አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ /ማቴ. 5፥24/

ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

  • ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ስኬት የአባቶቻችን ስምምነት ወሳኝ ነው

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሥጋ ሕይወት በነበሩበት ባለፉት ዓመታት “ስደተኛ ሲኖዶስ” ተብሎ ከተጠራው በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አባቶች ጋር ዕርቅ ለመፈጸም ጥረት ይደረግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገብ ሳይችል በእንጥልጥል እንዳለ ቅዱስነታቸው ዐረፉ፡፡

 

የእርሳቸው ዕረፍት ቀጣዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ከመመረጣቸው በፊት በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ተለይተው ከሚኖሩ አባቶች ጋር ውይይት ለመጀመር አስገዳጅ ሁኔታ አምጥቷል፡፡ ይህ እንዲታሰብ ግድ የሚያደርገውም ቀጣዩ ፓትርያርክ የሚሰየሙበት መንገድ ሁሉን የማያስማማ ከሆነ የነበረውን ልዩነት የሚያሰፋ ውዝግብ በዚህች ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ስለሚቻል ነው፡፡ ይህንን ከግምት አስገብቶ የወቅቱን አንገብጋቢነት ተረድቶ ወደ ዕርቅ የሚያደርስ ውይይት ማድረግ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን ወሳኝ አገልግሎቶች በብቃትና በስፋት ለመስጠት፣ ጠንካራ መሠረትም ለመገንባት ስለሚያስችል ነው፡፡

 

በመሠረቱ ሲኖዶስ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በጉልህ የተገለጠ ተግባሩ መለያየቶችን መፍታት ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መትከል ነው፡፡ ስለዚህ ሲኖዶስ ሲታሰብ ሰላምና አንድነት ይታሰባሉ፡፡ ትሕትናና ፍቅር ይነግሣሉ፡፡ ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን የሐዋርያዊ አገልግሎት አደራ መንጋውን የመጠበቅ ሓላፊነት ከመወጣት ሌላ ለሚሰበሰበው መንጋ አርአያነት ያለው ሕይወት አባቶቻችን እንዲኖራቸው፣ ብርሃናቸውም በዓለም እንዲያበራ ስለታዘዙም ነው፡፡

 

እነዚህ የክርስትና ዐበይት ተግባራት በአባቶቻችን ደግሞ ጎልተው እንዲገለጹ ይፈለጋል፡፡ አባቶች የክርስቶስን መልክ /እርሱን መምሰልን/ እንደያዙ በሚያስበው የእግዚአብሔር መንጋ፣ እንዲሁም የምድር ጨው ሆነን ሕይወታቸውን ለማጣፈጥ እንድንበቃ አደራ በተሰጡን የምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ በጎ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ብፁዓን አባቶች መልካሙን ጎዳና ሁሉ ሲከተሉ መገኘታቸው ታላቅ ሚና አለው፡፡

 

ከዚህ ጎዳና ወጥተን ፍቅርን በማጣት፣ በጠብ በክርክር ጸንተን ብንገኝ ፍቅር ከሆነ እግዚአብሔር ጋር ለመኖር ባለመፍቀዳችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከእርሱ ጋር እንዳይኖሩ ማሰናከያ በመሆናችንም ጭምር ያዝናል፤ ይፈርዳል፡፡ ስለዚህ ለብፁዐን አባቶች ብቻ ሳይሆን በክርስቲያኖች ሕይወትም በፍቅር ጸንቶ መኖር፣ ከበደልንም በይቅርታና በዕርቅ ሕይወት ውስጥ ማለፍ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ የዚህ ሕይወት መሠረቱ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያደረገው ዕርቅ ነው፡፡ ጠላቶቹ ከሆነው ከእኛ ጋር እግዚአብሔር ታረቀ መባሉ የሕይወታችን መሠረት ፍቅር መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ስለ ዕርቅ ሕይወት በብዙ ምሳሌና በብዙ ኃይለ ቃል ራሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንም በመሆኑ በጉልሕ በሕይወታችን መንጸባረቅ የሚገባው የጽድቅ ሥራ ነው፡፡

 

ለእግዚአብሔር ከምናቀርበው ከየትኛውም ዓይነት መባዕ አገልግሎታችን በፊት ከወንድሞቻችን መታረቅ እንደሚገባ ጌታችን አበክሮ ያስተማረው የሕይወት ቃል ነው፡፡ “አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ” ያለው የጌታ ቃል ይልቁንም በቤተ መቅደሱ ዕለት ዕለት መሥዋዕት ለሚያቀርቡ፣ ብዙዎችን በጸጋ እግዚአብሔር ባዕለ ጸጋ ለሚያደርጉ፣ ምስጢራትንም ሁሉ ለሚፈጽሙ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ምልክት ለሆኑ ከሁለቱም ወገን ላሉ ብፁዐን አባቶች የሚያስተምሩት ብቻ ሳይሆን ዘወትር እንዲኖሩት የሚጠበቅ ክርስቲያናዊ ሕይወት ነው፡፡

 

ይህ በመሆኑም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል “ክርክርና መለያየት አለ” መባሉ ሳይሆን ክርክሩን መፍታት፣ ልዩነትን ወደ አንድነት ስምምነት ማምጣት አለመቻል ከላይ የጠቀስነውን ወሳኝ የሕይወት ቃል የሚፈታተን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራት ባለን አቅምና በጎ ፈቃድ ላይ ጥያቄ የሚያሥነሣ ይሆናል፡፡ በዚህ የማይደሰተው እግዚአብሔርም ብቻ አይደለም፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ ያሉ የክርስቶስ ቤተሰቦችም ናቸው፡፡

 

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ አንድነት የሚያመጣ ዕርቀ ሰላም መፈጸም ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር አንጻር፣ ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ከማሰብ አንጻር፣ መንጋውን ከማነጽና ሐዋርያዊ አገልግሎትን ከማቅናት አንጻር ለአባቶቻችን ግዴታ ይሆንባቸዋል፡፡ የሚፈለገው ዕርቀ ሰላም እውን እንዲሆንም ለእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ለእውነት፣ ለኅሊና ምስክርነት መገዛት አግባብ ይሆናል፡፡

 

ከዚህ በፊትም ማኅበረ ቅዱሳን እንዳስገነዘበው አባቶች ሰላሙን ለማምጣት የሚያስችሉ ቀኖናዊ ጉዳዮችም ላይ ለመወሰን ለማጽናትም መንፈሳዊ ሥልጣንን የተጎናጸፉ በመሆናቸው ዕንቅፋትን ማራቅ ይችላሉ፡፡ የዕርቅ ሒደቱ ሲፈጸምም ሃይማኖታዊ መልክ ያጡ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና ምእመናንን የማያሳምኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመደርደር መታቀበ ከተቻለ በተስፋ የተሞላ ሒደት እንደሚሆን ይታመናል፡፡

 

ከማንምና ከምንም በላይ የቤተ ክርስቲያናችንን ቤተሰብ ማሳመን የማያስችሉ እርምጃዎች ውስጥ መግባት ተአማኒነትን ሊያሳጡ ይችላሉ፡፡ ለዓመታት የዘለቀውን መለያየት /ውዝግብ/ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥም የካህናቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ማኅበራትና በአጠቃላይ የሕዝበ ክርስቲያኑ ሐሳብና አስተያየቶች ከግምት የሚገቡበት አካሔድ ሊኖር ይገባል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ካልተሰማ በቀጣዩ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር አካላት ላይ የሚኖረው አመኔታ ይላላል፡፡ በመሆኑም በዚህ በዕርቁ ሒደት ክርስቲያኖች ያላቸው ሐሳብ ሊመረመር ይገባል፡፡ ስለዚህ ሁሉም የሃይማኖት ቤተሰብ ደስ የሚሰኝበት ምዕራፍ ላይ ለመድረስ መትጋት ከአባቶቻችን ይጠበቃል፡፡

 

ስለዚህም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ለሰላሙ መስፈን አስፈላጊ የሆነ ዋጋ እንዲከፈል ግፊት በማድረግ ሊረባረቡ ይገባል፡፡ ምእመናንም ከካህናት አባቶች ጋር በጸሎት በመትጋት ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እግዚአብሔር እንዲሰጠን መማጸን ይገባናል፡፡ የተጀመሩትን ሒደቶች ሁሉ በእውነተኛነት በሚዛናዊነት እየተከታተሉ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችው ያለፉት ዓመታት ኣሳዘኝ ሁኔታዎች እንዳይቀጥሉ ዛሬ ላይ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባን ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ለዚህም ይሠራል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

  • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 8 ታኅሣሥ 2005 ዓ.ም.

“ወበ እንተዝ ኢየኃፍር እግዚአብሔር ከመ ይትበሃል አምላኮሙ” (ክፍል 2)

ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቀሲስ ይግዛው መኰንን

4.    ሰማያዊውን ሕይወት ናፋቂዎች ስለሆኑ

ክቡር ዳዊት “በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘለዓለምም ያመሰግኑሃል፡፡ አቤቱ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው፡፡” በማለት ሰማያዊውን መናፈቅ እንደሚያስመሰግን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ተናገረ፡፡ መዝ. 83፥4 ቅዱስ ጳውሎስም የሚጠበቅበትን አገልግሎት ካከናወነ በኋላ “ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤” በማለት ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ሕይወት ምን ያህል እንደሚናፈቅ ገልጿል፡፡ ፊል.1፥23 ለዚህ ነው ቅዱሳን በሥጋ የምኞት ፈረስ እንዲጋልቡ፥ በኀጢአት ባሕር እንዲዋኙ፥ በክፉ አሳብ ጀልባ እንዲቀዝፉ የሚፈታተናቸውን ርኩስ መንፈስ በመልካም ሥራቸው በመቃወም ድል የሚያደርጉት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡” በማለት የአሁኑን ችግርና ፈተና ከሚመጣው ጋር በማመዛዘን የተናገረው፡፡ ሮሜ.8፥18

 

ቅዱስ ኤፍሬምም በውዳሴ ማርያም ጸሎቱ “ሰማዕታት በእውነት የዚህን ዓለም ጣዕም ናቁ፤ ስለ እግዚአብሔርም ሲሉ ደማቸውን አፈሰሱ፤ ስለመንግሥተ ሰማያትም ሲሉ መራራ ሞትን ታገሡ፡፡” በማለት የዚህን ዓለም መከራ መታገሥ ሰማያዊውን ክብር በማስታወስና የሚገኘውን ዋጋ በማመን እንደሆነ ገልጿል፡፡ /የሐሙስ ውዳሴ ማርያም/ ለዚህም ነው ሰማእታት እሳቱን ስለቱን፣ ጻድቃን ግርማ ሌሊቱን፥ ጽምፀ አራዊቱን፣ ጸብአ አጋንንቱን ታግሰው ሥጋቸውን ለነፍሳቸው አስገዝተው የኖሩበት ዐቢይ ምሥጢር፡፡ ሰማዕታት የሚታሰሩበትን ገመድ፣ የሚሰቀሉበትን ግንድ ይዘው ወደ ሞት ሲነዱ ጻድቃንም አስኬማቸውን ደፍተው፣ ደበሎአቸውን ለብሰው፣ ከምግበ ሥጋ ተለይተው ርሃቡን ጥሙን ችለው ሲኖሩ ደስ ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከፈጣሪያቸው እንደሚያገኙ ያውቃሉና ነው፡፡ መሬት ፊቷን ወደ ፀሐይ ስታዞር ብርሃን እንደምታገኝ፣ ፊቷን ስትመልስ ደግሞ ጨለማ እንደሚሆን ሳይንሱ ይነግረናል፡፡ የሰው ልጅም ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ካዞረ ብርሃን ይሆንለታል፤ ፊቱን ከፈጣሪው ካዞረ ግን ይጨልምበታል፡፡ ኑሮው፣ ትዳሩ፣ መንገዱ ሁሉ የተሳካ እንዲሆን፣ የውስጥ ሰላምን እንዲያገኝ፣ በሚያገኘው ተደስቶ እንዲኖር፣ ሰላም፣ ጤና በረከት ከቤቱ እንዳይርቁ፣ አሸሼ ገዳሜ በሉ፣ አይዟአችሁ ጨፍሩ የሚለውን የጥንት ጠላት የአጋንንት ስብከት በመልካም ሥራ በዝማሬ በማኅሌት በሰዓታት በቅዳሴ፣ በኪዳን ተጠምዶ መቃወም ያስፈልጋል፡፡ መቼም የሰይጣን የዘወትር ስብከት “ሥጋችሁ በነፍሳችሁ ላይ ትንገሥ” የሚል ስለሆነ እኛ ግን ነፍሳችንን በሥጋችን ላይ ልናነግሣት እንደ አባቶቻችን ቅዱስን ሰማያዊውን ናፋቂዎች ልንሆን ያስፈልጋል፡፡ “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፣ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡” እንዲል፡፡ 2ቆሮ.5፥1

 

5.    ለሌላው አሳቢዎች በመሆናቸው

ለሌላው ማሰብ፥ ለሌላው መጨነቅ፥ ከሚደሰቱ ጋር መደሰት፥ ከሚያዝኑ ጋር ማዘን፥ ችግር የወደቀባቸውን ሰዎች የችግራቸው ተካፋይ መሆን ፈጣሪን መምሰል ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር፣ አንድም ልብ፣ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፡፡ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡” በማለት ከራስ ይልቅ ለሌላው ማሰብን እንድናስቀድም ያስተምረናል፡፡ ፊልጰ.2፥1 ታላቁ ሊቅም በሰቆቃወ ድንግል ላይ “ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን፡፡ ኢየሱስ ግፉዕ ምስካዮሙ ለግፉዓን፡፡ እግዚአብሔር ማኅደር ዘአልቦ ከመ ነዳያን..” በማለት የጌታችን መሰደድ የተሰደደውን የሰውን ልጅ ለመመለስ እንደሆነ፤ ጌታችን ያለ በደሉ የተገፋው የተገፋ የሰውን ልጅ ሊያድን እንደሆነ፤ እግዚአብሔር ተስፋ፣ ላጡ ተስፋ ማረፊያ ቤት ለሌላቸው ማረፊያ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይህንን ስለሚያውቁ ቅዱሳን ከራሳቸው በላይ ለሌላው ያስባሉ፡፡ “ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ አለ፡፡” የሚለውን የታላቁን ሰው የሙሴን ልመና ስንመለከት ምን ያህል ለሌላው ማሰብ እንደሚገባ እንማራለን ዘፀ.32፥32 ዛሬ ቢሆን ምናልባት ሌላውን ደምስሰህ እኔን ጻፍ ሳይባል ይቀራል ትላላችሁ፡፡ ቅዱሳን ግን እንደፈጣሪያቸው ለሌላው አሳቢወች በመሆናቸው “እግዚአብሔር አያፍርባቸውም” ተባለ፡፡

 

ዛሬም ሰው ለድሃ እጁን ሲዘረጋ እግዚአብሔር ደግሞ የምሕረት እጁን ይዘረጋለታል፡፡ የወደቀ ባልንጀራውን ሲያነሣ እግዚአብሔር እርሱን ከወደቀበት ያነሣዋል፡፡ የተጨነቀውን ሲያጽናና፥ የተጨቆነውን ነጻ ሲያወጣ ተስፋ ለቆረጠው ሲደርስለት በእውነት ዋጋው አይጠፋበትም፡፡ ለዚህ ነው ክቡር ዳዊት “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ ሕያውም ያደርገዋል፡፡” በማለት ያስተማረን፡፡ መዝ. 40፥1 ስለዚህ በዘመናችን ያለውን የወገንተኝነት፥ የትዕቢትና የሥጋዊነትን አስተሳሰብና አመለካከት በወንጌል መሣሪያነት አፈራርሶና ንዶ ለራስ ነጻ በመውጣት ለሌላውም መትረፍ ያስፈልጋል፡፡ ከነዚህ ክፉ ተግባራት ካልተለየን ገና ዛሬም በጨለማ ውስጥ ስላለን እንጠንቀቅ፡፡

 

“ልጄ ድሃውን ምጽዋቱን አትከልክለው ከሚለምንህ ከድሃውም ዓይኖችህን አትመልስ፡፡ የተራበች ሰውነትን አታሳዝን ያዘነ ሰውንም አታበሳጭ፡፡ ያዘነ ልቡናን አታስደንግጥ፣ የሚለምንህን ሰው አልፈኸው አትሂድ፡፡ የሚገዛልህ ቤተ ሰብህን አትቆጣ፤ ከድሃም ፊትህን አትመልስ፡፡” ካለ በኋላ ቀጥሎ “ከሚለምንህ ሰው ፊትህን አትመልስ፤ በልቡናው አዝኖ ቢረግምህ ፈጣሪው ልመናውን ይሰማዋልና፡፡” በማለት ምስካየ ኅዙናን፣ ረዳኤ ምንዱባን የሆነ እግዚአብሔር የድሃውን ኀዘን ሰምቶ እንደሚበቀል ይነግረናል፡፡ ሲራ.4፥2 ስለዚህ የነዚህ ቅዱሳን ልጆች የሆን እኛ ፍትሕ ተጓድሎባቸው የሚሰማቸው አጥተው የሚገባቸውን፣ ተነፍገው፣ መከበር ሲገባቸው ተዋርደው ከሰው በታች ሆነው ለሚቆዝሙ ወገኖች ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባል፡፡ “ሳትሞት ለባልንጀራህ በጎ ነገርን አድርግ፡፡” ተብለን ተመክረናልና፡፡ ሲራ.14፥13

