ደብረ ምጥማቅ

የድንግል ማርያም መገለጥ

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኲሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር፤ የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ሁሉ በፊትሽ ይማለላሉ፤” በማለት ትንቢትን እንደተናገረላት ብዙዎች ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያምን ተገልጻላቸው ለማየት ተመኝተዋል፤ ልመናቸው ተሰምቶላቸው የአምላክ እናት ተገልጻላቸው እጅግ አስደናቂ ውበቷን አይተዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በደብረ ምጥማቅ የነበሩ ምእመናን ሌሎችም ብዙዎች ንጹሓን ክርስቲያኖች ይገኙበታል፡፡ (መዝ. ፵፬፥፲፪)

ልጇ አስቀድሞ በዘመነ ሥጋዌዉ በደብረ ምጥማቅ እንደምትገለጽ በገባላት ቃል ኪዳን መሠረት ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽ፣ ከአርመንያ፣ ከሶርያ፣ ከሮም፣ ከጽርዕ፣ ከፋርስ በምድረ በደብረ ምጥማቅ ድንኳን ተክለው፤ አጐበር ጥለው ከግንቦት ፳፩ ቀን ጀምረው እስከ ፳፭ ቀን ድረስ በፍጹም ደስታ የድንግልን በዓሏን ማክበር ይጀምራሉ፤ “ወድንግልሂ ታስተርእዮሙ በእሉ ኀምስ መዋዕል ዘእንበለ ጽርዐት ምስለ መላእክት ወጻድቃን ወሰማዕት ምስሌሃ” ይላል፤ እመቤታችን ከግንቦት ፳፩-፳፭ ያለማቋረጥ ከመላእክት፣ ከሊቃነ መላእክት፣ ከነቢያት፣ ከሐዋርያት፣ ከጻድቃን፣ ከሰማዕታት፣ ከደናግል እና ከመነኮሳት ጋራ ሁና ትገለጽላቸው ነበር፤ አማኒውም ኢአማኒውም ያያት ነበር፤ ያመኑት ክርስትያኖች እምነታቸው ሲጸናላቸው፤ ያላመኑት ደግሞ እያመኑ ከእግዚአብሔር ወልድ ከልጇ ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና ይቀበሉ ነበር፡፡

በጒልላቱ ላይ ስትገለጽ በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ንጽሕት የሆነችው የቅድስት ድንግል ማርያም የፊቷ ውበትና ብርሃን እጅግ ድንቅ ነበርና ካህናቱም ሕዝቡም ሁሉ ልክ እንደ ኤልሳቤጥ “የጌታችን እናት ለእኛ ትገለጪ ዘንድ እኛ ምንድን ነን” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ርሷም ትባርካቸው ነበር፡፡

የእመቤታችን ፍቅር በእጅጉ የበዛለት አባ ጽጌ ድንግልም በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ተገልጻ ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት ለርሱም ትገለጽለት ዘንድ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፉ ላይ፤ “አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሑ መዓልተ ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ፤ የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለዐምስት ቀናት ያህል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያህል ደስ ታሰኚ ኖሯል! በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው፤” በማለት ተማፅኗታል፡፡

