የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱንና ሰባክያኑን እንደግፍ

በገጠርና ጠረፋማ አካባቢዎች የሚያገለግሉ ሰባክያነ ወንጌል

በገጠርና ጠረፋማው የአገራችን ክፍል ተበታትነው የሚኖሩ ብዙ ወገኖቻችን እውነተኛውን የወንጌል ብርሃን ሳይመለከቱ፣ ለሥላሴ ልጅነት ሳይበቁ፣ በጎውን ነገር ሳያዩ፣ ድኅነትን እንደ ናፈቁ ሞተ ሥጋ ይቀድማቸዋል፡፡

ጥቂት የእግዚአብሔርን ቃል ያወቁ ወንድሞች የምሥራቹን የእግዚአብሔርን ቃል ለማብሠር፤ ለወገኖቻቸው የወንጌል ብርሃንን ፈንጥቀው ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ለማሸጋገር ሲሉ የበረኃው ንዳድ፣ የአራዊቱ ግርማ፣ ረኃቡና ጥሙ፣ ስቃዩና ሕመሙ ሳይበግራቸው፣ እንቅልፍ በዐይናቸው ሳይዞር የሐዋርያትን አሰር ተከትለው ከጠረፍ ጠረፍ እየተዘዋወሩ ወንጌልን ይሰብካሉ፡፡

የእናት ቤተ ክርስቲያናቸውን ርእይ በማንገብ ለወገኖቻቸው በጥምቀት የሥላሴ ልጅነትን ለማሰጠት ለቀናት በረኃውን በእግር ያቋርጣሉ፤ እነርሱ በእግር ሁለት፣ ሦስት ቀን የሚወጡ የሚወርዱበትን መንገድ ሌሎች የጥፋት መልእክተኞች (መናፍቃን) በዘመናዊ ተሽከርካሪ ገደል ኮረብታውን ጥሰው፣ በግል ሄሊኮፕተር ጭምር ያለ ችግር ቀድመው በመድረሳቸው ብቻ ወገኖቻችንን ይነጥቃሉ፤ ያልዘሩትን ያጭዳሉ፡፡ ይህም ለእኛ ሰባክያነ ወንጌል ሌላ ድካም ይኾንባቸዋል፤ ቀድመው ባለ መድረሳቸው በወገኖቻቸው ላይ የተዘራውን ክፉ አረም ለመንቀል ጊዜም ጕልበትም ይፈጃልና፡፡

እነዚያ የበረኃ ሐዋርያት ‹‹ወልድ ዋሕድ›› ብለው ሲያስተምሯቸው፣ ስለ ቅዱሳኑ ምልጃ ሲነግሯቸው፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረሻ ስለኾነችው ዳግም ልጅነትን ስለምታሰጠው አሐቲ ጥምቀት ሲያበሥሯቸው ‹‹እስከዚህ ዕድሜያችን ድረስ ስንጠብቃችሁ ነበር፤ እኛ የምናምነው አያቶቻችን የነገሩንን የቄሶች ሃይማኖት ነው፡፡ አስተምሩን፤ አጥምቁን፤›› ይሏቸዋል፡፡

ሰባክያኑ ከዚህ ያለውን አረም ነቅለው ሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ለመድረስ ሲነሡ በክንፍ አይበሩ ነገር እንዴት ይድረሱ? ሥጋ ለባሽ ናቸውና ከመንገድ ይመለሳሉ፡፡ እነዚህ የበረኃ ሐዋርያት በአንዲት ሞተር ሳይክል እጦት ምክንያት በጊንጥና በእባብ እየተነደፉ፣ አጋዥ አጥተው ለወገኖቻቸው ቃለ ወንጌልን ሳያዳርሱ ይቀራሉ፡፡

እነዚህ ሐዋርያት ያለምንም እገዛ በረኃውን በእግር እያቋረጡ ከ፹፮ ሺሕ በላይ ወገኖችን በጥምቀት የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ማድረግ ከተቻላቸው፣ ድካማቸውን በትንሹም ቢኾን ብንቀንስላቸው ደግሞ በመቶ ሺሕ የሚቈጠሩ ወገኖችን እንደሚያስጠምቁ የታመነ ነው፡፡

በጕዞ የደከመ የሰባክያኑን ጕልበት ለማደስ ፍቱን መድኀኒቱ ሞተር ሳይክል ነውና እኛ ከቤታችን ኾነን በጕዞ ሳንደክም አንዲት ሞተር ሳይክል በመለገስ ተራራውንና ቁልቁለቱን፣ በረኃውንና ቁሩን ከሐዋርያቱ ጋር አብረን እንውጣ፤ እንውረድ፡፡ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱንና ሰባክያኑን በመደገፍ የበረከቱ ተሳታፊዎች እንኹን፡፡

ሞተር

በጎ አድራጊው ምእመን የሞተር ሳይክል ስጦታ ሲያበረክቱ

ለድጋፋችሁና ሐሳቦቻችሁ በ 09 60 67 67 67 ደውሉልን

በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር

‹‹በእኛ ቤተ ክርስቲያን ሰላም የዘወትር መልእክት ነው፡፡››  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

 pat

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የካቲት ቀን ፳፻፱ .

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከየካቲት ፩ – ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄኔቭ የአራት ቀናት ፓትርያርካዊ ጉብኝት አካሔዱ፡፡

በአራት ቀናት ቆይታቸውም በስዊዘርላንድ የሚገኘው የኦርቶዶክስ ማእከልን ጐብኝተዋል፤ ቦሲ በሚገኘው የሃይማኖት ተቋም ለሚማሩ ተማሪዎችና ሠራተኞች አባታዊ ምክር አስተላልፈዋል፤ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች ጋርም ተገናኝተዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ የካቲት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በጄኔቭ ከተማ በሚገኘው ዓለማቀፋዊ የሃይማኖት ጉባኤ ማእከል ቃለ ምዕዳን በሰጡበት ወቅት ከ፶ ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን በመወከል ለጉባኤው ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ ዓለምን እርስበርስ የከፋፈለው ልዩነትን ከመቀነስ አኳያ ዓለም አቀፉ የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ያደረገውን ከፍተኛ ጥረት አድንቀዋል፡፡

የዓለም አቀፉ የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ሥራ ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ዘመን አስፈላጊ መኾኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ለጥቃት፣ ለፈተና እና ለግጭት መጋለጣቸውን ጠቁመው የጉባኤው መርሖችና እና ዓላማዎች ከዚህ ቀደሙ በበለጠ መልኩ በአሁኑ ሰዓት በተግባር መተርጐም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ecumenical

በስዊዘርላንድ ጄኔቭ ከተማ የሚገኘው ዓለማቀፋዊ የሃይማኖት ጉባኤ ማእከል

በተጨማሪም በዓለም ማኅበረሰብ መካከል ሰላምን ለማስፈን የሚሠራውን ዓለም አቀፉ የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤን እስካሁን ድረስ ለፈጸመው ስኬታማ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበው ጉባኤው ከተመሠረተበት ዓላማ አኳያ የሚጠበቁበት ቀሪ ሥራዎችን እንዲያከናውን የአደራ መልእክት አስተላለፈዋል፡፡

‹‹በእኛ ቤተ ክርስቲያን ሰላም የዘወትር መልእክት ነው›› ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ የፍትሕ መጓደል፣ ጦርነት፣ ጠብ፣ ድህነት እና ጠባብ ብሔርተኝነት ዓለምን እርበርስ እንደ ከፋፈሏት ጠቅሰው ከእግዚአብሔር ቃል በስተቀር ሰብአዊ ፍልስፍናዎች፣ ከፍተኛ የምርምር ውጤቶች፣ ወይም የጦር መሣሪያዎች ሰላምን እና እርቅን ማስፈን እንደማይችሉ በቃለ ምዕዳናቸው አስታውቀዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጉብኝታቸውን አጠናቀው የካቲት ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  ወደ መንበረ ፓትርያርካቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡

ምንጮች፡-

  • http://christiannewswire.com/news/7655779096.html
  • http://www.oikoumene.org/en/press-centre/news/patriarch-matthias-201cpeace-is-the-message-of-every-day201d

መንፈሳውያን በዓላት እና አሉታዊ አስተሳሰቦች – ካለፈው የቀጠለ

ketera1

በዳዊት አብርሃም

የካቲት ቀን ፳፻፱ .