 

6.    ለመከራ ራሳቸውን ያዘጋጁ በመሆናቸው

ከላይ እንዳየነው እምነታቸው በማዕበል ቢመታ የማይፈርስ እውነተኛ እምነት ስለሆነ ለመከራ አይበገሩም፡፡ ከእሳቱ ከሰይፉ ከመከራው በስተጀርባ የሚወርድላቸው አክሊለ ሕይወት ስለሚታያቸው ወደሞት ሲነዱ ደስ እያላቸው ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸውን ለሞት ራሳቸውን ለስቅላት፣ ራሳቸውን ለእንግልት አዘጋጅተው በሃይማኖት ስለሚኖሩ፣ ፈጣሪ ያዝንላቸዋል፡፡ ደስ ይሰኝባቸዋልም፡፡ ያለ መከራ ዋጋ እንደማይገኝም ስለሚያውቁ “አቤቱ ቅጣኝ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቁጣ አይሁን፡፡” እያሉ ድሎትን ሳይሆን መከራ ሥጋን ይለምናሉ፡፡ ኤር.1፥24 ሥጋ ሲጎሰም ለነፍስ እንደሚገዛ ይረዳሉ፡፡ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሃብ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፣ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጥረን” ተብሎ እንደተጻፈ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን በወደድን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ ግዛትም ፍጥረትም ቢሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፡፡” የሚለው የቅዱስ ጳውሎስም ትምህርት የሚያስተምረው ራስን ለመከራ ማዘጋጀትን ነው፡፡ ሮሜ.8፥35

 

ገበሬ ብርዱን፣ ዝናቡን፣ ፀሐዩን ታግሦ እሾሁን ነቅሎ መሬቱን አለምልሞ ተክል የሚተክለውና ከበቀለም በኋላ የሚኮተኩተው የሚያርመው ፍግ እያስታቀፈ የሚንከባከበው ውኃ እያጠጣ፣ ፀረ ተባይ መድኀኒት እየረጨ ከተባይ የሚጠብቀው፣ ቅጥር ምሶለት፣ አጥር አጥሮለት ከእንስሳት የሚያስጠብቀው በአጠቃላይ ብዙ የሚደክምለት መልካም ፍሬን  ለማግኘት ነው፡፡ እንዲህ ከለፋ በኋላ አመርቂ ውጤት ቢያገኝ በልፋቱ ይደሰታል፡፡ በሚቀጥለውም ከመጀመሪያው የበለጠ እንክብካቤ ያደርግለታል፡፡ ካልሆነ ግን ያዝናል፡፡ ተክሉ ፍሬ አልባ ቢሆን ወይም ደግሞ ጣፋጭ ፍሬን እየጠበቀ መራራ ፍሬን ቢያፈራ ከማዘንም አልፎ እንዲቆረጥ ያደርገዋል፡፡ ዮሐ.15፥5፣ ማቴ.21፥18

 

ሰውም የእግዚአብሔር ተክል ነው፡፡ በቃለ እግዚአብሔር በምክረ ካህን ተኮትኩቶ በረድኤተ እግዚአብሔር አጥርነት ተጠብቆ የሚኖር የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ስለሚያውቁ ቅዱሳን መልካም ፍሬን አፍርተው በመገኘታቸው እግዚአብሔር ተደስቶባቸዋል፡፡

 

ፍሬአቸው መራራ የሆኑ ተክሎች /ሰዎች/ ጨለማን ተገን አድርገው ሰው አየን አላየን ብለው ኀጢአትን የሚፈጽሙትን ያህል በእግዚአብሔር ቤት የተተከሉ፣ ፍሬአቸው ያማረ ቅዱሳን ጨለማው ሳይከለክላቸው ጽድቅን ሲሠሩበት ያድራሉ፡፡ በዓለም ላይ ለ5 ሲሕ 5 መቶ ዘመናት ኀጢአት በዓለም ላይ ነግሦ ይኑርም እንጂ በዚህ ኀጢአት በነገሠበት ዘመን ጽድቅን ሲሠሩ የኖሩ አባቶችና እናቶች ነበሩ፡፡ ዛሬም ኀጢአት በዓለማችን ላይ ጠፍንጎ ይዞ እያስጨነቀን እንዳለ ብንረዳም የነዚህ የቅዱሳን አበው በረከት ያደረባቸው በየገዳማቱ ወድቀው ለጽድቅ ራሳቸውን ሲያስገዙ እንመለከታለን፡፡

 

ማጠቃለያ

አንድን መንፈሳዊ ሥራ መጀመር ብቻውን የጽድቅ ምልክት አይደለም፡፡ ከላይ ያየናቸው የቅዱሳን ሕይወት ጽድቃቸው ከሰውም አልፎ በእግዚአብሔር የተመሰከረላቸው ከመጀመሪያው ይልቅ መጨረሻቸው በማማሩ ነው፡፡ ጀምረው ያቋረጡማ የሚነገርላቸው ማቋረጣቸው እንጂ ጽድቃቸው አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ሳጥናኤል የመላእክት አለቃ ነበር፡፡ አርዮስ ካህን፣ ይሁዳ ከሐዋርያቱ ጋር ተቆጥሮ የነበረ፣ ዴማስ ከአርድዕተ ክርስቶስ ከነ ሉቃስ ጋር ተደምሮ የነበረ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች የጀመሩትን መንፈሳዊ አገልግሎት ችላ ማለታቸው ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከክብር ወደ ውርደት፣ ከሹመት ወደ ሽረት፣ ከማግኘት ወደ ማጣት ተወረወሩ እንጂ ምን ጠቀማቸው? በትናንት ማንነት ብቻ ድኅነት አይገኝም፡፡ ዛሬ የማያሳፍር ሥራን መሥራት እንጂ፡፡

 

ትናንት ዘመነኞች፣ ቅንጦተኞች፣ ኩሩዎች፣ የነበሩ ነገሥታት ወመኳንንት ዛሬ የት አሉ? በሀብታቸው የሚኩራሩ፣ በሥልጣናቸው የሚንጠራሩ፣ ፊታቸውን ከፈጣሪ ያዞሩ ሁሉ ጊዜ አልፎባቸው ገንዘባቸው፣ ሥልጣናቸው፣ ወገናቸው አላድናቸው ብሎ በጸጸት አለንጋ ከመገረፍ ውጪ ምንም አላገኙም፡፡ ስለዚህ ከዚህ መማር የዘመኑ ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ በሃይማኖት ቁመው ከተጠቀሙት በሃይማኖት የመቆምን ጥቅም፣ ወድቀው ከተጎዱት የመውደቅን አስከፊነትና ጉዳት መማር እንችላለን፡፡ ስለዚህ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምር፡፡ በየመሥሪያ ቤታችን የምንሠራው ሥራ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነው ወይስ የሚያሳዝን፣ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ በተለይ በሐዲስ ኪዳን “ከአሁን በኋላ ባሮች አልላችሁም፣ ልጆች ብያችኋለሁ፡፡” በማለት ያቀረበውን ፍጹምም የወደደውን የሰው ልጅ እንዴት እያየነው ነው? እውነት የምንሠራው ሥራ አሳፋሪ ነው ወይስ የሚያስደስትና የሚያስከብር? የሚለውን ጠይቀን ለራሳችን ምላሽ ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ ያለ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ መልካምን ማድረግም አይቻልምና ለመልካም ሥራ እንዲያነሣሣን ኃይሉን ብርታቱንም እንዲሰጠን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

yaba gy. 7

ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት የገዳማት ድርሻለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት የገዳማት ድርሻ

ታኅሣሥ 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ሪፓርታዥ

yaba gy. 7የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማሳካት የገማት ድርሻ በሚል መሪ ቃል ማኅበረ ቅዱሳን ባዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ ለመገኘት ከ65 ገዳማት የመጡ አበምኔቶችና እመምኔቶች ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠዋት በማኅበሩ ሕንጻ  ላይ ስለ ማኅበሩ ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል በተዘጋጀው መርሐ ግብር ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

 

ከስዓት በኋላ  በዐውደ ጥናቱ ላይ ለመገኘት በተዘጋጀላቸው መኪና ከማኅበሩ ዋና ጽሕፈት ቤት ወደ ኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል አዳራሽ ያመሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል እንደደረሱ በማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን በዝማሬ በመታጀብ ወደ አዳራሹ ገብተዋል፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የተገኙ ምእመናን በእልልታና ዝማሬ አቀባበል በማድረግ ገዳማውያን አባቶችም እጅ እየነሱና ምእመናን እየባረኩ ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ በማምራት ቦታቸውን ያዙ፡፡

 

yaba gy 1የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን  እንደተገኙም ዐውደ ጥናቱ ተከፍቷል፡፡

 

የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታቸውን ለማስተላለፍ መድረኩን የተረከቡ ሲሆን በመልእክታቸውም ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ጥንታዊ ገዳማት ላይ እየደረሰ ያለውን ልዩ ልዩ ችግሮች ለመታደግና የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ያሉባቸውን ሁኔታ ለማጥናትና አግባብ ያለው መፈትሔ ለመስጠት መርሐ ግብር ነድፎ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

 

እስካሁን ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች የተተገበሩና በመተግበር ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ስብሰቢው በ145 አብነት ትምህርት ቤቶች ለ136 መምህንና ለ988 የአብነት ተማሪዎች ቋሚ ወርኀዊ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ለገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች ጥሪ የተደረገበትንም ምክንያት ሲገልጹ “ገዳማት ራሳቸውን እንዲችሉ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል፤ ገዳማት ከገዳማት ጋር ያላቸውን ትሥሥር ለማጠናከርና ወሳኝ አቅጣጫዎችን ለማስያዝ ከገዳማት አባቶች ጋር መመካከርና መወያያት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማኅበሩ ጥሪ አድርጓል” ብለዋል፡፡

 

ገዳማውያን አባቶችም ጥሪውን ተቀብለው አስቸጋሪውን ጉዞ ሁሉ ተቋቁመው በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

በቀጣይነት የቀረበው በቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዮም ለሁለንታናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት የገዳማት ድርሻ በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ በመመርኮዝ “የገዳማት መጠናከር ለቤተ ክርስቲያን እድገት ያለው ሚና ምንድን ነው?” በሚል ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡ በጥናታቸውም ከዳሰሷቸው መካከል

 

  • ገዳማት የቤተ ክርስቲያናችን ሥውር ጓዳዎችና የምስጢር መዝገቦች ናቸው፡፡

  • ገዳማት የመማጸኛ ከተሞች ናቸው፡፡

  • ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የተገኙባቸው ምንጮች ናቸው

  • የተግባራዊ ክርስትና ሞዴሎች ናቸው

  • ገዳማውያን ለእግዚአብሔር የሚቀርቡ አሥራት በኩራት ናቸው፡፡

  • ገዳማት የብዝሃ ሕይወት መገኛና መጠበቂያ ናቸው፡፡

  • ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሠረት ናቸው

  • የማኅበራዊ ደኅንነት አገልግሎት መሥጫ ሥፍራዎች ናቸው፡፡

 

በማለት ሰፊ ትንታኔ በመስጠት ገዳማት ለቤተ ክርስቲያን እድገት አስፈላጊ መሆናቸውውን አብራርተዋል፡፡

 

በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ በኢትዮጽያ ገዳማት ላይ ያደረጉትን ጥናት አቅርበዋል፡፡ በጥናታቸውም ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ገዳማት ያላቸው ሚናና እነዚህንም የሥልጣኔ ምንጮቻችንን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ትኩረት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ ጥንታዊ ገዳማት ውስጥ ከ1500 በላይ ዘመናት ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍት መኖራቸውና በምሳሌነትም በአባ ገሪማ ገዳም የሚገኘውን የብራና ወንጌልን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ሥዕላትና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ ቤተ ክርስቲያናትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ሳይፈርሱ በቅርስነት መያዝ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

 

yaba gy. 739በጥናታቸው ማጠቃለያም “እነዚህ ቅርሶች የእኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ የሁላችንም የኢትዮጵያውን /ሃይማኖታችን ምንም ቢሆን/፤  የመላው ጥቁር ሕዝቦች እንዲሁም  የሰው ልጆችና የዓለማችን ቅርሶች ናቸው፡፡ ጥቁር ሕዝቦች እጅግ የረዘመ የሥእልና የኪነ ጥበብ ቅርስ የላቸውም የሥእልና የኪነ ጥበብ ቅርስ ያለው ሕዝብ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እነዚህን ቅርሶች ያቆየችልን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት” ብለዋል፡፡

 

ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማት ውስጥ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል ለምሳሌነት የቀረቡ ገዳማትን በመጥቀስ የባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ የአቃቂ ደብረ ገነት አባ ሳሙኤል ቤተ ደናግል ገዳም፣ የምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አበምኔቶችና እመምኔት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ያከናወኑትን ሥራ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሚገኙትን ገዳማት በመከታተል ከፍተኛ አገልግሎት እያበረከተች የምትገኘው ጸጋ ኪሮስ ግርማይ ሪፖርት አቅርባለች፡፡

 

የባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም መጋቢ አባ ክንፈ ገብርኤል “ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ገዳማችን በመምጣትና ችግራችንን በማየት ባጠናው ጥናት መሠረት የከብት እርባታ ለመጀመር የሚያስችለን ፕሮጀክት በመንደፍ 2 የወተት ላሞችን ሰጥቶን ሥራችንን ጀመርን፡፡ ዛሬ 24 ደርሰውልናል፡፡ 27 ደግሞ ሸጠን ተጠቅመናል፡፡ 18 ሞተውብናል፡፡ ተጨማሪ ሥራዎችንም በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ ውጤታማም ሆነናል” ብለዋል፡፡

 

ከአቃቂ ደብረ ገነት አባ ሳሙኤል ቤተ ደናግል የገዳሙ እመ ምኔት እማሆይ መብዐ ጽዮን ማኅበሩ ስላደረገላቸው ድጋፍ ሲገልጹ “አንድ የልብስ ስፌት መኪና፤4 ጣቃ ጨርቅ እንዲሁም 2 ላሞችን ሰጥቶን ሥራችንን የጀመርን ሲሆን ዛሬ 10 የወተት ላሞች አድርሰናል” ብለዋል፡፡ በተጓዳኝም 10 ሕጻናትንም እያሳደጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

 

yaba gy 6የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ከገዳማት ጋር ባደረገው የተቀራረበ ሥራ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ አፈጻጸም ላሳዩ ገዳማት የዋንጫ ሽልማት  ማበርከቱ አንዱ የመርሐ ግብሩ አካል ነበር፡፡ ለሽልማት የበቁትም የባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ የአቃቂ ደብረ ገነት አባ ሳሙኤል ቤተ ደናግል ገዳምና የደቡብ ጎንደር ገዳመ ኢየሱስ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

 

በዐውደ ጥናቱ ላይ ከቀረቡት መርሐ ግብሮች መካከል የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እና የአባ በጸሎተ ሚካኤል ገድል ምረቃ ሲሆን ከምረቃው በፊት በገድሉ ዙሪያ አጭር ትንታኔ በማኅበረ ቅዱሳን የኤሌክትሮኒክስና ሚዲያ የቴሌቪዥን ክፍል አስተባባሪ በዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ ተሰጥቷል፡፡

 

የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገድል ለመተርጎም ከሦስት ዓመታት በላይ መውሰዱንና  ገድሉን ሦስት ተርጓሚያን እንደተሳተፉበት፤ በ350፣000 ብር ለመታታመም እንደበቃ  ተጠቅሷል፡፡በመጽሐፉ የሚገኘው ገቢም ሙሉ ለሙሉ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ሁለገብ ሕንፃ ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል፡፡

 

በተጨማሪም ለገዳሙ ሁለገብ ሕንፃ ማሠሪያ ደራሲት ፀሐይ መላኩ “የንስሐ ሸንጎ” የተሰኘውን መጽሐፋቸው አበርክተዋል፡፡

 

yaba gy 5ሁለቱንም መጻሕፍት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበር በመመረቅና በመባረክ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለማርያም ተረክበዋል፡፡ ደራሲት ጸሐይ መላኩ “እመምኔት” የተሰኘው መጽሐፋቸው ለማኅበሩ ሕንፃ ግንባታ እንዲውል ከዚህ ቀደም ማበርከታቸው ይታወሳል፡፡

 

በዐውደ ጥናቱ ላይ ከተገኙት ተጋባዥ እንግዶች መካከል የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለ አደራ ከንቲባ የነበሩት አቶ ብርሃነ ደሬሳ ሲሆኑ በዚህ መርሐ ግብር ላይ በመገኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

“ማኅበረ ቅዱሳን የሚመሰገንና ብዙ ቁም ነገር እየሠራ ያለ ማኅበረ ነው፡፡ አንድ ምክር ልለግሳችሁ፡፡ “ለነፍሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለሰላምም መሥራት አለባችሁ፡፡ ሰላም ስትኖር ትረሳለች ሳትኖር ግን ታንገበግባለች፡፡ ማኅበሩ ለዚህ መቆም አለበት፡፡” ብለዋል፡፡

