የሚበሉትን ስጡአቸው(ክፍል አንድ)
በመ/ር አፈወርቅ ወ/አረጋዊ
ማቴ. 14.16
ከዓለም አስቀደሞ የነበረ በማእከለ ዘመን ያለ ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም የሚኖር፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ቃል ነው፡፡ የሰውን ልጅ ለማዳን ከወደቀበት ለማንሣት ወደቀደመ ክብሩም ለመመለስ ከንጽሕተ ንጹሐን ከቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ አምላክ ሰው ሆነ፡፡
በመዋዕለ ትምህርቱም የእጁን ተአምራት አይተው የቃሉን ትምህርት ሰምተው ከአሥር አህጉር ከብዙ መንደር ተውጣጥተው የአምስት ገበያ ያህል ሰዎች ይከተሉት ነበር፡፡
ከተከታዮቹም ውስጥ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በጥቅሉ መቶ ሃያ ቤተሰብ በመ ሆን /የሐዋ.1.15/፤ በዋለበት እየዋሉ በአደረበት እያደሩ ትምህርት ከተአምራት ሳይከፈልባቸው ሥጋዊ ፍላጎታቸውን አሸንፈው ተከትለውታል፡፡
«እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን» /ማቴ 19.27/፤ በማለት የአገልግሎት ዋጋ ከጠየቁት ሐዋርያት በተጨማሪም ሌላ ብዙ ሕዝብ ይከተለው እንደነበር ወንጌላዊው ማቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፎልናል «ከገሊላም ከአሥር ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከአይሁድም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት» /ማቴ. 4.25/፡፡
በዘመነ ብሉይ በነቢያት አድሮ ለሕዝቡ መልእክቱን ያስተላለፈ አምላክ ከነቢያት አንዱ በሆነው ልበ አምላክ ዳዊት ላይ አድሮ እንዲህ የሚል ቃል አናግሮ ነበር፡፡ «ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል ፊታችሁም አያፍርም ይህ ችግረኛ ጮኸ እግዚብሔርም ሰማው ከመከራውም አዳነው» /መዝ. 33.5/፡፡
በምድራችን ላይ ብዙ ዓይነት ችግሮች ቢኖሩም ከረሀብ የበለጠ ችግር የለምና የራበው ሁሉ የሚበላውንና የሚጠጣውን ለማግኘት ወደ አምላኩ ይጮሃል፡፡ በሊቀ ነቢያት ሙሴ መሪነት ከግብፅ ባርነት ወደምድረ ርስት ሲጓዙ የነበሩ እስራኤላውያን በኃይለኛ ረሀብ ተመትተው ስለነበረ የምንበላውን ስጠን ብለው ወደ ሙሴ ጮኹ ይላል /ዘኁ. 21.4ጠ5/፡፡
ለቸርነቱ ወሰን ድንበር የሌለው፣ መግቦቱ የማይቋረጥ እግዚአብሔር ለተራቡት ሕዝብ መና ከደመና አዘነበላቸው፣ ውኃ ከዐለት ላይ አፈለቀላቸው፣ እነርሱም በሉ ጠገቡ ጠጡ ረኩ ይላል /ዘጸ. 16.8/፡፡
የፍጥረታት ሁሉ መጋቢ እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን የተረዳው መዝሙረኛው፤ «የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ አንተ እጅህን ትከፍታለህ ሕይወት ላለው ሁሉ መልካምን /የሚጠቅመውን/ ታጠግባለህ» ይላል /መዝ.144.15/፡፡
ስለ እርሱ የተነገረው ትንቢተ ነቢያት ተፈጽሞ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜም በነቢያት ያስተላለፈውን ጥሪ አማናዊ በማድረግ፤ «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደኔ ኑ … ለነፍሳሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜ ቀሊል ነው» /ማቴ.11.28ጠ30/፤ በማለት የርኅራኄ ድምፁን አስምቷል፡፡
በዚህ ጥሪ መሠረት ልዩ ልዩ ችግር ያለባቸውን ማለትም በረሀብ የተጎዱትን ኅብስት አበርክቶ መግቧቸዋል፡፡ አካላቸው በበሽታ የደከመውን ፈውሶአቸዋል፡፡