ስለ በዓላት አሉታዊ አስተሳሰቦች

፩. በዓላት ድህነትን ያስፋፋሉ

በዓላት ድህነትን ያስፋፋሉ የሚሉ ወገኖች እንደ ምክንያት የሚያነሡት በበዓላት ሰዎች ከተግባረ ሥጋ ታቅበው ረፍት ስለሚያደርጉ የሥራ ሰዓት ይባክናል የሚል ነው፡፡ በተጨማሪም ለበዓላት የሚወጡ ወጪዎች ቍጠባ እንዳይኖር ያደርጋሉ በሚል መነሻ በዓላት ድህነትን ያባብሳሉ ብለው ይደመድማሉ፡፡ አስቀድመን እንደ ተመለከትነው በበዓላት ተግባረ ሥጋ ቢከለከልም መንፈሳዊ ሥራና በጎ አድራጎት አልተከለከለም፡፡ ተግባረ ሥጋም ቢኾን በዅሉም በዓላት በእኩል ደረጃ የተከለከለ አይደለም፡፡ መከልከሉም ደግሞ የሰው ልጅ ዕረፍት ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ የሰው ልጅ ክቡር ፍጡር እንደ መኾኑ ዅልጊዜ እንደማሽን ሊሠራ ይገባዋል ማለት ሰብአዊ ክብርን የሚያንኳስስ አቋም ነው፡፡

ሠራተኛ ዕረፍት ማድረጉ ለበለጠ ሥራ ያነሳሣዋል እንጂ አያሰንፈውም፡፡ ዕረፍት ካደረጉ በኋላ የሠሩት ሥራ ደግሞ የበለጠ ጥራት ይኖረዋል፡፡ ሰው ዅልጊዜ ያለ ዕረፍት ሊሠራ ይገባዋል የሚሉ ወገኖች ሰዎችን እንደ ሰው ከመቍጠርና ከማክበር ይልቅ እንደ ቍስ የሚቈጥሩና ርኅራኄ የሌላቸው ናቸው፡፡ ሥራዎች የሚሠሩት በሰዎች ብቻ ሳይኾን ለሰዎችም ተብለው መኾኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከባሪያ ፍንገላ ዘመን ጀምሮ በዘመናችን እስከሚገኘው ጭፍን የሀብት ማጋበስ ዘመን ድረስ ሰው ለጥቂት ባለ ሀብቶች የማይጠግብ ምኞት ቁቍስ አምራችና ገንዘብ ፈጣሪ እንዲኾን የሚያስገድደው ዓለማዊው ሥርዓት የሰውን ክብር የሚያሳውቀውን የክርስትና እምነት መቃወሙ አይገርምም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሰው መሥራት እንዳለበት ታስተምራለች፤ በዚያውም መጠን ዕረፍት እንደሚያስፈልገው ታምናለች፡፡

፪. መንፈሳውያን በዓላት ‹‹ካርኒቫል›› ናቸው

መንፈሳውያን በዓላት የሥጋዊ ደስታ መፍጠሪያ መንገዶች እንዲኾኑና ዓለማዊነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲገባ የሚፈልጉ ወገኖች እንደ ጥምቀት ያሉ ክርስቲያንናዊ በዓላት በምዕራቡ ዓለም እንደሚታዩት ዓይነት በአብዛኛው ከባዕድ አምልኮ ጋር የተያያዘ የጀርባ ታሪክ እንዳላቸው በዓላት በስካርና ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ እንዲከበሩ ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የበዓላቱን መንፈሳዊነት አጥፍተው በዓላቱን ፍጹም ዓለማዊ በማድረግ በዓሉ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ብቻ ሲመለከቱት ልብ ያላሉት ሌላ ነገር በዚህ መልኩ በዓላት መከበራቸው ሥርዓት አልባነትን እንደሚያነግሡና የሥነ ምግባር ውድቀት እንደሚፈጥሩ ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚከበሩ በዓላት በምዕራቡ ዓለም ማኅበራዊ ቀውስን ሲፈጥሩ ይታያል፡፡ ከዅሉም በላይ ደግሞ በዓላቱ እውነተኛ ማንነታቸውን ካጡ የቱሪስት መስሕብ መኾናቸውም እንደሚቀር መታሰብ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ጥንታውያን በዓላት ‹‹ካርኒቫል›› ከኾኑማ አንድ ቱሪስት በዚያው በገዛ አገሩ እያለለት ለምን እኛ ዘንድ ይመጣል? ብሎ መጠየቅ ጉዳዩን በጥሞና ለማየት ይጠቅማል፡፡ (‹‹ካርኒቫል›› በዘፈን፣ በጭፈራ፣ ወዘተ በመሳሰሉ ዓለማዊ ባህሎች የሚከበር የአረማውያን በዓል ነው፡፡)

፫. በዓላት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘታቸው መንፈሳዊነታቸውን ይቀንሰዋል

ዛሬ ላይ ያለችው ዘመናዊቷ ዓለም በምዕራባውያን ተጽዕኖ ሥር ያለች በመኾኗ ሳቢያ ምዕራባውያኑ የጐሰቈለ የሥነ ምግባር አቋማቸውን በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል እንዲሠራጭ ያደርጋሉ የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች ልክ የመስቀል በዓል እንደ ኾነው ዅሉ በዓላቱ ዩኔስኮን በመሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና ማግኘታቸውን በበጎ አያዩትም፡፡ የእኛም ቤተ ክርስቲያን እንደ ሌሎች ቤተ እምነቶች ወደ ዓለማዊነት ትንሸራተታለች ብለው ይፈራሉ፡፡ በእርግጥ ለቤተ ክርስቲያን ማሰብና ዓለማዊ ዝንባሌዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ መጠንቀቅ ተገቢና አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

ኾኖም ጠቃሚ ነገሮችን በይኾናል ስጋት ተሸብረን እንዳናስቀራቸው መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢ ክርስቲያናዊ ሐሳቦችን መያዛቸው፣ እነዚህን ሐሳቦች እንደ ሕግ መቀበላቸውና ሀገራት እነዚህን እኩይ ሐሳቦቻቸውን ተቀብለው እንዲሠሩባቸው ጫና መፍጠራቸው ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለ መንቀሳቀሷ የተፈጠረ ክፍተት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖዋን ለማሳረፍ ብትሠራ ዓለም እንደማያሸንፋት ጌታችን ቃል ገብቶላታል፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ በዓሎቻችን በዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና ማግኘታቸው በጎ እንጂ ክፉ አይደለም፡፡ ሥጋቶችን ወደ በጎ ዕድሎች የመቀየር አንዱ ዘዴ በመኾኑ ይህ ጥረት በሌሎች ዘርፎችም ሊቀጥል ይገባል፡፡

፬. በበዓላት የምእመናንን ሱታፌ የሚገድቡ አመለካከቶች

በቤተ ክርስቲያን ዅሉም አካላት ልዩ ልዩ ድርሻ አላቸው፡፡ ካህናቱና ሊቃውንቱ ብቻ አገልግለው ሌላው ምእመን ተመልካች አይኾንም፡፡ በበዓላትም ምእመናን በልዩ ልዩ መንገድ ያገለግላሉ፤ በዓሉን ያደምቃል፡፡ ለምሳሌ በበዓለ ጥምቀት ምእመናን ለየት ባሉ ግጥሞችና ዜማዎች እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ እንሰማለን፡፡ አንዳንድ ዘመን አመጣሽና ጥሩ ያልኾኑ ነገሮች በመጠኑ ቢታዩም በአብዛኛው የሕዝቡ ባህል ክርስቲያናዊ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ታዳጊ ወንዶችና ልጃገረዶች በቡሄና ዘመን መለወጫ በዓላት የሚያዜሙት ዜማ ጠፍቶባቸው፣ ግራ ተጋብተው የምናየው ባህሉ በወጉ ለትውልድ መተላለፍ ባለመቻሉ ነው፡፡ ቀስ በቀስም ‹‹ነይ ነይ እምዬ ማርያም›› የሚለው የእናቶች ዜማ እየተዘነጋ እንዳይመጣ ያሰጋል፡፡ ስለኾነም ከዓለማዊ ዘፈን እና ከባዕድ ባህል ነጻ የኾኑ የሕዝብ የምስጋና ወይም የአገልግሎት ተሳትፎዎች ሊበረታቱ እንጂ ሊነቀፉ አይገባም፡፡

፭. በዓላትን በዓለማዊነት ፈለግ የማክበር ዝንባሌ

መንፈሳውያን በዓላት ከቤተ ክርስቲያን ያገኘናቸው፣ ታላላቅ መንፈሳዊ ትርጕሞችን ያዘሉ፣ ሰማያዊ ምሥጢራትን የያዙ፣ እኛን ከመለኮታዊ መገለጥ ጋር ድልድልይ ኾነው የሚያገናኙን ዕለታት ናቸው፡፡ እነዚህን በዓላት ከዓለም እንደ ተገኙ ዅሉ በዓለማዊ መርሐ ግብሮች ማክበር ከክርስቲያኖች አይጠበቅም፡፡ ከዚያም አልፎ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፣ በመስከር ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ ማሳለፍ የበዓሉን ትርጕም ማዛባት ነው፡፡ በዓላት በሥርዓተ አምልኮ፣ በማኅሌት በቅዳሴ፣ በዝማሬ፣ በቃለ እግዚአብሔር፣ በክርስቲያናዊ ፍቅርና አንድነት፣ አብሮ በመብላት፣ ችግረኞችን በማስታወስ ሊከበሩ እንደሚገባው የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ትምህርቷና ትእዛዟ ነው፡፡