 

ገዳማትን አስመልክቶም ቅዱስ መጽሐፍ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ይላል፡፡ የተዘረጉ የኢትዮጵያውያን እጆች የታጠፈበት ጊዜ ነበር እርሱም ደርግ እግዚአብሔር የለም ብሎ ቤተ ክርስቲያን ለመዝጋት በተነሣበት በ17ቱ ዓመት የቤተ ክርስቲያን የመከራ ወራት /ዘመን/ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜም ቢሆን ያልታጠፉ ወደ እግዚአብሔር የተዘረጉ እጆች ነበሩ፡፡ እነዚህ እጆች የመነኮሳትና የመነኮሳይያት እጆች ናቸው፤ ለዚህ ያበቃን የገዳማውያኑ ጸሎት ነው፡፡ ስለዚህ መረዳት አለባቸው” ብለዋል፡፡ ለዚህም አገልግሎት ይረዳ ዘንድ 20 ሺህ ብር ለመሥጠት ቃል ገብተዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት ከተገኙት መካከል በኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ፔፕሲ ኮላ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ደርቤ ሥነ ጊዮርጊስ ማኅበሩ ለገዳማት ለሚያከናውነው አገልግሎት 10 ሺህ ብር ለመሥጠት ቃል የገቡ ሲሆን “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አጥታ አይደለም እንደዚህ የሚያስተባብርላት፣ ፕሮጀክት ቀርጾ አቅርቦ የሚፈጽም አካል ብቻ ነበር የጠፋው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ማኅበረ ቅዱሳንን አስነሥቷል፡፡ የሚሠራውን ሥራ በተግባር ያየሁት በመሆኑ አብሬ እየሠራሁ ድጋፌን እቀጥላለሁ” ብለዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይም በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳን በመስጠት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በሰጡት ቃለ ምዕዳንም “አባቶቻችን የገደሟቸውን ገዳማት ለእግረኞችም ሆነ ለፈረሰኞች አይመቹም፡፡ ከዛሬ 4ዐ ዓመት በፊት ከዋልድባ ተነሥተን የኢትዮጵያ ገዳማትን ሁኔታ ለማየት ተንቀሳቅሰን ነበር፡፡ ነገር ግን አልቻልንም፡፡ ዛሬ ባለቤት ያገኘ ይመስላል፡፡ ልጆቻችን እየወጡ እየወረዱ የተዘጉትን ገዳማት በማስከፈት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን ልጆቻችን ስለሰጠን እናመሰግነዋለን፡፡ ….የጉርምስና ጊዜ ለመንፈሳዊ ሥራ አይመችም፡፡ ይህንን ለመሥራት ከእግዚአብሔር መመረጥ፤ መታደል ያስፈልጋል፡፡ ልጆቻችን ከኑሮ ጋር እየታገሉ ጊዜያቸውን ለማኅበራችን እንስጥ በማለት ለቤተ ክርስቲያን መሥዋእት እየሆኑ ነው፡፡ እኔም ከማኅበሩ ጎን በመቆም እታዘዛለሁ፡፡ ብለዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል የአማካሪ ቦርድ ሰብሪሳቢ በሰጡት ቃለ ምእዳንም “ማኅበሩ ከገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን አንሥቶ የቤተ ክርስቲያናችን አእምሮና ልቡና እስከ ሆነው ገዳም ድረስ በመዝለቅ ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ገዳማት የምስጢር፣ የዜማ፤ የመጻሕፍት፤ የሊቃውንት፣ የካህናት መገኛ ናቸው፡፡ ልጆቻችን የሚሠሩት ሥራ እስከዚያ ዘልቋል፡፡ እግዚአብሔር ያስተማረው ሰው የእግዚብሔርን ሥራ ይሠራል፡፡ የእግዚአብሔርን ንብረት ይጠብቃል፡፡ ልጆቻችን ከእግዚአብሔር የተማሩት እየሠሩበት ነው፡፡ ከጎናቸው እንቁም፡፡ እኛም ከማኅበሩ ጎን ቆመን እንሠራለን፣ እንላላካለን፣ እንልካለንም፡፡” ብለዋል፡፡

 

በመጨረሻም አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበርና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለምዕዳንና ቡራኬ “ያሰባችሁት ሁሉ መልካም ነገር ነውና ያሰባችሁትን ሁሉ እንድትሠሩ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡ ማኅበሩን ያስፋልን ማኅበሩን ከስም አወጣጥ ጀምሮ እኛ የሰጠነው በመሆኑ አብረን እንሠራለን ብለዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የገዳማት አበምኔቶችና እመምኔተች ካህናት የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

aa center support 2005

አባቶቻችንን አንተው

aa center support 2005

menekosate 4 2

ከታላላቅ ገዳማት ለመጡ አባቶች አቀባበል ተደረገ

ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

menekosate 4 2

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን ታላላቅ ገዳማት ለመጡ አበምኔቶችና እመምኔቶች አቀባበል ተደረገ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማሳካት የገዳማት ድርሻ በሚል በተዘጋጀው ዐውደ ጥናትና ለአምስት ቀናት በሚቆየው ሥልጠና፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ላይ ታላቅ አሻራቸውን ትተው ያለፉትን የታላቁ አባት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የገድል መጽሐፍ ምረቃ ላይ ለመገኘት ከሃምሳ በላይ ለሚደርሱ ገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች በተደረገው ጥሪ መሠረት ከማክሰኞ ጀምሮ ርቀቱ ሳይገድባቸው አዲስ አበባ በመግባት ላይ ሰንብተዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም  ዝግጅቱን አጠናቆ በጉጉት ከመጠባበቅ አልፎ በአክብሮት እየተቀበላቸው ይገኛል፡፡

 

ዓርብ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አገልጋዮች በማኅበሩ ሕንፃ 6ኛ ፎቅ ላይ ለአባቶች ማረፊያ ቦታ ለማዘጋጀት በመሯሯጥ ላይ ነው የዋሉት፡፡ ፍራሽ፤ አንሶላ፤ ምንጣፍ፤ ብርድ ልብስ አሰገብተው እያነጠፉ አባቶችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በመቀበል ላይ ናቸው፡፡

 

ማኅበሩ ይህንን ሓላፊነት ለመወጣት አባቶችን በመቀበልና በማስተናገድ አሰተዋጽኦ እንዲያደርጉ ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ለሚገኙ መንፈሳዊ ማኅበራትና በጎ አድራጊ ምእመናን ጥሪ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ለአገልግሎቱ ከጧት ጀምሮ የደጆችሽ አይዘጉ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር አባላት ለአባቶች የሚሆነውን ምግብ በማዘጋጀት ላይ ተጠምደዋል፡፡  አመሻሽ ላይ የማኅበሩ ዋናው ማእከል ግቢ ከ55 በላይ በሚደርሱ ገዳማት በመጡ አበምኔቶችና እመምኔቶች ደምቋል፡፡ ሁሉም የታቀደውን በጎ ዓላማ ለማሳካት በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ አባቶች ልጆቻቸውን ለመባረክ ደከመኝ ሰለቸን አላሉም፡፡ ልጆችም በረከት ለመቀበል አባቶች እግር ሥር ከመውደቅ አልሰነፉም፡፡ ፍጹም ክርስቲያናዊ መገለጫ የሆነውን ትሕትና በአባቶችም ሆነ በልጆች ዘንድ ይነበባል፡፡ በአባቶችና በመንፈስ ልጆቻቸው መካከል የሚታየው ቁርኝት ላስተዋለው ያስገርማል፡፡ በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ክርስትና ያስተሳሰረው አንድነት፡፡

 

ምሽት 12 ሰዓት ሲሆን ደጆችሽ አይዘጉ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር አባላት 6ኛው ፎቅ ኮሪደር መግቢያ ላይ ውሃ በባልዲና በጀሪካን ሞልተው ለበረከት ያለ እያገዛቸው 6ቱን ፎቅ ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ የአባቶችን እግር ለማጠብ ሁሉም በመሽቀዳደም ላይ ቢሆንም ሁሉም ከበረከቱ ይሳተፍ ዘንድ በየተራ ለማጠብ አንድ ሰው የአንደ አባት እግር እንዲያጥብ መመሪያ ተሠጠ፡፡ ሰባት የሚደርሱ ሳፋዎች ከነውሃቸው ተቀምጠው አባቶችን ይጠባበቃሉ፡፡ አባላቱ የአባቶችን እግር ለማጠብ ተሰልፈዋል፡፡ አባቶች ከማረፊያቸው እየወጡ ልጆቻቸውን እየባረኩ በትሕትናና ፍቅር በታጀበ መስተንግዶ በልጆቻቸው እግራቸውን ታጠቡ፡፡

 

በቀጣይነት የተካሄደው ለአባቶች ማእድ ማቅረብ ሲሆን የዕለቱን ሙሉ ወጪውንና መስተንግዶውን የቻለው ደጆችሽ አይዘጉ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር ነው፡፡ አባላቱም ለአባቶች ያዘጋጁትን ማእድ በማቅረብ ሳይሰቀቁ እንዲመገቡ በመጋበዝ ምን ይጨመር? እያሉ ይጠይቃሉ፤ ወጥ ያወጣሉ እንጀራ ይጨምራሉ፡፡ አባቶች ትሕትናን እንደተላበሱ ለኛ ይህ አይገባም የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ደስታ ግን ይነበብባቸዋል፡፡

 

menekosate 2 2ማእዱን እንደተመገቡ  የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ለማስተላለፍ ቅድሚያውን ወሰዱ፡፡ “የቤተ ክርስቲያን መሠረቷ ገዳማት ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጠነከረች የሚባለውም የገዳማት ጥንካሬ የሚያመጣው ነውና በዚህ ሁኔታ ላይ እንድንወያይ፤ ነገ ምን ማድረግ እንደሚገባን እንድንነጋገር፤ እኛም የምናስበውን ለማሳየት እንድንችል እንድትመክሩን፤ እንድተጸልዩልን ነው የተሰባሰብነው፡፡ እናንተን ለማየት በመታደላችን እጅግ ደስተኞች ነን፡፡ ቀሪውን ጊዜም መልካም ነገር የምናቅድበትና የምንፈጽምበት እንዲሆን እንመኛለን” ያሉ ሲሆን ደጆችሽ አይዘጉ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር ላከናወነው አርአያነት ያለው ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

የደጆችሽ አይዘጉ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር ተወካይ አቶ ሙሉጌታ በመርሐ ግብሩ ላይ የተሰማቸውን እንዲገልጹ እድሉ የተሰጣቸው ሲሆን “እግዚአብሔር ዛሬ ታላቅ ነገር አድርጎልናል፡፡ በረከት ለማግኘት ከከተማ ወደ ገጠር ነበር የምንወጣው፡፡ እግዚአብሔር የማይታሰብ ነገር አደረገልን፡፡ ሰው እንጨት ሊቆርጥ ወደ ተራራ ይወጣል እንጂ ተራራው ከነ እንጨቱ ወደ ሰው አይመጣም፡፡ እግዚአብሔር የሚሳነው ነገር ስለሌለ ዛሬ አባቶቻችንን ከነበረከታቸው ወደ እኛ አመጣቸው፡፡ አባቶቻችን እናንተ ባትኖሩ እኛም አንኖርም፡፡ እግዚአብሔር እናንተን ስለሰጠን ደስተኞች ነን” ብለዋል፡፡

 

በመጨረሻም አባቶች ከገዳም ወጥተው አዲስ አካባቢ ላይ የሚገኙ  በመሆናቸው ምግቡም ሆነ ውኃው በመለወጡ ምክንያት ሥጋዊ ሕመምmenekosate 2 1 ቢሰማቸው የማኅበሩ አባላት የሆኑ የሕክምና ዶክተሮችና ነርሶች 24 ሰዓት እነሱን ለማገልገል መመደባቸው ተገለጸላቸው፡፡ እንዲሁም ማንኛውንም አገልግሎት ቢፈልጉ እነሱን ለማገልገል የተመደቡ ወንድሞችና እኅቶች ስለሚገኙ የሚሹትን ነገር ሳይሰቀቁ እንዲጠይቁ በማሳሰብ የምሽቱ መርሐ ግብር በአባቶች ቡራኬ ተጠናቋል፡፡

 

ይቆየን……….

ገዳሞቻችንን ለሁሉ ዓቀፍ ልማት አናዘጋጃቸው፡፡

ታኅሣሥ 5 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበርካታ ገዳማት ባለቤት ነች፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር ከ5ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ እየተስፋፉና እያደጉ የመጡት እነዚሁ ገዳማት የምናኔና የጸሎት እንዲሁም ድኀነተ ሥጋ ወነፍስ የሚገኝባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ከመስጠት ጎን ለጎን የሊቃውንት መፍለቂያና የበርካታ ቅዱሳን ምንጭ በመሆንም ሲያገለግሉ እንደኖሩ ይታወቃል፡፡ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አዎንታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠራቸውም በላይ የሀገሪቱ የትምህርትና የሥልጣኔ ማእከላት በመሆን አገልግለዋል፡፡

 

የብዝኀ ሕይወት መገኛና መጠበቂያ ማእከላት መሆናቸው በተጨባጭ የሚታይ ሲሆን ለሥጋም ለነፍስም ስንቅ የሆኑ ትምህርቶች መቅሰሚያ ሕያዋን ትምህርት ቤቶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ለኪነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕድገት መሠረት ከመሆናቸውም በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና በቱሪስት መስህብነትና በምጣኔ ሀብት ምንጭነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ መላው ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡

 

ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት በተለያዩ አዝማናት በሀገሪቱና በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በደረሱ ውጪያዊና ውስጣዊ የጥፋት ዘመቻዎች ቀጥተኛ ተጠቂዎችም ነበሩ፡፡ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ችግሮችም እንደየአካባቢው መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ተጋላጭ ሆነው ኖረዋል፡፡ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንም በየጊዜው በተለያየ ስልት የገዳማውያኑን አኗኗር፣ ሥርዓትና ትውፊት ለመበረዝ ሲንቀሳቀሱና ገዳማቱን ሲዋጉ እንደኖሩ ግልጽ ነው፡፡

 

በእኛ ዘመንም ገዳማቱ በሀገሪቱ ሕዝብና መንግሥት የነበራቸውን መልካም ስምና ታሪክ ለማደብዘዝ እያበረከቱት ያለውን መንፈሳዊና ሀገራዊ አስተዋፅኦ ወደጎን በማለት በረቀቀ ስልት በኢትዮጵያ ገዳማት ላይ ዘርፈ ብዙ ዘመቻ እንደተከፈተባቸውም እንገነዘባለን፡፡ ከዘመቻውም በተጻራሪ የዘመኑን ችግር በዘመኑ ጥበብና ዕውቀት እየፈቱ እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ ሁሉ አገልግለው በክብር ያረፉ መንፈሳውያን አርበኞች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ ይልቁንም በወሳኝና አስቸጋሪ ወቅቶች እግዚአብሔር እያነሣሣ ሥራ የሠራባቸውንና የሚሠራባቸውን አባቶች፣ እናቶችና ተተኪ ልጆች ያጣችበት ጊዜ እንደሌለም በሚገባ እንረዳለን፡፡

 

በዘመነ ሉላዊነት ዓለማዊነት በገነነበት በዚህ እጅግ አስቸጋሪ ወቅት የገዳሞቻችን ተግዳሮቶችም የዚያኑ ያህል የረቀቁ፣ በቀላሉ ለመለየት የሚያስቸግሩና የተወሳሰቡ እንደሚሆኑ እሙን ነው፡፡ ከዚሁ አንጻር የመንፈሳዊ ሕይወት፣ የመልካም ሥነ ምግባራት፣ የልማት፣ የትምህርትና የዕድገት መሠረትነታቸውንና ማእከልነታቸውን ጠብቆ ለማስቀጠል፣ ብሎም ይህን ገዳማዊ እሴት አጥተው በስም ብቻ የሚጠሩትን ገዳሞቻችንን ስምና ግብራቸው የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ የዚያኑ ያህል በአግባቡ የታሰበበት፣ የተደራጀ፣ በዕቅድ የሚመራ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ፣ በየደረጃው ያሉ ወገኖችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠና ቀጣይነት ያለው ተግባር ለማከናወን ቆርጦ መነሣት ጊዜው የሚጠይቀው ሰማዕትነት እንደሆነ እናምናለን፡፡

 

ከዚህ አንጻር በገዳማት ዙሪያ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በተዋረድ ባሉ የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ሥር ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን በተደራጀ መንገድም ሆነ በተናጠል ያደረጉት፣ እያደረጉት ያለውና ለማድረግ ያቀዷቸው በርካታ ተግባራት የሚያስመሰግኑ ቢሆኑም ከችግሩ ስፋት፣ ግዝፈትና ጥልቀት አኳያ ሲታይ ደግሞ በቂ ሥራ ሠርተናል የሚያሰኝ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

