይ 21 ነበሩ፡፡ በውይይቱ ወቅት ሰፊ ጊዜ የወሰደው አንደኛው አጀንዳ የተረቀቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ መወያያ አሳቡም ሊቃነ ጳጳሳቱ ተጠሪነታቸው ለማን ይሁን የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡ የፊተኛው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ሲኖዶስ ይላል፡፡ አሁን ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ ተጠሪነታቸው ለፓትርያርኩና ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚል አሳብ ተነሥቶ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሐዋርያት ተጠሪነታቸው ለአንዱ እግዚአብሔር ነው፡፡ የጉባኤው መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በፊትም አሁንም ሊቃነ ጳጳሳቱን የሚሾመው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ስለዚህ የሊቃነ ጳጳሳት ተጠሪነት በፊት በነበረው እንዲቀጥል በአንድ ድምፅ ተስማምተዋል፡፡

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሊቃነ ጳጳሳት ዝውውርም ተነሥቷል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳትን ማዘዋወር የሚችለው ቋሚ ሲኖዶሱ መሆን እንዳለበት ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡ ለሃይማኖት፣ ለሥርዓት፣ ለምእመናንና ለሀገሪቱ የሚጠቅሙ ብዙ አሳቦች በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

 

ሁለተኛው የማኅበራት ጉዳይ ነው፡፡ በልዩ ልዩ አገልግሎቶች በማኅበር ስም ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ማኅበራት በምን መልኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሥር ይሁኑ በሚለው ምልዓተ ጉባኤው በስፋት ተወያይቷል፡፡ እገሌ ጥሩ ነው እገሌ መጥፎ ነው የተባለ ማኅበር የለም፡፡ ልጆቻችን ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ጠቃሚዎች ናቸው፤ መጀመሪያ ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን ያስፈላጓታል በማለት ደስ ደስ የሚሉ አሳቦች ተነሥተዋል፡፡ በዚህም የልጆቻችን አገልግሎት ጠቃሚ እንደሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በደንብ አምኖበታል፡፡

 

ልጆቻችንን ማቅረብና መውደድ እንደሚገባም ሁሉም ተስማምቷል፡፡ ስለዚህ ማኅበራት በሙሉ ተጠሪነታቸው ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ገቢያቸውንና ወጭያቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱ በምትጠቀማቸው ሞዴላ ሞዴሎች እንዲጠቀሙ ተወስኗል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንስ?


በማኅበረ ቅዱሳንም ላይ የተለየ አቋም የለም፡፡ ልጆቻችን፤ አገልግሎታቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን እያሳየ ያለው ተግባር ጠቃሚ ነው፤ ገደማትን፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች ልማቶችን በተመለከተ ማንኛውንም ሥራ በአጋርነት እየሠራ ያለ ትልቅ ማኅበር መሆኑን ምልዓተ ጉባኤው አምኗል፡፡ እንዲያውም ምሁራን ያሉበት፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሃይማኖት፣ ለሥርዓት፣ ለሀገር፣ ለልማት የሚጠቅሙ ሰዎች ያሉበት ነው የሚሉ ትልልቅ አሳቦች ተነሥተዋል፡፡ ወደ ፊትም የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ሆኖ እንደሚቀጥል ታምኖበታል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ምልዓተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ በዚህ መልክ ነው የተረዳው፡፡ ለአሁኑ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆኖ ተጠሪነቱ ግን ለማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ቁጥጥሩን፣ ግምገማውንና ክትትሉን የሚያደርገው ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው፡፡

የማኅበራት ሕግ ሲወጣም እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉት ማኅበራት ክፍል “ሀ”፣ ሌሎች ማኅበራት ክፍል “ለ” በሚል አደረጃጀት ሥርዓት እንዲይዝ ይደረጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ገንዘቡን በቤተ ክርስቲያኒቱ ሞዴላ ሞዴሎች እየተጠቀመ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል በሚል ተወስኗል፡፡ ገንዘቡ ለምን ለምን አገልግሎት እንደ ዋለ መከታተል እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣ የለም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት አይቶ በስፋት ተመልክቶ አስደሳች በሆነ መልኩ የወሰነው ይኼን ነው፡፡

 

ሌላው ስለ ሰላም ነው፡፡ ያለ ሰላም እግዚአብሔርን ማየት አይቻልም እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ በውጭ ያለው ዕርቀ ሰላም እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡ ዝርዝር ሁኔታው ወደፊት የሚወሰን ይሆናል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳዎች 21 ሆነው ሳለ በመግለጫው ግን 9ኙ ብቻ ነበር እንዲካተቱ የተደረገው፣ ለምን?


የዚህ ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ለዓለም መገለጽ የነበረባቸውን ለይቶ ነው መግለጫ የሰጠው፡፡ ሌላው የቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ አሠራር ስለሆነ ውሳኔዎቹ ተለይተው ነው የቀረቡት፡፡

ሙስና ቤተ ክርስቲያኗን ምን ያህል ነው የጎዳት?

