ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሐምሌ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በየዓመቱ ሐምሌ ፭ ቀን በአንድ በኩል የጾመ ሐዋርያት ፋሲካ የሚከበርበት ዕለት ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በዓለ ዕረፍትም በዚሁ ዕለት ይዘከራል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የእነዚህን ቅዱሳን ታሪክ በቅደም ተከተል በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤
ቅዱስ ጴጥሮስ
ቅዱስ ጴጥሮስ በአባቱ የሮቤል፣ በእናቱ የስምዖን ነገድ ሲኾን፣ የተወለደውም በገሊላ አውራጃ በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ‹ስምዖን› ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ጴጥሮስ› ብሎ ጠርቶታል፡፡ ትርጕሙም በግሪክ ቋንቋ ዓለት (መሠረት) ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የሚተዳደረው በዓሣ አጥማጅነት የነበረ ሲኾን፣ ሰዎችን በወንጌል መረብ እያጠመደ ወደ ክርስትና ሕይወት ይመልስ ዘንድ ጌታችን ለሐዋርያነት ጠርቶታል (ሉቃ. ፭፥፲፤ ማር. ፩፥፲፮)፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈሳዊ ቅንዓቱና ለጌታችን በነበረው ፍቅር የሐዋርያት አለቃ ኾኖ ተሹሟል፡፡ ለአገልግሎት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮም በእስያ፣ በሮም፣ በሰማርያ፣ በልዳ፣ በኢዮጴ፣ በአንጾኪያ፣ በገላትያና በሌሎችም አገሮች እየተዘዋወረ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ በስብከቱ ምክንያትም ልዩ ልዩ መከራን ተቀብሏል፡፡ በክርስቶስ ኀይል አጋዥነት ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከተሰጠው ጸጋ ብዛት የተነሣ በጥላው ሕሙማን ይፈወሱ ነበር (ሐዋ. ፭፥፲፭)፡፡ ሐዋርያው በቃል ካስተማረው ትምህርት በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ የተመዘገቡ ሁለት መልእክታትን ጽፏል (፩ኛ እና ፪ኛ ጴጥሮስ)፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተሰቅሎ በሰማዕትነት ሲያርፍ
የቅዱስ ጴጥሮስ ምድራዊ የአገልግሎት ዘመኑ ሊፈጸም ሲቃረብም እንዲህ ኾነ፤ በዘመኑ የክርስቲያኖች ጠላት የነበረው የሮም ንጉሥ ወደ አካይያ ዘምቶ ድል አድርጎ በደስታ ወደ ሮሜ ሲመለስ መኳንንቱን ለማስደሰት፤ ጣዖታቱንም ለማክበር ሲል በቅዱስ ጴጥሮስና በሌሎችም ክርስቲያኖች ላይ የሞት ፍርድ ዐወጀ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በሮም ሲያስተምር ቆይቶ የሮም መኳንንት እንዳይገድሉት ትጥቁን ለውጦ ከሮም ሲወጣ ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ተገለጸለት፡፡
በዚህ ጊዜ ‹‹አቤቱ ጌታ ሆይ ወዴት ትሔዳለህ?›› ሲል ቢጠይቀው ጌታችንም ‹‹ልሰቀል ወደ ሮም እሔዳለሁ›› አለው፡፡ ‹‹ዳግመኛ ትሰቀላለህን?›› ባለው ጊዜም ‹‹አንተ ስትፈራ ጊዜ ነው እንጂ›› ሲል መለሰለት፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን ታጥቀህ ወደ ወደድኸው ትሔድ ነበር፡፡ ስትሸመግል ግን እጅህን ታነሣና ሌላ ሰው ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል፤›› (ዮሐ. ፳፩፥፲፰) በማለት ጌታችን የነገረው ቃል አሟሟቱን የሚያመለክት መኾኑን አስታውሶ ወደ ሮም ተመልሶ ስብከቱን ቀጠለ፡፡