እናም ዕውቀታችንን፣ ሙያችንን፣ ጉልበታችንንና ገንዘባችንን ከምንም በላይ ደግሞ በጎ ፈቃዳችንንና ጊዜያችንን አቀናጅተን በዘመናት ርዝመት በገዳሞቻችን ላይ የሚታዩትን ተጨባጭ ችግሮች ለመቅረፍ ረጅምና አድካሚውን ጉዞ በጋራ መጀመር ይጠበቅብናል እንላለን፡፡ ይህን ስንል ደግሞ በአንድ ጊዜ የገዳማቱን ችግሮች ሁሉ ማስወገድ ይቻላል በማለት ሳይሆን፤ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እየመረጡ በተለይ ወሳኝ ችግሮች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ እያነጣጠሩ ተራ በተራ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ማለታችን እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ ገዳማቱም ከጸሎቱ፣ ከውስጥ አገልግሎቱና ከትህርምቱ (ከተጋደሎው) ጎን ለጎን ዘመኑን እየዋጁ ምእመናንን ከኋላቸው አሰልፈው የበረከተ ሥጋ ወነፍስ ተቋዳሽ ለማድረግ የፊት አውራሪነቱን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ገዳማት አንዱ የሆነው ታላቁና ታሪካዊው የደብረ ሊባኖስ ገዳም ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ የሆኑና የገዳሙን መንፈሳዊ እሴት የሚያስጠብቁ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን አስቀርፆ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ በእጅጉ የሚያስደስት ጅምር ሥራ ነው፡፡ ይህም ድርጊት ገዳሙን በአርአያነት የሚያስጠቅሰው ከመሆኑም በላይ በአረንጓዴ ልማትና በብዝኃ ሕይወት ጥበቃም (ሀገሪቱ ከምታራምደው ፖሊሲ ጋር የተዛመደ ሆኖ ቦታውን በዚህ ዘርፍ) ከሀገሪቱ ተመራጭ ቦታዎች አንዱ እንደሚያደርገው ጽኑ እምነታችን ነው፡፡

 

ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር ኅዳር 9 ቀን 2005 ዓ.ም በተዘጋጀው የምክክር መርሐ ግብር ላይ ገዳሙ ይፋ ያደረጋቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የገዳሙን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከመፍታት አንጻር ታላቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ በየገዳማቱና በየአብነት ትምህርት ቤቶቹ የተጀመሩ የመታደግና የማልማት ፕሮጀክቶች እየቀጠሉ እንዲህ ያለውን መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት ከማስፈጸም አንጻር ከገዳሙ ጋር አብሮ መሰለፍ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ሥራ ነው እንላለን፡፡ በቀጣይም በየአህጉረ ስብከቱ ለሌሎች ገዳማትና አድባራት ምሳሌ የሚሆኑ ቢያንስ አንዳንድ ገዳማትን በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ደንብ መሠረት ማደራጀት፣ ማልማትና በሁለንተናዊ ዘርፍ ማብቃት ይዋል ይደር የማይባል ጉዳይ እንደሆነም እናምናለን፡፡

 

በጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም የኖሩትንና አሁንም ያሉትን ችግሮች በቅደም ተከተል ለመፍታትና ገዳሙን ለመታደግ በመንፈሳውያን አባቶቻችንና በቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሙያ ልጆች «ብዝኃ ሕይወትና ሁሉን ዐቀፍ መሪ ዕቅድ» በሚል ስያሜ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት መዘጋጀቱ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ መሪ ዕቅድ የገዳሙን ብዝኃ ሕይወት ባሕላዊ አጠባበቅ ማጥናት፣ መጠበቅና ለቱሪዝም ያለውን ዋጋ ማስተዋወቅ፣ ለገዳሙ ማኅበረሰብ አማራጭ የኀይል አጠቃቀም አሳብ ማቅረብ፣ የተደራጀና የተቀናጀ የገዳም አስተዳደርን ማጠናከር፣ ገዳሙን ለምናኔ ሕይወት አመቺና ተመራጭ የሚያደርጉና የመሳሰሉት ተግባራት ተካተውበት የቀረበ መሆኑ መልካም ነው፡፡ ይህ መሪ ዕቅድ ወደ ተግባር ሲተረጎም የሚያስጠብቀው የገዳሙን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመላው ሀገሪቱን ብሎም የአህጉሪቱንና የዓለምን ጥቅም ጭምር መሆኑን በቅድሚያ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መሪ ዕቅዱ በሥራ ተተርጉሞ የታሰበውን ሁሉ ዐቀፍ ጠቀሜታ ያስገኝ ዘንድም የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም መላው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ ቀርቦ በማየትና በመረዳት የድርሻችንን ለመወጣት በቁርጠኝነት ልንነሣ ያስፈልጋል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳንም እንደ ቤተ ክርስቲያን አካልነቱ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አማካኝነት ባለፉት 10 ዓመታት ባካሄዳቸው ጥናቶች መሠረት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በ105 ገዳማት እንደየችግሮቻቸው ዓይነትና መጠን እያየ ለአብነት ትምህርት ቤች የመማሪያና የመኖሪያ ግንባታ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የዕደ ጥበብ ማእከላት ግንባታና ሥልጠና እንዲሁም የወፍጮ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በእርሻ ፕሮጀክት ዘርፍም የንብ ማነብ፣ የወተት ከብት እርባታ፣ የከብት ማድለብ፣ የዶሮ ዕርባታና የመስኖ አገልግሎትን በሳይንሳዊና ዘመናዊ መንገድ እንዲጠቀሙና ምርታማነትን በማሳደግ ራሳቸውን ችለው ለሌሎችም እንዲተርፉ ለማድረግ የበኩሉን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ለተለያዩ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ስምንት ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት በመተግበር ላይ ሲሆኑ ጥናታቸው ያለቀላቸው ዘጠኝ ፕሮጀክቶችን ደግሞ የበጎ አድራጊ ማኅበራትንና ምእመናንን ድጋፍ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ማኅበራችን እየተገበራቸው ያሉትንና የሚተገብራቸውን ቀጣይ ሥራዎች ሳያጓድል በሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል በኩል ከገዳሙ አስተዳደር ጋር ያጠናውን ይህን ሰፊ ሥራ ለመጀመርና ከዳር ለማድረስ የልጅነቱን ድርሻ የሚወጣ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል፡፡

 

ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች በሂደት እየተቀረፉ የልማት፣ የትምህርት፣ የመንፈሳዊ ሕይወት፣ የምናኔና የመልካም ሥነ ምግባራት ማእከልነታቸው እንዲጠበቅ ከማድረግ አኳያ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ሁላችንም በመንፈሳዊ ቅንዓት መረባረብ አለብን፡፡ ይህን ማድረግ የምንችል ከሆነ የጸሎት፣ የዕውቀትና የበረከት ምንጭ ከሆኑት ገዳሞቻችን ሀገሪቱም ሆነች ሕዝቦቿ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡ የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ በማስተዋወቅ የጽሑፍና ታሪካዊ፤ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ከማድረግ አንጻርም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ዘላቂና አስተማማኝ ማድረግ እንችላለን፡፡ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከሚያስገኙት የማይነጥፍ ገቢ ጎን ለጎን በእርሻና በዕደ ጥበብ ምርታቸው የሀገሪቱን አጠቃላይ ዕድገት ደግፈው በምግብ ራስን የመቻል መርሐ ግብር ዕውን ከማድረግ አንጻር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እናግዛቸዋለን፡፡ ገዳማቱ ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው ወገኖቻችንና ለዕጓለማውታ ሕፃናት የሚሰጡትን አገልግሎት ለማቀላጠፍና ቅዱሳን አባቶቻችን የደነገጉት /የሠሩት/ ሥርዐተ ገዳም በሚመለከታቸው ሁሉ በአግባቡ እንዲፈጸም ለማስቻል ሁለንተናዊ አቅማቸውን በተቀረፁና በሚቀረፁ ፕሮጀክቶች አማካኝነት እንዲያሳድጉ መደገፍ ከሁላችንም የሚጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ ነው እንላለን፡፡

 

  • ምንጭ፡- ጽምዐ ጽድቅ 20ኛ ዓመት ቁጥር 6 ከታኅሣሥ 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.
mahbre posterpsd

“ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መሳካት የገዳማት ድርሻ” በሚል ዐውደ ጥናት ይካሄዳል

ታኅሣሥ 4 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

  • የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የገድል መጽሐፍ ይመረቃል

mahbre posterpsdየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ለማሳካት የገዳማት ድርሻ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ አውደ ጥናት ታህሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሠዓት ጀምሮ 6 ኪሎ በሚገኘው በኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል ከሃምሳ በላይ የሚደርሱ ከታላላቅ ገዳማት የተውጣጡ አበምኔቶች በተገኙበት እንደሚካሄድ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲያቆን አእምሮ ይሔይስ ገለጹ፡፡

 

በዕለቱም ከዐውደ ጥናቱ ጋር ተያይዞ በገዳማት ላይ ጎልተው የሚታዩትን  ችግሮች መቅረፍ ይቻል ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን 12 ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በገዳማት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጅቷል፡፡ በዚህም መሠረት ከ5000 ለሚደርሱ ምእመናን ጥሪ የተደረገ ሲሆን ዋነኛ ዓላማውም ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ መሆኑን ከቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

 

በተጨማሪም በዚሁ ዕለት የታላቁ አባት የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫና የአባ በጸሎተ ሚካኤል የገድል መጽሐፍ የሚመረቅ ሲሆን ተተርጉሞ ለኅትመት ለማብቃት ከሦስት ዓመት በላይ እንደፈጀ ተገልጿል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአገልግሎት ላይ የሚገኙ መንፈሳዊ ማኅበራትና ምእመናን እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

 

በተያያዘ  ዜና ከየገዳማቱ ለተውጣጡት ከሃምሳ በላይ አበምኔቶች የሚሳተፉበትና ከታኅሣሥ 7 -11 ቀን 2005 ዓ.ም. የሚቆይ ሥልጠና መዘጋጀቱን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲያቆን አእምሮ ይሔይስ ገልጸዋል፡፡  ሥልጠናው የሚያተኩርባቸው ርዕሰ ጉዳዮችን ሲያብራሩም “ገዳማት በውስጣቸው ያለውን ሀብት እንዴት መጠቀም ይችላሉ? በገዳማት ውስጥ የሥራ ፈጠራን እንዴት ማዳበር ይቻላል? እንዴትስ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይቻላል? ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ገዳማት ያላቸውን የደን ሀብት እንዴት ተንከባክበው መያዝና መጠቀም ይችላሉ?  በቅርስ አያያዝ በኩልም በፈራረሰ ዕቃ ቤት ውስጥና አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን ቅርሶች በተሻለና በተቀናጀ መንገድ ጠብቀው  ለተተኪው ትውልድ እንዴት ማስተላለፍ ይችላሉ? የሚሉት ላይ ያተኩራል” ብለዋል፡፡

 

ሥልጠናው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ምሁራን፤ በቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎችና በተጋባዥ ምሁራን አማካይነት  እንደሚሰጥ ዲያቆን አእምሮ ይሔይስ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

pro.bya yemame

ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ምን ይላሉ?

ታኅሣሥ  4 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

  • የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ዕረፍት ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀጣዩ ፓትርያርክ ማንነት እያነጋገረ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቀጣዩ ፓትርያርክ አሰያየም ሂደትና ቀጣዩ ፓትርያርክ የሚጠብቃቸው ሓላፊነቶች በተመለከተ ከተለያዩ ወገኖች ጋር ውይይት አድርገናል፤ የሰጡንን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

 

ፕሮፌሰር ባዬ ይማም

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ


የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በሞት ሲለዩ ማን ይተካቸዋል? የሚተኩት አባት እንዴት ይመረጣሉpro.bya yemame? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርም፡፡ ከተነሣ ደግሞ የምርጫ መስፈርት ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከአሁን በፊት ቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ መርጣ የምትሾምበት ሥርዐት ካላት፤ ያ ሥርዐት አሁንም በተግባር መዋል አለበት፡፡ ምናልባት አዲስ የመምረጫ መስፈርት ማውጣት የሚያስፈልግ ከሆነ፣ ሲኖዶሱ ተጨማሪ መስፈርት ሊያወጣ፣ ያሉትን መስፈርቶች ሊያሻሽል የሚችልበት ሥልጣን አለው፡፡ በዚህም መሠረት ምርጫው ይከናወናል፡፡

 

በፓትርያርክ ምርጫው ላይ ምእመናን አስተዋጽኦዋቸው ምን ይሆናል የሚለውን ስንመለከት፦ ቤተ ክርስቲያኗን የሚጠብቅ፣ ምእመናኑን የሚያስተምሩ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን በልማት ማሰለፍ የሚችሉ መልካም አባት እንዲሰጠን በጾም፣ በጸሎት እግዚአብርሔርን መለመን ከምእመናን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ይህን ከመፈጸም ባለፈ በአደባባይ ወጥቶ እገሌ ይጠቅመናል ይሾምልን፣ እገሌ ይጐዳናል አይሾም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡

 

የምሁራኑንም አስተዋጽኦ ስንመለከት፦ ምሁራኑን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ እነዚህም ዓለማዊ ምሁራንና መንፈሳዊ ምሁራን /ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን/ ናቸው፡፡ ዓለማዊ ምሁራን ሆነን በተለያየ የሙያ መስክ የምንገኝ፣ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች የሆን፣ የነፍስ አባትም ያለን አለን፡፡ እንደ ባለሙያ ዜጋ ቤተ ክርስቲያኗ የእኛም ስለሆነች የእርሷን ደኅንነት፣ የእርሷን አመራር በሚመለከት አሳብ መስጠት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ፦ ምሁራኑ በቤተ ክርስቲያኗ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ በማማከር ወዘተ በሙያቸው አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ምርጫውን በሚመለከት ግን የምሁራኑ ተሳትፎ ይፈለጋል ተብሎ ከምሁራኑ መካከል ተጠቁመው በምርጫው ሂደት ላይ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ሁኔታ ካለ፤ እዚያ ላይ ሊሳተፉ  ይችላሉ፡፡ ከሌለ ግን በየሙያ መስካቸው ከቤተ ክርስቲያኗ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ መልኩ በልማቱ፣ በትምህርቱ በኩል አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

 

መንፈሳዊ ምሁራን /ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን/ ግን ለየት ያለ ሓላፊነት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የፓትርያርክ ምርጫ እንዴት ብሎ መፈጸም እንዳለበት ድምፃቸውንም የበለጠ ሊያሰሙ ይገባል፡፡ በአጥቢያ የሰበካ ጉባኤያት የአሳብ፣ የተግባር አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከምርጫው በፊት፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለያየ ምክንያት ሳይበታተን በአንድነት በጾም፣ በጸሎት ተወስኖ እግዚአብሔር መልካሙን አባት እንዲሰጠን መጸለይ፣ ምርጫው የተሳካ እንዲሆን፤ ሊያስተምሩ፣ ሊመሩ፣ ሊወቅሱም፣ ሊያሞግሱም ይገባል፡፡ ከውጭ ተመልካች ሳይሆኑ፤ ከውስጥ ሆነው በሲኖዶሱ አካባቢ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ የመምከር፤ የማማከር ሓላፊነት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ከምርጫውም በኋላ ተመራጩን አባት በሚመለከት በሕዝቡ ዘንድ ብዥታ እንዳይኖር፣ ልዩ ልዩ ወሬ ለሰማው ሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ የመስጠት፣  የተመረጠውን አባት ተቀብሎ በአዲስ መንፈስ በየሀገረ ስብከታቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ከተመረጡ በኋላ የሚጠብቋቸው ተግዳሮቶችንም በሁለት በኩል ማየት ይቻላል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ሕዝበ ክርስቲያኑን የመምራት፣ የማስተማር፣ የማቀራረብ ለልማት የማስተባበርና የማሰለፍ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ ከአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ጀምሮ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ባለው መዋቅር በልማቱም፣ በመንፈሳዊ ትምህርቱም፣ በአመራሩም አሳብ እንዲንሸራሸርና ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምእመኑን ድርሻ ምን እንደሆነ ማሳወቅ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በተዋረድ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ሕዝቡን ማንቀሳቀስ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን በሀገር ውስጥም፣ ከሀገር ውጭም አገልግሎቷን ማስፋፋት፣ ማጠናከር፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን መሰባሰብ፣ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በዓለም የማስፋፋትና ትምህርቱን የማዳረስ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የለውጥ ሂደት እንቅስቃሴ ውስጥ እየገባች ስለሆነ፤ በተጀመሩት የልማት መስመሮች ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዴት ሊሰለፍ ይችላል? ቤተ ክርስቲያኗ በትምህርቱ፣ በጤናው፣ በማኅበራዊ ዘርፍ የድርሻዋን ለመወጣት፣ የተጀመረውን የማስፈጸም ሓላፊነት ያለባት ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ የሚመረጡት አባትም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱም ይህን ማቀናጀትና መምራት ትልቅ ሓላፊነት ያለባት ይመስለኛል፡፡

 