 

ያለፉትን ጊዜያት ጨምሮ አሁን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ ስናይ በሙሰኞች እየታመሰች ትገኛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ስሟ በማይገባ (በሙስና) እንዲጠራ አድርገዋል፡፡ የእነዚህ ሰዎች ማንነት ሲፈተሸ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ያልሆኑ ገንዘቧን እንደፈለጉ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያኗ የመልካም አስተዳደር ባለቤት እንዳትሆን በተለያየ ስልት ሲያከሽፉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ችግሩ እንደመዥገር ተጣብቆ ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡

 

በቤተ ክህነቱ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር እንዳይሰፍንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የማይገባቸውን ቦታ ስም እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡ የችግሩ ስፋት በዚህ አያበቃም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዘረኝነትና በጎጠኝነት እንድትተበተብ የፈጠረው ቁርሾ ከባድ ነው፡፡ ገጠር ብትሔድ እንዲህ ዓይነት ችግር የለም፡፡

ካህኑም ምእመኑም ጉቦ አይሰጥም፣ አይቀበልም፡፡ ችግሩ ያለው አዲስ አበባ ዙሪያ ነው፡፡ ለሕዝቡም እየነገርን ከርመናል፤ አንተ ሕዝብ ገንዘብህን ጠብቅ!፤ አንተ ወጣት ቤተ ክርስቲያኗን ከነጣቂዎች ጠብቅ! እኛ ማስተማር ስላለብን ስንናገር ከርመናል፡፡

 

እንደ እውነቱ እኮ እኛ እየመራናቸው፣ ሰንበት ተማሪዎቻችን ጠንካራ ቢሆኑ ኖሮ ከሰባክያን፣ ከቀሳውስትና ከማኅበራት ጋር ተባብረው ሙስናን ከቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ይበቁ ነበር፡፡ በደንብ ተደራጅተው ገንዘቧን የሚበሉትን መቆጣጠር ይችሉ ነበር፡፡ ሌባ ፈሪ ነው፤ ሌባ ግንባር ለግንባር አይዋጋም፡፡ በሙዳየ ምፅዋቱ ብቻ ታጥረው ቀሩ እንጅ እንደቅዳቸው ቢሆንማ ቤተ ክርስቲያኗን ያጠፏት ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም፡፡

ወደ ፊት ሙስናን ከቤተ ክርስቲያቱ ለማጥፋት ምን የተጀመረ እንቅስቃሴ አለ?

ይህ የሚያበቃበት ጊዜ በቅርብ ቀን እንደሚሆን እምነት አለኝ፡፡ ሙስና ይቁም እያልን ሁሉ ጊዜ ስንጮህ ቆይተናልና፡፡ መጀመሪያ መሣሪያ ይዞ ማስወጣት ሳይሆን ማስተማር ስላለብን ቀደም ብለን እያንዳንዱ ምእመን እስኪሰርጸው ድረስ እያስተማርን ነው፡፡ አሁን ግን በአባቶቻችን ሊቃውንት እየተረቀቀ ያለው መሪ እቅድ ሲጠናቀቅ የሙሰኞች ሰንሰለት ይበጣጠሳል ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም መሪ ዕቅዱ ለካህናቱ፣ ለሰበካ ጉባኤው፣ ለሰንበት ተማሪዎች፣ ለማኅበራቱ ከፍተኛ አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡ እነዚህ አካላት ተባብረው ከሠሩ ቤተ ክርስቲያን ከሙስና ትጸዳለች፡፡

 

በዚህ አሠራር ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ የሚፈለገው ለውጥ ይመጣል ባይ ነኝ፡፡ በመሪ ዕቅዱ ካህኑ፣ አለቃው፣ ሒሳብ ሹሙ፣ ፀሐፊው እስከ የት ድረስ ነው ሓላፊነታቸው፣ የተቆጠረው ገንዘብ መዋል ማደር ያለበት የት ነው፤ ገንዘብ ቆጠራው ላይ ማን ይገኝ እና ሌሎች አሳቦች ይካተታሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ በምእመናን እጅ፣ በካህናት እጅ ስትሆን ነው ትክክል የምትመጣው፡፡ አለበለዚያ. . . ቤተ ክርስቲያኒቱን ባዶ ያደርጓታል፡፡ ይህ መቆም አለበት፡፡ እስከዛው ግን እያስተማርን እንደሆነ ሙሰኞች ይወቁት፡፡

ይልቅስ?


ቤተ ክርስቲያኒቷ ገና ያልሠራቻቸው ብዙ የቤት ሥራዎች አሉባት፡፡ ይህንን ነው መሥራት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ብዙ የልማት ሥራዎች ያስፈልጓታል፡፡ በበቂ ሁኔታ የረዳናቸው ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች የታሉ?፣ የምናሳድጋቸው ዕጓለማውታ ሕፃናት የታሉ? የታለ አረጋውያንን የምንጦረው? ስብከተ ወንጌል ያልተዳረሰባቸውን ጠረፋማ አካባቢዎች የታለ አስተምረን ያስጠመቅናቸው? ቤተ መጻሕፍት አዳራሽ የት ነው ያለው?፤

 

