ከጥቅምት 6-11 ቀን 2002 ዓ.ም ሲካሔድ የሰነበተው ይህ ስብሰባ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት የዓለም ሃይማኖቶች የክብር ፕሬዚዳንት በሀገር ውስጥና በወጪ ሀገር የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የየአህጉረ ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎች፣ የምእመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በተገኙበት ነው፡፡
ጉባኤውን በጸሎት የከፈቱት ቅዱስነታቸው፤ የቤተክርስቲያን ዓላማ ሰላም በመሆኑ በሥልጡንና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጉባኤውን ማካሔድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ «ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚካሔድ ውይይት የጎደለን ይሞላል የተጣመመን ያቃናል» ያሉት ቅዱስነታቸው «ቤተክርስቲያናችንን በልማቱ ለማሳደግ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል» በማለት ጉባኤውን አስጀምረዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በ2001 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነቱና በየአህጉረ ስብከቶች የተከናወኑትን ዐበይት ጉዳዮች የተመለከተውን ዘገባ በንባብ አሰምተዋል፡፡
ዘገባውን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ በጻፈው መልእክት /ም.5-42/ የጀመሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ለቤተክርስቲያን የደም ሥር፣ ለምእመናን የጀርባ አጥንት የሆነው ስብከተ ወንጌልን በስፋትና በአግባቡ እንዲሰበክ፤ ምእመናን በእምነታቸው እንዲጸኑ፣ በሥነ ምግባር እንዲጎለብቱ፣ ከባዕድ ሃይማኖት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲጠብቁ፣ ሰበካ ጉባኤያት እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ፣ የልማትና የምግባረ ሠናይ ሥራዎች እንዲሠሩ፣ ድህነትና ድንቁርና ከሕዝባችን ጫንቃ እንዲወርዱ ለማድረግ ሁሉም ጥረት ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ዐቢይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዓመታዊ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዚህ ሁኔታ ሲካሔድ ሃያ ስምንተኛ ዓመቱን መያዙን የተናገሩት ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ «ጉባኤው ከወጣኒነት ወደ ፍጹምነት መሸጋገር እንደሚኖርበት የሁላችንም እምነት ነው፡፡» ብለዋል፡፡ ስለሆነም መለኪያው ከማእከል እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚቀርበው ዘገባና ውጤት ተኮር ሥራ ተሠርቶ ሲገኝ ብቻ መሆኑን አመልክተው፤ ይህ ካልሆነ ግን በየዓመቱ የሚደረገው ስብሰባ ልማዳዊ እንዳይሆን በብርቱ ማጤን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመቀጠልም ሥራ አስኪያጁ ለግምገማና ለውይይት እንዲያመች ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ከመንበረ ፓትርያርከ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ ከየአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች በ2001 ዓ.ም የተከናወነውን የሥራ ክንውን ዘገባ አቅርበዋል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤትን በተመለከተው ዘገባ ቅዱስ ፓትርያርኩ በሀገር ውስጥና በውጪ ሐዋርያዊ አገልግሎትና ልዩ ልዩ የሥራ ክንውኖችን ማድርጋቸውን አመልክቷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሐምሌ 22 ቀን 2000 ዓ.ም የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን የቅዱስ ላሊበላን ታሪካዊ መካናት እንዲጎበኙ መደረጉና በኋላም ከቅዱስ አባታችን ጋር ተወያይተው ለቤተክርስቲያናችን አድናቆት መቸራቸው ገልጸዋል፡፡ ነሔሴ 29 ቀን 2000 ዓ.ም ቅዱስ አባታችን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንትና ልዩ ልዩ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር እንግዶች በተገኙበት ከጣሊያን መጥቶ አክሱም በቀድሞ ቦታው በተተከለው የአክሱም ሐውልት ሥነ ሥርዓት ላይ በክብር መገኘታቸው ተጠቅሷል፡፡
