በተክለ አብ

ጸሎተ ሐሙስ ጌታችን ምሥጢረ ቊርባንን ከምሥጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ የገለጠበት ዕለት ነው፡፡ በወንጌልም እንደተጻፈው ፋሲካውን የሚያከብሩበት ቀን ሲደርስ ጌታ ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሒዳችሁ ፋሲካን እንበላ ዘንድ አዘጋጁልን አላቸው፤ እነርሱም በየት እንድናዘጋጅልህ ትወዳለህ አሉት? ወደ ከተማ ገብታችሁ የውኃ ማድጋ የሚሸከም ስምዖን የተባለ ሰው ታገኛላችሁ፤ ወደ ገባበት ቤት እርሱን ተከተሉት፤ መምህር ከደቀ መዛሙርቶቼ ጋር ፋሲካ የሚያደርግበት አዳራሽ ወዴት ነው ይልሃል? በሉት እርሱ የተነጠፈውንና ታላቁን አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም ፋሲካን አዘጋጁልን አላቸው፤ እነርሱም ወደ ተላኩበት ከተማ ገብተው አልዓዛርን የውኃ ማድጋ ተሸክሞ አገኙት፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም ለስምዖን ጌታ በቤቱ ፋሲካን ሊያዘጋጅ መሻቱ እንደሆነ ነገሩት፤ እርሱም የፍጥረታት ጌታ በቤቱ ሊመጣ እንዳለ አስቦ ተደሰተ፤ ወደ ሚስቱ አክሮሲናም ሔዶ ይህ አልዓዛርን ከሞት ያስነሳ እኔንም በኃጢአቴ ይቅር ይለኛል፤ ያነጻኝ ዘንድ ከሐዋርያት ጋር በቤታችን ይመጣል አላት፤ አክሮሲናም እጅግ ተደሰተች፡፡

ጌታችንም ጊዜው ሲደርስ ከሐዋርያት ጋር በአንድነት መጣ፤ ስምዖንም ከቤቱ ወጥቶ ሮጦ ከጌታ እግር ሥር ሰገደ፤ ወደ ቤቱም ከሐዋርያት ጋር አስገባቸው፡፡ ይሁዳ ግን ይህን ሰዓት አልነበረም፤ ውጪ ከሻጭና ለዋጭ ጋር ገንዘብ ሲደራደር ነበር፤ ስምዖንም ለሚስቱ አክሮሲና ጌታና ሐዋርያት የሚገቡበት በእግራቸው የሚረግጡት ምንጣፍ እንድታነጥፍ አዘዛት፡፡ አክሮሲና ግን የጌታን መልክ አታውቀውም ነበር፤ ያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ጸሎት ሲጸልዩ አይታ ‹‹ከእናንተ ውስጥ መምህሩ ማነው›› አለቻቸው፤እነርሱም ዝም አሉ፤ መልከ መልካም ወደ ሆነውና የጌታ ወዳጅ ወደሆነው ዮሐንስ ተመልክታ እርሱ ይሆን አለች፤ ጴጥሮስ ግን ቀበል አድርጎ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ከውስጠኛው ክፍል ቆሞ ይጸልያል፤ ጌታ እርሱ ነው›› አላት፡፡ እርሷም ገብታ ሰገደችለት፤ ይሁዳም በመጨረሻ ሳጥን ተሸክሞ መጣ፤ ጠባቂውንም እኔ የጌታ ደቀ መዝሙር ነኝ አለው፡፡ በር ጠባቂውም እለእስክንድሮስም የተነጠፈውን እስካጥፍ ጠብቅ ብሎ ዘለፈው፤ ልብሱንም አንስቶ አስገባው፤ /ግብረ ሕማማት ፭፻፹፫-፫፻፹፭/፡፡

በአንደኛው ሰዓት ሌሊት (ሐሙስ ለአርብ ምሽት)፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ልብሱን አኖረ፤ማበሻ ጨርቅም አንስቶ ወገቡን ታጠቀ፤ ይህችውም ሥራ የምታሠራና የምታስጌጥ ናት፤ ለዛሬው የመነኮሳት መታጠቂያ አብነት ናት፡፡ ለምሳሌ፡- ኢዮአብ ወደ ሰልፍ ሲገባ እየለበሳት ይገባ እንደነበረችው ያለ ዓይነት ነው፤ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በጴጥሮስ ጀመረ፤ ጴጥሮስ ግን እኔ ባንተ ልታጠብ አይገባኝም አለ፤ ጌታችንም መልሶ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም›› (ዮሐ.፲፫፥፰)፡፡ ሌሎቹንም ሐዋርያት አጠባቸው፤ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳንም እግሩን አጠበው፡፡ ጌታ አሳልፎ እንደሚሰጠው ሳያውቅ ቀርቶ አልነበረም፤ ፍቅርን ሲያስተምረውና ለንስሐ ጊዜ ሲሰጠው ነው እንጂ፤ እኛንም ለሚወደን ብቻ ሳይሆን ለሚጠላን እንኳን በጎ ማድረግ እንደሚገባ ሲያስተምረን ነው፡፡

