‘’ከመላእክት አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ።’’ (ት.ዳን. ፲ ፥፱)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
እንኳን ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል አደረሳችሁ‼
በዓል “አብዐለ” አከበረ÷ አበለጠ÷ ዕለትን በዓል አደረገ ከሚለው ግስ የወጣ ስም ነው። ይህም የደስታ፥የዕረፍት ቀን ፥በዓመት በወርና በሳምንት የሚከበር፥ ያለፈ ድርጊት የሚታወስበትና ምእመናን የበዓሉን ምሥጢር እያሰቡ ሐሴት የሚያደርጉበት ማለት ነው:: ዕለቱም ምእመናን መደበኛ ሥራቸውን ትተው ለበዓሉ ይገባዋል የሚሉትን ተግባር የሚፈጽሙበት የበዓሉን ባለቤት እግዚአብሔርንና የበዓሉን ምክንያት እያሰቡና እያመሰገኑ ደስ የሚሰኙበት ነው። ቅዱስ ዳዊት “….በዓልን የሚያደርጉ ሰዎች በምስጋናና በደስታ ቃል ሲያመሰግኑ ተሰሙ:: ”(መዝ ፵፩፥፬፡፡) እንዳለው። በዓላት የዕረፍት ቀናት ናቸው ማለት ከሥጋዊ ወይም ምድራዊ (ዓለማዊ) ሥራዎች የሚያርፉባቸው ናቸው ለማለት ነው። በአንጻሩ ግን መንፈሳዊ ሥራዎች ሁሉ እንደየችሎታ የሚከናወንባቸው መሆናቸው መረሳት የለበትም፡፡ እነዚህ ዕለታት እግዚአብሔር በራሱ ወይም በቅዱሳኑ አድሮ ለሠራቸው ድንቅ ሥራዎች (ተአምራት) መታሰቢያዎች ናቸው። (መዝ፻፲፥፬)፡፡ ፻፲፩፥፮፡፡ ሉቃ፳፪፥፲፱፡፡)
በበዓሉ ዋዜማ ለዕለቱ የተሠራውን የምስጋና ቃል እየመሩ፣ እየተመሩ፣ እያነሡ፣ እየዘመሙ፣ መስተብቁዕ እየደገሙ፣ እያመረገዱ፣ እያመለጠኑ፣ እየጸፉ ሊቃውንቱ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። በዚህ መልኩ ከሚከበሩ ዐበይት በዓላትም አንዱ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል ነው።
ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሚ-መኑ፣ካ-ከመ፣ኤል-አምላክ መኑ ከማከ አምላክ? እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው? ማለት ነው።(ኪ.ወ.ክ)።
ቅዱስ ሚካኤል ዲያብሎስ በትዕቢቱ ፈጣሪነትን ሽቶ በዓለመ መላእክት ሁከት ባስነሣ ጊዜ የቅዱሳን መላእክት ፊታውራሪ ሆኖ ዲያብሎስን የተዋጋ ጽኑዕ መልአክ ነው።
“በሰማይም ሰልፍ ሆነ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉት፣ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውም። ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም።”(ራእይ ፳፪:፯)
ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ነው። ይሁዳ በመልእክቱ “የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በማለት ሊቀ መላእክትነቱን ገልጾአል። (ይሁዳ ፱)
ይህችውም ቅሩበ መንበር ተደርጎ የተፈጠረው ዲያብሎስ የተዋት ክብሩ ናት።
ቅዱስ ሚካኤል ይቅር የሚል ከመዓት የራቀ ነው።(ሄኖ፥፲፥፩፪)
ለሰው ባደረገው በጎነት ለሕዝቡ ሁሉ ታዛዥ ነው። የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይ ጭምር ነው፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል፣ ለእኛ ለሰዎች አማላጅ ሲሆን ለቅዱሳ ጻድቃንና ሰማዕታት ደግሞ አጋዣቸው ነው፤ በሕይወታቸውና በተጋድሏቸውም እስከ መጨረሻው ይረዳቸዋል፡፡
ይህንንም በቤተ ክርስቲያናችን በመጽሐፈ ስንክሳር እና በድርሳነ ሚካኤል ሰኔ ፲፪ ቀን ተጽፎ እናገኘዋለን። ይህም ቀን መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተከብሮ የሚውልበት ታላቅ ዕለት ነው፡፡ በእስክንድርያ ከተማ ክላወባጥራ የተባለች ንግሥት የበጥሊሙስ ልጅ ዙሐል በሚባል ኮከብ ስም ያሠራችው ታላቅ ምኲራብ ነበር፤ ሕዝቡም ሰኔ በገባ በዐሥራ ሁለት የዚህን ጣዖት በዓል ያከብሩ ነበር። ይህንንም ግብራቸውን እንዲተው አባታችን እለ እስክንድሮስ ቢነግራቸው አይሆንም አሉት።