በመስከረም 13 ቀን 2001 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በናዝሬት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የተሠራውን ሕንፃ መመረቃቸው፣ መስከረም 24 ቀን 2001 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ አምቦ በጃን መንግሥት የተሠራውን ትምህርት ቤት ምረቃ ወቅት መገኘታቸውና መስከረም 16 ቀን 2001 ዓ.ም የሚከበረውን የመስቀል ደመራ በዓል በበለጠ ተጠናክሮ እንዲውል ጉዳዩ ለሚመለከተው አመራር መስጠታቸው በዘገባው ተመልክቷል፡፡
በቅዱስነታቸው ሰብሳቢነት የተመራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው፣ በቅዱስነታቸው መመሪያ ሰጪነት ሸንኮራ ዮሐንስን ጨምሮ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙና አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትና ቅዳሴ ቤት ተገኝተው እንዲከበር መደረጉ ተጠቅሷል፡፡
ልዑል አክሊለ ብርሃን መኮንን ኃይለ ሥላሴ የተባሉ በጎ አድራጊ ለቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የሚውል አንድ ሚሊዮን፣ ለአክሱም ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተመጻሕፍት ወቤተመዘክር የሚውል አምስት መቶ ሺሕ ብር እርዳታ ሲለግሱ ቅዱስነታቸው በመገኘት ርዳታው ለተሰጣቸው ማስረከባቸው በልዩ ጽ/ቤቱ የተሠሩ ዐበይት ጉዳዮች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በውጪ ሀገርም በቅዱስነታቸው የተመረጡ ልዑካን ከኅዳር 5-16 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ ቦነስአይረስ በተካሔደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ መሳተፍ፣ ከስብሰባው መልስም በሶርያ በመገኘት ከፕሬዝዳንቱ ዶ/ር በሽር አል አሳድ ጋር ስለ ዓለም ሰላም ጉዳይ መወያየታቸው፣ ከሶርያም ወደ ሊባኖስ በመጓዝ በቤሩት በሚገኙ ምእመናን የተገነባውን ቤተ ሳይዳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በመገኘት ሕንፃውን ባርከው ቅዳሴ ቤት መክበሩ፤ እንዲሁም ወደ ግብጽ በማምራት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ጋር በሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት መወያየታቸው በውጪው ዓለም ካከናወኑት ዐበይት ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ በተመለከተ ዋና ሥራ አስኪያጁ ባቀረቡት ዘገባ፤ በዋናው መሥሪያ ቤት ያሉትን ሰባክያነ ወንጌልንና በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በአዲስ አበባ የሚገኙትን ጨምሮ በማስተባበር በ26 አህጉረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ሥምሪት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ስበከተ ወንጌልን ይበልጥ ለማስፋፋት እንዲረዳ በደቡብ ኦሞ፣ በሽሬ፣ በደቡብ፣ በሰሜንና በምዕራብ ወሎ፣ በሶማሌ፣ በወላይታና በዳውሮ፣ በጉራጌ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በአዲግራት፣ አክሱም፣ በአፋርና በምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት 1ሺሕ228 ያህል ሰባክያነ ወንጌል መመደባቸውንም ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡
ገቢና ወጪን አስመልክቶ ከቁልቢ ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ ከስብከተ ወንጌል ጉባኤ አንድ በመቶ አስተዋጽኦና ከመጽሔት ሽያጭ 238¸616.77 ገቢ ሲሆን ጠቅላላ ወጪው ደግሞ 238¸325.52 መሆኑን ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ አመልክተዋል፡፡
በሊቃውንት ጉባኤ በኩል በ2001 ዓ.ም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ከአምስት የቤተክርስቲያናችን ክፍሎች፣ ከተወካዮች ምክር ቤት እና ከልዩ ልዩ ድርጅቶች፣ ከአራት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና አምስት ግለሰቦች የተዘጋጁ በድምሩ 192 የሆኑ በጥልቅ ታይተው እንዲታረሙ የተላኩትን ታላላቅ መጻሕፍት፣ መለስተኛ ጽሑፎችንና ጥያቄዎች ተመ ልክቶ ከአስተያየት ጋር ወደ በላይ አካል መመለሱን እንዲሁም ተጠቃሎ እንዲታተም የተጀመረውን የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ እያመሳከረ በመጀመሪያ የማጣራት ሥራ ላይ እንደ ሚገኝም ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡
