የባሕር ዳር ማእከል ሐዊረ ሕይወት( የሕይወት ጉዞ) ማዘጋጀቱን አስታወቀ

መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

ግዛቸው መንግስቱ ከባሕር ዳር ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማእከል ምእመናን በጾሙ ወቅት መንፈሳዊ በረከትና ዕውቀት እንዲያገኙ በማሰብ መጋቢት 21/2006 ዓ.ም ወደ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ አብችክሊ ጽርሐ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሐዊረ ሕይወት ቁጥር ፪ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ እንደ ማእከሉ ገለጻ የዚህ የሐዊረ ሕይወት መዘጋጀት ዋና ዓለማው ሕዝበ ክርስቲያኑ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እንዲበረታና መንፈሳዊ እድገት እንዲያመጣ ማድረግ ነው፡፡ ዓላማውን ውጤታማ ለማድረግ በዕለቱ ጸሎተ ወንጌል በካህናት ይደረሳል፣ ምክረ አበውና ቡራኬ በሊቃነ ጳጳሳትና ገዳማውያን አባቶች ይሰጣል፣ የተጠየቁ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በሊቃውንቱ ምላሽ ያገኛሉ፣ ትምርህርተ ወንጌል፣ መዝሙር፣ መነባንቦችና ሌሎችም መንሳፈዊ መርሐ ግብራት በተያዘላቸው መርሐ ግብራት ይቀርባሉ፡፡

ጉዞው የሚደረግባት ጥንታዊና ታሪካዊት አብችክሊ ጽርሐ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን የምትገኘው በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ደቡብ አቸፈር ወረዳ ዱርቤቴ ከተማ ሲሆን ለጉዞ የተመረጠችው ቤተ ክርስቲያኗ ጥንታዊና ታሪካዊ በመሆኗ፣የእግር መንገድ ስለሌለው ለጉዞው ተሳታፊዎች ምቹ ስለሆነች፣ ለሐዊረ ሕይወት ጉዞ ማራኪ ቦታ ስለሆነች እንደሆነ አዘጋጅ ኮሚቴው አስታወቋል፡፡

 

ለጉዞው አብይና ንዑስ ኮሚቴዎች አቋቋሞ ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን ያስተወቀው ማዕከሉ በዚህ የሕይወት ጉዞ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ገዳማውያን አባቶች፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ዘማርያንና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

 

የሐዊረ ሕይወት አዘጋጅ ኮሚቴው እንደገለጸው 1500 የጉዞ ትኬቶች ብቻ የተዘጋጁ ስለሆነ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ምእመናን ትኬቶቹ በባሕር ዳር ከተማ ታዬ ሞላ ስቴሽነሪ፣ ከራድዮን ካፌ ቁጥር 1ና 2፣ በማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ ሱቅ፣ ባ/ዳር ማዕከል ጽ/ቤት፣ ከቅድስት ኪዳነ-ምሕረት ሰ/ት/ቤት ንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ ሱቅ እና ከሰላም አድርጊው ማርያም ሰ/ት/ቤት/ንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ ሱቅ፣ በዓታ ለማርያም ሰ/ት/ቤት ሱቅ፣ ከማኅበሩ አባላትና ከግቢ ጉባኤያት ማግኘትና ፈጥነው መግዛት እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

 

የደርሶ መልስ ዋጋ 100 ብር ብቻ ሲሆን ለጉዞው የሚስፈልጉ ልዩ ልዩ ወጪዎችንና ሙሉ መስተንግዶን የሚጨምር ሲሆን ኮሚቴው በጉዞው የሚሳተፉ ምእመናን ተገቢውን ክርስቲያናዊ አለባበስ መልበስና ማስታወሻ መያዣዎን እንዳይዘንጉ፣ ሊጠይቁት የሚፈልጉት ማንኛውም ጥያቄ ካለ ከታች በተገለፁት አድራሻዎች አስቀድመው መጠየቅ እንደሚችሉና በቂ ምላሽ እንደሚያገኙ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

  • በጽሑፍ በፖስታ አድርገው ከራድዮን ካፌ ቁጥር 1 እና 2 እና ከማኅበሩ ጽ/ቤት

  • በኢሜል፡- yemabu@gmail.comtsebank@gmail.com,bt.2005@yahoo.com

  • በስልክ በመልክት ወይም በመደወል 0913778229 /18020509/ 18728098/