በሀገር ውስጥና በውጭም በሚገኙ አባቶች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታትም ይጠበቅባቸዋል፡፡ እኔ በግሌ በአባቶች መካከል ይህ ሁኔታ መፈጠሩ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሲኖዶስ፤ ሕዝቡም እንዲሁ በሁለት፣ በሦስት መከፋፈሉ እጅግ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሁለት ሲኖዶስ ለምን አስፈለገ? ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያኗ ለሁለት ተከፍላለች ማለት ነው? ሕዝበ ክርስቲያኑም ለሁለት ተከፍሏል ማለት ነው? ከውስጥና ከውጭ ሲኖዶስ ለመፈጠሩ ምክንያቱ ምንድን ነው? ብሎ አጥንቶ ምንጩን ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱ መካከል የተፈጠረው ክፍተት የዶግማና የቀኖና ሳይሆን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳይ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን ሊከፍላት አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንድ ናት፡፡ ሊኖራት የሚገባው አንድ ሲኖዶስ ነው፤ ሊኖራት የሚችለውም አንድ አባት ነው፡፡ ሊኖራት የሚችለው አንድ ሕዝበ ክርስቲያን ነው፡፡ ሁለት፣ ሦስት ብሎ ነገር አይታየኝም፡፡ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች በአሜሪካም፣ በአውሮፓም … ያሉት ማእከላዊነቱን ጠብቆ በአንድ ሲኖዶስ በሚሰጠው መመሪያ በልማት፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚሳተፉ ሊሆኑ ይገባል፡፡

 

ሁለቱንም አባቶች /ከሀገር ውስጥም ከውጭም ያሉትን/ ወደ አንድ እንዴት ይምጡ የሚለው የእኛ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ሁለት ፓትርያርክ ሳይሆን አንድ ትርያርክ ይኑር፤ ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ወይም ሁለቱ ተማክረው አንድ ይሁኑ የሚለው አሳብ ከራሳቸው ከውስጣቸው ከሃይማኖታዊ ግዴታቸው ቢመጣና አንድ ቢሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ምእመኑ «አንተም ተው፤ አንተም ተው» ብለው ማስማማት መሞከራቸው  ተገቢ አይደለም፡፡ እኛ ተመሪዎች ነን፡፡ መሪዎቻችንን «ኑ ታረቁ፤ አንድ ሁኑ» ለማለት ሥልጣኑ አይፈቅድልንም፡፡ ሥልጣኑ ያለው በአባቶቻችን ስለሆነ፤ መታረቅም፣ መመካከርም የእነርሱ ፈንታ ነው፡፡ እኛ የምንችለው እግዚአብሔርን በጸሎት መለመን ነው፡፡ እነርሱ አንድ ሆነው ሕዝቡን አንድ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ አንድ ሲኖዶስ እዚህ፣ አንድ ሲኖዶስ እዚያ፤ አንድ መሪ እዚህ፣ አንድ መሪ እዚያ በማለት ሕዝቡን መበታተን ለማንም አይጠቅምም፡፡ መንግሥትም በዚህ ላይ የሚያገባው ይመስለኛል፤ ዝም የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ሕዝበ ክርስቲያኑን በአንድነት ለልማት እንዲነሣሱ ለማድረግ አቅሟን ማጐልበት አለባት፡፡ አሁን አንዳንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳሽ እያጡ ካህናቱ ወደ ከተማ እየፈለሱ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ወደፊት ቤተ ክርስቲያን ከአገልጋይ ካህናት እጥረት የተነሣ የምትዘጋበት ሁኔታ እንዳይመጣ ከላይ እስከታች ድረስ ማእከላዊነቱን የጠበቀ አሠራር ልትዘረጋ ይገባል፡፡ አንዱ ቤተ ክርስቲያን ጥሩ ገቢ ኖሮት ሌላው ቀዳሽ አጥቶ የሚዘጋበት ሁኔታ እንዳይኖር ትክክለኛና ፍትሐዊ የሆነ አሠራር መኖር አለበት፡፡

 

ስለዚህ አዲስ የሚመረጡት ፓትርያርክ ይህን ተገንዝበው በከተማም በገጠርም ያለችው ቤተ ክርስቲያን የልማቱ፣ የማንኛውም ነገር እኩል ተሳታፊ፣ እኩል ተጠያቂ፣ እኩል ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ አለባቸው፡፡ ተግዳሮቱም ይህ ይመስለኛል፡፡ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ትልቅ የልማት መስመር በየአቅጣጫው ዘርግታ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ከምታደርገው የበለጠ እንቅስቃሴዋን ማሳየት አለባት፡፡ እንቅስቃሴውን ለማሳየት ደግሞ ሕዝበ ክርስቲያኑን አንድ አድርጋ በማሰባሰብ በአንድ ሲኖዶስ፣ በአንድ አባት መምራት መቻል አለባት፡፡

 

«ለእርቅ፣ ለፍቅር ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው»

ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ


dr.yeraseworke ademasaየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ልትመርጥ በዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመጀመሪያ ያለኝ አስተያየት አሜሪካን ሀገር ያለውን ወገንና በዚህ መደበኛው ወይም ዕውቅና ያለውን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን ሲኖዶስ የሚመ ለከት ነው፡፡ ዋናው እዚህ ያለው ነው፡፡ እነኚህ ሁለቱ እኩል ሊታዩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የአንድ እምነት ተከታዮች እስከሆኑ ድረስ በውጭ ሀገር የሚገኘው የተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናትን ያቀፈ ቢሆንም፤ ሁለቱም አንድ የክርስቶስ ቤተሰቦች ስለሆኑ ለእርቅ፣ ለፍቅር ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡

 

ታላቅ የሆነው ወንድም ታናሹን ወንድም ወደ አንድ አባታቸው ቤት እንዲመለስ፤ አብረው እንዲሆኑ የተቻለውን ቢያደርግ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ከምርጫው በፊት የግድ ማለቅ የለበትም፤ ከምርጫው በኋላም የግድ መሆን የለበትም፡፡ ከምርጫው በፊት እርቅ መካሄድ አለበት ማለት ለዚያኛው ዕውቅና መስጠት ይሆናል ይህም አያስኬድም፡፡ ስለዚህ የተሻለ የሚሆነው ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው የሚካሄደው በሀገር ውስጥ በቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ምርጫው ከማለቁ በፊትም ሆነ ከአለቀም በኋላ ቢሆን፤ ያንን ወገን ወደዚህ ለመሳብ የሚቻለውን ሁሉ አድርጐ ቅሬታቸውንም አዳምጦ የቤተ ክርስቲያኑን አንድነት ለመመለስ ማንኛውንም ሙከራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 

በምርጫው ወቅትም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ለምርጫ የሚቀርቡት አባቶች በቤተ ክህነት አካባቢ ያሉ ናቸው፤ አቋማቸው ይታወቃል፡፡ የሚመረጡት አባት ከዚህ በፊት በነበራቸውና አሁንም ባላቸው አቋማቸው ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አገልግሎት ይሰጣሉ? ይህችን ቤተ ክርስቲያን ይታደጓታል ወይ? ይህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ችግር ይፈታሉ ወይ? ይህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ መጥፎ አዝማሚያዎችን ያርሟቸዋል ወይ? ቤተ ክርስቲያኒቱ በፊቷ ተደቅነው ያሉ ተግዳሮቶችን እልፍ የሚያደርግ ርዕይ ያላቸው ናቸው ወይ? ቁርጠኝነት ያላቸው ናቸው ወይ? ለማንኛውም ወገን ቢሆን ከትክክለኛው መንገድ ውጪ የሆነ ወገናዊነት የሚያሳዩ ሰው አይደሉም ወይ? የሚሉት ነጥቦች መታየት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዋናው መሪ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የዴሞክራሲ ጨዋታ አይደለም ያለው፡፡ ስለዚህ አንድ አባትን ቅዱስ ሲኖዶስ መረጠ ማለት፤ ከአሁን በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት /ዐሥርት ዓመታት/ አንድ ዓይነት አመራር የሚሰጡ አባት ተመረጡ ማለት ስለሆነ፤ ምርጫው ላይ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ይህ ጥንቃቄ ሊኖር የሚችለው ግልጽ የሆነ ውይይት ሲኖር ነው፡፡ ግልጽ የሆነ ውይይት የሚያስፈልገው የመጀመሪያው በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ልክ  አሁን ሐመር መጽሔት በጀመረችው የውይይት መድረክ ላይ በመሳተፍ አስተያየቶችን በመስጠት ነው፡፡ እንዴት ዓይነት አባት እንምረጥ የሚለውን መነጋገር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

 

ሌላው ሊታወቅ የሚገባው በዚህ ምርጫ ላይ ከጳጳሳት ጀምሮ እስከ ምእመኑ ድረስ ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጽኦዎች በየደረጃቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ ጳጳሳቱ በሲኖዶሱ ውስጥ መድረክ አላቸው፡፡ እንደውም መጨረሻ ላይ እነርሱ ናቸው መራጮች፡፡ የምእመናኑ አስተዋጽኦ ጸሎትና ምህላ መያዝ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ግልጽ የውይይት መድረክ ካለ፤ በዛ መድረክ አማካኝነት «እንደዚህ ያለ ሰው ይሁንልን፣ እንደዚህ ያለ ሰው ቢሆን ቤተክር ስቲያንንም ምእመናኑንም ይጠቅማል» ብለው በግልጽ ሰውየውን ራሱን ሳይሆን የቆመለትን ዓላማና የሚያንጸባርቀውን ጠባይ በመግለጽ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡

 

የምሁራኑንም አስተዋጽኦ ስንመለከት፦ ምሁራኑን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት የሚያውቁ ተሰሚነትና ዕውቀትም ያላቸው መንፈሳዊ ምሁራን  አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች የሆኑ ልዩ ልዩ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ ዓለማዊ ምሁራን አሉ፡፡ በተለይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የአሁኑ የግሎባላይዜሽን ዘመን ነው፡፡ የአሁኑ ዘመናዊ ትምህርት እየተስፋፋበት ሁሉም ልጆች ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የሚሄዱባት ኢትዮጵያ፣ ወደፊት የሕዝቧ ብዛት አንድ መቶ ሠላሳ ሚሊዮን፤ የከተማ ነዋሪዋ ወደ ሠላሳ ሚሊዮን የሚያድግ ኢትዮጵያ፣ ዜጐቿ ቀለም መማር ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚችሉ፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደራሽነት ያላቸው ዜጐች የሚኖሯት ናት፡፡ ይሄን የመዘመን ተሽከርካሪ ማንም ሊያቆመው የማይችል በመሆኑ ከዚህ ጋር ለመሄድ ራስን ማስተካከል ስለሚያስፈልግ ያንን ሥራ ላይ የሚያውል አመራር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን አመራር በአሳብ ሊደግፉ የሚችሉ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ ምሁራን ግን የቤተ ክርስቲያናችንን ፍላጐትና የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር የራሳቸው ያደረጉ ምሁራን አሉ፡፡ ቀደም ሲል ሃይማኖተ አበው የሚባል በጥቂት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቋቋመ ማኅበር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን አለ፡፡ እነኚህ የድሮውንና ዘመናዊ  ያደረጉ ምሁራን ይመስሉኛል፡፡ ቀደም ሲል ሃይማኖተ አበው የሚባል በጥቂት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቋቋመ ማኅበር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን አለ፡፡ እነኚህ የድሮውንና ዘመናዊውን፤ ቀደምቱንና ዘመናዊውን ለማያያዝ የሚጠቅሙ ሰንሰለቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምሁራን በፓትርያርክ ምርጫ ውይይት ውስጥ እንደ አስፈላጊነቱ ቢሳተፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ፡፡ ይህንንም ስል ምሁራን ስለሆኑ ይበልጥ ተደማጭ መሆን አለባቸው ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ምሁርነታቸው ጠቃሚ የሆነ አሳብ ማቅረብ ስለሚችሉ ነው፡፡

 

ፓትርያርኩ ከተመረጡም በኋላ ብዙ የሚጠብቋቸው፣ ማስተካከል የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ውጪ የሆኑ ከጐንና ከጐን የገቡ አንዳንድ ነገሮችን ማረምና ማስተካከል አለባቸው፡፡ ለምሳሌ- ብዙ ነገር ሥነ ሥርዐትም ሥርዐትም ያንሰዋል፡፡ የሰው ኃይሉ፣ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚሰጠው ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ወዘተ  ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

መቃብር ባሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት በአንዳንድ ቦታዎች መቃብራት እየተነሡ ለገቢ ማስገኛ ተብሎ ሕንፃ እየተሠራበት ነው፡፡ መሠራቱ ጥሩ ቢሆንም ሕዝቡ የሚቆምበት ቦታ መኖር የለበትም) በአንዳንድ ቦታዎች የሚሠሩ ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናትም እጅግ በጣም ትልቅ የሆኑ ከአቅም፣ ከትውፊታችን ጋር የማይያያዙ አሠራሮችን እየተመለከትን ነው፡፡ ይሄ መቅረት አለበት፡፡ ከዚህ ይልቅ ልክ ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም እንደሠሩት ዓይነት ትምህርት ቤት ማነፅ ይገባቸዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች የቀድሞውን ምሁራዊ እሴት ያልዘነጉ ልጆች በብዛት ለማውጣትና እነኛን ልጆች ለከፍተኛ ትምህርት ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡ ዛሬ በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ለገቢ ማስገኛ ከሚሠሯቸው ቤቶች ይልቅ እንደዚህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች ቢሠሩ ሁለት ጥቅም ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው ገቢ ያስገኛል፤ አንደገና የወደፊት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ተከታዮች፣ ደጋፊዎችን ማፍራት ይቻላል፡፡

 

ሌላው ካህናቱን ስንመለከት ምን ያህል ለድኻው የቆሙ ናቸው? እንዴት ነው ድኻውን የሚያጽናኑት? የድኻ ቤተሰብ ሰው ሲሞትበት አሳዛኝ በሆነ መንገድ ስንቱ ነው የሚሄደው? በተለይ በአሁኑ ዘመን እኮ ሰው «የቦሌ ቄስ፣ የእንትን ቄስ …» እያለ መቀለድ ጀምሯል፡፡ ካህናቱን የሚስባቸው ዘመናዊ ነገር ነው፡፡ ገንዘብ ያለው፣ የለቲካ ሥልጣን ያለው … እና ለድኻው የሚሰጠው አገልግሎት ይለያያል፡፡ ስለዚህ ብዙ የሚታረሙ ነገሮች አሉ፡፡

 

ፓትርያርኩም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ትልቅ ሓላፊነት ለመወጣት በመጀመሪያ ደረጃ የፓትርያርኩ ቢሮ ክፍት ሆኖ ከልዩ ልዩ አቅጣጫ የሚመጣውን አሳብ መቀበል አለበት፡፡ የፓትርያርኩ ቢሮ መቀበል ያለበት እንደዚህ ያለውን እንጂ፣ ዳቦ፣ ኬክ አስጋግረው የሚመጡ  ባልቴቶችን ማስተናገድ የለበትም፡፡ ልዩ ልዩ ተቃራኒ የሆኑ፤ ከእነርሱም የሚቃረን አሳብ ማዳመጥ አለባቸው፡፡ ሁለተኛው እርስ በርስም በውይይት ነገሮችን በሚገባ፣ በዝርዝር እየተወያዩ የተማመኑበትን በሥራ ላይ ማዋል አለባቸው፡፡ ፓትርያርኩ መሪ ነው የሚሆኑት፤ የፓትርያርኩን አሳብ አዳምጦ ያንን አሳብ አሰላስሎ ለብዙኃኑ የሲኖዶስ አባላትና ሌሎች በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለእነርሱ አቅርቦ አሳምኖ ፖሊሲ አውጥቶ ያንን ማስፈጸም መቻል አለበት፡፡ በዚህ ውስጥ ዝምድና፣ ወዳጅነት የመሳሰለው ነገር መጥፋት አለበት፡፡ በተለይ አሁን የተማረው ሰው ቤተ ክህነትን እንደጦር ነው የሚፈራው «ወይ እነርሱ» ነው የሚለው፤ ተጠራጣሪ፣ ምቀኛ… የሆኑ ሰዎች ዋሻ ነው ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ይህን አተያይ ለመፋቅ፣ ለማስወገድ መጣር አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ ግልጽ ሆነው ሲያደምጡ ነው፡፡ ስለዚህ ፓትርያርኩም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንና ሌሎችም ክፍተቶች ለመሙላት ትልቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡

 

«አንድ  ሆናችሁ ቤተክርስቲያናችንን ምሩ»

ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ


በአሁኑ ወቅት ሊደረግ ስለታሰበው የፓትርያርክ ምርጫ  አስተያየት ከመስጠቴ በፊት፤ ያለፉት አምስት ፓትርያርኮች አመራረጥ ሂደት ምን ይመስል እንደ ነበር ለግንዛቤ እንዲረዳን እርሱን ላስቀድም፡፡

 

dr.wedue tafeteእስከ አሁን ድረስ የተመረጡት አምስት ፓትርያርኮች በሦስት የተለያዩ  መንግሥታት፤ በዘውዳዊው አገዛዝ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለት፣ በወታደራዊው ደርግ ሁለት፣ አሁን ባለው በኢሕአዴግ መንግሥት አንድ ፓትርያርክ ተመርጠዋል፡፡ የመጀመሪያው ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ሲመረጡ ለፓትርያርክነት ለመምረጥ ውድድር አልተካሄደም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ «አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሆነው እንዲሾሙልን» ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ፡፡ አቡነ ባስልዮስ ከዐረፉ በኋላ ፓትርያርክ ለመምረጥ ዝግጅቱ አምስት ወራት ፈጅቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የወጣው ሕግ  «ከእንግዲህ በኋላ ፓትርያርክ ቢሞት ምርጫው በዐርባ ቀናት ውስጥ መፈጸም አለበት» የሚል ድንጋጌ ይዟል፡፡ በወቅቱ የቀረቡት ሦስት እጩዎች  አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ያዕቆብና አቡነ ጢሞቴዎስ ነበሩ፡፡ ከ156 መራጮች ውስጥ አቡነ ቴዎፍሎስ በ123፣ ድምፅ ማግኘት ሁለተኛው ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ፡፡ የምርጫውን ውጤት በቅድሚያ የሰሙት ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ፡፡ እርሳቸው ካጸደቁት በኋላ የምርጫው ውጤት ይፋ ሆነ፡፡

