የኅዳር ጽዮን በዓል አከባበር ዛሬም ቀጥሎ በድምቀት ተከብሯል።

ዲ/ን አሉላ መብራቱና በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

ኅዳር 20 ቀን ከዋዜማው ጀምሮ መከበር የጀመረው የኅዳር ጽዮን በዓል ዛሬም ቀጥሎ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

ከትናንትና ማታ 2፡00 ደወል ከተደወለበት ጀምሮ፥ ሊቃውንት ካህናትና ዲያቆናት  ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በስብሐተ ማኅሌት በማድረስ ሌሊቱን አሳልፈዋል።

ሥርዓተ ማኅሌት እንዳለቀ ዛሬ ጠዋት 1፡00 ዑደተ ታቦት ተጀምሯል። ሁለት ዓይነት ዑደት የተካሄደ ሲሆን የመጀመሪያው ዑደት በሐውልት አደባባይ ተደርጓል። በዚያም የአክሱም ሊቃውንትና የሰ/ት/ቤት መዘምራን የክብረ በዓሉን ዝማሬ አቅርበዋል። በቦታው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፥ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።

ሁለተኛው ዑደት ቅዱስ ያሬድ የአርያም ዜማውን ባሰማበት በሙራደ ቃል ተከናውኗል። በዚህኛው ዑደት፥ ቅዱስነታቸው አቡነ ጳውሎስ ሠፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል በሁለት ቋንቋ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ሰጥተዋል። የማዕከላዊ ትግራይ አክሱም ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሰላማ በዓሉን በተመለከተ አጠር ያለ መግለጫ ሠጥተዋል። በቅዱስነታቸው ጋባዥነት ብፁዕ አቡነ ኤልሣዕ ተጨማሪ ትምህርት ያስተማሩ ሲሆን የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው እለቱን አስመልክተው በንባብ ንግግር አሰምተዋል።

ሥርዓተ ቅዳሴ የተጀመረው ከቀኑ 6፡20 ነበር። በእለቱ ሠራየ ዲያቆን ሆኖ የቀደሱትና ከማኅበረ ቅዱሳን የአማርኛ መካነ ድር ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት መ/ር ፍስሐ ጽዮን ደሞዝ እንደገለጹልን፥ በብፁዕ አቡነ ገሪማ፥ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና በብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ የተመራው የቅዳሴ ሥርዓት በ3 መንበር የተከናወነ ሲሆን፥ ሥርዓተ ቁርባኑ በእያንዳንዳቸው በ3 አቅጣጫ በአጠቃላይ በ9 ሙሉ ቀዳሽ ተከናውኗል። የቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የጠጠር መጣያ ቦታ እስከሚታጣ ሙሉ ነበር።
እንደ መ/ር ፍስሐ ጽዮን ገለጻ፥ እርሳቸው በቀደሱበት በዋናው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩት መላው ምእመናን የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ተሳታፊ መሆናቸው ልዩ ድባብ ፈጥሯል። በአጠቃላይ ለምእመናን ቅዱስ ቁርባን ለማቀበል ብቻ ወደ አንድ ሰአት የሚጠጋ ክፍለ ጊዜ እንደወሰደ አያይዘው ገልጸውልናል።
ከዋዜማው ጀምሮ በ100,000ዎች ለሚገመቱ ምእመናን በአራቱም አቅጣጫ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲስጥ ውሏል።  

/ከትናንት ጀምሮ መረጃዎችን ሲያደርሱን ለነበሩና ለተባበሩን ለንቡረ እድ በላይ መረሳ፣ ለመ/ር ፍስሐ ጽዮን ደሞዝና ለመ/ር ዲበኩሉ ልሳነ ወርቅ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናችንን እያቀረብን ጥንቅራችን በዚህ እንቋጫለን/

        

አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል

በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት አሥራ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል ይባላሉ፡፡ ለክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል ማወቅና ዘወትር ማሰብ ተገቢ በመሆኑ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1.     ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተኰርዖት›› የሚለው ቃል ኩርዐ – መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ርእስ ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ 27-24፤ ማር 15-15፤ ሉቃ 23-25፤ ዮሐ 18-39)፡፡
 
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ የእሾህ አክሊል ጐንጉነው ራሱ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል (ማር 15-19)፡፡ የሰው ዘር ከአዳም ጀምሮ በጠላቱ በዲያብሎስ በተጐነጐነ የኃጢአት እሾህ ራሱ ተይዞ ነበርና ይህንኑ ለማስወገድ ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ የሆነ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ ተንኮል የተጐነጐነ አክሊለ ሦክ እንደ ዘውድ ደፋ፡፡ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡
 
2.     ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም፣ ጣቶቻቸው በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተፀፍዖ›› የሚለው ቃል ፀፍዐ በጥፊ መታ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ መልታሕት ደግሞ ፊት ጉንጭ ማለት ነው፡፡
 
ጌታችን ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን መናገር እንደ ስድብ ተቆጥሮበት መላልሰው ፊቱን በጥፊ መትተውታል፡፡ ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው ‹‹ክርስቶስ ሆይ በጥፊ የመታህ ማነው? ትንቢት ተናገርልን›› እያሉ ዘብተውበታል፡፡ በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይቀለድበትና ይንገላታ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጐሰመ፤ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ (ማቴ 27-27)፡፡ ጲላጦስ አሳልፎ ከሰጠው በኋላም አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን›› እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል (ዮሐ 19-2-4)፡፡ አላወቁትም እንጂ እርሱ በመንግሥቱ ሽረት፣ በባሕርዩ ሞት የሌለበት የዘለዓለም አምላክ ነው፡፡
 
3.     ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)

ርኩሳን አይሁድ በብርሃናዊው የክርስቶስ ፊት ላይ በሚያስጸይፍ ሁኔታ ምራቃቸውን እንደተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ወሪቅ›› የሚለው ቃል ወረቀ ካለው ግእዛዊ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም እንትፍ አለ፣ (ተፋ) ማለት ነው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ (ምዕራፍ 5ዐ-6) ‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደተነገረ እየዘበቱበት ምራቃቸውን ተፉበት (ማቴ 27-29-3ዐ፤ ማር 15-19)፡፡ በኃጢአት የቆሸሸውን የሰውን ሕይወት ለማጥራት የመጣው ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ተተፋበት፡፡ በሥራው ከገነት ተተፍቶ፤ ተንቆ፤ ተዋርዶ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኃጢአትን ይቅር የሚል እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢአቱ ተተፋበት፤ ተናቀ፤ ተዋረደ፡፡ እንኳን በአምላክ ፊት በሰው ፊት እንኳን መትፋት እጅግ ያስነውራል፡፡ እርሱ ግን የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የሆነውን ምራቅ ተቀበለ፡፡
 
4.     ሰትየ ሐሞት (መራራ ሐሞት መጠጣት)

ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሳለ ተጠማሁ ባለ ጊዜ መራራ ሐሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ሰተየ›› ማለት ጠጣ ማለት ነው፡፡ ሐሞት የሚለውም አሞት ተብሎ በቁሙ ይተረጐማል፡፡ በመዝሙር 68 ቁጥር 21 ላይ ‹‹ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፣ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ›› ብሎ ነቢዩ ዳዊትን ትንቢት ያናገረ የነቢያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ ሆምጣጤ ተሞልቶበት ተቀምጦ ከነበረው ዕቃ ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው ወደ አፉ አቀረቡለት፡፡ ውኃ አጠጡኝ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፡፡ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም (ማቴ 27-34)፡፡ ጌታችንም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ (ማቴ 27-48፤ ማር 15-36፤ ሉቃ 23-36፤ ዮሐ 19-29)፡፡
 
ቢጠጡት ለዘለዓለም የማያስጠማ ውኃ የሚሰጥ አምላክ፤ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ፤ ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወት ውኃ ምንጭ የሚያድል ፈጣሪ በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውኃ እንኳን የሚያጠጣው የሚያቀምሰውም አላገኘም (ኢሳ 55-1)፡፡ አርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ኳትነው ለነበሩ አባቶቻቸው ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ከአለት ላይ ውኃ አመንጭቶ ያጠጣቸው ክርስቶስ በተጠማ ጊዜ ቀዝቃዛ ውኃ ነፈጉት (ዘዳ 16-1-2ዐ፤ 1ቆሮ 1ዐ-3)፡፡ የዝናማት፤ የባሕርና የውቅያኖስ ጌታ በውኃ ጥም ተቃጠለ፡፡
 
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውሃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ፡፡ በኃጢአት ወድቀው፣ በበደል ረክሰው፣ በነፍሳቸው ተጐሳቁለው፣ መራራ መከራን የሚቀበሉትንና ምረረ ገሃነም አፉን ከፍቶ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ሁሉ ለማዳን መራራ ሐሞትን ቀመሰ፤ ሆምጣጣውንም ጠጣ፡፡ የመረረውን የሰው ልጆችን ሕይወት ለማጣፈጥ የመረረውን መጠጥ ተቀበለ፡፡

5.     ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባው እስኪላጥ ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተቀሥፎ›› የሚለው ቃል ቀሠፈ- ገረፈ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ዘባን›› ደግሞ ጫንቃ፣ ትከሻ፣ ጀርባ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጠው የተገረፈ አይሰቀልም፡፡ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር፡፡ ጲላጣስ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገረፈው፡፡ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ብሎ ከታጠበ በኋላ ክርስቶስን ያለ ኃጢአቱ በመግረፍ ለአይሁድም አሳልፎ በመስጠት ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› እንዲሉ የታጠበ እጁን መልሶ አቆሸሸው (ማቴ 27-28፤ ማር 15-15፤ ዮሐ19-1)፡፡
 
መድኃኒታችን መንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ በእሳት አለንጋ የሚገረፈውን የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ፡፡ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ተገረፈ፡፡ አይሁድ አገረ ገዥያቸው ጲላጣስ ላቀረበላቸው ምርጫ ይፈታላቸው ዘንድ ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣውን ክርስቶስን ሳይሆን ራሱን እንኳን ከምድራዊ ወህኒ ማውጣት ያልቻለውን ወንበዴውን በርባንን መረጡ፡፡ መገረፍ ይገባው የነበረ በርባን ተለቀቀ፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ›› (በኢሳ 5ዐ-6) ተብሎ እንደተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የሰው ልጅ ከሚያድነው አምላክ ይልቅ የሚገርፈውንና የሚዘርፈውን ወንበዴ መርጦ ስለተገኘ ነው፡፡
 
6.     ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)

አምላካችን ኢየሱስ ክርስስቶስ ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተዐርቆተ›› ማለት ታረዘ፤ ተራቆተ ማለት ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ልብሱን ተገፍፎ ዕራቁቱን ቆመ፡፡ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተንተርሶ ይኖር የነበረውን ሰው መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ፣ የጸጋ ሁሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡
 
የሲኦል ወታደሮች የሆኑት አጋንንት የሰውን ልጅ ጸጋ ገፍፈውት ነበርና ጲላጦስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ በሰጣቸው ሰዓት ወታደሮች ልብሱን ገፍፈውታል (ማቴ 27-27)፡፡ የሰው ልጅ ለቀረበለት ምርጫ የሰው ምላሽ ዘራፊው፤ ገራፊው ወንበዴ በርባን እንዲፈታለት ነበር፡፡ ‹‹አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ፣ ደይ እዴከ ኅበ ዘፈቀድከ! እነሆ እሳትና ውኃን አቅርቤልሃለሁ፣ እጅህን ወደ ፈቀድከው ስደድ›› ሲባል የሰው ልጅ እጁን ወደ እሳት ሰደደ፡፡
 
7.     ርግዘተ ገቦ (ጎንን መወጋት)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር መወጋቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ርግዘት›› የሚለው ቃል ረገዘ- ወጋ ከተሰኘ የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ገቦ ማለት ደግሞ ጎን ማለት ነው፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አጠገብ፣ በግራና በቀኙ ሁለት ወንበዴዎች ተሰቅለው ነበር፡፡ ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር ጭናቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ አይሁድ ጲላጦስን በለመኑት መሠረት ጭፍሮቹ የሁለቱን ወንበዴዎች ጭን ጭናቸውን ከሰበሩ በኋላ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ፈጽሞ እንደሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፡፡ ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ስለወጋው ወዲያው ከጎኑ ደምና ውኃ ፈሰሰ (ዮሐ 19-33)፡፡
 
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፤ የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና፡፡ ትልቁ ሞት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በጌታችን ሞት ግን ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ የሞት መውጊያ በሆነ ኃጢአት የሞተውን ሰው ለማዳን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢአት ከነሥሩ ነቅሎ ስለጣለው ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ?›› ተባለ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት ነበርና (1ቆሮ 15-54-55፤ ኢሳ 25-8፤ ሆሴ 13-14)፡፡
 
ከተወጋው የጌታችን ጎን ደምና ውኃ መፍሰሱም የእግዚአብሔርን ልጅነትና የዘለዓለምን ሕይወት አጥቶ የነበረው ሰው ልጅነቱና ሕይወቱ እንደተመለሰለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቆ ልጅነትን፣ ደሙንም ጠጥቶ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛልና (ዮሐ 3-5፤ ዮሐ 6-54)፡፡
 
8.     ተአሥሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን ወደኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ተአሥሮት›› የሚለው ቃል አሠረ (ሲነበብ ይላላል) ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አሠረ ማለት ነው፡፡ ‹‹ድኅሪት›› የሚለው ቃል ደግሞ ተድኅረ- ወደኋላ አለ ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለትና ሰዓት ሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል፡፡ አፍገምግመውታል (ዮሐ 18-12)፡፡
 
በኃጢአት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ ጠላት ዲያብሎስ የሚያፍገመግመውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ይፈታ ዘንድ ሲል መድኃኔዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡
 
9.     አምሥቱ ቅንዋተ መስቀል

መድኃኒታችን በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸውን ጠንካራ የብረት ችንካሮች (ምስማሮች) የሚገልጥ ነው፡፡ ‹‹ቅንዋት›› የሚለው ቃል ቀነወ- ቸነከረ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ መስቀል ማለት ደግሞ ዝም ብሎ የቆመ ግንድ ሳይሆን አሁን በየሥፍራው እንደምናየው ምልክት የተመሳቀለ እንጨት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቸነከረባቸው አምስቱ ችንካሮች ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ፤ ሮዳስ ይባላሉ፡፡ እነዚህም የአምሥቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መሆናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡
 
ሐዋርያው ቶማስ ከትንሣኤ በኋላ ወንድሞቹ ሐዋርያት ስለ ትንሣኤው በነገሩት ጊዜ ‹‹የችንካሩን ምልክት በዓይኖቼ ካላየእንኳን ብንሆን እግዚአብሔር ከኛ ጋር ከሆነ ማንም አያሸንፈንም፡፡ 

የቤተክርስቲያን ፈተና እና ምዕመናን

በዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ

መግቢያ

የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚጀምረው ከዓለመ መላእክት ነው፡፡ ታዲያ ፈተና ሁሌ አብሯት የሚኖር ቤተክርስቲያን መፈተን የጀመረችው በዚሁ በዓለመ መላእክት ነበር፡፡ ዲያብሎስ ትዕቢትንና ሐሰት ከራሱ አንቅቶ መላእክትን «እኔ ፈጠርኋችሁ» በማለት ባሰማው የሐሰት አዋጅ ከሰው ልጅ ወደዚህ ምድር መምጣት ጀምሮ በብሉይ ኪዳንም በርካታ ፈተናዎች ተፈራርቀዋል፡፡

በብሉይ ኪዳን በብዙ ኅብረ ምሳሌ ከአቤል እስከ ክርስቶስ ምጽዓት ስትታሰብ የመጣች ቤተክርስቲያን በሐዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን በመጣ ጊዜ በአማናዊ ደሙ አጽንቶ አካለ ክርስቶስ አድርጓታል፡፡ /ኤፌ 1፥23/ ቤተክርስቲያን ለሰው ዘር ሁሉ በሰማይ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የምታስተምር ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበትና ወደ ሰማያዊው ርስትም የምትመራ የጽድቅ መንገድ ናት፡፡ መቼም ቢሆን ደግ ነገር ሁሉ የሚገጥመው ፈተና አይጠፋምና ቤተክርስቲያን ጉዞዋ ሁሉ በፈተና የታጠረ ነው፡፡

በዚህች አጭር ጽሑፍ ቤተክርስቲያን ፈተና በሚያጋጥማት ወቅት ምእመናን ምን ዓይነት ኑሮ መኖር፤ ምን ዓይነት አቋም መያዝ እንዳለባቸው ለማየት እንሞክራለን፡፡ ካሰብነው ለመድረስም ዋና ዋና የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጮችንና ያስከተሏቸውን ጉዳቶች ለማንሳት እንጀምራለን፡፡
1.    ዋና ዋና የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጮች
የቤተክርስቲያንን ታሪክ ስናጠና ለቤተክርስቲያን የመፈተን ምክንያት የሚሆኑ አካላትንና ድርጊቶችን ቆጥሮና ወስኖ ማስቀመጥ ወይም መገደብ ባይቻልም ጐልተው የሚታዩትን መዘርዘር ግን ይቻላል፡፡ ከእነዚህ የፈተና ምንጮች ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.1 መናፍቃን
«የቤተክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች በጌታ አነጋገር «ጸራዊ» በሐዋርያት አነጋገር «ቢጽ ሐሳውያን» በሊቃውንት አነጋገር «መናፍቃን» ይባላሉ፡፡ የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይሆኑ የቤተክርስቲያን ልጆች መስለው ወይም ከቤተክርስቲያን እምነትና ትምህርት የተወሰነውን የተማሩ ፤የተወሰነውንም ተምረው ያልያዙ ጐደሎዎች ናቸው፡፡ እነርሱም እንክርዳድ ስንዴ መስሎ እንደሚያድግ በክርስቶስ ዐጸደ ወይን በቤተክርስቲያን ውስጥ የበቀሉ አሳሳቾች ናቸው፡፡ » /የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 48/
ብፁዕ አባታችን ከላይ እንደገለጹት እነዚህ ወገኖች ስልታቸውን በየስፍራውና በየዘመኑ እየለዋወጡ ሐመረ ኖኅ ቤተክርስቲያንን በምንፍቅና ማዕበላቸው እያንገላቷትና እያማቷት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ወዳልተሰበኩት ሕዝብ ደርሳ ትምህርቷን እንዳታስተምር ልዩ  ልዩ የክህደት ትምህርት በመፍጠር አባቶችን ሥራ ያስፈቱ ናቸው፡፡ይልቁንም በአሁኑ ዘመን በክህደት ትምህርታቸው ብቻ ሳይቆጠቡ ቤተክርስቲያን ላይ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ የከፈቱበት ወቅት ነው፡፡ የተቸገሩ ምእመናንን የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ እንሰጣለን በማለት፣ የቤተክርስቲያኒቱን የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት እንረዳለን በማለት፣ እንዲሁም ለሆዳቸው ያደሩ ሰዎችን በመጠቀም የቤተክርስቲያን ዋነኛ የፈተና ምንጭ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
1.2 አላውያን ነገሥታት
በቤተክርስቲያን ታሪክ ከጌታ ትንሣኤ እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ያለው ዘመን ዘመነ ሐዋርያት ከ70 ዓ.ም እስከ 160 ዓ.ም ያለው ደግሞ ዘመነ ሐዋርያነ አበው እንዲሁም ከ16ዐ ዓ.ም እስከ 312 ዓ.ም ያለው ዘመነ ሰማዕታት  በመባል ይታወቃል፡፡
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍላተ ዘመናት የነበረው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ከአይሁድ ጋር የተደረገ ተጋድሎ ነው፡፡ ይኸውም ምንም እንኳን የአይሁድ ማኅበረሰብ ቃል ኪዳን የተገባለት፣ ትንቢት የተነገረለት፣ በአንድ አምላክ አማኝ ቢሆንም የክርስቶስን አዳኝነትና አምላክነት ላለመቀበል በአመጽ በመግፋቱ፣ እነርሱን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስና ለማቅረብ የተደረገ ጥረት ነበር፡፡
ሦስተኛው ክፍል ግን ቅዱሳን አበው ከአላውያን ነገሥታት ጋር ባደረጉት ተጋድሎ የሚዘከር ዘመነ ሰማዕታት ነው፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ትምህርትና በመምህራኑ አማናዊ ምሳሌነት በመላው ሮም የክርስትና ሃይማኖት ተስፋፍቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ለባሮች የነጻነት ትምህርት የተሰበከላቸው ሲሆን ባለጸጋዎችም ቢያምኑ የክርስቶስ አገልጋዮች ለመሆን እንደሚበቁ ተነገራቸው፡፡ /1ቆሮ 7፥22/  የአሕዛብን የቀደመ ትዕቢትና ኩራት የእግዚአብሔር ቃል  ሲያፈራርሰው፤ የአሕዛብን የአመንዝራነት ሕይወት የክርስቲያኖች ቅድሰና አሸነፈው፡፡ በአሕዛብ ልማድ በወንዶች መካከል ሴቶች የክብር ቦታ ያልነበራቸው ሲሆን በክርስትና እኩልነትና መከባበር ታወጀ፡፡
ከዚህ በኋላ ግን ክፉዎች በክርስቲያኖች ላይ የሰውን ሥጋ ይበላሉ፤ ለቄሳር አይታዘዙም፤ ግብር አይከፍሉም፤ የሚሉ ተራና ክፉ ወሬዎችን አወሩ ፡፡ በዚህ የተነሳ እንደነ ዲዮቅልጥያኖስ ያሉ ኢአማኒያን/ከሃድያን/ ነገሥታት ስልጣናቸውን መከታ አድርገው ብዙ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት እንዲያልፉ ያደረጉበት እኩይ ተግባር ፈጸሙ፡፡ ይህም ደጉ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መንበረ ሥልጣኑን ይዞ ለክርስቲያኖች ሠላም እስኪያወርድላቸው ድረስ የቀጠለ ጉዳይ ነበር፡፡
ቤተክርስቲያን ለምድራዊ ኑሮ ሲባል በተለያየ ሥርዓተ መንግሥት ሥር የሚኖሩ ሰዎችን ነው በሥርዓቷና እና በትውፊቷ እንዲኖሩ የምትጥረው፤ የእርሷ ድርጊት ሁሉ ከአመራራቸው ጋር የማይሄድ የሚመስላቸው ሁሉ እንደየዘመናቸው ሁኔታ መከራን አጽንተውባቸዋል፡፡ ይህም የሁል ጊዜ የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጭ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡

1.3 የአባቶች አለመግባባት /በአባቶች መካከል አለመግባባት መከሰት/
«የክርስቶስ ፍቅር ገብቷቸው ክርስትናንና ከዚያ የሚከተሉትን ኃላፊነቶችን፣ ክህነትን እስከ ጵጵስና ድረስ «አውቃለሁ፤ እበቃለሁ» ብለው ወይም « ይገባኛል» ብለው ሹመት ፈልገውና ተካሰው ሳይሆን «እኛ አንበቃም ተውን» እያሉ፣ ነገር ግን ለመንጋው የግድ መሪ ስለሚያስፈልገው «እናንተ ለዚህ ሓላፊነት ትበቃላችሁ መንጋውን ጠብቁ» እየተባሉ አደራ ሲጣልባቸው የተሰጣቸውን ከባድ ሓላፊነት የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል የተወጡ ብዙ ቅዱሳን አባቶች ቤተክርስቲያናችን አሏት፡፡

«በተቃራኒው ደግሞ እነዚህን ሓላፊነቶች ለራሳቸው ግላዊ ክብርና ዝና መጠቀሚያ በማድረግ የክርስቶስን ክብርና በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያንን ደኅንነትና ዕድገት ሳይሆን የራሳቸውን ምድራዊና ጊዜያዊ ፍላጐት ማስፈጸሚያ መሣሪያ ያደረጉትም ብዙዎች እንደነበሩ የቤተክርስቲያን ታሪክ መስታወት ሆኖ ያሳየናል» /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ ገጽ 7/
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ በአሠራርና በአመራር ምክንያት በአባቶች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ የአባቶች አንድነት የቤተክርስቲያን የአንድነቷ መገለጫ ነው፡፡ ይህ አንድነት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ችግር ከገጠመው የቤተክርስቲያን የፈተና ምንጭ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፤ ይህም በተለይ ለውጭ ጠላቶች በራችንን ወለል አድርጐ የሚከፍትላቸው ነው፡፡
1.4 የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት መዳከም
የክርስትና ሕይወት በየጊዜው በመጠን እየተለካ የሚያድግ ሕንጻ እግዚአብሔር ነው፡፡ ክርስትና በቤተክርስቲያን መሠረተ እምነት /ዶግማ/ በማመን በክርስቶስ ሕግና ሥርዓት መመራትና መኖር ነው፡፡
ምእመናን የቤተክርስቲያንን ድምጽ አልሰማ ብለው ሕይወታቸውን በቃለ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ በሥጋዊ ፈቃድ ስሜት መመራት ከጀመሩ የቤተክርስቲያን ትልቁ አደጋዋ ነው፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ በአባቶችና በምእመናን መካከል መደማመጥ አይኖርም፡፡ በዚህ ወቅት እግዚአብሔር ጸጋውን ይነሳል፤ የምእመናን ማኅበርም በክፉ ይታወካል፡፡
1.5 የግል ጥቅም አጋባሽ የሆኑ ግለሰቦች
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት ይከተሉት ለነበሩት ሰዎች አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ጠይቋቸው ነበር፡፡ «ምን ልታዩ መጥታችኋል» /ማቴ 11፥7-1ዐ/ ምንም እንኳን  ጌታ የጠየቀው ስለ ዮሐንስ ቢሆንም እርሱን ስለመከተላቸውም የሚያመለክት ነው፡፡ በመጽሐፍ እንደምናነበው ጌታን ይከተል የነበረው ሕዝብ ሁሉ ትክክለኛና አንድ ዓላማ ብቻ የነበረው አልነበረም፡፡ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች በሦስት ዋና ዋና  ክፍል መመደብ ይቻላል፡፡
ሀ. ሕብስት አበርክቶ ያበላ ስለነበር ጊዜያዊ እንጀራ ለመብላት ለሆዳቸው የሚከተሉት ነበሩ
ለ. የማስተማር ጥበቡን፣ እውቀቱን ለማድነቅ እንዲሁም ዓለምን ሊያድን የመጣ ንጉሥ ምን ዓይነት እነደሚመስል መልኩን ለማየት የሚከተሉት ነበሩ
ሐ. ድውያንን ሲፈውስ ለምጻሞችን ሲያነጻ ሙታንን ሲያነሳ አይተው ከደዌ ሥጋ ብቻ ለመፈወስ የሚከተሉት ነበሩ፡፡
መ.ድውያንን ፈወሰ ለምጻሞችን አነጻ ሙታንን አነሳ እንዲሁም ከተለያዩ ሀጢአትን ከሚሠሩ ጋር ይውላል ያድራል በማለት ለክስ የሚከተሉትም ነበሩ።
እነዚህ ሁሉ ግን የጌታችን የእግር መንገድ ሥራዎች ምድራዊ ሀብት እንጅ ዋነኛ ዓላማዎች አልነበሩም፡፡ የቃሉን ትምህርት ሰምተው ተአምራቱን አይተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ለአድኅኖተ ዓለምና ለእኛ አርዓያ ምሳሌ ሊሆን በመሆኑ ከአምስቱ ገበያ ሕዝብ ግን ይህን ተረድተው የተገኙት መቶ ሃያው ቤተሰብ ብቻ ናቸው፡፡
በቤተክርስቲያን ጉዞ ውስጥ እስከ ዛሬም ድረስ ለሥጋዊ ጥቅማቸው ፤ ወይም አድናቂና አጨብጫቢ ሆነው ብቻ ቤተክርስቲያን ላይ እንደ ክፉ ተባይ የተጣበቁ ግለሰቦች ነበሩ፤ አሉ፡፡ እነዚህ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ፍላጐታቸው ሥጋዊ ጥቅማቸው ማጋበስ ብቻ ስለሆነ ከእነርሱ ጋር የማይስማማ አባት፣ ካህን፣ ዲያቆን፣ ምእመን እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ ለዚህም ሲሉ የማያሴሩት የክፋት ሴራ ባለመኖሩ ለቤተክርስቲየን አገልግሎት ነቀርሳዎች ሆነዋል፡፡
2.    ፈተናዎች በቤተክርስቲያን ላይ ምን አደረሱ?
በቤተክርስቲያናችን በመናፍቃን፣ በአላውያን ነገስታት፣ በጥቅም አጋባሽ ግለሰቦችና በመሳሰሉት የደረሰባት በደል በዚች አጭር ጽሑፍ ዳስሶ መጨረስ ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ዋና ዋናዎችን ማንሳት ግን ግድ ነው፡፡
2.1 ቤተክርስቲያንን መከፋፈል፦
በሦስቱ ጉባኤያት /ኒቅያ  ቁስጥንጥንያና ኤፌሶን/ ዶግማዋን አጽንታ፣ ክፉዎችን ለይታ፣ ጥርት ያለውን እምነት ይዛ፣ አንድነቷን ጠብቃ የተጓዘችው አንዲት ዓለም አቀፋዊት ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ዛሬ ላለችበት ሁኔታ የበቃችው እነ አርዮስ በጫሩት የምንፍቅን የክህደት እሳት ነው፡፡ዛሬ ክርስቲያን በሚለው መጠሪያ የሚታወቁ ቤተ እምነቶች በዓለም እንዲፈጠሩ የሆነው ከላይ በዘረዘርናቸው ምክንያቶች ነው፡፡
የሕንድ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን የአሳዛኝ ታሪክ ምሳሌ ያደረጋት የመናፍቃን ደባ ነው፡፡ የሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከኦርቶዶክሳውያኑ ጐራ ተለይታ የኖረችው  እዚህ ግባ በማይባል ፖለቲካዊ / ምድራዊ ሥልጣን/ ምክንያት በተጀመረ ጠብ ነው፡፡
ዛሬ በእኛ ቤተክርስቲያን በአገር ውስጥ አባቶችና በውጭ በሚኖሩት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ፍጹም ክርስቲያናዊ በሆነ አኳኋን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካልተፈታና መፍትሔ ካልተገኘ እንደ ሕንድ ቤተክርስቲያን በእኛም በየአጥቢያው ላለመከፋፈልና ጥቁር ነጥብ ስላለመከሰቱ እርግጠኛ መሆን ይከብዳል፡፡
2.2  ምዕመናን ግራ ማጋባት
ቤተክርስቲያን በአባቶች አለመግባባትና በክህደት ትምህርት በምትፈተንበት ወቅት የሚከሰተው ትልቁ ስጋት /ክስተት/ የምዕመናን ግራ መጋባት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እነርሱን ለመቀራመት አሰፍስፈው ለሚጠብቁ የቤተክርስቲያን ጠላቶች የመንጋውን በረት ወለል አድርጐ የሚከፍት ነው፡፡ ዛሬ በአሜሪካ ባለችው ቤተክርስቲያን ከሁለቱም ወገን አይደለንም፤ገለልተኛ ነን፤ግን ጳጳስ እንፈልጋን የሚሉ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን የዚህ  ምሳሌዎች ናቸው፡፡
2.3 ጽንፈኝነት፦
በክርስትና የሕይወት ጉዞ ውስጥ እጅግ አደገኛ ከሚባሉ በሽታዎች አንዱና ዋነኛው ጽንፈኝነት ነው፡፡ ያውም ደግሞ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ «በዚህ ዓለም ያሉ ነገሮች አፈጣጠራቸውና ሕይወታቸው ከተለያዩ ነገሮች ረቂቅና ድንቅ በሆነው ጥበብ መለኮታዊ ተመጥኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ መጠን ሲናወጥ ግን ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡» /ሐመረ ተዋሕዶ 2000 ዓ.ም ገጽ 12/
«ማዕከላዊ ደረጃ የሌላቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም እግዚአብሔርና ጣዖታት፤ እውነትና ሐሰት፤ ሕይወትና ሞት ፤መንግሥተ ሰማያትና ገሃነመ እሳት፤ ክርስትናና ከክርስትና ውጭ ያሉ እምነቶችና አስተሳሰቦች.. » /ሐመረ ተዋሕዶ 2000 ዓ.ም ገጽ 13 / እነዚህ በራሳቸው ብቻ ቀዋምያን ከሆኑ ነገሮች ውጪ ያሉትን ግን በመጠን፣ መያዝ መኖር ተገቢ ነው፡፡ «መጠን ማለት» አንተም ተው አንተም ተው» ዓይነት ጉዳይ ሳይሆን ሁሉንም ነገር በራሱ አግባብና በተገቢው መጠን ማድረግና ከዚያ አለማሳለፍ ሲሆን ጽንፈኝነት ደግሞ ከዚህ ከተገቢው ልክና መጠን ማለፍ ነው፡፡» /ሐመረ ተዋሕዶ 2000 ዓ.ም ገጽ 14/
አይሁድን ከክርስትና የለያቸው ክርስቶስ ምድራዊ መንግሥትን አልመሠረተም፤ አንቀበለውም የሚል ጽንፈኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ወደ ክርስትና የመጡትንም ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና ከመጡት ጋር ሲያጣላቸው የነበረው « ጥምቀት ያለ ግዝረት ዋጋ የላትም» የሚለው ጽንፈኛ አስተሳሰብ ነው፡፡
ዛሬ ብዙዎችን ከቤተክርስቲያን እየለየ ያለ ይህ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰባኪ እገሌ እንዲሰብክ ካለተፈቀደለት ጉባኤ አልመጣም፤ ዲያቆን እገሌ እንዲቀድስ ካልሆነ አላስቀድስም፤ እነ እገሌ ወጥተው’ እነ እገሊት ካልተመረጡ ይህንን ማኅበር አልፍልገውም፤ እዚህ  ሰንበት ት/ቤት አልደርስም፤ ብለው የቀሩ ሰዎች በጽንፈኝነት ቀሳፊ ቀስት የተወጉ ናቸው፡፡
ቤተክርስቲያን በተፈተነች ቁጥር አንዱን ጽንፈ ይዘው በማክረርና በመወጠር ከማኅበረ ምእመናን የተለዩትን ቆጥረን አንጨርስም፡፡
ምንተ ንግበር /ምን እናድርግ/?
«ሰውን ብትታገል ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል ቤተክርስቲያንን ግን ለማሸነፍ አይቻልም ቤተክርስቱያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች ተሸንፋ ግን አታውቅም ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱን ጨረሰ፡፡ ቤተክርስቲያንን ግን አልጎዳትም» ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን በመጥቀስ የጻፉት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ነው / የቤ.ተ. ገጽ 48/። ፈተና የቤተክርስቲያን የመኖሯ መገለጫ እንደሆነ በጽሑፋችን መግቢያ ላይ ገልጸናል፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ፈተና በሚገጥማት ወቅት በሚነሳው ማዕበል ተከፍተን ከመርከቧ ወደ ባሕር እንዳንወርድ ምን ማድረግ ይገባናል? ጥቂት ነጥቦችን እናነሳለን፡፡
3.1 መንፈሳዊ ሕይወትን መጠበቅና ማጽናት ነው
የ አበው አባቶቻችን የተጋድሎ ገድል ስናነብ የምንረዳው ምንም እንኳን ወጥ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ቢኖራቸውም ከባድ ፈተና በገጠማቸው ጊዜያት ግን የበለጠ ይበረታሉ። በርካታ ቃል ኪዳናትን የተቀበሉት በርካታ መንፈሳዊ መጻሕፍትን የጻፉት የብዙ ጸጋ ባለቤት የሆኑት በፈተና ውስጥ ነው፡፡
የምንማረው ከአባቶቻችን ነውና ቤተክርስቲያን ፈተና ላይ በምትሆን ጊዜ በጋዜጣ በሚጻፈው፣ በድረገጽ በሚለቀቀው «እንዲህ ሆነ እንዲህ ተደረገ» ወሬ ተገፍቶ እርሱን ብቻ በማውራት የራስ ሕይወትን መዘንጋት አይገባም፡፡ የሚሰሙት ዜናዎች፤ የሚፈጸሙት ድርጊቶች የግል መንፈሳዊ ሕይወትን የመሸርሸር አቅማቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የቀደመ መንፈሳዊ ሕይወታችን መጠበቅ ማጽናት እግዚአብሔር አምላክ በፈተና ውስጥ ለቤተክርስቲያን በጐ የሆነውን ሁሉ እንዲያደርግ ጉዳዩን በጸሎት መያዝ መሆን አለበት፡፡
3.2 የቤተክርስቲያንን ድምፅ ብቻ መስማት
ቤተክርስቲያናችን መሠረተ እምነታዊ /ዶግማዊ/ በሆነ ችግር የተፈተነች እንደሆነ የቤተክርስቲያን ቋሚ ምስክር የሆኑ መጻሕፍትን፣ ትውፊተ አበውን፣ የቀድሞ የቤተክርስቲያን ድንጋጌዎችን መጠየቅ፣ ማንበብ በእርሱም ብቻ መመራት ተገቢ ነው፡፡
በአባቶች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ቤተክርስቲያን በተፈተነች ጊዜ ከግጭቱ ተጠቃሚም ተጐጅም ያልሆኑ በአንድም በሌላም ያልወገኑ አባቶችን ድምፅ ብቻ መስማት ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የቀድሞ ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም ትምህርት ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡
የትኛውም ወገን’ትውልድ ቢሆን የኃይል ሚዛኑ ስለመዘነለት ብቻ የሚያራግበውን ተቀብሎ በስሜት መነዳት አያስፈልግም፡፡ የቤተክርስቲያን ድምጽ ከቅዱሳት መጻሕፍት ከትውፊትና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰማ ነው፡፡ እርሱን ብቻ መስማት ተገቢ ነው፡፡
3.3 ከጽንፍ ራስን መጠበቅ ነው::
በክርስትና ሕይወት የጽንፈኝነትን አደገኛነት ከላይ በጥቂቱ ለመግለጽ ሞክረናል፡፡ የአሁኑ ዘመን ምእመናን የባሕታዊ እገሌ ተከታይ፣ የአቡነ እገሌ ደጋፊ፣ የመምህር እንትና አድናቂ፣ የዘማሪ/ዘማሪት እገሌ ቡድን እየተባባልን መታየታችን የበሽታው ምልክት ነው፡፡ መጨረሻውም መከፋፈል ነው፡፡ አሁን በቅርቡ በተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖደስ ስብሰባ እንኳን ብዙዎቻችን ውሳኔዎችን እንመዝን የነበረው «ማን ምን ተናገረ? የትኛው ጐራ ተሸነፈ? ማን ምን ተደረገ?» በሚሉና በሚመስሉ መስፈርቶች እንጂ ውሳኔው ለቤተክርስቲያን ጠቃሚ ነው ወይስ ሌላ? የሚል አልነበረም፡፡
በእንዲህ አይነቱ ክስተት ማንም አሸናፊ ማንም ተሸናፊ የለም፡፡ ደግ ከተሰራ ቤተክርስቲያን አሸነፈች፤ አበራች፡፡ ሸፍጥ ከተሰራ ቤተክርስቲያን ተጐዳች፤ እውነታው ይሄ ነው፡፡
ከስሜት እንራቅ፤ ከጽንፈኝነት ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ወገንተኝነታችን ለቤተክርስቲያን ብቻ ይሁን፡፡ ያኔ የሰውም የእግዚአብሔርም ፍስሐ ይሆናል ፡፡ አምላከ ቅዱሳን ለዚያ ድል ያብቃን፡፡አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዝክረ ልሳነ ሰብእ ቀዳማዊ

