gelgale belase 3

በጠረፋማ አካባቢዎች ለተጠመቁ ወገኖች አብያተ ክርስቲያናት ለማነጽ ጥረት እየተደረገ ነው

 ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

gelgale belase 3የማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም በጠረፋማ አካባቢዎች ለተጠመቁ ወገኖች አብያተ ክርስቲያናት ለማነጽ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

በጂንካ፤በግልገል በለስ፤ በቦረና /ተልተሌ/፤ በቦንጋ/ጮራ/ እንዲሁም በሌሎች ጠረፋማ ወረዳዎች ነዋሪዎች ጥምቀት ተከናውኖላቸው የነበረ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን ሳይሠራላቸው ቆይቷል፡፡ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራምም ይህንን ችግር ለመፍታት ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በማጣት ከአገልግሎት ርቀው ወደ ኢ-አማኒነት እንዳይመለሱ ምእመናን እገዛ ማድረግ እንደሚገባቸው የጠቀሰው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያው በቅርቡ ሊሠሩ ለታቀዱ ለ12 አብያተ ክርስሰቲያናት የግንባታ ግብአቶችን፤ በተለይም ቆርቆሮ፤ ምስማር፤ እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶችን ምእመናን እንዲረዱ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጊያ መርሐ ግብር በማኅበሩ ጽ/ቤት አዘጋጅቷል፡፡

 

gelgale belase 1ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኙ 8 አብያተ ክርስቲያናትም የመገልገያ ንዋያተ ቅድሳት ከበሮ፤መጾር መስቀል፤ ጽንሐ፤ ልብሰ ተክህኖ፤ ዣንጥላ፤ መቋሚያ፤ ጸናጽል፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ፤ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ተጠማቂያንን ለሚያገለግሉ ሰባኪያነ ወንጌል ተንቀሳቃሽ ድምጽ ማጉያ፤ ባለሁለት ጎማ ተሸከርካሪ/ሞተር ብስክሌት/፤ አዳዲስ ለተቋቋሙት ሰንበት ትምህርት ቤቶችም አልባሳት፤ ኮምፒዩተሮችና ፎቶ ኮፒ ማሽኖች እንደሚያስፈልጉ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም ክፍል ገልጧል፡፡

 

ገጠርና ጠረፋማ አካባቢ በተለይ በጂንካ፤ በግልገል በለስ፤ በከረዩ በቦንጋ ለመጠመቅ በዝግጅት ላይ ለሚገኙ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ለጥምቀት አገልግሎት የሚውሉ ለተጠማቂዎች ነጠላ፤ የአንገት ማኅተብ ምእመናን ድጋፍ እንዲያደርጉ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም ክፍል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