የእመቤታችን ታማኝ ወዳጅ አባ ጽጌ ድንግል በተመስጦ በመሆን እጅግ ድንቅ የሆነችውን የአምላክን እናት ሥዕል ካየ በኋላ ይህንን የምስጋና ቃላት ለርሷ ያቀርባል፤ “ሥዕልኪ ጽግይተ ላሕይ ዘከመዝ ትኤድም በዓለም እፎ ይሤኒ በሰማይ ላሕየ ገጽኪ ማርያም ሐሤተ ትእምርትኪ እጽገብ አስተርእዪኒ በሕልም እስመ አውዐየኒ ነደ ፍቅርኪ ፍሕም አጥፍኦቶ ዘኢይክል ዝናም፤ ማርያም ሥዕልሽ በዓለም እንዲህ የምታበራ ከሆነ በሰማይ የፊትሽ መልክ ምን ያምር! አንቺን ከማየት የሚገኘውን ደስታ እጠግብ ዘንድ በሕልም ተገለጪልኝ፤ ዝናብ ሊያጠፋው የማይቻለው የፍቅርሽ እሳት አንድዶኛልና፤” ብሏል፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህነን መገለጧን በእንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ፡- “ኦ ንግሥት ይገንዩ ለኪ ነገሥት ወለኪ ንግሥታት ይትቀነያ ወኪያኪ የአኲታ ወለስምኪ ይገንያ ወለኪ ይሰግዳ ወለክብርኪ የሐልያ ጢሮስ ወሲዶና ሰብአ ግብጽ ወኢትዮጵያ ፊንቂ ወሮምያ ማሮን ወአርማንያ በሥነ ጸዳልኪ ይትፌሥሓ ወበላሕይኪ ይትሐሠያ፤ ንግሥት ሆይ ነገሥታት ለአንቺ ያገለግላሉ፤ ነግሥታትም አንቺን ያመሰግናሉ፤ አንቺንም ያሞግሳሉ፤ ለስምሽም ያጐነብሳሉ፤ ለአንቺ የጸጋ ስግደትን ይሰግዳሉ፤ ለክብርሽም ምስጋናን ያቀርባሉ፡፡ ጢሮስና ሲዶና የግብጽና የኢትዮጵያ ሰዎች፣ ፊንቄና ሮምያ፣ ማሮንና አርማንያ በወጋገንሽ ውበት ደስ ይሰኛሉ፤ በደም ግባትሽም እሰይ ይላሉ፤” በማለት ገልጦታል፡፡

ልቡናቸው በእጅጉ የበራላቸው አሁን እንዳለንበት ዘመን የቃላትም የምስጋናም ድርቅ ያላገኛቸው በምሥጢር ባሕር የዋኙ ቀደምት ሊቃውንት ስለ አምላክ እናት ውበት አምልተው አስፍተው ጽፈዋል፡፡

የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስም “እመቤታችን በሁሉም እርምጃዎቿ ጐበዝና የተከበረች ነበረች፤ የምትናገረው በጣም ጥቂት ሲሆን ርሱም ለማድረግ አስፈላጊ በሚሆንበት ብቻ ነበር፤ በጣም ዝግጁ ሆና የምትሰማና በቀላሉ ንግግር ለማድረግ የምትችል ናት፤ ለእያንዳንዱ ሰው አክብሮትና ክብር (ሰላምታ) ትሰጣለች፤ ቁመቷ መኻከለኛ ነው፤ አንዳንዶች ግን ቁመቷ ከፍ ያለ እንደነበር ይናገራሉ፤ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር ያለምንም ፍርሀት በግልጽነት ያለምንም ሳቅና መጯጯኽ ትናገራለች፤ በተለይ ፈጽማ ለቁጣ የምትጋበዝ አልነበረችም፤ መልኳ እንደ ደረሰ የስንዴ አዝመራ ያማረ ጸጒሯ ቀይማ ነው፤ ዐይኖቿ ብሩሃትና የዋህ የሆኑ ቀለማቸውም ፈዘዝ ያለ ቡናማ ሆኖ የዐይኖቿ ብሌኖች የዘይት-አረንጓዴ ይመስላል፤ የዐይኖቿ ቅንድብ (ሽፋሽፍት) ከፊል ክብና ደማቅ ጥቁር ናቸው፡፡ አፍንጫዋም ረዥም፣ ከናፍሮቿ ቀይና ምሉእ ሲሆኑ በቃሎቿ ጣፋጭነት የተመላባቸው ነበሩ፤ ፊቷ ክብ እንቁላልማ ዐይነት ቅርጽ ነበረው፡፡ እጆቿ ረዥምና ጣቶቿም በጣም ረዣዥም ነበሩ፤ ከማንኛውም ያልተገባ ኩራት ሙሉ በሙሉ የነጻች ስትሆን ግድ የለሽነት ፈጽሞ አልነበረባትም፤ የሚመጡትን ነገራት በፍጹም ትሕትና ትቀበል ነበር፤ ተፈጥሯዊ ቀለማት ያላቸው፤ ማለትም በቤት ድር የተሠሩ ልብሶችን ትለብስ ነበር፤ ይህም በእጅጉ አብሯት የሚሄደው አለባበስና ይህ እውነታ በራሷ ላይ በምታደርገው ቅዱስ ልብስ አሁን ቅሉ ሊረጋገጥ የሚችል እውነታ ነው፤ በመንገዶቿ ሁሉ በመለኮታዊ ጸጋ የተመላች ነበረች፤” ሲል ስለ ድንግል ማርያም ገልጿል፡፡

