‹‹እነርሱ በእምነት የእሳት ኀይልን አጠፉ›› (ዕብራውያን ፲፩፥፴፬)

ኃይለሚካኤል ወንድራድ

ታኅሣሥ ፲፯፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ለብዙዎቻችን እሳትን የሚያጠፋው ውኃ ብቻ ይመስለናል፡፡ ለእግዚአብሔር የታመኑ ቅዱሳን ሰማዕታት የእሳትን ኃይል በትዕግሥታቸው እንዳጠፉትና ጸሎታቸውም ለእኛ በአማላጅነታቸው ለምንታመን ምእመናን ሁልጊዜም እንደሚያስፈልገን ፈልፈለ ማኅሌት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ምስክር ሆኖ ያስተምረናል፤ አጥፍኡ ኃይለ እሳት በትዕግሥቶሙ፤ ይብጽሐነ ወትረ ጸሎቶሙ፤በትዕግሥታቸው የእሳትን ኃይል አጠፉ፤ ጸሎታቸው ዘወትር ይድረሰን” እንዲል፤ (ድጓ ዘታኅሣሥ ፪)

በሐዲስ ኪዳን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እምነት ማለት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ ፣ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት››  በማለት የተናገረውን ቃል (ዕብራውያን ፲፩፥፴፬) በብሉይ ኪዳን አስቀድሞ በተፈፀመ ገድል እንድናውቀው የሠለስቱ ደቂቅ የባቢሎን የዱራ ሜዳ ገድልና የእምነት ጽናት ዓይነተኛ የሕይወት ትምህርት እንዲሆነን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎልን እናገኛዋለን፡፡ እምነታችን እውነተኛ ሆኖ የሚገለጠው እግዚአብሔር በሚፈጽምልን የትድግና ሥራ ብቻ ሳይሆን መከራም ቢመጣ የመጣው እግዚአብሔር ፈቅዶ በመከራው ተፈትነን ካለፍን በኋላ እኛ ልጆቹ እንድናገኝ የፈለገውን ሰማያዊ አክሊልና ዋጋ እንድናገኝም ስለሚፈልግ መሆኑን ማመን ስንችል ነው፡፡

ጻድቁ አባታችን ቅዱስ ኢዮብ  እጅግ ብዙ መከራ ሲደርስበት ‹‹ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፤ ክፉውን ነገርስ አንታገሥምን?›› በማለት በደረሰበት ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በከንፈሩ ሳይበድል የሕይወቱን የፈተና ጊዜ ለማሳለፍ በቅቷል፡፡ (መጽሐፈ ኢዮብ ፪፥፲) የሠለስቱ ደቂቅ እውነተኛ እምነትም ለናቡከደነፆር በሰጡት ምላሽ ውስጥ የምናገኘው ነው፡፡ ንጉሥ ናቡከደነፆርም እኔ ላሠራሁት ምስል ስገዱ ባላቸው ጊዜ  ‹‹ናቡከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፤  ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን ፣ አማልክትህን እንዳናመልክ ፣ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ›› አሉት፡፡ (ትንቢተ ዳንኤል ፫፥፲፭-፲፰)

ከዚህ በኋላ ወደ እሳት እንዲጨመሩ ንጉሡ አዘዘ፡፡ አይደለም እሳት ላይ ተጥደን በመልካም ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንኳን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ላቃተን ለእኛ፣ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት መካከል ሆነው የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ብቻ ሳይሆን ረጅም ጸሎትን ሲያደርሱ

 

እንደነበር ማወቅ ምንኛ ግሩም ነው! (ወጸለዩ ማዕከለ እቶነ እሳት ነዋኃ ጸሎተ) (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ታኅሣሥ ፪)፡፡

በመከራ ላይ መከራ ቢያጸኑባቸው በምስጋና ላይ ምስጋና በመጨመር ታላቅ የሆነ የነገረ ክርስቶስ ትምህርትንም የያዘ ጸሎት ያደረሱት በእሳት ውስጥ ነው ቢባል ማን ያምናል፡፡ በጸሎታቸው እነርሱ ይህን ገድል ከፈፀሙ ከ፮፻ ዓመት በኋላ አምላክ የሰውን ሥጋ ለብሶ ተገልጦ እንደሚወለድ እና በዚህች ምድርም ፴፫ ዓመት እንደሚቆይ የሚያጠይቅ ነው፡፡

ሰው እግዚአብሔርን ካመነና ማመኑንም በሥራ ገልጦ ካከናወነ ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ረድኤት ከእርሱ ጋር ስለሚሆን በሥጋ ዓይን ስናየው በሥጋው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስበት የሚችል እሳት እንኳን አቅም ያጣል፡፡ ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሳት ወርውረው እንዲጨምሩ በንጉሡ የታዘዙትን ሰዎች የገደለ እሳት በመካከሉ የተገኙ ሠለስቱ ደቂቅ ላይ ግን አንዳች ጉዳት ማድረስ አልቻለም፡፡ የራሳቸው ጠጉር አንዲት ዘላላ እንኳ አልተቃጠለችም፤  ሰናፊላቸውም አልተለወጠም፤ ሽታቸውንም አልለወጠም፡፡ (ትንቢተ ዳንኤል ፫፥፳፯)

ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስ በዓላውያን ነገሥታት ላይ አድሮ ዛሬም በእኛ ላይ የጥላቻን እሳት እያነደደ ከራሳችን አልፎ ለሀገራችን ኢትዮጵያም የሚተርፍ መከራን አኑሯል፡፡ የባቢሎንን እሳት በመስቀሉ በማቀዝቀዝ ሠለስቱ ደቂቅን ከእግዚአብሔር ተልኮ ያዳነው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በእኛና በሀገራችን ኢትዮጵያ እየነደደ እጅግ መከራ ውስጥ የከተተንን የጥላቻ እሳት እንዲያበርድልንና ሁላችንም የፍቅር ሰው እንድንሆን አማላጅነቱና ጠብቆቱ አይለየን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር!