7ኛው ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ግቢ ጉባኤያት/ ሴሚናር ነገ ይጀመራል፡፡

(ሐሙስ የካቲት 24  2003 ዓ.ም. ) 
በእንዳለ ደጀኔ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን 7ኛውን የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ሴሚናር ከየካቲት 25-27 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ እንደሚያካሄድ አስታወቀ፡፡

የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊ ዲ/ን ተ/ብርሃን ገ/ሚካኤል እንደገለጹት በሴሚናሩ 310 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /የግቢ ጉባኤያት/  ተወካዮች የ41 ማእከላትና ወረዳ ማእከላት የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊዎች ይገኛሉ፡፡

ሴሚናሩም ማኅበሩ በ1984 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ግቢ ጉባኤያት/ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በማስተማርና ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ ትውልድ እንዲሆኑ ለማብቃት እየሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ሴሚናሩ በሚካሄድባቸው 3 ቀናት በሀገሪቱ ካሉ የከፍተኛ ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ሴሚናር ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የልምድ ተሞክሮ፣ የአገልግሎት ስልትና መንፈሳዊ ሕይወት እንዲሁም በምግባረ ሰናይ ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክረው የሚሔዱበትን አቅጣጫ መንደፍ የሚያስችል ውይይት እንዲደረግ ይጠበቃል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ቤተ ክርስቲያናቸውንና ሀገራቸውን በጥሩ ሥነ-ምግባርና በታማኝነት በተማሩበት ሙያ ለማገልገል የሚያስችል የተለያዩ የአገልግሎት ስልቶችን የሚረዱበት፣ ራዕይ ያላቸው፤ በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን አቅጣጫ የሚያውቁበት ሲሆን፣ ከተቋማቸው ማኅበረሰብ፣ ከአጥቢያ ሰ/ት/ቤቶችና ሰ/ጉባኤያት ጋር በመሆን የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ አገልግሎት ለመፈፀም የሚዘጋጁበት እንደሚሆን ሓላፊው ገልፀዋል፡፡

ማኅበሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ከተቋቋመበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ፣ ዓለም አቀፍ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሥሩ የሚገኙ ከ120.000 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማረ ይገኛል፡፡

ለ7ኛ ጊዜ በተዘጋጀው በዚሁ የግቢ ጉባኤ ተወካዮች ሴሚናር ቅዱስ ፓትሪያሪኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሃ/ስብከት የመምሪያ ሓላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ይገኛሉ፡፡