በዓለም እያሉ ከዓለም ውጪ መኖር

በዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በበሳል ትምህርቱ በመንፈሳዊ ጥብዐቱና በፍጹም መንፈሳዊ ሕይወቱ በቤተ ክርስቲያናችን የታወቀ አባት ሲሆን ኑሮውም የብህትውና ነበር። ካስተማራቸው በርካታ ትምህርቶቹ መካከል ውስጥ አንድ ክርስቲያን በምድር ሲኖር ሰማያዊውን ሕይወት እንዲኖር ነው። ይህንንም ያስተማረበትን ትምህርት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

“እግዚአብሔር የሚወዳችሁ እግዚአብሔርን የምትወዱ ወንድሞቼ ሆይ እነሆ ሰማያውያን ሆነናል፡፡ ዘበሰማያት የሚያሰኝ ሥጋውንና ደሙን ተቀብለናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ከዚህ ነገር የተነሣ እንፈራ ዘንድ እንንቀጠቀጥ ዘንድ ይገባናል፡፡ ሕሊናችንም ሰማያዊውን ማሰብ ትቶ ምድራዊውን ማሰብ እንዳይሆን መሆን ይገባናል፡፡ ሰማያዊነትን የሚወድ ሰው ምድራዊውን እንዳያስብ መሆን ይገባዋልና፡፡ ምድራዊውን ነገር ማሰብ ሰማያዊውን ነገር አለማሰብ ከክፉ ሕሊና ከክፉ ፈቃድ የሚገኝ ስለሆነ፡፡ በዚህ ዓለም እየኖርን እንደሌለን መሆን ይገባናል፡፡ ሰማያዊ አነዋወርን የሚወድ ሰው በዚህ ዓለም እየኖረ እንደሌለ መሆን ይገባዋልና፡፡ በዚህ እየኖሩ እንደሌሉ መሆን ለበጎ ሕሊና ከበጎ ፈቃድ የሚገኝ ስለሆነ፡፡”