፮. ክርስቲያናዊ በዓላትን ከባዕድ አምልኮ ጋር ማሻረክ

ክርስትና ጣዖትን ያጠፋ ሃይማኖት ነው፡፡ በጥንት ጊዜ በምዕራቡ ዓለም የጌታ ልደት በሚከበርበት ሰሞን ‹‹የፀሐይ ልደት›› እየተባለ የሚታሰብ የጦኦት አምልኮ ነበር፡፡ ሊቃውንቱ አማናዊው ፀሐይ ክርስቶስ ነውና በዚህ ዕለት የጌታችን ልደት እንዲከበር በማድረግ የሕዝቡን ልብ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ እግዚአብሔር መልሰውታል፡፡ በአገራችንም የመስቀል በዓል በሚከበርበት ሰሞን በደቡብ አካባቢ ይታሰብ የነበረውን ጣዖት አምልኮ ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ካስወገዱ በኋላ በምትኩ የጌታችን መስቀል መገኘት መከበር መጀመሩ የሕዝቡን ልብ ከጣዖት አምልኮ እንዲርቅ አድርጎታል፡፡ የሰው መንፈስ ሲዝል ግን የጠፋው ባዕድ አምልኮ ያንሰራራል፡፡ ሰይጣንም ይህን ለማድረግ አይተኛም፡፡ የተሻሩ ጣዖታት አንዳንድ ጊዜ መንፈሳዊ በዓላት ላይ ጥላቸውን ያጠላሉ፡፡ በእመቤታችን ልደት ባዕድ አምልኮን የሚደብሉ፣ በሊቃነ መላእክት በዓላት ላይ በጠንቋይ ታዘው ዝክር የሚዘክሩ ሰዎች አሉ፡፡ እንደዚሁም በመስቀልና በጥምቀት በዓላት ላይ ለሰይጣን የሚሰዉ ዅሉ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ክርስቲያናዊ በዓላት አርክሰዋልና በንስሐ ሊመለሱ፤ ለወደፊቱም ሊጠበቁ ይገባል፡፡

፯. የባዕድ በዓላትን ሳይመረምሩ መቀበል

በየጊዜው ከውጪ ሀገራት በተለይም ከምዕራባዊው ዓለም የሚገቡ በዓላት በዘመናችን ቍጥራቸው እየበዛ ነው፡፡ የእነዚህ ምዕራባዊ ባህሎች ተጽዕኖ ወደ ኢትዮጵያም በመዝለቅ ላይ ነው፡፡ ለአብነትም ‹‹ሀሎዊን›› በመባል የሚያታወቅ ከባዕድ አምልኮ ጋር የተቆራኘ፣ ክርስቲያኖች ሊያከብሩት የማይገባ የአሕዛብ በዓል በውጪ አገር በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከመከበር አልፎ በአገራችንም በአንዳንድ ቦታዎች መከበር መጀመሩ አሳሳቢ ነው፡፡ እንደዚሁም የጌታችንን ልደት በአገራችን የቀን አቈጣጠር ማክበር በቂ ኾኖ ሳለ ‹‹የፈረንጆች ገና›› እያሉ ማክበር ትክክል አይደለም፡፡

፰. የበዓል አከባበርን በባዕዳን ተጽዕኖ መቀየጥ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዓላት በዋዜማ ይጀምራሉ፡፡ ማኅሌት ተቁሞ ስብሐተ እግዚአብሔር ይደርሳል፡፡ ካህናትና ምእመናን በሥርዓት ለብሰው በቤተ መቅደሱ በመገኘት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ያድራሉ፡፡ በበዓሉ ቀንም በየቤታቸው እየተገባበዙ ደስ ብሏቸው ይውላሉ፡፡ አሁን አሁን ግን የበዓሉን ዋዜማ በመሸታ ቤት፣ በዳንኪራና በስካር ማክበር እየተለመደ ስለመጣ ዋዜማን እኛጋ አክብሩ የሚሉ ጥሪዎች ከተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ይጎርፋሉ፡፡ ከዚህም ውጪ ‹‹የገና ዛፍ›› እንደሚባለው ያለ በእኛ ባህል ትርጕምም፣ ጥቅምም የሌለው እንዲያውም ባዕድ ከመኾኑም በላይ የተፈጥሮ ሀብትን የሚያወድምና አካባቢን የሚያራቁት ተግባር በመፈጸም ፈርጀ ብዙ ቀውስ ማድረሳችንን ማቆም አልቻልንም፡፡

፱. በዓላትን የሚያጥላሉ የመናፍቃን አስተሳሰቦች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ማጥላላትና ማጠልሸት እንደ ዋና ሥራና ግብ አድርገው የሚሠሩ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን አጽዋማት ላይ ተቃውሞ እንደሚያነሡት ዅሉ በበዓላቶቿም ላይ የመረረ ተቃውሞን ይሰነዝራሉ፡፡ የመናፍቃኑ ተቃውሞ መጽሐፍ ቅዱስን በጭንብልነት የተጠቀመ ቢመስልም ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃና መነሻ የሌለው ከመኾኑም በላይ እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣረስና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የምናውቀውን የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ያፋለሰ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመናፍቃኑ ሐሳብ እንዳይወሰዱ ወደ ቤተክርስቲያን ቀርበው ሊማሩ፤ ጥያቄዎችን ለመምህራን አቅርበው መልስ ሊያገኙ፤ ስለ በዓላት የተጻፉ መጻሕፍትንም ሊያነቡ ይገባል፡፡ ያ ካልኾነ ግን በዕውቀት ማጣት ምክንያት በመናፍቃን ወጥመድ መያዝና መሳት ይመጣል፡፡

፲. በዓላትን ለወቅታዊ ኹኔታዎች ማስገዛት

አንዳንድ ጊዜ በዓላት በሌሎች ውጫዊ አጀንዳዎች ሲጠመዱ ይታያል፡፡ ለወቅታዊ የአረማውያን ጥቃት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ጽሑፎች የለጠፉ ልብሶችን (ቲ ሸርቶችን) በመልበስ፣ የዛቻና የማስፈራሪያ ይዘት ያላቸው ‹‹የካሴት›› መዝሙሮችን በማሰማት በዓላትን ማክበር አንዱ ችግር ነው፡፡ ሌላው ችግር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ወዘተ. የሚፈጥሩትን አጀንዳ ተሸክሞ በማሰብም ይኹን ባለማሰብ በመንፈሳዊ በዓላት ላይ ማቀንቀን፣ ‹‹ለመቻቻል›› እየተባለ ክርስቲያናዊ ያልኾኑ በዓላትን ማክበር ብዙ ጠንቅ አለው፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ሸቀጣቸው እንዲነሣላቸው የሚፈልጉ ነጋዴዎች የሚፈጥሯቸው በዓላትና የበዓላት አከባበሮች ክርስቲያኖችን የሸቀጥ ሰለባ እንዳያደርገን መጠንቀቅ አለብን፡፡ በአጠቃላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓላትን ስታከብር ሕግን ጠብቃና ሥርዓትን ሠርታ ስለኾነ ምእመናን በዓላትን በምናከብርበት ጊዜ ከኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እንዳንወጣና ሥርዓቱንም እንዳናፋልስ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች!

ይህ ጽሑፍ በጥር ወር ፳፻፱ ዓ.ም በወጣው ፳፬ኛ ዓመት ቍጥር ፱ የሐመር መጽሔት ዕትም፣ ገጽ ፲፬ – ፲፯፤ ‹‹ቤተ ክርስቲያን የሰጠችንን በዓላት እንዴት እናክብራቸው?›› በሚል ርእስ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ 

መንፈሳውያን በዓላት እና አሉታዊ አስተሳሰቦች – ክፍል አንድ

ketera1

በዳዊት አብርሃም

የካቲት ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዓል ‹‹አብዐለ-  አከበረ፤ አስከበረ›› ከሚለው ግስ የወጣ ሲኾን ትርጕሙም የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፤ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፤ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎት፣ ለብሶ፣ አጊጦ የሚዘምርበት፤ ዕልል የሚልበት ማለት ነው (ኪ.ወ.ክ. ገጽ ፪፸፰-፪፸፱)፡፡ ከዚህ መዝገበ ቃላዊ ፍቺ በርከት ያሉ ጽንሰ ሐሳባዊ ትርጕሞችን የምናገኝ ሲኾን የተወሰነቱን እንደሚከተለው እንመልከት፤

በዓላት የሚከበሩ ናቸው

በዓላት ምእመናን ከዘወትር ሥራዎቻቸው አርፈው በምትኩ መንፈሳዊ ተግባራትን በማከናወን የሚያከብሯቸው ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስለ በዓላት አከባበር በተሠራው ቀኖና በበዓላት ወቅት የማይፈጸም መንፈሳዊ ሥራ ስግደት ነው፡፡ ስግደት ሥጋን የሚያደክም ስለኾነ በበዓላት ወቅት አይሰገድም፡፡ ሌሎች መንፈሳዊ ሥራዎች ግን በበዓላት እንዲፈጸሙ ይፈቀዳል፡፡ ተግባረ ሥጋን በበዓላት መተው አስፈላጊ የሚኾንበት ምክንያት መንፈሳዊ ሥራ ለመሥራት እንዲቻል ነው፡፡

