የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ኀዳር ፳፭፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ውድ አንባብያን! እንደምን ከረማችሁ? አሜን! የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን! ከወራት በፊት ‹‹የቤተ ክርስቲያን ፍኖተ ካርታ›› በሚል ርእስ የተወሰኑ ጉዳዮችን በተከታታይ አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬም ከቤተ ክርስቲያናችን አዲሱ የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ከዚያው ጋር የተገናኘ ሐሳብ አቅርበንላችኋል፡፡
ዕቅድ የአንድ ተቋም የህልውና ጥያቄን የሚመልስ ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የማያቅድ ተቋም ቀርቶ ግለሰብ እንኳን ራሱን በትክክል መምራት፣ የሚያስበውንም ማሳካት፣ የሕይወትን እንቅፋቶችንም ማስወገድ፣ ነገን የተሻለ ማድረግ አይችልም፡፡
ቤተ ክርስቲያናችንም ከ ስልሳ ሚሊዮን በላይ አማኞችን (ምንጭ-ፍኖተ ካርታው) ከአርባ ሺህ ያላነሱ ገዳማትንና አድባራትን፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አገልጋዮችን፣ በብዙ ዋጋ የሚገመቱ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶችን የምታስተዳድር፣ ብዙ መንፈሳዊና አካላዊ ጦርነት ከብዙ አቅጣጫ ያለባት ቤተ ክርስቲያን በዕቅድ ካልተመራች ምድራዊ አገልግሎቷን ሰማያዊ በረከቷን ማቆየትና ማሸጋገር ይከብድባታል፡፡
ዓለም አቀፋዊቷና ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን እስከዛሬ ድረስ በመሪ ዕቅድ አለመመራቷ እጅግ ዋጋ እንዳስከፈላት ጥናት የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ሀብቷን ከውጭ ወራሪ ከውስጥ ሰርሳሪ እንዳትታደግ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቷ ለልጆቿ ሳይሆን ለአማሳኞችና ለሰርጎ ገቦች ሲሳይ እንዲሆን፣ ዳሯ እየተፈታ ማሐሏ ዳር እንዲሆን አድርጓል፡፡
ብዙ የደከሙ አገልጋዮቿ የሚንከራተቱባት ፍትሕ ርትዕ ጠፍቶ ለጠላት አጀንዳ የተጋለጠች እንድትሆን አድርጓት ከመቆየቱ በተጨማሪ በርካታ ምእመናን ልጆቿ የሌላ በረት ሲሳይ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ዛሬም ችግሩ አልተቀረም፡፡
ትናንትን ለመዘከር፣ ዛሬን ለመመስከር፣ ነገን ለመፍጠር ዕቅድ ዓይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ቤተ ክርስቲያን የዐሥር ዓመት መሪ ዕቅድ አዘጋጅታለች፡፡ በየደረጃው ላሉ ባለ ድረሻ አካላትም ዕቅዱን እያስተዋወቀች ትገኛለች፡፡
ማኅበረ ቅዱሳንም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ ዕቅዱ እንዲፈጸም፣ ቤተ ክርስቲያንም ዓላማዋን እንድታሳካ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር እንዲቻል በስልታዊ ዕቅዱ ውስጥ በማካተት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከኅምሳ ባላነሱ ማእከላቱ አማካኝነት የባለሙያዎች ኅብረት እንዲቋቋም፣ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ፣ የፓናል ውይይቶች እንዲደረጉ፣ የአሠልጣኞች ሥልጠና እንዲሰጥ፣ የሚድያ ሽፋን እንዲያገኝ፣ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር የሚያስችሉና መሰል ጉዳዮችን በስልታዊ ዕቅዱ አካቶ እየሠራ ይገኛል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ፍኖተ ካርታውን ለምእመናን በማስተዋወቅ፣ ግንዛቤን መፍጠር፣ ተነሣሽነትን መጨመር፣ ዕቅዱን በማስፈጸምና በመፈጸም ረገድ የእኔነት ስሜት መፍጠር፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችንና የዕቅድ ፈጻሚዎችን ከደጋፊና ባለድርሻ አካለት ጋር እንዲቀናጁ ማመቻቸትን፣ የአመለካከት ለውጥ ማምጣትን ታሳቢ ያደረገ ጽሑፍ ሲሆን ወደፊትም የፍኖተ ካርታውን ዝርዝር ይዘቶች፣ የማስፈጸሚያ ስልቶቹን እንዲሁም ሊያሳካቸው የታሰቡ ግቦችን በተከታታይ ለማድረስ ጥረት የሚደረግ ይሆናል፡፡
ቸር እንሰንብት!