ለአምላካችን ክብር ምስጋና ይግባውና እኛ በምድር ሳለን በባለሟልነት ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን በምድር ሳለን ፍጹማን ሆነን ሰማያውያን እንድንሆን ዛሬ ምን ያተጋናል? “የሰማይን ጌታ ካየሁት እኔ ሰማያዊ እሆናለሁና፡፡ እርሱ ጌታ አባቴና እኔ መጥተን እናድርበታለን” እንዳለ፡፡ ወንድሞች ሆይ እንዲህም ከሆነ  ራሳችንን ማኅደረ እግዚአብሔር እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡
ሰማይ እጅግ ያማረች ናትና፤ በተፈጥሮዋም ፈጽማ የበራች ናትና በክረምት አትጠቁርምና መልካም አይለወጥምና ራሳችንን በሰማይ እናድርግ፡፡ ደመናትም መጥተው ከታች ቢሸፍኑዋት ከላይ የሚያበራ ብርሃን አላት፡፡ እንደዚሁ እኛም ጨለማ የማያፈራርቀው እውነተኛ ፀሐይ ጌታችንን ገንዘብ እናድርግ፡፡
አስቀድሞ እስካሁን በሰማይ እንሆን ዘንድ ይቻለናል ብዬ ተናገርሁ፡፡ ዳግመኛም ከእንግዲህ ወዲህ ከሰማይ ይልቅ ያማርን የተወደድን እንሆን ዘንድ ይቻለናል ብዬ እናገራለሁ፡፡ ፀሐይን የፈጠረ ጌታ ክብር ምስጋና ይግባውና  በውስጥ በአፍአ ቢያድረብን በእውነት ከሰማይ ይልቅ ያማርን የተወደድን እንሆናለን ብዬ እመልሳለሁ፡፡
ሰማይስ ንጽሕት ናት ብርይት ናት፡፡ በክረምት ደመና በሌሊት ጨለማ አያገኛትም፡፡ እንደዚህም ከሆነ መከራ የሚያመጣብንን፤ ቀቢጸ ተስፋ፤  ከሚያመጣብን ጠላት ተንኮል እንታገሥ ዘንድ ይገባናል፡፡
ከምድራዊ ሥራ የራቅን የተለየን እንሆን ዘንድ ይገባናል?ሰማይ ከምድር የራቀች ናት፡፡ እንደዚህም ሁሉ ሰውነታችንን ምድራዊ ነገር ከማሰብ አርቀን ሰማያዊ ነገር እናስብ ዘንድ ይገባናል፡፡ ማኅደረ እግዚአብሔር እንሁን፡፡ ትሩፋት ሠርተን ከፍጹምነት እንድረስ፡፡
ከዚህ በኋላ  እንደ ጉንዳን እንደ ትል እናያቸዋለን፡፡ይህ ዓለምና በዓለም ያለው ሃብት ሁሉ አላፊ ጠፊ እንደሆነ እንረዳለን እናያለን። ድኃውን ባለጸጋውን ብቻ አይደለም፡፡ ንጉሡንም ራስ ቢትወደዱንም ቢሆን እንዲህ አድርገን እስከማየት ድረስ ነው እንጂ፡፡ የንቀተ ያይደለ የብቃት ነውና እንዲህ አለ፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡን ይጐዳናል አንድም ይጠቅመናል ብለን አናየውምና፡፡ ሕዝባዊውን አይጐዳንም አይጠቅመንም ብለን ለይተን አናውቅምና፡፡ ወርቁንም ብሩንም ለይተን አንድም ይጠቅመናል ብለን አናውቅምና፡፡ ከቀይ ሐር ከነጭ ሐር የተሠራውንም ልብስ ለይተን አንድም ይጠቅመናል ብለን አናውቀውምና እንደትል እናያቸዋለን፡፡
በዚያን ጊዜ ሁከት ሥጋዊ ፍርሃት ሥጋዊ የለም፡፡ በዚህ ዓለም ለሚኖር ሰው ከዚህን ያህል ማዕረግ መድረስ እንደምን ይቻለዋል የሚል ሰው ቢኖር ከዚህ ማዕረግ የደረሱ አበውን ጠቅሰን እንመልስለታለን፡፡ ንኡድ ክቡር ጳውሎስ በዚህ ዓለም ይኖር አልነበረምን፡፡ በዚህ ዓለም ሳለ ከሰማይ ደርሶ ከዚያ ተመልሶ የሰማይን አነዋወር በውኑ ይናገራል ብዬ እመልስለታለሁ፡፡ እርሱ ከሰማይ መድረሱን ለምን እናገራለሁ እግዚአብሔርን እናገኘው ዘንድ ካሰብን ፍቅሩን ክብሩን እንደሚገልጽልን እንረዳለን፡፡
እንዲህ ከሆነ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ዓለም አንመልከት፡፡ ጳውሎስ የሚታየውን ዓለም ይመለከት እንዳልነበረ ተረዳኽን? ወዳጄ ሆይ ከምድራዊ ግብር ሕሊናውን በለየ ጊዜ ከሁሉ በላይ እንዳደረገው ተረዳህን? ከጠፈር ብቻ ከዓለም መላእክት ብቻ አይደለም፡፡ የሉም እንጂ ያሉ ቢሆን ከሌላውም ፍጥረት በላይ እንዲያደርገው ተረዳህን?
መንግሥተ ሰማያት መግባትን ተስፋ አድርገን ግን ከትሩፋት ብንለይ በንዋመ ሀኬት /ከክፋትና ከተንኮል እንቅልፍ/ ብንያዝ ፈጽሞ ትሩፋት መሥራት አይቻለንም፡፡ መንግሥተ ሰማያትንም መውረስ አይቻለንም፡፡ እንዲህም ከሆነ ፈጽሞ ትሩፋት መሥራትን ትወዱ ዘንድ መንግሥተ ሰማያትን ትወዱ ዘንድ ወንድሞቼ ሆይ እማልዳችኋለሁ፡፡
የቅዱሱ በረከት ከሁላችን ጋር  ፀንቶ ይኑር።

/ምንጭ፡- ተግሣፅ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወረቅ ገጽ 175-184/