ለፈጣሪ በበጎ ፈቃድ መገዛት ይገባል!

ጥር ፭፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ሰው በራሱ ፈቃድ በጎ አልያም በክፉ ሐሳብና ምኞት መጥፎ ሊሆን ይችላል፡፡ የአዳም ዘር ጥንተ ተፈጥሮውን ዐውቆና ተረድቶ በድንቅ ሥራው ለፈጠረው አምላክ ተገዢ የመሆን ፈቃድም የራሱ ነው፡፡ በውዴታ ብቻ ሳይሆን በግዴታም ለፈጣሪ መገዛት እንዳለብን ቅዱሱ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡

ታዲያ ዓለምን ሁሉ ከእነ ጓዟ ለፈጠረ አልፋና ዖሜጋ፣ ኤልሻዳይ ለሆነው እግዚአብሔር መገዛት በፍቅር መሆን ሲገባው ብዙኃኑ ሰው ግን አሻፈረኝ ብሏል፡፡ ይባስ ብሎም በራሱ ፈቃድ ያለ እግዚአብሔር አምልኮ ለመኖር መወሰኑ ሳያንስ ዓለምን መግዛት እንደሚቻለው እያሰበ ነው፡፡ ሰው በራሱ ጥበብ ተጉዞ ጨረቃን አልያም ሌሎች በሰማያት ላይ ያሉ ድንቅ ፍጥረታት ላይ መድረስ ቢችልም ወደ ላይ የመምጠቅ ኃይሉ የተገደበ እንደሆነ ግን ማመን አዳግቶታል፡፡ ምንም መሣሪያ ቢሠራ፣ ምንም ተጠብቦ ወደ ሰማይ መጓዝ ቢችል እርሱ ባወቀ እንጂ የትም መድረስ አንችልም፡፡ ‹‹እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፣ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን አወርድሃለሁ›› ተብሎ እንደተጻፈ (አብድ. ፩፥፬) ጥበብም ከእግዚአብሔር በመሆኑ እርሱን ባለመፍራት የሚደረግ ነገር ማንም ምንም ማድረግ አይቻለውም፡፡

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ወደ ፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ የሆነ ማንም ሊያሸንፈውም የማይችል ነው፡፡ በቸርነቱ ብዛት ዓለምን ሲፈጥርም መልካም በመሆኑ ነው፡፡ ሰው ግን አምላክነትን ሽቶ ክሕደት ፈጸመ፤ ኃጢአት ሠራ፤ ከክብሩም ተዋርዶ መከራና ሥቃይ፣ ረኀብ፣ ጥም፣ እንግልት፣ ልፋት፣ ገዓር፣ ኀሣር ወዳለባት ምድር ተጣለ፡፡ በዚህም ሆኖ ሰው አምላኩን መበደል አላቆመም፡፡ የተፈቀደለትን ትቶ ያልተቀደለትን፣ የታዘዘውን ሳይፈጽም ያልታዘዘውን፣ የማይገባውን በመሻትም ፈጣሪውን መዳፈር ቀጠለ፡፡ ኃጢአት መሥራቱ ሳያንስ አምላክ ላይ መድረስ፣ ወደ ላይ መጥቆ ፈጣሪን ተዳፈረ፡፡

በኖኅ ዘመን የተፈጸመው የባቢሎናውያን ድርጊትም የዚህ ማሳያ ነው፡፡ በክፉ ምክራቸው ተነሣሥተው ፈጣሪ ወዳለበት ለመድረስ የሰናዖር ግንብን ሠሩ፡፡ መጽሐፉም እንደሚነግረን  ‹‹እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። ‹‹ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።›› (ዘፍ.፲፩፥፩-፱)

ታሪኩን በመቀጠል ስናነበውም አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ የሰናዖርን ግንብ አፍርሶ ባቢሎናውያኑን በትኗቸዋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ አንድነታቸውና ሦስትነታቸው የተገለጸበት ጥር ሰባት ቀን የከበረ በዓል እንደመሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡

ዓለማችን በጎርፍ እየተጥለቀለቀች፣ በመሬት መንቀጥቀጥ እየራደች፣ በሰደድ እሳት እየተለበለበች ያለችው የአዳም ዘር አምላኩን ክዶ፣ ሀብት፣ ሥልጣንና ኃይል በመሻት በኃጢአት ሰንሰለት ታስሮ የጠላት ዲያብሎስ ተገዢ በመሆኑ ነው፡፡ ወደ ላይ እየመጠቅን ሲመለስን ወደ ታች እየወረድን እንደሆነ ማን በነገረን? በሰው ሠራሽ ሥሪት የሚንቀሳቀሱ  ቁሳዊ አካላትን በመሥራት የአምላክን ክቡር ፍጡር ሰውን ለመተካትና ፈጣሪ ለመሆን፣ ከዚያም ባሻገር የተፈጥሮ ሂደትን በሚያዛባ መልኩ ዘር የመተካትን ሂደት ሰው ሠራሽ የማድረግ ጥረት አምላክነትን የመሻት ነው፡፡ ይህም የዳረገን ለከፋ ነገር መሆኑ በግልጽ የሚታይ ሆኗል፡፡ እኛ የማይገባንን ለማግኘት ስንጥር የሚገባንን ግን ተነጠቅን፡፡ ሰው የመሆን መብታችንን አጥተናል፡፡ በነጻ፣ ያለ ክፍያ ድንቅ ተደርገን ተሠርተን እኛ ግን በውድ ዋጋ ቁሳዊ አካልን ሸምተን የሰውን ሥራ ሁሉ እንዲሠራልን ተመኘን፡፡ የራሳችንን ክብር የሚያሳጣን ነገር መሆኑን ግን ለማወቅ ዓይነ ልቡናችን ታወረ፡፡

ጥበበኛ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪትም ሆነ በሕገ ወንጌል የገለጠልን ምሥጠር ድንቅ ሥራውን ብቻ ሳይሆን በክብር ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሰጥ ነው፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ ግን እርሱን መፍራት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› እንዲል፡፡ (ምሳሌ ፩፥፯) ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ ክብሩን አላወቀም፡፡ ስለዚህ የጥንተ ተፈጥሮአችንን አስታውሰን፣ የተፈጠርንበትን ምክንያትን ዐውቀንና ተድረተን፣ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር በበጎ ፈቃድ በመገዛት ልንኖር ይገባል፡፡

አምላካችን ቸርነቱንና ምሕረቱን ያብዛልን፤ ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!