በሮማውያን ሕግ ቅጣት የተፈረደበት ወንጀለኛ የሮም አገር ተወላጅ ከኾነ የወንጀሉ ክብደትና ቅለት እየታየ ግርፋት ወይም ሞት ይፈረድበታል እንጂ በአንድ ወንጀል ሁለት ቅጣት አይቀጣም ነበር፡፡ ወንጀለኛው የውጪ አገር ዜጋ (ከሮም ውጪ) ከኾነ ግን ለምሳሌ ቅጣቱ ግርፋት ከኾነ ከተገረፈ በኋላ እስራት ይጨመርበታል፤ ቅጣቱ ሞት ከኾነም ከገረፉት በኋላ በመስቀል ወይም በሌላ መሣርያ ይገድሉት ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ዜግነቱ ሮማዊ አልነበረምና በግርፋትም፣ በእስራትም በሞትም እንዲቀጣ ተፈረደበት፡፡
እንደ ሥርዓታቸውም ቅዱስ ጴጥሮስን ከገረፉት በኋላ ሊሰቅሉት ሲሉ ወታደሮቹን ‹‹እንደ ክብር ንጉሥ እንደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አቁማችሁ ሳይኾን፣ ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እንዳላቸው አድርገው ሐምሌ ፭ ቀን ዘቅዝቀው ሰቅለውታል፡፡ በመስቀል ላይ ሳለም ተከታዮቹን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ካዘዛቸው በኋላ ነፍሱን ለእግዚአብሔር ሰጠ፡፡ ሥጋውንም መርቄሎስ የሚባለው ደቀ መዝሙሩ ሽቱ ቀብቶ፣ በነጭ ሐር ገንዞ ዛሬ ቫቲካን በምትባለዋ ስፍራ በክብር ቀብሮታል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ
ቅዱስ ጳውሎስ ለአገልግሎት ከመጠራቱ በፊት ‹ሳውል› ይባል ነበር፡፡ ከኦሪቱ ምሁር ከገማልያል ሕገ ኦሪትንና መጻሕፍተ ነቢያትን ተምሯል፡፡ ለሕገ ኦሪት ቀናኢ ከመኾኑ የተነሣም የክርስቶስ ተከታዮችን ዅሉ ያሳድድ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተደብድቦ በሰማዕትነት በሞተ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ የገዳዮቹ ልብስ ጠባቂ ነበር (ሐዋ. ፯፥፶፰፤ ፳፪፥፳)፡፡ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ሲሔድ ከመንገድ ላይ ለሐዋርያነት ተጠርቷል (ሐዋ. ፱፥፩-፴፩፤ ፳፪፥፩-፳፩)፡፡
ለሐዋርያነት ከተጠራበት ጊዜ ጀምሮም በመላው ዓለም እየተዘዋወረ ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሳምኗል፡፡ ሲሰብክም ጣዖት አምላኪ፣ ሕመምተኛ፣ ችግረኛ፣ አረማዊና አይሁዳዊ እየመሰለ ብዙዎችን አስተምሮ ለእግዚአብሔር መንግሥት አዘጋጅቷል (፩ኛ ቆሮ. ፱፥፲፱-፳፫)፡፡ ዐረብ፣ አንጾኪያ፣ እልዋሪቆን፣ ሊቃኦንያ፣ ሦርያ፣ ግሪክና ልስጥራን ካስተማረባቸው አገሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ወንጌልን በመስበኩ ምክንያትም ከአይሁድና ከአረማውያን ዘንድ ብዙ መከራና ስቃይ ደርሶበታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጸጋ ብዙ ድንቆችንና ተአምራትን አድርጓል፡፡ በልብሱ ቅዳጅም ሕሙማን ይፈወሱ ነበር (ሐዋ. ፲፱፥፲፩)፡፡ ሐዋርያው በቃል ካስተማረው ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ የተመዘገቡ ፲፬ መልእክታት አሉት፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ሲያርፍ
አገልግሎቱን ሊፈጽም ሲልም የሮም ንጉሥ ኔሮን ቄሣር የክርስቲያኖች ቍጥር እየጨመረ የመጣው በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት በመማረካቸው ምክንያት መኾኑን ተረድቶ፤ ይልቁንም የቤተ መንግሥቱ ሰዎች ሳይቀር በቅዱስ ጳውሎስ በመማረካቸው ተቈጥቶ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ፍርድ ሸንጎው አስቀረበው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቀኝ እጁ ከሰንሰለቱ ጋር መስቀሉን ይዞ ንጉሡንና ወታደሮችን ሳይፈራ የኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነትና አምላካዊ ሥልጣን ይመሰክር ነበር፡፡
