የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ዛሬ ተጀመረ፡፡

ግንቦት 10፣ 2003ዓ.ም


በርክበ ካህናት የሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ዛሬ ተጀመረ። ጉባኤውን ተከትሎ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡

 
ወደ 1000 የሚጠጉ የሐዋሳ ከተማ ምዕመናን አዲስ የተመደቡትን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒን ሹመት በመቃወም በሀገረ ስብከታቸው የተፈጠሩ ችግሮች የመጨረሻ እልባት እንዲሰጥበት የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅድሳን ማረያም ገዳም በመገኘት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡  ከቅዱስ ሲኖዶስ መክፈቻ ጸሎት በኋላ ለቅዱስነታቸው እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ምዕመናኑ «በምልዐተ ጉባኤው አጀንዳ ተደርጎ ሊያዝ እንደሚችል ቃል ተገብቶልናል» ሲሉ በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ምእመን በተወካያቸው አማካይነት ገልጸዋል፡፡

ከሓዋሳ የመጡ ምእመናን አስፈላጊውን የሕግ አግባብነት ተከትለው ቢመጡም ባልታወቀ ምክንያት ዱከም ላይ ታግተው የቀሩ ምእመናን እንዳሉ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡

በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳንም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በአጀንዳ ሊያያቸው ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች በቀን 9/9/03 ዓ.ም በቁጥር ማ.ቅ.ሥ.እ.መ/17/02/ለ/03 በጻፈው ደብዳቤ አቅርቧል፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት እና በግለባጭ ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት በላከው ደብዳቤ በማኅበሩ ላለፉት 19 ዓመታት የተሠሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በአሁኑ ወቅት ግን ለቤተ ክርሰቲያን እድገትና መልካም አሠራር እንቅፋት የሆኑ ችግሮች  መኖራቸውን በአጽንኦት ይገልጻል፡፡

ወቅታዊውን የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በፊት ያሣለፋቸውን ውሳኔዎች ተፈጻሚነትን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትውልድን የማፍራት ጉዳይ ይኸውም የሕፃናትና የወጣቶች ሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርትና የማደራጃ መምሪያ ኃላፊዎችን ችላ ባይነት፣ የማኅበሩን ስም ለማጥፋት እየተንቀሳቀሱ ስላሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ለቅዱስ ሲኖዶስ አባልነትና የሚቀርቡና የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳትን ጉዳይ ይኸውም ወቅቱ የተሐድሶ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያኗ መዋቅርና የሓላፊነት ቦታ ለመግባት ከፍተኛ ርብርብ የሚያደርጉበት ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ለዚህ ጉዳይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚያመለክቱ አጀንዳዎች በአጀንዳነት ተይዘው ውሳኔ ሊሰጥባቸው ይገባል በማለት እንደልጅነታችን ሀሳባችንን እናቀርባለን ሲል ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተጻፈው ደብዳቤ ያሳስባል።


 


በተያያዘም እነዚህንና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የቀረቡ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በወቅታዊው የስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ሠፋ ያሉ ዘገባዎች ቀርበዋል።

ቅዱስ ሲኖዶስንና መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ልዕልናውን፣ የወቅታዊውን የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም አጽራረ ቤተ ክርስቲያን፣ በማኅበረ ቅዱሳን የውሸት /forged/ ማኅተም «የማኅበረ ቅዱሳን የረጅም ጊዜ ዕቅድ» በሚል ያዘጋጁትን እና በክስ መልክ ለፓትርያኩ ያቀረቡትን የሐሰት ጦማርና ሌሎችንም ወቅታዊ ጉዳዮች በተመለከተ ሰፋ ያለ ዘገባ በመያዝ ወጥታለች፤ የስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም።

ቤተ ክርስቲያን የማትነጥፍ መንፈሳዊት ጥገት ሆና ከምታፈሰው መንፈሳዊ ሐሊብ /ወተት/ ምእመኖቿ እንዲጠቀሙ የቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ልዕልና መከበር ወሳኝ ነው።

ቤተ ክርስቲያንም የቅድስና ዘውዷንና የክብር አክሊሏን ከራሷ ሳታወርድ ልዕልናዋ እንዳለ ሁሉ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች መከበር አለባቸው ስትል ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በልዩ እትሟ አስነብባለች።