መኪና ጋራዥ ገብቶ ሲለወጥ እኛ ግን ሰውን የምንለውጥበት መንፈሳዊ ጋራዥ የት ነው ያለው? ስለዚህ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ማኅበራት፣ አባቶት ካህናት እንደዚሁም ደግሞ ከላይም ከታችም ያሉ ምእመናን በሙሉ መጀመሪያ ትኩረታቸው ስለ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዐት፣ ስለ ልማት፣ ስለ አንድነትና ስለ ፍቅር መሆን ይገባዋል፡፡ አበክሬ የምገልጸው የእምነታቸው፣ የሥርዓታቸው፣ የታሪካቸው፣ የሀገራቸው ፍቅር እንዲኖራቸውና ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው ጠበቃ እንዲሆኑ ነው፡፡

በተለይ ማኅበራት፡- በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ማኅበራት አሉ፡፡ መጀመሪያ ቤተ ክርስቲያንን ማስቀደም አለባቸው፡፡ የእኔ መኖር ለቤተ ክርስቲያን ምን ጠቀመ? ማለት አለባቸው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጠግተው የእኔ ድርሻ ምን መሆን አለበት ብለው አባቶችን በመጠየቅ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሰው ለቤተ ክርስቲያን ዘብ መቆም አለበት፡፡ ይህቺ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያናችን እና አንጋፋ ሀገራችን በልጆቿ ማፈር የለባትም፤ ሌቦች ጥቂት ሆነው ብዙዎች ደጅ ሆነው ሲመለከቱ ያሳፍራል፣ በቤተ ክርስቲያኒቷ ሙስና አለ ማለት ያሳፍራል፣ በቤተ ክርስቲያን ድሆች ሲጦሩ፣ ልጆች ሲማሩ፣ መጻሕፍት ሲነበቡ አለማየት ያሳፍራል፡፡ ስለዚህ በአንድነት ስለቤተ ክርስቲያን ዘብ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው፡፡

 

በቤተ ክርስቲያኒቷ አሁን ያለው እጥረት ተቀራርቦ አለመሥራት፤ አለ መወያየት ነው፡፡ እኛ በአብዛኛው ያሳለፍነው በመወነጃጀል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አየነው የት እንዳደረሰን፡፡ አንዱ አንዱን ሲወነጅል ቤተ ክርስቲያኗን ምን ያህል እንደጎዳት፤ ምን ያህል እሞት አፋፍ እንዳደረሳት ባለፉት ጊዜያት አይተነዋል፡፡ ሁሉም በየራሱ የሚሔድ ከሆነ በጎ አይሆንም፡፡ ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ትልቅ የመቀራረብ ሥራ መሠራት አለበት፡፡

 

በአባቶቻችን መሪነት አንድ ሆነን አንተ በዚህ ዝመት፤ አንተ በዚህ ሒድ መባባል ይቻላል፡፡ እንደ ገበሬ አረሙን ወደ ውጭ እየጣሉ፣ የወደቀውን ሰው እያነሡ መሔድ ይቀረናል፡፡ ተቀራርቦ አለመተቻቸትም ይቀረናል፡፡ ጥሩ ወተት ለማግኘት እላሟ ሥር ያለውን መዥገር መንቀል ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም በየራሱ መቅረት መተው አለበት፡፡ አሁንም ጊዜው አለ ተቀራርበን እንሥራ ነው የምንለው፡፡ ምእመናንን ከተኩላዎች፣ ከነጣቂዎች መጠበቅ አለብን፡፡

 

በተጠራጣሪዎችና አማኝ ባልሆኑ አካላት የሚነገር፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ዘለፋ ከቀያጮች፣ ከበራዦች፣ ከስም አጥፊዎች የሚላኩ የኑፋቄ ቃላትን አለመቀበል ነው፡፡ የዘመኑን መሣሪያ ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚተጉ ተቃዋሚዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መቃወም መቻል አለብን፡፡ ሌላው ሥርዓቱንና ትውፊትን መጠበቅ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የሆነው ሥርዓቱን እያከበረ ሌሎችን ይወዳል፣ እምነታችን ሁል ጊዜ የአንድነት፣ የሰላም ምልክት ናት፡፡ መሠረታችን ፍቅር ነው፡፡ ቃሉ ሰውን ውደድ ስለሆነ በዚህ እንትጋ ነው የምለው፡፡

ምንጭ፤- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኅዳር 1-15 ቀን 2007 ዓ. ም.

የባሕር ዳር ማእከል የጽ/ቤት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

 

ኅዳር 16 ቀን 2007 ዓ.ም.

ግዛቸው መንግሥቱ /ከባሕር ዳር ማእከል/

bahirdar02በማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማእከል በደብረ ጽዮን ሰላም አድርጊው ማርያም ገዳም በተሠጠው ቦታ በመገንባት ላይ የሚገኘው ጽሕፈት ቤት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የጽ/ቤት ግንባታ ኮሚቴ የቴክኒክ ክፍል አስተባባሪ አቶ አስናቀ ለወየ አስታወቁ፡፡

የሕንፃ ግንባታ ኮሚቴው ኅዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም እየተገነባ ያለውን ጽሕፈት ቤት በተያዘለት እቅድ መሠረት እየተጠናቀቀ መሆኑን ለአባላቱ ለማብሠርና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ አስናቀ ለጽሕፈት ቤት ግንባታ የሚሆን ቦታ ለሰጠውና በዐሳብና ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ ለሚገኘው ለደብረ ጽዮን ሰላም አድርጊው ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ፣ እንዲሁም የግንባታውን ወጪ ወርሃዊ ደመወዛቸውን በመለገስ ሙሉ በሙሉ ለሚሸፈኑት የማኅበሩ አባላትን አመስግነዋል፡፡ እየተገነባ ያለው ጽሕፈት ቤት የመጀመሪያ ምእራፍ ሲሆን፤ የጣራ ሥራውና ቆርቆሮ ማልበሱ በኅዳር ወር፤ ሙሉ ግንባታው ደግሞ እስከ ጥር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠናቆ አገልግልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡

ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት እየተገነባ ያለው ጽሕፈት ቤት በቋሚነት የሚያገለግለው ለአዳራሽነት ሲሆን፤ ለቢሮ የሚያገለግሉ ክፍሎች በሁለተኛው የግንባታ ምእራፍ ከገዳሙ በተገኘው ክፍት ቦታ ላይ እንደሚገነቡ ተጠቅሷል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ የመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታ ልዩ ልዩ የሙያ ድጋፎችን ሳይጨምር እስከ 600,000 ብር የሚፈጅ በመሆኑ አባላት በሙያና በገንዘብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮሚቴው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ የባሕር ዳር ማእከል፣ የሰሜን ምእራብ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ የጣና ወረዳ ማእከልና ግቢ ጉባኤያት እንደሚገለገሉበት የተጠቀሰ ሲሆን፤ የጽሕፈት ቤቱ መገንባት ለማእከሉና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ለሚፈጽሟቸው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡

የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ በ2003 ዓ.ም ጽሕፈት ቤት መገንባት እንዳለበት ለአባላቱ ዐሳብ በማቅረብ፤ የጽሕፈት ቤት ግንባታ ኮሚቴ በማቋቋም አባላት ገንዘባቸውን አሰባስበው ግንባታውን ለመጀመር ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በተለየዩ ችግሮች ምክንያት የዘገየ ቢሆንም በጥቅምት 2005 ዓ.ም አሁን የሚያገለግልበትን ጊዜያዊ ጽ/ቤትና የግንባታ ቦታ በደብረ ጽዮን ሰላም አድርጊው ማርያም ገዳም ለማግኘት በመቻሉ ማእከሉ አገልግሎቱን ለማጠናከርና በርካታ ሥራዎችን እንዲሠራ አስችሎታል፡፡
ግንቦት 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ለጊዜው ተቋርጦ የነበረውን የጽሕፈት ቤት ግንባታ ፕሮጀክት አዲስ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ተግባር ለመሸጋገር እንቅስቀሴ ተጀመረ፡፡ ኮሚቴው ለግንባታ በሀብትነት ይዞት የተነሳው የባሕር ዳር ማእከል አባላትን ብቻ በመሆኑ አባላትን በማወያየት የወር ደመወዛቸውን በዐራት ጊዜያት ከፍለው እንዲያጠናቅቁ በማስወሰን ገንዘባቸውን በመለገስ፤ በሙያ በመደገፍ ባደረጉት ብርቱ ጥረት አሁን የጽሕፈት ቤት ግንባታው በተያዘለት እቅድ መሠረት እየተከናወነ መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

የባሕር ዳር ማእከል በማእከልነት የተቋቋመውና አገልግሎቱን የጀመረው በ1985 ዓ.ም ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በማእከልነት ተደራጅተው ሰፊ አገልግሎት እየፈጸሙ ያሉትን ዘጠኝ ማእከላት አቅፎ ነበር፡፡ ማእከሉ እንደተመሰረተ አገልግሎቱን ይፈጽም የነበረው በምእራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት በተሰጠችው አነስተኛ አንድ ክፍል ጽሕፈት ቤትና በግለሰብ ቤት እንደነበረ የጽሕፈት ቤት ግንባታ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ የባሕር ዳር ማእከል ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር አገልግሎቱን ለመፈጸም እንዲችል ከ1985 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2005 ዓ.ም ድረስ በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ዘጠኝ ጽ/ቤቶችን በመከራየት ሰፊ አገልግሎት የፈጸመ ቢሆንም ለከፍተኛ የቢሮ ኪራይ ወጭ ሲዳረግ የቆየ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ማእከሉ አገልግሎት ይፈጽምባቸው የነበሩ ጽ/ቤቶች የነበሩበት አካባቢ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የማይመቹ አስቸጋሪና ከቤተክርስቲያን ቅጽር የራቁ በመሆናቸው ማእከሉም ሆነ አባላቱ የማይረሱ ፈተናዎችና ችግሮችን እንዳሳለፉ የቀደሙ የማእከሉ አባላት ይገልጻሉ፡፡ ለረጅም ዓመታት ጽሕፈት ቤት ባለመኖሩ የደረሰበት ፈተናና በአገልግሎቱ ላይ የተፈጠረበት ጫና የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ ዓላማውን ለማሳካትና ለአገልግሎቱን በአግባቡ ለመፈጸም የሚያስችለውን ምቹ ጽሕፈት ቤት መገንባት እንዲያስብና አባላቱም በቆራጥነት ለግንባታው እንዲነቃቁ እንዳደረጋቸው የጽሕፈት ቤት ግንባታ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

