ከ400 በላይ የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት ተጠመቁ።
ከዚህ በተጨማሪም በዕለቱ የማኅበረ ቅዱሳን ሽንዲ ወረዳ ማዕከል አባላት፣ የኮሊ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መዘምራን፣ የሸንዲ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መዘምራን፣ ጎመር ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች መዝሙርና ሥነ ጽሑፍ በኦሮምኛ በአማርኛ ቋንቋ ለምእመናን አቅርበዋል፡፡
ሥርዓተ ጥምቀቱ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት የተጀመረ ሲሆን የተጠመቁት ምእመናን በሥርዓተ ቅዳሴው ተሳትፈው ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ በሊቀ ማዕምራን ሀዲስ ጤናው የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ እና በመጋቤ ምሥጢር ኃይለማርያም ታዬ ትምህርት ተሰጥቶ ሀገረ ስብከቱ ለተጠማቂያን የብሔረሰቡ አባላት 600 የአንገት መስቀል አበርክቷል፡፡
ተጠማቂ ምእመናኑ አባይ በረሃን ከሚያዋስኑ ከወንበርማ ወረዳ ሦስት ቀበሌዎች የመጡ ሲሆኑ በአካባቢው ከአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት ጀምሮ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት አልፎ አልፎ ያሉና የተጠመቁ የብሔረሰቡ ምእመናን ቢኖሩም ለዚህ በርካታ የብሔረሰቡ አባላት መጠመቅ ምክንያት የሆኑት አቶ አያና የተባሉ የቻግኒ ወረዳ ማዕከል አባል ወደ ቦታው ለሥራ በመጡና አሁን የተዛወሩት ግለሰብ እና መምህርት መድኃኒት ሞላ የሽንዴ ወረዳ ማዕከል አባል አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የሽንዲ ወረዳ ማዕከል በ1994 ዓ.ም ሁለት ህፃናትን ከአካባቢው በመውሰድና የአብነት ትምህርት ቤት ለማስገባት የጀመረው ሙከራ ልጆቹ ሊለምዱ ስላልቻሉ ቢቋረጥም ለዚህ እንቅስቃሴ መጠናከር በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወንበርማ ወረዳ ቤተክህነት እና ከአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጋር በመሆን 2000 ዓ.ም ግንቦት 16 ቀን ወደ የማቤል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በወረዳ ማዕከሉ አስተባባሪነት የተደረገ የእግር ጉዞና ከአካባቢው የጎሳ አካላት ጋር የተደረገው ትምህርትና ውይይት ትልቅ በር እንደከፈተና ከዚያም በኋላ በወረዳ ቤተክህነቱ እና ወረዳ ማዕከሉ የሚደረጉ ትምህርተ ወንጌል ይበልጥ ግንኙነታቸውን እንዳጠናከረው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የባህርዳር ማዕከል እና ሽንዲ ወረዳ ማዕከል በሽንዲ ከተማ የእራት ግብዣ በማዘጋጀትና ከበጎ አድራጊዎች 4000 ብር አስባስቦ ቆርቆሮ እና እንጨት ገዝቶ በማጓጓዣ፤ ግንቦት 2002 ዓ.ም ጉባኤ በማካሄድና ከ460 በላይ የብሔረሰቡ አባላት ጋር ውይይት አድርጎ በቀበሌው ባሉት በመምህርት መድኃኒት ሞላና አንድ ሌላ መምህር አስተባባሪነት ተጨማሪ እንጨት እንዲያዋጡ በማድረግ ቤተክርስቲያን በጎመር ቀበሌ ሊሠራ ችሏል፡፡
ብፁዕ አቡነ በርናባስ ከአሁን በፊት የተጠመቁትንና አዲስ ተጠማቂያንን እንዲበረቱ መክረው በበዓሉ ለተገኙ ምዕመናን እንዳሉት “የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ወገኖቻችን ወደዚህች ሃይማኖት ሊመጡ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በደስታ ልንቀበላቸው፣ ልንከባከባቸውና ልንደግፋቸው ይገባል”፡፡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የብሔረሰቡ አባላት በበኩላቸው ከ 2፡00-4፡00 ሰዓት የሚፈጅ የእግር ጉዞ ተጉዘው እንደተጠመቁ በመግለጽ ለሰሩት ቤተክርስቲያን ጽላት እንዲገባላቸው፣ በቅርብ ቦታ ተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናት እንደሰሩላቸውና ካህናት እንዲመደቡላቸው ጠይቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ በርናባስም ከወረዳ ቤተክህነት ጋር በመሆን የተቻላቸውን እንደሚፈጽሙና ምዕመናን ከጎናቸው በመሆን ለቤተክርስቲያን ሥራ እንዲተጉ ጠይቀዋል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።