ትምህርትና ማሠልጠኛን በተመለከተ ለ22 አህጉረ ስብከት አብነት ትምህርት ቤቶች አንድ ሚሊዮን 69 ሺሕ ብር፣ ለ14 አህጉረ ስብከት ንባብና ቅዳሴ ቤት 260 ሺሕ ብር፣ ለ21 አህጉረ ስብከት ካህናት ማሰልጠኛ 750 ሺሕ ብር በድምሩ 2 ሚሊዮን 79 ሺሕ ብር መላኩን ገልጸዋል፡፡
በጀትና ሒሳብን አስመልክተው ባቀረቡት ዘገባ ከቤተክርስቲያኒቱ የገቢ ርዕሶች 48 ሚሊዮን 631 ሺሕ 40 ብር ለማስገባት ታቅዶ 45 ሚሊዮን 711 ሺሕ 685 ብር ብቻ እንደተገኘና ከዚህም ውስጥ 39 ሚሊዮን 566 ሺሕ 487 ብር ወጪ ሆኖ በሥራ ላይ እንደዋለ አስረድ ተዋል፡፡
ጠቅላይ ቤተክህነቱ በስድስት መምሪያዎች እና በ10 የጠቅላይ ቤተክህነቱ ድርጅቶች፣ አራት አህጉረ ስብከቶችና የቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሒሳብ ተመርምሮ 387 ሚሊዮን 431 ሺሕ 782 ብር ገቢ፣ 344 ሚሊዮን 674 ሺሕ 313 ወጪ ሲሆን አራት ሺሕ 496 ብር ጉድለት መገኘቱን ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ በዘገባቸው አመልክተዋል፡፡
በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ በኩል በ 2001 ዓ.ም ያሬዳዊ ዜማ የካሴትና የመጽሔት ሥርጭትን በተመለከተ ወጥ የሆነ ያሬዳዊ መዝሙር እንዲዘመር ጥረትና እንቅስቃሴ መደረጉን፣ ሐምሌ 5 ቀን 2000 ዓ.ም የተከበረውን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ 16ኛ ዓመት በዓለ ሲመት ወጣቶችን የማስተባበር ሥራ መሠራቱን፣ ከነሐሴ 1-16 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ በጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሱባኤ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በየአብያተ ክርስቲያናቱ በመገኘት ተገቢውን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጡ በመምሪያው በኩል ትእዛዝ መተላለፉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም ማደራጃ መምሪያው መስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የእንኳን አደረሰዎ በዓል ላይ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት አገልግሎት እንዲሰጡ መመሪያ ማስተላለፉንና፣ የመስቀል ደመራ በዓል በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት እንዲከበር የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትን በማሠልጠን የሚጠበቀውን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ማድረጉን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ደግሞ በዋናው ማዕከል አማካኝነት ብቻ ለ22 ሕዝባዊ ጉባኤያት፣ በዐሥር የተለያዩ የወረዳ ከተሞች ሐዋርያዊ ጉዞ መደረጉን፣ ስብከተ ወንጌል ካልደረሰባቸው ጠረፋማ አህጉረ ስብከት ለተውጣጡ 40 ወጣቶችና በዝዋይና በጅማ ካህናት ማሠልጠኛ 135 ልዑካን ሥልጠና መስጠቱን፣ ትምህርተ ሃይማኖት እና መንፈሳዊ መልእክት የያዙ 325 ሺሕ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 225 ሺሕ ሐመር መጽሔትና ሰባት ሺሕ ልዩ እትም ሐመረ ተዋሕዶ በ2001 ዓ.ም ማኅበሩ ማሰራጨቱን ሥራ አስኪያጁ በዘገባቸው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ማኅበሩ ልዩ ልዩ የቤተክርስቲያን ትምህርት የያዙ ዘጠኝ መጻሕፍትን በአማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎች አሳትሞ ከ 57 ሺሕ ቅጂዎች በላይ ማሠራጨቱን፣ በድምፅና በምስል ልዩ ልዩ ወቅታዊነት ያላቸውን ጽሑፎች በአማርኛና በእንግሊዚኛ ቋንቋዎች በዌብሳይቱ /መካነ ድሩ/ ማስተላለፉን፣ በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተከታታይ ትምህርትና ሥልጠና መስጠቱ፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶች 300 ደቀመዛሙርት የመሠረታዊ ትምህርትና የስብከት ዘዴ፣ በአፍሪካ፤ በግብጽ፣ በኬንያና በአውሮፓ 11 ከተሞች መምህራንን ልኮ ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠቱን የሥራ አስኪያጁ ዘገባ አመልክቷል፡፡