በተያዘ ዜና በማኅበረ ቅዱሳን በባሕር ዳር ማእከል የደብረ ሰላም ወረዳ ማእከል ከወረዳ ማእከሉ አባላት ገንዘብ በማሰባሰብ ከደብረ ሰላም በዓለ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ባገኘው ቦታ ላይ ባለ 4 ክፍል ጽ/ቤት ገንብቶ የጣሪያ ማልበስና የግድግዳ ግርፍ ስራውን ማጠናቀቁና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት እንደሚያበቃ የወረዳው ማእከል አስታውቋል፡፡

 

 

‹‹አንተ በጎና ታማኝ አገልጋይ›› ማቴ:25

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ 

ህዳር 15 ቀን 2007 ዓ᎐ም

ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በክቡር ዳዊት አድሮ፤ “እከሥት በምሳሌ አፉየ፤ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት፤ አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሌት እናገራለሁ” ብሏል፡፡ /መዝ. 77፡2/
በዚሁ መሠረት ጌታችን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን በልዩ ልዩ ምሳሌ አስተምሯል፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ሁለት ምሳሌያትና አንድ ትንቢት ቀርበዋል፡፡

 

 ከምሳሌያቱ የመጀመሪያው በዐሥሩ ደናግል አንጻር የቀረበው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወጥተው ወርደው ነግደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን ስለሰጠ ነጋዴ የሚናገረው ነው፡፡ ትንቢቱም ስለ ኅልቀተ ዓለም የተነገረ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ዕትማችን ነግደው እንዲያተርፉበት ከጌታቸው የተሰጣቸውን መክሊት ስለተቀበሉት አገልጋዮች እንመለከታለን፡፡ ፈጣሪያችን ለብዎውን ማስተዋሉን ያድለን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸውን ምሳሌያዊ ትምህርቶችን በሰፊው ተጽፎ እናገኛለን፡፡

የእነዚህ ትምህርታዊ ምሳሌዎች መሠረታዊ ሀሳብና ዓላማ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምናገኝበትን የታማኝነትን ሥራን እንዴት መሥራት እንደሚገባንና እንደምንችል ማስተማር ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መንግሥተ ሰማያት ምሥጢር ያስተማራቸው ብዙ ምሳሌዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ብዙ ምሳሌዊ ትምህርቶች መካከል በማቴዎስ ወንጌልም 25 ላይ እንዲያተርፉበት መክሊት ስለተሰጣቸውና ወጥተው ወርደው ሌላ አትረፈው በጌታቸው ስለተመሰገኑት ቸርና መልካም አገልጋዮች፣ እንዲሁም መክሊቱን በመቅበሩ ምክንያት በጌታው ስለተወቀሰውና ፍርድን ስለተቀበለው ሰው ታሪክ፣ የታሪኩም ምሥጢር ምን እንደሚመስል ነው፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው በሚከተለው መልኩ ነበር ‹‹ወደ ሌላ ሀገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ ሀገር ወዲውኑ ሄደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄደ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡
ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡

 

አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡- ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ:: ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡፡ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ገታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ:: ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡

አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት እነሆ መክሊትህ አለህ አለው፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን:: ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር:: እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት:: 

 

ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል:: ከሌላው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት:: በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡›› የሚል ነው፡፡ መክሊት ጥንት የክብደት መለኪያ ነበር:: አንድ መክሊት 30 ኪሎ ግራም ያህል ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸውም መክሊት የሚለው ቃል ገንዘብን ያመለክታል፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ እርሱን የምናገለግል ሁላችን አንደየዓቅማችን ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ የአገልግሎት ሥራንና በአገልግሎታችን ውጤታማ በመሆናችንም ከእርሱ የምናገኘውን ዘላለማዊ ክብርና ዋጋን እንዲሁም መሥራት የሚገባንን ባለማድረጋችንም ምክንያት የሚገጥመንን መለኮታዊ ቅጣትን አመልክቶናል፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ባለ አምስት የተባለው ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣነው፡፡

 

በተመሳሳይም ባለሁለት የተባለው ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣ ሲሆን ባለአንድ የተባለው ደግሞ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ባለአምስትና ባለሁለት መክሊት የሆኑት ወጥተው ወርደው ደክመው’ መከራ መስቀልን ሳይሰቀቁና ሳይፈሩ’ ነፍሳቸውን ለታመነው አምላክ አደራ በመስጠት የተማሩትን ፍጹም ትምህርት ለሌላው አስተምረው ሌላውን አንደራሳቸው የተማረ አድርገው ሲያወጡ ባለአንድ የተባለው ግን አላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ ፈርቶ ሃይማኖቱን በልቡ ከመያዝ በቀር የተማረውን ትምህርት ለሌላው ሊያስተምርና የተሰጠውን አደራንም ሊወጣ አልወደደም፡፡

በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጠው ሌላ አምስትና ሁለት ያተረፉት በተሰጣቸው መክሊት ሌላ ማትረፋቸውን ለጌታቸው በገለጡ ጊዜ የመክሊቱ ባለቤት እጅግ አድርጎ እንዳመሰገናቸው ከላይ አንብበናል፡፡

ይህ የመክሊቱ ባለቤት የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለተወጡት ሁሉ እርሱ ፍጹም ዋጋን የሚሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም ሁኔታ ‹‹ መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› በሚል ተገልጧል፡፡ ይህ ቃል በሃይማኖት ለእግዚአብሔር የታመኑ ሁሉ ወደ ፍጹም ደስታ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ለሚያደርጉት ጉዞ እጅግ ተስፋ የሆነ ቃል ነው፡፡

 

በዚህ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም እርሱን የምናገለግልበትንና ለእርሱ በመታመን ዘላለማዊ ክብርን የምናገኝበትን ዕውቀትን ማስተዋልን’ ሀብትን’ ዓቅም ወይም ጉልበትን ሌሎችንም ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ለእኛ ለሰው ልጆች እንደየዓቅማችን መጠን ሰጥቶናል፡፡

እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሥጋችንን ምኞት እንድንወጣባቸው የተሰጡ ሳይሆኑ ነፍሳችን የምትከብርበትን መልካም ሥራን የምንሠራባቸው ናቸው፡፡
በመሆኑም እርሱ በሰጠን የአገልግሎት ጸጋ በታማኝነት በማገልገል በተሰጠን ነገር ሁሉ መንፈሳዊውን ሀብት የምናተርፍ ልንሆን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እኛ የተጠራ ነው ፍሬ ልናፈራና ሌላውንም ልናተርፍ መልካም ሥራን ልንሠራ እንጅ የሥጋችንን ፈቃድ በመከተል የኃጢኣት ባሮች ልንሆን አይደለም፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው በልዑል አምላክ በእግዚአብሔር አንደበት አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ መባልን የመሰለ አስደሳችና አስደናቂ ነገር የለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው ሃይማኖትን በሥራ በመግለጥ እንጅ ሃይማኖትን በልቦና በመያዝ ብቻ አይደለም፡፡ ከእነዚህም እንደ አቅማቸው መክሊት ተሰጥቷቸው ሌላ መክሊት ካተረፉት በጎና ታማኝ አገልጋዮች ከተባሉት የምንማረው እውነታ ይህ ነው፡፡ ስለዚህም በብዙ ለመሾም በጥቂቱ መታመን ግድ ነው፡፡
አንድ መክሊት የተሰጠውን ሰው ስንመለከተው ጌታውን ጨካኝ አድርጎ ከመቁጠር ውጪ በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ሊያተርፍ አልወደደም፡፡ መክሊቱንም ባስረከበ ጊዜ በጌታው ላይ የተናገራቸው ቃላት የእርሱን አለመታዘዝና አመጸኝነት ይገልጡ ነበር፡፡

 

በመሆኑም ይህ ሰው በጥቂቱ መታመን ያቀተውና በአስተሳሰቡ ደካማነት እጅግ የተጎሳቆለ ሰው ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ መሠረት ይህ ባለአንድ የተባለው ሰው ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ በማለት ሃይማኖቱን በልቡ ሸሽጎና ቀብሮ ከመያዙ ባሻገር በጌታ ፊት በድፍረት ቆሞ አንተ ሕግ ሳትሠራ በአዕምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ’ መምህርም ሳትሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ በሠራችሁ ብለህ የምትፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆንክን አውቃለሁና ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ ብየ ፈርቼ ሃይማኖቴን በልቡናየ ይዠዋለው በአዕምሮየ ጠብቄዋለሁ የሚል ሃይማኖቱን ግን በሥራ የማይገልጥ ሰነፍ ሰውን ያመለክታል፡፡

ለዚህ ዓይነት ሰው የጌታ መልስ ደግሞ በምሳሌው መሠረት የሚከተለው ነው፡፡ እኔ ሕግ ሳልሠራ በአዕምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ መምህር ሳልሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ አውቃችሁ በሠራችሁት ብየ የምፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆኔን ታውቃለህን? እንዲህስ ካወቅህ ሹመትክን ልትመልስልኝ ይገባኝ ነበር፡፡ ወጥቶ ወርዶ ለሚያስተምር በሰጠሁት ነበር፡፡ አሁንም የእርሱን መምህርነት ሹመት ነሥታችሁ (ወስዳችሁ) ለዚያ ደርቡለት! እርሱን ግን አውጡት የሚል ነው፡፡ ዛሬም እያንዳንዳችን በዓቅማችን መጠን መክሊት ተሰጥቶናል፡፡ በመሆኑም መክሊቱን እንደቀበረው እንደዚያ ሰው የተሰጠንን ቀብረን ለወቀሳና ለፍርድ እንዳንሰጥ በአገልግሎታችን ልንተጋ ይገባናል፡፡