 

በደርግ ዘመነ መንግሥት አቡነ ቴዎፍሎስ ሲታሰሩ ሁለት ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ሲኖዶሱ የራሱን ኮሜቴ አቋቋመ፣ በመንግሥት በኩል በዶ/ር ክነፈ ርግብ የሚመራ የቤተ ክርስቲያን ጊዜያዊ ኮሚቴ የሚል ተቋቋመ፡፡ ፓትርያርክ ለመምረጥ ሁለት ኮሚቴ አስፈላጊ ባለመሆኑ፤ ሁለቱ ተነጋግረው አንድ ኮሚቴ ተዋቀረ፡፡ ኮሚቴውን የመሩት የጊዜያዊው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ዶ/ር ክነፈ ርግብ ነበሩ፡፡ ይህ የተደረገበት ምክንያት መንግሥት ድርጊቱን መቆጣጠር ስለሚፈልግ ነበር፡፡ ለምርጫው አምስት ጳጳሳት ቀረቡ፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ከነበሩት 555 ወረዳዎች ውስጥ ሁለት፣ ሁለት መራጮች እንዲወከሉ ተደረገ፡፡ ምርጫው ሲካሄድ የሚታዘቡ ሁለት የደርግ ተወካዮችና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የነበሩትና፤ በኋላም የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር አክሊሉ ሀብቴም ተገኝተው ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዎች መንግሥትን በመወከል የተገኙ ነበሩ፡፡ ከ1049 መራጮች ውስጥ በ809 ድምፅ አባ መላኩ ተመረጡ፡፡ በወቅቱ ከቤተ ክርስቲያንም፣ ከመንግሥትም «ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ የዴሞክራቲክ ምርጫ» ተብሎ ተነገረ፡፡ አባ መላኩም ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተባሉ፡፡

 

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲያርፉ እንደገና ምርጫ ተደረገ፡፡ በዚህም ሦስት ተመራጮች አቡነ ሳሙኤል፣ አቡነ ገሪማና አቡነ መርቆሬዎስ ቀረቡ፡፡ 109 መራጮች የመረጡ ሲሆኑ፤ መንግሥትን በመወከል በምርጫው የተገኙት የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ዲበኩሉ ዘውዴ ነበሩ፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ፡፡ ኋላም አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ስደት ሲሄዱ ምርጫ ተካሄደ፡፡ ከዚያ በፊት በስደት ላይ የነበሩት አባ ጳውሎስ ተመረጡ፡፡

 

ስለዚህ እዚህ ላይ ማየትና ማወቅ የሚገባን በሦስቱም መንግሥታት ፓትርያርክ ከተመረጡ በኋላ መንግሥት እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡ በምርጫው የሚስማማ ወይም የማይስማማ መሆኑን ለማወቅ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የመንግሥት ይሁንታ ደግሞ አስፈላጊ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ነው እስከ አሁን ድረስ በተደረገው የፓትርያርክ ምርጫ የመንግሥት እጅ አለበት የሚያሰኘው፡፡ ስለዚህ በንጉሡ፣ በደርግ ጊዜም ሆነ አሁን ባለው መንግሥት፤ መንግሥት ሳያውቀው የሚደረግ የፓትርያርክ ምርጫ ይኖራል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

 

ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ወቅት ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ እንደሚከተለው እገልጻለሁ፡፡ አቡነ ባስልዮስ ዐርፈው አቡነ ቴዎፍሎስ ሲሾሙ የወጣው ሕግ አሁን ይሠራል? ወይስ ከዛ በኋላ ሕጉ ተሻሽሏል? መራጮች ሊሆኑ የሚገባቸው እነማን ናቸው? ጳጳሳት ብቻ የቤተ ክርስቲያን አና የገዳማት መምህራን ናቸው? ምእመናን ይሳተፉበታል? የምንመርጠው ምን ዓይነት አባት ነው? የሚለውን ነገር ማየት አለብን፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ፈተና ውስጥ ያለችበት ወቅት ነው፡፡ ይህን ፈተና ለማለፍ ምን ዓይነት ስትራቴጂ፣ ምን ዓይነት የአመራር ዘዴ ቀይሶ ወደሚቀጥለው ጊዜ ለማስተላለፍ ምን ይደረግ? የሚ ሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዛሬ የአስተዳደር ችግር፣ ከተለያዩ ሃይማኖቶች የሚመጡ ችግሮች አሉ፡፡ ተመራጩ አባት ቤተ ክርስቲያን ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፉ፣ ቤተ ክርስቲያኗ ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል የሚያደርጉ፣ ሃይማኖቷን የሚያስፋፉ፣ ምእመናንን የሚጠብቁ፣ እገሌን ከእገሌ የማይከፋፍሉ፣ አባት መሆን አለባቸው፡፡

 

ሌላው መታየት ያለበት ተመራጩ ፓትርያርክ ትምህርት አላቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ትምህርት ስል ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት በተጨማሪ ዘመናዊ ትምህርት አላቸው? ከሌላው ዓለም ጋር ይተዋወቃሉ? የሚለውንም ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አባል ናት፡፡ በውጭ ትወክላለች፡፡ አቡነ ጳውሎስ ምን ምን ዓይነት ሹመት እንደነበራቸው እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ከሌላው ዓለም ጋር የሚያስተዋውቁን፤ ቢያንስ አንድ የውጭ ቋንቋ የሚያውቁ አባት ቢሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ላላት ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ጠቃሚ ይሆናል የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡

 

ይህች ቤተ ክርስቲያን ከደርግ ጊዜ ጀምሮ  በሁለት እንደተከፈለች አድርገን መቁጠር እንችላለን፡፡ በውጭ ሀገር ስደተኛ ሲኖዶስ አለ፡፡ ከዚህ ቀደም ፓትርያርክ የነበሩ ሰው አሉ፤ ስደተኛ ሲኖዶስ መርጦ የሾማቸው ጳጳሳት አሉ፡፡ እኛ ነን ትክክለኛዋ የቤተ ክርስቲያን አመራር የሚሉ ፓትርያርክም ሲኖዶስም ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ ይሄ መከፋፈል ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አይጠቅምም፡፡ ውጭ ሀገር ስንሄድ በስደተኛው ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፤ አዲስ አበባ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደሩ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከሁለቱም ያልወገኑ ገለልተኛ የሆኑ አሉ፡፡ ይሄ መከፋፈል መቼ ይቆማል? እንዴት ወደ ሰላም መምጣት እንችላለን? እርቅ ተጀመረ እንጂ፤ ምን ተነጋገሩ? ጉዳዩ ከምን እንደደረሰ አይሰማም፡፡ እርቁን ተግባራዊ ለማድረግ እዚህ የሚመረጡት ፓትርያርክ ብቻ ሳይሆኑ፤ እዛ ያሉትም ሰዎች በቅንነት ይህችን አሐቲ ቤተ ክርስቲያን ለምን እንከፋፍላታለን? ብለው ወደ እርቅ ለመምጣት መሞከር አለባቸው፡፡ አንድ ሰው እጁን ዘርግቶ አየተራመደ ለእርቅ ሲጠራ፤ ሌላኛው እየሸሸ እጁን አጥፎ የሚቀመጥ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ የሩሲያን ቤተ ክርስቲያን ብንመለከት እ.ኤ.አ. 1917 በተካሄደው አብዮት ለሁለት ተከፍላ፣ ለረጅም ጊዜ ተለያይተው ነበር፤ አሁን ግን ታርቀዋል፡፡ የእኛም ቤተ ክርስቲያን የማትታረቅበት ምክንያቱ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም በውጭ ያሉትን አሻግሮ መመልከት ሳይሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት  አለባቸው፡፡ ይህንን የሚያደርግ አባት ይህች ቤተ ክርስቲያን የምትፈልግበት ወቅት አሁን ነው፡፡

 

ዛሬ በገጠሪቷ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ አባቶች እየቸገራቸው ወደ ከተማም ከዚያም ከኢትዮጵያ ውጭ እየተሰደዱ ነው፡፡ ካህናቱና መነኮሳቱ እንደ ዓለማዊ ሰው ኑሮአቸውን ለማሻሻል ውጭ ሀገርን እየተመለከቱ ነው፡፡ ይህን ፍልሰት የሚያስቀር፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት የሚከፈቱት፣ የተዳከሙ ትምህርት ቤቶችን የሚያጠናክር አባት ያስፈልጋል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤት ተዘጋ ማለት እኮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተዘጋ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር በሰላም፣ በመተሳሰብ እንዲኖሩ፣ የገንዘብ አሰባሰቡ ሥርዐት እንዲኖረው፣  ወጣቱን ትውልድ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያሉትን የሚያሰባስቡ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዳይዘጉ የሚያደርጉ፣ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆችን የሚከፍቱ አባት እንጠብቃለን፡፡

 

ሌላው ቤተ ክርስቲያኗን ዘመናዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዘመናዊ ስል ያሉትን ቀኖናዎች፣ ዶግማዎች ይሻሻሉ ማለት አይደለም፡፡ የአስተዳደር ዘርፍ፣ የገንዘብ አያያዟ ዘርፍ፣ የትምህርት አሰጣጧን ዘርፍ ዘመናዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዘመናዊ ለማድረግም ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ  ጊዜ ዲያቆናቷና ካህናቷ ዘመናዊ ትምህርት ተምረው በተለያየ የሙያ ዘርፍ የሠለጠኑ ናቸው፡፡ እነዚህን በቤተ ክርስቲያኗ የአስተዳደር ዘርፍ ውስጥ በመቅጠር ዘመናዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያኗ ባሏት ኮሌጆች ውስጥ፤ በሒሳብ አያያዝ፣ በአስተዳደር፣ በሌሎችም የሥራ መስኮች የተማሩ ሰዎችን ማፍራት ትችላለች፡፡ ስለዚህ የሚመረጡት አባት በእነዚህ ላይም ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በሚመረጡት ፓትርያርክ ትከሻ ላይ ብቻ የሚጣሉ አይደሉም፡፡ ከሥር ያሉ አማካሪዎቻቸው፣ ጳጳሳቱ፣ በተዋረድ በሀገረ ስብከት የሚመደቡ አስተዳዳሪዎች፣ የሥራ ሓላፊዎች ብቃትና ጥራት አብረው የሚታሰቡ ናቸው፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስም ለፓትርያርኩ ሥራ ቀና መንገድ መምረጥ አለበት፡፡ ጠንካራ ሲኖዶስ በሌለበት አንድ አባት ብቻቸውን ጠንካራ ሆነው ይሠራሉ ማለት አይቻልም፡፡ ሲኖዶሱ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የሚቀጥለው ርምጃዋ ምንድን ነው? የት መድረስ አለባት? በምን ዓይነት ሁኔታ ተራምዳ ነው እዛ ልትደርስ የምትችለው? ብሎ ማቀድ አለበት፡፡ በተለይ እንደ አሁኑ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ፈተና በበዛባት ጊዜ፤ የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና አቋም ይሄ ነው ብሎ መግለጫ የሚሰጥ ጠንካራ ሲኖዶስ መኖር አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለሙ ሁሉ ተስፋፍታለች ጠንካራ መሪና ጠንካራ ሲኖዶስ ከሌለ ደግሞ ይህን ሁሉ ድካም ከንቱ ነው የሚያደርገው፡፡ ስለዚህ ሲኖዶሱ ከፓትርያርኩ ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

 

ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የምንሰማው የቤተ ክርስቲያን ጭቅጭቅና የሌሎች መሳለቂያ መሆናችን መቅረት አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሰበክ ያለበት ሰላም ነው፡፡ በሲኖዶሱ መካከልም አለመግባባት ተወግዶ፤ በአዲስ አስተሳሰብ፣ በአዲስ ራእይ አንድ ሆነው ሀገራችን በጀመረችው የልማት ጐዳና አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ደግሞ የራሷን ገቢ በመፍጠር፣ ንብረት አያያዟን በማደራጀት፣ ቅርሶቿን በሙዚየም በማስቀመጥ ቱሪስቶች እንዲመለከቷቸው ልታደርግ ይገባል፡፡ ይህንንም ተመራጩ ፓትርያርክ ትኩረት ሊሰጡባቸው ይገባል፡፡

 

ፓትርያርክ ለመምረጥ የሚገቡ ሰዎችም ሊያስተውሉት የሚገባው ነገር አለ፡፡ ዝም ብለው መጥተው አዳምጠው ድምፅ ሰጥቶ ለመሄድ አይደለም፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ከእኛ ምንድን ነው የምትፈልገው ብለው፤ ሊሠሩ የሚችሉትን አባት ለይተው ድምፃቸውን መስጠት አለባቸው፡፡ መራጮቹ ወክለው የሚመጡት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ምእመን ነውና፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኗ በተለያየ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ በርካታ ምሁራን ልጆች አሏት፡፡ እነዚህን ምሁራን በአማካሪነት ልትጠቀምባቸው ትችላለች፡፡ ምሁራኑም ሐመር መጽሔት አሁን በከፈተችው የውይይት መድረክ ላይ አሳባቸውን መስጠት አለባቸው፡፡ «ይህን ብናገር፤ እንዲህ ብባልስ» እያልን ከቤተ ክርስቲያን እየራቅን ከሄድን ነገ ያልሆነ ሰው ተመርጦ በቤተ ክርስቲያኗ ችግር ሲከሰት አብረን ማማት የለብንም፡፡ እስከ አሁን አምስት ፓትርያርኮችን ብቻ ነው የመረጥነው፤ ያለን ልምድ አጭር ነው፡፡ ያለፉት የአምስቱ ፓትርያርኮች የሥራ ዘመን ደግሞ ትንሽ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በእያንዳንዱን ዘመን ምን እንደተሠራ እንዴት አንደመረጥን ትምህርት ሊሆነን ይችላል፡፡ ከዛ በመነሣት በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ አባቶች ተስማምተው ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት እንዲያራምዱ፣ ጠንካራ አስተዳደር እንዲኖራት፣ ርእይ ያለው ሥራ እንዲሠራ መጣር አለባቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶቻችን ይህን ሓላፊነት ለመወጣት ትልቅ አደራ አለባቸው፡፡

 

«እግዚአብሔር መልካም መሪ እንዲሰጠን ልንለምነው ይገባል»

ኢንጂነር ዮሐንስ ዘውዴ

 

ingn. yohanse zewdeከፓትርያርክ ምርጫው በፊት እርቁ መቅደም አለበት የሚል አሳብ አለኝ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሊታረቀን የሚችለው እርቅ ሲመሠረት ነው፡፡ እርቅ ሲመሠረት፣ እግዚአብሔር የምንጠይቀውን ነገር ያሟላልናል፡፡ በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉት ፓትርያርኮች፣ ጳጳሳት ብቻ አይደለም፤ ምእመናኑም ካህናት አባቶቻችንም በሙሉ እርቅ መመሥረት አለባቸው፡፡

 

አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተለያይታ «የእገሌ ሲኖዶስ፤ የእገሌ ሲኖዶስ» ልትባል አይገባም፡፡ ከዚሁም ጋር ተያይዞ ደግሞ እገሌን አልቀበልም የሚሉ አሉ፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቱን መለያየቶች ለማስቀረት እርቅ ሰላሙ አንድ መስመር መያዝ አለበት፡፡ በካህናቱም መካከል ሰላም እንዲወርድ ቤተ ክርስቲያንን በአንድነት እንዲያገለግሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁ የተጣሉ ምእመናንም  የሚታረቁበት መድረክ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዘጋጀት አለበት፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ሁላችንም በፍቅር ሆነን እግዚአብሔርን በንጹሕ ልብ ልንለምነው ይገባል፡፡ ይህን እርቅ ከመሠረትን በኋላ ነው እግዚአብሔርም ይታረቀናል፤ የምንጠይቀውን በጎ ነገር ይሰጠናል፡፡ በውጭም፣ በሀገር ውስጥም ያሉት አባቶቻችን የራስን አቋም በማሰብ ሳይሆን  የእግዚአብሔርን መሻት ፈቃድ በማሰብ ሁሉን ነገር ለእርሱ አሳልፎ መስጠት ይገባል፡፡

 