1. ግእዝ ምስለ ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመናት የፈተና ገፈታ ቀማሽ በመሆን፣ ልጆቿን እያበረታታች ለሀገራዊ ሀብት መጠበቅም እስከ ሰማዕትነት እያበረከተች በየአድባራቱና ገዳማቱ ጠብቃ አሳድጋ ለዚህ ትውልድና ዘመን ካቆየቻቸው ዕሤቶች አንዱ ግእዝ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ቤተ መዘክር፣ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት፣ ቤተ ክርስቲያን ግምጃ ቤት፣ ቤተክርስቲያን የሥልጣኔ ማዕከል፣ ቤተ ክርስቲያን ከተማ ሀገር በመሆን ስታገለግል ቆይታለች፡፡

ስለዚህም ነው በሀገሪቱ የታሪክና የመዛግብት ጥናት ላይ የረጅም እድሜ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር ሪቻድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ባህል ጠባቂ ናት ሲሉ በውዳሴ ዘጽድቅ የሚመሰክሩላት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የግእዝን ሥነ ጽሑፍ ሆነ ቋንቋ እንደሚከተለው ጠብቃ አስረክባናለች፡፡

በየጉባኤያቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ማዕከለ ትምህርት በመሆን ለዘመናት ሕዝቡን አገልግላለች፡፡ በራሷ ባሕላዊ ሥርዓተ ትምህርት ዜማውን ቅኔውን ትርጓሜ መጻሕፍቱን በዚሁ ቋንቋ ስታስተላልፍ ቆይታለች፡፡ እነዚህም ትምህርቶች የሚከናወኑበትን ትምህርት ቤት ከቤተክርስቲያኗ ዐውደ ምሕረት ዙሪያ በተዘጋጁ የመቃብር ቤቶች፣ ዙሪያውን  በተሠሩ ጎጆች አልያም በዙሪያዋ በተተከሉ ዐጸዶች አትሮንሷን ዘርግታ፣ አዘጋጅታ፣ ዜማውን አሰምታ፣ ግሱን አስገስሳ ምስጢሩን አብራርታ አስተላልፋለች፡፡ ይህንንም ስታደርግ ለደቀመዛሙርቱ ከሰንበቴው ከደጀ ሰላሙ ረድኤት እያሳተፈች ነው፡፡

በሊቃውንት የሊቃውንት፣ የፍቅር ሀገር፣ ሕይወተ ክርስትና፣ ፍሬ በረከት ስላላቸውና ዘወትር ቃለ እግዚአብሔርን በመናገር፣ ደቀ መዝሙር ሲያጠፋ ሲያርሙ ሲሳሳት ሲያስተካክሉ፣ የተበላሸውን ሲያቀኑ ባሳለፉት ድካም ሀብተ ታሪክን አውርሰዋል፡፡ የደረሷቸውን ቅኔያት፣ የጻፏቸውን መጻሕፍት ዜና መዋዕላቱን ጭምር ሲደጉሱ፣ ሲኮትቱ የተሻለ ቅርጸ ፊደልን ሲያወርሱን ወዘተ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው አብልጠው በመኖራቸው ነው፡፡ በመሆኑም ዳዊቱን እየደገሙ፣ መጻሕፍትን እየተረጎሙ ያብራሩበትም በዚሁ ልሳን ነው፡፡ በዚህ ሳይወሰኑ ሌትም ቀንም እንቅልፍ አጥተው ከማኅሌቱ፣ ከሰዓታቱ፣ ከጉባኤ ቤቱ ሳይለዩ ስለ ነገዋ ቤተ ክርስቲያን በመጨነቅ ያስተማሩትን ደቀ መዛሙር «ኦ ወልድየ ጽንዐ በጸጋሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅዱር ላዕሌከ በመንፈስ ቅዱስ» ልጄ ሆይ አድሮብህ ባለው በመንፈስ ቅዱስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋው ጽና ምከር አስተምር ብለው የቃል አደራ በመስጠት በየአህጉሩ ሲያሰማሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ጸሎታቸውን ለሀገር በሱባኤ ሲያደርሱ ኖረዋል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ሀገረ ሙላዳቸውን በመተው ደበሎ ለብሰው፣ ቁራሽን ተማምነው፣ አኮፋዳቸውን ከሰሌን አዘጋጅተው፣ ዳዊታቸውን በትከሻቸው አንግበው በትምህርተ ቤተክርስቲያን ዘመናቸውን ያቆዩ ተማሪዎችም ባለውለታ መሆናቸው የማይዘነጋ ነው፡፡ እድሜ ሳይገድባቸው ገና በልጅነት እድሜያቸው ጥሬ እየቆረጠሙ በውርጭ እየተነሡ ሀገር ለሀገር በመዞር ምስጢር ሲሸምቱ የአባቶቻቸውን ትውፊት በቃል በመጽሐፍ ያስተላለፉ ደቀ መዛሙርቱም እነዚሁ ናቸው፡፡ እነዚህም በሌሊት እየተነሡ ከመምህራቸው እግር ሥር ሆነው በብርዱ፣ በቁሩ ሲቀደሱ ሲያስቀድሱ፣ የሌሊቱን ዝናብ ታግሰው ሳይታክቱ በመምህራቸው ጓሮ በትጋት የተማሩባቸውን ጉባኤያት እያስታወሱ ሲያስተላልፉ ኖረዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ያለኀፍረት ራሱን ዝቅ አድርጎ በምእመናን ደጃፍ ዐረፍ ብሎ የተገኘውን እየተዘከሩ ወደ ጉባኤው ሲመለሱ እያዜሙ፣ ቅኔውን እየቆጠሩ፣ ወንዙን እየተሻገሩ፣ ተራራውን እየወጡ፣ እየወረዱ የአራዊቱን ድምጽ እየሰሙ፣ ተፈጥሮን እየቃኙ፣ ምስጢርን እያዩ ያዩትንም በቅኔው እየቀመሙ ለነባር ሲያስተላልፉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለክብረ በዓሉ ያለውን ቀለም በአፋፍ ላይ ሆነው እየቀጸሉ በጎጆአቸው ሌሊቱን ሲያዜሙ በራሳቸው ቋንቋ «አዛኘን» እስኪ በልልኝ  በመባባል እየተሳሳሉ ለዘመናት ትምህርቱን አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መምህራቸውን በእርሻ፣ በማሳ፣ በሥራ እየረዱ ነው፡፡

 
ምዕመናን ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው ባላቸው ፍቅር ሃይማኖታቸውን ከቤተ ክርስቲያን አጣምረው ኖረዋል፡፡ በባህል ግንባታውም ተሳትፈዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ተማሪንም ከመሶባቸው ማዕድ ሳይሰስቱ እየመገቡ ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ቤተክርስቲያን እንድትገለገል ጧፉን መጋረጃውን አሥራቱን ሲያስገቡ ባደረጉት አስተዋፅኦ የቤተ ክርስቲያኗ ሀብቷ እንዲህ ሊተላለፍ ችሏል፡፡ ዋዜማ እየደገሱ ቁመት ሲያስቆሙ ዕድሞ ሲያስከብሩ ኖረዋል፡፡

2. የግእዝ ቋንቋ እንዲያድግ ለምን አስፈለገ?

