‹‹ወዕለቱሰ ለእግዚአብሔር ግብተ ትመጽእ ከመ ሰራቂ፤ የእግዚአብሔር ቀን እንደሌባ ድንገት ትመጣለች›› (፪ ጴጥ.፫፥፲)

መጋቤ ሐዲስ ምስጢረ ሥላሴ ማናየ

ደብረ ዘይት ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ምሥጢረ ምጽአቱን ያስተማረበት፤ የገለጠበት፤ ደቀ መዛሙርቱም የመምጣቱን ምሥጢር የተረዱበት፤ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ በወይራ ዛፍ የተሞላ፤የተከበበ ተራራ ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው አዘውትሮ ከተመላለሰባቸው ቦታዎችም አንዱ ነው፡፡ ቀን በምኩራብ ሲያስተምር ውሎ ሌሊት ሌሊት በደብረ ዘይት ያድር እንደነበር ቅዱስ ወንጌል ምስክር ነው፡፡

 ‹‹መዓልተ ይሜህር በምኩራብ ወሌሊተ ይበይት ውስተ ደብረ ዘይት፤ ዕለት ዕለት በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደሚባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር›› እንዲል ሉቃ፤ ፳፩፥፴፯። ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን በደብረ ታቦር እንደገለጠ ምሥጢረ ምጽአቱን በደብረ ዘይት ገልጧል፡፡ ይህንንም ሲገልጥ ሦስቱ የምሥጢር ደቀ መዛሙርት ተብለው የሚጠሩት ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ጴጥሮስ የዚህ ምሥጢር መደበኞች እንደነበሩ መተርጒማን አስተምረዋል፡፡ ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይንገር የነበረ እንዲሉ አበው ያን ጊዜ የተገለጠለትን የጌታችንን የመምጣት ቀን ‹‹የእግዚአብሔር ቀን እንደሌባ ድንገት ትመጣለች›› በማለት በዘመኑ፣ ኅልፍተ ሰማይ ወምድር፣ በዘመኑ ሙታን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚል የስንፍና ትምህርት ይዘው ክርስቲያኖችን ያወናብዱ ለነበሩ ቢጽ ሐሳውያን ትንሣኤ ሙታን እንዳለ ገልጾ ጽፏል፡፡

ታዲያ ከእኛ ቀድመው የሞቱት ለምን ቀድመውን ተነሥተው አናይም? መከር አንድ ጊዜ ይካተታልን? ከሰማይስ ከፊሉ ታንጾ፣ ከመሬቱስ እኩሌታው ተጐርዶ ሲወርድ ለምን አናይም? እያሉ ሲያስቸግሩ ትምህርቱን ሲነቅፉ የክርስትናውን ትምህርት ሲያጐድፉ ለነበሩት በክሕደት ለሚመላለሱ ሰዎች ነው ይህን የጻፈው፡፡ የእግዚአብሔር ቀን ማን ናት? የሚለውን ማየት ጥሩ ነው፤ የእግዚአብሔር የተለየች ቀንስ አለችው? ቀናት በሙሉ የማን ሆነው ነው? የሚል ሐሳብ በውስጣችን መመላለሱ አይቀርም፤ እውነት ነው! ቀናቱ ሁሉ የእርሱ ናቸው፡፡ እርሱ ያለ ቀንና ያለ ጊዜ ከዘመን በፊት የነበረ ‹‹ያለና የሚኖር›› አምላክ ሲሆን ቀናትን የሰጠን ዘመናትን በልግስና የቸረን እርሱ ነው፤ ሁሉ ቀናት የእርሱ ገንዘቦች መሆናቸውን መጻሕፍት ያስተምራሉ፤ ‹‹ዚኣከ ውእቱ መዓልት ወዚኣከ ውእቱ ሌሊት – አቤቱ ቀኑ ያንተ፤ ሌሊቱም የአንተ ነው›› መዝ.፸፫፥፲፮። ሁሉም ባሪያዎችህ ናቸው፤ ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል፤ መዝ ፻፲፱፥፲፮፡፡