ጌታችን ጾመና ጹሙ አለን፤ተጠመቀና ተጠመቁ አለን፤ ጸለየና ጸልዩ፤ ሰገደናም ስገዱ አለን፤ የሐዋርያትንም እግር አጥቦ እናንተም እንዲህ አድርጉ ብሎ መምህረ ትሕትናነቱን ገለጠልን፡፡ ዛሬም ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፤ካህናት በየመአርጋቸው የምእመናኑን እግር በማጠብ የጌታን የትሕትና ሥራ ያስቡታል፡፡

ለሐዋርያት ትሕትናን ሲያስተምራቸው ጌታችን እግራቸውን እንደ አጠባቸው ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ከዚያም ዝ ውእቱ ሥጋየ ዝ ውእቱ ደምየ ብሎ ሥጋውንና ደሙን ሰጣቸው፤ ዛሬም የልጅነት ጥምቀት የሚቀበሉ ምእመናን በዚያኑ ዕለት ከክርስትና ቤት ወደ ቤተ መቅደስ ሔደው የጌታን ክቡር ሥጋና ደም ይቀበላሉ፤ መሠረቱም ጌታችን ለሐዋርያት ያደረገውን ተመርኩዞ ነው፡፡ ከፍ ከፍ ሊል የሚወድ ራሱን ዝቅ ያድርግ ብሎም አስተምሯቸዋል፤ አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር ጌታ ለጴጥሮስ ‹‹እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም›› ያለውን ሲተረጉሙ ‹‹እኔ በአገልጋይ አምሳል እግርህ ካላጠብኩህ አንተም ከበታችህ ላሉት ራስህን ዝቅ ለማድረግ አትችልም፤ ራስህን ዝቅ ዝቅ ካላደረግህ አለቃ ልትሆን አትችልም›› ለማለት ነው ብለው ተርጉመውታል፡፡ ጌታችን ደግሞ አምላክ ፈጣሪ መምህር ሳለ ዝቅ ብሎ እንዳጠባቸው እነርሱም ክህነታቸውንና መምህርነታቸውን በትሕትና እንዲጀምሩ ሲያስተምራቸው ነው፡፡ 

በሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት ምሽት፤ ጌታችን ሕብስቱን ባርኮ ለዐሥራ ሦስት ፈትቶ ሰጣቸው፤ ዐሥራ ሦስተኛውን እርሱ የሚቀበለው ነውና ነገር ግን የሚረባውና የሚጠቅመው አይደለም፤ ‹‹ዝ ውእቱ ሥጋየ ዝ ውእቱ ደምየ›› ብሎ ሕብስቱን ባርኮ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ ›› ወይኑንም ባርኮ ‹‹ይህ ደሜ ነው እንካችሁ ጠጡ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡አስራ ሦስት አድርጎ መፈተቱ ሐዋርያትን እንዳይገርማቸው (እንዳያስፈራቸው) ነው፤ እራሱም ጥዒሞ አጥዐሞሙ/ቀምሶ አቀመሳቸው/ እንዲል አብነት ለመሆን፤ አንድም ነገ በመልዕተ መስቀል አስራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል እቀበላለሁ ሲል ነው፤ ጌታ ይህን ባያደርግ ኖሮ ዛሬ ካህኑ የጌታን ሥጋና ደም ሳይቀበል አቀብሎ ብቻ በሄደ ነበርና ለእነርሱ ለማስተማር ነው፡፡

ማዕዱንም እየበሉ ጌታችንም ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ! ከእናንተ መካከል አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል›› አላቸው፤ (ዮሐ.፲፫፥፳፩)፡፡ ሐዋርያት ሁሉ ደነገጡ! እርስ በርሳቸው ተያዩ፤‹‹እኔ እሆን? እኔ እሆን?›› ተባባሉ፤ ጴጥሮስም ዮሐንስን ጠጋ ብሎ ‹‹ማነው አሳልፎ የሚሰጠህ ብለህ ጌታን ጠይቀው›› አለው፤ወንጌላዊው ዮሐንስም ጌታን ጠጋ ብሎ ጠየቀው ጌታችንም ‹‹ከእኔ ጋር እጁን ከወጪቱ የሚያገባ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል›› አለ፤ (ማቴ.፳፮፥፳፫/ሉቃ.፳፪፥፳፩)፡፡  ሐዋርያትም ‹‹ሁላችን ከወጪቱ የምንጠቅስ አይደለምን?›› ሲሉ ጌታችን ‹‹እኔ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው ነው›› አላቸው፤ ያንጊዜ አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ይሁዳ  ሰጠው፤ ስለዚህ ወንጌላውያኑ ይህን ታሪክ ይዘው አንድ ሳለ በተለያየ አገላለጥ ገለጡልን፡፡