ንጉሡም በቍጣ ይሙት በቃ ፈረደበት፡፡ ከላይ እንደ ተገለጸው ሮማውያን የሞት ፍርድ ሲፈርዱ የሚቀጣው ሰው የሌላ አገር ዜጋ ከኾነ ከፍርዱ ውጪ ተጨማሪ ቅጣት ይቀጡትና ይገድሉት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን የሮም ዜግነት ስለ ነበረው ሳይገርፉ በአንድ ቅጣት ብቻ በሰይፍ እንዲገደል ወስነውበታል፡፡ ወደሚገደልበት ስፍራ ሲወስዱትም በንግግሩና በአስተያየቱ ዅሉ ምንም ፍርኀት አይታይበትም ነበር፡፡ እንዳውም በጦርነት ድል አድርጎና ማርኮ እንደ ተመለሰ ወታደር ይደሰት ነበር እንጂ፡፡ ለሚገድሉትም ይቅርታን ይለምን ነበር፡፡
በገዳዮቹና በተከታዮቹ ፊትም የክርስትና ሽልማቱ የእግዚአብሔር መንግሥት መኾኑን የሚያስገነዝብ ቃል እያስተማረ እግዚአብሔር የሚሰጠውን የጽድቅ አክሊል ለመቀበል ይቻኮል ነበር (፪ኛ ቆሮ. ፬፥፮-፲፰)፡፡ ወታደሮች ሊገድሉት ሲወስዱትም ከንጉሥ ኔሮን ወገን የኾነችውን የአንዲት ብላቴና መጐናጸፊያ ‹‹ዛሬ እመልስልሻለሁ›› ብሎ ከተቀበላት በኋላ ‹‹መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፡፡ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፤ ወደፊትም የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤›› በማለት ራሱ በመልእክቱ እንደ ተናገረው (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፯-፰)፣ ፊቱን በብላቴናዋ መጐናጸፊያ ተሸፍኖ አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ አገልግሎቱን በሰማዕትነት ፈጽሟል፡፡
ደቀ መዛሙርቱም ራሱን ከአንገቱ ጋር ቢያደርጉት እንደ ቀድሞው ደኅና ኾኖላቸው በክብር ገንዘው ቀብረውታል፡፡ ሰያፊው ቅዱስ ጳውሎስን እንደ ገደለው ለመናገር ወደ ንጉሡ ሲመለስም ያቺ መጐናጸፊያዋን የሰጠችው ብላቴና ‹‹ጳውሎስ ወዴት አለ?›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ራሱን ተቈርጦ በመጐናጸፊያሽ ተሸፍኖ ወድቋል›› ሲላት ‹‹ዋሽተሃል፤ እነሆ ጴጥሮስና ጳውሎስ በእኔ በኩል አልፈው ሔዱ፡፡ እነርሱም የመንግሥት ልብስ ለብሰዋል፡፡ በራሳቸውም በዕንቍ ያጌጡ አክሊላትን አድርገዋል፡፡ መጐናጸፊያዬንም ሰጡኝ፡፡ ይህችውም እነኋት፤ ተመልከታት›› ብላ ሰጠቸው፡፡ ከእርሱ ጋር ለነበሩትም አሳየቻቸው፡፡ አይተውም አደነቁ፤ ስለዚህም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡
ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ጨለማውን ዓለም በማድመቃቸው ‹ብርሃናተ ዓለም› ተብለው ይጠራሉ፡፡ የቅዱሳኑ አገልግሎት፣ ገድላቸው እና ተአምራቸው በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በዜና ሐዋርያት እና በገድለ ሐዋርያት በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡ እኛም በዓለ ዕረፍታቸውን ለማስታወስ ያህል ታሪካቸውን በአጭሩ አቀረብን፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጠብቀን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን እንድንኖር፤ በመጨረሻም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንድንበቃ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ምንጭ፡-
- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሐምሌ ፭ ቀን፤
- ዜና ሐዋርያት፤
- ገድለ ሐዋርያት፡፡