ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል ስለምትገኝበት ሁኔታ ዐውደ ጥናት ተካሄደ
ግንቦት 7/2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል የምትገኝበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ተካሔደ፡፡ አውደ ጥናቱ በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን በዋና ክፍሉ ስር ከሚገኙት ዴስኮች መካከል የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ አማካይነት ቀርቧል፡፡
የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ በመደበኛና በኢመደበኛ አባላት የተጠናከረ ክፍል እንደመሆኑ በኦሮሚያ ክልል ቤተ ክርስቲያናችን ምን ላይ እንደምትገኝ የሚያሳይ ጥናት ይዞ እንዲቀርብ በተሰጠው ሓላፊነት መሠረት ጥናቱን ይዞ መቅረቡን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ገልጸዋል፡፡ የጥናቱ ዋነኛ ዓላማን አስመልክተው ቤተ ክርስቲያናችን በኦሮሚያ ክልል ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ መዳሰስ፤ ችግሮቹን ለመፍታት ምን መደረግ እንደሚገባና ምዕመናን በአንዳንድ እምነቶች እንዳይወሰዱ በመረጃ የተደገፈ ምላሾችን መስጠት የሚያስችል ጥናት እንደሆነ ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ ሓላፊ የሆኑት ቀሲስ ምስጋናው አገሳ እንደገለጹት ዴስኩ የትርጉም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ፣ በተለይም ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞችና እኅቶችን በማሰባሰብ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ በመተርጎም ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም 5 መፃሕፍትን ተርጉመው ለምእመናን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና ይህ ጥናት በእነዚሁ አባላት አማካይነት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥናት አቅራቢዎቹ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ያሏቸውን የሚያሳይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ክልሉ ሰፊ እንደመሆኑ ችግሮቹም ስፋት ያላቸው ስለሆነ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ያሏቸውንም በሁለት በመክፈል ውስጣዊ ችግሮችና ውጫዊ ችግሮች በማለት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ምዕመናን ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀር መስማትና መናገር ባለመቻላቸው በቋንቋቸው የሚገባውን አገልግሎት መስጠትና ማግኘት ያለመቻሉ፤ ንስሐ ለመግባት በአስተርጓሚ እስከማከናወን መድረሱ፣ በቋንቋው የተዘጋጁ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትና የቋንቋው ተናጋሪ አገልጋይ ያለመኖር፣ የምዕመናን ባህልና አኗኗር ማዕከል ያደረገ ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት ያለመቻሉ፤ በተለያዩ እምነቶችና ባዕድ አምልኮዎች መጠመዱ…. የመሳሰሉት እንደሆኑ በጥናት አቅራቢዎቹ ተዳስሰዋል፡፡
ከተለያዩ ዋና ዋና ክፍሎች የተገኙት የማኅበሩ አባላት በጥናቱ ላይ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን እንዲሁም የመፍትሔ ዐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ከጥናቱ አቅራቢዎችም ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም መፍትሔዎቹን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በክልሉ ምዕመናን በቋንቋቸው የሚገለገሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በተወላጆቹ /በቋንቋው ተናጋሪ አገልጋዮች/ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል፣ በኦሮምኛ ቋንቋ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማዘጋጀትና ማሰራጨት፣ አገልጋዮችን ለማፍራት ማሠልጠኛ ተቋም መክፈት፣ በግቢ ጉባኤያት ለሚገኙ ተማሪዎች የአብነት ትምህርት መስጠት፣ ተጨባጭ ጥናቶችን በተጠናከረ ሁኔታ ማካሔድ…… የመሳሰሉትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የተገለጹት ችግሮችና ከአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የቀረቡ ጥያቄዎችና የመፍትሔ ዐሳቦችን በማጠናከር ከማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ ጋር ተነጋግሮና አጽድቆ በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንደሚሸጋገር ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ የገለጹ ሲሆን ጥናት አቅራቢዎቹንና የየክፍሉ ተወካዩችን በአውደ ጥናቱ በመገኘታቸው አመስግነዋል፡፡




የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደትና የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምሥረታ እሑድ ሚያዚያ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በድምቀት ተከበረ፡፡ “ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት አብረን እንሥራ በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን ህዝብ ግንኙነት ክፍል የተዘጋጀው መርሐ ግብር በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት ተጀምሮ በዝማሬ በስብከተ ወንጌል አገልግሎትና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምክር ተካሒዷል፡፡
ብፁዕ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ ሊሞቱ ሲሉ ካስተማሯቸው ተማሪዎቻቸው /ማኅበረ ቅዱሳንን ከመሠረቱት/ መካከል ሁለቱን፣ አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ አቅፈው፣ ጸሎት አድርገው የሁለቱን ራስ አጋጭተው በመያዝ” በሉ ልጆቼ መቃብሬ ላይ እናንተ ናችሁ የምታለቅሱት እኔ ለኩሼዋለሁ እናንተ አንድዱት አሏቸው ለአትክልተ ጎርጎርዮስ፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ምንጭና ግንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም የማኅበረ ቅዱሳን ግንድ ደግሞ አቡነ ጎርጎርዮስ ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚገባውን ምግብ እያበላና እያጠጣ እዚህ ያደረሰው ማኅበር ነው፡፡” /ብፁዕ አቡነ ኤልያስ/
ካልዕ በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ተተኪ ሰባኪያንን ለማፍራት ባደረጉት ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ከግቢ ጉባኤያት 12 ተማሪዎችን በማሠልጠን ጀመረ፡፡ ዛሬ ይህ ጥረት አድጎ በጅማ፣ በአዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በባሕርዳርና በማይጨው ሥልጠናው ተጠናክሮ በመቀጠል በሺዎች የሚቆጠሩ መምህራንን ማፍራት ተችሏል፡፡ ብለዋል፡፡ አያይዘውም በመላው ዓለም በአገር ውስጥና በውጪ የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴ ሲገልጹ ማኅበረ ቅዱሳን 44 ማዕከላት፣ 333 ወረዳ ማዕከላት 181 ግንኙነት ጣቢያዎች 325 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን በማስተባበርና በመምራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከምዕመናን ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ ለተጠየቁ ጥየቄዎች የማኅበሩ ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