በዓላት የደስታ ዕለታት ናቸው

‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና የምስጋና ቃል አሰሙ›› (መዝ.፵፩፥፭) እንደ ተባለው፤ በዓል የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ ከምግብ የሚከለከሉበት ወይም የሚጾሙበት ዕለት ሳይኾን ደስ የሚሰኙበት፣ በደስታ ውስጥም ኾነው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ቀን ነው፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹ደስ ያለው ይዘምር›› (ያዕ. ፭፥፲፬) እንዳለው የደስታ ቀን በኾነው በበዓል ስብሐተ እግዚአብሔር በስፋት ይቀርባል፡፡

በዓላት የዕረፍት ቀናት ናቸው

ሌሎች ቀናት የሥራ ቀናት ናቸው፡፡ በዓላት ግን ከእነዚህ ከብዙዎቹ ቀናት ተለይተው ሰው ከሥራው (ከተግባረ ሥጋው) የሚያርፍባቸው ዕለታት ናቸው፡፡ የበዓላት ጥንት የኾነችው ቀዳሚት ሰንበት እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ ያረፈባት በመኾኑ እግዚአብሔር ሰዎች እንዲያርፉባት፤ በዕረፍትም ኾነው እንዲያከብሯት አዝዟል (ዘፍ. ፪፥፩-፫)፡፡ ኾኖም ማረፍ ማለት እጅና እግርን አጣጥፎ መዋል ማለት አይደለም፡፡ በዓላት ከተግባረ ሥጋ የሚታረፍባቸው ዕለታት ቢኾኑም በበዓላት ወቅት መንፈሳዊ ሥራ መሥራት ተገቢና አስፈላጊ መኾኑ ‹‹ክርስቲያኖች እንደ አይሁድ በዕለተ ቀዳሚት ሥራ ፈትተው መዋል አይገባቸውም፡፡ ይልቁንም ለክርስቲያን እንደሚገባ ሥራ ሊሠሩ ይገባቸዋል፤›› ተብሎ በፍትሐ ነገሥት ታዝዟል፡፡

በዓላት የመታሰቢያ ዕለታት ናቸው

እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ከሥራው ያረፈባትን የሰንበት ዕለት እንድናስባት አዝዞናል፡፡ ተአምራት ያደረገባቸውን፣ እስራኤል ዘሥጋን በግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣበትንና የመሳሰሉትን ዅሉ በበዓላት እንዲታሰቡ አዝዟል (መዝ. ፻፲፥፬)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ‹‹ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› በማለት አዝዟል (ሉቃ. ፳፪፥፱)፡፡ የፈጣሪን ሥራም ብቻ ሳይኾን ቅዱሳን ጻድቃንንና ሥራዎቻቸውን መዘከር የበዓላት አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል›› ተብሎ መጻፉም ስለዚህ ነው (መዝ. ፻፲፯፥፳፬)፡፡

የበዓላት አከባበር

በዓላት በልዩ ልዩ መንገዶች ይከበራሉ፡፡ በበዓላት የሚከናወኑ መንፈሳዊና ሕዝባዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ የተወሰኑ በዓላትን ሕዝብ ወደ ዐደባባይ በመውጣት በጋራ ያከብራቸዋል፡፡ አከባበሩም በዋናነት በጋራ ኾኖ የሚፈጸመውን ሥርዓተ አምልኮና የምስጋና ሥርዓት የሚያመለክት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እስራኤል ዘሥጋ በዓላትን ሊያከብሩ ወደ ዐደባባይ ሲወጡ ይዘምሩ ነበር፡፡ ይዘምሩዋቸው ከነበሩ ዝማሬያት መካከልም በመዝሙረ ዳዊት ከመዝሙር ፻፲፱ እስከ ፻፴፫ ያሉት የመዝሙር ክፍሎች ይገኙባዋል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፴፩)፡፡ ክቡር ዳዊትም በታቦቱ ፊት በቤተ መቅደስ ምስጋና የሚያቀርቡ ካህናትን መድቦ ነበር (፩ኛ ዜ.መ. ፲፮፥፬)፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ በዐደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል ቤተ ክርስቲያን የምታውቃቸው ሁለት ዋና ዋና በዓላት የሚገኙ ሲኾን እነዚህም በዓለ መስቀልና በዓለ ጥምቀት ናቸው፡፡ ከዐደባባይ በዓላት መካከል በዓለ መስቀል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ተርታ ለመመዝገብ የበቃ ታላቅ በዓል ሲኾን ጥምቀትም በዐደባባይ በዓልነቱ ከአማንያኑ በተጨማሪ የብዙዎችን በተለይም የውጪ ቱሪስቶችን በመሳብ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ በዓል ነው፡፡ ከወር በፊት በድምቀት ያከበርነው በዓለ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያናችን ታቦታትን በማውጣት የምታከብረው ዐቢይ በዓል ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የማስተማር ሥራውን የጀመረው በጥምቀት ነው፡፡ በየዓመቱ የጥምቀት በዓል የሚከበረውም ይህን ምሥጢር ለመዘከርና ለመመስከር ነው፡፡

ጌታችን ያሳየውን ትሕትና እና ለእኛ አርአያ መኾኑን ለመመስከር፣ ለጥምቀት ኀይልን ለመስጠት እንደዚሁም ውኃን ለመቀደስ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀቱን በየዓመቱ ታከብራለች፡፡ በየዓመቱ ውኃ ዳር ሔዶ ማክበር በየዓመቱ መጠመቅ ተብሎ እንዳይተረጐምና ሰዎችን እንዳያሳስትም ታስተምራለች፡፡ ይህንኑ ትምህርት ለማስገንዘብም ‹‹የጠበሉን መረጨት አይተው በቀድሞ ዘመን ወደ አገራችን መጥተው የነበሩ ኢየሱሳውያን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ታጠምቃለች ብለው አጥላልተው ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ይህን የምትፈጽመው ጌታችን ለኛ ብሎ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከር፣ የጌታን በረከተ ጥምቀት ለምእመናን ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ምእመናን እየደመለሰች በየዓመቱ አታጠምቅም፤›› ሲሉ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጽፈዋል (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገጽ ፻፳፫)፡፡

የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዓት ከሌሎቹ በዓላት የተለየ ነው፡፡ ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው በበዓሉ ዋዜማ በሕዝብ ታጅበው ወደ ወንዝ ዳር ይወርዳሉ፡፡ በዚያ ዳስ ተጥሎ፣ ከተራም ተከትሮ ሌሊቱን መዘምራኑ በማኅሌት ካህናቱ በሰዓታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡ ይህም ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሔዱ ምሳሌ ነው፡፡ ሲነጋም ጸሎተ ቅዳሴው ተጠናቅቆ ወደ ወንዙ በመሔድ ጸሎተ አኮቴት ተደርሶ፣ ዐራቱ ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል፣ ወንዝም ሲሆን ሰዎች እየገቡ ሊጠመቁ ይችላሉ፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያንም፣ ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ዓባይ ወንዝ ወርደው በድምቀት ያከብሩት ነበር፡፡ ከዐረቦች መግባት በኋላ ግን ከሊፋዎቹ (ሡልጣኖቹ) ስለከለከሏቸው በቤተ ክርስቲያን ብቻ ለማክበር ተገድደዋል (The Coptic encyclopedia P.1103)፡፡

ከበዓለ መስቀል እና በዓለ ጥምቀት በተጨማሪ ‹‹አሸንዳ›› (‹‹አሸንድዬ››) በመባል የሚታወቀውና በሰሜን ኢትዮጵያ የሚከበረው የዐደባባይ በዓልም ሙሉ በሙሉ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚከናወን በዓል ባይኾንም ሕዝቡ በአለባበሱ፣ በአዘማመሩና በሚያደርጋቸው ሌሎች ክዋኔዎች በዓሉ እንደ ሌሎች ሕዝባዊ ባህሎች አረማዊ ወግን ያልተከተለ መኾኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

የበዓላት ፋይዳ

በዓላት በቀዳሚነት የሚከበሩት መንፈሳዊ ዓላማ ይዘው ነው፡፡ ኾኖም በዓላት በሕዝብ የሚከበሩ እንደ መኾናቸው ሌሎች ጥቅሞችም አሏቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰው መሥራት ብቻ ሳይኾን ማረፍም አለበትና በዓላት ለማረፍና ለመዝናናት ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በዅሉም ሀገራት ያሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ግብይትን በማሳለጥና የገንዘብ ዝውውርን በማፋጠን ለአገር ኢኮኖሚ ማደግ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የመስኩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ሌላው የበዓላት ጥቅም ደግሞ ማኅበራዊ ግንኙነትን ማዳበር ነው፡፡ በበዓላት ሰዎች ይገናኛሉ፤ ስጦታዎችን ይለዋወጣሉ፤ ይገባበዛሉ፡፡ በዚህም ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ያዳብራሉ፡፡ በበዓላት ወቅት ችግረኞች ርዳታ ያገኛሉ፡፡