ባህል በቋንቋ ይለካል፡፡ እምነቶች ሥነ ሕዝብ ማኅበራዊ መሠረቶች /ዐምዶች ልምዶች ዕውቀቶች ሁሉ በቋንቋ አሉ፡፡ በአደጋ ላይ ያለ ቋንቋ ማለትም በአደጋ ላይ ያለ ዕውቀት አሳሳቢ፤ ባህል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ አገባብ የሚታወቀው ዕውቀት ካፀፀ መሠረት የለሽ ድካምን ያስከትላል፡፡

በመሆኑም ቋንቋ የኅብረተሰብእ /የአንድ ሕዝብ አካል ነው፡፡ ስለ ሕይወት ባህል ልምድ የሚፈስ ዕውቀት ሁሉ ትርጉም የሚኖረው በራስ ቋንቋ በሚገኝ ዕውቀት እንጂ የተጻፈን በመቀበል አለመሆኑ ደግሞ የራስ ቋንቋን ማወቅ ወሳኝ መሆኑን ያሳያል፡፡ ልሳናት በአባቶች ቅድመ አያቶች ቀሩ ማለት የልጆች ሀገራዊ አንደበታቸው ማንነት የሚጠብቁበት ኃይል ጠፋ ማለት ነው፡፡ የእኛ ማንነትና ታሪካችን ያለው የተቆራኘው በብዙ መንገድ ከቋንቋችን /ከግእዝ ጋር ነውና ያለበትን ደረጃ ልንመረምርና ልናስተውለው ይገባል፡፡ ሌላው ይቅርና መለያችን ልዩነታችን እንኳን በቋንቋችን ሰዋስው አገባብ ሊታወቅ ይችላል፡፡ ቋንቋችን ካልተጠበቀ የሚተላለፈው ዕውቀት ትውፊት ባለበት ይቆማል፡፡ አብሮ አስሮ የያዘቸውን እውቀቶች ፍልስፍናዎች ሁሉ ይዞ ይጠፋል፡፡ ነገር ሁሉ በአዲስ ይጀምራል፡፡ ሥር የሌለው በአሸዋ የተገነባ ሕንፃን ይመስላል፡፡ የሌሎች የባህል ጎርፍ በመጣ ጊዜ በቀላሉ ይወድቃል፡፡ ቋንቋን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን እንደገና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ በስደት፣ በዝርፊያ በዓለም ዙሪያ በየቦታው ያሉትን የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ሊመረምሩ የሚችሉ ልጆች ሊተኩ ያስፈልጋል፡፡ የተበረዘውን ማቅናትና የጠፋውን ታሪክ መፈለግ፣ የተለየንን የጥበብ ምንጭ ፍለጋ መውጣት መውረድ ያስፈልጋል፡፡ ሊጠፉ የተቃረቡትንም መጠበቅና ብሎም ዘመኑ ባፈራቸው መሳሪያዎች ተጠቅሞ በመቅረጽ ለትውልዱ ማስተላለፍ ትልቁ ኃላፊነት ይኸው ነው፡፡

አፍሪካውያን ዛሬ ቋንቋቸውን ለመጠበቅ የሚያደክማቸው ለብዙ ዘመናት በተሰላ እቅድ ሥር ተጽዕኖ በመውደቃቸውና በሌላኛው የቅኝ ግዛት መንገድ ማለፋቸው ነው። እንዳልነው ይህ ችግር ደግሞ ዛሬም ከአፍሪካ ምድር ስላልተወገደ በአደጋ ላይ የነበሩ ዕውቀቶች ሁሉ ጠፍተዋል፡፡ መፍቀርያነ ባህል አፍረንጅም በመብዛታቸው ነባሩ/ የአከባቢው መንፈሳዊውም ሆነ ቁስ አካላዊው ዕውቀት እየተረሳ መጥቷል፡፡ ይህንን እየተረሳ ያለ ሀብት ደግሞ ለመጠበቅ ልምዱ ያላቸው ወላጆችና ሽማግሌዎች አስረካቢ ሕፃናት ተረካቢ ሊሆኑለት ይገባል፡፡ እንግሊዘኛቸውን ሲናገሩ በማበላሸታቸው የሚስቁ ይቅርታ የሚጠይቁትን ወጣቶችን ልብ አማርኛን ግእዝን ግን በማበላሸታቸው ግን ይቅርታ የማይጠይቁትን አእምሮ ሊያጠቁት ይችላሉ፡፡ በዚያውም ላይ የውጪውን ቋንቋ በመጠቀም የአንደበታቸው አርአያነት ብቻ ሳይሆን መልዕክቱ የተዛባ እየሆነ መጥቷል፡፡

 

በዓለም እያሉ ከዓለም ውጪ መኖር

በዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በበሳል ትምህርቱ በመንፈሳዊ ጥብዐቱና በፍጹም መንፈሳዊ ሕይወቱ በቤተ ክርስቲያናችን የታወቀ አባት ሲሆን ኑሮውም የብህትውና ነበር። ካስተማራቸው በርካታ ትምህርቶቹ መካከል ውስጥ አንድ ክርስቲያን በምድር ሲኖር ሰማያዊውን ሕይወት እንዲኖር ነው። ይህንንም ያስተማረበትን ትምህርት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

“እግዚአብሔር የሚወዳችሁ እግዚአብሔርን የምትወዱ ወንድሞቼ ሆይ እነሆ ሰማያውያን ሆነናል፡፡ ዘበሰማያት የሚያሰኝ ሥጋውንና ደሙን ተቀብለናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ከዚህ ነገር የተነሣ እንፈራ ዘንድ እንንቀጠቀጥ ዘንድ ይገባናል፡፡ ሕሊናችንም ሰማያዊውን ማሰብ ትቶ ምድራዊውን ማሰብ እንዳይሆን መሆን ይገባናል፡፡ ሰማያዊነትን የሚወድ ሰው ምድራዊውን እንዳያስብ መሆን ይገባዋልና፡፡ ምድራዊውን ነገር ማሰብ ሰማያዊውን ነገር አለማሰብ ከክፉ ሕሊና ከክፉ ፈቃድ የሚገኝ ስለሆነ፡፡ በዚህ ዓለም እየኖርን እንደሌለን መሆን ይገባናል፡፡ ሰማያዊ አነዋወርን የሚወድ ሰው በዚህ ዓለም እየኖረ እንደሌለ መሆን ይገባዋልና፡፡ በዚህ እየኖሩ እንደሌሉ መሆን ለበጎ ሕሊና ከበጎ ፈቃድ የሚገኝ ስለሆነ፡፡”

ለአምላካችን ክብር ምስጋና ይግባውና እኛ በምድር ሳለን በባለሟልነት ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን በምድር ሳለን ፍጹማን ሆነን ሰማያውያን እንድንሆን ዛሬ ምን ያተጋናል? “የሰማይን ጌታ ካየሁት እኔ ሰማያዊ እሆናለሁና፡፡ እርሱ ጌታ አባቴና እኔ መጥተን እናድርበታለን” እንዳለ፡፡ ወንድሞች ሆይ እንዲህም ከሆነ  ራሳችንን ማኅደረ እግዚአብሔር እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡
ሰማይ እጅግ ያማረች ናትና፤ በተፈጥሮዋም ፈጽማ የበራች ናትና በክረምት አትጠቁርምና መልካም አይለወጥምና ራሳችንን በሰማይ እናድርግ፡፡ ደመናትም መጥተው ከታች ቢሸፍኑዋት ከላይ የሚያበራ ብርሃን አላት፡፡ እንደዚሁ እኛም ጨለማ የማያፈራርቀው እውነተኛ ፀሐይ ጌታችንን ገንዘብ እናድርግ፡፡
አስቀድሞ እስካሁን በሰማይ እንሆን ዘንድ ይቻለናል ብዬ ተናገርሁ፡፡ ዳግመኛም ከእንግዲህ ወዲህ ከሰማይ ይልቅ ያማርን የተወደድን እንሆን ዘንድ ይቻለናል ብዬ እናገራለሁ፡፡ ፀሐይን የፈጠረ ጌታ ክብር ምስጋና ይግባውና  በውስጥ በአፍአ ቢያድረብን በእውነት ከሰማይ ይልቅ ያማርን የተወደድን እንሆናለን ብዬ እመልሳለሁ፡፡
ሰማይስ ንጽሕት ናት ብርይት ናት፡፡ በክረምት ደመና በሌሊት ጨለማ አያገኛትም፡፡ እንደዚህም ከሆነ መከራ የሚያመጣብንን፤ ቀቢጸ ተስፋ፤  ከሚያመጣብን ጠላት ተንኮል እንታገሥ ዘንድ ይገባናል፡፡
ከምድራዊ ሥራ የራቅን የተለየን እንሆን ዘንድ ይገባናል?ሰማይ ከምድር የራቀች ናት፡፡ እንደዚህም ሁሉ ሰውነታችንን ምድራዊ ነገር ከማሰብ አርቀን ሰማያዊ ነገር እናስብ ዘንድ ይገባናል፡፡ ማኅደረ እግዚአብሔር እንሁን፡፡ ትሩፋት ሠርተን ከፍጹምነት እንድረስ፡፡
ከዚህ በኋላ  እንደ ጉንዳን እንደ ትል እናያቸዋለን፡፡ይህ ዓለምና በዓለም ያለው ሃብት ሁሉ አላፊ ጠፊ እንደሆነ እንረዳለን እናያለን። ድኃውን ባለጸጋውን ብቻ አይደለም፡፡ ንጉሡንም ራስ ቢትወደዱንም ቢሆን እንዲህ አድርገን እስከማየት ድረስ ነው እንጂ፡፡ የንቀተ ያይደለ የብቃት ነውና እንዲህ አለ፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡን ይጐዳናል አንድም ይጠቅመናል ብለን አናየውምና፡፡ ሕዝባዊውን አይጐዳንም አይጠቅመንም ብለን ለይተን አናውቅምና፡፡ ወርቁንም ብሩንም ለይተን አንድም ይጠቅመናል ብለን አናውቅምና፡፡ ከቀይ ሐር ከነጭ ሐር የተሠራውንም ልብስ ለይተን አንድም ይጠቅመናል ብለን አናውቀውምና እንደትል እናያቸዋለን፡፡
በዚያን ጊዜ ሁከት ሥጋዊ ፍርሃት ሥጋዊ የለም፡፡ በዚህ ዓለም ለሚኖር ሰው ከዚህን ያህል ማዕረግ መድረስ እንደምን ይቻለዋል የሚል ሰው ቢኖር ከዚህ ማዕረግ የደረሱ አበውን ጠቅሰን እንመልስለታለን፡፡ ንኡድ ክቡር ጳውሎስ በዚህ ዓለም ይኖር አልነበረምን፡፡ በዚህ ዓለም ሳለ ከሰማይ ደርሶ ከዚያ ተመልሶ የሰማይን አነዋወር በውኑ ይናገራል ብዬ እመልስለታለሁ፡፡ እርሱ ከሰማይ መድረሱን ለምን እናገራለሁ እግዚአብሔርን እናገኘው ዘንድ ካሰብን ፍቅሩን ክብሩን እንደሚገልጽልን እንረዳለን፡፡
እንዲህ ከሆነ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ዓለም አንመልከት፡፡ ጳውሎስ የሚታየውን ዓለም ይመለከት እንዳልነበረ ተረዳኽን? ወዳጄ ሆይ ከምድራዊ ግብር ሕሊናውን በለየ ጊዜ ከሁሉ በላይ እንዳደረገው ተረዳህን? ከጠፈር ብቻ ከዓለም መላእክት ብቻ አይደለም፡፡ የሉም እንጂ ያሉ ቢሆን ከሌላውም ፍጥረት በላይ እንዲያደርገው ተረዳህን?
መንግሥተ ሰማያት መግባትን ተስፋ አድርገን ግን ከትሩፋት ብንለይ በንዋመ ሀኬት /ከክፋትና ከተንኮል እንቅልፍ/ ብንያዝ ፈጽሞ ትሩፋት መሥራት አይቻለንም፡፡ መንግሥተ ሰማያትንም መውረስ አይቻለንም፡፡ እንዲህም ከሆነ ፈጽሞ ትሩፋት መሥራትን ትወዱ ዘንድ መንግሥተ ሰማያትን ትወዱ ዘንድ ወንድሞቼ ሆይ እማልዳችኋለሁ፡፡
የቅዱሱ በረከት ከሁላችን ጋር  ፀንቶ ይኑር።

/ምንጭ፡- ተግሣፅ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወረቅ ገጽ 175-184/

ቅዱስ ሲኖዶስ

በዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ
«አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት»
kidusSinodos.jpg
በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባዔ ጌታ በሚያውቃት ዕለት ይህች ዓለም ታልፋለች፡፡ እንደ ቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ ይህ ዓለም ካለፈ በኋላ የማይጠፋ እና የማይለወጥ የዘለዓለም መኖሪያ የሆነ ሌላ ዓለም ደግሞ አለ፡፡ ያም የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፡፡ የሰውን ልጆች ለእግዚአብሔር መንግሥት የምታበቃው እውነተኛዋ ፍኖት ደግሞ ክርስትና ናት፡፡ /ኤር 6.16/ እርሷም አንዲት ናት፡፡ የተሰጠችውም ፈጽማ አንድ ጊዜ ነው፡፡ /ይሁዳ 1-3/

ክርስትና አንድ ጌታ የሚመለክበት በአንዲት ጥምቀት ልጅነት የሚገኝበት በአንድ ተስፋ በአንድነት የሚኖርበት ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ እምነት በየጊዜው በዓለም በሚነሱ መጤ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች እንዳይበከል በእርሱም አምነው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚጓዙ አማንያን አንድነታቸው እንዳይፈታ በእግዚአብሔር የተሠራ ጉባዔ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስለቤተክርስቲያን ዶግማ ቀኖና ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም አስተዳደር የሚመክሩበት በመንፈስ ቅዱስ የሚቃኝ ጉባዔ ነው፡፡ ይህም «ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ፓትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳትና ኤጲስ  ቆጶሳት የሚያደርጉት ዓቢይ ጉባዔ ነው፡፡» ተብሎ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተገለፀው ነው፡፡ /ሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 2(2)/፡፡

አንዳንድ ሊቃውንት የቅዱስ ሲኖዶስን ሥርዓት አጀማመር ጌታ ከሐዋርያት ጋር ያደረጋቸው ስብሰባዎች መነሻ አድርገው ያመጣሉ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው የሚገኙ ሦስት ጉባዔያትን አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያው በይሁዳ ምትክ አንድ አባት መርጠው ሐዋርያ ለመሾም ያደረጉት ጉባዔ ነው፡፡/የሐዋ 1፥15-16/ ሁለተኛው ሰባቱን ዲያቆናት ለመሾም የተደረገው ጉባዔ (ሲኖዶስ) ነው፡፡ /የሐዋ 6.1-6/ የመጨረሻው ከአሕዛብና ከአይሁድ ወደ ክርስትና በመጡት መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተደረገው ነው፡፡/የሐዋ.15፥1/

በጉባዔ ኬልቄዶን ምክንያት የሃይማኖት መከፋፈል ከመጀመሩ በፊት የአካባቢ ሲኖዶሶች እምብዛም የተለመዱ አልነበሩም፡፡ ዛሬ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሦስቱ ጉባዔት ብቸኞቹ ዓለም አቀፍ ጉባዔያት ናቸው፡፡ እርሱም በኒቅያ በ325 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም እንዲሁም በኤፌሶን 431 ዓ.ም የተካሔዱት ናቸው፡፡

ከዚያ በኋላ ግን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በየራሣቸው መንበር የአካባቢ ሲኖዶስ ማድረግ ቀጥለዋል፡፡ እነሆ የእኛም ቤተ ክርስቲያን በራሷ ሲኖዶስ መመራት ከጀመረች ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ሆኗል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋነኛ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መገለጫ ነው፡፡ በየጊዜው በሚወለዱ ክስተቶች ዶግማዊ ቀኖናዋ ሥርዓቷ ትውፊቷ እንዲሁም አስተዳዳሯ እንዳይፈታ መጠበቂያ ነው፡፡ በዚህም በመሠረት እምነቷ ላይ ጥያቄ ሲነሳ ማብራሪያ መስጠት አዳዲስ አስተምህሮዎች ሲመጡ በዶግማዊ መሠረት ማረቅ ማቅናት የጾም የጾሎት ሥርዓትን መሥራት ልጆቿን የሚመሩ አበው ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋነኛ ተግባራት ናቸው፡፡

አስቀድመን እንደገለጽነው ክርስትና በማኅበር የሚኖርበት በማኅበር ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡

ይህ ማኅበር በአንዳች ምክንያት እንዳይበተን የአንድነት መገለጫው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

ምዕመናን ሁል ጊዜ ሊሰሙት የሚገባው የቤተ ክርስቲያን ድምጽ ይህ የአንድነቷ መገለጫ ከሆነው ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጣው ድምጽ መሆን አለበት፡፡ አንድ ክርስቲያን በአኗኗሩ ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሚደነግጋቸው ድንጋጌዎች ተገዢ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ አልተስማማኝም ይህ ጐረበጠኝ ብሎ በግልም በቡድንም መጓዝ ከሕይወት መንገድ ይለያል፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ፍጹምና የማይሳሳት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሲኖዶስ ተሳሳተ ተብሎ ሌላ አቋራጭ መንገድ መከተል ደግሞ የበለጠ ለጥፋት የሚዳርግ ነው፡፡ ሲኖዶስ ቢሳሳት የሚስተካከለው በራሱ በሲኖዶሱ ሥርዓትና ደንብ ብቻ ነው፡፡

ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መገዛት የማኅበረ ምዕመናን አባልነት በዚህ ምድር ያላችው የእግዚአብሔር መንግሥት ነዋሪነት መገለጫ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ እግዚአብሔር ሃሣቡን ፈቃዱን ለልጆቹና ለቤተ ክርስቲያን የሚያስተላልፍበት መንፈሳዊ ጉባዔ ነው፡፡
ለእስራኤል ዘሥጋ ሥለ አንድነታቸው ስለአኗኗራቸው በነሊቀነብያት ሙሴ በኩል ሥርዓትን የሠራ እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ክርስቲያኖች እስራኤል ዘነፍስም ሥለ አንድነታችን ማኅበራችን እንዴት በሥርዓት ልንኖርበት እንዲገባ ሥርዓቱን የሚሠራልን በብጹአን አበው አማካኝነት ነው፡፡ በዚህም ከመንጋው ተለይቶ ላለመቅበዝበዝ የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ መስማት ተገቢ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

mk20thyearCD

ኢንኅድግ ማኅበረነ

mk20thyearCD

ቤተ ክርስቲያን

በዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ

ቤተ ክርስቲያን ሦስት ትርጉም ያለው በዘርፍና በባለቤትነት የተቀመጠ ስም ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስንል የክርስቲያኖች መገናኛ መሰብሰቢያ በዓት ማለት ነው፡፡ይህም ክርስቲያኖች በአንድነት የሚጸልዩበት፣ የሚሰግዱበት፣ ሥጋ ወደሙን የሚቀበሉበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታና የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡(ኢሳ. 56፥7 ፣ ኤር. 7፥10-11 ማር. 11፥17 ሉቃ.19፥46 ) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የራሳቸው የጸሎት ቤት በተወሰነ ቦታ አላደረጉም፣ የተለየ ሕንጻ አላሰሩም ነበር፤ ነገር ግን ወደ አይሁድ ቤተ መቅደስ በመሄድ ይጸልዩ ነበር፡፡እንዲሁም በግል የክርስቲያን ቤቶች በተለያዩ ክፍሎች እየተገናኙ ይጸልዩ ቅዱስ ቁርባንን ያዘጋጁ ነበር፡፡ክርስትና እየተስፋፋና እየታወቀ ከሄደ በኋላ ቤተ ክርስቲያንም በፊልጵስዩስ ለመጀመሪያ ጊዜ በጌታችን ፈቃድ ከተሰራ በኋላ ክርስቲያኖች ሥጋ ወደሙን የሚቀበሉት በቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆን ጀመረ፡፡ ከዚያ በፊት የነበሩ ምኩራብና መቅደስም አገልግሎታቸውን ለቤተ ክርስቲያን አስረከቡ፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን ስንል ሁለተኛው ትርጉም የክርስቲያኖች አንድነት «ማኅበረ ምዕመናን» ማለት ነው፡፡ ይህም በአንድ ጌታ  በአንድ እምነት እና በአንድ ጥምቀት አምነው የተጠመቁ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኙ፣  በዚህ ምድር በአንድ አሳብ እና ተስፋ የሚኖሩ፣ በመጪው ዓለምም በእግዚአብሔር መንግስት በዘለዓለማዊ አንድነት የሚኖሩ ክርስቲያኖችን የሚያመለክት ነው፡፡
በሦስተኛውና የመጨረሻው ትርጉም ቤተ ክርስቲያን ስንል እያንዳንዱን ምዕመን ማለታችን ነው፡፡ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ አታውቁምን ? ›› በማለት የገለጸው ነው፡፡ (1ቆሮ.6፣19) ክርስቶስ ለሰው ልጆች የፈጸመውን የማዳን ሥራ አምኖ  በስመ ሥላሴ የተጠመቀ እያንዳንዱ ምዕመን ማኅደረ ክርስቶስ «ቤተ ክርስቲያን» ይባላል፡፡
አሁን አሁን በሚታየው የክርስቲያኖች አስተሳሰብ ከመጀመሪያው ትርጉም ውጪ ለተቀሩት ሁለት ትርጉሞች ትኩረት ሲነፈጋቸው ይስተዋላል፡፡ ለሕንፃ  ቤተ ክርስቲያን  ከምንሰጠው አክብሮት ጋር ሲነጻጸር ለግል ክርስቲያዊ ሕይወታችን እና ለአንድነታችን የምንሰጠው ትኩረት አናሳ ሆኗል፡፡ክርስቲያናዊ አንድነት ማለት ምን ማለት እንደሆነና ይህን አንድነት መጠበቅ እንደሚያስፈልግና የሚያስገኘውን ዋጋ እንዲሁም ይህን አንድነት የማይጠብቁ የሚያገኛቸውን ቅጣት አስመልክቶ ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ የሰጠውን ትምህርት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
ስለ ቤተ ክርስቲያን (ምዕመናን) አንድነት
ስለዚህ ሁሉንም እኔ አንድ ሰው ፈጽሞ በትጋት ስለ አንድነት እንደሚሠራ ሠርቻለሁ፡፡ መከፋፈልና መጥፎ አመለካከት ባለበት እግዚአብሔር አያድርም፡፡ ነገር ግን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንጂ ምንም ዓይነት ሁከት እና ጥል እንዳታደርጉ እመክራችኋለሁ፡፡ እንድነትና ስምምንት በመካከላችሁ ይኑር፡፡ በአንድነት ጽኑ፡፡ አንዱ ለሌላው ይጸልይ፤ ይህም ለሁላችሁ ይገባልና በተለይ ካህናት ጳጳሱን ማበረታታት አለባቸው፡፡
ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ ሞትን በማሸነፉና ሰይጣንን ድል በመንሳቱ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው አንድነት ተመልሶለታል፡፡ ይህን ሊያደርግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ስለነበረ የእግዚአብሔር ሰው መሆን የግድ ሆኗል፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ነገር ክርስቶስን ማክበር ይገባናል፡፡ እርሱም እኛን ያከበረን ነው፡፡በአንድ ላይ በአንድነት በመታዘዝ ፍጹም አንድ ወደ ሆነ አስተሳሰብና አመለካካት ትመጣላችሁ፡፡በዚህም ስለ አንድ ነገር ሁላችሁም አንድ አይነት የሆነ ንግግር ትናገራላችሁ፡፡የክርስቲያን የመጀመሪያ ጠባይ መሆን ያለበት አንዲት በሆነች እምነት ፍጹም አንድ የሆነና ራስ ወዳድ ባልሆነ መንፈስ መዋደድ ነው፡፡
ለቅዱስ ፖሊካርፐስ በላከው መልዕክቱ እንዲህ ይላል፡- ለአንድነት ትኩረት ስጥ፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ምንም ነገር የለምና፤ እግዚአብሔር አንተን እንደ ያዘህ ሁሉንም በደንብ ያዛቸው፤ በሕይወትህ እንደ ፍጹም ሯጭ ሁን፡፡ ሥራው ድካሙ ብዙ ነው፤ ነገር ግን የሚገኘው የበለጠ ነው፡፡
ክርስቶስ በሞትና በሰይጣን ላይ ድል በማድረጉ ምዕመናን ከአምላክ ሕይወትንና ፍቅርን አግኝተዋል፡፡እንዲሁም ከወንድሞቻቸው ጋር በክርስቶስ አንድ ሆነዋል፡፡በክርስቶስ ላለን ሕይወት እምነት የመጀመሪያው ነው፤ ፍቅር ግን የመጨረሻው ነው፡፡ የሁለቱም አንድነት እግዚአብሔር ነው፡፡ ክርስቶስ ዘለዓለማዊ ሕይወት ነው፡፡ለእኛ ሕይወትን እንደ ሰጠን ፍቅርንም ሰጥቶናል፡፡በዚህ ፍጹም ፍቅራችሁ ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት እንዳለን በዚህ ማወቅ እንችላለን፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ አንዱ ከሌላው ጋር በአንድነት በመዋደድ ቅድስና ይፈጽማል፡፡
በመካከላቸሁ ማንኛውንም ዓይነት መከፋፈል እንዳገኝ አልፈልግም፡፡ ማንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መለያየትንና መከፋፈልን የሚያመጣን ሰው የሚከተል እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፡፡ማንም ሰው እንግዳ በሆነ አስተሳሰብ የሚነዳ ከሆነ ክርስቶስ ስለ እኛ በተቀበለው በሕማሙ የማያምን ነው ፡፡ በጥቂት አላዋቂ ሰዎች ክፉ ንግግር አጠቃላይ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሰደብ የለበትም፡፡ ‹‹ በሌሎች መካከል በእነርሱ ግብዝነት ስሜ ይሰደባል ›› እንደ ተባለ፡፡(ኢሳ.52፣5)
በንስሐ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ለመመለስ የሚፈልጉትን ሁሉ በምህረትና በርህራሄ መቀበል ይገባል፤ ከዲያብሎስ ወጥመድ ያመልጡ ዘንድና በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት በእርሱ መንግስት ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያገኙ ዘንድ፡፡ወንድሞች ሆይ አትታለሉ፡፡ራሱን ከእውነት የሚለየውን ሰው የሚከተለው ቢኖር የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፡፡ ሐሰትን ከሚናገርና ከሚያስተምር ሰው ራሱን የማይለይ ሰውም እርሱ በሲኦል ይፈረድበታል፡፡ መልካም ከሆነው እንዳንለይ ክፉ ከሆነው ደግሞ እንድንሸሽ ግዴታ ነውና፡፡
ነገር ግን ሁላችሁም መከፋፈል በሌለበት በአንድ ልቡና፣ ሙሉ ፈቃድ ባለው ሕሊና አንድ ሁኑ፡፡ በሰላማችሁ ጊዜም ሆነ በችግር ላይ ስትሆኑ፣ በሐዘንም ሆነ በደስታችሁ ጊዜ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ አመለካከት እንዲኖራችሁ ያስፈልጋል፡፡ ያለ ጳጳሱ ፈቃድ ምንም ነገር አታድርጉ፡፡ ሰውነታችሁን እንደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ጠብቁ፡፡ አንድነትን ውደዱ፤ መለያየትን ግን ፈጽማችሁ ተጸየፉ፡፡
ጌታችን በፈቃድ ከአባቱ ጋር አንድ ስለሆነ ያለ አባቱ ምንም ነገር እንዳልሠራ ፣ ‹‹ እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም››፤   (ዮሐ.5፣19) ይላልና፤ እናንተም ቄስም ቢሆን ዲያቆንም ቢሆን ምዕመንም ቢሆን ማንም ቢሆን ያለ ጳጳሳት ምንም ነገር መሥራት የለባችሁም፡፡ እንዲሁም ለብቻ በመለየት የሚሠራ ምንም ዓይነት ሥራ መቼም ቢሆን ትክክል ይሆናል ወይም አግባብነት ይኖረዋል ብላችሁ አታስቡ፡፡ ነገር ግን በአንድ ቦታ (በቤተ ክርስቲያን) በመሰባሰብ አንድ ጸሎት፣ አንድ አስተበቁዖት፣ አንድ ሕሊና፣ አንድ ተስፋ ንጹሕ በሆነ ፍቅርና ደስታ ይኑር፡፡ ይህም ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ሊኖር ይገባል፡፡ የሁላችን አባት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለን ሁሉ ሁላችሁም ወደ አንድ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገስግሱ ወደ አንድ ምስዋዕ ቅረቡ፡፡
የተለያዩ ሲሆኑ ነገር ግን ተስማምተውና ተዋሕደው ጣዕመ ዜማ ያለውን ግሩም መዝሙር እንደሚያሰሙ መዘምራንና አውታሮች እኛም በስምምነትና አንድ በሚያደርግ ፍቅር ተገጣጥመን ለእግዚአብሔር ልዩ የፍቅርንና የአንድነትን መባዕ የምናቀርብ ልንሆን ይገባናል፡፡ ጌታችን ‹‹አንተ አባት ሆይ አንተ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ›› (ዮሐ.17፣21) ብሏልና፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ነውር ነቀፋ በሌለበት አንድነት አንድ ብትሆኑና የክርስቶስ አካል እንደመሆናችሁ ከእርሱ ጋር ተዋሕዳችሁ ብትኖሩ ጠቃሚያችሁ ነው፡፡
መከፋፈልና ቁጣ ባለበት በዚያ እግዚአብሔር አያድርም ፡፡ በንስሐ ለሚመለሱት ግን በእውነት ወደ እግዚአብሔር አንድነትና ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ቢመለሱ ጌታ ይቅር ይላቸዋል፡፡ምንም ዓይነት ነገር በሁከትና በጠብ እንዳታደርጉ እመክራችኋለሁ፤ ለእርሱ አስተምህሮ እንደሚገባ ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረን መሠረት በፍቅርና በሰላም እንጂ፡፡
የአንድና የሁለት ሰው ጸሎት ታላቅ ጥቅም አለው፡፡ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ኅብረትና አንድነትማ ምን ያህል ጠቀሜታና ኃይል ይኖረው ይሆን? በሥርዓትና በአምልኮት ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት ጋር አንድ አልሆንም የሚል በትዕቢት ራሱን ከቤተ ክርስቲያን እየለየ ነው፡፡ ከልባችን እርስ በእርስ መከራከርን አስወግደን ለእግዚአብሔር በአንድነት እንገዛ፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔርን ለማመስገን ዘወትር በአንድ ላይ ትሰባሰቡ ዘንድ አስተውሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአንድነት በምትሰባሰቡ ጊዜ የሰይጣን ኃይል ይደክማል፤ እርሱ ያሰበው የጥፋት ዓላማውም በእምነታችሁ በአንድነት ይከሽፋል፤ ይጠፋል፡፡ ‹‹ መጋደላችሁ ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፉ መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ›› (ኤፌ.6፣12) በሰማይም ሆነ በምድር ያለውን ጦርነት ጸጥ ረጭ አድርጎ ከሚያጠፋው ከሰላም የበለጠ የከበረ ነገር የለም፡፡ ማንኛውንም የምትሠሩትን ነገር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሆነና እርሱን ደስ በሚያሰኝ አንድነትና ስምምነት አድርጉት፡፡
ወንድሞች ሆይ አትሳቱ፡፡ ቤተሰብን የሚያፈርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡(1ኛ ቆሮ.6፣9) የሰዎችን ቤተሰቦች የሚያፈርሱ ሞት የሚፈረድባቸው ከሆነ፣ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ መስቀልን እስኪሸከም ድረስ የወደዳትንና የሞተላትን ቤተ ክርስቲያን በመለያየት የሚያፈርሱትንማ ምን ያህል ቅጣት ይጠብቃቸው ይሆን ? ስለዚህ ጥበብ የጎደለውን እረኛ የሚከተልና ስለ እውነት ፈንታ ሐሰትን የሚቀበል ቢኖር ይቀጣል፡፡
ከእውነተኛው እረኛችሁና መምህራችሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ለሌላ ለማንም ጆሯችሁንና ልባችሁን አትስጡ፡፡በመካከላችሁ ወገናዊነትና መለያየት ቦታ አያግኝ፡፡ አንድ ጌታ አንድ እምነት አንድ ጥምቀት አለና፡፡(ኤፌ.4፣4)
ስለዚህ የብርሃን ልጆች እንደ መሆናችሁ ከመለያየትና ከክፉ ትምህርት ሽሹ፡፡ ነገር ግን እረኛችሁ ባለበት እንደ በጎች እርሱን ተከተሉ እንጂ፡፡(ዮሐ.10፣7) ተአማኒና እውነተኞች የሚመስሉ ብዙ ተኩላዎች አሉና ፡፡ እነርሱም ሰዎችን ክፉ በሆነ ምኞትና ሥጋን በሚስቡ ነገሮች ወደ እግዚአብሔር የሚገሰግሱትንና ወደ እርሱ ለመቅረብ በመንገድ ላይ ያሉትን ሰዎች እየጠለፉ ወደ ጥፋት ይወስዷቸዋል፡፡(2ኛ ጢሞ.3፣6) እንዲህ ያሉት በቤተ ክርስቲያን አንድነት ውስጥ ምንም ቦታ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ስለዚህ ከምንም በላይ የሆነውን አንድነታችሁን ለመጠበቅ ትጉ፡፡ አንዳችሁ ሌላውን በትህትና ሆኖ በፍጹም ትዕግሥት ይሸከመው፤ እግዚአብሔር ለእኛ እንዲህ እንደ ሆነ ያህል፡፡

ምንጭ፡ወ/ሮ ዘውዴ ገ/እግዚአብሔር ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ሐዋርያዊ ጳጳስ ወሰማዕት(ገጽ 80 – 85)

 

metshafe_bilhat.jpg

የአዳዲስ ፈጠራ ግኝቶች ማበረታቻ የሽልማት ፕሮጀክት ትግበራ ተጀመረ።

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
 
metshafe_bilhat.jpgየሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል የአዳዲስ ፈጠራ ግኝቶች ማበረታቻ የሽልማት ፕሮጀክት ትግበራ ጀመረ። በፕሮጀክቱ ትውውቅ መርሐ ግብር ላይ ለትግበራ መነሻ ይሆናል የተባለው «መጽሐፈ ብልሃትም» ተገምግሟል።
 
