akebabele.jpg

ከ400 በላይ የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት ተጠመቁ።

በሪሁን ተፈራ ከባህር ዳር ማዕከል
በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወንበርማ ወረዳ የሚገኙ ከ400 በላይ የሚሆኑ የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት በጎመር ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስቲያን እሑድ  የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ በርናባስ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በሀገረ ስብከቱ ቆሞሳትና ካህናት መጠመቃቸውን የማኅበረ ቅዱሳን ባህር ዳር ማዕከል ገለጸ፡፡

 
ብፁዕ አቡነ በርናባስ የካቲት 12ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ በ10፡40 ሰዓት ጎመር ሲደርሱ  የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ሠራተኞች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ባሕር ዳር ማዕከል፣ የሽንዲ ወረዳ ማዕከል አባላት፣ የአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምእመናን እና የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት፣ በመዝሙርና በእልልታ የታጀበ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
akebabele.jpg

ከዚህ በተጨማሪም በዕለቱ የማኅበረ ቅዱሳን ሽንዲ ወረዳ ማዕከል አባላት፣ የኮሊ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መዘምራን፣ የሸንዲ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መዘምራን፣ ጎመር ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች መዝሙርና ሥነ ጽሑፍ በኦሮምኛ በአማርኛ ቋንቋ ለምእመናን አቅርበዋል፡፡

Abune Bernabas Siatemku.jpgሥርዓተ ጥምቀቱ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት የተጀመረ ሲሆን የተጠመቁት ምእመናን በሥርዓተ ቅዳሴው ተሳትፈው ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ በሊቀ ማዕምራን ሀዲስ ጤናው የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ እና በመጋቤ ምሥጢር ኃይለማርያም ታዬ ትምህርት ተሰጥቶ ሀገረ ስብከቱ ለተጠማቂያን የብሔረሰቡ አባላት 600 የአንገት መስቀል አበርክቷል፡፡

ተጠማቂ  ምእመናኑ አባይ በረሃን ከሚያዋስኑ ከወንበርማ ወረዳ ሦስት ቀበሌዎች የመጡ ሲሆኑ በአካባቢው ከአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት ጀምሮ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት አልፎ አልፎ ያሉና የተጠመቁ የብሔረሰቡ ምእመናን ቢኖሩም ለዚህ በርካታ  የብሔረሰቡ አባላት መጠመቅ ምክንያት የሆኑት አቶ አያና የተባሉ የቻግኒ ወረዳ ማዕከል አባል ወደ ቦታው ለሥራ በመጡና አሁን የተዛወሩት ግለሰብ እና መምህርት መድኃኒት ሞላ የሽንዴ ወረዳ ማዕከል አባል አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሽንዲ ወረዳ ማዕከል በ1994 ዓ.ም ሁለት ህፃናትን ከአካባቢው በመውሰድና የአብነት ትምህርት ቤትYewerwda Maekelu Meketel sebsabi Betemeherte laye.jpg ለማስገባት የጀመረው ሙከራ ልጆቹ ሊለምዱ ስላልቻሉ ቢቋረጥም ለዚህ እንቅስቃሴ መጠናከር በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወንበርማ ወረዳ ቤተክህነት እና ከአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጋር በመሆን 2000 ዓ.ም ግንቦት 16 ቀን ወደ የማቤል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በወረዳ ማዕከሉ አስተባባሪነት የተደረገ የእግር ጉዞና ከአካባቢው የጎሳ አካላት ጋር የተደረገው ትምህርትና ውይይት ትልቅ በር እንደከፈተና ከዚያም በኋላ በወረዳ ቤተክህነቱ እና ወረዳ ማዕከሉ የሚደረጉ ትምህርተ ወንጌል ይበልጥ ግንኙነታቸውን እንዳጠናከረው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባህርዳር ማዕከል እና ሽንዲ ወረዳ ማዕከል በሽንዲ ከተማ የእራት ግብዣ በማዘጋጀትና ከበጎ አድራጊዎች 4000 ብር አስባስቦ ቆርቆሮ እና እንጨት ገዝቶ በማጓጓዣ፤ ግንቦት 2002 ዓ.ም ጉባኤ በማካሄድና ከ460 በላይ የብሔረሰቡ አባላት ጋር ውይይት አድርጎ በቀበሌው ባሉት በመምህርት መድኃኒት ሞላና አንድ ሌላ መምህር አስተባባሪነት ተጨማሪ እንጨት እንዲያዋጡ በማድረግ ቤተክርስቲያን በጎመር ቀበሌ ሊሠራ ችሏል፡፡

ብፁዕ አቡነ በርናባስ ከአሁን በፊት የተጠመቁትንና አዲስ ተጠማቂያንን እንዲበረቱ መክረው በበዓሉ ለተገኙ ምዕመናን እንዳሉት “የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ወገኖቻችን ወደዚህች ሃይማኖት ሊመጡ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በደስታ ልንቀበላቸው፣ ልንከባከባቸውና ልንደግፋቸው ይገባል”፡፡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የብሔረሰቡ አባላት በበኩላቸው ከ 2፡00-4፡00 ሰዓት የሚፈጅ የእግር ጉዞ ተጉዘው  እንደተጠመቁ በመግለጽ ለሰሩት ቤተክርስቲያን ጽላት እንዲገባላቸው፣ በቅርብ ቦታ ተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናት እንደሰሩላቸውና ካህናት እንዲመደቡላቸው ጠይቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ በርናባስም ከወረዳ ቤተክህነት ጋር በመሆን የተቻላቸውን እንደሚፈጽሙና ምዕመናን ከጎናቸው በመሆን ለቤተክርስቲያን ሥራ እንዲተጉ ጠይቀዋል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

 ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።