በኋላም ጻድቅ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ሲነግሥ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኃዋ ወአብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ የሚል አዋጅ ስለወጣ በዚህ ምቹ ጊዜም የጣዖት አምልኮ እንደምን ያለ ክፉ ግብር እንደሆነና በጎ ዋጋም እንደሌለው ነግሮ እንዲተዉ ቢጠይቃቸው እኛስ ይህን አንተውም አሉት። እርሱም በጥበብ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ይህን ግብር ብትተው በዚህች ቦታ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን እንሠራለን። መሥዋዕታችሁንም በዚያ ለቅዱስ እግዚአብሔር ታቀርባላችሁ አላቸው።›› በዚህ ተደስተው ተመለሱና ያንን የጣዖት ቤት አፍርሰው እጅግ ያማረች ቤተ ክርስቲያንን በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ስም ሠሩ። የመልአኩንም በዓለ ንግሥ በዚህች ዕለት አከበሯት። ከዚያን ጊዜም ጀምሮ የከበረ የመላእክት አለቃ የመልአኩ የሚካኤል የመታሰቢያውን በዓል በሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡ዳግመኛም ንዑድ ክቡር የሚሆን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ባሕራንን በሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን ያዳነበት ድንቅ ተአምርም ይህ ነው። አንድ ደግ ሰው በዚያች ሀገር ይኖር ነበር። ክፉ ጎረቤትም ነበረው። ይህም ደግ ሰው ነዳያንን እጅግ የሚወድ የቅዱስ ሚካኤልንም ዝክር ሳያስታጉል የሚዘክር ሰው ነው። በዚህ ሥራው ግን ይህ ክፉ ጎረቤቱ ይዘብትበት ነበር። በኋላም ያ ደግ ሰው የሚሞትበት ቀን ሲደርስ ሚስቱን ዝክረ ሚካኤልን እንዳታቋርጥና ነዳያንን እንዳትዘነጋ ነግሯት ያርፋል። እርሷም ፀንሳ ነበርና እርሱ ከሞተ በኋላ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ። ምጥም ቢጠናባት ወደ መልአኩ ጮኸች፤ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም ተራዳትና መልከ መልካም የሆነ ወንድ ልጅ ወለደች። መልአኩም እንዲህ አላት። ‹‹ልጅሽ የዚህ የጎረቤትሽን ሀብት ይወርሳል።›› መልአኩም ለጎረቤታቸው ጆሮውም ከፍቶለት ነበርና ይህን ነገር ሰማ። በዚህም ‹‹በምን ምክንያት ወስጄ ላጥፋው›› ብሎ ሲያስብ ሴቲቱ ልጅዋን ብቻዋን ለማሳደግ ተቸገረች፤ ‹‹ላሳድግልሽ፤ ለአንቺም ይኸው ገንዘብ እሰጥሻለሁ›› ብሎ ብዙ ወርቅ ሰጣት። እርሱም ‹‹ከእንግዲህ አርፋለሁ›› ብሎ ልጁን መጣያ ሳጥን ያዘጋጅና ወደ ባሕር ቢጥለው ባሕሩም ሩቅ ሀገር ወስዶት ከዳር ይጥለዋል።
ከዚህም በኋላ አንድ በጎቹን ያሠማራ ሰው ያገኘዋል። ያንንም ሳጥን ወስዶ ከቤት ያኖረዋል፤ በምን መክፈት እንደሚችል ሲያስብ ዳግመኛ ወደ ባሕሩ እንዲሄድ እግዚአብሔር ሐሳብ ያሳድርበትና ተነሥቶ ይሄዳል። ሲሄድም ዓሣ አጥማጅ ያገኝና ዓሣ ለእርሱና ለቤተሰቡ እንዲያጠምድለት ይነግረዋል። ያም ዓሣ አጥማጅ ሲያጠምድ ታላቅ ዓሣ አገኘና ሰጠው። ዋጋውን ሰጥቶም ወደ ቤት ተመለሰና ሆዱን ቢሰነጥቀው ቁልፉን በዚያ አገኘው። በዚያም ሳጥኑን ቢከፍት መልከ መልካም ልጅ አገኘ። ልጅም ስላልነበረው እጅጉን ተደሰተ። ባሕራን ብሎም ሰየመው።
ከብዙ ጊዜያት በኋላ ያ ክፉ ሰው ከንግድ ተመልሶ በዚያ መንገድ ሲያልፍ መሸበትና ከዚህ ሰው ቤት አደረ። ባሕራንንም ተመለከተውና ሰውየውን ልጁ እንደሆነ ለማወቅ ታሪኩን ጠየቀው፤ ሰውየውም የሆነውን ሁሉ ነገረው። ክፉ ሰውየውም ልጁ እንዳልሞተ ባወቀ ጊዜ ደነገጠና መልእክት ሊልከው ስለሚፈልግ የባሕራንን አባት ልጁን እንዲሰጠው ጠየቀው። እርሱም ተስማምቶ ሰጠው። በክፋትም ተነሣሥቶ ባሕራንን እንዳገኘው እንዲገድለው ለአገልጋዩ ደብዳቤ ጽፎ አገልጋዩና እርሱ ብቻ የሚያውቁትን ማኅተም አድርጎ ሰጠው። ‹‹ይቺን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው፡፡ ማንም እንዳያውቅ›› ለባሕራንም ለመንገዱ የሚሆነውን ስንቅ ሰጠው፡፡