ፕሮጀክቱ ማኅበረ ቅዱሳንና ኢንጅነር ሙሉጌታ ዘርፉ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሠነድ መሠረት ፈጠራንና መልካም የሆነውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ማበረታት፥ ቤተ ክርስቲያንን፣ ትውልድን ፣ ሀገርን የሚጠቅም አቅም ለማሳደግ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሆነ በመርሐ ግብሩ ትውውቅ ወቅት የተበተነው ወረቀት ያስረዳል፡፡
መርሐ ግብሩን ያዘጋጀው የማኅበረ ቅዱሳን የሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል ሲሆን በፕሮጀክት ትውውቅ መርሃ ግብር ላይ የክፍሉ ሓላፊ ዶ/ር ሣሙኤል ኃ/ማርያም እንደተናገሩት ከሆነ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በየደረጃቸው መስራትና የፈጠራ ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ ማሳየት ነው፡፡ በግኝቱ ውስጥ ለሚያሸንፋ ግለሰቦች ሽልማቶችን በመስጠት ፈጠራን ያበረታታል በተጨማሪም ያለብንን የተለያዩ ችግሮች በሙያ በማገልገል በተሰጠን መክሊት አትርፈንባቸው ገብርሄር ተብለን ሰማያዊ ሽልማት እንድናገኝ ነው፡፡

በትውውቅ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙትም የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እንደገለጹት ማኅበሩ ይህንን ፕሮጀክት ለተጠቃሚ ለማድረስ ሲወስን ከዘርፉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤተ ክርስቲያንንና ሀገሩን በአካባቢያው ከሚያገኛቸው ቁሳቁሶች በማዘጋጀት እንዲጠቀም ነው፡፡ በዚህ በኩል ሁላችንም የድርሻችንን እና የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይገባናል ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ለፕሮጀክቱ ትግበራ መነሻ ይሆናል የተባለውና በኢ/ር ሙሉጌታ ዘርፉ የተዘጋጀው መጽሐፈ ብልሃት አንደኛ መጽሐፍም ተገምግሟል፡፡ መጽሐፉ በ24 ክፍሎችና በ92 ገጾች በምርምርና ሥርዐት የተዋቀረ መሆኑን ዶ/ር ኢ/ር ብርሃኑ ይግዛው የግምገማ ግብረ መልስ /Feed back/ ሲያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

ገምጋሚው መጽሐፉ የተጻፈበትን ሥርዓትና ስልት ሲገልጹ፥ ሥልጣኔ የሚፈጥሩት እንጂ የሚቀበሉት ነገር ያለመሆኑን ያመሰጠረ መጽሐፍ ነው ብለው፥ በይዞታቸው ጥንታዊ ግኝቶች፣ በአቀራረብ ስልታቸው ግን አዲስ ሊባሉ የሚችሉ እሳቤዎችን፣ ምን አልባትም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ገና ያልተፈለሰፉ ግን ሊተገበሩ የሚችሉ ድንቅ ሀሳቦችንም እያዋዛ የሚያቀርብ መጽሐፍ ነው ብለዋል፡፡   

ስለ መጽሐፉ ጠቀሜታ በዘረዘሩበት የግምገማቸው አካል ምርምርና ሥርፀት ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያስረዳና፥ እያንዳንዱ ሰው የፈጠራ ችሎታን በተመለከተ እንዲማር የሚያደርግ ነው፡፡ እኒህም የመጠቁ ቤተ ሙከራዎችን በማይጠይቅ ሁኔታ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ኢ/ር ብርሃኑ በማጠቃለያ ሀሳባቸው መጽሐፉ ጥቂት ሊያካትታቸው ስለሚገቡ ነገሮች ጠቅሰው፥ ይህ በጎ ጀማሮ በየት/ቤቱ፣ በቤተሙከራዎች እንዲሁም በፋብሪካዎች ተሠራጭቶ በዚህ ረገድ ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ይሄው በጎ የቴክኖሎጂ መሠረታዊ ሀሳብ የሚስፋፋበትን መንገድ በመቀየስ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የማ/ቅዱሳን ሙያ አገልግሎትና አቅም ማጐልበቻ ዋና ክፍል ማኅበሩ ከተነሣለት ቤ/ክንን በሙያ በእውቀትና በገንዘብና በጉልበት ለማገልገል ካለው ዓላማ አንፃር የቤ/ክንን ልጆች በሙያ አገልግሎት ለማሣተፍ የተቋቋመ ክፍል ነው፡፡
     
   

በ«ተሐድሶ» መሰሪ እንቅስቃሴ ላይ ዛሬም እንንቃ!

ኢትዮጵያ  ያላት ክብርና ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ የታሪክ ሰነዶች የተመሰከረ፣ በታላላቅ ማራኪ ቅርሶችም የታጀበ ነው። የነበራት ክብርና ገናናነት ከምዕራብ እስከ ምስራቅ፣ ከሰሜንም እስከ ደቡብ  የታወቀ ነው። ከዚህ ጉልህ ታሪክ ውስጥ የበለጠ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ የሀገራችን የሃይማኖት ታሪክ ነው። ኢትዮጵያ ከእስራኤል ወገን ቀጥሎ ብሉይ ኪዳንን በመቀበል ቀዳሚ ሀገር ናት። በመሆኑም በዘመነ ብሉይ ሕግና ነቢያትን በመቀበልና በመፈጸም እንዲሁም የተስፋውን ቃል በመጠበቅ ኖራለች። ጊዜው ሲደርስም የሐዋርያትን ስብከት ተቀብላ የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነትና ጌትነት አምና ጥምቀትን ወደ ምድሯ አምጥታለች። በመሆኑም ወንጌልን ተቀብላ አምና ስትሰብክ ኖራለች። አሕዛብ ሕግና ነብያትን በናቁበት ጊዜ ከአሕዛብ ወገን ቀድማ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ኦሪትን በመቀበሏ እንዲሁም ደግሞ እስራኤል ወንጌልን በናቁበት፣ ክርስቶስን በጠሉበት ጊዜ ከአሕዛብ ጋር ሐዲስ ኪዳንን በጊዜው በመቀበሏ ሁለቱንም ኪዳናት በጊዜያቸው ያስተናገደች ብቸኛ ሀገር ናት ማለት ይቻላል። ስለዚህ በዓለምም ሆነ በአፍሪካ መድረክ የሚያስከብር የሃይማኖት ታሪክ ባለቤት ናት። ከዚያም በመነጨ ሊሻሩ ከማይችሉት ከሕግና ከነቢያት እንዲሁም ከክርስቶስ ወንጌል፣ ከሐዋርያት ትምህርት፣ ከሊቃውንቱም ትርጓሜ የመነጨ ሰውንም እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ ሥርዓተ አምልኮ ባለቤት ለመሆን አስችሏታል።
 
ይህ ብዙዎችን የሚያስደስተውን ያህል አንዳንዶች ደግሞ በቅናት የሚመለከቱትና ለራሳቸው ፍላጎት ማሰፈጸሚያ አበላሽተው ሊጠቀሙበት ሲቋምጡ ታይተዋል፤ እየታዩም ነው። ይህንንም ታሪክ ለማጥፋት ወይም ባለበት በርዞ ከልሶ የራሳቸውን ኑፋቄና የክህደት አጀንዳ ለማስፈጸም ይሻሉ። በተለይ የምዕራቡ ዓለም «የካህኑ ንጉሥ» ሀገር እያለ የሚጠራትን ኢትዮጵያን ከመስቀል ጦርነት ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ለሚከተሉት ለየትኞቹም አጀንዳዎቻቸው መንደርደሪያ የማድረግ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ግልጽ ነው። ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ለሀገሪቱ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ለባህላዊና ማኅበራዊ ትስስር መሠረት ነች የሚሏትን የኦርቶዶክስ ቤተክስቲያን መቆጣጠር፤ በእነርሱም ርዕዮት ማራመድ፤ ካልሆነም ማዳከም፤ ከተቻለም መከፋፈል ይፈልጋሉ።
 

ይህንንም ከሱስንዮስ ዘመን ጀምሮ ለማድረግ የሚችሉትን ያህል ጥረዋል። ይህንን መሰል ቅሰጣና ሰርጎ ገብነት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በመሰሉ ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ላይ ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል። ለዚህም በሕንድ ቅኝ ገዢ የነበሩት ፖርቹጋሎችና እንግሊዞች ዋነኞቹ ተጠቃሾች ናቸው። በሚገርም ሁኔታ ኢትዮጵያም ውስጥ ተቀራራቢ በሆነ ጊዜ እነዚሁ ኃይሎች የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ለማዳከም ለማጥፋት ተንቀሳቅሰዋል። ለዚህም በሱስኒዮስ መንግሥት ጊዜያዊ ድጋፍ አግኝተው በነበሩት በነፔድሮኤዝ የሚመራው የፖርቹጋል ሚሲዮናውያን ጥማታቸውን ለማርካት ቢተጉም በኢትዮጵያውያን ሊቃውንትና ምእመናን ጥረት ከሽፏል።
 

ሕንድ ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረው ቸርች ሚሽነሪ ሶሳይቲ /CMS/ የተባለው የአንግሊካን ፕሮቴስታንቶች ሚሽን በንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ዘመን አይዘንበርግና ክራፕፍ የተባሉ ግለሰቦችን ወደ ኢትዮጵያ ከመላክ ጀምሮ በተከታታይ በሌሎችም ሚሽነሪዎች ጥረት ቢያደርግም ከስለላ ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም። ቅኝ አገዛዙም ሆነ ቤተክርስቲያኒቱን ካቶሊካዊ  ወይም ፕሮቴስታንት የማድረግ ወይም የመከፋፈሉ ሁኔታ ሕንድ ውስጥ እን ደያዘላቸው በዚህ ሀገር ሊሳካ አልቻለም፤ ሌላ በኦርቶዶክሳዊነት ስም የተመሠረተ የተለየ የእምነት ተቋም የለምና።
 

በቤተክርስቲያኒቱ በእነርሱ ምክንያት ወይም በሌላ ምክንያት የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በነገሥታቱና በሊቃውንቱ ከፍተኛ ጥረት በጉባኤዎች እየተፈቱ ያለምንም የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት አንድነታችንን ጠብቀን ኖረናል። ይህም ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገር አንድነትም መሠረት ሆኗል።

የሀገሪቱ ነጻነትና አንድነት እንዲሁም ለረጅም ዘመን የኖረ የሃይማኖት ታሪክ ባለቤትነት በተለይ አፍሪካውያንንና የዓለምን ጥቁር ሕዝቦች እየሳበ መምጣቱ ለእነዚህ ኃይሎች የበለጠ የሚያንገበግብ ሆኖባቸዋል። ስለዚህ መላውን አፍሪካና ሌላውንም ሕዝብ ለመማረክ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን መቆጣጠር፤ የተለየና የተወገዘ አስተምህሮአቸውን መጫን ወይም አንሸራቶ ማስገባት፤ ካልሆነም አዳክሞና አጥፍቶ ሌላ መሠረት በመሥራት ወደሌላው ወገን  የመዝመት ብርቱ ዓላማ አላቸው።

 

በተለይ በአሁን ጊዜ ማንኛውም ወገን በሀገሪቱ የራሱን ሃይማኖት በነጻነት የማራመድ መብት ያለው በመሆኑ የራሳቸውን አምልኮ የሚፈጽሙበት በዓይነት ብዙ ድርጅት ቢኖራቸውም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ያላትን የሃይማኖት ታሪክ ክብርና ትኩረት ያህል የማግኘት ምንም እድል እንደሌላቸው ተገንዝበዋል። በመሆኑም ሌላ ዘርፈ ብዙ መላ መዘየድ ጊዜው ጠይቁአቸዋል። ለዚህ የመረጡት አካሔድ «ተሐድሶ» የተባለውን የመናፍቃን ተላላኪ ኃይል በቤተክርስቲያን ውስጥ ማስረግ ነው።

 

«ተሐድሶ» የተባለው በተለያዩ መናፍቃን የሚደገፍ፣ ተቋማዊ ሆኖ ያልተደራጀ፣ ወጥ አስተምህሮ የሌለው፤ ነገር ግን ኦርቶዶክሳዊ ነኝ ብሎ የተሰለፈ፤ በየትኛውም መንገድ የቀጠሩትን የተለያዩ የመናፍቃን ፍላጎት ለማርካት  ቤተክርስቲያንን ለመቆጣጠር በውስጥና በውጭ ያሸመቀ ኃይል ነው።  ከዚህ ቀደም ማኅበራችን ይህንኑ በኅቡዕ የተደራጀ የተወሰኑ መነኮሳት፣ መርጌቶችና  የዲያቆናት የተላላኪነትና የምንፍቅና አካሔድን ካጋለጠ ጀምሮ ግን ካህናትና ምእመናን ጉዳዩን ወደ ማጤን እንዲገቡ አስገድዷል። ይሁን እንጅ በጊዜው ለአንዳንዶች እነዚህ አካላት የቤተክርስቲያን ጠላቶች ሳይሆኑ የማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት ተገዳዳሪዎች ተደርገው ይታሰቡ ነበር። ይህን ድብቅ እንቅስቃሴያቸውን የሚከታተል ታዛቢ፣ ተመልካች በየሰንበት ትምህርት ቤቱ መኖሩን፤ ካህናቱም እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መፈተሽ በመጀመራቸው ለስውር  እንቅስቃሴአቸው በር እየተዘጋ መምጣቱን ተረዱ። በመሆኑም ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ግእዝ ተናጋሪ መናፍቅ ሆነው፡ የቤተክርስቲያንን መዓርጋት በስማቸው እየቀጸሉ፡ ለመጻሕፍት፣ መጽሔትና ጋዜጦቻቸው ኦርቶዶክሳዊ ገጽታ እያላበሱ በግልጽ ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮን መዝራት ጀመሩ። ይህ ደግሞ የ«ተሐድሶ»ን እንቅስቃሴ እውነተኛ ምንነትና በቤተክርስቲያን ጠላትነት የተሰለፈ ኃይል እንጂ የማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት ተገዳዳሪ አለመሆኑን በራሱ እንቅስቃሴ ግልጽ አደረገ።

 

በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የተመሠረተው ኑፋቄን የመዝራት ስልት በመምህራንና በሊቃውንቱ በተደረገው ለእምነት ጠበቃ የመሆን ተከታታይ እንቅስቃሴ ዋጋ እያጣ ሲመጣ ክርክራቸውን ወደ ገድላትና ድርሳናት በማዞር የነርሱን የኑፋቄ ዘር ከማምከኑ እንቅስቃሴ ሊቃውንቱ ዞር ብለው ቤተክርስቲያኒቱ ብቻ በምትጠቀምባቸው በራሷ መጻሕፍት ላይ በመከራከር ሊቃውንቱ ጊዜ እንዲያጠፉ፤ ከተቻለም በቤተክርስቲያን መከፋፈል እንዲፈጠር ተንቀሳቅሰዋል። ይህንን ለማድረግም ግእዝ ጠቃሽ ነን የሚሉ፤ በማኩረፍ፣ ጥቅምን በመፈለግና በመታለል ወዘተ ወጥተው በየጥጋጥጉ የሚወራጩ መርጌቶችን በመጠቀም ነው። ይህ ደግሞ ከመቶ ዓመት በፊት ከሁለት ምዕተ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የቤተክርስቲያኒቱን ሊቃውንት ሲያተራምሱበት እንደቆዩት የቅባትና የጸጋ አስተምህሮ የቤት ሥራ ዓይነት ለሊቃውንቱ የመስጠት ስልት ነው። እነዚሁ «ተሐድሶ» ብለው ራሳቸውን የሚጠሩት የመናፍቃን ተላላኪዎች ቤተክርስቲያናችንን ለመቆጣጠር ያስችለናል የሚሉትን የትኛውንም ስልት ከመጠቀም ወደኋላ የማይሉ አካላት ናቸው። ጎሳና ጎጥን ለማናከስ፣ በፖለቲካ ጉዳዮች በማስመሰል ለመክሰስ፣ ስም በማጥፋት አንዱን በአንዱ ላይ ለማነሣሣት ወዘተ ይጥራሉ፤ እየጣሩም ነው።