ከዚህም በላይ በዓላት ለባህል ግንባታ ለመልካም ዕሴት መፈጠር ምክንያት ኾነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ በዓላት የቱሪስት መስሕቦችም ናቸው፡፡ እንደ በዓለ መስቀል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኙ፣ እንደ ጥምቀት ብዙ ሕዝብን የሚያሳትፉ በዓላት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከመፍጠራቸውም ባሻገር የውጪ አገር ሰዎች ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው መጥተው እንዲጐበኙ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ በዚህም አገር የውጪ ምንዛሪ ታገኛለች፡፡ ከዅሉም በላይ በዓላት የአገርን ገጽታ ይገነባሉ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን በመሰለች ስሟ በድርቅና በረኀብ ለምትነሣ አገር በዓላት መጥፎ ገጽታንና ክፉ ስምን የሚቀይሩ ፍቱን መድኀኒቶች ናቸው፡፡

ስለ በዓላት አሉታዊ አስተሳሰቦች

የቤተ ክርስቲያን በዓላት የተጠቀሱትና ሌሎች ያልተጠቀሱ በርካታ ጥቅሞች እንዳሏቸው የታወቀ ቢኾንም አንዳንድ ወገኖች ግን በማወቅም ይኹን ባለማወቅ በዓላትን የሚዘልፉና የሚያንቋሽሹ ወይም የበዓላቱን ዓላማ የሚቃረኑ ሐሳቦችን ያዛምታሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከእነዚህ የተቃርኖ ሐሳቦች መካከል ጥቂቶቹን በመጥቀስና የሐሳቦቹን ድክመት በማሳየት ምላሽ እንሰጥባቸዋለን፤

ይቆየን

ክብረ በዓላት በመጽሐፍ ቅዱስ

timket

በዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ

የካቲት ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዓል ማለት ‹‹አብዐለ – አከበረ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ‹‹መታሰቢያ ማድረግ፣ ማክበር›› ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላታቸው ‹‹በዓል (ላት) በቁሙ፣ የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፤ በዓመት፣ በወር፣ በሳምንት የሚከበር፤ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፤ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎት እና ለብሶ፣ አጊጦ የሚዘፍንበት የሚዘምርበት፤ ዕልል የሚልበት፤ ሽብሸባ፣ ጭብጨባ የሚያደርግበት፤ ሲያረግድ እስክስታ ሲወርድ ባንገቱ የሚቀጭበት እንደ ጥጃ የሚፈነጭበት ነው›› በማለት የበዓልን ትርጕም ገልጸውታል፡፡ በአጠቃላይ በዓል ማለት ማሰብ፣ መዘከር፣ ማስታወስ የሚል ትርጕም አለው፡፡

የበዓላት ዑደት

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ይህም ቀን መታሰቢያ ይኹናችሁ፤ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፡፡ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ኾኖ ለዘለዓለም ታደርጉታላችሁ፤›› በማለት በዓል ዘለዓለማዊ መታሰቢያ እንደ ኾነ ተናግሯል /ዘፀ.፲፪፥፲፬-፲፯፤ ዘሌ.፳፫፥፪-፬/፡፡ ስለዚህም በዓላት በዓመታት፣ በወራት እና በሳምንታት ዑደት እየተመላለሱ ይከበራሉ፡፡ በየዓመቱ ከምናከብራቸው መንፈሳውያን በዓላት መካከል በዓለ ልደት፣ በዓለ ጥምቀት፣ በዓለ ትንሣኤ ይጠቀሳሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የልደት በዓልን የምታከብረው ክርስቶስ በየዓመቱ የሚወለድ ኾኖ አይደለም፤ የልደቱን መታሰቢያ ለማሰብ ነው እንጂ፡፡ ጥምቀትን ስታከብርም የወንጌልን አስተምህሮ ተከትላ፣ ምሥጢር አስተካክላ፣ ወቅቱን ‹‹ዘመነ አስተርእዮ›› ብላ ሰይማ የክርስቶስን መገለጥ በማስተማር በዓሉን ታስበዋለች፡፡ የጥምቀት በዓልን እኛ ምእመናን ስናከብርም ዅልጊዜ እንጠመቃለን ማለት አይደለም፤ በዓሉን የምናከብረው ክርስቶስ መጠመቁን ለመዘከር፤ ከበረከቱም ለመሳተፍ ነው፡፡ በዓለ ትንሣኤን የምናከብረውም የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በማሰብ፣ የእኛንም ትንሣኤ ተስፋ በማድረግ ነው እንጂ ጌታችን በየዓመቱ ከሙታን ይነሣል በማለት አይደለም፡፡ ሌሎችን በዓላትም እንደዚሁ፡፡

በዓላትን በማክበራችን ምን ጥቅም እናገኛለን?

፩. በረከት

‹‹አምላክህ እግዚአብሔር በፍሬህ ዅሉ በእጅህም ሥራ ዅሉ ይባርክሃልና እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰባት ቀን በዓል ታደርጋለህ፤ አንተም ፈጽሞ ደስ ይልሃል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ዘዳ.፲፮፥፲፭/ በዓል ማክበር በረከትን ያሰጣል፡፡

፪. ፍጹም ደስታ

በዓል ስናከብር መንፈሳዊ ደስታ ይሰማናል፡፡ በበዓላት ወቅት እርስበርስ በመጠራራት ቤተሰብ ከሩቅም ከቅርብም ይሰባሰባል፤ ዕለቱ የደስታ ቀን ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴም ‹‹አንተም፣ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህ እና ሴት ባሪያህ፣ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለ ሌዋዊ እና መጻተኛ፣ ድሃ አደግ እና መበለትም በበዓል ደስ ይበላችሁ፤›› በማለት በበዓል ቀን በዓሉን በማክበር መደሰት እንደሚገባ ይናገራል /ዘዳ.፲፮፥፲፬/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታ እና የምስጋና ቃል አሰሙ፤›› ይላል /መዝ.፵፪፥፬/፡፡ ነቢዩ ዕዝራ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ደስ አሰኝቷቸዋልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ፤›› ሲል የእስራኤላውያንን በበዓል ቀን መደሰት አስረድቶናል /ዕዝ.፮፥፳፪፤ ፪ኛ ዜና መዋዕል ፴፥፳፫-፳፭/፡፡ በአገራችን አባባልም ‹‹አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም›› እንደሚባለው በዓመት በዓል ሕዝበ ክርስቲያኑ እርስበርስ እየተጠራራ አብሮ በመብላት በመጠጣት ይጫወታል፤ ይደሰታል፡፡

የበዓላት ክብር እኩል ነውን?

በዓላት በክብር ይለያያሉ፤ ለምሳሌ የእመቤታችን በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየወሩ በ፳፩ ቀን ይከበራል፡፡ መስከረም ፳፩፣ ኅዳር ፳፩፣ እና ጥር ፳፩ ቀን ደግሞ የእመቤታችን ዐበይት በዓላት ናቸው፡፡ እንደዚሁም የቅዱስ ሚካኤል በዓል ወር በገባ በ፲፪ኛው ቀን ይከበራል፡፡ ኾኖም ግን የቅዱስ ሚካኤል ዐቢይ በዓል የሚከበረው በየዓመቱ በኅዳር ፲፪ እና ሰኔ ፲፪ ቀን ነው፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ደግሞ በየወሩ በ፲፱ ቀን በዓሉ ቢታሰብም ታኅሣሥ እና ሐምሌ ፲፱ ቀን ዐቢይ በዓሉ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በወር ውስጥ የሚገኙትን እያንዳንዱን ቀናት በቅዱሳን ስም ብትሰይምም በዓላትን በዐቢይነትና ታቦታትን በማውጣት የምታከብራቸው በዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ሥርዓትም በዓላት በአከባር የተለያዩ መኾቸውንና ልዩ የበዓል ቀኖችም እንዳሉ እንረዳለን፡፡ በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ ምዕራፍ ፴፥፳፮ ላይ ‹‹በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ኾነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተደረገም ነበር፤›› ተብሎ የተጻፈው ኃይለ ቃል ለዚህ ማረጋገጫችን ነው፡፡

በዓላትን አለማክበር ምንን ያመጣል?