ዕለተ ምጽአት

የቀናት ሁሉ ማጠቃለያ፤ የሁሉም ፍጻሜ ዕለተ ምጽአት፣ ዳግም ምጽአት፣ የመጨረሻዋ ዕለት ናት፡፡ ቀን የምትባለው ከዕለተ ፍጥረት ጀምሮ ያለው ሥጋዊና ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ፍጻሜውን የሚያገኝባት፤ ክፉም ደጉም የሠራው እንደየሥራው መጠን ዋጋውን የሚቀበልባት፤ የጭንቅ፣ የመከራ ቀን፤ ይህ ዓለም የሚያልፍባት፤ የሁሉም ፍጻሜ የሆነች ቀን ናት፡፡ ጌታችን ስለሚመጣባት የጌታ ቀን ተብላም ትጠራለች፡፡ ስለዚህ የመጨረሻዋ ቀን ዕለተ ምጽአት ወይም  በሌላ አነጋገር የፍርድ ቀን ስለተባለችው ነቢያት፣ ራሱ ጌታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት አስተምረዋል፡፡ ቀዳማዊ ምጽአቱን እንደ ዘር ደኃራዊ ዳግም ምጽአቱን እንደ መከር አድርጐ ዓለም ይጠብቀዋል፤ በመጀመሪያው ምጽአቱ ትሕትናውን በዳግም ምጽአቱ ግርማውን ዓለም ሁሉ ያያል፤ መጀመሪያ በትሕትና መጣ ዓለምን አስተማረው፤ በኋላ በግርማ መንግሥት በክበበ ትስብእት ይመጣል፤ ይህ የጌታ ቀን ተበሎ ይጠራል፡፡ ‹‹እነሆ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፤ ሚል.፬፥፩፡፡

ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኃለሁ››ሚል.፬፥፭፡፡ ‹‹የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ መክ.፲፪፥፩። ያ ቀን የመዓት፤ የመከራ፤ የጭንቀት፤ የመፍረስ፤ የመጥፋት፤ የጨለማ ፤ የጭጋግ፤ የደመናና፤ የድቅድቅና ጨለማ ቀን ነው›› ሶፎ. ፩፥፲፭።

‹‹እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፤ መጥቶም ዝም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነድዳል›› መዝ. ፵፱፥፫። በዚያች ቀን ለእያንዳንዱ እንደየሥራው መጠን የሚከፍል መሆኑን አስረድቷል፤ እንደ ቀድሞው በትሕትና ሳይሆን በግርማ መንግሥቱ እንደሚመጣም ያሳያል፡፡ ‹‹ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃይል ይመጣል፤ እነሆ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው›› ኢሳ. ፵፥፲።

‹‹እነሆ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፤ በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ይቆማሉ›› ዘካ. ፲፬፥፩‐፭።  ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህችን ዕለት ከእነምልክቶቿ ያስተማረው በደብረ ዘይት ነው፤ ይህች ዕለትና የጌታ ምጽአት ምሥጢር ናቸው፤ ምሥጢረ ምጽአቱን በደቀ መዛሙርቱ አማካኝነት ለዓለም ገልጧል፤ አስረድቷልም፡፡

የምጽአት ምልክቶች

‹‹ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ፡፡ ጦርነትን፤ የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደናገጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፤መንግሥትም በመንግሥትም ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረሀብ፣ ቸነፈርም፤ የምድር መናወጥም ይሆናል፡፡ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡ ያንጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰዎች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ ያንጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ፡፡ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ ከዐመፅም ብዛት የተነሣ ፍቅር ከብዙዎች ዘንድ  ትጠፋለች፡፡ እስከ መጨረሻው የሚታገስ ግን እርሱ ይድናል፡፡ በሕዝብ ሁሉ ምስክር ሊሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ይሰበካል፤ ያንጊዜም ፍጻሜ ይደርሳል›› ማቴ. ፳፬፥፭‐፲፬።

በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ በክብሩ ከቅዱሳን መላእክት ጋር  በዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጐችን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በእርሳቸው ይለያቸዋል፤ በጐችን /ጻድቃንን/ በቀኝ ፍየሎችን /ኃጥኣንን/ በግራ ያቆማቸዋል፡፡ ‹‹ሙታንን ያስነሣቸዋል፤ ሙታን ይነሣሉ፤ በመቃብር ያሉ ሬሳዎችም ሕያዋን ይሆናሉ፤ ከአንተ የሚገኝ ጠለ ረድኤት ሕይወታቸው ነውና››፤ ኢሳ. ፳፮፥፲፱።

የዘለዓለም ሕይወት ይሰጣል፤ ሕይወት ለማይገባቸውም የዘለዓለም ቅጣት ይፈርድባቸዋል፡፡ በመቃብር ያሉት ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል መልካም ያደርጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ ያደርጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይመጣሉ፤ ዮሐ.፭፥፳፰-፳፱። ከላይ እንዳየነው ጻድቃን በቀኝ ኃጥአን በግራ ይቆማሉ ማለት ጻድቃን በክብር መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ ኃጥኣን በውርደት ወደ ገሃነመ እሳት ይሄዳሉ፤ ‹‹እነዚያም ወደ ዘለዓለም ቅጣት ይሄዳሉ ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ›› እንዲል፤ ማቴ.፳፭፥፵፮፡፡

የእኛንም እድል ፈንታ ከጻድቃን ጋር ያድርግልን፤አሜን!