የ«ተሐድሶ» ኃይል ከውጭ ተበታትኖ ያለ ፈታኝ ይምሰል እንጂ በሁለት መልኩ ተሰልፎ የሚሠራ እርስ በእርሱ የሚተዋወቅም የማይተዋወቅም ኃይል ያለው ነው። በአንድ ገጽ ከውጭ ኦሮቶዶክሳዊ ነኝ እያለ በግእዝ እየጠቀሰ፣ አሉባልታ እያራባ፣ የሊቃውንቱን ትምህርት እያጣመመ፤ ስልት በመሰለው መንገድ ሁሉ ከአርዮሳውያን ጀምሮ እስከ ንስጥሮሳውያን፣ ከሊዮን እስከ ሉተር የተነሡ መናፍቃንን ትምህርት በተለያዩ መንገዶች /መጻሕፍት በመጻፍ፣ መጽሔትና ጋዜጣ በማሳተም፣ በራሪ ወረቀት በማሳተም/ እየዘራ፡ ከቤተክርስቲያን ውጡ እያለ ወደ ውጭ የሚስብ በፈሪሳውያን መንገድ የቆመ ጎታች ኃይል /pulling power/ ነው። ሌላው ደግሞ ከውስጥ ሆኖ  አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ለዓላማው ተባባሪ ከሆኑ የቤተክርስቲያኒቱ የውስጥ አካላት ጋር በተለያየ መንገድ ምእመናንን እያስደነበረ የሚያስወጣ ገፊ ሃይል /pushing power/ ሆኖ በአስቆርቱ ይሁዳ መንገድ የቆመ ነው።

 

በዚሀ ይሁዳዊ ግብር ውስጥ የሚሳተፈው ተላላኪ ቤተክርስቲያንን አሳልፎ ለመስጠት በሚያስችለው መመሳሰል ውስጥ ያለ ሲሆን በምእመናንና በሊቃውንቱ ፊት ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ እስከሚቀርብብኝ ድረስ ተሰውሬ እሠራለሁ ብሎ የሚያስብ በተናጠልና በቡድን የሚሹለከለክ ኃይል ነው።

ይሄ ወገን በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ሆኖ በተለያዩ የቤተክርስቲያኒቱ መዋቅሮች ውስጥ እንቅፋት እየፈጠረ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብቁ አገልግሎት እንዳትሰጥ ያዳክማል። የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር የበቃና የነቃ አገልግሎት ፈጽሞ ካህናትና ምእመናንን እንዳያረካ፤ በምእመናንና በሊቃውንቱ በቤተ ክርስቲያኒቱም አስተዳደር መካከል መለያየትና መጠራጠር እንዲነግሥ የበኩሉን ሚና ይጫወታል። የካህናትን ስምና ክብር በማጉደፍ ምእመናን ለክህነት ክብር እንዳይኖራቸው፤ የንስሐ አባትና ልጅ ግነኙነታቸው እንዲላላ ያደርጋል።  በካህናት ወይም በሊቃውንት አባቶች በኩል የሚታዩ ግድፈቶች ወይም ጥፋቶችን በማጯጯኽ አጠቃላይ የቤተክርስቲያኒቱ ድክመት አድርጎ በማወራረድ የሚያታልል፤ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ አካሔድ ተስፋ እንዲቆርጡ በጋዜጣና በመሳሰሉት ብዙኃን መገናኛዎች በመዝራት ትርፍ ለማግኘት የሚጥር ነው። ብርቱ አገልግሎት በመፈጸም የቤተክርስቲያኒቱን ተልእኮ ለመወጣት ጥረት የሚያደርጉ ማኅበራትን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን፣ መምህራንን፣ አባቶችን ስም በማጥፋት ከምእመናን ለመለይት ይንቀሳቀሳል። «ተሐድሶ» ለዚህ ግብሩ ከምእመናን ጀምሮ እስከ ታላላቅ አባቶች  ድረስ አውቀውም ሳያውቁም የአጀንዳው አስፈጻሚ ወይም መሰላል የሚሆኑ ድጋፍ ሰጭዎችን ለመመልምል ጥረት ያደርጋል:: እነዚህም አካላት የቤተክርስቲያኒቱን አሠራር እንዲያውኩ ብቻ ሳይሆን ገጽታዋን በማበላሸት መንጋው ደንብሮ እንዲበተን መሣሪያ ለማድረግ ነው:: የቤተክርስቲያኒቱን አገልጋዮች መለያ ለብሰው ወይም መስለው፣ በማይገባ ጊዜና ቦታ የማይገባ ነገር ሲያደርጉ በመታየት ምእመናንን በማስቆጣት ላይ ያሉ ሐሳዌ መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ባህታውያን ወዘተ የዚህ ስልት አስፈጻሚዎች ናቸው:: በመልካም ግብር ለመጽናት ባለመቻላቸው ተስፋ ቆርጠው አላግባብ በእንዝህላልነት የሚራመዱ አንዳንድ አገልጋዮችም የዚህ የጥፋት ዓላማ ተባባሪዎች እየሆኑ ነው:: ተግባራቸው ምእመናንን ከቤተክርስቲያን አስወጥቶ  የሚጥል በመሆኑ በውስጥ እየሠራ ያለው የ«ተሐድሶ» ገፊ ኃይል መሣሪያ ሆነዋል:: ቢያንስ ምእመናንን ላለማሰናከል ጥንቃቄ ሲያደርጉ አታይምና::

ከሁሉም በላይ አሳሳቢው አካሔድ ግን የቤተክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ ተልእኮ ወዴትም እንዳይራመድ አሳስሮ ለማስቀመጥ፤ ይህንን የ«ተሐድሶ» መረብ በጥሰው በማለፍ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት  የሚንቀሳቀሱ አካላትንም ከአስተዳደሩ በማ ጋጨት ወይም ለመከፋፈል በመሞከር ወዘተ ምንም ዓይነት ውጤታማ የአገልግሎት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የሚችለውን ያህል ጥረት ማድረግ ነው:: ቤተ ክርስቲያን ያላትን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ አውላ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ማቀላጠፍ እንዳትችል ለማድረግ፡ ከዚያም አልፎ የካህናቱን የኑሮ ሁኔታ ሊያሻሽሉ የሚችሉ ውጤታማ ፕሮጄክቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ ተግባራዊ እንዳይደረጉ፤ የቤተክርስቲያን የአገልግሎት ተቋማት የመፈጸም አቅም እንዳይጎለብት የተለያዩ መሰናክሎችንና ውዥንብሮችን ለመፍጠር ይጥራል:: ይህን ውዥንብር «ተሐድሶ» የሚፈልግበት ወሳኝ ምክንያት በቤተክርስቲያኒቱ አጠቃላይ አካሔድ አለመርካት እንዲኖር፤ ተስፋ መቁረጥም በምእመናንና ካህናቱ ዘንድ እንዲሰፍን፤ ከዚያም መከፋፈል እንዲፈጠር ለማድረግ ነው::በቤተክርስቲያን አካባቢ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ውዝንብሮችና ዓላማና ግባቸው የማይታወቁ መጠላለፎች በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ገፊ ኃይሎች ሆነው በስውርና በግልጽ የሚንቀሳቀሱ የ«ተሐድሶ» መረብ አባላትና ተባባሪዎቻቸው የሚፈጥሯቸው ውዝግቦች ናቸው::

እነዚህ ገጽታን በማጉደፍና ቁሳዊ ጥቅሞቻቸውን ለማርካት ቤተክርስቲያኒቱን እስከመሸጥ የተሰለፉ አካላት በሕግና በቀኖና መሠረት ቤተክርስቲያን እንዳትሠራ፤ በየትኞቹም ጉዳዮች ለቁጥጥር የሚያመች ማዕከላዊ አሠራር እንዳይዘረጋ ይታገላሉ:: ይህንንም የሚያደርጉበት ምክንያት አዲስ የኑፋቄ ትምህትን አንሸራቶ ለማስገባት ለሚተጉበት እንቅስቃሴያቸው የተመቹ ሁኔታዎችን  ለመትከልና ለ«ተሐድሶ» እንቅስቃሴ አውቀውም ሳያውቁም ገፊ ኃይል በመሆን ለተሰለፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ወረታ የሚሆን፣  ለሥጋዊ ፍላጎታቸው የሚጠቀሙበትን ንግድ በስብከተ ውንጌል ስም ለማስፋፋት ነው::

«ተሐድሶ» ቤተክርስቲያኒቱ ያላትን አሠራር በማስረጀት፣ ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮን ወደ ቤተክርስቲያን ለማንሸራተት ሲተጋ ለቤተክርስቲያን የሚያስፈልጋትን የአሠራር የመዋቅር እና የመፈጸም አቅም ተሐድሶ /Renaissance/  ግን ለመቅበር ይታገላል:: ቤተክርስቲያናችን በራሷ ሉዓላዊ አስተዳደር መመራት የጀመረችበት ጊዜ መቶ ዓመት ያልሞላው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዲሁም ከዚያም በኋላ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦች ባስከተሉት ጫና በአሠራር፣ በመዋቅርና በመፈጸም አቅም በተከታታይ ሊደረጉ የሚገባቸው የእድገትና የለውጥ እንቅስቃሴዎች ሳይታሰቡ፤ ሳይተገበሩም ቆይተዋል:: «ተሐድሶ» የተባለው ይህ የመናፍቃን ተላላኪ ደግሞ አስፈላጊውን የለውጥና የማሻሻያ እርምጃ በማፈን በአውሮፓ በመካከለኛው የታሪክ ዘመን እንደተደረገው በተሐድሶ ስም ሌላ የእምነት አስተምህሮን አንሸራቶ ለማስገባት ይሠራል::

ተፈላጊውን ማሻሻያ የሚጠላበት ምክንያት ቤተክርስቲያን በአፈጻጸም ደካማ እየሆነች ስትሔድ ምናልባትም በሚያስቆጣ ደረጃ ምእመናን ያልተደራጀና ከክርስትና ሥነምግባር ውጭ የሆነ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው በካህናቱ ላይ እንዲነሡ፤  ቤተክርስቲያንም እንድትበታተን ለማድረግ የታለመ ነው:: አሁንም በግልጽ እየታየ ያለው የአባቶች መወጋገዝና መከፋፈል እየጨመረ በጎጥና በዘር ላይ የተመሠረተ የተበታተነ አደረጃጀት እንዲኖር ለማድረግ ነው:: ይህንንም አሁን «ተሐድሶ» በግልጽ እየጻፈ በሚያወጣው መጻሕፍት ከእነ እገሌ ወገን ጳጳሳት ለምን አይሾሙም እያለ የሚያነሣው ከንቱ ልፍለፋ ይህን ያሳያል:: የካቶሊክ ቤተ እምነት በመካከለኛው የአውሮፓ የታሪክ ዘመን በነበረበት የጊዜውን ማኅበረሰብ ያለማርካት ችግር በተፈጠረው ተቃውሞ ቤተ እምነቱን ከሁለት የከፈለ ድንገተኛ ክስተት በ«ተሐድሶ» ስም ማስተናገዱ ይታወቃል:: በዚህ ያለው የመናፍቃን ተላላኪ «ተሐድሶ» ያንን መሰል ተከፍሎ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲፈጠር ያልማል:: ለዚህም ለተቃውሞ የሚያነሣሡ ብልሹ አሠራሮች በየደረጃው ባሉ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ እንዲሰፍን ገፊ ኃይል ሆኖ በውስጥ በሚሹለከለከው መረቡ በኩል ይጥራል:: ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በፊት በመል እክቱም ደጋግሞ እንደጠቀሰው ቤተ ክርስቲያን ጠፍረው የያዙአትን ኋላቀርና ብልሹ አሠራሮች በተሻለና ሰውና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ፣ መተማመንንና አንድነትን በሚያጸና አሠራር መተካተ እንዳለባቸው ያምናል:: ይህንን ማድረግ ካልቻልን «ተሐድሶ» «ለውጥ! ለውጥ!» በሚለው ድምፅ ውስጥ እነዚህን የአሠራር ችግሮቻችንን ሽፋን አድርጎ በግልጽ የጀመረውን ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ በሒደት አንሸራቶ ማስገባት የሚችልበት እድል እንሰጠዋለን:: ስለዚህ ያሉብንን የአሠራር ውስንነቶች በሁሉም ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን ተሳትፎ መቅረፍና ወደተፈላጊው ትንሣኤ ልቡና መድረስ አለብን:: ለዚህም ሁሉም የክርስቲያን ወገን ሓላፊነት ቢኖርበትም የብፁዓን አባቶች ድርሻ የጎላ ነው::

ብፁዓን አባቶቻችን በታሪክ አጋጣሚ ይህ የ«ተሐድሶ» መሰሪ ኃይል በውስጥም በውጭም በተደራጀበት ዘመን ላይ ይህቺን በብዙዎች መንፈሳዊ ተጋድሎ እዚህ የደረሰች ቤተክርስቲያን ባለደራዎች ናቸው:: አባቶች ለመንጋው የማይራሩ «ተሐድሶ»ን የመሰሉ ጨካኞች በታዩ ጊዜ ሁሉ ለራሳቸውና ለመንጋው እንዲጠነቀቁ መንፈስ ቅዱስ የዘወትር ማሳሰቢያን የሰጣቸው ናቸው:: በመሆኑም ጊዜው የሚጠይቀውን የጥንቃቄ እርምጃ ከሀገረ ስብከቶቻቸው ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ የሚወስዱበት፣ ለመንፈሳዊ ተጋድሎ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት ወቅት ነው:: ከምንም በላይ «ተሐድሶ» በአባቶችና በልጆች መካከል መለያየትን ለማስፈን የሚሠራ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ ያሉት ብፁዓን አባቶች የመፍታተት አቅም የሌላቸው፣ ለእውነትም የመቆም ቁርጠኝነት የሌላቸው አድርጎ ስለሚያሳይ ውጤቱ ቤተክርስቲያንን መጉዳቱ ብቻ ሳይሆን የብፁዓን አባቶችን ክብርና ስብእና የሚጎዳ ሁኔታ ሊከተል ይችላል::

የ«ተሐድሶ» ግብና ዓላማ መንጋውን ከበረቱ መበተን በመሆኑ አባት የምንሆ ንላቸውን ልጆች ከማሳጣቱም ሌላ በታሪክ ተወቃሽ ሊያደርግ የሚችል ነው:: ከዚያም አልፎ በአሠራሮቻችን ድክመት  ክብረ ክህነቱ ሊጎዳ ስለሚችል «ተሐድሶ» ለሚፈልገው ሁሉም ሰው ካህን ነው ወደሚለው ፕሮቴስታንታዊ  ጸረ ሃይማኖት አቋም ያሻግራል:: ስለዚህ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተሸሽገው ለሚሠሩ የትኞቹም ገፊ ኃይሎች እንቅስቃሴ የሚመቹ ክፍተቶችን መድፈን፤ በነገሮች ሁሉ የጸናና የተጠና ማዕከላዊ አሠራርን ማስፈን፤ የቤተክርስቲያኒቱ ቀኖናና ሕግጋት ተጠብቆ እንዲሠራ ቁርጠኛ አቋም መያዝ ይገባዋል::
ማኅበረ ቅዱሳን አባቶች እንዲረዱለት የሚፈልገውም ወሳኝ ቁም ነገር እነርሱ ጳጳሳት ሆነው የተሾሙላት ቤተክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት ክብርና ታሪክ ተጠብቆ፡  በብዙ ሊቃውንት ተጋድሎ ተጠብቆ ዘመናትን ተሻግሮ የተቀበልነው ማራኪ ሥርዓትም ቀጣዩ ትውልድ የማየትና የመሳተፍ እድል እንዲኖረው ማድረግ ነው:: የሃይማኖት ትምህርት በዚህ ረገድ አባቶች ለሚኖራቸው እርምጃ ሁሉ በየትኛውም መልክ ቢሆን ድጋፍ መስጠት ማኅበራችን የተቋቋመበት ዓላማ መሆኑንም ያምናል:: በመሆኑም ይህ እውን እንዳይሆን የሚታገሉ የ«ተሐድሶ» መናፍቃንን ሰርጎ ገብ የጥፋት አካሔድ ለመመከት ከአባቶች ቁርጠኛ አቋምና ተከታታይ ሥራዎች ሊኖሩ ይገባል::