ጌታችን የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቆረጡንና በድኑን ወስደው መቅበራቸውን ከደቀ መዛሙርቱ በሰማ ጊዜ ብቻውን ወደምድረ በዳ ፈቀቅ አለ፡፡ «ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት እርሱም ወጥቶ የተከተሉትን ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ፡፡» በልዩ ልዩ ችግር ተጠምደው መከራ በርትቶባቸው፣ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ አሠቃይቶአቸው የመጡትን በሽተኞች ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ፈወሳቸው፡፡ የሥጋ ረሀብተኞችንም ምግበ ሥጋን ሰጣቸው፤ በረሀበ ነፍስ የተጎዱትንም በቃሉ ትምህርት ፈወሳቸው፡፡ የእያንዳንዱን የችግር ቋጠሮ ሁሉ በአምላካዊ ጥበቡና ቸርነቱ ፈታላቸው እርሱ ሁሉን አዋቂ ነውና፡፡
ዛሬም እኛ ወደ እርሱ ከቀረብን ጉድለታችን ይሞላልናል፣ ያለው ይበረክትልናል፣ የራቀው ይቀርብልናል፣ አሳባችንን ችግራችንን በፍጹም እምነት በእርሱ ላይ እንተወው፤ /መዝ. 54.22/፡፡ የእኛ ድርሻ እርሱን መከተል ለእርሱ መታዘዝ ይሁን፤ በራት ላይ ዳረጎት እንዲሉ ሁሉ ይጨመርልናል /ማቴ. 6.33፡፡
ሁሉን ትተው የተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ የእርሱ አገልጋዮችና የቅርብ ባለሟሎች ናቸውና፤ ለመምህራቸው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀረብ ብለው በምስጢር፤ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁን ሰዓቱ መሽቷል ጊዜው አልፏል ወደመንደሮች ሔደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት፤ አሉት፡፡ እርሱ ግን ልብ ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን የሚመረምር ከአሳብ አስቀድሞ የሚታሰበውን የሚያውቅ አምላክ፤ በረሀብ የጠወለገ የደከመ ሰውነታቸው በበሽታ የተጎዳ አካላቸው በምግበ ሥጋ መጠንከር ነበረበትና፡፡ ደቀ መዛሙርቱን «የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ በረሀብ በተጎዳ ሰውነታቸው ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው፡፡»
በሥጋ አለስልሶ በደም አርሶ በጅማት አስሮ በአጥንት አጠንክሮ የፈጠረውን ሰውነት ለደቂቃ እንኳን ሳይዘነጋ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ አባት ነው፡፡
ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱ የምድርን ፍሬ አንዲቷን ቅንጣት በመቶ፣ በሺሕ አብዝቶ የፈጠረውን ፍጥረት ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ሳያቋርጥ ከትንኝ እስከ ዝሆን ከሰው እስከ እንስሳ ያለውን እርሱ ባወቀ መመገብ የሚገባውን ሁሉ የሚመግብ አምላክ ነው፡፡
ስለሆነም የእርሱን ርኅራኄ የሐዋርያትን መብትና ግዴታ ለመግለጥ፤ የሚበሉትን ስጡአቸው አለ፡፡ እነርሱም የአምላካቸውን የመምህራቸውን ትእዛዝ በፍጹም ፍቅር በመቀበል መስጠትስ ይቻል ነበር ነገር ግን ያለው ጥቂት ነው፡፡ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር የለም ለዚህ ሁሉ ሕዝብ አይበቃም ነው ያሉት፡፡