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ ሲገልጥ ‹‹አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግሥና ይስጥ›› (ሮሜ12፥7) በማለት ተናግሯል፡፡ ለመሆኑ ዛሬ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ…›› ተብሎ በእግዚአብሔር ሊመሰገን የሚችል ማን ይሆን? በእውነት በዘመናችን እንዲህ ተብሎ የሚመሰገን በጎና ታማኝ ካህን’ ታማኝ መምህርና ሰባኪ’ ታማኝ ዘማሪ የመሳሰለውን ማግኘት ይቻል ይሆንን? ትልቅ መሠረታዊ ሊሆን የሚገባው ጥያቄ ቢኖር ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ስለ ታማኝነት የሁላችንንም ሕይወት የሚዳስስና ሁላችንንም የሚመለከት ነውና፡፡

 

በእርግጥም ዛሬም ቢሆን እንደ አባቶቻችን ማለትም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በእምነት’ በትዕግስት በፍቅር’ በትህትናና በትጋት በማገልገል የተሰጣቸውን መክሊት የሚያበዙ አገልጋዮች አሉ፡፡ የእነዚህ ክብራቸው በምድርም በሰማይም እጅግ የበዛና ራሳቸውን አስመስለው በትምህርት የወለዷቸው ልጆቻቸውም ለቤተክርስቲያን ውድ ልጆች ናቸው፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን’ ቅዱስ ጳውሎስም ጢሞቴዎስን አፍርተዋል፡፡

 

ሌሎችም አበው ቅዱሳን በወንጌል ቃል መንፈሳውያንና ትጉሃን የሆኑ ምእመናንን በሚገባ አፍርተዋል፡፡ ያላመኑትንም አሳምነው ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመመለስ ለዘላለማዊ ክብር የበቁ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል፡፡ በመሆኑም በክርስቶስ በደሙ የተከፈለውን ወደር የሌለውን ዋጋ ዓለም አምኖና አውቆ በክርስትና ሃይማኖት እንዲድንበትና እዲጠቀምበት በማድረግ እንዲሁም በታማኝነት ሥራቸው ጥንትም ዛሬም ላለችዋና ወደፊትም ለምትኖርዋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ድምቀትም ውበትም የሆኑት ቅዱሳን አበው ሊገኙ የቻሉት ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን ደስ ለማሰኘት በመድከማቸው ሳይሆን የተጠሩበትን ዓላማና የጠራቸውን እርሱን በሚገባ አውቀውና ከልብ ተረድተው ለዘላለማዊ ህይወት ተግተው በመሥራታቸው ነው፡፡ (ገላ1፥10)

ዛሬም በዚህ ዘመን ያለንና በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን የተጠራን ሁላችንም የተሰጠንን መክሊት (ጸጋ) አውቀን ለእግዚአብሔር ለአምላካችን በመታመን ወጥተን ወርደን ሌላ ልናተርፍ ይገባናል፡፡ በተለይ ደግሞ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ያለ ሰው ከምንም በላይ በከፍተኛ መንፈሳዊ ኃላፊነት ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖትም በሥነምግባርም ለሌላው ዓርዓያ በመሆን እንደ እርሱ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር አስተባብረው የያዙ ምእመናንን ማፍራት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ልንባል የምንችለው፡፡ 

 

አሁን ባለንበት በዘመናችን ብዙ ፈታኝ የሆኑ ችግሮች አሉ፡፡ የችግሮቹም መሠረታዊ ምንጭ በተጠሩበት ጸንቶ መቆም ፈጽሞ አለመቻልና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ በማድላት ኃላፊነትን መዘንጋት ናቸው፡፡ በሥጋዊ አምሮት ፍላጎትና ምርጫ ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት የሚያስችለንን የታማኝነት ሥራን መሥራት አይቻልምና ከምናድነው ሰው ይልቅ መክሊታችንን በመቅበር መሰናክል የምንሆንበት ሰው ሊበዛ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ በመሆኑም ከእርሱ ዘንድ እንደዓቅማችን የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት ለሌላው በማድረስ መክሊታችንን ልናበዛ የምንችለውና አገልግሎታችን ወይም ክርስትናችን ውጤታማ የሚሆነው ምርጫችንን አውቀን እንደ ቃሉ ሆነንና ጸንተን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡

 

ይህ ባለመሆኑ ነው ዛሬ ብዙዎቻችን በህይወታችን ሌላውን ማትረፍ አቅቶን በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ በሚያስወቅሰን የስንፍና መንገድ ላይ ቆመን የምንገኘው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ›› (ማቴ24፥42) ብሎናል፡፡

እንግዲህ ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በደሙም መፍሰስ ህይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘላለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላክ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመታመን እርሱ ያዘዘንን ሁሉ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ምን ጊዜም ትጉህ ሠራተኛ ደግሞ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በትግራይ ሦስት ገዳማት የተገበራቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ

•ለፕሮጅክቶቹ ማስፈጸሚያ ከ3 ሚሊዮን 180 ሺሕ ብር በላይ ወጪ ሆኗል፡፡ 

ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

gundagundi 02ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አማካይነት በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም፤ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ጽምባላ ወረዳ በአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ፤ በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳማት ያከናወናቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ፡፡

