“ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ትንቢተ ዮናስ ፪፥፲)

እግዚአብሔር ለነፍሳችን ብቻ ሳይሆን ለምድራዊ ሕይወታችንም ያስባል፤ ባዶነት ሲሰማን፣ ደስታ ከእኛ ሲጠፋ፣ ጭንቀትና መከራ ሲከበን ነፍሳችን ትዝላለች፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ነፍሴ አንተን ተጠማች፤” እንዳለው ነፍስ ፈጣሪዋን ትፈልጋለች፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ፈጠረው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡” በእያንዳንዳችን ያለችው ነፍስ ሕያው በመሆኗ ፈጣሪያችንን እንፈልጋለን፡፡ (መዝሙር ፷፪፥፩፤ ዘፍጥረት ፪፥፯)

ነቢዩ ዮናስ አምላኩን ሸሽቶ ወደ ተርሴስ ከተማ በመርከብ ሲሄድ ማዕበሉ በተናወጠ ጊዜ  መርከበኞቱ ወደ ባሕር እንደጣሉት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር አሳውን አዘዘው፤ የምድር አራዊቶች፤ እንስሶች እንዲሁም የባሕር ውስጥ ፍጡሮች፤ ነፍሱ፤ ማዕበሉ ድንጋዩ ሁሉ ለእግዚአብሔር ይታዘዛልና፡፡

በቅጽበትም ዓሣው መጥቶ ዮናስን ዋጠው፡፡ በዚያም ለሦስት ቀን ቆየ፤ ነገር ግን ማንም ሊደርስለት እንደማይችል በመረዳቱ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ “ውኆች እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ፤ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ነበረ፤ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠምጥሞ ነበር፡፡ ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ፤ በምድርና በመወሪያዎችዋ ለዘለዓለም ተዘጋሁ፤ አንተ ግን÷ አቤቱ አምላኬ ሕይወቴን ከጒድጓድ አወጣህ፡፡ ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን አሰብኩት፤ ጸሎቴም ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች፤ ከንቱነትና ሐሰትን የሚጠብቁ ምሕረታቸውን ትተዋል፡፡ እኔ ግን በምስጋና ቃል በቃል እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልኩትንም እከፍላለው፤ ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡” ስለሆነም የታዘዘው ዓሣ ዮናስን ነነዌ ከተማ መግቢያ በር ላይ ተፋው፡፡ ለእኛም እንዲሁ ባሰብነው መንገድ ሳይሆን እግዚአብሔር በሚያውቀው ለእኛ የሚጠቅመንን ያደርግልናል፡፡ (ትንቢተ ዮናስ ፪፥፮-፲)

ዛሬ እያንዳንዳችን በራሳችን ኃይልና ችሎታ የምንኖር ይመስለናል፡፡ ሁሉን ነገር የሚያዘጋጅልን እግዚአብሔር እንደሆነ ግን አናውቅም፡፡ አንድ እናት ጡቷ ወተት የሚያፈሰው ልጅ ስትወልድ ነው፤ ከዚያ በፊት ወተት አይኖራትም፤ ልጇንም በተፈጥሮ በተዘጋጀላት መግባ ታሳድጋለች፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ ረቂቅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች በምድር ላይ ረኀብ የበዛው በሰው ቁጥር መብዛት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን እግዚአብሔር “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት” ብሏል፤ የፈጠረን የሚያስፈልገንን ሁሉ አዘጋጅቶ ነውና፤ ባለመዋደዳችን እንጂ የሚበላ አላጣንም፤ መንገድ ላይም ሆነ የቤታችን በር ላይ ግን የእኔ ቢጤ ወድቆ ሊሆን ይችላል፤ ድሀውን አንስተን ለማብላትና ለማጠጣት የምንፈልግ ግን ጥቂቶች ነን፡፡

ነቢዩ ዮናስ እግዚአብሔርን ሲለምነው ጸሎቱን እንደሚሰማው በማመኑ ዳነ፤ የዚህ ሀገር ሰዎች ግን በሕመምና በበሽታ ሲሠቃዩ እንዲህ ይላሉ “ጥቁር አንበሳ፣ የካቲት፣ ዘውዲቱ እንዲሁም ሌሎች ሆስፒታሎች ሄድኩ፤ እስኪ ደግሞ ወደ እንጦጦ ሔጄ ጸበሉን ልሞክረው”፡፡ ነገር ግን ጸበልን ልሞክረው ተብሎ መጠመቅ እምነት የጎደለውና ከክርስቲያናዊ ሥርዓት ውጪ የሆነ ተግባር በመሆኑ ከደኀነት ይልቅ ጥፋትን ያመጣል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ድውያንን በፈወሰበት ዘመነ ሥጋዌ ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችው ሴት ከፊቱ እንኳን ልቁም ሳትል፤ የልብሱን ጫፍ የዳሰሰሁ እንደሆነ እድናለሁ፤” ብላ በማመኗ ልትፈወስ ችላለች፡፡  (ማርቆስ ፭፥፳፰)

በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈው ደግሞ የማርያምና ማርታ ወንድም አልዓዛር ሲሞት ጌታችን “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም አቤቱ ከተኛስ ይነቃል፤ ይድናልም፤ አሉት፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መሞቱን ነገራቸው፤” (ዮሐንስ ፲፩፥፲፩-፲፭)

አልዓዛር ከሞተ ከአራት ቀን በኋላ ጌታ ወደ መቃብሩ ሲሄድ ማርያምና ማርታ ተስፋ ቆርጠው ነበር፡፡ አምላክ ግን የሚሠራውን ያውቃልና፤ “የት ቀበራችሁት” ብሎም ጠየቃቸው፤ እነርሱም የቀብር ስፍራውን አሳዩት፡፡ ጌታም፤ “አልዓዛር ና ወደ ውጭ ውጣ” ሲለው ሞቶ የነበረው እንደተገነዘ፥ እጁንና እግሩንም እንደ ታሰረ፥ ፊቱም በሰበን እንደ ተጠቀለለ ወጣ፤” ምንም ለማይሳነው አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ከሞት አስነሳላቸው፡፡  የሞተውን አልዓዛርን ቢያስነሳው ፈሪሳዊያን ከሰውት ነበር፤ የእኛም ልብ እንደዚያ ነው፤ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ስለሆነ አይቶም ማመን አይችልም፤ ዓይኑ በክፋት ታውሯልና፡፡ (ዮሐንስ ፲፩፥፴፬፥፵፫)

እግዚአብሔር ከበሽታ ይፈውሳል፤ ከችግርና መከራም ይሰውራል፡፡ በየጸበል ቦታው ተጠምቀው ከኤች አይ ቪ፣ ከካንሰር እና ከሌሎች በሽታዎች የተፈወሱ ሰዎች እንዳሉ ዓይናችን እንዲሁም የሕክምና ማስረጃዎች ምስክሮች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ኃያል አምላክ፤ ሥራውም ድንቅ ነው፤ ተአምራትንም ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ድኅነተ ሥጋንም ሆነ ድኅነተ ነፍስን ከእርሱ ለማግኘት እምነት ያስፈልጋል፡፡

በሕይወታችን ውስጥ መፍትሔ የለውም ብለን ተስፋ የቆረጥንበትን ነገር እግዚአብሔር አምላክ መለወጥ ይቻለዋልና በፍጹም ልባችን ሆነን እንለምነው፡፡ አሁን የመጣውን ቸነፈርና መከራ እንዲያቆምልንም ፈጣሪያችንን በጸሎታችን እንማጸን፤ በንጹሕ ልቡናም ምሕረትን እንለምን፡፡