ይሁዳም እንደቸኮለ ሰው ይቅበዘበዝ ነበር፤እርሱም ጌታን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጠው በልቡ እያሰበ ነበር፡፡ ጌታም ወደ ይሁዳ ጠጋ ብሎ ‹‹ወዳጄ ይሁዳ ሆይ! ልትሠራው የምትሻው ሥራ  ካለ ሒድ›› አለው፤ (ዮሐ.፲፫፥፳፯)፤ ይሁዳም ፈጥኖ ወጥቶ ወደ አይሁዳውያን ጌታን አሳልፎ ሊሰጥ ዋጋ ሊነጋገር ሔደ፡፡

ከሦስተኛው ሰዓተ ሌሊት እስከ አምስተኛይቱ ሰዓተ ሌሊት ድረስ

ለደቀ መዛሙርቱ ሲመክራቸው የመንፈስ ቅዱስንም መምጣት አብዝቶ ሲነግራቸው፤ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቀና፤ እርሱ ከአባቱ ጋር አንድ እንደሆነም ነገራቸው፤ ለብቻው ፈቀቅ ብሎ ወዙ እንደ ደም እስኪፈስ እየሰገደ ጸለየ፤ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመለሰ፤ ተኝተው አገኛቸው፤ ቀሰቀሳቸው፤ ጴጥሮስንም አንድ ሰዓት ያህል እንኳን ከእኔ ጋር መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ አለው! (ሉቃ.፳፪፥፲፬-፵፮)፡፡

የጌታችን በአይሁድ መያዝ (ስድስተኛው ሰዓተ ሌሊት)

ጌታችንም ከአብ ጋር ስላለው አንድነትና ክብር ለሐዋርያት ካስተማራቸው በኋላ ‹‹ኢየሱስም ይህን ተናግሮ አትክልት ወደ አለበት ስፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ በዚያም ገባ›› (ዮሐ.፲፰፥፩)፡፡ወንዙን ተሻግሮ ያለውን ዛፍ አልፎ ወዳለው ዱር ገባ፡፡ ይሁዳም ይህችን ስፍራ  ቀድሞ ጌታ ይመጣባት ስለነበር ያውቃት ነበርና ጭፍሮችንና የካህናት አለቆችን ፈሪሳውያን ሌሎች ፋና ጋሻ ጦርም የያዙትን አስከትሎ መጣ፡፡ ጌታችንም ‹‹ተነሡ እንሂድ! እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል›› አላቸው  ወደ እነርሱ መጥቶ ቀረበ፤ ይሁዳም ወደርሱ ቀርቦ፤ ‹‹መምህር ሆይ ቸር ውለሃል፤ ሰላም ላንተ ይሁን›› ብሎ ሳመው፤ ይህ መሳም ለአይሁድ ጥቆማ ወይም ምልክት ነበር፡፡ ምክንያቱም የጌታ መልክና የወንጌላዊው የዮሐንስ መልክ ይመሳሰልባቸው ነበርና ሲለይላቸው ነው፤ ጌታችንም ‹‹በስኢምኑ ታገብኦ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?›› አለው (ሉቃ.፳፪፥፵፰)፡፡

ይሁዳም ከጭፍሮቹ ጋር መጣ፤ ጌታ ኢየሱስንም ከበውት ወደ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቃ ቀያፋ ወዳለበት ወሰዱት፤ ጴጥሮስ ግን ከሩቅ ሆኖ ይከተለው ነበር፤ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ከአንደኛው ቅጥር ግቢ ገብቶ ተቀመጠ፡፡ አይሁድም በክርስቶስ ላይ ሁለት የሐሰት ምስክሮችን አመጡ ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛው ቀን እሰራዋለሁ›› ብሏል ብለው ከሰሱት፤ ሊቀ ካህናቱም ተነስቶ ‹‹እንዲህ ሲያጣሉህ አትሰማምን›› አለው፡፡ ጌታችን ግን ምንም አልመለሰለትም፤ሊቀ ካህናቱም ‹‹ክርስቶስ ተብሎ የተነገረልህ የእግዚብሔር ልጅ አንተ እንደሆንክ ንገረኝ›› አለው፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተ አልክ›› አለው፤ ያን ጌዜ ሊቀ ካህናቱ ተናዶ ልብሱን ቀደደው፤ራሱንም በብረት ዘንግ መቱት፤ የስቃዩ ጅማሬ ይህን ጊዜ ነበር፡፡