ቆሞሳት ቀሳውስት ዲያቆናትና በአጠቃላይ ከብፁዓን አባቶች ቀጥሎ ሓላፊነት ያለባቸው የቤተክህነቱ ወገን ሁሉ ከአጥቢያ እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት ባለው አገልግሎት ውስጥ የዚህች ታሪካዊት ቤተክርስቲያን ባላደራዎች እንዲሆኑ መንፈስ ቅዱስ በጳጳሳት እጅ የሾማቸው የመንጋው ጠባቂዎች ናቸው:: በመሆኑም መንጋውን ለመበተን በውስጥና በውጭ ተደራጅቶ በዓይነት ብዙ ፈተናዎችን ለማስከተል እየሠራ ያለውን የ«ተሐድሶ» የኑፋቄ ፍላጻ በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ በጸሎት በጾም ከማምከን ጀምሮ ባልንጀሮቻችን በተለያዩ ምክንያቶች በ«ተሐድሶ» ገፊ ኃይል መረብ ውስጥ እየተጠለፉ የጥፋቱ ተባባሪ እንዳይሆኑ መጠበቅ ይገባናል:: የ«ተሐድሶ» እንቅስቃሴ በዋናነት ምስጢረ ክህነትን የሚክድ፣ ሁሉን እንደ ካህን የሚቆጥረውን ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ አንሸራቶ የማስገባት ፍላጎት ያለው መሆኑን በግልጽ በሚጽፋቸው መልእክቶች መረዳት ይቻላል:: በመሆኑም «ተሐድሶ» በተባለው የመናፍቃን ተላላኪዎች ተንኮል በሃይማኖት፣ በአካልም ሆነ በሥነልቦና የመጀመሪያው ተጎጂዎች የቤተክህነቱ ወገኖች መሆናቸው አሌ የማይባል ነው:: ስለዚህ በየደረጃው ባሉ የቤተክርስቲያናችን የአስተዳደር መዋቅሮች የሚፈጠሩ ችግሮች ዘገምተኛና ስልታዊ ያልሆኑ ኋላቀር አሠራሮች ሌሎችም ችግሮች የሚያስከትሉብንን ተጽእኖዎች ተስፋ ሳያስቆርጡን ወደተሻለ አሠራር ለመግባት  እየጣርን የእነዚህን መናፍቃን የውስጥና የውጭ እንቅስቃሴ በእግዚአብሔር ረድኤት በብቃት መቋቋም አለብን:: ፈተናውንም ልንሻገረው ይገባል:: ቤተክርስቲያኒቱ ያላትን ሀብት ስልታዊ በሆነ መንገድ ማኅበረ ካህናቱንና ከዚያም አልፎ  ለሀገር እድገት ትርጉም ባለው መልክ ባለመጠቀም የካህናቱ ኑሮ እየተጎዳ ገዳማትና አድባራት እየተፈተኑ ቢሆንም፤ ይህንን ውስጣዊ ችግር የሚፈታ ጠንካራና ዘመናዊ የአስተዳደር መዋቅር ተግባራዊ ለማድረግ ከመታገል ጋር የ«ተሐድሶ»ን መሰሪ መረብ መበጣጠስ አለብን::

ይልቁንም የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ቤተክርስቲያናችንን ለማዳከም ከአሁኑ የበለጠ ጠንካራ አሠራር ዘርግታ  ቀድሞ  ከነበራት ክብርና ታሪክ በላይ መሥራት እንዳትችል የሚፈልጉ በዓይነት ብዙ የሆኑ አጽራረ ቤተክርስቲያን በግልጽና በስውር የሚሠሩት ደባ በመሆኑ በፍጹም ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ተያይዘን መርዛቸውን ማርከስ አለብን:: በተለይ ከውስጥ ሆኖ ገጽታን በማጉደፍ ክርስቲያኖችን በየምክንያቱ በማስደንበር ገፍቶ ለማስወጣት የሚሠራውን የ«ተሐድሶ» ገፊ ሃይል እንቅስቃሴ ለማምከን ተባብረን መቆም አለብን:: ይህ ኃይል በጎ የሚመስሉ ገጽታዎችን ተላብሶ የሚጫዎት የጥፋት ተዋናይ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ካህናት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል:: «ተሐድሶ» በሚፈጠሩ ጥፋቶችም ሁሉ ምእመናን በካህ ናቱ እየፈረዱ፣ በጥላቻም ካህናቱን እያዩ እንዲሄዱ የማለያየት ተልእኮም ስላለው በነገር ሁሉ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል:: በየመዋቅሮቻችን ያሉ አስተዳደራዊ ዘይቤዎችንም  ፈጣንና አርኪ ለማድረግ ተገቢ የአሠራር ማሻሻያ ልናደርግ ይገባል:: ለዚህም መተባበር አለብን:: ይህንን ደግሞ የግድ የሚያደርገው ወቅቱ ነው:: ወቅቱ ግድ የሚለን «ተሐድሶ» እንደሚለው ሃይማኖታችንን እንድንለውጥ ሳይሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ሃይማኖታችንን የምናስተምርበት፣ የምናጸናበት፣ ያሉንን ሥርዓተ አምልኮ ለቀጣዩም ትውልድ የምናስተላልፍበትን የተሻለ አስተዳደራዊ ሁኔታ ማስፈን ነው:: ለዚህም ካህናት ሁሉ ሊተባበሩ ይገባል እንላለን::

ሰንበት ትምህርት ቤቶችም «ተሐድሶ» ቤተክርስቲያኒቱን ለማዳከም መሣሪያ ሊያደርጋቸው የሚፈልጋቸው የቤተክርስቲያኒቱ የአገልግሎት ተቋማት ናቸው:: በመሆኑም ይህንን ደባ ከማክሸፍ አንጻር የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እየቃኙ ወደ ከፍተኛ የስብከት ወንጌል መድረክነት ሊለወጡ ይገባል:: ሰንበት ት/ቤቶች መረዳት ያለባቸው ወሳኝ ነጥብ የአገልግሎት አሰጣጣችን ወደሚፈለገው ደረጃ አለማደግ በምእመናን ዘንድ ከፍተኛ የቃለ እግዚአብሔር ጥማት ይፈጥራል:: ይህ ደግሞ የራሳቸውን ንግድ ሊያጧጡፉ ለሚፈልጉ አንዳንድ ሰባክያንና ዘማርያን በር ከፍቷል::«ተሐድሶ» ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮን አንሸራቶ በማለማመድ ሊያስገባበት የሚፈልገው ክፍተት ይህ ነው::ስለዚህ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ከነበረው በተሻለ አፈጻጸም ውስጥ ሊገኙ ይገባል:: በአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው ውስጥ የሚደረጉ የትኞቹንም እንቅስቃሴዎች የመከታተል፣ የአጥቢያውን ሰበካ ጉባኤ በሚያከናውናቸው መንፈሳዊና ልማታዊ ተግባራት ውስጥ ድጋፍ መስጠት የአጥቢያውንም ምእመናን ማስተባበር በአጥቢያው ውስጥ እንግዳ ትምህርትና ተገቢ ያልሆኑ ሥርዓቶችን ለማስረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በግልጽ የመቃወም ሓላፊነትም አለባቸው:: አሁን አሁን በአንዳንድ ጠንካራ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እንደሚደረገው የአብነት ትምህርቶችን ለሕፃናትና ወጣቶች በመስጠት፣ ካህናትን የሚደግፉና የሚተኩ ወጣቶችን ማፍራት፣ ወቅቱን የሚዋጅ አጽራረ ቤተክርስቲያንን የሚያስታግስ ተከታታይ ትምህርቶችን አርኪ በሆነ መንገድ በዓይነትና በደረጃ ለይቶ መስጠት፣ ስልታዊ በሆኑ የመረጃ ቅብብሎሽ እየታገዙ የ«ተሐድሶ»ን ገፊና ጎታች ኃይል እንቅስቃሴ ለመግታት መተባበር አለባቸው:: በተለይ ወቅቱ ተራ በሆኑ የወጣትነት ስሜቶች የምንዘናጋበት ባለመሆኑ ቤተክርስቲያን ለዚህ ትውልድና ለዚህች ሀገር ማበርከት ያለባትን አስተዋጽኦ ማበርከት እንድትችል የማያቋርጥ ተሳትፎ ልናደርግ ይገባል::

ማኅበራትም ለቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት በተለያየ መንገድ ድጋፍ ለማድረግ የተቋቋሙ በመሆናቸው፡ የ«ተሐድሶ» ሤረኛ እንቅስቃሴ ሰለባና ተባባሪ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ ይገባል:: ማኅበራት ከመገንባት ይልቅ አፍራሽ በሆነ መንገድ ላይ ሳያውቁት እንዳይቆሙ የሚችሉትን ያህል ጥንቃቄ እያደረጉ ለቤተክርስቲያኒቱ አንድነት መሥራት አለባቸው::በተቻለ መጠን ቤተእግዚአብሔርን ማገልገል የሚፈልጉ የተለያዩ ማኅበራትን ማስተባበር የምትችልበትን አቅም ቤተክርስቲያን አግኝታ፣  ጠንካራ ማዕከላዊ አሠራር ሰፍኖ ተቀናጅተን መሥራት የምንችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ልንተጋ ይገባል:: የማኅበሮቻችን አባላት በውስጥና በውጭ ተደራጅቶ ቤተክርስቲያንን ለማዳከምና ለማፍረስ የሚጥረውን የ«ተሐድሶ» ተንኮል ነቅተው ሊከላከሉ፤ ለዚያ የተንኮል ሥራው ምቹ ሆነው የሚንቀሳቁ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ሊመክሩና ሊያስተካክሉ ካልሆነም ሊለዩ ይገባቸዋል እንላለን::

ምእመናን የዚህች የእግዚአብሔር የጸጋ ግምጃ ቤት በሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ተወልደው በቃሉ ወተት እያደጉ ያሉ፤ የአገልግሎቱ ደጋፊ፣ ተቀባይ፣ ተሳታፊም በመሆናቸው ቤተክርስቲያን ማለት እነሱ ራሳቸው እንደሆኑ መረዳት ይገባቸዋል:: አባቶቻችን የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ሆኖ ለመባረክ ክርስቶስ ያደረገልንን ማዳንም አምነው፤ በየዘመናቱ የምንነሣ እኛ ልጆቻቸውም በዚያ ጸንተን ለቀጣዩም ትውልድ ባለአደራ እንድንሆን አድርገዋል:: ይህንን ሓላፊነት የተረዱ በየዘመኑ የተነሡ ምእመናን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ በመክፈል ቤተክርስቲያናቸውን ሊያፈርስ ከመጣ የዲያብሎስ ሠራዊት ጋር ተጋድለዋል:: አሸናፊም ሆነዋል:: በዚህም ምክንያት ምዕተ ዓመታትን ተሻግሮ የመጣን ማራኪ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ሕይወትን የሚሰጥ ሃይማኖትን ለማየትና ለመመስከር በቅተናል:: የያሬድን ዜማ፣ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ሰዓታት የበርካታ ሊቃውንትን ትምህርትና ቅዳሴ የመስማት እድል አግኝተናል::

ይህንን እድል ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፉ አደራ በእኛ ትውልድ ላይ በወደቀበት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ ደግሞ በቀጣዩ ትውልድ ውስጥ በሚሰበሰበው መንጋ ላይ መጨከን የለብንም:: በየዘመናቱ ቤተክርስቲያንን ከአገልግሎት ለማዘግየት የሚወረወረው የሰይጣን ፍላጻ ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ይኖራል:: አባቶቻችንም በእግዚአብሔር ረድኤት ያ ፍላጻ ቤተክርስቲያንን ከአገልግሎት እንዳያስተጓጉላት ዋጋ ከፍለዋል:: አሁን ደግሞ ከውስጥም ከውጭም የሚንበለበል «ተሐድሶ» የተባለ ፍላጻ እየወጋን ይገኛል:: የዚህ ሁሉ ውጊያው ዓላማ እናንተን ምእመናንን ከመንጋው ኅብረት ለይቶ ለምድ ለለበሰ ተኩላ ለመስጠት፤ ከተቻለም ራሳቸው ምእመናን የምታገለግላቸውን ቤተክርስቲያን በማጥፋቱ ሒደት እንዲሳተፉ ለማድረግ ነው:: ስለዚህ ምእመናን በዚህ አካሔድ ላይ በመንቃት ጥንቃቄ በተሞላበት እርምጃ ውስጥ እንድንገባ ያስፈልጋል:: በተለይ ትኩረት የሚስቡ የተለያዩ ሁኔታዎችን በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሒደት ውስጥ በማስገባት ብዙ መንጋ ከሰበሰቡ በኋላ ገንዘቡን  ከመብላት አልፈው በሒደት አዲስ ትምህርትን አምጥቶ በማለማመድ ወደ ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ ማንሸራተት ይፈልጋሉ:: በዚህም ግማሹን መንጋ ይዞ ለመንጎድ ቀውንም በመምህራንና ዘማርያን ላይ እምነት በማሳጣት በቤተክርስቲያኒቱ የትኛውም የስብከተ ወንጌል ማዕድ ላይ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ነው:: በመሆኑም ምእመናን ክርስቶስን ትኩር ብሎ ከማየት አዘንብለው በዓለም እንዳለው የግለሰቦች ዝና ገንቢና ሳያውቁት ለሥጋዊና ቡድናዊ ፍላጎታቸው መጠቀሚያ እንዳይሆኑ፤ ብሎም ውሎ አድሮ ለሚያስከትሉት ቤተክርስቲያንን የማዳከም ዘመቻ ተባባሪ እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባል:: ቤተክርስቲያን በአገልግሎት ሒደት ውስጥ ያሉባት ክፍተቶች እንዲሞሉ በጸሎት ከመትጋት ጋር የ«ተሐድሶ» ዘርፈ ብዙ ወጥመድ ለመበጣጠስ መቆም አለብን::
በአጠቃላይ «ተሐድሶ» ትናንት ሲያደርግ የነበረውን የተላላኪነት ሤራ ተልእኮ የሰጡት አካላት የሚሰጡትን የገንዘብና የቀሳቁሰ ሰፊ ድጋፍ በመጠቀም ከውጭ ፈሪሳዊ በሆነ መንገድ ከውስጥ ይሁዳዊ በሆነ ስልት ለመዝመት እየጣረ ነው:: ሰይጣን በርካታ ጠላቶችን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እያዘመተ ቢሆንም ከውጭ ያለውን ለማስታገስ እንዳትችል አንቆ የያዛትን የ«ተሐድሶ»ን መሰሪ ኃይል መለየትና በቤተክርስቲያናችን ውስጥ አገልግሎቱን በቅልጥፍና የሚመራ አስተዳደራዊ ትንሣኤ እንዲኖር ማድረግ ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን የጸና እምነት አለው:: ጉዳዩም የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያምናል፡፡ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችልም ያስባል:: ነገር ግን በተናጠልም ይሁን በኅብረት ክርስቲያናዊ ግዳጃችንን መወጣት ለነገ የማይባል ነው:: የራሳችንን ቤተክርስቲያን እንዳንጠብቅ የሚከለክለን ወይም በቁማችን ዓይናችንም እያየ ስትፈርስ እዩአት የሚለን አካል አለ ብለን አናምንም:: ምክንያቱም ቤተክርስቲያኒቱ ወልድ ዋሕድ ብለው የሚያምኑ፣ የቤተክርስቲያኒቱን ቀኖናና ሕግ ጠብቀው፣ አስከብረው የሚሔዱ ብፁዓን አባቶች፤ ቀን ከሌሊት በሚሰጡት የማያቋርጥ አገልግሎት መንጋውን የሚጠብቁ ካህናት፤ በዝማሬ በውዳሴ የሚተጉ ሰንበት ተማሪዎች፤ ሕይወት የሚያገኙባትን ኅብረት በሚሰጡት ዐሥራት በኩራት የሚጠብቁ ምእመናን ቤተክርስቲያን ነችና:: በተለይም ቅጥረኛ ሆኖ በውስጣችን ለመሸመቅ የሚጥረውን ጨካኝና መሰሪ የ«ተሐድሶ» እንቅስቃሴ መታገስ የማይቻል ነው:: ክቡር ዳዊት «ጠላትስ ቢሰድበኝ በታገስሁ ነበር፤ የሚጠላኝም አፉን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር፤ አንተ ሰው አንተ ግን እንደራሴ ነበርህ» /መዝ.4÷02/ እንዳለ የ«ተሐድሶ» ፍላጻ ከውስጥ የሚወረወር በመሆኑ የከፋ ነው:: ስለዚህ እኛ ሁላችን ቤተክርስቲያናችንን ተባብረን የመጠበቅ ሓላፊነት አለብን::  ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ረገድ ያለበትን ሓላፊነት በእግዚአብሔር ረድኤት ከሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ጋር በመመካከር በተከታታይ ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል::

                                                   ምንጭ፡ ሐመረ ተዋሕዶ ነሐሴ 2002 ዓ.ም.