ማኅበረ ቅዱሳን በተለያዩ ቋንቋዎች የመዝሙር አልበሞችን በማዘጋጀት ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ገለጸ
በማኅበረ ቅዱሳን የዜማና ኪነ ጥበባት ማእከል ምእመናን በሚሰሙት ቋንቋ መዝሙራትን በማዘጋጀት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በተለያዩ ቋንቋዎች የመዝሙር አልበሞችን አዘጋጅቶ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።
በዚህም በዘንድሮው ዓመት ከያዘው ዕቅድ መካከል ከዚህ በፊት በ2017 ዓ.ም ቀረጻ የተከናወነላቸውን አዊኛ፣ ቡርጅኛ፣ባይሶኛና ሞስዬኛ ቋንቋዎችን የቅንብር ሥራ በመሥራት የማሰራጨትና አዳዲስ ቀረጻዎችን በኽምጣጞ(ኽምጠኛ)፣ በሐዲይሳ፣ በማሌኛ፣ በትግርኛ(የበገና) ቋንቋዎች ቀረጻ በማከናወን እንዲሁም በሐዲይሳ፣ ማሌኛና ትግርኛ(የበገና) መዝሙራትን የቅንብር ሥራቸዎችን በመሥራት ማጠናቀቁንም አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪ በውጭ አገር ቋንቋዎች ማለትም በእንግሊዝኛ እና በጀርመንኛ ሥራዎች ላይም የልዩ ልዩ ድጋፍ ሥራዎች ተከናውኗል።
የዜማና ኪነ ጥበባት ማእከል እንደገለጸው በ6 ቋንቋዎች ከ18 በላይ አልበሞች የታተሙ ሲሆን በ4 ቋንቋዎች 12 አልበሞች የቀረጻ ሥራዎች መከናወኑን ጠቅሷል።
በአጠቃላይ በዚህ ዓመት በቀረጻ፣ በቅንብር፣ በመሣሪያ ማስገባት ወዘተ የተሠሩ ቋንቋዎች ቡርጅኛ፣ አዊኛ፣ ሞስዬኛ፣ ኽምጠኛ፣ ሐዲይሳ፣ ባይሶኛ፣ ማሌኛ፣ ትግርኛ፣ እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ቋንቋዎች ናቸውም ተብሏል።