፩. ረድኤተ እግዚአብሔርን ያርቃል

በሰቆቃወ ኤርምያስ ምዕራፍ ፩፥፬ ላይ ‹‹ዳሌጥ፣ ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፡፡ በሮችዋ ዅሉ ፈርሰዋል፡፡ ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ፡፡ እርስዋም በምሬት አለች፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ በዓላትን በማክበራችን ከእግዚአብሔር በረከትን እንደምንቀበል ዅሉ ባለማክበራችን ደግሞ ረድኤተ እግዚአብሔር ከእኛ ይርቃል፡፡

፪. ቅጣትን ያስከትላል

በመጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ እንደ ተገለጸው የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ ነቢዩ ዳዊት በደስታ ምስጋና ያቀርብ ነበር፡፡ ሚስቱ ሜልኮል ግን ሲዘምር ባየችው ጊዜ ንጉሥ ኾኖ ሳለ ራሱን አዋረደ በሚል ሐሳብ ባለቤቷ ንጉሥ ዳዊትን ናቀችው፡፡ ዳዊትም ሜልኮልን ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እኾን ዘንድ ከአባትሽ እና ከቤቱ ዅሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይኹን፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እዘምራለሁ፤›› በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ እንደሚያስከብርና ከፍ ከፍ እንደሚደርግ ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔርም ለአምላኩ የዘመረውን ዳዊትን በመናቋ ልጅ እንዳትወልድ የሜልኮልን ማኅፀን ዘግቶታል /፪ኛ ሳሙ. ፮፥፲፮-፳፫/፡፡ ከዚህ ታሪክ በዓሉን ብቻ ሳይኾን በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎችንም ማክበር እንደሚገባን እንማራለን፡፡ ‹‹ዕልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ.፹፱፥፲፭/፡፡

በክብረ በዓላት ምን ዓይነት ልብስ መልበስ አለብን?

ሰው ወደ ሰርግ ሲጠራ ከቤቱ ያለውን፣ የተሻለውን ልብስ መርጦ እንዲለብስ መንፈሳውያን በዓላት የቤተ ክርስቲያን የክብሯ መግለጫ ቀናት እንደ መኾናቸው መጠን እኛ ክርስቲያኖችም በእነዚህ ቀናት የምንለብሰው ልብስ የተለየ መኾን ይገባዋል፡፡ የሌሊት ልብስ ለብሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ እንደማይገባ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡ በገዳማውያን አባቶች ዘንድ ለቅዱስ ቍርባን መቀበያ የሚኾን ልብስ ከሌሎች አልባሳት ተለይቶ ውኀ፣ ጭስ፣ አቧራ ከማይደርስበት ቦታ ይቀመጣል፡፡ አባቶች ይህንን ልብስ የሚለብሱት ለቅዱስ ቍርባን ብቻ ነው፡፡ በገጠሩ የአገራችን ክፍልም ልጆች ልብስ የሚገዛላቸው በአብዛኛው በጥምቀት ወቅት ነው፡፡ ይህም ለበዓሉ የሚሰጠውን ልዩ ክብር ያስረዳናል፡፡ እናቶቻችንም ‹‹ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› እያሉ በበዓለ ጥምቀት ያላቸውን አዲስ ቀሚስ አውጥተው ይለብሳሉ፡፡

በዓመት በዓል ቀን እንስሳት የሚታረዱት ለምንድን ነው?

በዓል ሲደርስ ገበያው ይደምቃል፤ ቤታችን ያምርበታል፡፡ እንበላቸው ዘንድ የተፈቀዱ እንስሳት ይታረዳሉ፡፡ በተለይም በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ለፋሲካ፣ ለልደት እየተባለ በግ ተቀጥቅጦ  ይቀመጥና ጊዜው ሲደርስ ይታረዳል፡፡ በበዓላት ቀን የከብት፣ የበግ፣ የፍየል መሥዋዕት ይቀርብ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ መጽሐፈ ዕዝራ ፫፥፬ ‹‹እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዓቱም ለዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ፤›› ይላል፡፡ ዛሬም በበዓላት ቀን በየቤተ ክርስቲያኑ እና በየቤቱ የሚታረደው ይህንኑ አብነት በማድረግ ነው፡፡ (በተጨማሪም ዘሌ.፳፫፥፴፯፤ ሕዝ.፵፮፥፲፩ ይመልከቱ)፡፡

በአጠቃላይ በዓላትን ከሥጋዊ ሥራ ተከልክሎ ማክበር እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ ‹‹በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኹንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ዅሉ አትሥሩበት፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ዘሌ.፳፫፥፯/፡፡ የበዓላት አከባበርም እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ በኾነ ባህል ሳይኾን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ፤ የበዓሉን መንፈሳዊ ታሪክ በተመረኮዘ መንገድ የተሰጠን ትእዛዝ ነው፡፡ ዮሴፍ ወልደ ኮሪዮን በዜና አይሁድ መጽሐፉ እንደ ጠቀሰው አይሁድ በዕለተ ሰንበት ወደ መጸዳጃ ቤት እንኳን አይሔዱም ነበር፡፡ እኛ ግን እንደ አይሁዳውያን በተጋነነ መንገድ ሳይኾን ሰውነትን ከሚያደክም ሥጋዊ ሥራ ተከልክለን በዓላትን እንድናከብር በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ አስቀድማ በሕገ ልቦና እግዚአብሔርን ስታመልክ የኖረች በኋላም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕፀ መስቀሉ የቀደሳት፣ በኪደተ እግሩ የባረካት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው መንፈሳውያን በዓላትን በሥርዓት ሲያከብሩ ኖረዋል፡፡ አሁን አሁን ግን በብዙዎቻችን ዘንድ እንደሚስተዋለው የበዓላት አከባበር ሥርዓት እየተጣሰ ይገኛል፡፡ በበዓላት ቀን ሥራ መሥራት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ልማድ ሊስተካከልና ሊቀረፍ ይገባል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም እንደ በዓለ ጥምቀት ባሉ የዐደባባይ በዓላት ወቅት የሚታየው የሥጋዊ ገበያ ግርግር ክርስቲያናዊ የበዓላት አከባበር ሥርዓትን እንዳያጠፋብን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡

በአገራችን ብሂል ‹‹በዓል ሽሮ የከበረ፣ ጦም ገድፎ የወፈረ የለም›› እንደሚባለው በዓላትን መሻር ከሚሰጠው ትርፍ ይልቅ የሚያመጣው መቅሠፍት ይብሳልና በዓላትን ለሥጋዊ ጉዳይ መጠቀሚያ ከማድረግ ይልቅ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገን በአግባቡ ማክበር ይገባናል፡፡ አንድ ክርስቲያን መንፈሳውያን በዓላትን በሥርዓት ሲያከብር የሚመለከቱ አካላት ‹‹ሃይማኖቱ እንዴት ደስ ይላል? እኛም እንደ እርሱ በኾንን›› በማለት እርሱንም ሃይማኖቱንም ያደንቃሉ፤ መንፈሳዊ ቅናትንም ይቀናሉ፡፡ ስለዚህም የጥንቱን ሥርዓት ጠንቅቀን፣ መልኩን ሳንለውጥ፣ ሥርዓቱንም ሳናፋልስ በዓላትን ማክበር ይገባናል፡፡ በዓላትን በሥርዓቱ አክብረን በረከትን እናገኝባቸው ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ኢትዮ አሜሪካውያን ሕፃናት መዓርገ ዲቁና ተቀበሉ

usa

ጥር ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን ሰሜን አሜሪካ ማእከል ዋሺንግተን ስቴት በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል ለመዓርገ ዲቁና የሚያበቃ የአብነት ትምህርታቸውን ለሁለት ዓመታት ሲከታተሉ የቆዩ ኢትዮ አሜሪካውያን ሕፃናት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዋሺንግተን እና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መዓርገ ዲቁና ተቀበሉ፡፡

ሕፃናቱ መዓርገ ዲቁና የተቀበሉት በዓለ ጥምቀት በሲያትል ከተማ በተከበረበት ጥር ፲፬ ቀን እና የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በሲያትል ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተዘከረበት ጥር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ነው፡፡

ዲያቆናት

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከዲያቆናቱ ጋር

በተያያዘ ዜና ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማእከል ከሲያትል ንዑስ ማእከል በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ማሠልጠኛ ማእከል ባትል ከተማ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤትን ጐብኝተዋል፡፡ ለተመራቂ ተማሪዎችም የአንገት መስቀል አበርክተውላቸዋል፡፡

በዕለቱ የአካባቢው ማኅበረ ካህናትና የተማሪዎቹ ወላጆች ለብፁዕነታቸው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲኾን የትምህርት ቤቱ የአብነት መምህር በግእዝ እና አማርኛ ቋንቋዎች መወድስ ቅኔ፤ ተማሪዎቹም የቃል ትምህርትና ምስባክ አቅርበዋል፡፡

uu

በመርሐ ግብሩ ላይ የትምህርትና ሥልጠና ማእከሉ በሲያትል ንዑስ ማእከል ውስጥ በሲያትል፣ በቤልቪዉ እና በባትል፤ እንደዚሁም በሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ባሉ ሦስት ከተማዎች በድምሩ በስድስት ትምህርት ቤቶች ከ፪፻ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ፤ በዚሁ ትልቅ ድካምና ጥረት በሚጠይቀው አገልግሎት ውስጥ ከማኅበሩ አባላት በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ መምህራን፣ ካህናትና ዲያቆናት እንደዚሁም ሰባክያነ ወንጌል እና ወላጆች የሚያደርጉት አስተዋጽዖ የጎላ መኾኑ ለብፁዕነታቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም በአሜሪካ ማእከል የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል አማካይነት በውጭው ዓለም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተተኪ አገልጋይና ምእመናንን ለማፍራት ማኅበረ ቅዱሳን እያበረከተ ስለሚገኘው አተዋጽዖ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

u

ብፁዕነታቸውም ‹‹በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ›› በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ሲሰጡ ማኅበረ ቅዱሳን ከመነሻው ጀምሮ ዓላማውና ተልእኮው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተተኪዎችን ማፍራትና ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት መኾኑን እንደሚያውቁ ገልጸው አሁንም ማኅበሩ በማከናወን ላይ የሚገኘውን መንፈሳዊ አገልግሎት አድንቀዋል፡፡