እንዲሁም ለአብነት ትምህርት ቤቶች ደቀመዛሙርት፣ ለንዋየ ቅድሳትና ለአህጉረ ስብከት ድጋፍ፣ ለቅኔ ትምህርት ማስተዋወቅ፣ በተለያዩ አህጉረ ስብከት ርክክብ ለተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያና ገና እየተሠሩ ላሉ ፕሮጀክቶች፣ ለአብያተ ክርስቲያናት በነፃ ለተሠሩ የአሠራር ንድፎች /ዲዛይኖች/ በጠቅላላ ከብር 2 ሚሊዮን 760 ሺሕ 186 በላይ ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በቅርሳ ቅርስ ምዝገባና ጥበቃ በኩልም በበጀት ዓመቱ ብዙ ጥረት መደረጉን በዘገባቸው ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ በቅርሳቅርስ ቀላጤዎች ተሰርቀው የነበሩ መጻሕፍትንና ንዋየ ቅድሳትን ለማስመለስ በተደረገ ጥረት 22 ጥንታውያን መጻሕፍትን፣ 10 የተለያዩ ንዋያተ ቅዱሳትንና ሁለት ጽላቶችን ለማስመለስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ግምታቸው 223 ሺሕ 780 ብር የሆኑ ባለሥዕል የብራና ተአምረ ኢየሱስ፣ አንድ የብራና ተአምረ ማርያምና አንድ ድርሳነ ሚካኤል መጽሐፍ በፖሊስ ጣቢያ በኤግዚቢት ተይዘው በምርመራ ላይ ስለሆኑ ቅርሶቹ ወደቦታቸው እንዲመለሱም ክትትል እየተደረገ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ የዋናውንና የየአህጉረ ስብከቶቹን የሥራ እንቅስቃሴ በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በመ ምሪያዎች፣ በድርጅቶችና በ45 አህጉረ ስብከት አሉ ያሏቸውንም ችግሮች ገልጸዋል፡፡
ካጋጠሙ ችግሮች መካከል በጠቅላይ ቤተክህነቱ ያለው የገንዘብ ወጪ ጫና፣ ከየአህጉረ ስብከቱ ለሚዘዋወሩ ሠራተኞች ደሞዝ ከጠቅላይ ቤተክህነት መከፈሉ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ደቀ መዛሙርት የሚመደበው አዲስ በጀትና የተቋማቱ የውስጥ ገቢ አለመፍጠር፣ ከበጀት ውጪ የሚቀርበው የገንዘብ ጥያቄና ከበቂ በላይ ሠራተኞች እያሉ ተጨማሪ ሠራተኞች ያለ ሥራ መመደብና መቅጠር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ወደ ውጪ ሀገርና ሀገር ውስጥም ለአገልግሎት የሚመደቡና የሚላኩትም ወጪያቸው ከዚያው እንዲሸፈን አለመደ ረጉ ይገኙበታል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን የ 27 ዓመት ጉዞን የሚያሳይ ዐውደ ርእይ የቀረበ ሲሆን ዐውደ ርእዩም በቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ ተከፍቷል፡፡ ዓውደ ርእዩ ከጥቅምት 6-15 ቀን 2002 ዓ.ም ለዘጠኝ ቀናት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ ዓውደ ርእዩን የተመለከቱት ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የቤተክርስቲያኒቱን ታላቅ ጉባኤ የሚያመለክት በመሆኑ ተጨማሪ የመጎብኛ ጊዜያት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
በስብሰባው ማጠናቀቂያ ላይ ከቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ጎን ለጎን አገልግሎቷን ለማቀላጠፍ በልማቱ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሀገረ ስብከቶችና አብያተ ክርስቲያናት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ለተመረጡት አብያተ ክርስቲያናት ሽልማት የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እንደተናገሩት፤ ቤተ ክርስቲያን በልማቱ ዘርፍ በማሳተፍ ለሀገር ዕድገት የበኩሏን አስተዋጽኦ እያደረገች ነው፡፡
ይህንንም አስተዋጽኦ የበለጠ አጠናክራ እንደምትቀጥል ቅዱስነታቸው ተናግረዋል፡፡ በሠሩት የልማት ሥራ ለሽልማት የበቁት አብያተ ክርስቲያናት የተመረጡት ከመላው ሀገሪቱ ሲሆን አህጉረ ስብከቶቹና የሰበካ ጉባኤ አባላቱ ልማቱን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጄኔሬተር፣ የውኃ ¬ምፕና ኮሚፒዩተር መሸለማቸው ታውቋል፡፡
ለሽልማት ከበቁት ውስጥ የባሌ፣ የሰሜን ሸዋ፣ የምሥራቅ ሸዋና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል፡፡
ጉባኤው ሲጠናቀቅም የጉባኤውን ሒደት በቅደም ተከተል እንዲካሔድ የተሰየመው የቃለ ጉባኤ አርቃቂ ኮሚቴ ባለ 26 ነጥብ ያለው የጋራ የአቋም መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