ምርጫው ላይ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ በቅድሚያ የአመራረጡ ሂደት ነው፡፡  እኔ ከቅዱሳን መጻሕፍት እንደተረዳሁት ሁለት ዓይነት ምርጫዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ቅዱስ ድሜጥሮስ የተመረጠበት መንገድ ነው፡፡ የእስክንድርያው ጳጳስ የነበሩት ዩልያኖስ ከማረፋቸው በፊት ሱባኤ ገብተው ሕዝቡም ሱባኤ እንዲገቡ አድርገው እግዚአብሔር ድሜጥሮስን እንዲመረጥ ገልጾላቸዋል፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው፤ በይሁዳ ምትክ የተተካው ማትያስ የተመረጠበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ሁለተኛውን መንገድ በመከተል  በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያርክ ምርጫ ሲከናወን ለቦታው ብቁ ናቸው፣ ይመጥናሉ የሚባሉ ሦስት አባቶች አስቀድመው ቢመረጡ፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡም፣ ጳጳሳቱ፣ ካህናቱ ሁሉ በአንድነት ሱባኤ ገብተው  እግዚአብሔር የፈቀደውን ከሦስቱ እንዲመርጥ ቢደረግ መልካም ይመስለኛል፡፡ ሌላው በፓትርያርክ ምርጫው ላይ ልንጠነቀቅ የሚገባው ምርጫውን በሥጋዊ ዐይናችን ተመልክተን ዘርን፣ ጎሣንና ፖለቲካን እንደመስፈርት ማየት የለብንም፡፡ እኛ ሰማያዊ ነገረ ነው የምናስበው የምንነሣውም እግዚአብሔርን  እንጂ ሰዎችን ብለን አይደለም፡፡

 

ለምርጫው መሳካት ሊቃውንቱ፣ ጳጳሳቱ፣ ምእመናኑ ሁሉም በጸሎት መትጋት ይገባናል፡፡ ይህም በሥጋ ፈቃድ ተመርተው «እገሌ ይሾምልን» የሚለውን አመለካከት ከእኛ ማራቅ የምንችለው በጸሎት ስንተጋ ብቻ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የሚመርጥ እግዚአብሔር እንጂ ሰው መሆን የለበትም፡፡ ምርጫውንም የተሳካ እንዲያደርግልን ለእርሱ እንስጠው፡፡ፓትርያርኩ ከተመረጡ በኋላም ሊፈጽሟቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም ጥቂቱን ልጥቀስ፡፡ ከላይ እስከ ታች ባሉ የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ተሰግስገው የሚገኙትን ሃይማኖት ቦርቧሪዎችን በመለየት እንዲታረሙ አድርጎ ለንስሐ ማብቃት ካልሆነም ከአገልግሎት ማራቅ ቢቻል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት አላግባብ ለሥጋዊ ኑሮአቸው ማበልጸጊያ የሚያደርጉትን ሕገ ወጦች መቆጣጠር ማረም መቅጣት ቢቻል፡፡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ደብር ያለው አሠራር በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ ወጥና የተሟላ መረጃ ሊኖረው የሚችል ባለሙያ የተጠናና የታገዘ አሠራር በመዘርጋት በገጠርዋ የምትገኘው ደሳሳዋና በከተማ በዘመናዊ ሕንፃ የተገነባው ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱም ክብሩም አንድ ዓይነት በመሆኑ በማእከል የተጠናና ገጠሩንም፣ ከተማውንም የአካተተ የአገልግሎት ክፍያ በማደላደል በገጠሩም ሆነ በከተማ አገልግሎት የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

ዛሬ የአብነት ትምህርት ቤቶች በየቦታው እየተዘጉ መምህራንና ተማሪዎች እየተሰደዱ ናቸው፡፡ እነዚህ የአብነት ትምህርት ቤቶች የነገ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች  የሚወጡበት ቦታዎች ናቸው፡፡ ምእመናኑም በየገጠሩ አገልጋይ፣ እረኛ፣ አስተማሪ በማጣቱ  በቀበሮ እየተነጠቀ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በገጠር አካባቢ ስብከተ ወንጌል አልተስፋፋም፡፡ በጥቂቱም ተስፋፍቶ የምናየው በከተማ አካባቢ ብቻ ነው፡፡ አገልጋይ ባለመኖሩ ወንጌል ባለመስፋፋቱ ብዙ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን በመሳሰሉ ነገሮች ላይ ጠንከር ያለ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ ስለዚህ ተመራጩ ፓትርያርክ እነዚህን ችግሮች በሂደት ለመቅረፍ ቆርጠው ሊነሡ ይገባል፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስም በርካታ ተግዳሮቶች ይጠብቁታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ህልውና መሠረት ቅዱስ  ሲኖዶስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ የሚሆኑበትን ነገር መከታተል ይገባዋል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምንሰማው በሲኖዶስ ተወስነው፣ ተግባራዊ ያልሆኑ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ካህናቱ እንዲሁም ምእመናኑ ይፈተኑበታል፡፡ ለሲኖዶስ የሚሰጠውን ክብርም ያዛባዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስን መንፈስ ቅዱስ ነው የሚመራው በመሆኑም  መንፈስ ቅዱስ የሚወሰነው ተግባራዊ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ መንፈስ ቅዱስ ነው የሚወሰነው የሚለው አጠያያቂ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወሰኑትን ውሳኔዎች በሙሉ ተግባራዊ ሊያደርግ፣ ተግባራዊነታቸውንም ሊከታተል ይገባል፡፡

 

ይህን ትልቅ ሓላፊነት ለመወጣት ከንጉሥ ሰሎሞን መማር ያስፈልጋል፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ሲሾም እግዚአብሔር «ይህን ሕዝብ የሚያስተዳድርበትን ጥበብ ስጠኝ» ብሎ ነው የጠየቀው፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን ይህችን ሃይማኖት ጠብቀው አቆይተዋል፡፡ ዛሬም አባቶቻችን ይህንን ሓላፊነት ለመወጣት ለተተኪው ትውልድ ሳትሸራረፍ፣ ሳትከለስ፣ ሳትበረዝ ሊያስተላልፉ የሚችሉበትን ኃይልና ጥበብ እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው መለመን ይገባቸዋል፡፡

 

በአጠቃላይ ይህ የፓትርያርክ ምርጫ የተሳካ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔርም መልካም መሪ እንዲሰጠን ሃይማኖታችን ከጎበጠችበት የምትነሣበትን ትንሣኤ እንድናገኝ በጸሎት እንትጋ፡፡ አስተዋይ መንፈሳዊ መሪ፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚያስብ፣ መንጋውን ሊጠብቅ የሚችል ትጉህ እረኛ እንዲሰጠን መንጋውም የእረኛው ቃልን የሚሰማ አስተዋይ እንዲሆን እግዚአብሔርን እንለምነው፡፡

 

  • ምንጭ፡- ሐመር 20ኛ ዓመት ቁጥር 6 ጥቅምት 2005 ዓ.ም.

ዕጣ በቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓት

ታኅሣሥ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ምትኩ አበራ

ዕጣ /እጻ/ የሚለው ቃል ዐፀወ ዕጣ ተጣጣለ /አወጣ/ ከሚለው ግስ የወጣ ሲሆን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በግእዝ አማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው “አጭርና ቀጭን እንጨት፤ ከመካከለኛ ጣት የሚበልጥ፤” ብለው ይፈቱታል፡፡ ዕጣ እድል ድርሻም ሊባል ይችላል፡፡ የዕጣ አሠራር ከክርስቶስ ልደት በፊት ከኦሪቱ ጊዜ ጀምሮ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ በጥንት ጊዜ ሰዎች ዕጣን በእንጨት፣ ጽሑፍ ባለበት ድንጋይ /ጠጠር/ ይጥሉ ነበር፡፡

 

የዕጣ ሥርዓትን ለሰዎች ያስተዋወቀው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ “እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፡- ለእነዚህ በየስማቸው ቁጥር ምድሪቱ ርስት ሆና ትከፈላለች… ለሁሉ እንደቁጥራቸው መጠን ርስታቸው ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን ምድሪቱ በዕጣ ትከፈላለች፤ በብዙዎችና በጥቂቶች መካከል ርስታቸው በዕጣ ትከፈላለች”፡፡ /ዘኁ.26፥52-56/ ይህንን ትእዛዝ እግዚአብሔር ሲያስተላልፍ ሥርዐተ ዕጣውን የሚመሩትንም ጭምር “….ርስት ትሆናችሁ ዘንድ በዕጣ የምትደርሳችሁን ምድር…. የሚከፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ፡፡” በማለት አሳውቋቸዋል፡፡ /ዘኁ.30፥2-16/ በዚህ ዐቢይ ትእዛዝ መሠረት ተሿሚዎቹ በተፈጥሮ ወጣ ገባ፣ ጭንጫና ለም ወዘተ… የሆነችውን ምድር ከሐሜት በጸዳና ከአድልኦ በራቀ መለኮታዊ ሥርዓት ርስቱን አከፋፍለዋል፡፡

 

ከዚህም ውጪ እስራኤላውያን በዕጣ ለእግዚአብሔር የሚሠዋውን ከማይሰዋው ለይተውበታል፤ ዘሌ.16፥8፣ ንጉሣቸውን መርጠውበታል፤ 1ሳሙ.10፥11-21፣ ወንጀለኞችን ለይተውመበታል፤ /ኢያ.7፥18፣ ዮና.1፥7/፣ ለጦር ሥራ ተጠቅመውበታል፤ 1ኛ ዜና.24፥19 መሳ.20፥9-10፣ ንብረት ለመካፈል ተጠቅመውበታል፡፡ ማቴ.27፥35፣ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በእግዚአብሔር ትእዛዝና ፈቃድ ሲሠራበት የቆየው ዕጣ ወደ ሐዲስ ኪዳን ዘልቆ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

 

ዕጣና ጥቅሙ

በዕጣ መመዘኛዎቹን ተከተለን በአግባቡ መጠቀም ከቻልን በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ዕጣ የፈቃደ እግዚአብሔር ማወቂያ መንገድ ሆኖ በሐዋርያትም ዘመን አገልግሎ ነበር፡፡ ሐዋርያት ይሁዳ ረግጧት በሄደው ዕድል ፈንታ ለመተካት የራሳቸውን ዕውቀት ተጠቅመው ሁለት ሰው /ማትያስንና ዮሴፍን/ በእጩነት ካቀረቡ በኋላ፤ የሚፈለገው አንድ ብቻ ነበርና “የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ሥፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው” ብለው ጸለዩ፡፡ ከዚያም “ዕጣን ተጣጣሉላቸው ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ” /ግብ.ሐዋ.1፥23-26/ ፈቃደ እግዚአብሔር በዕጣው ላይ ተገለጠ፡፡

 

ዕጣ ዳኛ ሆኖ ያለ አድልኦ ይፈርዳል፤ ሰው ከፈረደው ፍርድ ይልቅ በዕጣ የተገኘን ፍርድ ሰው አክብሮ ያለማጉረምረም ይቀበለዋል፡፡ እስራኤላውያን በኢያሱ አማካይነት ምድረ ርስትን ሲከፋፈሉ በዕጣ ባይሆን ኖሮ መሬት ባላት ወጥ ያልሆነ አቀማመጥ ሳቢያ የሚፈጠረው ጦስ ያስከተለውን ጉዳት እናነብ ነበር፡፡ ያ ሳይሆን የቀረው ግን ርስት የማከፋፈሉ ሥራ በፈቃደ እግዚአብሔር ላይ ተመሥርቶ በዕጣ በመሆኑ ነው፡፡

 

ዕጣ ሐሜትን፣ ጭቅጭቅን፣ አድልዎን ከማስወገዱ በተጨማሪም አስተማማኝና አምላካዊ ውሳኔን አውቆ በእምነት ለመቀበል ያስችላል፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ሰቃልያኑ ጭፍሮች ያቺን ሰብአሰገል ለጌታ የሰጡትን ከተግባረ ዕድ ነጻ የሆነች ቅድም፤ ስፍም የሌላትን ወጥ የሆነች ቀሚስ እንዳይቀዷትም እንዳይተውአትም ሳስተው ዕጣ ተጣጣሉ፡፡ “ጭፍሮቹም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡን ደግሞ ወሰዱ፡፡ እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም፡፡ ስለዚህ እርስ በእርሳቸው ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ፡፡….” እንደተባለ፡፡ /ዮሐ.19፥23-24/

 

ጭፍሮቹ ነገሮቹን በትንቢቱ /መዝ.24/ መሠረት የፈጸሙት ይሁን እንጂ የዕጣውን አሠራር ባይጠቀሙ ኖሮ ቀሚሷን ሁሉም ከወደዷት ለመውሰድ ሲሞክሩ የሚፈጽሙትን ሌላ የእርስ በእርስ ጠብ ልናነብ እንችል እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡ ስለዚህ ዕጣ አንድ ልብ አንድ አሳብ ለመሆን ይሰጣል፡፡

 

መንፈሳዊ የዕጣ ሥርዓት የሚኖሩት ዋና ዋና መርሖዎች

1.    በዕጣው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመረዳትና ያንንም ለመቀበል ተዘጋጅተን የሚፈጸም በመሆኑ ጸሎት የዕጣ ሥርዓት ቁልፍና ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ ብላታ ወልደጊዮርጊስ እንዲህ ይላሉ

 

“አሳብ እንደ አንደበት በከንፈር፣ እንደ ዐይን በቅንድብ፣ እንደዦሮ በጣት አይዘጋም፡፡ አሳብ ረቂቅ ስለሆነ የነፍሳችን እንጂ የሥጋችን ሥራ አይደለም፤ ስለዚህ በግዙፉ ሥጋችን ልናግደው አንችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ትርምስ ውስጣችን ሲያነቃ በቅድሚያ እግዚአብሔርን ሁሉ የሚቻልህ አምላኬ ሆይ የምችለውንና የምሠራውን ብቻ አሳስበኝ የተበተነውንና የሚባክነውን አሳብ ወስንልኝ ብለን እንለምነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡ ተብሏልና ተገቢውን ጸሎት ካደረጉ በኋላ አሳብን በዕጣ መቁረጥ ተገቢ ነው፡፡ /1ጴጥ.5፥7/ አንዳንድ ጊዜ ሁለት በጎ አሳቦችን ስናወጣና ስናወርድ እንገኛለን፡፡ የሁለቱም አሳቦቻችን ጥቅምና ጉዳት ተካክሎ ሲታየን እግዚአብሔር በማትያስ መመረጥ ጊዜ በሐዋርያት ኅሊና እንዳደረገው መምረጥን ለእሱ እንድንተውለት ሲሻብን ነውና በጸሎት ለምነን በዕጣ መቁረጥ ተገቢ ነው፡፡”

 

2.    ከብዙ ነገሮች አንድን ነገር ለመምረጥ የሚፈጸም ሳይሆን በእኛ አቅም ለምንሻው ግልጽ ዓላማ ግልጽ መስፈርት አውጥተን ከብዙ ጥቂቶችን ከለየን በኋላ የሚያጋጥመንን ማመንታት በእርግጠኝነት ለማለፍ በመሆኑ ከሁለት ወይም ከሦስት ሰዎች ወይም ሁኔታዎች የበለጡ ነገሮችን በዕጣ መለየት ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በተመረጡ ሰዎች አለማመን ብቃታቸውን መጠራጠር ወ.ዘ.ተ. ስለሚከተል ይህ እንደ መርኅ መያዝ የሚችል ነው፡፡ መጽሐፍም “ዕጣ ክርክርን ትከለክላለች” ይላል፡፡ መክ.18፥18

 

3.    የዕጣ ሥርዓት በራሱ ሁል ጊዜ ከአድልዎ የጸዳ ቢመስልም ከዕጣ ዝግጅትና አወጣጥ ጋር የተያያዙ ሥርዓቶችን በፍጹም ታማኝነትና ግልጽነት መፈጸም ይገባቸዋል፡፡ በዕጣው መካተት ያለባቸው ተመራጮች መካተታቸው፣ ዕጣው በምንም መሥፈርት የተለያየ ያልሆነና አንዱ ከአንዱ መለያ የሌላቸውና ለማንኛችንም ወገኖች ወጥተው ከመገለጣቸው በፊት ሥውር ሊሆኑ ይገባል፡፡ “ዕጣ በጉያ /በስውር/ ይጣላል፤ መደብዋ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” እንዲል፡፡ /ምሳ.16፥3/ የዕጣ አሠራር ከዚህ ሥርዓት ሲወጣ ከባሕር የወጣ ዓሣ ይሆናል፡፡

 

4.    ሲያወጡም ከአድልዎ ነጻ በሆነና ሁሉም በሚያምንባቸው አካላት ሊሆን ይገባል፡፡

ብዙ ጊዜ የተጠቀለለን ዕጣ በሕፃናት ማስወጣት የተለመደ ተግባር ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ሰዎች ተንኮል ባልተቀላቀለው ፍቅር እንወድሃለን ሲሉ የሚያከብሩትንና የሚወዱትን እንግዳ በሕፃናት እጅ እቅፍ አበባ በማበርከት ይቀበሉታል፡፡ ዕጣን ማንኛውም ሰው ሊያወጣው ሲችል ሕፃናት የተመረጡበት ምክንያት ግን ለሁላችንም ግልጽ ይመስለናል፡፡ ሕፃናት ንጽሐ ጠባይ ያላደፈባቸው ስለሆኑ እግዚአብሔር በእነሱ ላይ አድሮ በዕጣው አማካኝነት እንዲፈርድልን ከማሰብ የተነሣ ነው፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ራሱ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ትገቡ ዘንድ አትችሉም” /ማቴ.18፥3/ በማለት እንደ ሕፃናቱ ኅዳጌ በቀል፣ የዋሕ፣ ንጹሕና ታማኝ እንድንሆን ይመክረናል፡፡ በየ ዓመቱ ሚያዝያ 3 ቀን በዓለ ዕረፍቱ የሚታሰብለትና በአንድ ወቅት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበረው አባ ሚካኤል በስንክሳር መጽሐፍ የሰፈረው ታሪኩ የዕጣና ሕፃናትና አንድነት ያስረዳናል፡፡