በማእከሉ በተመለከቱት መልካም ተግባር በከፍተኛ ኹኔታ መደሰታቸውንና ይህ ሥራም ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን እየገጠማት ባለው ፈርጀ ብዙ ፈተና የተወሰነውን አገልግሎት ሊቀርፍ የሚችል ተግባር መኾኑን ጠቅሰው ማኅበረ ቅዱሳንን፣ የማእከሉ መምህራንን፣ ወላጆችን እና ተማሪዎችን በአጠቃላይ ዅሉንም ባለ ድርሻ አካላት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል አመስግነዋል፡፡

በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳን እና ጸሎተ ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ኾኗል፡፡

ምንጭ፡- በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል

ታላቅ የምሥራች ለኦርቶዶክሳውያን ምእመናን!

app-01

በማኅበረ ቅዱሳን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል የተሠራው ‹‹ተዋሕዶ›› የተሰኘው የስልክ አፕሊኬሽን አንድሮይድ (Android) የተባለውን የቴክኖሎጂ ውጤት ለሚጠቀሙ ዘመናዊ ስልኮች እና የኪስ ኮምፒውተሮች አመቺ በኾነ መልኩ እንደገና ተሻሽሎ ቀረበ፡፡

ይህ አፕሊኬሽን በ፳፻፮ ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲኾን፣ ክፍሉ ከተጠቃሚዎቹ የደረሱትን አስተያየቶች በማካተት ልዩ ልዩ ማሻሻያዎችን አድርጎ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡

አፕሊኬሽኑ በውስጡም የጸሎት መጻሕፍትን፣ ወቅታዊ የኾኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን፣ ዜናዎችን እና ልዩ ልዩ መረጃዎችን፤ ያሬዳውያን መዝሙሮችን፣ መንፈሳዊ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን፤ እንደዚሁም የየዕለቱ ምንባባትን እና የሬዲዮ ሥርጭቶችን፤ የቀን መቍጠሪያዎችን፣ የበዓላትና አጽዋማት ማውጫዎችን፤ በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ እና በአውሮፓ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚከናወኑ መርሐ ግብራትንና ሌሎችንም አርእስተ ጉዳዮች አካቷል፡፡

በልዩ ልዩ የመገናኛ መንገዶችና ገጾች ላይ በሃይማኖት ስም የሚጻፉ የኑፋቄ ትምህርቶች በስፋት በሚለቀቁበት በዚህ ዘመን ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት መዘጋጀቱ ለምእመናን ታላቅ የምሥራች ነው፡፡

ስለዚህም አንድሮይድ (Android) የተሰኘውን የቴክኖሎጂ ውጤት መጠቀም የሚችል ዘመናዊ ስልክ ወይም የኪስ ኮምፒዩተር ያላችሁ ምእመናን ዅሉ ከጎግል ፕለይ (Google Play) ውስጥ ተዋሕዶ (Tewahedo) የሚለውን ቃል በመፈለግ በዚህ አፕሊኬሽን እንድትጠቀሙና ኦርቶዶክሳዊ ይዘት ባለው ቃለ እግዚአብሔር ነፍሳችሁን እንድታጠግቡ፣ አእምሯችሁንም በመንፈሳዊ ዕውቀት እንድታጎለብቱ ስንል መንፈሳዊ ግብዣችንን እናቀርባለን፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል ይኼንኑ አፕሊኬሽን አይ ኦ ኤስ (IOS)ን ለሚጠቀሙ የእጅ ስልኮች እና የኪስ ኮምፒውተሮች ከአሁን በፊት ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡

ታላቁ የቅኔ ጉባኤ ቤት በእሳት ወደመ

chegodie

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት በቋሪት ወረዳ ቤተ ክህነት ልዩ ስሙ ፈንገጣ በሚባል ቀበሌ በጨጎዴ ሐና የተቋቋመው፤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ሲያፈራ የኖረውና እስከ አሁን ድረስም ሊቃውንትን የመተካት ተልእኮውን በመወጣት ላይ የሚገኘው የሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው የቅኔ ምስክር ጉባኤ ቤት ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ረፋድ ላይ ድንገት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ወደመ፡፡

100_0718

የጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው ከከፊል ደቀ መዛሙርታቸው ጋር (ጉባኤ ቤቱ በእሳት ከመቃጠሉ በፊት)

በቦታው የተገኙ የዓይን እማኞች እንደሚያስረዱት በአካባቢው ያለው የአየር ጠባይዕ ነፋሻ ከመኾኑ፣ ጉባኤ ቤቱ ከእንጨትና ከሣር ከመሠራቱ ባሻገር ደቀ መዛሙርቱ ለክብረ በዓል በወጡበትና የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን በሔዱበት ሰዓት ቃጠሎው መከሠቱ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል፡፡

ድንገት በደረሰው በዚህ የእሳት ቃጠሎ ሁለት መቶ ሃያ አምስት የደቀ መዛሙርት መኖሪያ ጎጆዎች፣ ልዩ ልዩ መጻሕፍት፣ ምግብ እና አልባሳት በአጠቃላይ ከሰባት መቶ ስልሳ ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የፍኖተ ሰላም ማእከል የላከልን ዘገባ ያመላክታል፡፡

ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ጉባኤ ቤቱ ከአምስት መቶ እስከ ስድስት መቶ የሚደርሱ ደቀ መዛሙርት ይማሩበት የነበረ ሲኾን በአሁኑ ሰዓትም በከፊል ከቃጠሎው በተረፈው የጉባኤ ቤቱ ማኅበር ቤት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

chegodie

የእሳት ቃጠሎው ያደረሰው ጉዳት በከፊል

የቋሪት ወረዳ ማእከል ከቦታው ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጸው እሳቱ የተነሣው ከጉባኤ ቤቱ አጥር አካባቢ ሲኾን፣ እሳቱ በምን ምክንያትና በማን አማካይነት እንደ ተለኮሰ ለማረጋገጥ መንሥኤው በፖሊስ በመጣራት ላይ ይገኛል፡፡

ለደቀ መዛሙርቱ ምግብ፣ መጠለያና አልባሳት ድጋፍ ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚገባም የምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት ከፍኖተ ሰላም ማእከልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን ውይይት በማካሔድ ላይ እንደሚገኝ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን ቀሲስ አያና በላቸው ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ጉባኤ ቤቱን ወደ ነበረበት ህልውና ለመመለስ፤ ደቀ መዛሙርቱን ከመበተንና የጉባኤውን ወንበርም ከመታጠፍ ለመታደግ እንችል ዘንድ ‹‹መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፋችሁ አይለየን?›› ሲሉ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው በጉባኤ ቤቱ ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ቤት ላይ በደረሰው ጉዳት ለጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው፣ ለደቀ መዛሙርቱና ለአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን መጽናናትን ይመኛል፡፡

በሐዊረ ሕይወቱ መደሰታቸውን ተሳታፊዎች ተናገሩ

በዝግጅት ክፍሉ

ታኅሣሥ ፳፯ ቀን ፳፻፱ .

img_0298

ዓለም ገና ደብረ ናዝሬት ኢየሱስ ክርስቶስ እና ቅድስት ማርያም ገዳም

img_0351

፲፩ኛው የማኅበረ ቅዱሳን ሐዊረ ሕይወት በዓለም ገና ደብረ ናዝሬት ኢየሱስ ክርስቶስ እና ቅድስት ድንግል ማርያም ገዳም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን፣ አባቶች ካህናትና ዐሥራ አንድ ሺሕ የሚኾኑ ምእመናን በተገኙበት ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም መካሔዱ የሚታወስ ነው፡፡

img_0325

በሐዊረ ሕይወቱ ጠዋትና ከሰዓት በኋላ በተከናወነው መርሐ ግብር በብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ በማኅበሩ ሰባክያነ ወንጌል መ/ር ምትኩ አበራና መ/ር ያረጋል አበጋዝ ልቡናን የሚገዛና ድካመ ነፍስን የሚጠግን ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡

img_0296

ምክረ አበው አቅራቢ አባቶች

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ለ ‹‹ምክረ አበው›› በተጋበዙት በቆሞስ አባ ሳሙኤል በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉያትና ሐዲሳት ትርጓሜ መምህር፤ በአባ ገብረ ኪዳን በደቡብ ጎንደር እስቴ መካነ ኢየሱስ ደብር የአባ ኤስድሮስ ጉባኤ ቤት የሐዲሳት ትርጓሜ መምህርና የብሉያት ደቀ መዝሙር፤ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ በአዲስ አበባ የምሥራቀ ፀሐይ ቀበና መድኀኔ ዓለም ደብር የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር እና የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ የብዙ ምእመናንን ጥያቄ የሚመልስ ትምህርት ቀርቧል፡፡