አስደናቂው ነገር ደቀ መዛሙርቱ የምግቡን ማነስ ተናገሩ እንጂ ይህ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ እንኳን ለሌላው ለእኛም አይበቃም፡፡ እኛ ምን እንበላለን የሚል የስስት የስግብግብነት አስተሳሰብም ሆነ ንግግር አላደረባቸውም፡፡ ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ግን በሰው ሰውኛው አመለካከት አለመብቃቱን ገልጸዋል፡፡
ዓለም እጅግ ብዙ ነገር ይፈልጋል ብዙ ነገር ይሰበስባል ያከማቻል ነገር ግን ያንሰዋል፡፡ የሰበሰበው ይበተናል የሞላው ይጎልበታል፤ ይገርማል በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ ከሆነ ግን ጥቂቱ ይበቃል፤ /ሉቃ. 10.42/፡፡
እርሱም የያዛችሁትን ያለውን አምጡልኝ አላቸው፡፡ አመጡለት በእርሱም እጅ ላይ አበረከተው፡፡ እኛም እንደ ደቀ መዛሙርቱ ያለንን ይዘን ወደ እርሱ እንቅረብ ከእርሱ መደበቅ የለብንም፤ አሥራቱን በኩራቱን ቀዳምያቱን ስሙ ለሚጠራበት ቤተ ክርስቲያን እንስጥ፤ ወደ እርሱ ይዞ መቅረብ ማለት ይህ ነውና ለእኛ በቅቶ ለሌላው ይተርፋል፡፡
ያለምንም ቅሬታ ማጉረምረም ትእዛዙን ተቀብለው የያዙትን ወደ አምላካቸው አቀረቡት፡፡ ምእመናን ቅር ሳይላቸው ሳያጉረመርሙ እንደ ደቀመዛሙርቱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መቀበል አለባቸው፡፡ ጌታችንም የቀረበውን እንጀራ ባረከው፡፡ ከባረከው በኋላ ቆረሰው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው ሥራው ሁሉ ድንቅ ነውና የሰጣቸው ሁሉ በእጃቸው ላይ ይበረከት ነበር፡፡ «እግዚአብሔርን ሥራህ ግሩም ነው በሉት» /መዝ. 25.3/፡፡
ለጌታ የሰጡትን ከጌታም የተቀበሉትን እንጀራ በአካባቢው ለነበረው ሕዝብ ሁሉ ሰጡ አቀረቡ፤ ሕዝቡን አስተናገዱ፡፡ እነርሱም የመመገብ የማስተናገድ ሓላፊነት አገኙ፤ ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከነበሩት ሁሉ ያልበላ አልተገኘም፡፡ መብላት ብቻ ሳይሆን እስከሚበቃቸው ድረስ በሉ አተረፉ፡፡ እውነት ነው ከአምላክ የተሰጠ ሁሉ ያጠግባል፡፡ ይትረፈረፋል፡፡
ቀድሞ በሊቀ ነቢያት ሙሴና በሊቀ ካህናት አሮን ላይ አድሮ፤ መና ከደመና አውርዶ፣ ውኃ ከዐለት አፍልቆ፣ አእላፈ እስራኤልን የመገበ ያጠጣ፣ ከሁሉ በላይ የሆነ፣ በሁሉ ያለ በሁሉ የሚሠራ ኃያል አምላክ፤ በብሉይ ኪዳን ሰው ሊደርስበት በማይችል ረቂቅ ጥበቡ ይሠራው የነበረውን መግቦት ሰው በመሆን በሚታይ በሚዳሰስ በሚጨበጥ ሰውነት /አካል/ እጁን ወደሰማይ በመዘርጋት፤ ሥርዓተ ጸሎትን አድርሶ፣ ሥርዓተ ምግብን አስተምሮ፣ እንጀራውን ፈትቶ /ቆርሶ/ እንካችሁ ብሎ በመስጠት ሰዎችን መገበ፡፡ እርሱ ከመገበ የማይመገብ ማን አለ) እሱ ከሰጠ የማይቀበልስ ማን አለ) ሁሉም ከተመገቡ በኋላ የተረፈው ማዕድ ሲነሣ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ሆነ በእሱ ሥራ ጉድለት የለምና ከሴቶች ከልጆች በቀር አምስት ሺሕ ወንዶች ያህሉ ነበር፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የተናገረው ቃል ምንኛ ያማረና የተወደደ እውነተኛ ቃል ነው፡፡ «በሉ እጅግ ጠገቡ ለምኞታቸውም ሰጣቸው ከወደዱትም አላሳጣቸውም» /መዝ.77.29/ እንዲል፡፡
እውነት ነው አምላካችን ሲመግበን እንጠግባለን፤ መልካም ምኞታችን የተሳካ ሥራችን የተከናወነ፣ ምርታችን የተትረፈረፈ፣ አገልግሎታችን የተቀደሰ፣ ዕውቀታችን የመጠቀ፣ አስተሳሰባችን የረቀቀ ከመሆን ባሻገር ከእኛ አልፎ ተርፎ ለሌላው የሚሆን የበረከት እንጀራ ይገኛል፡፡ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በሥርዓቱ ስንመራና በተሰጠን የሕይወት መንገድ ወደቀኝ ወደ ግራ ሳንል መራመድ ስንችል ነው /ኢያ. 1.7/፡፡
ይቆየን፡፡