 

አባ ሚካኤል ከታናሽነቱ ጀምሮ በገዳመ አስቄጥስ በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን መንኲሶ በተጋድሎ የኖረ አባት ነው፡፡ ከእርሱ በፊት የነበረው ሊቀ ጳጳስ አባ ገብርኤል ሲያርፍ የቅዱስ ማርቆስ መንበር ለ4 ወር ባዶ ሆኖ ቆየ፡፡ ሊቃውንት አባቶች በመንበሩ ላይ የሚተካ ሰው ከየገዳማቱ በመምረጥ ብዙ ከደከሙ በኋላ ሦስት ገዳማውያን አባቶችን በእጩነት አቀረቡ፡፡ ከዛም የሦስቱንም ስም በክርታስ /ወረቀት/ ጽፈው በመሠውያው /ታቦቱ/ ላይ ካኖሩ በኋላ ለሦስት ቀን እየጸለዩና ቅዳሴ እየቀደሱ እግዚአብሔር የወደደውን ያደርግ ዘንድ በመማለድ ቆዩ፡፡ ከሦስቱ ቀናት በኋላ አንድ ታናሽ ብላቴና ጠርተው ከእነዚህ ከሦስቱ ስሞች አንዱን አንሥተህ ስጠን አሉት፡፡ ያም ብላቴና የአባ ሚካኤል ስም ያለበትን ክርታስ አንሥቶ ሰጣቸው፡፡ ሁሉም እግዚአብሔር እንደመረጠው አውቀው ይገባዋል ብለው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት፡፡ ይለናል፡፡

 

ዕጣና ውጤቱ

ዕጣ የጣልንበት አሳብ በዕጣው ሲገለጥ ውጤቱ እኛ የጠበቅነውም ያልተቀበልነውም ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ሁል ጊዜም ትክክል መሆኑን ካመንን ምንም ይሁን ምን ውጤቱን መቀበል ግዴታችን ነው፡፡ ለዕጣ የምናቀርበው አሳብ ወይም ሥራ በጎ ከሆነና እንደ ሐዋርያት በጸሎትና በተገቢው ሥርዓት የተደገፈ ሲሆን እግዚአብሔር በዕጣው ውስጥ ተምኔታችንን ይፈጽምልናል፡፡

 

የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ እስካሁን ድረስ የዕጣ ሥርዓቱን አልተወም፡፡ የሕዝብ ድምፅ የሚሰጠው ከዕጣ በፊት ነው፡፡ በሐዋርያት ቀኖና እንደተገለጸው ለከፍተኛ የክህነት መዓርግ የሚታጭ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ይሁንታ ማግኘት አለበት፡፡ በዚሁ መሠረት ለፓትርያርክነት የሚታጩትን ሦስት በሰዎች ለመምረጥ ከአባቶች ጀምሮ ምእመናኑ ሁሉ ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ በዚሁ መሠረት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡት አባቶት ይለያሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የሦስቱም ስም ይጻፍና ሥርዓተ ሲመቱ በሚፈጸምበት ቤተ ክርስቲያን መንበር ላይ ተደርጎ ሁለት ሱባኤ /ለ14 ቀናት/ ሁሉም ሲደልዩ ይሰነብታሉ፡፡ በአሥራ አራተኛው ቀን በዕለተ እሑድ ጸሎተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ በዓይነ ስውር ሰው ወይም ለዚሁ በተዘጋጀ ሰው ዕጣው ይወጣል፤ በዕጣው የተመረጠው ሰው ፓትርያርክ ይሆናል፤ ሕዝቡም ይደልዎ ብለው ይቀበሉታል፡፡

 

አሁን በፕትርክና መንበር ላይ ያሉት የእስክንድርያው ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ ሣልሳዊ ከሌሎች ሁለት አባቶች ጋር ለዚህ ታላቅ ሰማያዊ ሥልጣን ሲታጩ የግብፅ ምእመናንም ይሁኑ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ማለት ይቻላል አቡነ ሽኖዳ ከምእመናን ጋር ከነበራቸው ሰፊ ግንኙነት አንጻር ፓትርያርክ እንዲሆኑላቸው ቀድመው /ቢመኙም/ በዕጣ የመለየቱ ሥርዓት በግብፅ ቤተ ክርስቲያን የተቀመጠ ግዴታ ስለሆነ ተገቢው ሥርዓተ ጸሎት ደርሶ እግዚአብሔር የወደደውን ያደርግ ዘንድ ዕጣው እንደተጣለ ይታወቃል፡፡

 

በጣም የሚገርመው የሁሉም ምኞት የተሳካና ዕጣው የአቡነ ሽኖዳን ስም ይዞ ብቅ አለ፡፡ እግዚአብሔር በዕጣው ላይ ፈርዶ የልጆቹን የልቡናቸውን መልካም መሻት ፈጸመ፡፡ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንም ሆነ ሊቃ ጳጳሳቱ የእግዚአብሔርን ምርጫ በምስጋና ተቀበሉት፡፡ ውጤቱ ካሰቡትና ከተመኙት በተቃራኒው እንኳን ቢሆን መቀበል ግን ግዴታቸው ነው፡፡

 

አንዳንድ ሰው ዕጣውን ለመጣል ይቸኩላል እንጂ ለዕጣው አጣጣል ካለመጠንቀቁም ሌላ ውጤቱን በጸጋ መቀበል እያቃተው ይሰነካከላል፡፡ ተገቢውን ሥርዓት ፈጽመን እግዚአብሔር በዕጣው እንዲፈርድ ድርሻ ሰጥተነው ስናበቃ በዕጣ በቆረጥነው አሳብና ተግባር ክፉ ቢያገኘን የእግዚአብሔር ፍርድ መሆኑን አውቀን፣ በጎም ቢያገኘን እሱን አመስግነን በጸጋ መቀበል እንጂ ምኞታችንና የዕጣው ሥርዓት ከመግባታችን በፊት ያስጨንቁን ከነበሩት መንታ አሳቦችና ወደ ዕጣ እንድንገባ ምክንያት ከሆነን ተግባር ይልቅ ይህ ምሬታችን ብርቱ ፈተና ሆኖን ከእግዚአብሔር እቅፍ ሊያወጣን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ የከፋ እንዳያገኘን “ምርሐኒ ፍኖተ እግዝኦ እንተ ባቲ አሐውር” /አቤቱ የምሄድባትን መንገድ አንተ ምራኝ/ እያልን ቆራጥ ልቡናን ከፈጣሪ መለመን አለብን፡፡

 

የማይገባ ዕጣ

በምንኖርባት ዓለም ለሰዎች ልጆች የተፈጠሩትንና የሚሆኑትን ስናስብ ለመልካም እንጂ አንድም ለጥፋት የሆነና የሚሆን የለም፡፡ /ዘፍ.1፥4፣ 16፣ 19፣ 21፣ 25፣ 31/ ሁሉም ለመልካም ቢፈጠርም ቅሉ በአግባቡና በሥርዓቱ ስለማንጠቀምበት አንጻራዊ በሆነ መልኩ መልካሙ መጥፎ፣ ጠቃሚው ጎጂ፣ ለጽድቅ የሆነው ለኀጢአት ሲሆንብንና ስናደርገው ይታያል፡፡ “በጨለማ ለሚኖሩት ብርሃን ወጣላቸው” ተብሎ የተነገረለት ጌታ አይሁድ ባለማወቃቸው ምክንያት “የሚያዩ እንዲታወሩ፤ የማያዩ እንዲያዩ መጥቻለሁ” ብሎ ሲናገር እናነባለን፡፡

 

እንደዚሁም ሥርዓተ ዕጣ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም እንዳለው ልናውቅ ያስፈልጋል፡፡ እንዲያውም ዕጣ በተሳሳተ መንገድ እየተፈጸመ በማየታቸው ብቻ አብዝተው የሚናገሩት የዕጣን አላስፈላጊነት ነው፡፡ በጥቅሉ ዕጣ አያስፈልግም ተብሎ መደምደም ባያስኬድም ስለማይገቡ ዕጣዎች ገልጦ ማስረዳት ግን ግድ ነው፡፡

 

ዕጣ አውጭው ጠንቋይ፣ ዕጣው የጠንቋይ ጠጠር ሲሆን ጐጂም ኀጢአትም ነው፡፡ ቀደም ሲል በገጠሩ አሁን አሁን ግን በሚያሳዝን መልኩ በየከተሞቻችን ሰዎች ለትዳር የፈለጉትን አጋር ወደ ጠንቋይ ቤት ተጉዘው “ዕጣ ክፍሌ ማን ነው?” በማለት ለማግኘት ሲሞክሩና ሚስት ወይም ባልሽ ዕጣ ክፍልህ /ሽ/ አይደለም /ችም/ እየተባሉ ትዳራቸውን ፈተው ልጆቻቸውን ሲበትኑ እያስተዋልን ነው፡፡ “ዕጣ”ን ለተቀደሰ ዓላማ እንጂ ለክፋት ለማዋል መሞከርም አደጋው ከፍ ያለ ነው፡፡

 

ሌላው የማይገባ ዕጣ ደግሞ ከክፉ ዓላማ ተነሥተን ክፉንም ለመፈጸም ስንጠቀምበት ነው፡፡ ክፉ ማለትም ሕገ እግዚአብሔር ለሚያስጥሰን ለየትኛው ተግባር ማለታችን ነው፡፡

 

ይህንንም ከንጉሥ አርጤክስስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሐማ ውድቀት መማር ይቻላል፡፡ ሐማ መርዶክዮስ ለምን እግሬ ሥር ወድቆ እጅ አልነሳኝም በሚል ከንቱ ስሜት ተነሥቶ በመቶ ሃያ ሰባት ሀገሮች የሚኖሩ አይሁዳውያንን በጅምላ ለማስጨፍጨፍ የትኛው ጊዜና ወቅት ምቹ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ በቤተ መንግሥቱ ዕጣ አስጥሎ ነበር፡፡ “ሐማ. በአርጤክስ መንግሥት የነበሩትን አይሁድን ሁሉ ሊያጠፋ ፈለገ፡፡…. ከመጀመሪያው ወር ከኒሳን ጀምሮ በየዕለቱና በየወሩ እስከ ዐሥራ ሁለተኛው ወር እስከ አዳር ድረስ በሐማ ፊት ፉር የተባለውን ዕጣ /በአገራችን እንደጠጠር ጣይ የምንለው ዓይነት ማለት ነው/ ይጥሉ ነበር፡፡” /መጽ.አስ.3፥6-7/ ዳሩ ግን ሥርዓተ ዕጣው ከመነሻው የተበላሸና ዓላማው እግዚአብሔር የማይወደው ስለነበረ ውጤቱ ከፍቶ ሐማን በግንድ ላይ አሰቅሎ ተደመደመ፡፡ ሐማ የቤተ መንግሥቱን አዋቂዎች ሰብስቦ ዕጣ ሲያስጥል የነበረው አይሁድን በጅምላ ለመጨፍጨፍ የሚያስችለውን ጊዜ በመፈለግ መሆኑ ከላይ ተገልጧል፡፡

 

ማጠቃለያ

ዕጣ ውሳኔ ለሚያስፈልገው ለሁሉም ነገር የምንጠቀምበት ሥርዓት አይደለም፡፡ ለታወቀና ግልጽ ለሆነ ነገር ላንጠቀም እንችላለን፡፡ አንጥረን ለለየናቸው በደረጃ እኩል ለሆኑ ለምናመነታባቸው ጉዳዮች ብንጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ወይም በሥርዓት ተደንግጎ የሆነውን ደረጃ እኛ ካከናወነው በኋላ ቀሪውን እግዚአብሔር እንዲገባበት ስንሻ ተግባራዊ የምናደርገው ይሆናል፡፡ ወይም ውሳኔያችን ክርክርና ፍቅር ማጣትን የሚያስከትል ከሆነ በዕጣ እናስማማዋለን፡፡ ከላይ በዝርዝር እንዳየነው ዕጣ በፈቃደ እግዚአብሔር ለሰዎች የተሰጠ የዳኝነት ሥርዓትና የመንታ ልብ መቁረጫ መሣሪያ ከሆነ በሃይማኖታዊውም ሆነ በማኅበራዊው ሕይወታችን ለበጎ ዓላማ ብንጠቀምበት መልካም ነው፡፡ የዕጣ ሥርዓት በዓውደ ዓመት ጊዜ የቅርጫን ሥጋ ለመከፋፈልና ለዕቁብ ቤት አንዳንዴም የሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን በየዓውደ ምሕረቱ ከሚጠቀሙበት የገቢ ማስገኛ ባለፈ መልኩ ለተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ዓላማዎች በሐዋርያት ዘመን ይደረግ እንደነበረው ከብርቱ ጸሎትና ምልጃ ጋር ቢተገበር መልካም ነው፡፡ በነቢያትና በሐዋርያት የነበረውን ሥርዓትና ለረጅም ዘመንም በሀገራችን የነበረውን ትውፊት ከማስጠበቅ አንጻር በአፈጻጸም ክፍተት ሊኖርባቸው የሚችሉ አሠራሮቻችን ውስጥ ሁሉ ሥራ ላይ እንዲውል ሐዋርያት በሚታሰቡበት በዚህ ወቅት ለመጠቆም እንወዳለን፡፡

 

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 17ኛ ዓመት ቁጥር 2 ግንቦት – ሰኔ 2001 ዓ.ም.

debube omo 2 1

በደቡብ ኦሞ ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች ተጠመቁ

ታኅሣሥ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


debube omo 2 1በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም አስተባበሪነት፤ በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙና በልዩ ልዩ ቤተ እምነቶች ውስጥ የነበሩ ከሰባት መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ሥርዓተ ጥምቀት ተፈጽሞላቸው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመለሱ፡፡ በሜጸር የቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም በቶልታ የቅድስት ሥላሴ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ኅዳር 23 ቀን 2005 ዓ.ም. በተከናወነው ሥርዓተ ጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ያገኙ ሰዎች በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማእከልና በሰንበት ትምህርት ቤት ጥምረት በሁለት ልዩ ልዩ የስብከት ኬላዎች አማካኝነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሲማሩ የቆዩ ናቸው፡፡

 

debube omo 2 2አዳዲስ ተጠማቂያኑ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አተያየት ፡ በተፈጸመላቸው ሥርዓት ጥምቀት እጅግ በጣም መደሰታቸውን ገልጸው፤ በአቅራቢያቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲታነፅላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል  “የምእመናኑ ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ሲቋቋሙ አብሮ መተዳደሪቸውም ሊታሰብ ይገባዋል፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንዳስተዋልነው ምእመናን በቅንነት በዚህ ቦታ እንዲህ ያለ ታቦት ይተከልልን እኛ ሙሉ ወጪውን እንሸፍናለን በማለት ያሳነፅዋቸው አብያተ ክርስቲያናት ምእመናኑ በሕይወት እስካሉ ድረስ ያገለግሏቸውና፤ እነሱ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ሲለዩ አገልግሎቱ እየተቋረጠ አብያተ ክርስቲያናቱ እስከ መዘጋት የደረሱባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያኗ እንዴት ትገለገላለች? በሚለው ላይ ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ የቤተ ክርስቲኒቱ ልጆች ሊያስቡበት ይገባል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም ሁል ጊዜ በልመና መተዳደር የለባቸውም” ብለዋል፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም፤ የፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆኑት ሊቀ ብርሃናት ሃይማኖት ተስፋዬ ስለ ተከናወነው አገልግሎት ሲናገሩ “ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራሙ በዐስር ዓመታት ለመፈጸም ከያዛቸው ዕቅዶች አንዱ በጂንካ ማእከል አማካኝነት ለንዑሳን ክርስቲያኖች በአቅራቢያቸው የስብከት ኬላዎችን (ቃለ እግዚአብሔር የሚሰሙባቸው ቤቶች)  እንዲቋቋምላቸውና መሠረታዊ የሃማኖት ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ነበር፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ቸርነት የተፈጸመ ነው፡፡ በቅርቡም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ሀገረ ስብከት በማንዲራና ድብጤ ወረዳዎች ሲያስተምራቸው ለነበሩት ሰዎች በቅርቡ የማጥመቅ ተግባርን ለመፈጸም ዝግጅቱ ተጠናቋል” ብለዋል፡፡

 

debube omo 2 4የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያው በቶልታና ሜጠር ቀበሌዎች ላስጠመቃቸው አዳዲስ ምእመናን በቀጣይ ለሚፈጽምላቸው  እገዛ አስመልክተው ሊቀ ብርሃናት ሃማኖት ተስፋዬ እንዲህ ብለዋል፡፡ “የልጅነት ጥምቀት አግኝተው በቅርቡ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለገቡ ምእመናን በአቅራቢያቸው ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙባቸውን አብያተ ክርስቲያናትን ማነፅና እነሱንም ማጽናት ይጠበቅብናል፡፡”