የመልክአ ማርያም ደራሲ የአምላኩን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፊቷን ለማየት ሽቶ “ሰላም ለመልክእኪ ዘተሠርገወ አሜረ ዘያበርህ ወትረ ፍቅርትየ አንቲ እንተ ታበድሪ ፍቅረ አርእዪኒ ገጸ ዚኣኪ ማርያም ምዕረ ዘኢይሰምዖ ካልእ እንግርኪ ነገረ”
፤ዘወትር የሚያበራ ፀሓይን ጌጥ ላደረገ መልክሽ ሰላምታ ይገባል፤ ፍቅርን የምትመርጪ (የምታስቀድሚ) አንቺ ፍቅረኛዬ ማርያም ሌላ የማይሰማው ነገርን እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ያንቺን ፊት ግለጪልኝ፤” በማለት ተማፅኗታል፡፡

ልክ እንደ ርሱ የአምላክን እናት ፊቷን ለማየት የተመኙ ብዙዎች ቅዱሳን ነበሩ፤ ከአበው መኻከል አባ ይሥሐቅ እመቤታችንን በፍጹም ልቡናው ከመውደዱ የተነሣ ከሠርክ ጸሎት በኋላ ሌሎች መነኮሳት ለመኝታ ወደ የበኣታቸው ሲሄዱ ርሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ቆሞ በፊቷ እየተማለለ እና ሦስት መቶ ስግደትን እየሰገደ ይጸልይ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ስግደቱም “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አርእየኒ እመከ አሐተ ሰዓተ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንዲት ሰዓት እናትህን አሳየኝ” እያለ ተማጽኗል፡፡ ለሰባት ዓመት ከቈየ በኋላ፤ በታላቅ ግርማ ተገልጻለት የአምላክን እናት ፊት ለማየት በቅቷል፤ ርሷም ምን እንደሚሻ ስትጠይቀው የንግሥተ ሰማይ ወምድር፤ የርሷን ገጽ ያዩ ዐይኖቹ ሌላ ነገርን ማየት እንደማይፈልጉና ከልጇ እንድታማልደው ብቻ ለመናት፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም ከሦስት ቀን በኋላ የዕረፍቱ ቀን መሆኑን ካሳውቀችው በኋላ ባርካው ወደ ሰማይ ዐረገች፤ ይህ ቅዱስ አባት ይሥሐቅ መልኳን የማየት ክብር ካገኘ በኋላ በሦስተኛው ቀን ዐርፏል፡፡

በመሆኑም ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ የተገለጠችላቸው ምእመናን የአምላክን እናት አይተው እንደተደሰቱ፤ ዛሬም ለእኛ ለልጆቿ በረድኤት ትገለጽልን ዘንድ አበው ካህናት ሌሊቱን በሰዓታት ምስጋና “ንዒ ኀቤየ ኦ ድንግል ምስለ ወልድኪ ፍቁርኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትባርኪ ላዕሌነ፤ ድንግል ሆይ ከተወዳጅ ልጅሽ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ወደ እኔ ነዪ እኛን ትባርኪ ዘንድ በእኛ ላይ በረከትን እንድታሳድሪ” በማለት ይማፀኗታል፡፡ በገዳም እና በበረሓ ያሉት አበውም ምስጋናዋን በማድረስ ፍጹም በረከቷን ሽተው በፊቷ ይማለላሉ፤ ርሷም ለሱባኤዋ በወደቁበት በረሐ እየተገለጸች በረከቷን ታድላቸዋለች፡፡

የአምላክ እናት ዛሬም ለእኛ ለምንወድሽ ለልጆችሽ ትገለጪልን ዘንድ እንማፀንሻለን፡፡