በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መመረቃቸው ተገለጸ።
በማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማእከል ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ዋና ክፍል ሰአሊተ ምሕረት ማስተባበሪያ አድማስ ግቢ ጉባኤ፣ ሎርካን ግቢ ጉባኤ፣ ቅዱስ ገብርኤል ማስተባበሪያና ደቡብ ማስተባበሪያ አድማስ ግቢ ጉባኤ ቃሊቲ ካምፓስና መካኒሳ ካምፓስ፣ ኪውንስ ግቢ ጉባኤ፣ ንፋስ ስልክ ፓሊ ቴክኒክ ግቢ ጉባኤ፣ ሪፍት ቫሊ ግቢ ጉባኤ ሲያስተምራቸው የነበሩ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን ሐምሌ 11 እና 12 ቀን 2018 ዓ.ም አስመርቋል።
በዕለቱም ትምህርተ ወንጌል፣ መዝሙር ፣ወረብ ፣ሥነ ጽሑፍ፣ በገና ዝማሬ በተመራቂ ተማሪዎች የቀረበ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የተመራቂ ወላጆች፣የማእከሉና የማስተባበሪያ ተወካዮች ፣ተመራቂ ተማሪዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ለተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ በማለት የማኅበሩ መልእክት የተላለፈ ሲሆን “በምትሰማሩበት መስክ ላይ ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት፣ በታማንነትና በቁርጠኝነት እንድታገለግሉ እንዲሁም በሥራው ዓለምም ውጤታማ እንድትሆኑ የተሰጣችሁን አደራ ልትወጡ ይገባል” በማለት በተወካዮች መልእክት ተላልፏል።
በመጨረሻም ለተመራቂ ተማሪዎች በአባቶች ቡራኬ የአደራ መስቀል ተሰጥቶ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።