ኮሚቴው ባቀረበው የአቋም መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ እንዳመለከተው ቅዱስነታቸው በጉባኤው መክፈቻ ላይ የሰጡት የሥራ መመሪያና በተለይ በሀገራችን ሊከናወን ስለሚገባው ልማታዊ ሥራ፣ ለዚህ ተግባራዊነትም ሊኖር ስለሚገባው ሰላም አስመልክቶ ያስተላለፉት መልእክት ጉባኤው በአድናቆትና ከልብ እንደተቀበለውና ለተግባራዊነቱም እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በተገኙበት ከየካቲት 9-10 ቀን 2001 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ የስብከተ ወንጌል አስተባባሪነት የተካሔደው ዓውደ ጥናት ጠቃሚ ትምህርት የተገኘበት፣ ነፃና ግልጽ በሆነ መንገድ ውይይት የተደረገበትና ተሳታፊዎቹን የበለጠ ለሥራ ያተጋ በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን የአቋም መግለጫው አመልክቶ መምሪያው በ2002 ዓ.ም ያቀረበው ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ጉባኤው መጠየቁን አመልክቷል፡፡
ከጣና ቂርቆስ ገዳም ወደ ፈረንሳይ ተወስዶ በሪስ ሙዚየም ለብዙ ዓመታት የቆየው ቅዱስ መስቀል በቅዱስ ፓትርያርኩ ጥረት ግንቦት 28 ቀን 2001 ዓ.ም መመለሱን ጉባኤው አድንቆና ምስጋና አቅርቦ በቀጣይም በባዕድ ሀገር የሚገኙ ቅርሶችን ወደ ሀገር ቤት ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት እንዲጠናከር ጠይቋል፡፡
በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ያለው የአብነት ትምህርት ቤት መዳከም ምክንያቱ የአብነት ትምህርት ቤቶች በብዛት የሚገኙት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል መሆኑን የጠቆመው የአቋም መግለጫው ለነዚህም በቂ በጀት አለመመደቡ ይልቁንም በአብዛኛው አህጉረ ስብከት ትምህርት ቤቶች አለመኖራቸው ባሉበትም ቢሆን የሚ ሰጠው ትምህርት ወቅታዊና ዘመናው በሆነ መልኩ ሊካሔድ አለመቻሉን ጉባኤው ግንዛቤ መውሰዱን አመል ክቷል፡፡
ለዚህም በምክንያት የሚጠቀሰው ትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ በበቂ የሰውና የገንዘብ ኃይል ያልተደራጀ መሆኑ ግንዛቤ መያዙን ኮሚቴው አመልክቶ፤ በዚህ መሠረታዊ በሆነ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጉባኤው ማሳሰቡን አስረድቷል፡፡
የነገይቱን ቤተክርስቲያን የሚረከቡና ዛሬም የቤተክርስቲያን ውበት የሆኑት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶችን በመንከባከብ፣ በማስተማርና ከጠላት ወረራ እንደጠበቁ ለማድረግ፣ ከአባቶች የተማሩትን ንጹሕ ትምህርት ለፍሬ እንዲያበቁ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑ የሚገኙትን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ለማስተማር ያሉትን እያጠናከርን ባልተቋቋመባቸው አብያተ ክርስቲያናትም ለማቋቋም ጥረቱ እንደሚቀጥል የአቋም መግለጫው አመልክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱም በተከናወኑ የልማት ሥራዎች በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በየአህጉረ ስብከቱ በሚገኙ ወረዳዎችና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለልማት ሥራ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን በጥንታዊ ትምህርት ቤቶችና በሐዋርያዊ አገልግሎት ተዛማጅ ሥራዎች እንደተከናወኑ ከዘገባው መገንዘቡን በአቋም መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን ባደረገው እገዛ ጉባኤው እያመሰገነ ወደፊትም ማእከላዊ አሠራርን በጠበቀ መልኩ ማኅበሩ እገዛውን እንዲቀጥል ጉባኤው ማሳሰቡን መግለጫው አስረድቷል፡፡
ኮሚቴው ባቀረበው ባለ 26 ነጥብ የአቋም መግለጫ ሕጋዊ ባልሆኑና ባልተፈቀደላቸው ሰባክያን በየመንደሩም ሆነ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚካሔዱ ስብከቶች ማዕከላዊ አሠራርን ያልተከተሉ መሆናቸውን፣ በውጪው ዓለም ባለው መለያየት ጉባኤው እንደሚያዝንና በተለይ በሰሜን ምዕራብና ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት የቀረበው ዘገባ አባቶችን ለማቀራረብ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያደንቁና ጉባኤውም ሰላም እንዲገኝ ሙሉ ድጋፍ እንዳለው በአቋም መግለጫው ተገልጿል፡፡