img_0333

የማኅበሩ መዘምራን ወረብና መዝሙር ሲያቀርቡ

በማኅበሩ ዘማርያንና በሊቀ መዘምራን ዲ/ን ቴዎድሮስ ዮሴፍ የቀረበው ያሬዳዊ ወረብና መዝሙርም የጉባኤው ክፍል ነበር፡፡

የሐዊረ ሕይወቱ ዐቢይ ኰሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኤርምያስ ዓለሙ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቁት ትኬት በመግዛት የመጡ ስምንት ሺሕ፤ ለልዩ ልዩ አገልግሎት ለመስጠት የተመደቡ አንድ ሺሕ፤ ከዓለም ገና እና ከአካባቢው የመጡ ደግሞ በግምት ሁለት ሺሕ፤ በድምሩ ዐሥራ አንድ ሺሕ የሚኾኑ ምእመናን በመርሐ ግብሩ ላይ የታደሙ ሲኾን በሐዊረ ሕይወቱ መደሰታቸውንም ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ቃለ ምዕዳን በሰጡበት ወቅት ‹‹ይህ ጉባኤ በዚህ ቦታ መዘጋጀቱ ለገዳሙ ብቻ ሳይኾን አጠቃላይ ለሀገረ ስብከታችን ትልቅ ዕድል ነው፤ በዚህ አካባቢ የሚገኙ ምእመናንም በመርሐ ግብሩ ትልቅ ተስፋ አግኝተዋል፤›› ካሉ በኋላ ‹‹ይህንን ጉባኤ በዚህ ቦታ በማካሔድ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስደሰቱ ማኅበሩን አመስግነዋለሁ፤›› በማለት የማኅበሩን አገልግሎት አበረታተዋል፡፡

ብ

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከከፊል የጉባኤው ተሳታፊዎች ጋር

ከመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሐዊረ ሕይወቱ በመሳተፋቸው በርካታ መንፈሳዊ ቁም ነገር ማግኘታቸውን፣ በትምህርቱ ነፍሳቸው መርካቷንና አእምሯቸውም መደሰቱን ጠቅሰው ይህን ዅሉ ምእመን በአንድ ድንኳን ሥር አሰባስቦ፤ ቍርስ እና ምሳ መግቦ ቃለ እግዚአብሔር እንዲማር በማድረጉ ማኅበረ ቅዱሳንን አድንቀዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹መርሐ ግብሩ ከዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይኾን በየወሩ ቢካሔድልን?›› የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ed

የጉባኤው ተሳታፊ አባቶችና ወንድሞች በከፊል

የዓለም ገና እና የአካባቢው ማኅበረ ካህናትና ምእመናንም ሐዊረ ሕይወቱ በአካባቢያቸው በመካሔዱ ካገኙት መንፈሳዊ ትምህርት ባሻገር ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ መንፈሳዊ ጉባኤ የማዘጋጀት ልምድን ከማኅበረ ቅዱሳን መማራቸውንም ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ በማኅበሩ ሰብሳቢ በአቶ ታምሩ ለጋ የማኅበሩ መልእክት የቀረበ ሲኾን በመልእክቱም ማኅበሩ በሚያበረክተው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመሳተፍ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በጋራ ለመደገፍና አገልግሎቷን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ መላው ሕዝበ ክርስቲያን የበኩሉን እገዛ ያደርግ ዘንድ ሰብሳቢው ጥሪያቸውን በቤተ ክርስቲያን ስም አስተላልፈዋል፡፡

wo

የጉባኤው ተሳታፊ እናቶችና እኅቶች በከፊል

እንደዚሁም የማኅበሩ የስድስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎችን የስልታዊ ዕቅዱ ክንውንና ትግበራ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ፋንታኹን ዋቄ አቅርበው ለዕቅዱ መሳካትም ምእመናን በሚቻላቸው ዓቅም ዅሉ የድርሻቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበርክቱ አሳስበዋል፡፡

በመቀጠልም ሐዊረ ሕይወቱ በተሳካ ኹኔታ እንዲከናወን ድጋፍና ትብብር ያደረጉ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስንና የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችን፤ የሰበታ አዋስ ወረዳ ቤተ ክህነትና ወረዳ ማእከሉን፤ የደብረ ናዝሬት ኢየሱስ ክርስቶስና ቅድስት ማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትን፣ ማኅበረ ካናትንና ምእመናንን፤ ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ በየደረጃው እስከ ከተማ አስተዳደሩ ድረስ የሚገኙ የመንግሥት አካላትን ማኅበሩ በእግዚአብሔር ስም አመስግኗል፡፡

11

መርሐ ግብሩ በጸሎት ሲፈጸም

በመጨረሻም ፲፩ኛው የማኅበረ ቅዱሳን ሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ተፈጽሟል፡፡

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የእሳት ቃጠሎ ደረሰበት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

sebeta

የተቃጠለው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ወለልና የሕንጻው ቍሳቍስ በከፊል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰበታ ወረዳ ቤተ ክህነት የሚገኘውና በጥር ወር ፳፻፮ ዓ.ም የተመሠረተው የሰበታ ዋታ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና በዓታ ለማርያም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከጠዋቱ ፪ ሰዓት ከ፴ ደቂቃ አካባቢ የእሳት ቃጠሎ ደረሰበት፡፡

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ በቆርቆሮና በኮምፖርሳቶ ከመታነጹ በተጨማሪ ቃጠሎው የደረሰው ካህናቱ አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከቤተ ክርስቲያን ከወጡ በኋላ መኾኑ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል፡፡

የቃጠሎው መንሥኤ እስካሁን በግልጽ እንዳልታወቀና በቃጠሎውም ከጽላቶቹ በስተቀር ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ በሙሉ እንደ ወደመ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ሐዋዝ ተስፋ ለማኅበረ ቅዱሳን ሚድያ ክፍል አስታውቀዋል፡፡ እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ ከአምስት መቶ ሺሕ ሰማንያ ብር በላይ የሚገመቱ ንዋያተ ቅድሳት በቃጠሎው ወድመዋል፡፡

sebeta-copy

በቃጠሎው የወደሙ ንዋያተ ቅደሳት በከፊል

የማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጠኞች ቦታው ድረስ በመሔድ እንደ ተመለከትነው ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ረፋድ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በደብሩ ተገኝተው ማኅበረ ካህናቱንና ሕዝበ ክርስቲያኑን አጽናንተዋል፤ የደብሩን ይዞታ የሚያስከብርና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን የሚያስገነባ የልማት ኰሚቴም አስመርጠዋል፡፡ እንደዚሁም የሰበታ ወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ የየአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን ለሕንጻው ማሠሪያና ለንዋያተ ቅድሳት መግዣ የሚኾን ገንዘብ በማሰባሰብ ለልማት ኰሚቴው አበርክተዋል፡፡

አቡነ ሳዊሮስ

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

ብፁዕነታቸው በዕለቱ ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ የልማት ኰሚቴው ከሐሜት በጸዳ መልኩ የማያድግምና ዘላቂ የኾነ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ለሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ብቻ ሳይኾን ለሃይማኖታችን መጠበቅና ለምእመናን አንድነትም ዘብ መቆም ይገባዋል ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ዅሉ የደረሰው በእኛ ኀጢአት ነው›› ያሉት ብፁዕነታቸው የደብሩ አገልጋይ ካህናትና የአካባቢው ምእመናን ጥላቻንና መለያየትን በማስወገድ፤ ከኀጢአት በመራቅ፤ በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት በመኾን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት እንዲያገለግሉ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያም በደብሩ ላይ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ከማጥፋት ጀምሮ መቃኞ ቤት በመሥራትና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍና ትብብር ያደረጉትን ምእመናንና በአካባቢው የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮችን አመስግነዋል፡፡

መቃኞ

በአካባቢው ነዋሪዎች ትብብር የታነጸው መቃኞ ቤት

በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የደረሰውን የቃጠሎ አደጋ ሰበካ ጉባኤው ለፖሊስ ሪፖርት እንዳደረገና በቃጠሎው ዕለትም የሰበታ ወረዳ ኮማንድ ፖስት፣ የጸጥታ ዘርፍ ሠራተኞችና ሌሎችም የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደ ተገኙ የተናገሩት አስተዳዳሪው የቃጠሎው መንሥኤ እስኪጣራ ድረስም የደብሩ ሰሞነኛ ካህናትና የጥበቃ ሠራተኞች በሕግ ከለላ ሥር ይገኛሉ ብለዋል፡፡

አማንያንም ኾኑ ኢአማንያን የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ በመረባረብ ለታቦተ ሕጉ መቀመጫ የሚኾን ጊዜያዊ መቃኞ ቤት ማነጻቸውን ያስታወቁት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ እንደ ገና ታድሶ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድም የመላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍና ርዳታ አይለየን ሲሉ በቤተ ክርስቲያን ስም ጥሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