 

በተለያዩ ጊዜያት ተጀምረው የነበሩት እነዚህ ፕሮጅክቶች ከኅዳር 3/2007 ዓ.ም. – ኅዳር 8/2007 ዓ.ም. ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለየገዳማቱ አስረክቧል፡፡ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ፅብላ ወረዳ ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም የተመረቀው የአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ አንድነት ገዳም በ630 ሺሕ ብር የተሠራ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሲሆን፤ 150 ሺሕ ሊትር መያዝ ይችላል፡፡ ይህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በገዳሙ ውስጥ ተገንብቶ በመጠናቀቁ ማኅበረ መነኮሳቱ የመጠጥ ውኃ ፍለጋ በቀን ከ4-5 ሰዓት በመጓዝ የሚባክንባቸውን የአገልግሎትና የጸሎት ጊዜያቸውን እንደሚያስቀርላቸው የገዳሙ አባቶች ተናግረዋል፡፡

abune tomas zehayda 02 1ገዳሙ ያለበትን ችግር በማጥናት የውኃ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ መንገዱ በጣም አስቸጋሪና ከ3-4 ሰዓት በእግር የሚያስኬድ በመሆኑ አባቶች በሸክም፤ እንዲሁም ግመሎችን በመጠቀም የግንባታ ቁሳቁስ በማመላለስ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተችሏል፡፡

ገዳሙ ጥንታዊና ገዳማዊ ቀኖና እና ሥርዓት ተጠብቆ የሚገኝበት ሲሆን፤ በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በማፍራትም ይታወቃል፡፡

gundagundi 03በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ደግሞ ለደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም የተገነባው ሁለገብ ሕንፃ ነው፡፡ ሁለገብ ሕንፃው በአዲግራት ከተማ የተገነባ ሲሆን፤ ለተለያየ አገልግሎት በማከራየት ገቢ ማስገኘት የሚችል ነው፡፡ ሕንፃው በብር 2,326,717.87 /ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሃያ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ ዐሥራ ሰባት ብር ከ87 ሣንቲም/ ተገንብቶ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡

ሕንፃው በ416.49 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ማኅበሩ የሠራው የምድሩን ወለል ብቻ ነው፡፡ መሠረቱ ባለ ሁለት ወለል ሕንፃን መሸከም እንዲችል ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ ቀሪውን የግንባታ ሥራ ገዳሙ ባቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ይገነባል፡፡

ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ቀድሞ በርካታ መነኮሳት የነበሩባት ቢሆንም በደርግ መንግሥት የነበራት ሰፊ ይዞታ በመነጠቋ የመነኮሳቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በችግር ምክንያት እየተመናመነ ሄዶ ሁለት መነኮሳት ብቻ ቀርተው ነበር፡፡ እነሱም በገዳሟ ውስጥ የሚገኙትን ንዋያተ ቅድሳትና በሌሎች ገዳማት የማይገኙ ቅዱሳት የብራና መጻሕፍትን ለማን ጥለን እንሔዳለን በማለት ችግሩን ተቋቁመው ዛሬ ድረስ ለመዝለቅ ችለዋል፡፡

ወደ ገዳሟ ለመድረስ መንገዱ አስቸጋሪና መኪና የማይገባ በመሆኑ የአንድ ቀን ሙሉ የእግር መንገድ መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ለመመለስም እንዲሁ የአንድ ቀን የእግር ጉዞ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ገዳሟ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላት ሲሆን፤ የሁለገብ ሕንፃው መገንባት ችግሩን እንደሚቀርፍ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የመነኮሳቱ ቁጥር ከሁለት ወደ ሰባት ከፍ ለማለት ችሏል፡፡

dibo 02በተጨማሪም በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ማኅበሩ በብር 225,343.65 /ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ሦስት ብር ከ65 ሣንቲም/ ተግባራዊ ያደረገውን የሽመና ውጤቶችን መሥሪያ አዳራሽ ሠርቶ በማጠናቀቅ፤ የሽመና ቁሳቁስ በማሟላት፤ እንዲሁም የልብስ ሥፌት መኪናዎችን ገዝቶ በማቅረብ ርክክብ ተደርጓል፡፡

የሽመና ፕሮጀክቱ ታሳቢ ያደረገው በገዳሟ ውስጥ ለሚገኙት መነኮሳይያት ሲሆን፤ መነኮሳይያቱ ቁጥራቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የሽመና ውጤቶችን ማምረት ያስችላቸዋል፡፡

ደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ጥንታዊ ከሚባሉ ገዳማት መካከል የምትመደብ ስትሆን በውስጧም ጥንታዊ ሥዕላትን ጠብቃ ለትውልድ በማቆየት ትታወቃለች፡፡ ለትኅርምት እና ለጽሞና የምትመረጥም ገዳም ናት፡፡

ማኅበሩ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍሉ አማካይነት ለበርካታ ገዳማትና አድባራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር ገዳማት የልማት ሥራዎችን በመሥራት ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ሲሆን፤ ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል፡፡