የራሱን የሞት ደብዳቤ እንደያዘ ሳያውቅ ባሕራን ወደ ታዘዘበት ሥፍራ ተጓዘ፤ ከዚያ ሰው ቤት ለመድረስ ሲቀርብ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ‹‹አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው›› አለው፡፡ ‹‹ወደ ዕገሌ ሀገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለ ጠጋ የተጻፈች መልእክት ናት›› አለው፡፡ ‹‹ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ›› አለው፤ እርሱም ስለ ፈራ ሰጠው፡፡ የሞቱን ደብዳቤ ያቺን የሞት መልእክት ደምስሶ በሕይወት ቀየረለት። በእርሱም ፈንታ በንፍሐት ለውጦ እንዲህ ብሎ ጻፈ፤ ‹‹ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ሰው ይቺ ደብዳቤ ደርሳ በምትነበብበት ጊዜ ልጄ ዕገሊትን አጋቡት፡፡ በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን፣ ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን፣ ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና እኔን አትጠብቁኝ፡፡ እኔ ብዙ እዘገያለሁ የኔ ሹም እገሌ ሆይ! በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት፡፡››
አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ‹‹ወደ ባለ ጠጋው ቤት ሂደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ስጠው፡፡ በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው፡፡ እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጬልሃለሁ›› አለው፡፡ ባሕራንም ‹‹እሺ ጌታዬ ያዘዝኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ›› አለ፡፡
ባሕራንም ወደ ባለ ጠጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው፡፡ ካነበባት በኋላም በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ፡፡ አስተውሎም እርግጠኛ እንደ ሆነ ዐወቀ፡፡ ለባሕራን ሰርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለ ጠጋውን ልጅ አጋቡት፡፡ ዓርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ፡፡ ሀብቱንም ሁሉ አወረሱት።
ከዚህ በኋላ ባለ ጠጋው ከሄደበት በተመለሰ ጊዜ በደስታ የሆነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ‹‹ይህ የምሰማው ምንድነው›› ብሎ ጠየቀ፡፡ እነርሱም ‹‹ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት፡፡ እነሆ ዓርባ ቀናት በሰርግ ላይ ነው፡፡ ገንዘብህንና ጥሪትህን ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝህ ሰጥተውታል›› አሉት፡፡ ይህንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ በድንገትም ሞተ፡፡
ባሕራንም ከዚህ በኋላ የቅዱስ ሚካኤልን ዝክር በሚገባ እየዘከረና ለቤተ ክርስቲያኑም እየታዘዘ የሚያገለግል ሆነ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዓሉን በሚገባ አክብረን በረከት እንድንቀበል ይርዳን፤ የቅዱስ ሚካኤል የረድኤቱ ኀይል በሀገራችን በሃይማኖታቸው ምክንያት ከተሠውት የክርስቲያን ወገኖች ጋር ይሁን፤ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ምንጭ፡– ድርሳነ ቅዱስ ሚካኤል፣ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ
